መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ።

(ክለሳ.1.20020507)

_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡1።______________
ምዕራፍ፡1።
1፤2፤አዳም፥ሴት፥ሄኖስ፥ቃይናን፥መላልኤል፥
3፤ያሬድ፥ሔኖክ፥ማቱሳላ፥ላሜሕ፥
4፤ኖኅ፥ሴም፥ካም፥ያፌት።
5፤የያፌት፡ልጆች፤ጋሜር፥ማጎግ፥ማዴ፥
6፤ያዋን፥ቶቤል፥ሞሳሕ፥ቴራስ።
7፤የጋሜርም፡ልጆች፤አስከናዝ፥ሪፋት፥ቴርጋማ።የያዋንም፡ልጆች፤ኤሊሳ፥ተርሴስ፥ኪቲም፥ሮድኢ።
8፤የካምም፡ልጆች፤ኵሽ፥ምጽራይም፥ፉጥ፥ከነዓን።
9፤የኵሽም፡ልጆች፤ሳባ፥ኤውላጥ፥ሰብታ፥ራዕማ፥ሰብቃታ።የራዕማም፡ልጆች፤ሳባ፥ድዳን።
10፤ኵሽም፡ናምሩድን፡ወለደ፤ርሱም፡በምድር፡ኀያል፡መኾንን፡ዠመረ።
11፤ምጽራይምም፡ሉዲምን፥ዐናሚምን፥ላህቢምን፥
12፤ነፍተሂምን፥ፈትሩሲምን፥ፍልስጥኤማውያን፡የወጡበትን፡ከስሉሂምን፥ከፍቶሪምን፡ወለደ።
13፤ከነዓንም፡የበኵር፡ልጁን፡ሲዶንን፥
14፤ኬጢን፥ኢያቡሳዊውን፥አሞራዊውን፥
15፤ጌርጌሳዊውን፥ዔዊያዊውን፥ዐርካዊውን፥
16፤ሢኒያዊውን፥አራዴዎንን፥ሰማሪዎንን፥አማቲን፡ወለደ።
17፤የሴምም፡ልጆች፤ዔላም፥አሶር፥አርፋክስድ፥ሉድ፥አራም፥ዑፅ፥ኁል፥ጌቴር፥ሞሳሕ።
18፤አርፋክስድም፡ቃይንምን፡ወለደ፤ቃይንምም፡ሳላን፡ወለደ፤ሳላም፡ዔቦርን፡ወለደ።
19፤ለዔቦርም፡ኹለት፡ልጆች፡ተወለዱለት፤በዘመኑ፡ምድር፡ተከፍላለችና፡የአንደኛው፡ስም፡ፋሌቅ፡ተባለ፤የወን ድሙም፡ስም፡ዮቅጣን፡ነበረ።
20፤ዮቅጣንም፡አልሞዳድን፥
21፤ሳሌፍን፥ሐስረሞትን፥ያራሕን፥ሀዶራምን፥
22፤አውዛልን፥ደቅላን፥ዖባልን፥አቢማኤልን፥
23፤ሳባን፥ኦፊርን፥ኤውላጥን፥ዮባብን፡ወለደ፤እነዚህ፡ዅሉ፡የዮቅጣን፡ልጆች፡ነበሩ።
24፤25፤ሴም፥አርፋክስድ፥ሳላ፥ዔቦር፥ፋሌቅ፥
26፤27፤ራግው፥ሴሮሕ፥ናኮር፥ታራ፥አብርሃም፡የተባለ፡አብራም።
28፤የአብርሃምም፡ልጆች፤ይሥሐቅ፥እስማኤል።
29፤ትውልዳቸውም፡እንደዚህ፡ነው።የእስማኤል፡በኵር፡ልጅ፡ነባዮት፤ከዚህ፡በዃላ፡ቄዳር፥ነብዳኤል፥መብሳም፥
30፤ማስማዕ፥ዱማ፥ማሣ፥ኩዳን፥ቴማን፥
31፤ኢጡር፥ናፌስ፥ቄድማ፤እነዚህ፡የእስማኤል፡ልጆች፡ናቸው።
32፤የአብርሃምም፡ገረድ፡የኬጡራ፡ልጆች፤ዘምራን፥ዮቅሳን፥ሜዳን፥ምድያም፥የስቦቅ፥ስዌሕ።የዮቅሳንም፡ልጆች ፤ሳባ፥ድዳን።
33፤የምድያምም፡ልጆች፤ጌፌር፥ዔፌር፥ሄኖኅ፥አቢዳዕ፥ኤልዳዓ።እነዚህ፡ዅሉ፡የኬጡራ፡ልጆች፡ነበሩ።
34፤አብርሃምም፡ይሥሐቅን፡ወለደ።የይሥሐቅም፡ልጆች፡ዔሳውና፡እስራኤል፡ነበሩ።
35፤የዔሳው፡ልጆች፤ኤልፋዝ፥ራጉኤል፥የዑስ፥የዕላም፥ቆሬ።
36፤የኤልፋዝ፡ልጆች፤ቴማን፥ኦማር፥ስፎ፥ጎቶም፥ቄኔዝ፥ቲምናዕ፥ዐማሌቅ።
37፤የራጉኤል፡ልጆች፤ናሖት፥ዛራ፥ሳማ፥ሚዛህ።
38፤የሴይርም፡ልጆች፤ሎጣን፥ሦባል፥ጽብዖን፥ዐና፥ዲሶን፥ኤጽር፥ዲሳን።
39፤የሎጣንም፡ልጆች፤ሖሪ፥ሔማም፤ቲሞናዕ፡የሎጣን፡እኅት፡ነበረች።
40፤የሦባል፡ልጆች፤ዓልዋን፥ማኔሐት፥ዔባል፥ስፎ፥አውናም።የጽብዖንም፡ልጆች፤አያ፥ዐና።
41፤የዐና፡ልጅ፤ዲሶን።የዲሶንም፡ልጆች፤ሔምዳን፥ኤስባን፥ይትራን፥ክራን።
42፤የኤጽር፡ልጆች፤ቢልሐን፥ዛዕዋን፥ዐቃን።የዲሳን፡ልጆች፤ዑፅ፥አራን።
43፤በእስራኤልም፡ልጆች፡ላይ፡ገና፡ንጉሥ፡ሳይነግሥ፡በኤዶምያስ፡ምድር፡የነገሡ፡ነገሥታት፡እነዚህ፡ናቸው። የቢዖር፡ልጅ፡ባላቅ፤የከተማዪቱም፡ስም፡ዲንሃባ፡ነበረ።
44፤ባላቅም፡ሞተ፥በርሱም፡ፋንታ፡የባሶራ፡ሰው፡የዛራ፡ልጅ፡ኢዮባብ፡ነገሠ።
45፤ኢዮባብም፡ሞተ፥በርሱም፡ፋንታ፡የቴማን፡አገር፡ሰው፡ሑሳም፡ነገሠ።
46፤ሑሳምም፡ሞተ፥በርሱም፡ፋንታ፡በሞዐብ፡ሜዳ፡ምድያምን፡የመታው፡የባዳድ፡ልጅ፡ሃዳድ፡ነገሠ፤የከተማዪቱም ፡ስም፡ዓዊት፡ነበረ።
47፤ሃዳድም፡ሞተ፥በርሱም፡ፋንታ፡የመሥሬቃ፡ሰው፡ሰምላ፡ነገሠ።
48፤ሰምላም፡ሞተ፥በርሱም፡ፋንታ፡በወንዙ፡አጠገብ፡ያለችው፡የረሆቦት፡ሰው፡ሳኡል፡ነገሠ።
49፤ሳኡልም፡ሞተ፥በርሱም፡ፋንታ፡የዓክቦር፡ልጅ፡በዓልሐናን፡ነገሠ።
50፤በዓልሐናንም፡ሞተ፥በርሱም፡ፋንታ፡ሃዳድ፡ነገሠ፤የከተማዪቱም፡ስም፡ፋዑ፡ነበረ፤ሚስቱም፡የሜዛሃብ፡ልጅ ፡የመጥሬድ፡ልጅ፡መሄጣብኤል፡ነበረች፤ሃዳድም፡ሞተ።
51፤የኤዶምያስም፡አለቃዎች፡እነዚህ፡ነበሩ፤ቲምናዕ፡አለቃ፥ዓልዋ፡አለቃ፥የቴት፡አለቃ፥
52፤አህሊባማ፡አለቃ፥ኤላ፡አለቃ፥ፊኖን፡አለቃ፥
53፤ቄኔዝ፡አለቃ፥ቴማን፡አለቃ፥ሚብሳር፡አለቃ፥
54፤መግዲኤል፡አለቃ፥ዒራም፡አለቃ፤እነዚህ፡የኤዶምያስ፡አለቃዎች፡ነበሩ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡2።______________
ምዕራፍ፡2።
1፤የእስራኤልም፡ልጆች፡እነዚህ፡ናቸው፤ሮቤል፥ስምዖን፥ሌዊ፥ይሁዳ፥ይሳኮር፥ዛብሎን፥
2፤ዳን፥ዮሴፍ፥ብንያም፥ንፍታሌም፥ጋድ፥አሴር።
3፤የይሁዳ፡ልጆች፤ዔር፥አውናን፥ሴሎም፤እነዚህ፡ሦስቱ፡ከከነዓናዊቱ፡ከሴዋ፡ልጅ፡ተወለዱለት።የይሁዳም፡የበ ኵር፡ልጅ፡ዔር፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ክፉ፡ነበረ፤ገደለውም።
4፤ምራቱም፡ትዕማር፡ፋሬስንና፡ዛራን፡ወለደችለት፤የይሁዳም፡ልጆች፡ዅሉ፡ዐምስት፡ነበሩ።
5፤የፋሬስ፡ልጆች፤ኤስሮም፥ሐሙል።
6፤የዛራም፡ልጆች፤ዘምሪ፥ኤታን፥ሄማን፥
7፤ከልኮል፥ዳራ፤ዅሉም፡ዐምስት፡ነበሩ።የከርሚም፡ልጅ፡እስራኤልን፡ያስጨነቀ፥ዕርሙንም፡ሰርቆ፡የበደለ፡ዐካ ን፡ነበረ።
8፤የኤታንም፡ልጅ፡ዐዛርያ፡ነበረ።
9፤ለኤስሮም፡የተወለዱለት፡ልጆች፤ይረሕምኤል፣አራም፣ካልብ፡ነበሩ።
10፤አራምም፡ዐሚናዳብን፡ወለደ፤ዐሚናዳብም፡የይሁዳን፡ልጆች፡አለቃ፡ነአሶንን፡ወለደ፤
11፤ነአሶንም፡ሰልሞንን፡ወለደ፤ሰልሞንም፡ቦዔዝን፡ወለደ፤
12፤ቦዔዝም፡ኢዮቤድን፡ወለደ፤ኢዮቤድም፡እሴይን፡ወለደ፤
13፤እሴይም፡የበኵር፡ልጁን፡ኤልያብን፥ኹለተኛውንም፡ዐሚናዳብን፥ሦስተኛውንም፡ሳማን፥
14፤አራተኛውንም፡ናትናኤልን፥
15፤ዐምስተኛውንም፡ራዳይን፥ስድስተኛውንም፡አሳምን፥ሰባተኛውንም፡ዳዊትን፡ወለደ፤
16፤እኅቶቻቸውም፡ጽሩያና፡አቢግያ፡ነበሩ።የጽሩያም፡ልጆች፡አቢሳ፥ኢዮአብ፥ዐሳሄል፡ሦስቱ፡ነበሩ።
17፤አቢግያም፡ዐማሳይን፡ወለደች፤የዐማሳይም፡አባት፡እስማኤላዊው፡ዬቴር፡ነበረ።
18፤የኤስሮምም፡ልጅ፡ካሌብ፡ከሚስቱ፡ከዓዙባ፡ከይሪዖትም፡ልጆች፡ወለደ፤ልጆቿም፡ያሳር፥ሶባብ፥አርዶን፡ነበ ሩ።
19፤ዓዙባም፡ሞተች፥ካሌብም፡ኤፍራታን፡አገባ፤ርሷም፡ሆርን፡ወለደችለት።
20፤ሆርም፡ኡሪን፡ወለደ፥ኡሪም፡ባስልኤልን፡ወለደ።
21፤ከዚያም፡በዃላ፡ኤስሮም፡ስድሳ፡ዓመት፡በኾነው፡ጊዜ፡ወዳገባት፡ወደገለዓድ፡አባት፡ወደማኪር፡ልጅ፡ገባ፤ ሰጉብንም፡ወለደችለት።ሰጉብም፡ኢያዕርን፡ወለደ፤
22፤ለርሱም፡በገለዓድ፡ምድር፡ኻያ፡ሦስት፡ከተማዎች፡ነበሩት።
23፤ጌሹርና፡አራምም፡የኢያዕርን፡ከተማዎች፡ከቄናትና፡ከመንደሮቿ፡ጋራ፡ስድሳውን፡ከተማዎች፡ወሰዱባቸው።እ ነዚህ፡ዅሉ፡የገለዓድ፡አባት፡የማኪር፡ልጆች፡ነበሩ።
24፤ኤስሮምም፡በካሌብ፡ኤፍራታ፡ከሞተ፡በዃላ፡የኤስሮም፡ሚስት፡አቢያ፡የቴቁሔን፡አባት፡አሽሑርን፡ወለደችለ ት።
25፤የኤስሮምም፡የበኵር፡ልጁ፡የይረሕምኤል፡ልጆች፡በኵሩ፡ራም፥ቡናህ፥ኦሬን፥ኦጼም፥አኪያ፡ነበሩ።
26፤ለይረሕምኤልም፡ዓጣራ፡የተባለች፡ሌላ፡ሚስት፡ነበረችው፤ርሷም፡የኦናም፡እናት፡ነበረች።
27፤የይረሕምኤል፡የበኵሩ፡የራም፡ልጆች፡መዓስ፥ያሚን፥ዔቄር፡ነበሩ።
28፤የኦናምም፡ልጆች፡ሸማይና፡ያዳ፡ነበሩ።የሸማይ፡ልጆች፡ናዳብና፡አቢሱር፡ነበሩ።
29፤የአቢሱርም፡ሚስት፡አቢካኢል፡ነበረች፤አኅባንንና፡ሞሊድን፡ወለደችለት።
30፤የናዳብም፡ልጆች፡ሴሊድና፡አፋይም፡ነበሩ፤ሴሌድም፡ያለልጆች፡ሞተ።
31፤የአፋይምም፡ልጅ፡ይሽዒ፥የይሽዒም፡ልጅ፡ሶሳን፥የሶሳንም፡ልጅ፡አሕላይ፡ነበረ።
32፤የሸማይም፡ወንድም፡የያዳ፡ልጆች፡ዬቴርና፡ዮናታን፡ነበሩ፤ዬቴርም፡ያለልጆች፡ሞተ።
33፤የዮናታንም፡ልጆች፡ፌሌትና፡ዛዛ፡ነበሩ፤እነዚህ፡የይረሕምኤል፡ልጆች፡ነበሩ።
34፤ለሶሳንም፡ሴቶች፡ልጆች፡እንጂ፡ወንዶች፡ልጆች፡አልነበሩትም፤ለሶሳንም፡ኢዮሄል፡የተባለ፡ግብጻዊ፡አገል ጋይ፡ነበረው።
35፤ሶሳንም፡ለአገልጋዩ፡ለኢዮሄል፡ልጁን፡አጋባት፥ርሷም፡ዐታይን፡ወለደችለት።
36፤ዐታይም፡ናታንን፡ወለደ፤ናታንም፡ዛባድን፡ወለደ፤
37፤ዛባድም፡ኤፍላልን፡ወለደ፤ኤፍላልም፡ዖቤድን፡ወለደ፤ዖቤድም፡ኢዩን፡ወለደ፤
38፤ኢዩም፡ዐዛርያስን፡ወለደ፤
39፤ዐዛርያስም፡ኬሌስን፡ወለደ፤ኬሌስም፡ኤልዓሣን፡ወለደ፤
40፤ኤልዓሣም፡ሲስማይን፡ወለደ፤
41፤ሲስማይም፡ሰሎምን፡ወለደ፤ሰሎምም፡የቃምያን፡ወለደ፤የቃምያም፡ኤሊሳማን፡ወለደ።
42፤የይረሕምኤልም፡ወንድም፡የካሌብ፡ልጆች፡በኵሩ፡የዚፍ፡አባት፡ሞሳ፥የኬብሮንም፡አባት፡የመሪሳ፡ልጆች፡ነ በሩ።
43፤የኬብሮንም፡ልጆች፡ቆሬ፥ተፉዋ፥ሬቄም፥ሽማዕ፡ነበሩ።
44፤ሽማዕም፡የዮርቅዓምን፡አባት፡ረሐምን፡ወለደ፤ሬቄምም፡ሸማይን፡ወለደ።
45፤የሸማይም፡ልጅ፡ማዖን፡ነበረ፤ማዖንም፡የቤትጹር፡አባት፡ነበረ።
46፤የካሌብም፡ቁባት፡ዔፋ፡ሀራንን፥ሞዳን፥ጋዜዝን፡ወለደች።
47፤ሀራንም፡ጋዜዝን፡ወለደ።የያህዳይም፡ልጆች፡ሬጌም፥ኢዮታም፥ጌሻን፥ፋሌጥ፥ሔፋ፥ሸዓፍ፡ነበሩ።
48፤የካሌብም፡ቁባት፡ማዕካ፡ሸቤርንና፡ቲርሐናን፡ወለደች።
49፤ደግሞም፡የመድማናን፡አባት፡ሸዓፍንና፡የመክቢናንና፡የጊብዓን፡አባት፡ሱሳን፡ወለደች፤የካሌብም፡ሴት፡ል ጅ፡ዓክሳ፡ነበረች።
50፤የካሌብ፡ልጆች፡እነዚህ፡ናቸው፤የኤፍራታ፡የበኵሩ፡የሆር፡ልጅ፡የቂርያትይዓሪም፡አባት፡ሦባል፥
51፤የቤተ፡ልሔም፡አባት፡ሰልሞን፥የቤት፡ጋዴር፡አባት፡ሐሬፍ።
52፤ለቂርያትይዓሪምም፡አባት፡ለሦባል፡ልጆች፡ነበሩት፤ሀሮኤ፡የመናሕታውያን፡እኩሌታ።
53፤የቂርያትይዓሪምም፡ወገኖች፤ይትራውያን፥ፉታውያን፥ሹማታውያን፥ሚሽራውያን፤ከነዚህም፡ጾርዓውያንና፡ኤሽ ታኦላውያን፡ወጡ።
54፤የሰልሞንም፡ልጆች፡ቤተ፡ልሔም፥ነጦፋውያን፥ዓጣሮትቤትዮአብ፥የመናሕታውያን፡እኩሌታ፥ጾርዓውያን፡ነበሩ ።
55፤በያቤጽም፡የተቀመጡ፡የጸሓፊዎች፡ወገኖች፤ቲርዓውያን፥ሺምዓታውያን፥ሡካታውያን፡ነበሩ፤እነዚህ፡ከሬካብ ፡ቤት፡አባት፡ከሐማት፡የወጡ፡ቄናውያን፡ናቸው።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡3።______________
ምዕራፍ፡3።
1፤በኬብሮንም፡ለዳዊት፡የተወለዱለት፡ልጆች፡እነዚህ፡ናቸው።በኵሩ፡አምኖን፡ከኢይዝራኤላዊቱ፡ከአኪናሖም፥ኹ ለተኛውም፡ዳንኤል፡ከቀርሜሎሳዊቱ፡ከአቢግያ፥
2፤ሦስተኛው፡አቤሴሎም፡ከጌሹር፡ንጉሥ፡ከተልማይ፡ልጅ፡ከመዓካ፥አራተኛው፡አዶንያስ፡ከአጊት፥
3፤ዐምስተኛው፡ሰፋጥያስ፡ከአቢጣል፥ስድስተኛው፡ይትረኃም፡ከሚስቱ፡ከዔግላ።
4፤ስድስቱ፡በኬብሮን፡ተወለዱለት፤በዚያም፡ሰባት፡ዓመት፡ከስድስት፡ወር፡ነገሠ፤በኢየሩሳሌምም፡ሠላሳ፡ሦስት ፡ዓመት፡ነገሠ።
5፤እነዚህ፡ደግሞ፡በኢየሩሳሌም፡ተወለዱለት፤ከዓሚኤል፡ልጅ፡ከቤርሳቤሕ፥ሳሙስ፥ሶባብ፥ናታን፥
6፤ሰሎሞን፥አራት፤ኢያቤሐር፥ኤሊሱዔ፥
7፤ኤሊፋላት፥ኖጋ፥ናፌቅ፥ያፍያ፥
8፤ኤሊሳማ፥ኤሊዳሄ፥ኤሊፋላት፥ዘጠኝ።
9፤እነዚህ፡ዅሉ፡ከቁባቶች፡ልጆች፡በቀር፡የዳዊት፡ልጆች፡ነበሩ፤ትዕማርም፡እኅታቸው፡ነበረች።
10፤የሰሎሞንም፡ልጅ፡ሮብዓም፡ነበረ፤ልጁ፡አቢያ፥
11፤ልጁ፡አሣ፥ልጁ፡ኢዮሳፍጥ፥ልጁ፡ኢዮራም፥ልጁ፡አካዝያስ፥ልጁ፡ኢዮአስ፥
12፤ልጁ፡አሜስያስ፥ልጁ፡ዐዛርያስ፥ልጁ፡ኢዮአታም፥
13፤ልጁ፡አካዝ፥ልጁ፡ሕዝቅያስ፥ልጁ፡ምናሴ፥
14፤ልጁ፡ዓሞጽ፥ልጁ፡ኢዮስያስ።
15፤የኢዮስያስም፡ልጆች፤በኵሩ፡ዮሐናን፥ኹለተኛውም፡ኢዮአቄም፥ሦስተኛውም፡ሴዴቅያስ፥አራተኛውም፡ሰሎም።
16፤የኢዮአቄምም፡ልጆች፤ልጁ፡ኢኮንያን፥ልጁ፡ሴዴቅያስ።
17፤የምርኮኛውም፡የኢኮንያን፡ልጆች፡ሰላትያል፥መልኪራም፥
18፤ፈዳያ፥ሼናጻር፥ይቃምያ፥ሆሻማ፥ነዳብያ፡ነበሩ።
19፤የፈዳያ፡ልጆች፡ዘሩባቤልና፡ሰሜኢ፡ነበሩ፤የዘሩባቤልም፡ልጆች፤ሜሱላም፥ሐናንያ፥እኅታቸውም፡ሰሎሚት።
20፤ሐሹባ፥ኦሄል፥በራክያ፥ሐሳድያ፥ዮሻብሒሴድ፡ዐምስት፡ናቸው።
21፤የሐናንያም፡ልጆች፡ፈላጥያና፡የሻያ፡ነበሩ።የረፋያ፡ልጆች፥የአርናን፡ልጆች፥የዐብድዩ፡ልጆች፥የሴኬንያ ፡ልጆች።
22፤የሴኬንያም፡ልጅ፡ሸማያ፡ነበረ።የሸማያም፡ልጆች፡ሐጡስ፥ይግአል፥ባርያሕ፥ነዓርያ፥ሻፋጥ፡ስድስት፡ነበሩ ።
23፤የነዓርያም፡ልጆች፡ኤልዮዔናይ፥ሕዝቅያስ፥ዐዝሪቃም፡ሦስት፡ነበሩ።
24፤የኤልዮዔናይም፡ልጆች፡ሆዳይዋ፥ኤልያሴብ፥ፌልያ፥ዐቁብ፥ዮሐናን፥ደላያ፥ዓናኒ፡ሰባት፡ነበሩ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡4።______________
ምዕራፍ፡4።
1፤የይሁዳ፡ልጆች፡ፋሬስ፥ኤስሮም፥ከርሚ፥ሆር፥ሦባል፡ናቸው።
2፤የሦባልም፡ልጅ፡ራያ፡ኢኤትን፡ወለደ፤ኢኤትም፡አሑማይንና፡ላሃድን፡ወለደ።እነዚህ፡የጾርዓውያን፡ወገኖች፡ ናቸው።
3፤እነዚህም፡የኤጣም፡አባት፡ልጆች፡ናቸው፤ኢይዝራኤል፥ይሽማ፥ይድባሽ፥እኅታቸውም፡ሃጽሌልፎኒ።
4፤የጌዶርም፡አባት፡ፋኑኤል፥የሑሻም፡አባት፡ኤጽር፤እነዚህ፡የቤተ፡ልሔም፡አባት፡የኤፍራታ፡የበኵሩ፡የሆር፡ ልጆች፡ናቸው።
5፤ለቴቁሔም፡አባት፡ለአሽሑር፡ሔላና፡ነዕራ፡የተባሉ፡ኹለት፡ሚስቶች፡ነበሩት።
6፤ነዕራም፡አሑዛምን፥ኦፌርን፥ቴምኒን፥አሐሽታሪን፡ወለደችለት።እነዚህ፡የነዕራ፡ልጆች፡ናቸው።
7፤የሔላም፡ልጆች፡ዴሬት፥ይጽሐር፥ኤትናን፡ናቸው።
8፤ቆጽ፡ዓኑብን፥ጾቤባን፥የሃሩምንም፡ልጅ፡የአሐርሔልን፡ወገኖች፡ወለደ።
9፤ያቤጽም፡ከወንድሞቹ፡ይልቅ፡የተከበረ፡ነበረ፤እናቱም፦በጣር፡ወልጄዋለኹና፡ብላ፡ስሙን፦ያቤጽ፡ብላ፡ጠራች ው።
10፤ያቤጽም፦እባክኽ፥መባረክን፡ባርከኝ፥አገሬንም፡አስፋው፤እጅኽም፡ከእኔ፡ጋራ፡ትኹን፤እንዳያሳዝነኝም፡ከ ክፋት፡ጠብቀኝ፡ብሎ፡የእስራኤልን፡አምላክ፡ጠራ፤እግዚአብሔርም፡የለመነውን፡ሰጠው።
11፤የሹሐም፡ወንድም፡ክሉብ፡የኤሽቶንን፡አባት፡ምሒርን፡ወለደ።
12፤ኤሽቶንም፡ቤትራ፡ፋንና፡ፋሴሐን፡የዒርናሐሽንም፡አባት፡ተሒናን፡ወለደ፤እነዚህ፡የሬካ፡ሰዎች፡ናቸው።
13፤የቄኔዝም፡ልጆች፡ጎቶንያልና፡ሰራያ፡ነበሩ።የጎቶንያልም፡ልጅ፡ሐታት፡ነበረ።
14፤መዖኖታይ፡ዖፍራን፡ወለደ።ሰራያም፡የጌሃራሽምን፡አባት፡ኢዮአብን፡ወለደ፤እነርሱም፡ጠራቢዎች፡ነበሩ።
15፤የዮፎኒም፡ልጅ፡የካሌብ፡ልጆች፡ዒሩ፥ኤላ፥ነዓም፡ነበሩ።
16፤የዔላም፡ልጅ፡ቄኔዝ፡ነበረ።የይሃሌልኤል፡ልጆች፡ዚፍ፥ዚፋ፥ቲርያ፥አሳርኤል፡ነበሩ።
17፤የዕዝራም፡ልጆች፡ዬቴር፥ሜሬድ፥ዔፌር፥ያሎን፡ነበሩ፤ዬቴርም፡ማርያምን፥ሸማይን፥የኤሽትምዓን፡አባት፡ይ ሽባን፡ወለደ።
18፤አይሁዳዊቱም፡ሚስቱ፡የጌዶርን፡አባት፡ዬሬድን፥የሦኮንም፡አባት፡ሔቤርን፥የዛኖዋንም፡አባት፡ይቁቲኤልን ፡ወለደች።እነዚህም፡ሜሬድ፡ያገባት፡የፈርዖን፡ልጅ፡የቢትያ፡ልጆች፡ናቸው።
19፤የሆዲያ፡ሚስት፡የነሐም፡እኅት፡ልጆች፡የገርሚው፡የቅዒላ፡አባትና፡ማዕካታዊው፡ኤሽትሞዐ፡ነበሩ።
20፤የሺሞንም፡ልጆች፡አምኖን፥ሪና፥ቤንሐናን፥ቲሎን፡ነበሩ።የይሽዒም፡ልጆች፡ዞሔትና፡ቢንዞሔት፡ነበሩ።
21፤የይሁዳም፡ልጅ፡የሴሎም፡ልጆች፡የሌካ፡አባት፡ዔር፥የመሪሳ፡አባት፡ለዓዳ፥ከአሽቤዓ፡ቤት፡የሚኾኑ፡ጥሩ፡ በፍታ፡የሚሠሩ፡ወገኖች፥
22፤ዮቂም፥የኮዜባ፡ሰዎች፥ኢዮአስ፥ሞዐብን፡የገዛ፡ሳራፍ፥ያሹቢሌሔም፡ነበሩ።
23፤ይህ፡ዝና፡ከቀድሞ፡ዠምሮ፡ነበረ።እነዚህ፡በነጣዒምና፡በጋዴራ፡የሚቀመጡ፡ሸክላ፡ሠራተኛዎች፡ነበሩ።በዚ ያ፡በንጉሡ፡ዘንድ፡ስለ፡ሥራው፡ይቀመጡ፡ነበር።
24፤የስምዖንም፡ልጆች፤ነሙኤል፥ያሚን፥ያሪን፥ዛራ፥ሳኡል፤
25፤ልጁ፡ሰሎም፥ልጁ፡መብሳም፥ልጁ፡ማስማዕ።
26፤የማስማዕም፡ልጆች፤ልጁ፡ሐሙኤል፥ልጁ፡ዘኩር፥ልጁ፡ሰሜኢ።
27፤ለሰሜኢም፡ዐሥራ፡ስድስት፡ወንዶችና፡ስድስት፡ሴቶች፡ልጆች፡ነበሩት፤ለወንድሞቹ፡ግን፡ብዙ፡ልጆች፡አልነ በሯቸውም፥ወገናቸውም፡ዅሉ፡እንደ፡ይሁዳ፡ልጆች፡አልተባዙም።
28፤በቤርሳቤሕም፥በሞላዳ፥
29፤በሐጸርሹዓል፥በቢልሃ፥በዔጼም፥
30፤በቶላድ፥በቤቱኤል፥በሔርማ፥በጺቅላግ፥
31፤በቤትማርካቦት፥በሐጸርሱሲም፥በቤትቢሪ፥በሸዓራይም፡ይቀመጡ፡ነበር።እስከዳዊትም፡መንግሥት፡ድረስ፡ከተ ማዎቻቸው፡እነዚህ፡ነበሩ።
32፤መንደሮቻቸውም፡ኤጣም፥ዐይን፥ሬሞን፥ቶኬን፥ዐሻን፥ዐምስቱ፡ከተማዎች፤
33፤እስከ፡በዓልም፡ድረስ፡በእነዚህ፡ከተማዎች፡ዙሪያ፡የነበሩ፡መንደሮቻቸው፡ዅሉ፡ነበሩ።መቀመጫቸውና፡የት ውልዳቸው፡መዝገቦች፡እነዚህ፡ናቸው።
34፤ምሾባብ፥የምሌክ፥የአሜስያስ፡ልጅ፡ኢዮስያ፥
35፤ኢዮኤል፥የዮሺብያ፡ልጅ፥የሰራያ፡ልጅ፡የዓሢኤል፡ልጅ፡ኢዩ፥
36፤ኤልዮዔናይ፥ያዕቆባ፥የሾሐያ፥ዐሳያ፥ዓዲዔል፥ዩሲምኤል፥በናያስ፥
37፤የሺፊ፡ልጅ፡ዚዛ፥የአሎን፡ልጅ፡የይዳያ፡ልጅ፡የሺምሪ፡ልጅ፡የሸማያ፡ልጅ፤
38፤እነዚህ፡በስማቸው፡የተጠሩ፡በወገኖቻቸው፡ላይ፡አለቃዎች፡ነበሩ፤የአባቶቻቸውም፡ቤቶች፡በዝተው፡ነበር።
39፤ለመንጋዎቻቸው፡መሰምሪያ፡ይሹ፡ዘንድ፡ወደጌዶር፡መግቢያ፡እስከ፡ሸለቆው፡ምሥራቅ፡ድረስ፡ኼዱ።
40፤የለመለመችም፡እጅግም፡ያማረች፡መሰምሪያ፡አገኙ፤ምድሪቱም፡ሰፊና፡ጸጥተኛ፡ሰላም፡ያላትም፡ነበረች፤በቀ ድሞም፡ጊዜ፡በዚያ፡ተቀምጠው፡የነበሩ፡ከካም፡ወገን፡ነበሩ።
41፤እነዚህም፡በስማቸው፡የተጻፉ፡በይሁዳ፡ንጉሥ፡በሕዝቅያስ፡ዘመን፡መጥተው፡ድንኳኖቻቸውንና፡በዚያ፡የተገ ኙትን፡ምዑናውያንን፡መቱ፥እስከ፡ዛሬም፡ድረስ፡ፈጽመው፡አጠፏቸው፤በዚያም፡ለመንጋዎቻቸው፡መሰምሪያ፡ነበረ ና፡በስፍራቸው፡ተቀመጡ።
42፤የስምዖንም፡ልጆች፡ዐምስት፡መቶ፡ሰዎች፡ወደሴይር፡ተራራ፡ኼዱ፤አለቃዎቻቸውም፡የይሽዒ፡ልጆች፥ፈላጥያ፥ ነዓርያ፥ረፋያ፥ዑዝኤል፡ነበሩ።
43፤ያመለጡትንም፡የዐማሌቃውያንን፡ቅሬታ፡መቱ፥በዚያም፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡ተቀምጠዋል።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡5።______________
ምዕራፍ፡5።
1፤የእስራኤልም፡በኵር፡የሮቤል፡ልጆች፡እነዚህ፡ናቸው።ርሱ፡የበኵር፡ልጅ፡ነበረ፤ነገር፡ግን፥የአባቱን፡ምን ጣፍ፡ስላረከሰ፡ብኵርናው፡ለእስራኤል፡ልጅ፡ለዮሴፍ፡ልጆች፡ተሰጠ፤ትውልዱ፡ግን፡ከብኵርና፡ጋራ፡አልተቈጠረ ም።
2፤ይሁዳም፡በወንድሞቹ፡መካከል፡በረታ፥አለቃም፡ከርሱ፡ኾነ፤ብኵርናው፡ግን፡ለዮሴፍ፡ነበረ።
3፤የእስራኤል፡በኵር፡የሮቤል፡ልጆች፤ሄኖኅ፥ፈሉስ፥አስሮን፥ከርሚ፡ነበሩ።
4፤የኢዮኤል፡ልጆች፤ልጁ፡ሸማያ፥
5፤ልጁ፡ጎግ፥ልጁ፡ሰሜኢ፥ልጁ፡ሚካ፥
6፤ልጁ፡ራያ፥ልጁ፡ቢኤል፥የአሶር፡ንጉሥ፡ቴልጌልቴልፌልሶር፡የማረከው፡ልጁ፡ብኤራ፤ርሱ፡የሮቤል፡ነገድ፡አለ ቃ፡ነበረ።
7፤ወንድሞቹ፡በየወገናቸው፡የትውልዶቻቸው፡መዝገብ፡በተቈጠረ፡ጊዜ፤አንደኛው፡ኢዮኤል፥
8፤ዘካርያስ፥እስከ፡ናባውና፡እስከ፡በዓልሜዎን፡ድረስ፡በዐሮዔር፡የተቀመጠው፡የኢዮኤል፡ልጅ፡የሽማዕ፡ልጅ፡ የዖዛዝ፡ልጅ፡ቤላ፤
9፤በገለዓድ፡ምድር፡እንስሳዎቻቸው፡በዝተው፡ነበርና፥በምሥራቅ፡በኩል፡ከኤፍራጥስ፡ወንዝ፡ዠምሮ፡እስከምድረ ፡በዳው፡መግቢያ፡ድረስ፡ተቀመጠ።
10፤በሳኦልም፡ዘመን፡ከአጋራውያን፡ጋራ፡ተዋጉ፥እነርሱም፡በእጃቸው፡ተመትተው፡ወደቁ፤በገለዓድ፡ምሥራቅ፡በ ኩል፡ባለው፡አገር፡ዅሉ፡በድንኳኖቻቸው፡ተቀመጡ።
11፤የጋድም፡ልጆች፡በባሳን፡ምድር፡እስከ፡ሰልካ፡ድረስ፡በአፋዛዣቸው፡ተቀመጡ።
12፤አንደኛው፡ኢዮኤል፥ኹለተኛው፡ሳፋም፥ያናይ፥ሳፋጥ፡በበሳን፡ተቀመጡ።
13፤የአባቶቻቸውም፡ቤቶች፡ወንድሞች፡ሚካኤል፥ሜሱላም፥ሳባ፥ዮራይ፥ያካን፥ዙኤ፥ኦቤድ፡ሰባት፡ነበሩ።
14፤እነዚህም፡የቡዝ፡ልጅ፡የዬዳይ፡ልጅ፡የኢዬሳይ፡ልጅ፡የሚካኤል፡ልጅ፡የገለዓድ፡ልጅ፡የኢዳይ፡ልጅ፡የዑሪ ፡ልጅ፡የአቢካኢል፡ልጆች፡ነበሩ።
15፤የአባቶቻቸውም፡ቤቶች፡አለቃ፡የጉኒ፡ልጅ፡የዐብዲኤል፡ልጅ፡ወንድም፡ነበረ።
16፤በገለዓድም፡ምድር፡በባሳን፡በመንደሮቹም፡በሳሮንም፡መሰምሪያዎች፡ዅሉ፡እስከ፡ዳርቻቸው፡ድረስ፡ተቀምጠ ው፡ነበር።
17፤እነዚህ፡ዅሉ፡በትውልዶቻቸው፡በይሁዳ፡ንጉሥ፡በኢዮአታም፡ዘመንና፡በእስራኤል፡ንጉሥ፡በኢዮርብዓም፡ዘመ ን፡ተቈጠሩ።
18፤የሮቤልና፡የጋድ፡ልጆች፡የምናሴም፡ነገድ፡እኩሌታ፥ጽኑዓን፥ጋሻና፡ሰይፍ፡የሚይዙ፥ቀስተኛዎችም፥ሰልፍ፡ የሚያውቁ፡ሰልፈኛዎችም፥አርባ፡አራት፡ሺሕ፡ሰባት፡መቶ፡ስድሳ፡ነበሩ።
19፤ከአጋራውያንና፡ከኢጡር፡ከናፌስና፡ከናዳብ፡ጋራ፡ተዋጉ።
20፤በሚዋጉበትም፡ጊዜ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ጮኸዋልና፥በርሱም፡ታምነዋልና፥ተለመናቸው፤በላያቸውም፡ረዳት፡ኾ ናቸው፥አጋራውያንና፡ከነርሱ፡ጋራ፡የነበሩትም፡ዅሉ፡በእጃቸው፡ተሰጡ።
21፤ከከብቶቻቸውም፡ዐምሳ፡ሺሕ፡ግመሎች፥ኹለት፡መቶ፡ዐምሳ፡ሺሕም፡በጎች፥ኹለት፡ሺሕም፡አህያዎች፥ከሰዎችም ፡መቶ፡ሺሕ፡ማረኩ።
22፤ሰልፉ፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ነበረና፡ብዙ፡ሰዎች፡ተገድለው፡ወደቁ፤እስከ፡ምርኮም፡ዘመን፡ድረስ፡በስፍ ራቸው፡ተቀመጡ።
23፤የምናሴ፡የነገድ፡እኩሌታ፡ልጆች፡በምድሪቱ፡ተቀመጡ።ከባሳንም፡ዠምሮ፡እስከ፡በዓልአርሞንዔምና፡እስከ፡ ሳኔር፡እስከአርሞንዔም፡ተራራ፡ድረስ፡በዙ።
24፤የአባቶቻቸውም፡ቤቶች፡አለቃዎች፡እነዚህ፡ነበሩ፤ዔፌር፥ይሽዒ፥ኤሊኤል፥ዓዝርኤል፥ኤርምያ፥ሆዳይዋ፥ኢየ ድኤል፤እነርሱ፡ጽኑዓን፡ኀያላን፡የታወቁ፡ሰዎች፡የአባቶቻቸውም፡ቤቶች፡አለቃዎች፡ነበሩ።
25፤የአባቶቻቸውንም፡አምላክ፡በደሉ፥እግዚአብሔርም፡ከፊታቸው፡ባጠፋቸው፡በምድሩ፡አሕዛብ፡አማልክት፡አመነ ዘሩ።
26፤የእስራኤልም፡አምላክ፡የአሶርን፡ንጉሥ፡የፎሐን፡መንፈስ፥የአሶርንም፡ንጉሥ፡የቴልጌልቴልፌልሶርን፡መን ፈስ፡አስነሣ፤የሮቤልንና፡የጋድን፡ልጆች፡የምናሴንም፡ነገድ፡እኩሌታ፡አፈለሰ፥እስከ፡ዛሬም፡ወዳሉበት፡ወደ ፡አላሔና፡ወደ፡ኦቦር፥ወደ፡ሃራና፡ወደጎዛን፡ወንዝ፡አመጣቸው።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡6።______________
ምዕራፍ፡6።
1፤የሌዊ፡ልጆች፤ጌድሶን፥ቀአት፥ሜራሪ።
2፤የቀአትም፡ልጆች፤ዕምበረም፥ይስዓር፥ኬብሮን፥ዑዝኤል።
3፤የዕምበረምም፡ልጆች፤አሮን፥ሙሴ፥ማርያም።የአሮን፡ልጆች፤ናዳብ፥አብዮድ፥አልዓዛር፥ኢታምር።
4፤አልዓዛር፡ፊንሐስን፡ወለደ፤ፊንሐስ፡አቢሱን፡ወለደ፤
5፤አቢሱም፡ቡቂን፡ወለደ፤ቡቂም፡ዖዚን፡ወለደ፤
6፤ዖዚም፡ዘራእያን፡ወለደ፤ዘራእያም፡መራዮትን፡ወለደ፤
7፤መራዮት፡አማርያን፡ወለደ፤
8፤አማርያም፡አኪጦብን፡ወለደ፤አኪጦብም፡ሳዶቅን፡ወለደ፤ሳዶቅም፡አኪማዐስን፡ወለደ፤
9፤አኪማዐስም፡ዐዛርያስን፡ወለደ፤
10፤ዐዛርያስም፡ዮሐናንን፡ወለደ፤ዮሐናንም፡ዐዛርያስን፡ወለደ፤ርሱም፡ሰሎሞን፡በኢየሩሳሌም፡በሠራው፡ቤት፡ ካህን፡ነበረ፤
11፤ዐዛርያስም፡አማርያን፡ወለደ፤አማርያም፡አኪጦብን፡ወለደ፤
12፤አኪጦብም፡ሳዶቅን፡ወለደ፤ሳዶቅም፡ሰሎምን፡ወለደ፤
13፤ሰሎምም፡ኬልቅያስን፡ወለደ፤ኬልቅያስም፡ዐዛርያስን፡ወለደ፤
14፤ዐዛርያስም፡ሰራያን፡ወለደ፤ሰራያም፡ኢዮሴዴቅን፡ወለደ፤
15፤እግዚአብሔርም፡ይሁዳንና፡ኢየሩሳሌምን፡በናቡከደነጾር፡እጅ፡ባስማረከ፡ጊዜ፡ኢዮሴዴቅ፡ተማርኮ፡ኼደ።
16፤የሌዊ፡ልጆች፤ጌድሶን፥ቀአት፥ሜራሪ።
17፤የጌድሶንም፡ልጆች፡ስም፡ይህ፡ነው፤ሎቤኒ፡ሰሜኢ።
18፤የቀአትም፡ልጆች፤ዕምበረም፥ይስዓር፥ኬብሮን፥ዑዝኤል፡ነበሩ።
19፤የሜራሪ፡ልጆች፤ሞሖሊም፥ሙሲ።የሌዋውያን፡ወገኖች፡በያባቶቻቸው፡ቤቶች፡እነዚህ፡ናቸው።
20፤ከጌድሶን፤ልጁ፡ሎቤኒ፥ልጁ፡ኢኤት፥ልጁ፡ዛማት፥
21፤ልጁ፡ዮአክ፥ልጁ፡አዶ፥ልጁ፡ዛራ፥ልጁ፡ያትራይ።
22፤የቀአት፡ልጆች፤ልጁ፡ዐሚናዳብ፥ልጁ፡ቆሬ፥ልጁ፡አሴር፥
23፤ልጁ፡ሕልቃና፥ልጁ፡አቢሣፍ፥ልጁ፡አሴር፥
24፤ልጁ፡ኢኢት፥ልጁ፡ኡሩኤል፥ልጁ፡ዖዝያ፥ልጁ፡ሳውል።
25፤የሕልቃናም፡ልጆች፤ዐማሲ፥አኪሞት።
26፤የሕልቃናም፡ልጆች፤ልጁ፡ሱፊ፥
27፤ልጁ፡ናሐት፥ልጁ፡ኤልያብ፥ልጁ፡ይሮሐም፥ልጁ፡ሕልቃና።
28፤የሳሙኤልም፡ልጆች፤በኵሩ፡ኢዮኤል፥ኹለተኛውም፡አብያ።
29፤የሜራሪ፡ልጆች፤ሞሖሊ፥ልጁ፡ሎቤኒ፥ልጁ፡ሰሜኢ፥
30፤ልጁ፡ዖዛ፥ልጁ፡ሳምዓ፥ልጁ፡ሐግያ፥ልጁ፡ዐሳያ።
31፤ዳዊትም፡ታቦቱ፡ዐርፎ፡ከተቀመጠ፡በዃላ፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡ያቆማቸው፡የመዘምራን፡አለቃዎች፡እነዚህ፡ ናቸው።
32፤ሰሎሞንም፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡በኢየሩሳሌም፡እስኪሠራ፡ድረስ፡በመገናኛ፡ድንኳን፡ማደሪያ፡ፊት፡እያዜ ሙ፡ያገለግሉ፡ነበር፤በየተራቸውም፡ያገለግሉ፡ነበር።
33፤አገልጋዮቹና፡ልጆቹ፡እነዚህ፡ናቸው፤ከቀአት፡ልጆች፡ዘማሪው፡ኤማን፡ነበረ፤ርሱም፡የኢዮኤል፡ልጅ፥
34፤የሳሙኤል፡ልጅ፥የሕልቃና፡ልጅ፥የይሮሐም፡ልጅ፥የኤሊኤል፡ልጅ፥የቶዋ፡ልጅ፥
35፤የሱፍ፡ልጅ፥የሕልቃና፡ልጅ፥የመሐት፡ልጅ፥
36፤የዐማሲ፡ልጅ፥የሕልቃና፡ልጅ፥የኢዮኤል፡ልጅ፥የዐዛርያስ፡ልጅ፥የሶፎንያስ፡ልጅ፥
37፤የታሐት፡ልጅ፥የአሴር፡ልጅ፥
38፤የአብያሣፍ፡ልጅ፥የቆሬ፡ልጅ፥የይስዓር፡ልጅ፥የቀአት፡ልጅ፥የሌዊ፡ልጅ፥የእስራኤል፡ልጅ፡ነው።
39፤በቀኙም፡የቆመ፡ወንድሙ፡አሣፍ፡ነበረ፤አሣፍም፡የበራክያ፡ልጅ፥
40፤የሳምዓ፡ልጅ፥የሚካኤል፡ልጅ፥የበዓሤያ፡ልጅ፥
41፤የመልክያ፡ልጅ፥የኤትኒ፡ልጅ፥የዛራ፡ልጅ፥
42፤የዓዳያ፡ልጅ፥የኤታን፡ልጅ፥የዛማት፡ልጅ፥
43፤የሰሜኢ፡ልጅ፥የኢኤት፡ልጅ፥የጌድሶን፡ልጅ፥የሌዊ፡ልጅ፡ነው።
44፤በግራቸውም፡በኩል፡ወንድሞቻቸው፡የሜራሪ፡ልጆች፡ነበሩ፤ኤታን፡የቂሳ፡ልጅ፥የዐብዲ፡ልጅ፥
45፤የማሎክ፡ልጅ፥የሐሸብያ፡ልጅ፥የአሜስያስ፡ልጅ፥
46፤የኬልቅያስ፡ልጅ፥የአማሲ፡ልጅ፥
47፤የባኒ፡ልጅ፥የሴሜር፡ልጅ፥የሞሖሊ፡ልጅ፥የሙሲ፡ልጅ፥የሜራሪ፡ልጅ፥የሌዊ፡ልጅ።
48፤ወንድሞቻቸውም፡ሌዋውያን፡ለእግዚአብሔር፡ቤት፡ማደሪያ፡አገልግሎት፡ዅሉ፡ተሰጡ።
49፤አሮንና፡ልጆቹ፡ግን፡የእግዚአብሔር፡ባሪያ፡ሙሴ፡እንዳዘዘው፡ዅሉ፡ለቅድስተ፡ቅዱሳን፡ሥራ፡ዅሉ፡ስለ፡እ ስራኤልም፡ያስተሰርይ፡ዘንድ፡ለሚቃጠለው፡መሥዋዕት፡በሚኾነው፡መሠዊያ፡ላይ፡ይሠዉ፡ነበር፥በዕጣኑም፡መሠዊ ያ፡ላይ፡ያጥኑ፡ነበር።
50፤የአሮንም፡ልጆች፡እነዚህ፡ናቸው፤ልጁ፡አልዓዛር፥
51፤ልጁ፡ፊንሐስ፥ልጁ፡አቢሱ፥ልጁ፡ቡቂ፥
52፤ልጁ፡ዖዚ፥ልጁ፡ዘራእያ፥ልጁ፡መራዮት፥
53፤ልጁ፡አማርያ፥ልጁ፡አኪጦብ፥ልጁ፡ሳዶቅ፥ልጁ፡አኪማዐስ።
54፤ማደሪያዎቻቸውም፡በየሰፈራቸው፡በየዳርቻቸው፡እነዚህ፡ናቸው፤ለአሮን፡ልጆች፡ለቀአት፡ወገኖች፡አንደኛው ፡ዕጣ፡ነበረ።
55፤ለእነርሱ፡በይሁዳ፡አገር፡ያለችውን፡ኬብሮንን፥በርሷም፡ዙሪያ፡የነበረውን፡መሰምሪያ፡ሰጡ፤
56፤የከተማዪቱን፡ዕርሻ፡ግን፡መንደሮቿንም፡ለዮፎኒ፡ልጅ፡ለካሌብ፡ሰጡ።
57፤ለአሮንም፡ልጆች፡የመማፀኛውን፡ከተማዎች፥ኬብሮንን፥ልብናንና፡መሰምሪያዋን፥ደግሞ፡የቲርን፥
58፤ኤሽትሞዐንና፡መሰምሪያዋን፥ሖሎንንና፡መሰምሪያዋን፥ዳቤርንና፡መሰምሪያዋን፥
59፤ዓሳንንና፡መሰምሪያዋን፥ቤትሳሚስንና፡መሰምሪያዋን፤
60፤ከብንያምም፡ነገድ፡ጌባንና፡መሰምሪያዋን፥ጋሌማትንና፡መሰምሪያዋን፥ዐናቶትንና፡መሰምሪያዋን፡ሰጡ።ከተ ማዎቻተው፡ዅሉ፡በየወገናቸው፡ዐሥራ፡ሦስት፡ነበሩ።
61፤ለቀሩትም፡ለቀአት፡ልጆች፡ከነገዱ፡ወገን፡ከምናሴ፡ነገድ፡እኩሌታ፡ዐሥር፡ከተማዎች፡በዕጣ፡ተሰጡ።
62፤ለጌድሶንም፡ልጆች፡በየወገናቸው፡ከይሳኮር፡ነገድ፥ከአሴርም፡ነገድ፥ከንፍታሌምም፡ነገድ፥በባሳንም፡ካለ ው፡ከምናሴ፡ነገድ፥ዐሥራ፡ሦስት፡ከተማዎች፡ተሰጡ።
63፤ለሜራሪ፡ልጆች፡በየወገናቸው፡ከሮቤል፡ነገድ፥ከጋድም፡ነገድ፥ከዛብሎንም፡ነገድ፥ዐሥራ፡ኹለት፡ከተማዎች ፡በዕጣ፡ተሰጡ።
64፤የእስራኤልም፡ልጆች፡ለሌዋውያን፡ከተማዎችን፡ከመሰምሪያዎቻቸው፡ጋራ፡ሰጡ።
65፤ከይሁዳም፡ልጆች፡ነገድ፥ከስምዖንም፡ልጆች፡ነገድ፥ከብንያምም፡ልጆች፡ነገድ፥እነዚህን፡በስማቸው፡የተጠ ሩትን፡ከተማዎች፡በዕጣ፡ሰጡ።
66፤ከቀአትም፡ልጆች፡ወገኖች፡ለአንዳንዶቹ፡ከኤፍሬም፡ነገድ፡ከተማዎች፡ድርሻ፡ነበራቸው።
67፤በተራራማው፡በኤፍሬም፡አገር፡ያሉትን፡የመማፀኛውን፡ከተማዎች፡ሴኬምንና፡መሰምሪያዋን፥ደግሞም፡ጌዝርን ና፡መሰምሪያዋን፥ዮቅምዓምንና፡መሰምሪያዋን፥
68፤ቤትሖሮንንና፡መሰምሪያዋን፥
69፤ኤሎንንና፡መሰምሪያዋን፥ጋትሪሞንንና፡መሰምሪያዋን፡ሰጧቸው።
70፤ከምናሴም፡ነገድ፡እኩሌታ፡ዐኔርንና፡መሰምሪያዋን፥ቢልዓምንና፡መሰምሪያዋን፡ከቀአት፡ልጆች፡ወገን፡ለቀ ሩት፡ሰጡ።
71፤ለጌድሶን፡ልጆች፡ከምናሴ፡ነገድ፡እኩሌታ፡ወገን፡በባሳን፡ያለችው፡ጎላንና፡መሰምሪያዋ፥ዐስታሮትና፡መሰ ምሪያዋ፤
72፤ከይሳኮርም፡ነገድ፡ቃዴስና፡መሰምሪያዋ፥ዳብራትና፡መሰምሪያዋ፥
73፤ራሞትና፡መሰምሪያዋ፥ዐኔምና፡መሰምሪያዋ፤
74፤ከአሴርም፡ነገድ፡መዓሳልና፡መሰምሪያዋ፥ዐብዶንና፡መሰምሪያዋ፥
75፤ሑቆቅና፡መሰምሪያዋ፥ረአብና፡መሰምሪያዋ፤
76፤ከንፍታሌምም፡ነገድ፡በገሊላ፡ያለችው፡ቃዴስና፡መሰምሪያዋ፥ሐሞንና፡መሰምሪያዋ፥ቂርያታይምና፡መሰምሪያ ዋ፡ተሰጡ።
77፤ከሌዋውያን፡ለቀሩት፡ለሜራሪ፡ልጆች፡ከዛብሎን፡ነገድ፡ሬሞንና፡መሰምሪያዋ፥ታቦርና፡መሰምሪያዋ፤
78፤ከሮቤልም፡ነገድ፡በኢያሪኮ፡አንጻር፡በዮርዳኖስ፡ማዶ፡በምሥራቅ፡በኩል፡በምድረ፡በዳ፡ያለችው፡ቦሶርና፡ መሰምሪያዋ፥
79፤ያሳና፡መሰምሪያዋ፥ቅዴሞትና፡መሰምሪያዋ፥ሜፍዓትና፡መሰምሪያዋ፤
80፤ከጋድም፡ነገድ፡በገለዓድ፡ያለችው፡ሬማትና፡መሰምሪያዋ፥መሃናይምና፡መሰምሪያዋ፥
81፤ሐሴቦንና፡መሰምሪያዋ፥ኢያዜርና፡መሰምሪያዋ፡ተሰጡ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡7።______________
ምዕራፍ፡7።
1፤የይሳኮርም፡ልጆች፥ቶላ፥ፉዋ፥ያሱብ፡ሺምሮን፥አራት፡ናቸው።
2፤የቶላም፡ልጆች፥ዖዚ፥ራፋያ፥ይሪኤል፥የሕማይ፥ይብሣም፥ሽሙኤል፥የአባታቸው፡የቶላ፡ቤት፡አለቃዎች፥በትውል ዳቸው፡ጽኑዓን፡ኀያላን፡ሰዎች፡ነበሩ፤በዳዊት፡ዘመን፡ቍጥራቸው፡ኻያ፡ኹለት፡ሺሕ፡ስድስት፡መቶ፡ነበረ።
3፤የዖዚም፡ልጆች፡ይዝረሕያ፤የይዝረሕያም፡ልጆች፡ሚካኤል፥ዐብድዩ፥ኢዮኤል፥ይሺያ፡ዐምስት፡ናቸው፤ዅሉም፡አ ለቃዎች፡ነበሩ።
4፤ከነርሱም፡ጋራ፡በየትውልዳቸው፡በያባቶቻቸው፡ቤቶች፡ለሰልፍ፡የተዘጋጁ፡የሰራዊት፡ጭፍራዎች፡ነበሩ፤ብዙም ፡ሴቶችና፡ልጆች፡ነበሯቸውና፡ሠላሳ፡ስድስት፡ሺሕ፡ነበሩ።
5፤ወንድሞቻቸውም፡በይሳኮር፡ወገኖች፡ዅሉ፡ጽኑዓን፡ኀያላን፡ሰዎች፡በትውልዳቸው፡ዅሉ፡የተቈጠሩ፡ሰማንያ፡ሰ ባት፡ሺሕ፡ነበሩ።
6፤የብንያም፡ልጆች፡ቤላ፥ቤኬር፥ይዲኤል፡ሦስት፡ነበሩ።
7፤የቤላም፡ልጆች፥ኤሴቦን፥ዖዚ፥ዑዝኤል፥ኢያሪሙት፥ዒሪ፥ዐምስት፡ነበሩ፤የአባቶቻቸው፡ቤቶች፡አለቃዎች፥ጽኑ ዓን፡ኀያላን፡ሰዎች፡ነበሩ፤በትውልድ፡የተቈጠሩ፡ኻያ፡ኹለት፡ሺሕ፡ሠላሳ፡አራት፡ነበሩ።
8፤የቤኬርም፡ልጆች፤ዝሚራ፥ኢዮአስ፥አልዓዛር፥ኤልዮዔናይ፥ዖምሪ፥ኢያሪሙት፥አብያ፥ዐናቶት፥ዓሌሜት፤እነዚህ ፡ዅሉ፡የቤኬር፡ልጆች፡ነበሩ።
9፤በየትውልዳቸው፡መዝገብ፡የተቈጠሩ፥የአባቶቻቸው፡ቤቶች፡አለቃዎች፥ጽኑዓን፡ኀያላን፡ሰዎች፡ኻያ፡ሺሕ፡ኹለ ት፡መቶ፡ነበሩ።
10፤የይዲኤልም፡ልጅ፡ቢልሐን፡ነበረ፤የቢልሐንም፡ልጆች፡የዑስ፥ብንያም፥ኤሑድ፥ክንዓና፥ዜታን፥ተርሴስ፥አኪ ሳአር፡ነበሩ።
11፤እነዚህ፡ዅሉ፡የይዲኤል፡ልጆች፡ነበሩ፤በያባቶቻቸው፡ቤቶች፡አለቃዎች፥ጭፍራ፡እየኾኑ፡ወደ፡ሰልፍ፡የሚወ ጡ፡ጽኑዓን፡ኀያላን፡ሰዎች፡ዐሥራ፡ሰባት፡ሺሕ፡ኹለት፡መቶ፡ነበሩ።
12፤ደግሞም፡ሳፊን፥ሑፊም፡የዒር፡ልጆች፥ሑሺም፡የአሔር፡ልጆችም፡ነበሩ።
13፤የንፍታሌም፡ልጆች፥ያሕጽኤል፥ጉኒ፥ዬጽር፥ሺሌም፥የባላ፡ልጆች፡ነበሩ።
14፤የምናሴ፡ልጆች፡ሶርያዪቱ፡ቁባቱ፡የወለደችለት፡እስርኤልና፡የገለዓድ፡አባት፡ማኪር፡ናቸው።
15፤ማኪርም፡ከሑፊምና፡ከሳፊን፡ወገን፡ሚስት፡አገባ፤የእኅቷም፡ስም፡መዓካ፡ነበረ፤የኹለተኛውም፡ስም፡ሰለጰ አድ፡ነበረ፤ለሰለጰዓድም፡ሴቶች፡ልጆች፡ነበሩት።
16፤የማኪርም፡ሚስት፡መዓካ፡ልጅ፡ወለደች፥ስሙንም፡ፋሬስ፡ብላ፡ጠራችው፤የወንድሙም፡ስም፡ሱሮስ፡ነበረ፤ልጆ ቹም፡ኡላም፥ራቄም፡ነበሩ።
17፤የኡላምም፡ልጅ፡ባዳን፡ነበረ፤እነዚህ፡የምናሴ፡ልጅ፡የማኪር፡ልጅ፡የገለዓድ፡ልጆች፡ነበሩ።
18፤እኅቱ፡መለኬት፡ኢሱድን፥አቢዔዝርን፥መሕላን፡ወለደች።
19፤የሸሚዳም፡ልጆች፡አኂያን፥ሴኬም፥ሊቅሒ፥አኒዐም፡ነበሩ።
20፤የኤፍሬም፡ልጆች፤ሹቱላ፥ልጁ፡ባሬድ፥ልጁ፡ታሐት፥ልጁ፡ኤልዓዳ፥ልጁ፡ታሐት፥ልጁ፡ዛባድ፥ልጁ፡ሽቱላ፥
21፤የአገሩም፡ተወላጆች፡የጌት፡ሰዎች፡ከብቶቻቸውን፡ሊወስዱ፡ወርደው፡ነበርና፥የገደሏቸው፡ልጆቹ፡ኤድርና፡ ኤልዓድ፡ነበሩ።
22፤አባታቸውም፡ኤፍሬም፡ብዙ፡ቀን፡አለቀሰ፥ወንድሞቹም፡ሊያጽናኑት፡መጡ።
23፤ወደ፡ሚስቱም፡ገባ፥አረገዘችም፥ወንድ፡ልጅም፡ወለደች፤በቤቱም፡መከራ፡ኾኗልና፥ስሙ፡በሪዐ፡ብሎ፡ጠራው።
24፤ሴት፡ልጁም፡ታችኛውንና፡ላይኛውን፡ቤትሖሮንንና፡ኡዜንሼራን፡የሠራች፡ሲአራ፡ነበረች።
25፤ወንዶች፡ልጆቹም፡ፋፌ፥ሬሴፍ፥ልጁ፡ቴላ፥
26፤ልጁ፡ታሐን፥ልጁ፡ለአዳን፥ልጁ፡ዐሚሁድ፥ልጁ፡ኤሊሳማ፥
27፤ልጁ፡ነዌ፥ልጁ፡ኢያሱ።
28፤ግዛታቸውና፡ማደሪያቸው፡ቤቴልና፡መንደሮቿ፥በምሥራቅም፡በኩል፡ነዓራን፥በምዕራብም፡በኩል፡ጌዝርና፡መን ደሮቿ፥ደግሞ፡ሴኬምና፡መንደሮቿ፡እስከ፡ጋዛና፡እስከ፡መንደሮቿ፡ድረስ፥
29፤በምናሴም፡ልጆች፡ዳርቻ፡ቤትሳንና፡መንደሮቿ፥ታዕናክና፡መንደሮቿ፥መጊዶና፡መንደሮቿ፥ዶርና፡መንደሮቿ፡ ነበሩ፤በእነዚህ፡የእስራኤል፡ልጅ፡የዮሴፍ፡ልጆች፡ተቀመጡ።
30፤የአሴር፡ልጆች፡ዪምና፥የሱዋ፥የሱዊ፥በሪዐ፥እኅታቸውም፡ሤራሕ።
31፤የበሪዐም፡ልጆች፤ሔቤር፥የቢርዛዊት፡አባት፡የነበረው፡መልኪኤል።
32፤ሔቤርም፡ያፍሌጥን፥ሳሜርን፥ኮታምን፥እኅታቸውንም፡ሶላን፡ወለደ።
33፤የያፍሌጥም፡ልጆች፡ፋሴክ፥ቢምኻል፥ዐሲት፡ነበሩ፤እነዚህ፡የያፍሌጥ፡ልጆች፡ነበሩ።
34፤የሳሜርም፡ልጆች፡አኪ፥ሮኦጋ፥ይሑባ፥አራም፡ነበሩ።
35፤የወንድሙም፡የዔላም፡ልጆች፡ጾፋ፥ይምና፥ሰሌስ፥ዓማል፡ነበሩ።
36፤የጾፋም፡ልጆች፡ሱዋ፥ሐርኔፍር፥
37፤ሦጋል፥ቤሪ፥ይምራ፥ቤጼር፥ሆድ፥ሳማ፥ሰሊሳ፥ይትራን፥ብኤራ፡ነበሩ።
38፤የዬቴር፡ልጆች፡ዮሮኒ፥ፊሥጳ፥አራ፡ነበሩ።
39፤የዑላ፡ልጆች፡ኤራ፥ሐኒኤል፥ሪጽያ፡ነበሩ።
40፤እነዚህ፡ዅሉ፡የአሴር፡ልጆች፥የአባቶቻቸው፡ቤቶች፡አለቃዎች፥የተመረጡ፡ጽኑዓን፡ኀያላን፡ሰዎች፥የመኳን ንቱ፡አለቃዎች፡ነበሩ።በትውልዳቸውም፡በሰልፍ፡ለመዋጋት፡የተቈጠሩ፡ኻያ፡ስድስት፡ሺሕ፡ሰዎች፡ነበሩ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡8።______________
ምዕራፍ፡8።
1፤ብንያምም፡በኵሩን፡ቤላን፥ኹለተኛውንም፡አስቤልን፥
2፤ሦስተኛውንም፡አሐራን፥አራተኛውንም፡ኖሐን፥ዐምስተኛውንም፡ራፋን፡ወለደ።
3፤ለቤላም፡ልጆች፡ነበሩት፤አዳ፟ር፥ጌራ፥አቢሁድ፥
4፤አቢሱ፥ናዕማን፥አኆዋ፥ጌራ፥ሰፉፋም፥ሑራም።
5፤6፤እነዚህም፡የኤሑድ፡ልጆች፡ናቸው፤እነዚህ፡በጌባ፡የሚቀመጡ፡የአባቶቻቸው፡ቤቶች፡አለቃዎች፡ናቸው፤
7፤ወደ፡መናሐትም፡ተማረኩ፤ናዕማን፥አኪያ፥ጌራ፥እነርሱም፡ተማረኩ።ዖዛንና፡አኂሁድን፡ወለደ።
8፤ሸሐራይምም፡ሚስቶቹን፡ሑሺምንና፡በዕራን፡ከሰደደ፡በዃላ፡በሞዐብ፡ሜዳ፡ልጆች፡ወለደ።
9፤ከሚስቱ፡ከሖዴሽ፡ዮባብን፥
10፤ዲብያን፥ማሴን፥ማልካምን፥ይዑጽን፥ሻክያን፥ሚርማን፡ወለደ።እነዚህም፡ልጆች፡የአባቶች፡ቤቶች፡አለቃዎች ፡ነበሩ።
11፤ከሑሺምም፡አቢጡብንና፡ኤልፍዓልን፡ወለደ።
12፤የኤልፍዓልም፡ልጆች፤ዔቤር፥ሚሻም፥ኦኖንና፡ሎድን፡መንደሮቻቸውንም፡የሠራ፡ሻሚድ፤
13፤በሪዐ፥ሽማዕ፡የጌትን፡ሰዎች፡ያሳደዱ፡የኤሎን፡ሰዎች፡የአባቶቻቸው፡ቤቶች፡አለቃዎች፡ነበሩ፤
14፤አኂዮ፥ሻሻቅ፥ይሬምት፥
15፤16፤ዝባድያ፥ዓራድ፥ዔድር፥ሚካኤል፥ይሽጳ፥ዮሐ፥የበሪዐ፡ልጆች፤
17፤ዝባድያ፥ሜሱላም፥
18፤ሕዝቂ፥ሔቤር፥ይሽምራይ፥ይዝሊያ፥ዮባብ፥የኤልፍዓል፡ልጆች፤
19፤ያቂም፥ዝክሪ፥ዘብዲ፥
20፤21፤ኤሊዔናይ፥ጺልታይ፥ኤሊኤል፥ዓዳያ፥ብራያ፥ሺምራት፥የሰሜኢ፡ልጆች፤
22፤ይሽጳን፥
23፤ዔቤር፥ኤሊኤል፥ዐብዶን፥ዝክሪ፥
24፤25፤ሐናን፥ሐናንያ፥ዔላም፥ዐንቶትያ፥ይፍዴያ፥ፋኑኤል፥የሶሴቅ፡ልጆች፤
26፤ሸምሽራይ፥
27፤ሸሃሪያ፥ጎቶልያ፥ያሬሽያ፥ኤልያስ፥ዝክሪ፥የይሮሐም፡ልጆች።
28፤እነዚህ፡በትውልዶቻቸው፡አለቃዎች፡ነበሩ፤የአባቶቻቸው፡ቤቶች፡አለቃዎች፡ነበሩ፤እነዚህ፡በኢየሩሳሌም፡ ተቀመጡ።
29፤የሚስቱ፡ስም፡መዓካ፡የነበረው፡የገባዖን፡አባት፡ይዒኤል፥
30፤የበኵር፡ልጁ፡ዐብዶን፥
31፤ዱር፥ቂስ፥በዓል፥ናዳብ፥ጌዶር፥አኂዮ፥ዛኩር፡በገባዖን፡ተቀመጡ።
32፤ሚቅሎት፡ሳምአን፡ወለደ፤እነርሱ፡ደግሞ፡ከወንድሞቻቸው፡ጋራ፡በኢየሩሳሌም፡በወንድሞቻቸው፡ፊት፡ለፊት፡ ተቀመጡ።
33፤ኔር፡ቂስን፡ወለደ፤ቂስም፡ሳኦልን፡ወለደ፤ሳኦልም፡ዮናታንን፥ሚልኪሳን፥ዐሚናዳብን፥አስበዓልን፡ወለደ።
34፤የዮናታንም፡ልጅ፡መሪበዓል፡ነበረ፤መሪበዓልም፡ሚካን፡ወለደ።
35፤የሚካም፡ልጆች፡ፒቶን፥ሜሌክ፥ታሬዓ፥አካዝ፡ነበሩ።
36፤አካዝም፡ይሆዓዳን፡ወለደ፤ይሆዓዳም፡ዓሌሜትን፥ዓዝሞትን፥ዘምሪን፡ወለደ፤ዘምሪም፡ሞጻን፡ወለደ።
37፤ሞጻም፡ቢንዓን፡ወለደ፤ልጁም፡ረፋያ፡ነበረ፥ልጁ፡ኤልዓሣ፥ልጁ፡ኤሴል፤
38፤ለኤሴልም፡ስድስት፡ልጆች፡ነበሩት፤ስማቸውም፡ይህ፡ነበረ፤ዐዝሪቃም፥ቦክሩ፥እስማኤል፥ሽዓርያ፥ዐብድዩ፥ ሐናን፤እነዚህ፡ዅሉ፡የኤሴል፡ልጆች፡ነበሩ።
39፤የወንድሙም፡የአሴል፡ልጆች፤በኵሩ፡ኡላም፥ኹለተኛውም፡ኢያስ፥ሦስተኛውም፡ኤሊፋላት።
40፤የኡላም፡ልጆች፡ጽኑዓን፡ኀያላንና፡ቀስተኛዎች፡ነበሩ፤ለእነርሱም፡መቶ፡ዐምሳ፡የሚያኽሉ፡ብዙ፡ልጆችና፡ የልጅ፡ልጆች፡ነበሯቸው፤እነዚህ፡ዅሉ፡የብንያም፡ልጆች፡ነበሩ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡9።______________
ምዕራፍ፡9።
1፤እስራኤልም፡ዅሉ፡በየትውልዳቸው፡ተቈጠሩ፤እንሆም፥በእስራኤል፡ነገሥታት፡መጽሐፍ፡ተጽፈዋል።ይሁዳም፡ስለ ፡ኀጢአታቸው፡ወደ፡ባቢሎን፡ተማረኩ።
2፤በአውራጃዎቻቸውና፡በከተማዎቻቸው፡መዠመሪያ፡የተቀመጡ፡እስራኤልና፡ካህናት፡ሌዋውያንም፡ናታኒምም፡ነበሩ ።
3፤ከይሁዳ፡ልጆችና፡ከብንያም፡ልጆች፡ከኤፍሬምና፡ከምናሴ፡ልጆች፡በኢየሩሳሌም፡ተቀመጡ።
4፤ከይሁዳ፡ልጅ፡ከፋሬስ፡ልጆች፡የባኒ፡ልጅ፡የአምሪ፡ልጅ፡የዖምሪ፡ልጅ፡የዐሚሁድ፡ልጅ፡ዑታይ፡ደግሞ፡ተቀመ ጠ።
5፤ከሴሎናውያንም፡በኵሩ፡ዐሣያና፡ልጆቹ።
6፤ከዛራም፡ልጆች፡ይዑኤልና፡ወንድሞቻቸው፥ስድስት፡መቶ፡ዘጠና።
7፤ከብንያምም፡ልጆች፡የሐስኑአ፡ልጅ፡የሆዳይዋ፡ልጅ፡የሜሱላም፡ልጅ፡ሰሉ፤
8፤የይሮሐም፡ልጅ፡ብኔያ፤የሚክሪ፡ልጅ፡የዖዚ፡ልጅ፡ኤላ፤የዪብኒያ፡ልጅ፡የራጉኤል፡ልጅ፡የሰፋጥያስ፡ልጅ፡ሜ ሱላም፤
9፤በየትውልዳቸውም፡ወንድሞቻቸው፡ዘጠኝ፡መቶ፡ኀምሳ፡ስድስት፡ነበሩ፤እነዚህ፡ሰዎች፡ዅሉ፡የአባቶቻቸው፡ቤቶ ች፡አለቃዎች፡ነበሩ።
10፤ከካህናቱም፡ዮዳዔ፥ዮአሪብ፥ያኪን፤
11፤የእግዚአብሔርም፡ቤት፡አለቃ፡የአኪጦብ፡ልጅ፡የመራዮት፡ልጅ፡የሳዶቅ፡ልጅ፡ሜሱላም፡ልጅ፡የኬልቅያስ፡ል ጅ፡ዐዛርያስ፤
12፤የመልኪያ፡ልጅ፡የጳስኮር፡ልጅ፡የይሮሐም፡ልጅ፡ዓዳያ፤የኢሜር፡ልጅ፡የምሺላሚት፡ልጅ፡የሜሱላም፡ልጅ፡የ የሕዜራ፡ልጅ፡የዓዲኤል፡ልጅ፡መዕሣይ፤
13፤የአባቶቻቸውም፡ቤቶች፡አለቃዎች፡ወንድሞቻቸው፡ሺሕ፡ሰባት፡መቶ፡ስድሳ፡ነበሩ፤ለእግዚአብሔር፡ቤት፡ማገ ልገል፡ሥራ፡እጅግ፡ብልኀተኛዎች፡ሰዎች፡ነበሩ።
14፤ከሌዋውያንም፡የሜራሪ፡ልጆች፡የዐሳብያ፡ልጅ፡የዐዝሪቃም፡ልጅ፡የዐሱብ፡ልጅ፡ሸማያ፤
15፤በቅበቃር፥ዔሬስ፥ጋላል፥የአሣፍ፡ልጅ፡የዝክሪ፡ልጅ፡የሚካ፡ልጅ፡መታንያ፤
16፤የኤዶታም፡ልጅ፡የጋላል፡ልጅ፡የሰሙስ፡ልጅ፡ዐብድያ፤በነጦፋውያንም፡መንደሮች፡የተቀመጠው፡የሕልቃና፡ል ጅ፡የአሣ፡ልጅ፡በራክያ።
17፤በረኛዎችም፡ሰሎም፥ዐቁብ፥ጤልሞን፥አኂማን፥ወንድሞቻቸውም፡ነበሩ፤ሰሎምም፡አለቃ፡ነበረ።
18፤እስከ፡ዛሬም፡ድረስ፡በንጉሥ፡በር፡በምሥራቅ፡በኩል፡ነበሩ፤ለሌዊ፡ልጆች፡ሰፈር፡በረኛዎች፡ነበሩ።
19፤የቆሬም፡ልጅ፡የአብያሣፍ፡ልጅ፡የቆሬ፡ልጅ፡ሰሎም፡ከአባቱም፡ቤት፡የነበሩ፡ወንድሞቹ፡ቆሬያውያን፡በማገ ልገል፡ሥራ፡ላይ፡ነበሩ፥የድንኳኑንም፡መድረክ፡ይጠብቁ፡ነበር።አባቶቻቸውም፡የእግዚአብሔርን፡ሰፈር፡መግቢ ያ፡ጠብቀው፡ነበር።
20፤አስቀድሞም፡የአልዓዛር፡ልጅ፡ፊንሐስ፡አለቃቸው፡ነበረ፤እግዚአብሔርም፡ከርሱ፡ጋራ፡ነበረ።
21፤የሜሱላም፡ልጅ፡ዘካርያስ፡የመገናኛው፡ድንኳን፡ደጅ፡በረኛ፡ነበረ።
22፤የመድረኩ፡በረኛዎች፡ይኾኑ፡ዘንድ፡የተመረጡ፡እነዚህ፡ዅሉ፡ኹለት፡መቶ፡ዐሥራ፡ኹለት፡ነበሩ።ዳዊትና፡ነ ቢዩ፡ሳሙኤል፡በሥራቸው፡ያቆሟቸው፡እነዚህ፡በመንደሮቻቸው፡በየትውልዳቸው፡ተቈጠሩ።
23፤እነርሱና፡ልጆቻቸውም፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡በድንኳኑ፡ደጆች፡ላይ፡ዘበኛዎች፡ነበሩ።
24፤በአራቱ፡ማእዘኖች፥በምሥራቅ፥በምዕራብ፥በሰሜን፥በደቡብ፥በረኛዎች፡ነበሩ።
25፤ወንድሞቻቸውም፡በመንደሮቻቸው፡ኾነው፥በየሰባትም፡ቀን፡ከነርሱ፡ጋራ፡ሊኾኑ፡ከጊዜ፡ወደ፡ጊዜ፡ይገቡ፡ነ በር።
26፤ከሌዋውያንም፡የነበሩ፡አራቱ፡የበረኛዎች፡አለቃዎች፡ዘወትር፡በሥራቸው፡ይቀመጡ፡ነበር፤በእግዚአብሔርም ፡ቤት፡ባሉ፡ጓዳዎችና፡ቤተ፡መዛግብት፡ላይ፡ነበሩ።
27፤የእግዚአብሔርንም፡ቤት፡የሚጠብቁ፥ጧት፡ጧትም፡ደጆቹን፡የሚከፍቱ፡እነርሱ፡ነበሩና፥በዚያ፡ያድሩ፡ነበር ።
28፤ዕቃውም፡በቍጥር፡ይገባና፡ይወጣ፡ነበርና፥ከነዚህ፡አንዳንዱ፡በማገልገያው፡ዕቃ፡ላይ፡ሹሞች፡ነበሩ።
29፤ከነርሱም፡አንዳንዶቹ፡በመቅደሱ፡ዕቃ፡ዅሉ፡በመልካሙም፡ዱቄት፥በወይን፡ጠጁ፥በዘይቱም፥በዕጣኑም፥በሽቱ ውም፡ላይ፡ሹሞች፡ነበሩ።
30፤ከካህናቱም፡ልጆች፡አንዳንዶቹ፡የሽቱውን፡ቅባት፡ያጣፍጡ፡ነበር።
31፤የቆሬያዊውም፡የሰሎም፡በኵር፡ሌዋዊው፡ማቲትያ፡በምጣድ፡በሚጋገረው፡ነገር፡ላይ፡ሹም፡ነበረ።
32፤በየሰንበቱም፡ያዘጋጁ፡ዘንድ፡ከወንድሞቻቸው፡ከቀአታውያን፡አንዳንዱ፡በገጹ፡ኅብስት፡ላይ፡ሹሞች፡ነበሩ ።
33፤ከሌዋውያኑም፡ወገን፡የአባቶቻቸው፡ቤቶች፡አለቃዎች፡የነበሩ፡መዘምራን፡እነዚህ፡ናቸው፤ሥራቸውም፡ሌሊት ና፡ቀን፡ነበረና፡ያለሌላ፡ሥራ፡በየጓዳቸው፡ይቀመጡ፡ነበር።
34፤እነዚህ፡ከሌዋውያን፡የአባቶቻቸው፡ቤቶች፡አለቃዎች፡በየትውልዳቸው፡አለቃዎች፡ነበሩ።እነዚህም፡በኢየሩ ሳሌም፡ይቀመጡ፡ነበር።
35፤የሚስቱ፡ስም፡መዓካ፡የነበረው፡የገባዖን፡አባት፡ይዒኤል፥
36፤የበኵር፡ልጁም፡ዐብዶን፥
37፤ዱር፥ቂስ፥በዓል፥ኔር፥ናዳብ፥ጌዶር፥አኂዮ፥ዛኩር፥ሚቅሎት፥በገባኦን፡ይቀመጡ፡ነበር።
38፤ሚቅሎትም፡ሳምአን፡ወለደ፤እነርሱ፡ደግሞ፡ከወንድሞቻቸው፡ጋራ፡በኢየሩሳሌም፡በወንድሞቻቸው፡ፊት፡ለፊት ፡ይቀመጡ፡ነበር።
39፤ኔርም፡ቂስን፡ወለደ፤ቂስም፡ሳኦልን፡ወለደ፤ሳኦልም፡ዮናታንን፥ሚልኪሳን፥ዐሚናዳብን፥አስበዓልን፡ወለደ ።
40፤የዮናታንም፡ልጅ፡መሪበዓል፡ነበረ፤መሪበዓልም፡ሚካን፡ወለደ።
41፤የሚካም፡ልጆች፡ፒቶን፥ሜሌክ፥ታሬዓ፥አካዝ፡ነበሩ።
42፤አካዝም፡የዕራን፡ወለደ፤የዕራም፡ዓሌሜትን፥ዓዝሞትን፥ዘምሪን፡ወለደ፤ዘምሪም፡ሞጻን፡ወለደ።
43፤ሞጻም፡ቢንዓን፡ወለደ፥ልጁም፡ረፋያ፡ነበረ፥ልጁ፡ኤልዓሣ፥ልጁ፡ኤሴል፤
44፤ለኤሴልም፡ስድስት፡ልጆች፡ነበሩት፤ስማቸውም፡ይህ፡ነበረ፤ዐዝሪቃም፥ቦክሩ፥እስማኤል፥ሸዓሪያ፥ዐብድዩ፥ ሐናን፤እነዚህ፡የኤሴል፡ልጆች፡ነበሩ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡10።______________
ምዕራፍ፡10።
1፤ፍልስጥኤማውያንም፡ከእስራኤል፡ጋራ፡ተዋጉ፤የእስራኤልም፡ሰዎች፡ከፍልስጥኤማውያን፡ፊት፡ሸሹ፥ተወግተውም ፡በጊልቦአ፡ተራራ፡ላይ፡ወደቁ።
2፤ፍልስጥኤማውያንም፡ሳኦልንና፡ልጆቹን፡በእግር፡በእግራቸው፡ተከትለው፡አባረሯቸው፤ፍልስጥኤማውያንም፡የሳ ኦልን፡ልጆች፡ዮናታንንና፡ዐሚናዳብን፡ሜልኪሳንም፡ገደሉ።
3፤ሰልፍም፡በሳኦል፡ላይ፡ጠነከረ፥ቀስተኛዎችም፡አገኙት፤ከቀስተኛዎችም፡የተነሣ፡ተጨነቀ።
4፤ሳኦልም፡ጋሻ፡ዣግሬውን፦እነዚህ፡ቈላፋን፡መጥተው፡እንዳይዘብቱብኝ፡ሰይፍኽን፡መዘ፟ኽ፡ውጋኝ፡አለው።ጋሻ ፡ዣግሬው፡ግን፡እጅግ፡ፈርቶ፡ነበርና፥እንቢ፡አለ።ሳኦልም፡ሰይፉን፡ወስዶ፡በላዩ፡ወደቀ።
5፤ጋሻ፡ዣግሬውም፡ሳኦል፡እንደ፡ሞተ፡ባየ፡ጊዜ፡ርሱ፡ደግሞ፡በሰይፉ፡ላይ፡ወድቆ፡ሞተ።
6፤ሳኦልና፡ሦስቱ፡ልጆቹ፡የቤቱም፡ሰዎች፡ዅሉ፡ባንድ፡ላይ፡ሞቱ።
7፤በሸለቆውም፡የነበሩት፡የእስራኤል፡ሰዎች፡ዅሉ፡እንደ፡ሸሹ፥ሳኦልና፡ልጆቹም፡እንደ፡ሞቱ፡ባዩ፡ጊዜ፡ከተማ ዎቻቸውን፡ለቀ፟ው፡ሸሹ፤ፍልስጥኤማውያንም፡መጥተው፡ተቀመጡባቸው።
8፤በነጋውም፡ፍልስጥኤማውያን፡የሞቱትን፡ለመግፈፍ፡በመጡ፡ጊዜ፡ሳኦልንና፡ልጆቹን፡በጊልቦአ፡ተራራ፡ላይ፡ወ ድቀው፡አገኟቸው።
9፤ገፈፉትም፥ራሱንና፡መሣሪያውንም፡አንሥተው፡ለጣዖቶቻቸውና፡ለሕዝቡ፡የምሥራች፡ይወስዱ፡ዘንድ፡ወደፍልስጥ ኤማውያን፡አገር፡ዙሪያ፡ሰደዱ።
10፤መሣሪያውንም፡በአምላኮቻቸው፡ቤት፡ውስጥ፡አኖሩ፤ራሱንም፡በዳጎን፡ቤት፡ውስጥ፡ቸነከሩት።
11፤የኢያቢስ፡ገለዓድም፡ሰዎች፡ዅሉ፡ፍልስጥኤማውያን፡በሳኦል፡ላይ፡ያደረጉትን፡ዅሉ፡በሰሙ፡ጊዜ፥
12፤ጽኑአን፡ሰዎች፡ዅሉ፡ተነሥተው፡የሳኦልን፡ሬሳ፡የልጆቹንም፡ሬሳ፡ወሰዱ፥ወደ፡ኢያቢስም፡አመጧቸው፤በኢያ ቢስም፡ካለው፡ከትልቁ፡ዛፍ፡በታች፡ዐጥንቶቻቸውን፡ቀበሩ፥ሰባት፡ቀንም፡ጾሙ።
13፤እንዲሁ፡ሳኦል፡በእግዚአብሔር፡ላይ፡ስላደረገው፡ኀጢአት፥የእግዚአብሔርንም፡ቃል፡ስላልጠበቀ፡ሞተ።ደግ ሞም፡መናፍስት፡ጠሪ፡
14፤ስለ፡ጠየቀ፡እግዚአብሔርንም፡ስላልጠየቀ፥ስለዚህ፡ገደለው፥መንግሥቱንም፡ወደእሴይ፡ልጅ፡ወደ፡ዳዊት፡አ ሳለፈው።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡11።______________
ምዕራፍ፡11።
1፤እስራኤልም፡ዅሉ፡በኬብሮን፡ወደ፡ዳዊት፡ተሰብስበው፦እንሆ፥እኛ፡የዐጥንትኽ፡ፍላጭ፡የሥጋኽ፡ቍራጭ፡ነን፤
2፤አስቀድሞ፡ሳኦል፡ንጉሥ፡ኾኖ፡ሳለ፡እስራኤልን፡የምታወጣና፡የምታገባ፡አንተ፡ነበርኽ፤አምላክኽ፡እግዚአብ ሔርም፦ሕዝቤን፡እስራኤልን፡አንተ፡ትጠብቃለኽ፤በሕዝቤም፡በእስራኤል፡ላይ፡አለቃ፡ትኾናለኽ፡ብሎኽ፡ነበር፡ አሉት።
3፤የእስራኤልም፡ሽማግሌዎች፡ዅሉ፡ወደ፡ንጉሡ፡ወደ፡ኬብሮን፡መጡ፤ዳዊትም፡በኬብሮን፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ቃ ል፡ኪዳን፡ከነርሱ፡ጋራ፡አደረገ፤በሳሙኤልም፡እጅ፡እንደተናገረው፡እንደእግዚአብሔር፡ቃል፡በእስራኤል፡ላይ ፡ንጉሥ፡ይኾን፡ዘንድ፡ዳዊትን፡ቀቡት።
4፤ዳዊትም፡እስራኤልም፡ዅሉ፡ኢያቡስ፡ወደምትባል፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ኼዱ፤በአገሩም፡የተቀመጡ፡ኢያቡሳውያን፡ በዚያ፡ነበሩ።
5፤በኢያቡስም፡የተቀመጡ፡ዳዊትን፦ወደዚህ፡አትገባም፡አሉት፤ዳዊት፡ግን፡ዐምባዪቱን፡ጽዮንን፡ያዘ፤ርሷም፡የ ዳዊት፡ከተማ፡ናት።
6፤ዳዊትም፦ኢያቡሳውያንን፡አስቀድሞ፡የሚመታ፡ሰው፡አለቃና፡መኰንን፡ይኾናል፡አለ።የጽሩያም፡ልጅ፡ኢዮአብ፡ አስቀድሞ፡ወጣ፥አለቃም፡ኾነ።
7፤ዳዊትም፡በዐምባዪቱ፡ውስጥ፡ተቀመጠ፤ስለዚህም፡የዳዊት፡ከተማ፡ብለው፡ጠሯት።
8፤ከሚሎም፡ዠምሮ፡በዙሪያው፡ከተማ፡ሠራ፤ኢዮአብም፡የቀረውን፡ከተማ፡አበጀ።
9፤ዳዊትም፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡ከርሱ፡ጋራ፡ነበርና፥እየበረታ፡ኼደ።
10፤ለዳዊትም፡የነበሩት፡የኀያላን፡አለቃዎች፡እነዚህ፡ናቸው፤ስለ፡እስራኤል፡እንደተናገረው፡የእግዚአብሔር ፡ቃል፡ያነግሡት፡ዘንድ፡ከእስራኤል፡ዅሉ፡ጋራ፡በመንግሥቱ፡ላይ፡አጸኑት።
11፤የዳዊትም፡ኀያላን፡ቍጥር፡ይህ፡ነበረ፤የሠላሳው፡አለቃ፡የአክሞናዊው፡ልጅ፡ያሾብአም፡ነበረ፤ርሱ፡ጦሩን ፡አንሥቶ፡ሦስት፡መቶ፡ሰው፡ባንድ፡ጊዜ፡ገደለ።
12፤ከርሱም፡በዃላ፡በሦስቱ፡ኀያላን፡መካከል፡የነበረ፡የአሆሃሂው፡የዱዲ፡ልጅ፡አልዓዛር፡ነበር።
13፤ርሱ፡ከዳዊት፡ጋራ፡በፈስደሚም፡ነበረ፥በዚያም፡ገብስ፡በሞላበት፡ዕርሻ፡ውስጥ፡ፍልስጥኤማውያን፡ለሰልፍ ፡ተሰብስበው፡ነበር፤ሕዝቡም፡ከፍልስጥኤማውያን፡ፊት፡ሸሹ።
14፤በዕርሻውም፡መካከል፡ቆመው፡ጠበቁት፥ፍልስጥኤማውያንንም፡ገደሉ፤እግዚአብሔርም፡በታላቅ፡ማዳን፡አዳናቸ ው።
15፤ከሠላሳውም፡አለቃዎች፡ሦስቱ፡ወርደው፡ዳዊት፡ወዳለበት፡ወደ፡አለቱ፡ወደዓዶላም፡ዋሻ፡መጡ፤የፍልስጥኤማ ውያንም፡ጭፍራ፡በራፋይም፡ሸለቆ፡ሰፍሮ፡ነበር።
16፤በዚያም፡ጊዜ፡ዳዊት፡በምሽጉ፡ውስጥ፡ነበረ፥የፍልስጥኤማውያንም፡ጭፍራ፡በቤተ፡ልሔም፡ነበረ።
17፤ዳዊትም፦በበሩ፡አጠገብ፡ካለችው፡ከቤተ፡ልሔም፡ምንጭ፡ውሃ፡ማን፡ይሰጠኛል፧ብሎ፡ተመኘ።
18፤እነዚህም፡ሦስቱ፡የፍልስጥኤማውያንን፡ሰራዊት፡ቀደ፟ው፡ኼዱ፥በበሩም፡አጠገብ፡ካለችው፡ከቤተ፡ልሔም፡ም ንጭ፡ውሃ፡ቀዱ፤ይዘውም፡ለዳዊት፡አመጡለት።ርሱ፡ግን፡ሊጠጣ፡አልወደደም፥ነገር፡ግን፥ለእግዚአብሔር፡አፍሶ ፟።
19፤ይህን፡ኣደርግ፡ዘንድ፡አምላኬ፡ይከልክለኝ፤በነፍሳቸው፡የደፈሩትም፡እነዚህ፡ሰዎች፡ደም፡እጠጣለኹን፧በ ነፍሳቸው፡አምጥተውታል፡አለ።ስለዚህም፡ይጠጣ፡ዘንድ፡አልወደደም።ሦስቱም፡ኀያላን፡ያደረጉት፡ይህ፡ነው።
20፤የኢዮአብም፡ወንድም፡አቢሳ፡የሦስቱ፡አለቃ፡ነበረ፤ጦሩንም፡በሦስት፡መቶ፡ላይ፡አንሥቶ፡ገደላቸው፥በሦስ ቱም፡መካከል፡ስሙ፡የተጠራ፡ነበረ።
21፤በኹለተኛውም፡ተራ፡በኾኑት፡በሦስቱ፡መካከል፡የከበረ፡ነበረ፥አለቃቸውም፡ኾነ፤ነገር፡ግን፥ወደ፡ፊተኛዎ ቹ፡ወደ፡ሦስቱ፡አልደረሰም።
22፤በቀብስኤልም፡የነበረው፥ታላቅ፡ሥራ፡ያደረገው፡የጽኑዕ፡ሰው፡የዮዳዔ፡ልጅ፡በናያስ፡የሞዐባዊን፡የአሪኤ ል፡ኹለቱን፡ልጆች፡ገደለ፤በዐመዳይም፡ወራት፡ወርዶ፡በጕድጓድ፡ውስጥ፡አንበሳ፡ገደለ።
23፤ቁመቱም፡ዐምስት፡ክንድ፡የነበረውን፡ረዥሙን፡ግብጻዊውን፡ሰው፡ገደለ፤በግብጻዊውም፡እጅ፡የሸማኔ፡መጠቅ ለያ፡የመሰለ፡ጦር፡ነበረ፤ርሱ፡ግን፡በትር፡ይዞ፡ወደ፡ርሱ፡ወረደ፥ከግብጻዊውም፡እጅ፡ጦሩን፡ነቅሎ፡በገዛ፡ ጦሩ፡ገደለው።
24፤የዮዳዔ፡ልጅ፡በናያስ፡ያደረገው፡ይህ፡ነው፤ስሙም፡በሦስቱ፡ኀያላን፡መካከል፡የተጠራ፡ነበር።
25፤እንሆ፥ከሠላሳው፡ይልቅ፡የከበረ፡ነበረ፥ነገር፡ግን፥ወደ፡ፊተኛዎቹ፡ወደ፡ሦስቱ፡አልደረሰም።ዳዊትም፡በ ዘበኛዎቹ፡ላይ፡ሾመው።
26፤ደግሞም፡በጭፍራዎች፡ዘንድ፡የነበሩት፡ኀያላን፡እነዚህ፡ናቸው፤የኢዮአብ፡ወንድም፡ዐሳሄል፥የቤተ፡ልሔሙ ፡ሰው፡የዱዲ፡ልጅ፡ኤልያናን፥
27፤ሃሮራዊው፡ሳሞት፥ፈሎናዊው፡ሴሌስ፥
28፤የቴቁሔ፡ሰው፡የዒስካ፡ልጅ፡ዒራስ፥
29፤ዓናቶታዊው፡አቢዔዜር፥ኩሳታዊው፡ሴቤካይ፥
30፤አሖሓዊው፡ዔላይ፥ነጦፋዊው፡ኖኤሬ፥የነጦፋዊው፡የበዓና፡ልጅ፡ሔሌድ፥
31፤ከብንያም፡ወገን፡ከግብዓ፡የሪባይ፡ልጅ፡ኤታይ፥
32፤ጲርዓቶናዊው፡በናያስ፥የገዓስ፡ወንዝ፡ሰው፡ኡሪ፥
33፤ዐረባዊው፡አቢኤል፥ባሕሩማዊው፡ዓዝሞት፥
34፤ሰዓልቦናዊው፡ኤሊያሕባ፥የጊዞናዊው፡የአሣን፡ልጆች፥የሃራራዊው፡የሻጌ፡ልጅ፡ዮናታን፥
35፤የአሮዳዊው፡የአራር፡ልጅ፡አምናን፥
36፤የኡር፡ልጅ፡ኤሊፋል፥ሚኬራታዊው፡ኦፌር፥
37፤ፍሎናዊው፡አኪያ፥ቀርሜሎሳዊው፡ሐጽሮ፥የኤዝባይ፡ልጅ፡ነዕራይ፥
38፤የናታንም፡ወንድም፡ኢዮኤል፥የሐግሪ፡ልጅ፡ሚብሐር፥
39፤አሞናዊው፡ጼሌቅ፥የጽሩያ፡ልጅ፡የኢዮአብ፡ጋሻ፡ዣግሬ፡ቤሮታዊው፡ነሃራይ፥
40፤ይትራዊው፡ዒራስ፥ይትራዊው፡ጋሬብ፥
41፤ኬጢያዊው፡ኦርዮ፥የአሕላይ፡ልጅ፡ዛባድ፥
42፤የሮቤላዊው፡የሺዛ፡ልጅ፡ዓዲና፥ርሱ፡የሮቤላውያን፡አለቃ፡ነበረ፥
43፤ከርሱም፡ጋራ፡ሠላሳ፡ሰዎች፡ነበሩ፥የማዕካ፡ልጅ፡ሐናን፥ሚትናዊው፡ኢዮሳፍጥ፥
44፤ዐስታሮታዊው፡ዖዝያ፥የአሮኤራዊው፡የኮታም፡ልጆች፡ሻማና፡ይዒኤል፥
45፤የሽምሪ፡ልጅ፡ይድኤል፥ወንድሙም፡ይድኤል፥ወንድሙም፡ቲዳዊው፡ዮሐ፥
46፤መሐዋዊው፡ኤሊኤል፥ይሪባይ፥ዮሻዊያ፥የኤልናዓም፡ልጆች፥ሞዐባዊው፡ይትማ፥
47፤ኤልኤል፥ዖቤድ፥ምጾባዊው፡የዕሢኤል።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡12።______________
ምዕራፍ፡12።
1፤በጺቅላግም፡ከቂስ፡ልጅ፡ከሳኦል፡በተሸሸገ፡ጊዜ፡ወደ፡ዳዊት፡የመጡ፡እነዚህ፡ናቸው፤በሰልፍም፡ባገዙት፡ኀ ያላን፡መካከል፡ነበሩ።
2፤ቀስተኛዎችም፡ነበሩ፥በቀኝና፡በግራም፡እጃቸው፡ድንጋይ፡ሊወነጭፉ፡ፍላጻም፡ሊወረውሩ፡ይችሉ፡ነበር፤ከብን ያም፡ወገን፡የሳኦል፡ወንድሞች፡ነበሩ።
3፤አለቃቸው፡አኂዔዝር፡ነበረ፥ከርሱም፡በዃላ፡ኢዮአስ፥የጊብዓዊው፡የሸማዓ፡ልጆች፤ይዝኤል፥ፋሌጥ፥የዓዝሞት ፡ልጆች፤በራኪያ፥ዓናቶታዊው፡ኢዩ፥
4፤ገባዖናዊው፡ሰማያስ፥ርሱ፡በሠላሳው፡መካከልና፡በሠላሳው፡ላይ፡ኀያል፡ሰው፡ነበረ፤ኤርምያስ፥የሕዚኤል፥ዮ ሐናን፥
5፤ገድሮታዊው፡ዮዛባት፥ኤሉዛይ፥ኢያሪሙት፥በዓልያ፥ሰማራያ፥ሐሩፋዊው፡ሰፋጥያስ፥
6፤ቆርያውያን፡ሕልቃና፥ይሺያ፥ዐዛርኤል፥ዮዛር፥ያሾቢአም፤
7፤የጌዶር፡ሰው፡የይሮሃም፡ልጆች፡የኤላ፥ዝባድያ፡
8፤ዳዊትም፡ከምድረ፡በዳ፡ውስጥ፡ባለችው፡በዐምባዪቱ፡ሳለ፡ከጋድ፡ወገን፡የኾኑ፡እነዚህ፡ጋሻና፡ጦር፡የሚይዙ ፥ጽኑዓን፡ኀያላን፥ሰልፈኛዎች፥ወደ፡ርሱ፡ተጠጉ፤ፊታቸውም፡እንደ፡አንበሳ፡ፊት፡ነበረ፥በተራራም፡ላይ፡እን ደሚዘል፟፡ሚዳቋ፡ፈጣኖች፡ነበሩ።
9፤አለቃው፡ዔጼር፥ኹለተኛው፡ዐብድዩ፥
10፤ሦስተኛው፡ኤልያብ፥አራተኛው፡መስመና፥
11፤ዐምስተኛው፡ኤርምያስ፥ስድስተኛው፡አታይ፥
12፤ሰባተኛው፡ኤሊኤል፥ስምንተኛው፡ዮሐናን፥
13፤ዘጠነኛው፡ኤልዛባድ፥ዐሥረኛው፡ኤርምያስ፥ዐሥራ፡አንደኛው፡መክበናይ።
14፤እነዚህ፡የጋድ፡ልጆች፡የጭፍራ፡አለቃዎች፡ነበሩ፤ከነርሱም፡ታናሹ፡ከመቶ፥ታላቁ፡ከሺሕ፡ይመዛዘኑ፡ነበር ።
15፤በመዠመሪያው፡ወር፡ዮርዳኖስ፡ከዳር፡እስከ፡ዳር፡ሞልቶ፡በነበረ፡ጊዜ፡የተሻገሩት፡እነዚህ፡ናቸው፤በሸለ ቆውም፡ውስጥ፡በምሥራቅና፡በምዕራብ፡በኩል፡የተቀመጡትን፡ዅሉ፡አባረሩ።
16፤ዳዊትም፡ወደነበረባት፡ወደ፡ዐምባዪቱ፡ከብንያምና፡ከይሁዳ፡ወገን፡ሰዎች፡መጡ።
17፤ዳዊትም፡ሊገናኛቸው፡ወጥቶ፦ትረዱኝ፡ዘንድ፡በሠላም፡ወደ፡እኔ፡መጥታችኹ፡እንደ፡ኾነ፡ልቤ፡ከእናንተ፡ጋ ራ፡አንድ፡ይኾናል፤ለጠላቶቼ፡አሳልፋችኹ፡ልትሰጡኝ፡መጥታችኹ፡እንደ፡ኾነ፡ግን፥በእጄ፡ዐመፅ፡የለብኝምና፡ የአባቶቻችን፡አምላክ፡ይመልከተው፥ይፍረደውም፡አላቸው።
18፤መንፈስም፡በሠላሳው፡አለቃ፡በአማሳይ፡ላይ፡መጣ፥ርሱም፦ዳዊት፡ሆይ፥እኛ፡የአንተ፡ነን፤የእሴል፡ልጅ፡ሆ ይ፥እኛ፡ከአንተ፡ጋራ፡ነን፤አምላክኽ፡ይረዳኻልና፥ሰላም፡ሰላም፡ለአንተ፡ይኹን፥ለሚረዱኽም፡ሰላም፡ይኹን፡ አለ።ዳዊትም፡ተቀበላቸው፥የጭፍራም፡አለቃዎች፡አደረጋቸው።
19፤ዳዊትም፡ከፍልስጥኤማውያን፡ጋራ፡ሳኦልን፡ሊወጋ፡በመጣ፡ጊዜ፡ከምናሴ፡ወገን፡ሰዎች፡ወደ፡ዳዊት፡ከዱ፤የ ፍልስጥኤማውያን፡አለቃዎች፡ግን፦በራሳችን፡ላይ፡ጕዳት፡አድርጎ፡ወደ፡ጌታው፡ወደ፡ሳኦል፡ይመለሳል፡ሲሉ፡ተ ማክረው፡ሰደ፟ውታልና፥እነርሱ፡አልረዷቸውም።
20፤ወደ፡ጺቅላግም፡ሲኼድ፡ከምናሴ፡ወገን፡የምናሴ፡ሻለቃዎች፡የነበሩ፡ዓድና፥ዮዛባት፥ይዲኤል፥ሚካኤል፥ዮዛ ባት፥ኤሊሁ፥ጺልታይ፡ወደ፡ርሱ፡ከዱ።
21፤ዅሉም፡ጽኑዓን፡ኀያላንና፡በሰራዊቱ፡ላይ፡አለቃዎች፡ነበሩና፥በአደጋ፡ጣዮቹ፡ላይ፡ዳዊትን፡አገዙት።
22፤እንደእግዚአብሔርም፡ሰራዊት፡ታላቅ፡ሰራዊት፡እስኪኾን፡ድረስ፡ዳዊትን፡ለመርዳት፡ዕለት፡ዕለት፡ይመጡ፡ ነበር።
23፤እንደእግዚአብሔርም፡ቃል፡የሳኦልን፡መንግሥት፡ወደ፡ርሱ፡ይመልሱ፡ዘንድ፡በኬብሮን፡ሳለ፡ወደ፡ዳዊት፡የ መጡት፡የሰራዊቱ፡አለቃዎች፡ቍጥር፡ይህ፡ነው።
24፤ጋሻና፡ጦር፡ተሸክመው፡ለሰልፍ፡የተዘጋጁ፡የይሁዳ፡ልጆች፡ስድስት፡ሺሕ፡ስምንት፡መቶ፡ነበሩ።
25፤ለሰልፍ፡ጽኑዓን፡ኀያላን፡ሰዎች፡የነበሩ፡የስምዖን፡ልጆች፡ሰባት፡ሺሕ፡አንድ፡መቶ፡ነበሩ።
26፤የሌዊ፡ልጆች፡አራት፡ሺሕ፡ስድስት፡መቶ፡ነበሩ።
27፤የአሮንም፡ቤት፡አለቃ፡ዮዳዔ፡ነበረ፥ከርሱም፡ጋራ፡ሦስት፡ሺሕ፡ሰባት፡መቶ፡ነበሩ፤
28፤ከርሱም፡ጋራ፡ጽኑዕ፡ኀያል፡ጕልማሳ፡ሳዶቅ፡ነበረ፥ከአባቱም፡ቤት፡ኻያ፡ኹለት፡አለቃዎች፡ነበሩ።
29፤የሳኦልም፡ወንድሞች፡ከኾኑ፡ከብንያም፡ወንድሞች፡የሚበልጠው፡ክፍል፡እስከዚያ፡ዘመን፡ድረስ፡የሳኦልን፡ ቤት፡ይከተል፡ነበርና፥ከነርሱ፡ዘንድ፡የመጡ፡ሦስት፡ሺሕ፡ነበሩ።
30፤ጽኑዓን፡ኀያላን፡የኾኑ፡በአባቶቻቸውም፡ቤት፡የታወቁ፡የኤፍሬም፡ልጆች፡ኻያ፡ሺሕ፡ስምንት፡መቶ፡ነበሩ።
31፤በየስማቸውም፡የተጻፉ፡ዳዊትን፡ያነግሡት፡ዘንድ፡የመጡ፡የምናሴ፡ነገድ፡እኩሌታ፡ዐሥራ፡ስምንት፡ሺሕ፡ነ በሩ።
32፤እስራኤልም፡የሚገ፟ባ፟ውን፡ያደርግ፡ዘንድ፡ዘመኑን፡የሚያውቁ፡ጥበበኛዎች፡ሰዎች፡የይሳኮር፡ልጆች፡አለ ቃዎች፡ኹለት፡መቶ፡ነበሩ፤ወንድሞቻቸውም፡ዅሉ፡ይታዘዟቸው፡ነበር።
33፤በጭፍራውም፡ውስጥ፡የወጡ፡ለሰልፍም፡የተዘጋጁ፥የማያመነቱ፥መሣሪያም፡ዅሉ፡የያዙ፡የዛብሎን፡ሰዎች፡ዐም ሳ፡ሺሕ፡ነበሩ።
34፤የንፍታሌምም፡አለቃዎች፡አንድ፡ሺሕ፡ነበሩ፥ከነርሱም፡ጋራ፡ጋሻና፡ጦር፡የሚይዙ፡ሠላሳ፡ሰባት፡ሺሕ፡ነበ ሩ።
35፤ለሰልፍም፡የተዘጋጁ፡የዳን፡ሰዎች፡ኻያ፡ስምንት፡ሺሕ፡ስድስት፡መቶ፡ነበሩ።
36፤በጭፍራውም፡ውስጥ፡የሚወጡ፥ለሰልፍም፡የተዘጋጁ፡የአሴር፡ሰዎች፡አርባ፡ሺሕ፡ነበሩ።
37፤በዮርዳኖስም፡ማዶ፡ካሉ፡ከሮቤልና፡ከጋድ፡ሰዎች፡ከምናሴም፡ነገድ፡እኩሌታ፡መሣሪያን፡ዅሉ፡ይዘው፡የመጡ ፡መቶ፡ኻያ፡ሺሕ፡ነበሩ።
38፤እነዚህ፡ዅሉ፡ዳዊትን፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ላይ፡ያነግሡት፡ዘንድ፡ዐርበኛዎችና፡ሰልፈኛዎች፡እየኾኑ፡በፍጹ ም፡ልባቸው፡ወደ፡ኬብሮን፡መጡ፤ደግሞም፡ከእስራኤል፡የቀሩት፡ዅሉ፡ዳዊትን፡ያነግሡት፡ዘንድ፡አንድ፡ልብ፡ነ በሩ።
39፤ወንድሞቻቸውም፡አዘጋጅተውላቸው፡ነበርና፥እየበሉና፡እየጠጡ፡በዚያ፡ከዳዊት፡ጋራ፡ሦስት፡ቀን፡ተቀመጡ።
40፤ደግሞም፡በእስራኤል፡ዘንድ፡ደስታ፡ኾኗልና፥እስከ፡ይሳኮርና፡እስከ፡ዛብሎን፡እስከ፡ንፍታሌምም፡ድረስ፡ ለርሱ፡አቅራቢያ፡የነበሩ፡በአህያና፡በግመል፡በበቅሎና፡በበሬ፡ላይ፡እንጀራና፡ዱቄት፡የበለስ፡ጥፍጥፍና፡የ ዘቢበ፡ዘለላ፡የወይንም፡ጠጅ፡ዘይትም፡በሬዎችንና፡በጎችንም፡በብዙ፡አድርገው፡ያመጡ፡ነበር።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡13።______________
ምዕራፍ፡13።
1፤ዳዊትም፡ከሻለቃዎችና፡ከመቶ፡አለቃዎች፡ከአለቃዎቹም፡ዅሉ፡ጋራ፡ተማከረ።
2፤ዳዊትም፡የእስራኤልን፡ጉባኤ፡ዅሉ፦መልካም፡መስሎ፡የታያችኹ፡እንደ፡ኾነ፥ከአምላካችን፡ከእግዚአብሔርም፡ ወጥቶ፡እንደ፡ኾነ፥በእስራኤል፡አገር፡ዅሉ፡ለቀሩት፡ወንድሞቻችን፡በከተማዎቻቸውና፡በመሰምሪያዎቻቸውም፡ለ ሚቀመጡ፡ካህናትና፡ሌዋውያን፡ወደ፡እኛ፡ይሰበሰቡ፡ዘንድ፡እንላክ፤
3፤በሳኦልም፡ዘመን፡አልፈለግነውምና፡የአምላካችንን፡ታቦት፡ወደ፡እኛ፡እንመልስ፡አላቸው።
4፤ነገሩም፡በሕዝቡ፡ዅሉ፡ዐይን፡ዘንድ፡ቅን፡ነበረና፡ጉባኤው፡ዅሉ፦እንዲሁ፡እናደርጋለን፡አሉ።
5፤የእግዚአብሔርንም፡ታቦት፡ከቂርያትይዓሪም፡ያመጡ፡ዘንድ፡ዳዊት፡እስራኤልን፡ዅሉ፡ከግብጽ፡ወንዝ፡ከሺሖር ፡ዠምሮ፡እስከሐማት፡መግቢያ፡ድረስ፡ሰበሰበ።
6፤ዳዊትም፡እስራኤልም፡ዅሉ፡በኪሩቤል፡ላይ፡የተቀመጠውን፡ስሙም፡በርሱ፡የተጠራውን፡የአምላክን፡የእግዚአብ ሔርን፡ታቦት፡ከዚያ፡ያወጡ፡ዘንድ፡በይሁዳ፡ወዳለችው፡ቂርያትይዓሪም፡ወደተባለች፡ወደ፡በዓላ፡ኼዱ።
7፤የእግዚአብሔርንም፡ታቦት፡በዐዲስ፡ሠረገላ፡ላይ፡ጫኑት፥ከዐሚናዳብም፡ቤት፡አመጡት፤ዖዛና፡አኂዮም፡ሠረገ ላውን፡ይነዱ፡ነበር።
8፤ዳዊትና፡እስራኤል፡ዅሉ፡በቅኔና፡በበገና፡በመሰንቆና፡በከበሮ፡በጸናጽልና፡በመለከት፡በእግዚአብሔር፡ፊት ፡በሙሉ፡ኀይላቸው፡ይጫወቱ፡ነበር።
9፤ወደኪዶንም፡ዐውድማ፡በደረሱ፡ጊዜ፡በሬዎቹ፡ይፋንኑ፡ነበርና፥ታቦቱን፡ሊይዝ፡ዖዛ፡እጁን፡ዘረጋ።
10፤የእግዚአብሔርም፡ቍጣ፡በዖዛ፡ላይ፡ነደደ፥እጁንም፡ወደ፡ታቦቱ፡ስለ፡ዘረጋ፡ቀሠፈው፤በዚያም፡በእግዚአብ ሔር፡ፊት፡ሞተ።
11፤እግዚአብሔርም፡ዖዛን፡ስለ፡ቀሠፈው፡ዳዊት፡ዐዘነ፤እስከ፡ዛሬም፡ድረስ፡የዚያን፡ስፍራ፡ስም፡የዖዛ፡ስብ ራት፡ብሎ፡ጠራው።
12፤በዚያም፡ቀን፡ዳዊት፦የእግዚአብሔርን፡ታቦት፡ወደ፡እኔ፡እንዴት፡አመጣለኹ፡ብሎ፡እግዚአብሔርን፡ፈራ።
13፤ዳዊትም፡ታቦቱን፡ወደጌት፡ሰው፡ወደአቢዳራ፡ቤት፡አሳለፈው፡እንጂ፡ወደ፡ርሱ፡ወደዳዊት፡ከተማ፡አላመጣው ም።
14፤የእግዚአብሔርም፡ታቦት፡በአቢዳራ፡ቤተ፡ሰብ፡ዘንድ፡በቤቱ፡ውስጥ፡ሦስት፡ወር፡ተቀመጠ፤እግዚአብሔርም፡ የአቢዳራን፡ቤትና፡ያለውን፡ዅሉ፡ባረከ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡14።______________
ምዕራፍ፡14።
1፤የጢሮስም፡ንጉሥ፡ኪራም፡ቤት፡ይሠሩለት፡ዘንድ፡መልእክተኛዎችን፡የዝግባ፡ዕንጨትንም፡ጠራቢዎችንም፡ዐናጢ ዎችንም፡ወደ፡ዳዊት፡ላከ።
2፤ስለ፡ሕዝቡም፡ስለ፡እስራኤል፡መንግሥቱ፡ከፍ፡ብሏልና፥እግዚአብሔር፡በእስራኤል፡ላይ፡ንጉሥ፡አድርጎ፡እን ዳጸናው፡ዳዊት፡ዐወቀ።
3፤ዳዊትም፡በኢየሩሳሌም፡ሚስቶችን፡ጨምሮ፡ሌላዎችን፡ወንዶችንና፡ሴቶችን፡ልጆች፡ወለደ።
4፤በኢየሩሳሌምም፡የወለዳቸው፡የልጆቹ፡ስም፡ይህ፡ነው፤ሳሙስ፥
5፤ሶባብ፥ናታን፥ሰሎሞን፥ኢያቤሐር፥ኤሊሱዔ፥
6፤ኤሊፋላት፥ኖጋ፥ናፌቅ፥ያፍያ፥
7፤ኤሊሳማ፥ኤሊዳሄ፥ኤሊፋላት።
8፤ፍልስጥኤማውያንም፡ዳዊት፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ላይ፡ንጉሥ፡ኾኖ፡አንደ፡ተቀባ፡ሰሙ፥ፍልስጥኤማውያንም፡ዅሉ፡ ዳዊትን፡ሊፈልጉ፡ወጡ፤ዳዊትም፡በሰማ፡ጊዜ፡ሊጋጠማቸው፡ወጣ።
9፤ፍልስጥኤማውያንም፡መጥተው፡በራፋይም፡ሸለቆ፡አደጋ፡ጣሉ።
10፤ዳዊትም፦ወደ፡ፍልስጥኤማውያን፡ልውጣን፧በእጄስ፡አሳልፈኽ፡ትሰጣቸዋለኽን፧ብሎ፡እግዚአብሔርን፡ጠየቀ። እግዚአብሔርም፦በእጅኽ፡አሳልፌ፡እሰጣቸዋለኹና፡ውጣ፡አለው።
11፤ወደ፡በአልፐራሲም፡ወጡ፥በዚያም፡ዳዊት፡መታቸው።ዳዊትም፦ውሃ፡እንዲያፈርስ፡እግዚአብሔር፡ጠላቶቼን፡በ እጄ፡አፈረሳቸው፡አለ።ስለዚህም፡የዚያን፡ስፍራ፡ስም፡በአልፐራሲም፡ብለው፡ጠሩት።
12፤አማልክታቸውንም፡በዚያ፡ተዉ፤ዳዊትም፡አዘዘ፥በእሳትም፡አቃጠሏቸው።
13፤ፍልስጥኤማውያንም፡ደግሞ፡በሸለቆው፡አደጋ፡ጣሉ።
14፤ዳዊትም፡እንደ፡ገና፡እግዚአብሔርን፡ጠየቀ፤እግዚአብሔርም፦ከነርሱ፡ዞረኽ፡በሾላው፡ዛፍ፡ፊት፡ለፊት፡ግ ጠማቸው፡እንጂ፡ወደ፡እነርሱ፡አትውጣ።
15፤በሾላውም፡ዛፍ፡ራስ፡ውስጥ፡የሽውሽውታ፡ድምፅ፡ስትሰማ፡የፍልስጥኤማውያንን፡ጭፍራ፡ሊመታ፡እግዚአብሔር ፡በፊትኽ፡ይወጣልና፥በዚያን፡ጊዜ፡ወደ፡ሰልፍ፡ውጣ፡አለው።
16፤ዳዊትም፡እግዚአብሔር፡እንዳዘዘው፡አደረገ፤ከገባዖንም፡ዠምሮ፡እስከ፡ጌዝር፡ድረስ፡የፍልስጥኤማውያንን ፡ጭፍራ፡መቱት።
17፤የዳዊትም፡ዝና፡በያገሩ፡ዅሉ፡ወጣ፤መፈራቱንም፡እግዚአብሔር፡በአሕዛብ፡ዅሉ፡ዘንድ፡አደረገው።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡15።______________
ምዕራፍ፡15።
1፤ዳዊትም፡በከተማው፡ላይ፡ለራሱ፡ቤቶችን፡ሠራ፤ለእግዚአብሔርም፡ታቦት፡ስፍራ፡አዘጋጀ፥ድንኳንም፡ተከለለት ።
2፤በዚያን፡ጊዜም፡ዳዊት።የእግዚአብሔርን፡ታቦት፡ይሸከሙ፡ዘንድ፥ለዘለዓለሙም፡ያገለግሉት፡ዘንድ፡እግዚአብ ሔር፡ከመረጣቸው፡ከሌዋውያን፡በቀር፡ማንም፡የእግዚአብሔርን፡ታቦት፡ይሸከም፡ዘንድ፡አይገ፟ባ፟ውም፡አለ።
3፤ዳዊትም፡ወዳዘጋጀለት፡ስፍራ፡የእግዚአብሔርን፡ታቦት፡ያመጣ፡ዘንድ፡እስራኤልን፡ዅሉ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ሰ በሰበ።
4፤ዳዊትም፡የአሮንን፡ልጆችና፡ሌዋውያንን፡ሰበሰበ።
5፤ከቀአት፡ልጆች፤አለቃው፡ኡርኤል፥ወንድሞቹም፡መቶ፡ኻያ፤
6፤ከሜራሪ፡ልጆች፤አለቃው፡ዐሳያ፥ወንድሞቹም፡ኹለት፡መቶ፡ኻያ፤
7፤ከጌድሶን፡ልጆች፤አለቃው፡ኢዮኤል፥ወንድሞቹም፡መቶ፡ሠላሳ፤
8፤ከኤሊጻፋን፡ልጆች፤አለቃው፡ሸማያ፥ወንድሞቹም፡ኹለት፡መቶ፤
9፤ከኬብሮን፡ልጆች፤አለቃው፡ኤሊኤል፥ወንድሞቹም፡ሰማንያ፤
10፤ከዑዝኤል፡ልጆች፤አለቃው፡ዐሚናዳብ፥ወንድሞቹም፡መቶ፡ዐሥራ፡ኹለት።
11፤ዳዊትም፡ካህናቱን፡ሳዶቅንና፡አቢያታርን፥ሌዋውያንንም፡ኡርኤልን፥ዐሳያን፥ኢዮኤልን፥ሸማያን፥ኤሊኤልን ፥ዐሚናዳብንም፡ጠርቶ፦
12፤እናንተ፡የሌዋውያን፡አባቶች፡ቤቶች፡አለቃዎች፡ናችኹ፤ወዳዘጋጀኹለት፡ስፍራ፡የእስራኤልን፡አምላክ፡የእ ግዚአብሔርን፡ታቦት፡ታመጡ፡ዘንድ፡እናንተና፡ወንድሞቻችኹ፡ተቀደሱ።
13፤ቀድሞም፡አልተሸከማችኹምና፥እንደ፡ሥርዐቱም፡አልፈለግነውምና፡አምላካችን፡እግዚአብሔር፡በመካከላችን፡ ስብራት፡አደረገ፡አላቸው።
14፤የእስራኤልንም፡አምላክ፡የእግዚአብሔርን፡ታቦት፡ያመጡ፡ዘንድ፡ካህናቱና፡ሌዋውያኑ፡ተቀደሱ።
15፤ሙሴም፡እንዳዘዘው፡እንደእግዚአብሔር፡ቃል፡የሌዋውያን፡ልጆች፡የእግዚአብሔርን፡ታቦት፡በትከሻቸው፡ላይ ፡በመሎጊያዎቹ፡ተሸከሙ።
16፤ዳዊትም፡በዜማ፡ዕቃ፡በመሰንቆና፡በበገና፡በጸናጽልም፡እንዲያዜሙ፥ድምፃቸውንም፡በደስታ፡ከፍ፡እንዲያደ ርጉ፡መዘምራኑን፡ወንድሞቻቸውን፡ይሾሙ፡ዘንድ፡ለሌዋውያን፡አለቃዎች፡ተናገረ።
17፤ሌዋውያኑም፡የኢዮኤልን፡ልጅ፡ኤማንን፥ከወንድሞቹም፡የበራክያን፡ልጅ፡አሣፍን፥ከወንድሞቻቸውም፡ከሜራሪ ፡ልጆች፡የቂሳን፡ልጅ፡ኤታንን፥
18፤ከነርሱም፡ጋራ፡በኹለተኛው፡ተራ፡የኾኑትን፡ወንድሞቻቸውን፡ዘካርያስን፥ቤንን፥ያዝኤልን፥ሰሚራሞትን፥ይ ሒኤልን፥ዑኒን፥ኤልያብን፥በናያስን፥መዕሴያን፥መቲትያን፥ኤሊፍሌሁን፥ሚቅንያን፥በረኛዎችንም፡ዖቤድኤዶምን ና፡ይዒኤልን፡አቆሙ።
19፤መዘምራንም፡ኤማንና፡አሣፍ፡ኤታንም፡በናስ፡ጸናጽል፡ከፍ፡አድርገው፡ያሰሙ፡ነበር።
20፤ዘካርያስ፥ዓዝዔል፥ሰሚራሞት፥ይሒኤል፥ዑኒ፥ኤልያብ፥መዕሴያ፥በናያስ፡በመሰንቆ፡ምስጢር፡ነገር፡ያዜሙ፡ ነበር።
21፤መቲትያ፥ኤልፍሌሁ፥ሚቅኒያ፥ዖቤድኤዶም፥ይዒኤል፥ዓዛዝያ፡ስምንት፡አውታር፡ባለው፡በገና፡ይዘምሩ፡ነበር ።
22፤የሌዋውያኑም፡አለቃ፡ክናንያ፡በዜማ፡ላይ፡ተሹሞ፡ነበር።ብልኀተኛ፡ነበረና፡ዜማ፡ያስተምራቸው፡ነበር።
23፤በራክያና፡ሕልቃናም፡ለታቦቱ፡በረኛዎች፡ነበሩ።
24፤ካህናቱም፡ሰበንያ፥ኢዮሳፍጥ፥ናትናኤል፥ዐማሳይ፥ዘካርያስ፥በናያስ፥አልዓዛር፡በእግዚአብሔር፡ታቦይ፡ፊ ት፡መለከት፡ይነፉ፡ነበር።ዖቤድኤዶምና፡ይሒያም፡ለታቦቱ፡በረኛዎች፡ነበሩ።
25፤ዳዊትም፥የእስራኤልም፡ሽማግሌዎች፥የሻለቃዎችም፡የእግዚአብሔርን፡የቃል፡ኪዳኑን፡ታቦት፡ከአቢዳራ፡ቤት ፡በደስታ፡ያመጡ፡ዘንድ፡ኼዱ።
26፤የእግዚአብሔርንም፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡የተሸከሙትን፡ሌዋውያንን፡እግዚአብሔር፡በረዳቸው፡ጊዜ፡ሰባት፡በ ሬዎችና፡ሰባት፡አውራ፡በጎች፡ሠዉ።
27፤ዳዊትም፥ታቦቱንም፡የተሸከሙ፡ሌዋውያን፡ዅሉ፥መዘምራኑም፥የመዘምራኑም፡አለቃ፡ከናንያ፡የጥሩ፡በፍታ፡ቀ ሚስ፡ለብሰው፡ነበር፤ዳዊትም፡የበፍታ፡ኤፉድ፡ነበረው።
28፤እንዲሁ፡እስራኤል፡ዅሉ፡ሆ፡እያሉ፡ቀንደ፡መለከትና፡እንቢልታ፡እየነፉ፥ጸናጽልና፡መሰንቆም፡በገናም፡እ የመቱ፥የእግዚአብሔርን፡የቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡አመጡ።
29፤የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡ወደዳዊት፡ከተማ፡በደረሰ፡ጊዜ፡የሳኦል፡ልጅ፡ሜልኮል፡በመስኮት፡ኾ ና፡ተመለከተች፤ንጉሡም፡ዳዊት፡ሲዘፍንና፡ሲጫወት፡አይታ፡በልቧ፡ናቀችው።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡16።______________
ምዕራፍ፡16።
1፤የእግዚአብሔርንም፡ታቦት፡ይዘው፡ገቡ፥ዳዊትም፡በተከለለት፡ድንኳን፡ውስጥ፡አኖሩት፤የሚቃጠለውን፡መሥዋዕ ትና፡የደኅንነቱን፡መሥዋዕትም፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡አቀረቡ።
2፤ዳዊትም፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕትና፡የደኅንነቱን፡መሥዋዕት፡ማቅረብ፡በፈጸመ፡ጊዜ፡በእግዚአብሔር፡ስም፡ሕ ዝቡን፡ባረከ።
3፤ለእስራኤልም፡ለወንዱም፡ለሴቱም፡ለያንዳንዱ፡አንዳንድ፡እንጀራ፤አንዳንድም፡ቍራጭ፡ሥጋ፥አንዳንድም፡የዘ ቢብ፡ጥፍጥፍ፡አካፈለ።
4፤በእግዚአብሔርም፡ታቦት፡ፊት፡ያገለግሉ፡ዘንድ፥የእስራኤልንም፡አምላክ፡እግዚአብሔርን፡ይወድሱት፡ዘንድ፥ ያመሰግኑትና፡ያከብሩትም፡ዘንድ፡ከሌዋውያን፡ወገን፡አቆመ።
5፤አለቃው፡አሣፍ፡ነበረ፤ከርሱም፡በዃላ፡ዘካርያስ፥ይዒኤል፥ሰሚራሞት፥ይሒኤል፥መቲትያ፥ኤልያብ፥በናያስ፥ዖ ቤድኤዶም፥ይዒኤል፡በመሰንቆና፡በበገና፡አሣፍም፡በጸናጽል፡ይዘምሩ፡ነበር።
6፤ካህናቱም፡በናያስና፡የሕዚኤል፡በእግዚአብሔር፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡ፊት፡ዅልጊዜ፡መለከት፡ይነፉ፡ነበር።
7፤በዚያም፡ቀን፡ዳዊት፡በአሣፍና፡በወንድሞቹ፡እጅ፡እግዚአብሔርን፡እንዲያመሰግኑ፡ትእዛዝን፡ሰጠ።
8፤እግዚአብሔርን፡አመስግኑ፥ስሙን፡ጥሩ፤ለአሕዛብ፡ሥራውን፡አውሩ።
9፤ተቀኙለት፥ዘምሩለት፤ተኣምራቱንም፡ዅሉ፡ተናገሩ።
10፤በቅዱስ፡ስሙ፡ተጓደዱ፤እግዚአብሔርን፡የሚፈልግ፡ልብ፡ደስ፡ይበለው።
11፤እግዚአብሔርን፡ፈልጉት፥ትጸናላችኹም፤ዅልጊዜ፡ፊቱን፡ፈልጉ።
12፤13፤ባሪያዎቹ፡የእስራኤል፡ዘር፥ለርሱም፡የተመረጣችኹ፡የያዕቆብ፡ልጆች፡ሆይ፥የሠራትን፡ድንቅ፡ዐስቡ፥ተ ኣምራቱንም፡የአፉንም፡ፍርድ።
14፤ርሱ፡እግዚአብሔር፡አምላካችን፡ነው፤ፍርዱ፡በምድር፡ዅሉ፡ነው።ቃል፡ኪዳኑን፡ለዘለዓለም፥እስከ፡ሺሕ፡ት ውልድ፡ያዘዘውን፡ቃሉን፡ዐሰበ፥
16፤ለአብርሃም፡ያደረገውን፥ለይሥሐቅም፡የማለውን፤
17፤ለያዕቆብ፡ሥርዐት፡እንዲኾን፡ለእስራኤልም፡የዘለዓለም፡ኪዳን፡እንዲኾን፡አጸና፤
18፤እንዲህም፡አለ፦ለአንተ፡የከነዓንን፡ምድር፡የርስታችኹን፡ገመድ፡እሰጣለኹ፤
19፤ይህም፡የኾነው፡እነርሱ፡በቍጥር፡ጥቂቶች፡ሰዎች፥እጅግ፡ጥቂቶችና፡ስደተኛዎች፡ሲኾኑ፡ነው።
20፤ከሕዝብ፡ወደ፡ሕዝብ፥ከመንግሥትም፡ወደ፡ሌላ፡ሕዝብ፡ዐለፉ።
21፤22፤የቀባዃቸውን፡አትዳስሱ፥በነቢያቴም፡ክፉ፡አታድርጉ፡ብሎ፥ሰው፡ግፍ፡ያደርግባቸው፡ዘንድ፡አልፈቀደም ፤ስለ፡እነርሱም፡ነገሥታትን፡ገሠጸ።
23፤ምድር፡ዅሉ፡እግዚአብሔርን፡አመስግኑ፤ዕለት፡ዕለት፡ማዳኑን፡አውሩ።
24፤ክብሩን፡ለአሕዛብ፥ተኣምራቱንም፡ለወገኖች፡ዅሉ፡ንገሩ።
25፤እግዚአብሔር፡ታላቅ፥ምስጋናውም፡ብዙ፡ነውና፤በአማልክትም፡ዅሉ፡ላይ፡የተፈራ፡ነው።
26፤የአሕዛብ፡አማልክት፡ዅሉ፡ጣዖታት፡ናቸው፤እግዚአብሔር፡ግን፡ሰማያትን፡ሠራ።
27፤ክብርና፡ግርማ፡በፊቱ፥ኀይልና፡ደስታ፡በስፍራው፡ውስጥ፡ናቸው።
28፤የአሕዛብ፡ወገኖች፡ለእግዚአብሔር፡አምጡ፥ክብርንና፡ኀይልን፡ለእግዚአብሔር፡አምጡ።
29፤ለስሙ፡የሚገ፟ባ፟፡ክብርን፡ለእግዚአብሔር፡አምጡ፤ቍርባንን፡ይዛችኹ፡በፊቱ፡ግቡ፤በቅድስናው፡ስፍራ፡ለ እግዚአብሔር፡ስገዱ።
30፤ምድር፡ዅሉ፡በፊቱ፡ትነዋወጥ፤ዓለሙም፡እንዳይናወጥ፡ጸንቷል።
31፤ሰማያት፡ደስ፡ይበላቸው፥ምድርም፡ሐሴትን፡ታድርግ፤በአሕዛብም፡መካከል።እግዚአብሔር፡ነገሠ፡በሉ።
32፤ባሕርና፡ሞላዋ፡ትናወጥ፤በረሓ፡በርሷም፡ያሉ፡ዅሉ፡ሐሤትን፡ያድርጉ።
33፤በምድር፡ሊፈርድ፡ይመጣልና፥የዱር፡ዛፎች፡በዚያን፡ጊዜ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ደስ፡ይላቸዋል።
34፤ቸር፡ነውና፥ምሕረቱም፡ለዘለዓለም፡ነውና፥እግዚአብሔርን፡አመስግኑ።
35፤የመዳናችን፡አምላክ፡ሆይ፥አድነን፤ቅዱስ፡ስምኽን፡እናመሰግን፡ዘንድ፥በምስጋናኽም፡እንመካ፡ዘንድ፥ከአ ሕዛብ፡ሰብስበኽ፡ታደገን፡በሉ።
36፤ከዘለዓለም፡እስከ፡ዘለዓለም፥የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡ይባረክ።ሕዝቡም፡ዅሉ፡አሜን፡ይበሉ፤እ ግዚአብሔርንም፡ያመስግኑ።
37፤እንዲሁም፡በየቀኑ፡እንደሚገ፟ባ፟ቸው፡በታቦቱ፡ፊት፡ዘወትር፡ያገለግሉ፡ዘንድ፡አሣፍንና፡ወንድሞቹን፥ዖ ቤድኤዶምንም፥ስድሳ፡ስምንቱንም፡ወንድሞቻቸውን፡በዚያ፡በእግዚአብሔር፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡ፊት፡ተዋቸው።
38፤የኤዶታምም፡ልጅ፡ዖቤድኤዶምና፡ሖሳ፡በረኛዎች፡ይኾኑ፡ዘንድ፡ተዋቸው።
39፤ካህኑም፡ሳዶቅንና፡ካህናቱን፡ወንድሞቹን፡በገባዖን፡በኰረብታው፡መስገጃ፡ባለው፡በእግዚአብሔር፡ማደሪያ ፡ፊት፡አቆማቸው፥
40፤ለእስራኤልም፡ባዘዘው፡በእግዚአብሔር፡ሕግ፡እንደ፡ተጻፈ፡ዅሉ፡ለሚቃጠለው፡መሥዋዕት፡በሚኾነው፡መሠዊያ ፡ላይ፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፡ዅል፡ጊዜ፡ጧትና፡ማታ፡ለእግዚአብሔር፡ያቀርቡ፡ዘንድ።
41፤ምሕረቱም፡ለዘለዓለም፡ነውና፥እግዚአብሔርን፡ያመሰግኑ፡ዘንድ፡ኤማንንና፡ኤዶታምን፥በስማቸውም፡የተጻፉ ትን፡ተመርጠው፡የቀሩትን፡ከነርሱ፡ጋራ፡አቆመ።
42፤ከነርሱም፡ጋራ፡ካህናቱ፡ከፍ፡አድርገው፡ለማሰማት፡መለከትና፡ጸናጽል፡ለእግዚአብሔርም፡መዝሙራት፡የዜማ ፡ዕቃ፡ይዘው፡ነበር፤የኤዶታምም፡ልጆች፡በረኛዎች፡ነበሩ።
43፤ሕዝቡ፡ዅሉ፡እያንዳንዱ፡ወደ፡ቤቱ፡ኼደ፤ዳዊትም፡ቤቱን፡ይባርክ፡ዘንድ፡ተመለሰ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡17።______________
ምዕራፍ፡17።
1፤እንዲህም፡ኾነ፤ዳዊት፡በቤቱ፡በተቀመጠ፡ጊዜ፡ዳዊት፡ነቢዩን፡ናታንን፦እንሆ፥እኔ፡ከዝግባ፡በተሠራ፡ቤት፡ ተቀምጫለኹ፤የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡በመጋረጃዎች፡ውስጥ፡ተቀምጧል፡አለው።
2፤ናታንም፡ዳዊትን፦እግዚአብሔር፡ከአንተ፡ጋራ፡ነውና፥በልብኽ፡ያለውን፡ዅሉ፡አድርግ፡አለው።
3፤በዚያም፡ሌሊት፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ወደ፡ናታን፡መጣ፡እንዲህም፡አለው፦
4፤5፤ኺድ፥ለባሪያዬ፡ለዳዊት፡ንገረው፦እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እስራኤልን፡ካወጣኹበት፡ቀን፡ዠምሮ፡እ ስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡ከድንኳን፡ወደ፡ድንኳን፥ከማደሪያም፡ወደ፡ማደሪያ፡እኼድ፡ነበር፡እንጂ፡በቤት፡ውስጥ፡አል ኖርኹምና፡የምኖርበትን፡ቤት፡አትሠራልኝም።
6፤ከእስራኤል፡ዅሉ፡ጋራ፡ባለፍኹበት፡ስፍራ፡ዅሉ፦ስለ፡ምን፡ቤትን፡ከዝግባ፡ዕንጨት፡አልሠራችኹልኝም፧ብዬ፡ ሕዝቤን፡ይጠብቅ፡ዘንድ፡ከእስራኤል፡ፈራጆች፡ላዘዝኹት፡ለአንዱ፡በእውኑ፡ተናግሬያለኹን፧
7፤አኹንም፡ባሪያዬን፡ዳዊትን፡እንዲህ፡በለው፦የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦አንተ፡መንጋውን ፡ስትከተል፡በሕዝቤ፡በእስራኤል፡ላይ፡አለቃ፡ትኾን፡ዘንድ፡ከበግ፡ጥበቃ፡ወሰድኹኽ።
8፤በኼድኽበትም፡ዅሉ፡ከአንተ፡ጋራ፡ነበርኹ፥ጠላቶችኽንም፡ዅሉ፡ከፊትኽ፡አጠፋኹ፤በምድርም፡ላይ፡እንዳሉ፡እ ንደታላላቆች፡ስም፡ለአንተ፡ስም፡አደርጋለኹ።
9፤10፤ለሕዝቤም፡ለእስራኤል፡ስፍራ፡አደርግለታለኹ፥እተክለውማለኹ፥በስፍራውም፡ይቀመጣል፥ከዚያም፡በዃላ፡ አይናወጥም፤እንደቀድሞው፡ዘመንና፡በሕዝቤም፡በእስራኤል፡ላይ፡ፈራጆች፡እንዳስነሣኹበት፡ጊዜ፡ግፈኛዎች፡ተ መልሰው፡አያስጨንቁትም፤ጠላቶችኽንም፡ዅሉ፡አዋርዳቸዋለኹ።እግዚአብሔር፡ደግሞ፡ቤት፡እንዲሠራልኽ፡እነግር ኻለኹ።
11፤ወደ፡አባቶችኽም፡ትኼድ፡ዘንድ፡ዕድሜኽ፡በተፈጸመ፡ጊዜ፡ከልጆችኽ፡የሚኾነውን፡ዘርኽን፡ከአንተ፡በዃላ፡ አስነሣለኹ፤መንግሥቱንም፡አጸናለኹ።
12፤ርሱ፡ቤት፡ይሠራልኛል፤ዙፋኑንም፡ለዘለዓለም፡አጸናለኹ።
13፤እኔም፡አባት፡እኾነዋለኹ፥ርሱም፡ልጅ፡ይኾነኛል፤ከአንተ፡አስቀድሞ፡ከነበረው፡እንዳራቅኹ፥ምሕረቴን፡ከ ርሱ፡አላርቅም።
14፤በቤቴና፡በመንግሥቴም፡ለዘለዓለም፡አቆመዋለኹ፤ዙፋኑም፡ለዘለዓለም፡ይጸናል።
15፤እንደዚህ፡ነገር፡ዅሉ፡እንደዚህም፡ራእይ፡ዅሉ፡ናታን፡ለዳዊት፡ነገረው።
16፤ንጉሡም፡ዳዊት፡ገባ፥በእግዚአብሔርም፡ፊት፡ተቀምጦ፡እንዲህ፡አለ፦አቤቱ፡አምላክ፡ሆይ፥እስከዚህ፡ያደረ ስኸኝ፡እኔ፡ማን፡ነኝ፧ቤቴስ፡ምንድር፡ነው፧
17፤አምላክ፡ሆይ፡ይህ፡በፊትኽ፡ጥቂት፡ነበረ፤አቤቱ፡አምላክ፡ሆይ፥ስለ፡ባሪያኽ፡ቤት፡ደግሞ፡ለሩቅ፡ዘመን፡ ተናገርኽ፤እንደ፡አንድ፡ባለማዕርግ፡ሰው፡ተመለከትኸኝ።
18፤አንተ፡ባሪያኽን፡ታውቀዋለኽና፡ለባሪያኽ፡ስለ፡ተደረገ፡ክብር፡ዳዊት፡ጨምሮ፡የሚለው፡ምንድር፡ነው፧
19፤አቤቱ፥ይህን፡ታላቅ፡ነገር፡ዅሉ፡ታስታውቀው፡ዘንድ፡ስለ፡ባሪያኽ፡እንደ፡ልብኽም፡ይህን፡ተኣምራት፡ዅሉ ፡አድርገኻል።
20፤አቤቱ፥እንዳንተ፡ያለ፡የለም፥በዦሯችንም፡እንደ፡ሰማን፡ዅሉ፡ከአንተ፡በቀር፡አምላክ፡የለም።
21፤አንተ፡እግዚአብሔር፡ከግብጽ፡ካወጣኸው፡ከሕዝብኽ፡ፊት፡አሕዛብን፡በማሳደድ፡በታላቅና፡በሚያስፈራ፡ነገ ር፡ለአንተ፡ስም፡ታደርግ፡ዘንድ፥ለአንተም፡ሕዝብ፡ትቤዥ፡ዘንድ፡እንደኼድኽለት፡እንዳንተ፡ሕዝብ፡እንደ፡እ ስራኤል፡ያለ፡በምድር፡ላይ፡ሌላ፡ሕዝብ፡አለን፧
22፤ሕዝብኽንም፡እስራኤልን፡ለዘለዓለም፡ሕዝብኽ፡አደረግኸው፤አንተም፥አቤቱ፥አምላክ፡ኾነኸዋል።
23፤አኹንም፥አቤቱ፥ስለ፡ባሪያኽና፡ስለ፡ቤቱ፡የተናገርኸው፡ለዘለዓለም፡የጸና፡ይኹን፤አንደ፡ተናገርኽም፡አ ድርግ።
24፤የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡ርሱ፡የእስራኤል፡አምላክ፡ነው፥በእውነት፡የእስራኤል፡አምላክ፡ነው፡ይባል ፡ዘንድ፡ስምኽ፡ለዘለዓለም፡ጽኑና፡ታላቅ፡ይኹን፤የባሪያኽም፡የዳዊት፡ቤት፡በፊትኽ፡ጸንቷል።
25፤አምላኬ፡ሆይ፥ቤት፡እንድሠራለት፡ለባሪያኽ፡ገልጠኻልና፥ስለዚህ፡ባሪያኽ፡ወዳንተ፡ይጸልይ፡ዘንድ፡በልቡ ፡ደፈረ።
26፤አኹንም፥አቤቱ፥አንተ፡አምላክ፡ነኽ፥ይህንም፡መልካም፡ነገር፡ለባሪያኽ፡ተናግረኻል።
27፤አኹንም፡በፊትኽ፡ለዘለዓለም፡ይኖር፡ዘንድ፡የባሪያኽን፡ቤት፡እንድትባርክ፡ፈቅደኻል፤አንተም፥አቤቱ፥ባ ርከኸዋል፥ለዘለዓለምም፡ቡሩክ፡ይኾናል።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡18።______________
ምዕራፍ፡18።
1፤ከዚህም፡በዃላ፡ዳዊት፡ፍልስጥኤማውያንን፡መታ፥አዋረዳቸውም፥ከፍልስጥኤማውያንም፡እጅ፡ጌትንና፡መንደሮቿ ን፡ወሰደ።
2፤ሞዐብን፡መታ፤ሞዐባውያንም፡ለዳዊት፡ገባሮች፡ኾኑ፤ግብርም፡አመጡለት።
3፤ዳዊትም፡በኤፍራጥስ፡ወንዝ፡አጠገብ፡የነበረውን፡ግዛት፡ለመያዝ፡በኼደ፡ጊዜ፡የሱባን፡ንጉሥ፡አድርዐዛርን ፡እስከ፡ሃማት፡ድረስ፡መታ።
4፤ዳዊትም፡ከርሱ፡አንድ፡ሺሕ፡ሠረገላዎች፥ሰባት፡ሺሕም፡ፈረሰኛዎች፥ኻያ፡ሺሕም፡እግረኛዎች፡ወሰደ፤ዳዊት፡ ለመቶ፡ሠረገላዎች፡የሚኾኑትን፡ብቻ፡አስቀርቶ፡የሠረገላዎቹን፡ፈረሶች፡ቋንዣ፡ቈረጠ።
5፤ከደማስቆም፡ሶርያውያን፡የሱባን፡ንጉሥ፡አድርዐዛርን፡ሊረዱ፡በመጡ፡ጊዜ፡ዳዊት፡ከሶርያውያን፡ኻያ፡ኹለት ፡ሺሕ፡ሰዎችን፡ገደለ።
6፤ዳዊትም፡በደማስቆ፡ሶርያ፡ጭፍራዎች፡አኖረ፤ሶርያውያንም፡ለዳዊት፡ገባሮች፡ኾኑ፥ግብርም፡አመጡለት።እግዚ አብሔርም፡ዳዊት፡በኼደበት፡ዅሉ፡ድል፡ይሰጠው፡ነበር።
7፤ዳዊትም፡ለአድርዐዛር፡ባሪያዎች፡የነበሩትን፡የወርቅ፡ጋሻዎች፡ወሰደ፥ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡ይዟቸው፡መጣ።
8፤ከአድርዐዛርም፡ከተማዎች፡ከጢብሐትና፡ከኩን፡ዳዊት፡እጅግ፡ብዙ፡ናስ፡ወሰደ፤ከዚህም፡ሰሎሞን፡የናሱን፡ኵ ሬና፡ዐምዶች፡የናሱንም፡ዕቃ፡ሠራ።
9፤የሐማትም፡ንጉሥ፡ቶዑ፡ዳዊት፡የሱባን፡ንጉሥ፡የአድርዐዛርን፡ጭፍራ፡ዅሉ፡እንደ፡መታ፡ሰማ።
10፤ቶዑም፡ከአድርዐዛር፡ጋራ፡ዅል፡ጊዜ፡ይዋጋ፡ነበርና፥ዳዊት፡አድርዐዛርን፡ወግቶ፡ስለ፡መታው፡ደኅንነቱን ፡ይጠይቅ፡ዘንድ፡ይመርቀውም፡ዘንድ፡ልጁን፡አዶራምን፡ወደ፡ዳዊት፡ላከው፤ርሱም፡የወርቅና፡የብር፡የናስም፡ ዕቃ፡ይዞ፡መጣ።
11፤ንጉሡም፡ዳዊት፡ከአሕዛብ፡ዅሉ፡ከኤዶምና፡ከሞዐብ፡ከዐሞንም፡ልጆች፡ከፍልስጥኤማውያንም፡ከዐማሌቅም፡ከ ማረከው፡ብርና፡ወርቅ፡ጋራ፡እነዚህን፡ደግሞ፡ለእግዚአብሔር፡ቀደሰ።
12፤ደግሞ፡የጽሩያ፡ልጅ፡አቢሳ፡ከኤዶማውያን፡በጨው፡ሸለቆ፡ውስጥ፡ዐሥራ፡ስምንት፡ሺሕ፡ሰዎች፡ገደለ።
13፤በኤዶምያስም፡ጭፍራዎች፡አኖረ፥ኤዶማውያንም፡ዅሉ፡ለዳዊት፡ገባሮች፡ኾኑ።እግዚአብሔርም፡ዳዊት፡በኼደበ ት፡ዅሉ፡ድል፡ይሰጠው፡ነበር።
14፤ዳዊትም፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ላይ፡ነገሠ፤ለሕዝቡም፡ዅሉ፡ፍርድንና፡ጽድቅም፡አደረገላቸው።
15፤የጽሩያ፡ልጅ፡ኢዮአብም፡የሰራዊት፡አለቃ፡ነበረ፤የአኂሉድም፡ልጅ፡ኢዮሳፍጥ፡ታሪክ፡ጸሓፊ፡ነበረ።
16፤የአኪጦብም፡ልጅ፡ሳዶቅ፥የአቢሜሌክም፡ልጅ፡አብያታር፡ካህናት፡ነበሩ፤ሱሳ፡ጸሓፊ፡ነበረ።
17፤የዮዳዔ፡ልጅ፡በናያስ፡በከሊታውያንና፡በፈሊታውያን፡ላይ፡ነበረ፤የዳዊትም፡ልጆች፡በንጉሡ፡አጠገብ፡አለ ቃዎች፡ነበሩ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡19።______________
ምዕራፍ፡19።
1፤ከዚህም፡በዃላ፡የዐሞን፡ልጆች፡ንጉሥ፡ናዖስ፡ሞተ፥ልጁም፡በርሱ፡ፋንታ፡ነገሠ።
2፤ዳዊትም፦አባቱ፡ስላደረገልኝ፡ወረታ፡እኔ፡ለናዖስ፡ልጅ፡ለሐኖን፡ቸርነት፡አደርጋለኹ፡አለ።ዳዊትም፡አባቱ ፡ስለ፡ሞተ፡ሊያጽናናው፡መልእክተኛዎችን፡ላከ፤የዳዊትም፡ባሪያዎች፡ሊያጽናኑት፡ወደ፡ሐኖን፡ወደዐሞን፡ልጆ ች፡ምድር፡መጡ።
3፤የዐሞን፡ልጆች፡አለቃዎች፡ግን፡ሐኖንን፦ዳዊት፡አባትኽን፡አክብሮ፡የሚያጽናኑኽን፡ወዳንተ፡የላከ፡ይመስል ኻልን፧ባሪያዎቹስ፡አገሪቱን፡ለመመርመር፥ለማጥፋት፥ለመሰለልም፡ወዳንተ፡የመጡ፡አይደሉምን፧አሉት።
4፤ሐኖንም፡የዳዊትን፡ባሪያዎች፡ወስዶ፡አስላጫቸው፥ልብሳቸውንም፡እስከ፡ወገባቸው፡ድረስ፡ከኹለት፡ቀዶ፟፡ሰ ደዳቸው።
5፤ወሬኛዎችም፡ኼደው፡በሰዎቹ፡ላይ፡የተደረገውን፡ለዳዊት፡አስታወቁት።ሰዎቹም፡በብዙ፡ዐፍረዋልና፥ተቀባዮች ፡ላከ፤ንጉሡም፦ጢማችኹ፡እስኪያድግ፡ድረስ፡በኢያሪኮ፡ተቀመጡ፥ከዚያም፡በዃላ፡ተመለሱ፡አለ።
6፤የዐሞንም፡ልጆች፡በዳዊት፡ዘንድ፡እንደ፡ተጠሉ፡ባዩ፡ጊዜ፡ሐኖንና፡የዐሞን፡ልጆች፡ከመስጴጦምያ፥ከአራምመ ዓካ፥ከሱባ፡ሠረገላዎችንና፡ፈረሰኛዎችን፡ይቀጥሩ፡ዘንድ፡አንድ፡ሺሕ፡መክሊት፡ብር፡ላኩ።
7፤ሠላሳ፡ኹለትም፡ሺሕ፡ሠረገላዎች፡የመዓካንም፡ንጉሥ፡ሕዝቡንም፡ቀጠሩ፤መጥተውም፡በሜድባ፡ፊት፡ለፊት፡ሰፈ ሩ።የዐሞንም፡ልጆች፡ከየከተማዎቻቸው፡ተሰብስበው፡ወደ፡ሰልፍ፡መጡ።
8፤ዳዊትም፡ይህ፡በሰማ፡ጊዜ፡ኢዮአብንና፡የኀያላኑን፡ሰራዊት፡ዅሉ፡ላከ።
9፤የዐሞንም፡ልጆች፡ወጥተው፡በከተማዪቱ፡በር፡አጠገብ፡ተሰለፉ፤የመጡትም፡ነገሥታት፡ለብቻቸው፡በሜዳው፡ላይ ፡በሩ።
10፤ኢዮአብም፡በፊትና፡በዃላ፡ሰልፍ፡እንደ፡ከበበው፡ባየ፡ጊዜ፡ከእስራኤል፡ምርጥ፡ምርጦችን፡ዅሉ፡ለይቶ፡በ ሶርያውያን፡ላይ፡አሰለፋቸው።
11፤የቀረውንም፡ሕዝብ፡ለወንድሙ፡ለአቢሳ፡ሰጠው፥በዐሞንም፡ልጆች፡ላይ፡ተሰለፉ።
12፤ርሱም፦ሶርያውያን፡ቢበረቱብኝ፡ርዳኝ፤የዐሞንም፡ልጆች፡ቢበረቱብኽ፡እረዳኻለኹ።
13፤አይዞኽ፥ስለ፡ሕዝባችንና፡ስለአምላካችንም፡ከተማዎች፡እንበርታ፤እግዚአብሔርም፡ደስ፡ያሠኘውን፡ያድርግ ፡አለ።
14፤ኢዮአብና፡ከርሱም፡ጋራ፡የነበረው፡ሕዝብ፡ለሰልፍ፡ወደሶርያውያን፡ፊት፡ቀረቡ፥እነርሱም፡ከፊቱ፡ሸሹ።
15፤የዐሞንም፡ልጆች፡ሶርያውያን፡እንደ፡ሸሹ፡ባዩ፡ጊዜ፡እነርሱ፡ደግሞ፡ከወንድሙ፡ከአቢሳ፡ፊት፡ሸሹ፥ወደ፡ ከተማዪቱም፡ገቡ።ኢዮአብም፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡መጣ።
16፤ሶርያውያንም፡በእስራኤል፡ፊት፡እንደ፡ተሸነፉ፡ባዩ፡ጊዜ፡መልእክተኛዎች፡ልከው፡በወንዝ፡ማዶ፡የነበሩት ን፡ሶርያውያን፡አስመጡ፤የአድርዐዛርም፡ሰራዊት፡አለቃ፡ሾፋክ፡በፊታቸው፡ነበረ።
17፤ዳዊትም፡በሰማ፡ጊዜ፡እስራኤልን፡ዅሉ፡ሰበሰበ፥ዮርዳኖስንም፡ተሻግሮ፡መጣባቸው፥ከነርሱም፡ጋራ፡ተዋጋ፤ ዳዊትም፡በሶርያውያን፡ላይ፡በተሰለፈ፡ጊዜ፡እነርሱ፡ከርሱ፡ጋራ፡ተዋጉ።
18፤ሶርያውያንም፡ከእስራኤል፡ፊት፡ሸሹ፤ዳዊትም፡ከሶርያውያን፡ሰባት፡ሺሕ፡ሠረገለኛዎች፥አርባ፡ሺሕም፡እግ ረኛዎች፡ገደለ፥የሰራዊቱንም፡አለቃ፡ሾፋክን፡ገደለ።
19፤የአድርዐዛርም፡ባሪያዎች፡በእስራኤል፡ፊት፡እንደ፡ተሸነፉ፡ባዩ፡ጊዜ፡ከዳዊት፡ጋራ፡ታረቁ፥ገበሩለትም፤ ሶርያውያንም፡ከዚያ፡ወዲያ፡የዐሞንን፡ልጆች፡ይረዱ፡ዘንድ፡እንቢ፡አሉ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡20።______________
ምዕራፍ፡20።
1፤እንዲህም፡ኾነ፤በዓመት፡መለወጫ፡ነገሥታት፡ወደ፡ሰልፍ፡በሚወጡበት፡ጊዜ፡ኢዮአብ፡ሰራዊቱን፡አወጣ፥የዐሞ ንንም፡ልጆች፡አገር፡አጠፋ፤መጥቶም፡ረባትን፡ከበበ።ዳዊትም፡በኢየሩሳሌም፡ቈይቶ፡ነበር።
2፤ኢዮአብም፡ረባትን፡መቶ፟፡አፈረሳት።ዳዊትም፡የንጉሣቸውን፡ዘውድ፡ከራሱ፡ላይ፡ወሰደ፥ክብደቱም፡አንድ፡መ ክሊት፡ወርቅ፡ያኽል፡ነበር፥ክቡርም፡ዕንቍ፡ነበረበት፥በዳዊትም፡ራስ፡ላይ፡አስቀመጡት፤ከከተማዪቱም፡እጅግ ፡ብዙ፡ምርኮ፡አወጣ።
3፤በውስጧም፡የነበረውን፡ሕዝብ፡አውጥቶ፡በመጋዝና፡በብረት፡መቈፈሪያ፡በመጥረቢያም፡እንዲሠሩ፡አደረጋቸው። እንዲሁም፡ዳዊት፡በዐሞን፡ልጆች፡ከተማዎች፡ዅሉ፡አደረገ።ዳዊትም፡ሕዝቡም፡ዅሉ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ተመለሱ።
4፤ከዚህም፡በዃላ፡በጌዝር፡ላይ፡ከፍልስጥኤማውያን፡ጋራ፡ሰልፍ፡ኾነ፤ኩሳታዊውም፡ሴቦካይ፡ከራፋይም፡ወገን፡ የነበረውን፡ሲፋይን፡ገደለ።
5፤ደግሞም፡ከፍልስጥኤማውያን፡ጋራ፡ሰልፍ፡ነበረ፤የያዒርም፡ልጅ፡ኤልያናን፡የጦሩ፡የቦ፡እንደ፡ሸማኔ፡መጠቅ ለያ፡የነበረውን፡የጌት፡ሰው፡የጎልያድን፡ወንድም፡ለሕሚን፡ገደለ።
6፤ደግሞ፡በጌት፡ላይ፡ሰልፍ፡ነበረ፤ከዚያም፡በእጁና፡በእግሩ፡ስድስት፡ስድስት፡ዅላዅሉ፡ኻያ፡አራት፡ጣቶች፡ ያሉት፡አንድ፡ረዥም፡ሰው፡ነበረ፤ርሱም፡ደግሞ፡ከራፋይም፡የተወለደ፡ነበረ።
7፤እስራኤልንም፡በተገዳደረ፡ጊዜ፡የዳዊት፡ወንድም፡የሳምዓ፡ልጅ፡ዮናታን፡ገደለው።
8፤እነዚያም፡በጌት፡ውስጥ፡ከራፋይም፡የተወለዱ፡ነበሩ፤በዳዊትም፡እጅ፡በባሪያዎቹም፡እጅ፡ወደቁ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡21።______________
ምዕራፍ፡21።
1፤ሰይጣንም፡በእስራኤል፡ላይ፡ተነሣ፥እስራኤልንም፡ይቈጥር፡ዘንድ፡ዳዊትን፡አንቀሳቀሰው።
2፤ዳዊትም፡ኢዮአብንና፡የሕዝቡን፡አለቃዎች፦ኺዱ፥ከቤርሳቤሕ፡ዠምሮ፡እስከ፡ዳን፡ድረስ፡እስራኤልን፡ቍጠሩ፥ ድምራቸውንም፡ዐውቅ፡ዘንድ፡አስታውቁኝ፡አላቸው።
3፤ኢዮአብም፦እግዚአብሔር፡ሕዝቡን፡በአኹኑ፡ላይ፡መቶ፡ዕጥፍ፡ይጨምር፤ጌታዬ፡ንጉሥ፡ሆይ፥ዅሉ፡የጌታዬ፡ባሪ ያዎች፡አይደሉምን፧ይህን፡ነገር፡ጌታዬ፡ለምን፡ይሻል፧በእስራኤል፡ላይ፡በደል፡ስለ፡ምን፡ያመጣል፧
4፤ነገር፡ግን፥የንጉሡ፡ቃል፡በኢዮአብ፡ላይ፡አሸነፈ፤ኢዮአብም፡ወጥቶ፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ላይ፡ተዘዋወረ፥ወደ ፡ኢየሩሳሌምም፡መጣ።
5፤ኢዮአብም፡የቈጠራቸውን፡የሕዝቡን፡ድምር፡ለዳዊት፡ሰጠ፤ከእስራኤልም፡ዅሉ፡አንድ፡ሚልዮን፡ከመቶ፡ሺሕ፡ሰ ይፍ፡የሚመዙ፟፡ሰዎችን፡አገኘ፤ከይሁዳም፡አራት፡መቶ፡ሰባ፡ሺሕ፡ሰይፍ፡የሚመዙ፟፡ሰዎችን፡አገኘ።
6፤የንጉሡ፡ትእዛዝ፡ግን፡በኢዮአብ፡ዘንድ፡የተጠላ፡ነበርና፥ሌዊና፡ብንያም፡ከነርሱ፡ጋራ፡አልተቈጠሩም።
7፤ከዚህም፡ነገር፡የተነሣ፡እግዚአብሔር፡ተቈጣ፥እስራኤልንም፡ቀሠፈ።
8፤ዳዊትም፡እግዚአብሔርን፦ይህን፡በማድረግ፡እጅግ፡በድያለኹ፤አኹን፡ግን፡ታላቅ፡ስንፍና፡አድርጌያለኹና፡የ ባሪያኽን፡ኀጢአት፡ታስወግድ፡ዘንድ፡እለምንኻለኹ፡አለው።
9፤እግዚአብሔርም፡ለዳዊት፡ባለራእይ፡ለጋድ።
10፤ኺድ፥ለዳዊት፦እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ሦስቱን፡ነገሮች፡በፊትኽ፡አኖራለኹ፤አደርግብኽ፡ዘንድ፡ከነ ርሱ፡አንዱን፡ምረጥ፡ብለኽ፡ንገረው፡ብሎ፡ተናገረው።
11፤ጋድም፡ወደ፡ዳዊት፡መጥቶ፦እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦የምትወደ፟ውን፡ምረጥ፤
12፤የሦስት፡ዓመት፡ራብ፥ወይም፡ሦስት፡ወር፡የጠላቶችኽ፡ሰይፍ፡እንዲያገኝኽ፡ከጠላቶችኽ፡መሰደድን፥ወይም፡ ሦስት፡ቀን፡የእግዚአብሔር፡ሰይፍ፡ቸነፈርም፡በምድር፡ላይ፡መኾንን፥የእግዚአብሔርም፡መልአክ፡በእስራኤል፡ ምድር፡ዅሉ፡ማጥፋትን፡ምረጥ፤አኹንም፡ለላከኝ፡ምን፡እንድመልስ፡ተመልከት፡አለው።
13፤ዳዊትም፡ጋድን፦እጅግ፡ተጨንቄያለኹ፤ምሕረቱ፡ብዙ፡ነውና፥በእግዚአብሔር፡እጅ፡ልውደቅ፤በሰው፡እጅ፡ግን ፡አልውደቅ፡አለው።
14፤እግዚአብሔርም፡በእስራኤል፡ላይ፡ቸነፈርን፡ሰደደ፤ከእስራኤልም፡ሰባ፡ሺሕ፡ሰዎች፡ወደቁ።
15፤እግዚአብሔርም፡ያጠፋት፡ዘንድ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡መልአክን፡ሰደደ፤ሊያጠፋትም፡በቀረበ፡ጊዜ፡እግዚአብሔ ር፡አይቶ፡ስለ፡ክፉው፡ነገር፡ተጸጸተ፥የሚያጠፋውንም፡መልአክ፦በቃኽ፤አኹን፡እጅኽን፡መልስ፡አለው።የእግዚ አብሔርም፡መልአክ፡በኢያቡሳዊው፡በኦርና፡ዐውድማ፡አጠገብ፡ቆሞ፡ነበር።
16፤ዳዊትም፡ዐይኖቹን፡አነሣ፤የእግዚአብሔር፡መልአክ፡በምድርና፡በሰማይ፡መካከል፡ቆሞ፥የተመዘዘም፡ሰይፍ፡ በእጁ፡ኾኖ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ተዘርግቶ፡አየ።ዳዊትም፡ሽማግሌዎችም፡ማቅ፡ለብሰው፡በግንባራቸው፡ተደፉ።
17፤ዳዊትም፡እግዚአብሔርን፦ሕዝቡ፡ይቈጠር፡ዘንድ፡ያዘዝኹ፡እኔ፡አይደለኹምን፧የበደልኹና፡ክፉ፡የሠራኹ፡እ ኔ፡ነኝ፤እነዚህ፡በጎች፡ግን፡ምን፡አድርገዋል፧አቤቱ፡አምላኬ፡ሆይ፥እጅኽ፡በእኔና፡በአባቴ፡ቤት፡ላይ፡ትኹ ን፥ነገር፡ግን፥ይቀሠፍ፡ዘንድ፡በሕዝብኽ፡ላይ፡አትኹን፡አለው።
18፤የእግዚአብሔርም፡መልአክ፡ዳዊት፡ወጥቶ፡በኢያቡሳዊው፡በኦርና፡ዐውድማ፡ላይ፡ለእግዚአብሔር፡መሠዊያ፡ይ ሠራ፡ዘንድ፡ለዳዊት፡እንዲነግረው፡ጋድን፡አዘዘው።
19፤ዳዊትም፡በእግዚአብሔር፡ስም፡እንደተናገረው፡እንደ፡ጋድ፡ነገር፡ወጣ።
20፤ኦርናም፡ዘወር፡ብሎ፡መልአኩን፡አየ፥ከርሱም፡ጋራ፡የነበሩ፡አራቱ፡ልጆቹ፡ተሸሸጉ፤ኦርናም፡ስንዴ፡ያበራ ይ፡ነበር።
21፤ዳዊትም፡ወደ፡ኦርና፡በመጣ፡ጊዜ፡ኦርና፡ተመልክቶ፡ዳዊትን፡አየ፤ከዐውድማውም፡ወጥቶ፡ዳዊትን፡እጅ፡ሊነ ሣ፡በምድር፡ላይ፡ተደፋ።
22፤ዳዊትም፡ኦርናን፦በላዩ፡ለእግዚአብሔር፡መሠዊያ፡እሠራ፡ዘንድ፡ይህን፡የዐውድማ፡ስፍራ፡ስጠኝ፤በሙሉ፡ዋ ጋ፡ስጠኝ፤መቅሠፍቱን፡ከሕዝቡ፡ይከለከላል፡አለው።
23፤ኦርናም፡ዳዊትን፦ለአንተ፡ውሰደው፥ጌታዬ፡ንጉሡም፡ደስ፡የሚያሠኘውን፡ያድርግ፤እንሆ፥ለሚቃጠለው፡መሥዋ ዕት፡በሬዎቹን፥ለዕንጨትም፡የዐውድማውን፡ዕቃ፥ከእኽልም፡ቍርባን፡ስንዴውን፡እሰጥኻለኹ፤ዅሉን፡እሰጣለኹ፡ አለው።
24፤ንጉሡም፡ዳዊት፡ኦርናን፦አይደለም፥ነገር፡ግን፥ለአንተ፡ያለውን፡ለእግዚአብሔር፡አምጥቼ፡የሚቃጠል፡መሥ ዋዕት፡በከንቱ፡አላቀርብምና፡በሙሉ፡ዋጋ፡እገዛዋለኹ፡አለው።
25፤ዳዊትም፡ስለ፡ስፍራው፡ስድስት፡መቶ፡ሰቅል፡ወርቅ፡በሚዛን፡ለኦርና፡ሰጠው።
26፤ዳዊትም፡በዚያ፡ለእግዚአብሔር፡መሠዊያ፡ሠራ፥የሚቃጠለውን፡መሥዋዕትና፡የደኅንነቱን፡መሥዋዕት፡አቀረበ ፥እግዚአብሔርንም፡ጠራ፤ከሰማይም፡ለሚቃጠለው፡መሥዋዕት፡በሚኾነው፡መሠዊያ፡ላይ፡በእሳት፡መለሰለት።
27፤እግዚአብሔርም፡መልአኩን፡አዘዘው፥ሰይፉንም፡በአፎቱ፡ከተተው።
28፤በዚያን፡ጊዜ፡እግዚአብሔር፡በኢያቡሳዊው፡በኦርና፡ዐውድማ፡እንደ፡መለሰለት፡ዳዊት፡ባየ፡ጊዜ፥በዚያ፡መ ሥዋዕት፡ሠዋ።
29፤ሙሴም፡በምድረ፡በዳ፡የሠራት፡የእግዚአብሔር፡ማደሪያና፡ለሚቃጠል፡መሥዋዕት፡የሚኾነው፡መሠዊያ፡በዚያን ፡ጊዜ፡በገባዖን፡ባለው፡በኰረብታው፡መስገጃ፡ነበሩ።
30፤ዳዊት፡ግን፡የእግዚአብሔርን፡መልአክ፡ሰይፍ፡ስለ፡ፈራ፡እግዚአብሔርን፡ለመጠየቅ፡ወደዚያ፡ይኼድ፡ዘንድ ፡አልቻለም።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡22።______________
ምዕራፍ፡22።
1፤ዳዊትም፦ይህ፡የእግዚአብሔር፡ቤት፡ነው፥ይህም፡ለእስራኤል፡ለሚቃጠል፡መሥዋዕት፡የሚኾነው፡መሠዊያ፡ነው፡ አለ።
2፤ዳዊትም፡በእስራኤል፡ምድር፡የነበሩትን፡መጻተኛዎች፡ይሰበስቡ፡ዘንድ፡አዘዘ፤የእግዚአብሔርንም፡ቤት፡ለመ ሥራት፡የሚወቀሩትን፡ድንጋዮች፡ይወቅሩ፡ዘንድ፡ጠራቢዎችን፡አኖረ።
3፤ዳዊትም፡ለበሮቹ፡ሳንቃ፡ለሚኾኑ፡ለምስማርና፡ለመጠረቂያ፡ብዙ፡ብረት፥ከብዛቱም፡የተነሣ፡የማይመዘን፡ናስ ፡አዘጋጀ።
4፤ሲዶናውያንና፡የጢሮስ፡ሰዎች፡ብዙ፡የዝግባ፡ዕንጨት፡ወደ፡ዳዊት፡ያመጡ፡ነበርና፥ቍጥር፡የሌላቸውን፡የዝግ ባ፡ዕንጨቶች፡አዘጋጀ።
5፤ዳዊትም፦ልጄ፡ሰሎሞን፡ታናሽና፡ለጋ፡ብላቴና፡ነው፥ለእግዚአብሔርም፡የሚሠራው፡ቤት፡እጅግ፡ማለፊያና፡በአ ገሩ፡ዅሉ፡ስሙና፡ክብሩ፡እንዲጠራ፡ይኾን፡ዘንድ፡ይገ፟ባ፟ል፤ስለዚህ፥አዘጋጅለታለኹ፡አለ።ዳዊትም፡ሳይሞት ፡አስቀድሞ፡ብዙ፡አዘጋጀ።
6፤ልጁንም፡ሰሎሞንን፡ጠርቶ፡ለእስራኤል፡አምላክ፡ለእግዚአብሔር፡ስም፡ቤት፡ይሠራ፡ዘንድ፡አዘዘው።
7፤ዳዊትም፡ሰሎሞንን፡እንዲህ፡አለ፦ልጄ፡ሆይ፥እኔ፡ለአምላኬ፡ለእግዚአብሔር፡ቤት፡እሠራ፡ዘንድ፡በልቤ፡ዐስ ቤ፡ነበር።
8፤ነገር፡ግን፥የእግዚአብሔር፡ቃል፡እንዲህ፡ሲል፡ወደ፡እኔ፡መጣ፦እጅግ፡ደም፡አፍሰ፟ኻል፥ታላቅም፡ሰልፍ፡አ ድርገኻል፤በፊቴ፡በምድር፡ላይ፡ብዙ፡ደም፡አፍሰ፟ኻልና፥ለስሜ፡ቤት፡አትሠራም።
9፤እንሆ፥የዕረፍት፡ሰው፡የሚኾን፡ልጅ፡ይወለድልኻል፤በዙሪያው፡ካሉ፡ከጠላቶቹ፡ዅሉ፡አሳርፈዋለኹ፤ስሙ፡ሰሎ ሞን፡ይባላልና፥በዘመኑም፡ሰላምንና፡ጸጥታን፡ለእስራኤል፡እሰጣለኹ።
10፤ርሱ፡ለስሜ፡ቤት፡ይሠራል፥ልጅም፡ይኾነኛል፥እኔም፡አባት፡እኾነዋለኹ፤የመንግሥቱንም፡ዙፋን፡በእስራኤል ፡ላይ፡ለዘለዓለም፡አጸናለኹ።
11፤አኹንም፥ልጄ፡ሆይ፥እግዚአብሔር፡ከአንተ፡ጋራ፡ይኹን፤ስለ፡አንተም፡እንደተናገረው፡ያከናውንልኽ፥የአም ላክኽንም፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡ሥራ።
12፤ብቻ፡የአምላክኽን፡የእግዚአብሔርን፡ሕግ፡ትጠብቅ፡ዘንድ፡እግዚአብሔር፡ጥበብንና፡ማስተዋልን፡ይስጥኽ፥ በእስራኤልም፡ላይ፡ያሠልጥንኽ።
13፤እግዚአብሔር፡ስለ፡እስራኤል፡ሙሴን፡ያዘዘውን፡ሥርዐትና፡ፍርድ፡ታደርግ፡ዘንድ፡ብትጠነቀቅ፡በዚያን፡ጊ ዜ፡ይከናወንልኻል፤አይዞኽ፥በርታ፤አትፍራ፥አትደንግጥም።
14፤አኹንም፥እንሆ፥በድኽነቴ፡ለእግዚአብሔር፡ቤት፡መቶ፡ሺሕ፡መክሊት፡ወርቅና፡አንድ፡ሚልዮን፡መክሊት፡ብር ፥ሚዛንም፡የሌላቸው፡ብዙ፡ናስና፡ብረት፡አዘጋጀኹ፤ደግሞም፡ዕንጨትና፡ድንጋዮች፡አዘጋጀኹ፥አንተም፡ከዚያ፡ በላይ፡ጨምር።
15፤ባንተም፡ዘንድ፡ብዙ፡ሠራተኛዎች፥ድንጋይና፡ዕንጨት፡ወቃሪዎችና፡ጠራቢዎች፥ሥራውንም፡ዅሉ፡ለማድረግ፡ጠ ቢባን፡ሰዎች፡ዅሉ፡አሉ።
16፤የሚሠሩበት፡ወርቅና፡ብር፡ናስና፡ብረት፡ቍጥር፡የለውም፤ተነሥተኽ፡ሥራ፥እግዚአብሔርም፡ከአንተ፡ጋራ፡ይ ኹን።
17፤ዳዊትም፡ደግሞ፡ልጁን፡ሰሎሞንን፡ያግዙ፡ዘንድ፡የእስራኤልን፡አለቃዎች፡ዅሉ፡እንዲህ፡ሲል፡አዘዛቸው።
18፤አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡ከእናንተ፡ጋራ፡አይደለምን፧በምድርም፡የሚቀመጡትን፡በእጄ፡አሳልፎ፡ሰጥቷልና ፥ምድርም፡በእግዚአብሔርና፡በሕዝቡ፡ፊት፡ተገዝታለችና፥በዙሪያችኹ፡ዅሉ፡ዕረፍትን፡ሰጥቷችዃል።
19፤አኹንም፡አምላካችኹን፡እግዚአብሔርን፡ትፈልጉ፡ዘንድ፡ልባችኹንና፡ነፍሳችኹን፡ስጡ፤ለእግዚአብሔርም፡ስ ም፡ወደሚሠራው፡ቤት፡የእግዚአብሔርን፡የቃል፡ኪዳኑን፡ታቦትና፡የእግዚአብሔርን፡ንዋየ፡ቅድሳት፡ታመጡ፡ዘን ድ፡ተነሥታችኹ፡የአምላክን፡የእግዚአብሔርን፡መቅደስ፡ሥሩ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡23።______________
ምዕራፍ፡23።
1፤ዳዊትም፡በሸመገለ፡ጊዜ፥ዕድሜንም፡በጠገበ፡ጊዜ፡ልጁን፡ሰሎሞንን፡በእስራኤል፡ላይ፡አነገሠው።
2፤የእስራኤልንም፡አለቃዎች፡ዅሉ፥ካህናቱንም፥ሌዋውያኑንም፡ሰበሰበ።
3፤ሌዋውያንም፡ከሠላሳ፡ዓመት፡ዕድሜ፡ዠምሮ፡ወደ፡ላይ፡ተቈጠሩ፤ቍጥራቸው፡በያንዳንዱ፡ነፍስ፡ወከፍ፡ሠላሳ፡ ስምንት፡ሺሕ፡ነበረ።
4፤ከነዚህም፡ውስጥ፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡ሥራ፡የሚያሠሩት፡ኻያ፡አራት፡ሺሕ፡ነበሩ፤ስድስቱ፡ሺሕም፡አለቃዎ ችና፡ፈራጆች፡ነበሩ።
5፤አራቱ፡ሺሕም፡በረኛዎች፡ነበሩ፤አራቱ፡ሺሕም፡ለምስጋና፡በተሠሩት፡በዜማ፡ዕቃዎች፡እግዚአብሔርን፡ያመሰግ ኑ፡ነበር።
6፤ዳዊትም፡እንደ፡ሌዊ፡ልጆች፡እንደ፡ጌድሶንና፡እንደ፡ቀአት፡እንደ፡ሜራሪም፡በየሰሞናቸው፡ከፈላቸው።
7፤ከጌድሶናውያን፡ለአዳንና፡ሰሜኢ፡ነበሩ።
8፤የለአዳን፡ልጆች፡አለቃው፡ይሒኤል፥ዜቶም፥ኢዮኤል፡ሦስት፡ነበሩ።
9፤የሰሜኢ፡ልጆች፡ሰሎሚት፥ሐዝኤል፥ሀራን፡ሦስት፡ነበሩ።እነዚህ፡የለአዳን፡አባቶች፡ቤቶች፡አለቃዎች፡ነበሩ ።
10፤የሰሜኢ፡ልጆች፡ኢኢት፥ዚዛ፥የዑስ፥በሪዐ፡ነበሩ።እነዚህ፡አራቱ፡የሰሜኢ፡ልጆች፡ነበሩ።
11፤አለቃው፡ኢኢት፡ነበረ፤ኹለተኛው፡ዚዛ፡ነበረ፤የዑስና፡በሪዐ፡ግን፡ብዙ፡ልጆች፡አልነበሯቸውም፤ስለዚህ፥ እንደ፡አንድ፡አባት፡ቤት፡ኾነው፡ተቈጠሩ።
12፤የቀአት፡ልጆች፡ዕምበረም፥ይስዓር፥ኬብሮን፥ዑዝኤል፡አራት፡ነበሩ።
13፤የዕምበረም፡ልጆች፡አሮንና፡ሙሴ፡ነበሩ፤አሮንም፡ከዅሉ፡በላይ፡የተቀደሰ፡ይኾን፡ዘንድ፡ተለየ፥ርሱና፡ል ጆቹ፥ለዘለዓለም፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ያጥንና፡ያገለግል፡ዘንድ፥በስሙም፡ለዘለዓለም፡ይባርክ፡ዘንድ።
14፤የእግዚአብሔርም፡ሰው፡የሙሴ፡ልጆች፡በሌዊ፡ነገድ፡ተቈጠሩ።
15፤የሙሴ፡ልጆች፡ጌርሳምና፡አልዓዛር፡ነበሩ።
16፤የጌርሳም፡ልጆች፡አለቃ፡ሱባኤል፡ነበረ።
17፤የአልዓዛርም፡ልጆች፡አለቃ፡ረዓብያ፡ነበረ፤አልዓዛርም፡ሌላዎች፡ልጆች፡አልነበሩትም፤የረዓብያ፡ልጆች፡ እጅግ፡ብዙ፡ነበሩ።
18፤የይስዓር፡ልጆች፡አለቃው፡ሰሎሚት፡ነበረ።
19፤የኬብሮን፡ልጆች፡አለቃው፡ይሪያ፥ኹለተኛው፡አማርያ፥ሦስተኛው፡የሕዚኤል፥አራተኛው፡ይቅምዓም፡ነበሩ።
20፤የዑዝኤል፡ልጆች፡አለቃው፡ሚካ፥ኹለተኛው፡ይሺያ፡ነበሩ።
21፤የሜራሪ፡ልጆች፡ሞሖሊና፡ሙሲ፡ነበሩ።የሞሖሊ፡ልጆች፡አልዓዛርና፡ቂስ፡ነበሩ።
22፤አልዓዛርም፡ሴቶች፡ልጆች፡ብቻ፡እንጂ፡ወንዶች፡ልጆች፡ሳይወልድ፡ሞተ፤ወንድሞቻቸውም፡የቂስ፡ልጆች፡አገ ቧቸው።
23፤የሙሲ፡ልጆች፡ሞሖሊ፥ዔደር፥ኢያሪሙት፡ሦስት፡ነበሩ።
24፤የእግዚአብሔርን፡ቤት፡አገልግሎት፡በሠሩ፡ከኻያ፡ዓመት፡ዕድሜ፡ዠምሮ፡ወደ፡ላይ፡በነበሩ፡በያንዳንዳቸው ፡በስማቸው፡በተቈጠሩት፡ላይ፡የአባቶች፡ቤት፡አለቃዎች፡የኾኑት፡በያባቶቻቸው፡ቤት፡የሌዊ፡ልጆች፡እነዚህ፡ ነበሩ።
25፤ዳዊትም፦የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡ለሕዝቡ፡ዕረፍት፡ሰጥቷል፥በኢየሩሳሌምም፡ለዘለዓለም፡ይቀመ ጣል።
26፤ሌዋውያንም፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡ማደሪያውንና፡የማገልገያውን፡ዕቃ፡ዅሉ፡አይሸከሙም፡አለ።
27፤በመጨረሻውም፡በዳዊት፡ትእዛዝ፡ከኻያ፡ዓመት፡ዕድሜ፡ዠምሮ፡ከዚያም፡በላይ፡ያሉት፡የሌዊ፡ልጆች፡ተቈጠሩ ።
28፤ሥራቸውም፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡በያደባባዩና፡በየጓዳው፡ውስጥ፡ለማገልገል፥ቅዱሱንም፡ዕቃ፡ዅሉ፡ለማን ጻት፥የእግዚአብሔርንም፡ቤት፡አገልግሎት፡ለመሥራት፡ከአሮን፡ልጆች፡እጅ፡በታች፡ነበረ።
29፤ደግሞም፡ገጸ፡ኅብስት፥ሥሥ፡ቂጣም፡ቢኾን፥በምጣድም፡ቢጋገር፥ቢለወስም፥ለእኽል፡ቍርባን፡በኾነው፡በመል ካሙ፡ዱቄት፡በመስፈሪያና፡በልክ፡ዅሉ፡ያገለግሉ፡ነበር።
30፤ሥራቸውም፡በየጧቱና፡በየማታው፡ቆመው፡እግዚአብሔርን፡ለማመስገንና፡ለማክበር፥
31፤በየሰንበታቱም፡በየመባቻዎቹም፡በየበዓላቱም፡እንደ፡ሥርዐቱ፡ቍጥር፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ዘወትር፡ለእግ ዚአብሔር፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፡ዅሉ፡ለማቅረብ፥
32፤ለእግዚአብሔርም፡ቤት፡አገልግሎት፡የመገናኛውን፡ድንኳን፡ሥርዐት፡የመቅደሱንም፡ሥርዐት፡የወንድሞቻቸው ንም፡የአሮንን፡ልጆች፡ሥርዐት፡ለመጠበቅ፡ነበረ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡24።______________
ምዕራፍ፡24።
1፤የአሮንም፡ልጆች፡ሰሞን፡ይህ፡ነው።የአሮን፡ልጆች፡ናዳብ፥አብዩድ፥አልዓዛር፥ኢታምር፡ነበሩ።
2፤ናዳብና፡አብዩድ፡ግን፡ልጆች፡ሳይወልዱ፡ከአባታቸው፡በፊት፡ሞቱ፤አልዓዛርና፡ኢታምርም፡ካህናት፡ኾኑ።
3፤ዳዊትም፡ከአልዓዛር፡ልጆች፡ከሳዶቅ፡ጋራ፥ከኢታምርም፡ልጆች፡ከአቢሜሌክ፡ጋራ፡ኾኖ፡እንደ፡አገልግሎታቸው ፡ሥርዐት፡ከፍሎ፡መደባቸው።
4፤የአልዓዛርም፡ልጆች፡አለቃዎች፡ከኢታምርም፡ልጆች፡አለቃዎች፡በልጠው፡ተገኙ፤እንዲህም፡ተመደቡ፤ከአልዓዛ ር፡ልጆች፡እንደ፡አባቶቻቸው፡ቤቶች፡ዐሥራ፡ስድስት፥ከኢታምርም፡ልጆች፡እንደ፡አባቶቻቸው፡ቤቶች፡ስምንት፡ አለቃዎች፡ነበሩ።
5፤ከአልዓዛርና፡ከኢታምርም፡ልጆች፡መካከል፡የመቅደሱና፡የእግዚአብሔር፡አለቃዎች፡ነበሩና፥እነዚህና፡እነዚ ያ፡እንዲህ፡በዕጣ፡ተመደቡ።
6፤ከሌዋውያንም፡ወገን፡የነበረው፡የናትናኤል፡ልጅ፡ጸሓፊው፡ሸማያ፡በንጉሡና፡በአለቃዎቹ፡ፊት፥በካህኑ፡በሳ ዶቅና፡በአብያታርም፡ልጅ፡በአቢሜሌክ፡ፊት፥በካህናቱና፡በሌዋውያኑ፡አባቶች፡ቤቶች፡አለቃዎች፡ፊት፡ጻፋቸው ፤አንዱንም፡የአባት፡ቤት፡ለአልዓዛር፥አንዱንም፡ለኢታምር፡ጻፈ።
7፤መዠመሪያውም፡ዕጣ፡ለዮአሪብ፡ወጣ፥ኹለተኛው፡ለዮዳዔ፥
8፤ሦስተኛው፡ለካሪም፥
9፤አራተኛው፡ለሥዖሪም፥ዐምስተኛው፡ለመልክያ፥
10፤ስድስተኛው፡ለሚያሚን፥ሰባተኛው፡ለአቆስ፥
11፤ስምንተኛው፡ለአብያ፥ዘጠነኛው፡ለኢያሱ፥
12፤ዐሥረኛው፡ለሴኬንያ፥ዐሥራ፡አንደኛው፡ለኤልያሴብ፥ዐሥራ፡ኹለተኛው፡ለያቂም፥
13፤ዐሥራ፡ሦስተኛው፡ለኦፓ፥ዐሥራ፡አራተኛው፡ለየሼብአብ፥
14፤ዐሥራ፡ዐምስተኛው፡ለቢልጋ፥ዐሥራ፡ስድስተኛው፡ለኢሜር፥
15፤ዐሥራ፡ሰባተኛው፡ለኤዚር፥ዐሥራ፡ስምንተኛው፡ለሃፊጼጽ፥
16፤ዐሥራ፡ዘጠነኛው፡ለፈታያ፥
17፤ኻያኛው፡ለኤዜቄል፥ኻያ፡አንደኛው፡ለያኪን፥ኻያ፡ኹለተኛው፡ለጋሙል፥
18፤ኻያ፡ሦስተኛው፡ለድላያ፥ኻያ፡አራተኛው፡ለመዓዝያ።
19፤የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡እንዳዘዘ፥አባታቸው፡አሮን፡እንደ፡ሰጣቸው፡ሥርዐት፡ወደእግዚአብሔር ፡ቤት፡የሚገቡበት፡የአገልግሎታቸው፡ሥርዐት፡ይህ፡ነበረ።
20፤ከቀሩትም፡የሌዊ፡ልጆች፤ከዕምበረም፡ልጆች፡ሱባኤል፤ከሱባኤል፡ልጆች፡ዬሕድያ፤
21፤22፤ከረዓብያ፡ልጆች፡አለቃው፡ይሺያ፤ከይስዓራውያን፡ሰሎሚት፤ከሰሎሚት፡ልጆች፡ያሐት፤
23፤ከኬብሮንም፡ልጆች፡አለቃው፡ይሪያ፥ኹለተኛው፡አማርያ፥ሦስተኛው፡የሕዚኤል፥አራተኛው፡ይቀምዓም፤
24፤የዑዝኤል፡ልጅ፡ሚካ፤
25፤የሚካ፡ልጅ፡ሻሚር፤የሚካ፡ወንድም፡ይሺያ፤
26፤ከይሺያ፡ልጆች፡ዘካርያስ፤የሜራሪ፡ልጆች፡ሞሖሊ፥ሙሲ፤ከያዝያ፡ልጅ፡በኖ፤
27፤የሜራሪ፡ልጆች፤ከያዝያ፡በኖ፥ሾሃም፥ዘኩር፥ዔብሪ፤
28፤ከሞሖሊ፡አልዓዛር፥ርሱም፡ልጆች፡አልነበሩት፤
29፤ከቂስ፤የቂስ፡ልጅ፡ይረሕምኤል፤የሙሲም፡ልጆች፤ሞሖሊ፥ዔዳር፥ኢያሪሙት።
30፤እነዚህ፡እንደ፡አባቶቻቸው፡ቤቶች፡የሌዋውያን፡ልጆች፡ነበሩ።
31፤እነዚህም፡ደግሞ፡በንጉሡ፡በዳዊትና፡በሳዶቅ፡በአቢሜሌክም፡በሌዋውያንና፡በካህናት፡አባቶች፡ቤቶች፡አለ ቃዎች፡ፊት፥ታላቁም፡እንደ፡ታናሹ፥እንደ፡ወንድሞቻቸው፡እንደ፡አሮን፡ልጆች፡ዕጣ፡ተጣጣሉ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡25።______________
ምዕራፍ፡25።
1፤ዳዊትና፡የሰራዊቱ፡አለቃዎችም፡ከአሣፍና፡ከኤማን፡ከኤዶታም፡ልጆች፡በመሰንቆና፡በበገና፡በጸናጽልም፡ትን ቢት፡የሚናገሩትን፡ሰዎች፡ለማገልገል፡ለዩ፤በአገልግሎታቸውም፡ሥራ፡የሠሩ፡ሰዎች፡ቍጥር፡ይህ፡ነበረ።
2፤ከአሣፍ፡ልጆች፤ዘኩር፥ዮሴፍ፥ነታንያ፥አሸርኤላ፤እነዚህ፡የአሣፍ፡ልጆች፡በንጉሡ፡ትእዛዝ፡ትንቢት፡ከተና ገረው፡ከአሣፍ፡እጅ፡በታች፡ነበሩ።
3፤ከኤዶታም፡የኤዶታም፡ልጆች፤ጎዶልያስ፥ጽሪ፥የሻያ፥ሰሜኢ፥ሐሸብያ፥መቲትያ፥እነዚህ፡ስድስቱ፡ለእግዚአብሔ ር፡ምስጋናና፡ክብር፡በመሰንቆ፡ትንቢት፡ከተናገረው፡ከአባታቸው፡ከኤዶታም፡እጅ፡በታች፡ነበሩ።
4፤ከኤማን፡የኤማን፡ልጆች፤ቡቅያ፥መታንያ፥ዓዛርዔል፥ሱባኤል፥ኢያሪሙት፥ሐናንያ፥ሐናኒ፥ኤልያታ፥ጊዶልቲ፥ሮ ማንቲዔዘር፥ዮሽብቃሻ፥መሎቲ፥ሆቲር፥መሐዝዮት፤
5፤እነዚህ፡ዅሉ፡ቀንደ፡መለከቱን፡ከፍ፡ያደርጉ፡ዘንድ፡በእግዚአብሔር፡ቃል፡የንጉሡ፡ባለራእይ፡የኾነው፡የኤ ማን፡ልጆች፡ነበሩ።እግዚአብሔርም፡ለኤማን፡ዐሥራ፡አራት፡ወንዶች፡ልጆችንና፡ሦስት፡ሴቶች፡ልጆችን፡ሰጠው።
6፤እነዚህ፡ዅሉ፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡በጸናጽልና፡በበገና፡በመሰንቆም፡ይዘምሩ፡ዘንድ፥በእግዚአብሔርም፡ቤት ፡ያገለግሉ፡ዘንድ፡ከአባታቸው፡እጅ፡በታች፡ነበሩ፤አሣፍም፡ኤዶታምም፡ኤማንም፡ከንጉሡ፡ትእዛዝ፡በታች፡ነበ ሩ።
7፤የብልኀተኛዎቹም፡ቍጥር፡እግዚአብሔርን፡ለማመስገን፡ከሚያውቁ፡ከወንድሞቻቸው፡ጋራ፡ኹለት፡መቶ፡ሰማንያ፡ ስምንት፡ነበረ።
8፤ዅሉም፡ተካክለው፥ታናሹ፡እንደ፡ታላቁ፥አስተማሪውም፡እንደ፡ተማሪው፥ለሰሞናቸው፡ዕጣ፡ተጣጣሉ።
9፤የፊተኛው፡ዕጣ፡ከአሣፍ፡ወገን፡ለነበረው፡ለዮሴፍ፡ወጣ፤ኹለተኛው፡ለጎዶልያስ፡ወጣ፤ርሱ፡ወንድሞቹም፡ልጆ ቹም፡ዐሥራ፡ኹለት፡ነበሩ፤
10፤ሦስተኛው፡ለዘኩር፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
11፤አራተኛው፡ለይጽሪ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
12፤ዐምስተኛው፡ለነታንያ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
13፤ስድስተኛው፡ለቡቅያ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
14፤ሰባተኛው፡ለይሽርኤል፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
15፤ስምንተኛው፡ለየሻያ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
16፤ዘጠነኛው፡ለመታንያ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
17፤ዐሥረኛው፡ለሰሜኢ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
18፤ዐሥራ፡አንደኛው፡ለዓዛርኤል፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
19፤ዐሥራ፡ኹለተኛው፡ለሐሸብያ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
20፤ዐሥራ፡ሦስተኛው፡ለሱባኤል፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
21፤ዐሥራ፡አራተኛው፡ለመቲትያ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
22፤ዐሥራ፡ዐምስተኛው፡ለኢያሪሙት፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
23፤ዐሥራ፡ስድስተኛው፡ለሐናንያ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
24፤ዐሥራ፡ሰባተኛው፡ለዮሽብቃሻ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
25፤ዐሥራ፡ስምንተኛው፡ለሐናኒ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
26፤ዐሥራ፡ዘጠነኛው፡ለመሎቲ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
27፤ኻያኛው፡ለኤልያታ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
28፤ኻያ፡አንደኛው፡ለሆቲር፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
29፤ኻያ፡ኹለተኛው፡ለጊዶልቲ፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
30፤ኻያ፡ሦስተኛው፡ለመሐዚዮት፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
31፤ኻያ፡አራተኛው፡ለሮማንቲዔዘር፡ለልጆቹም፡ለወንድሞቹም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፡ወጣ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡26።______________
ምዕራፍ፡26።
1፤በረኛዎችም፡እንደዚህ፡ተመደቡ፤ከቆሬያውያን፡ከአሣፍ፡ልጆች፡የቆሬ፡ልጅ፡ሜሱላም።
2፤ሜሱላም፡ልጆች፡ነበሩት፤በኵሩ፡ዘካርያስ፥ኹለተኛው፡ይዲኤል፥ሦስተኛው፡ዮዛባት፥
3፤አራተኛው፡የትኒኤል፥ዐምስተኛው፡ዔላም፥ስድስተኛው፡ይሆሐናን፥ሰባተኛው፡ኤሊሆዔናይ።
4፤እግዚአብሔርም፡ባርኮታልና፥ዖቤድኤዶም፡ልጆች፡ነበሩት፤በኵሩ፡ሸማያ፥ኹለተኛው፡ዮዛባት፥ሦስተኛው፡ኢዮአ ስ፥አራተኛው፡ሣካር፥ዐምስተኛው፡ናትናኤል፥
5፤ስድስተኛው፡ዓሚኤል፥ሰባተኛው፡ይሳኮር፥ስምንተኛው፡ፒላቲ።
6፤ለልጁም፡ለሸማያ፡ደግሞ፡ልጆች፡ተወለዱለት፤ጽኑዓንም፡ኀያላን፡ነበሩና፥በአባታቸው፡ቤት፡ሠለጠኑ።
7፤ለሸማያ፡ልጆች፡ዖትኒ፥ራፋኤል፥ዖቤድ፥ወንድሞቹም፡ኀያላን፡የነበሩ፡ኤልዛባድ፥ኤልሁ፥ሰማክያ።
8፤እነዚህ፡ዅሉ፡የዖቤድኤዶም፡ልጆች፡ነበሩ፤እነርሱም፡ልጆቻቸውም፡ወንድሞቻቸውም፡ለማገልገል፡ኀያላን፡የነ በሩ፡የዖቤድኤዶም፡ልጆች፡ስድሳ፡ኹለት፡ነበሩ።
9፤ለሜሱላም፡ኀያላን፡የነበሩ፡ዐሥራ፡ስምንት፡ልጆችና፡ወንድሞች፡ነበሩት።
10፤ከሜራሪም፡ልጆች፡ለነበረው፡ለሖሳ፡ልጆች፡ነበሩት፤አለቃውም፡ሽምሪ፡ነበረ፤በኵር፡አልነበረም፥አባቱ፡ግ ን፡አለቃ፡አደረገው፤
11፤ኹለተኛውም፡ኬልቅያስ፥ሦስተኛው፡ጥበልያ፥አራተኛው፡ዘካርያስ፡ነበረ፤የሖሳ፡ልጆችና፡ወንድሞች፡ዅሉ፡ዐ ሥራ፡ሦስት፡ነበሩ።
12፤እንደ፡ወንድሞቻቸው፡ኾነው፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡ያገለግሉ፡ዘንድ፡የበረኛዎች፡የአለቃዎች፡ሰሞነኛዎች፡ እነዚህ፡ነበሩ።
13፤በበሩም፡ዅሉ፡ያገለግሉ፡ዘንድ፡በያባቶቻቸው፡ቤቶች፡ታናሹና፡ታላቁ፡ተካክለው፡ዕጣ፡ተጣጣሉ።
14፤በምሥራቅም፡በኩል፡ዕጣ፡ለሰሌምያ፡ወደቀ።ለልጁም፡ብልኅ፡መካር፡ለኾነው፡ለዘካርያስ፡ዕጣ፡ጣሉ፤ዕጣውም ፡በሰሜን፡በኩል፡ወጣ።
15፤ለዖቤድኤዶም፡በደቡብ፡በኩል፥ለልጆቹም፡ለዕቃ፡ቤቱ፡ዕጣ፡ወጣ።
16፤ለሰፊንና፡ለሖሳ፡በምዕራብ፡በኩል፥በዐቀበቱም፡መንገድ፡ባለው፡በሸሌኬት፡በር፡በኩል፡ጥበቃ፡ከጥበቃ፡ላ ይ፡ዕጣ፡ወጣ።
17፤በምሥራቅ፡በኩል፡ስድስት፡ሌዋውያን፡ነበሩ፤በሰሜን፡በኩል፡ለየዕለቱ፡አራት፥በደቡብ፡በኩል፡ለየዕለቱ፡ አራት፥ለዕቃ፡ቤቱም፡ኹለት፡ኹለት፡ነበሩ።
18፤በምዕራብ፡በኩል፡በፈርባር፡መንገድ፡ላይ፡አራት፥በፈርባርም፡አጠገብ፡ኹለት፡ነበሩ።
19፤ከቆሬና፡ከሜራሪ፡ልጆች፡የነበሩ፡የበረኛዎች፡ሰሞን፡ይህ፡ነበረ።
20፤ከሌዋውያን፡አኪያ፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡በሚኾኑ፡ቤተ፡መዛግብትና፡በንዋየ፡ቅድሳቱ፡ቤተ፡መዛግብት፡ላይ ፡ተሾሞ፡ነበር።
21፤የለአዳን፡ልጆች፤ለለአዳን፡የኾኑ፡የጌድሶናውያን፡ልጆች፥ለጌድሶናዊ፡ለለአዳን፡የኾኑ፡የአባቶች፡ቤቶች ፡አለቃዎች፡ይሒኤሊ፤
22፤የይሒኤሊ፡ልጆች፤በእግዚአብሔር፡ቤት፡በሚኾኑ፡ቤተ፡መዛግብት፡ላይ፡የነበሩ፡ዜቶም፥ወንድሙም፡ኢዮኤል።
23፤ከዕምበረማውያን፥ከይስዓራውያን፥ከኬብሮናውያን፥ከዑዝኤላውያን፤
24፤የሙሴ፡ልጅ፡የጌርሳም፡ልጅ፡ሱባኤል፡በቤተ፡መዛግብት፡ላይ፡ተሾሞ፡ነበር።
25፤ወንድሞቹም፤ከአልዓዛር፡ልጁ፡ረዓብያ፥ልጁም፡የሻያ፥ልጁም፡ኢዮራም፥ልጁም፡ዝክሪ፥ልጁም፡ሰሎሚት፡መጡ።
26፤ይህ፡ሰሎሚትና፡ወንድሞቹ፡ንጉሡ፡ዳዊትና፡የአባቶች፡ቤቶች፡አለቃዎች፥ሻለቃዎችና፡የመቶ፡አለቃዎች፡የሰ ራዊቱም፡አለቃዎች፥በቀደሱት፡በንዋየ፡ቅድሳቱ፡ቤተ፡መዛግብት፡ዅሉ፡ላይ፡ተሾመው፡ነበር።
27፤በሰልፍም፡ከተገኘው፡ምርኮ፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡ለማበጀት፡ቀደሱ።
28፤ባለራእዩም፡ሳሙኤል፥የቂስም፡ልጅ፡ሳኦል፥የኔርም፡ልጅ፡አበኔር፥የጽሩያም፡ልጅ፡ኢዮአብ፡የቀደሱት፡ንዋ የ፡ቅድሳት፡ዅሉ፡ከሰሎሚትና፡ከወንድሞቹ፡እጅ፡በታች፡ነበረ።
29፤ከይስዓራውያን፡ከናንያና፡ልጆቹ፡ሹማምትና፡ፈራጆች፡ይኾኑ፡ዘንድ፡በውጭው፡ሥራ፡በእስራኤል፡ላይ፡ተሾመ ው፡ነበር።
30፤ከኬብሮናውያን፡ሐሸብያና፡ወንድሞቹ፥ጽኑዓን፡የነበሩት፡ሺሕ፡ሰባት፡መቶ፡ሰዎች፥ለእግዚአብሔር፡ሥራ፡ዅ ሉ፡ለንጉሡም፡አገልግሎት፡በዮርዳኖስ፡ማዶ፡በምዕራብ፡በኩል፡ባለው፡በእስራኤል፡ላይ፡ተሾመው፡ነበር።
31፤ከኬብሮናውያንም፡እንደ፡አባቶች፡ቤቶች፡ትውልዶች፡የኬብሮናውያን፡አለቃ፡ይርያ፡ነበረ።ዳዊት፡በነገሠ፡ በአርባኛው፡ዓመት፡ይፈልጓቸው፡ነበር፤በእነርሱም፡መካከል፡በገለዓድ፡ኢያዜር፡ጽኑዓን፡ኀያላን፡ሰዎች፡ተገ ኙ፤
32፤ወንድሞቹም፡ጽኑዓን፡የነበሩት፡የአባቶች፡ቤቶች፡አለቃዎች፡ኹለት፡ሺሕ፡ሰባት፡መቶ፡ነበሩ።ንጉሡም፡ዳዊ ት፡ለእግዚአብሔር፡ጕዳይ፡ዅሉና፡ለንጉሡ፡ጕዳይ፡በሮቤላውያንና፡በጋዳውያን፡በምናሴም፡ነገድ፡እኩሌታ፡ላይ ፡ሹሞች፡አደረጋቸው።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡27።______________
ምዕራፍ፡27።
1፤የእስራኤልም፡ልጆች፡የአባቶች፡ቤቶች፡አለቃዎችና፡የሺሕ፡አለቃዎች፡የመቶ፡አለቃዎችም፡በክፍሎች፡ነገር፡ ዅሉ፡ንጉሡን፡ያገለገሉትም፡ሹማምት፡እንደ፡ቍጥራቸው፡እነዚህ፡ነበሩ።እነዚህም፡ክፍሎች፡እያንዳንዳቸው፡ኻ ያ፡አራት፡ሺሕ፡ኾነው፡በዓመት፡ወራት፡ዅሉ፡በየወሩ፡ይገቡና፡ይወጡ፡ነበር።
2፤ለመዠመሪያው፡ወር፡በአንደኛው፡ክፍል፡ላይ፡የዘብድኤል፡ልጅ፡ያሾብዓም፡ነበረ፤በርሱም፡ክፍል፡ኻያ፡አራት ፡ሺሕ፡ጭፍራ፡ነበረ።
3፤ርሱ፡ከፋሬስ፡ልጆች፡ነበረ፤ለመዠመሪያው፡ወር፡በጭፍራ፡አለቃዎች፡ዅሉ፡ላይ፡ተሾሞ፡ነበር።
4፤በኹለተኛውም፡ወር፡ክፍል፡ላይ፡አሖሓዊው፡ዱዲ፡ነበረ፤በርሱም፡ክፍል፡ኻያ፡አራት፡ሺሕ፡ጭፍራ፡ነበረ።
5፤ለሦስተኛው፡ወር፡ሦስተኛው፡የጭፍራ፡አለቃ፡የካህኑ፡የዮዳዔ፡ልጅ፡በናያስ፡ነበረ፤በርሱም፡ክፍል፡ኻያ፡አ ራት፡ሺሕ፡ጭፍራ፡ነበረ።
6፤ይህ፡በናያስ፡በሠላሳው፡መካከል፡ኀያል፡ኾኖ፡በሠላሳው፡ላይ፡ነበረ፤በርሱም፡ክፍል፡ልጁ፡ዓሚዛባድ፡ነበረ ።
7፤ለአራተኛው፡ወር፡አራተኛው፡አለቃ፡የኢዮአብ፡ወንድም፡ዐሳሄል፥ከርሱም፡በዃላ፡ልጁ፡ዝባድያ፡ነበረ፤በርሱ ም፡ክፍል፡ኻያ፡አራት፡ሺሕ፡ጭፍራ፡ነበር።
8፤ለዐምስተኛው፡ወር፡ዐምስተኛው፡አለቃ፡ይዝራዊው፡ሸምሁት፡ነበረ፤በርሱም፡ክፍል፡ኻያ፡አራት፡ሺሕ፡ጭፍራ፡ ነበረ።
9፤ለስድስተኛው፡ወር፡ስድስተኛው፡አለቃ፡የቴቁሐዊው፡የዒስካ፡ልጅ፡ዒራስ፡ነበረ፤በርሱም፡ክፍል፡ኻያ፡አራት ፡ሺሕ፡ጭፍራ፡ነበረ።
10፤ለሰባተኛው፡ወር፡ሰባተኛው፡አለቃ፡ከኤፍሬም፡ልጆች፡የኾነ፡ፍሎናዊው፡ሴሌስ፡ነበረ፤በርሱም፡ክፍል፡ኻያ ፡አራት፡ሺሕ፡ጭፍራ፡ነበረ።
11፤ለስምንተኛው፡ወር፡ስምንተኛው፡አለቃ፡ከዛራውያን፡የነበረው፡ኩሳታዊው፡ሲቦካይ፡ነበረ፤በርሱም፡ክፍል፡ ኻያ፡አራት፡ሺሕ፡ጭፍራ፡ነበረ።
12፤ለዘጠነኛው፡ወር፡ዘጠነኛው፡አለቃ፡ከብንያማውያን፡የነበረው፡ዓናቶታዊው፡አቢዔዜር፡ነበረ፤በርሱም፡ክፍ ል፡ኻያ፡አራት፡ሺሕ፡ጭፍራ፡ነበረ።
13፤ለዐሥረኛው፡ወር፡ዐሥረኛው፡አለቃ፡ከዛራውያን፡የነበረው፡ነጦፋዊው፡ኖኤሬ፡ነበረ፤በርሱም፡ክፍል፡ኻያ፡ አራት፡ሺሕ፡ጭፍራ፡ነበረ።
14፤ለዐሥራ፡አንደኛው፡ወር፡ዐሥራ፡አንደኛው፡አለቃ፡ከኤፍሬም፡ልጆች፡የነበረው፡ጲርዓቶናዊው፡በናያስ፡ነበ ረ፤በርሱም፡ክፍል፡ኻያ፡አራት፡ሺሕ፡ጭፍራ፡ነበረ።
15፤ለዐሥራ፡ኹለተኛው፡ወር፡ዐሥራ፡ኹለተኛው፡አለቃ፡ከጎቶንያል፡ወገን፡የነበረው፡ነጦፋዊው፡ሔልዳይ፡ነበረ ፤በርሱም፡ክፍል፡ኻያ፡አራት፡ሺሕ፡ጭፍራ፡ነበረ።
16፤በእስራኤልም፡ነገዶች፡ላይ፡እነዚህ፡ነበሩ፡በሮቤላውያን፡ላይ፡የዝክሪ፡ልጅ፡አልዓዛር፡አለቃ፡ነበረ፤በ ስምዖናውያን፡የመዓካ፡ልጅ፡ሰፋጥያስ፤
17፤በሌዊ፡ላይ፡የቀሙኤል፡ልጅ፡ሐሸቢያ፤
18፤በአሮን፡ላይ፡ሳዶቅ፤በይሁዳ፡ላይ፡ከዳዊት፡ወንድሞች፡ኤሊሁ፤በይሳኮር፡ላይ፡የሚካኤል፡ልጅ፡ዖምሪ፤
19፤በዛብሎን፡ላይ፡የዐብድዩ፡ልጅ፡ይሽማያ፤በንፍታሌም፡ላይ፡የዓዝሪኤል፡ልጅ፡ኢያሪሙት፤
20፤በኤፍሬም፡ልጆች፡ላይ፡የዓዛዝያ፡ልጅ፡ሆሴዕ፤በምናሴ፡ነገድ፡እኩሌታ፡ላይ፡የፈዳያ፡ልጅ፡ኢዮኤል፤
21፤በገለዓድ፡ባለው፡በምናሴ፡ነገድ፡እኩሌታ፡ላይ፡የዘካርያስ፡ልጅ፡አዶ፤በብንያም፡ላይ፡የአበኔር፡ልጅ፡የ ዕሢኤል፤
22፤በዳን፡ላይ፡የይሮሐም፡ልጅ፡ዓዛርኤል፤እነዚህ፡የእስራኤል፡ልጆች፡ነገዶች፡አለቃዎች፡ነበሩ።
23፤እግዚአብሔር፡ግን፡እስራኤልን፡እንደሰማይ፡ከዋክብት፡ያበዛ፡ዘንድ፡ተናግሮ፡ነበርና፥ዳዊት፡ከኻያ፡ዓመ ት፡በታች፡የነበሩትን፡አልቈጠረም።
24፤የጽሩያ፡ልጅ፡ኢዮአብ፡መቍጠር፡ዠመረ፥ነገር፡ግን፥አልፈጸመም፤ስለዚህም፡በእስራኤል፡ላይ፡ቍጣ፡ኾነ፥ቍ ጥራቸውም፡በንጉሡ፡በዳዊት፡መዝገብ፡አልተጻፈም።
25፤በንጉሡም፡ቤተ፡መዛግብት፡ላይ፡የዓዲኤል፡ልጅ፡ዓዝሞት፡ሹም፡ነበረ፤በሜዳውም፡በከተማዎችም፡በመንደሮች ም፡በግንቦችም፡ቤተ፡መዛግብት፡ላይ፡የዖዝያ፡ልጅ፡ዮናታን፡ሹም፡ነበረ፤
26፤መሬቱን፡የሚያበጃጁትና፡ዕርሻውን፡በሚያርሱት፡ላይ፡የክሉብ፡ልጅ፡ዔዝሪ፡ሹም፡ነበረ፤
27፤በወይንም፡ቦታዎች፡ላይ፡ራማታዊው፡ሰሜኢ፡ሹም፡ነበረ፤ለወይንም፡ጠጅ፡ዕቃ፡ቤት፡በሚኾነው፡በወይኑ፡ሰብ ል፡ላይ፡ሸፋማዊው፡ዘብዲ፡ሹም፡ነበረ፤
28፤በቈላውም፡ውስጥ፡ባሉት፡በወይራውና፡በሾላው፡ዛፎች፡ላይ፡ጌድራዊው፡በአልሐናን፡ሹም፡ነበረ፤በዘይቱም፡ ቤቶች፡ላይ፡ኢዮአስ፡ሹም፡ነበረ፤
29፤በሳሮንም፡በሚሰማሩ፡ከብቶች፡ላይ፡ሳሮናዊው፡ሰጥራይ፡ሹም፡ነበረ፤በሸለቆዎቹም፡ውስጥ፡በነበሩት፡ከብቶ ች፡ላይ፡የዓድላይ፡ልጅ፡ሻፍጥ፡ሹም፡ነበረ፤
30፤በግመሎችም፡ላይ፡እስማኤላዊው፡ኡቢያስ፡ሹም፡ነበረ፤በአህያዎቹም፡ላይ፡ሜሮኖታዊው፡ይሕድያ፡ሹም፡ነበረ ፤
31፤በመንጋዎቹም፡ላይ፡አጋራዊው፡ያዚዝ፡ሹም፡ነበረ።እነዚህ፡ዅሉ፡በንጉሡ፡በዳዊት፡ሀብት፡ላይ፡ሹሞች፡ነበ ሩ።
32፤አስተዋይና፡ጸሓፊ፡የነበረው፡የዳዊት፡አጎት፡ዮናታን፡አማካሪ፡ነበረ፤የሐክሞኒም፡ልጅ፡ይሒኤል፡ከንጉሡ ፡ልጆች፡ጋራ፡ነበረ፤
33፤አኪጦፌልም፡የንጉሡ፡አማካሪ፡ነበረ፤አርካዊውም፡ኩሲ፡የንጉሡ፡ወዳጅ፡ነበረ፤
34፤ከአኪጦፌልም፡ቀጥሎ፡የበናያስ፡ልጅ፡ዮዳዔና፡አብያታር፡ነበሩ፤ኢዮአብም፡የንጉሡ፡ሰራዊት፡አለቃ፡ነበረ ።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡28።______________
ምዕራፍ፡28።
1፤ዳዊትም፡የእስራኤልን፡አለቃዎች፡ዅሉ፥የነገዶቹንም፡አለቃዎች፥ንጉሡንም፡በክፍል፡የሚያገለግሉትን፡የጭፍ ራዎች፡አለቃዎች፥ሻለቃዎቹንም፥የመቶ፡አለቃዎችንም፥በንጉሥና፡በልጆች፡ሀብትና፡ግዛት፡ላይ፡የተሾሙትን፥ጃ ን፡ደረባዎችንም፥ጽኑዓን፡ኀያላኑንም፡ዅሉ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ሰበሰበ።
2፤ንጉሡም፡ዳዊት፡በእግሩ፡ቆሞ፡እንዲህ፡አለ፦ወንድሞቼና፡ሕዝቤ፡ሆይ፥ስሙኝ፤ለእግዚአብሔር፡ለቃል፡ኪዳኑ፡ ታቦትና፡ለአምላካችን፡እግር፡ማረፊያ፡የዕረፍት፡ቤት፡ለመሥራት፡እኔ፡በልቤ፡ዐስቤያለኹ፤ለሥራም፡የሚያስፈ ልገውን፡አዘጋጅቻለኹ፤
3፤እግዚአብሔር፡ግን፦የሰልፍ፡ሰው፡ነኽና፥ደምም፡አፍሰ፟ኻልና፥ለስሜ፡ቤት፡አትሠራም፡ብሎኛል።
4፤ነገር፡ግን፥የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡በእስራኤል፡ላይ፡የዘለዓለም፡ንጉሥ፡እኾን፡ዘንድ፡ከአባቴ ፡ቤት፡ዅሉ፡መርጦኛል፤ይሁዳም፡አለቃ፡ይኾን፡ዘንድ፡መርጦታል፤ከይሁዳም፡ቤት፡የአባቴን፡ቤት፡መርጧል፤ከአ ባቴም፡ልጆች፡መካከል፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ላይ፡ያነግሠኝ፡ዘንድ፡ሊመርጠኝ፡ወደደ።
5፤እግዚአብሔርም፡ብዙ፡ልጆች፡ሰጥቶኛልና፥ከልጆቼ፡ዅሉ፡በእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ዙፋን፡ላይ፡ተቀምጦ፡በእ ስራኤል፡ላይ፡ይነግሥ፡ዘንድ፡ልጄን፡ሰሎሞንን፡መርጦታል።
6፤ርሱም፦ልጅ፡ይኾነኝ፡ዘንድ፡መርጬዋለኹና፥እኔም፡አባት፡እኾነዋለኹና፡ልጅኽ፡ሰሎሞን፡ቤቴንና፡አደባባዮቼ ን፡ይሠራል።
7፤ትእዛዜንና፡ፍርዴንም፡በማድረግ፡እንደ፡ዛሬው፡ቢጸና፡መንግሥቱን፡ለዘለዓለም፡አጸናዋለኹ፡አለኝ።
8፤አኹንም፡የእግዚአብሔር፡ጉባኤ፡እስራኤል፡ዅሉ፡እያዩ፥አምላካችንም፡እየሰማ፥ይህችን፡መልካሚቱን፡ምድር፡ ትወርሱ፡ዘንድ፥ለልጆቻችኹም፡ለዘለዓለም፡ታወርሷት፡ዘንድ፡የአምላካችኹን፡የእግዚአብሔርን፡ትእዛዝ፡ዅሉ፡ ጠብቁ፥ፈልጉም።
9፤አንተም፥ልጄ፡ሰሎሞን፡ሆይ፥እግዚአብሔር፡ልብን፡ዅሉ፡ይመረምራልና፥የነፍስንም፡ዐሳብ፡ዅሉ፡ያውቃልና፥የ አባትኽን፡አምላክ፡ዕወቅ፤በፍጹም፡ልብና፡በነፍስኽ፡ፈቃድም፡አምልከው፤ብትፈልገው፡ታገኘዋለኽ፤ብትተወው፡ ግን፡ለዘለዓለም፡ይጥልኻል።
10፤አኹንም፥እንሆ፥እግዚአብሔር፡ለመቅደስ፡የሚኾን፡ቤትን፡ትሠራ፡ዘንድ፡መርጦኻልና፥ጠንክረኽ፡ፈጽመው።
11፤ዳዊትም፡ለመቅደሱ፡ወለል፥ለቤቱም፥ለቤተ፡መዛግብቱም፥ለደርቡና፡ለውስጡም፡ጓዳዎች፥ለስርየቱም፡መክደኛ ፡መቀመጫ፡ምሳሌውን፡ለልጁ፡ለሰሎሞን፡ሰጠው።
12፤ደግሞም፡ለእግዚአብሔር፡ቤት፡አደባባዮችና፡በዙሪያው፡ለሚኾኑ፡ጓዳዎች፥ለእግዚአብሔርም፡ቤት፡ለሚኾኑ፡ ቤተ፡መዛግብት፥ለንዋየ፡ቅድሳቱም፡ለሚኾኑ፡ቤተ፡መዛግብት፡በመንፈሱ፡ላሰበው፡ዅሉ፡ምሳሌን፡ሰጠው።
13፤14፤የካህናቱንና፡የሌዋውያኑንም፡ክፍላቸውን፡በእግዚአብሔርም፡ቤት፡በሚያገለግሉበት፡ሥራ፡ዅሉ፡አስታወ ቀው።በእግዚአብሔርም፡ቤት፡ለሚያገለግሉበት፡ዕቃ፡ዅሉ፥ለአገልግሎት፡ዅሉ፡ለሚኾነውም፡ለወርቁ፡ዕቃ፡ወርቁ ን፡በሚዛን፡ሰጠው፤ለአገልግሎት፡ዅሉ፡ለሚኾነውም፡ለብር፡ዕቃ፡ዅሉ፡ብሩን፡በሚዛን፡ሰጠው፤
15፤ለወርቁም፡መቅረዞችና፡ለቀንዲሎችም፡ወርቁን፡በየመቅረዙና፡በየቀንዲሉ፡በሚዛን፡ሰጠው፤ለብሩም፡መቅረዞ ች፡እንደ፡መቅረዙ፡ዅሉ፡ሥራ፡ዅሉ፡ብሩን፡በየመቅረዙና፡በየቀንዲሉ፡በሚዛን፡ሰጠው፤
16፤ለገጹ፡ኅብስት፡ገበታዎች፡ወርቁን፡በሚዛን፡ለገበታዎቹ፡ዅሉ፥ብሩንም፡ለብሩ፡ገበታዎች፡ሰጠው፤
17፤ለሜንጦቹና፡ለድስቶቹ፡ለመቅጃዎቹም፡ጥሩውን፡ወርቅ፥ለወርቁም፡ጽዋዎች፡ወርቁን፡በየጽዋው፡ዅሉ፡በሚዛን ፥ለብሩም፡ጽዋዎች፡ብሩን፡በየጽዋው፡ዅሉ፡በሚዛን፡ሰጠው፤
18፤ለዕጣኑም፡መሠዊያ፡ጥሩውን፡ወርቅ፡በሚዛን፥ክንፎቻቸውንም፡ዘርግተው፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦ ት፡የሸፈኑትን፡የኪሩቤልን፡የወርቅ፡ሠረገላ፡ምሳሌ፡ሰጠው።
19፤ዳዊትም፦የሥራውን፡ዅሉ፡ምሳሌ፡ዐውቅ፡ዘንድ፡ይህ፡ዅሉ፡በእግዚአብሔር፡እጅ፡ተጽፎ፡መጣልኝ፡አለ።
20፤ዳዊትም፡ልጁን፡ሰሎሞንን፦ጠንክር፥አይዞኽ፥አድርገውም፤አምላኬ፡እግዚአብሔር፡አምላክ፡ከአንተ፡ጋራ፡ነ ውና፥አትፍራ፥አትደንግጥም፤ለእግዚአብሔርም፡ቤት፡አገልግሎት፡የሚኾነው፡ሥራ፡ዅሉ፡እስኪፈጸም፡ድረስ፡ርሱ ፡አይተውኽም፥አይጥልኽምም።
21፤እንሆም፥ለእግዚአብሔር፡ቤት፡አገልግሎት፡ዅሉ፡የሚኾኑ፡የካህናትና፡የሌዋውያን፡ክፍሎች፡በዚህ፡አሉ፤ለ ዅሉም፡ዐይነት፡አገልግሎትና፡ሥር፡በብልኀትና፡በነፍሱ፡ፈቃድ፡የሚሠራ፡ዅሉ፡ከአንተ፡ጋራ፡ይኾናል፤አለቃዎ ችና፡ሕዝቡም፡ዅሉ፡ፈጽመው፡ይታዘዙኻል፡አለው።
_______________መጽሐፈ፡ዜና፡መዋዕል፡ቀዳማዊ፥ምዕራፍ፡29።______________
ምዕራፍ፡29።
1፤ንጉሡም፡ዳዊት፡ለጉባኤው፡ዅሉ፡እንዲህ፡አለ፦እግዚአብሔር፡ብቻውን፡የመረጠው፡ልጄ፡ሰሎሞን፡ገና፡ብላቴና ፡ለጋ፡ነው፤ሕንፃው፡ግን፡ለእግዚአብሔር፡ለአምላክ፡ነው፡እንጂ፡ለሰው፡አይደለምና፡ሥራው፡ታላቅ፡ነው።
2፤እኔም፡እንደ፡ጕልበቴ፡ዅሉ፡ለአምላኬ፡ቤት፡ለወርቁ፡ዕቃ፡ወርቁን፥ለብሩም፡ዕቃ፡ብሩን፥ለናሱም፡ዕቃ፡ናሱ ን፥ለብረቱም፡ዕቃ፡ብረቱን፥ለዕንጨቱም፡ዕቃ፡ዕንጨቱን፥ደግሞም፡መረግድንና፡በፈርጥ፡የሚገባ፡ድንጋይን፥የ ሚለጠፍ፡ድንጋይን፥ልዩ፡ልዩ፡መልክ፡ያለውንም፡ድንጋይ፥የከበረውንም፡ድንጋይ፡ከየዐይነቱ፥ብዙም፡እብነ፡በ ረድ፡አዘጋጅቻለኹ።
3፤ከዚህም፡በላይ፡ደግሞ፡የአምላኬን፡ቤት፡ስለ፡ወደድኹ፥ለመቅደሱ፡ካዘጋጀኹት፡ዅሉ፡ሌላ፡የግል፡ገንዘቤ፡የ ሚኾን፡ወርቅና፡ብር፡አለኝና፡ለአምላኬ፡ቤት፡ሰጥቼዋለኹ።
4፤የቤቶቹ፡ግንብ፡ይለበጡበት፡ዘንድ፡ከኦፊር፡ወርቅ፡ሦስት፡ሺሕ፡መክሊት፡ወርቅ፥ሰባት፡ሺሕም፡መክሊት፡ጥሩ ፡ብር፥
5፤በሠራተኛዎች፡እጅ፡ለሚሠራው፡ሥራ፡ዅሉ፡ለወርቁ፡ዕቃ፡ወርቁን፥ለብሩም፡ዕቃ፡ብሩን፡ሰጥቻለኹ።ዛሬ፡በፈቃ ዱ፡ራሱን፡ለእግዚአብሔር፡የሚቀድስ፡ማነው፧
6፤የአባቶችም፡ቤቶች፡አለቃዎች፥የእስራኤልም፡ነገዶች፡አለቃዎች፥ሻለቃዎችም፥የመቶ፡አለቃዎችም፥በንጉሡም፡ ሥራ፡ላይ፡የተሾሙት፡በፈቃዳቸው፡አቀረቡ።
7፤ለእግዚአብሔርም፡ቤት፡አገልግሎት፡ዐምስት፡ሺሕ፡መክሊት፡ወርቅና፡ዐሥር፡ሺሕ፡ዳሪክ፥ዐሥር፡ሺሕም፡መክሊ ት፡ብር፥ዐሥራ፡ስምንት፡ሺሕም፡መክሊት፡ናስ፥መቶ፡ሺሕም፡መክሊት፡ብረት፡ሰጡ።
8፤ዕንቍም፡ያለው፡ሰው፡ዅሉ፡ለእግዚአብሔር፡ቤት፡ለኾነው፡ቤተ፡መዛግብት፡በጌድሶናዊው፡በይሒኤል፡እጅ፡ሰጠ ።
9፤ሕዝቡም፡ፈቅደው፡ሰጥተዋልና፥በፍጹም፡ልባቸውም፡ለእግዚአብሔር፡በፈቃዳቸው፡አቅርበዋልና፥ደስ፡አላቸው፤ ንጉሡም፡ዳዊት፡ደግሞ፡ታላቅ፡ደስታ፡ደስ፡አለው።
10፤ዳዊትም፡በጉባኤው፡ዅሉ፡ፊት፡እግዚአብሔርን፡ባረከ፤ዳዊትም፡አለ፦አቤቱ፥የአባታችን፡የእስራኤል፡አምላ ክ፡ሆይ፥ከዘለዓለም፡እስከ፡ዘለዓለም፡ተባረክ።
11፤አቤቱ፥በሰማይና፡በምድር፡ያለው፡ዅሉ፡የአንተ፡ነውና፥ታላቅነትና፡ኀይል፥ክብርም፥ድልና፡ግርማ፡ለአንተ ፡ነው፤አቤቱ፥መንግሥት፡የአንተ፡ነው፥አንተም፡በዅሉ፡ላይ፡ከፍ፡ከፍ፡ያልኽ፡ራስ፡ነኽ።
12፤ባለጠግነትና፡ክብር፡ከአንተ፡ዘንድ፡ነው፥አንተም፡ዅሉን፡ትገዛለኽ፤ኀይልና፡ብርታት፡በእጅኽ፡ነው፤ታላ ቅ፡ለማድረግ፥ለዅሉም፡ኀይልን፡ለመስጠት፡በእጅኽ፡ነው።
13፤አኹንም፡እንግዲህ፥አምላካችን፡ሆይ፥እንገዛልኻለን፥ለክቡር፡ስምኽም፡ምስጋና፡እናቀርባለን።
14፤ዅሉ፡ከአንተ፡ዘንድ፡ነውና፥ከእጅኽም፡የተቀበልነውን፡ሰጥተንኻልና፥ይህን፡ያኽል፡ችለን፡ልናቀርብልኽ፡ እኔ፡ማን፡ነኝ፧ሕዝቤስ፡ማን፡ነው፧
15፤አባቶቻችንም፡ዅሉ፡እንደነበሩ፡እኛ፡በፊትኽ፡ስደተኛዎችና፡መጻተኛዎች፡ነን፤ዘመናችንም፡በምድር፡ላይ፡ እንደ፡ጥላ፡ናት፥አትጸናም።
16፤አቤቱ፡አምላካችን፡ሆይ፥ለቅዱስ፡ስምኽ፡ቤት፡እንሠራ፡ዘንድ፡ይህ፡ያዘጋጀነው፡ባለጠግነት፡ዅሉ፡ከእጅኽ ፡የመጣ፡ነው፥ዅሉም፡የአንተ፡ነው።
17፤አምላኬ፡ሆይ፥ልብን፡እንድትመረምር፥ቅንነትንም፡እንድትወድ፟፡ዐውቃለኹ፤እኔም፡በልቤ፡ቅንነትና፡በፈቃ ዴ፡ይህን፡ዅሉ፡አቅርቤያለኹ፤አኹንም፡በዚህ፡ያለው፡ሕዝብኽ፡በፈቃዱ፡እንዳቀረበልኽ፡በደስታ፡አይቻለኹ።
18፤አቤቱ፥የአባቶቻችን፡የአብርሃምና፡የይሥሐቅ፡የእስራኤልም፡አምላክ፡ሆይ፥ይህን፡ዐሳብ፡በሕዝብኽ፡ልብ፡ ለዘለዓለም፡ጠብቅ፥ልባቸውንም፡ወዳንተ፡አቅና።
19፤ትእዛዝኽንም፡ምስክርኽንም፡ሥርዐትኽንም፡ይጠብቅ፡ዘንድ፥ይህንም፡ነገር፡ዅሉ፡ያደርግ፡ዘንድ፥ያዘጋጀኹ ለትንም፡ቤት፡ይሠራ፡ዘንድ፡ለልጄ፡ለሰሎሞን፡ፍጹም፡ልብ፡ስጠው።
20፤ዳዊትም፡ጉባኤውን፡ዅሉ፦አምላካችኹን፡እግዚአብሔርን፡ባርኩ፡አላቸው።ጉባኤውም፡ዅሉ፡የአባታቸውን፡አም ላክ፡እግዚአብሔርን፡ባረኩ፥ራሳቸውንም፡አዘንብለው፡ለእግዚአብሔርና፡ለንጉሡ፡ሰገዱ።
21፤በነጋውም፡ለእግዚአብሔር፡መሥዋዕት፡ሠዉ፥የሚቃጠለውንም፡መሥዋዕት፡ለእግዚአብሔር፡አቀረቡ፤አንድ፡ሺሕ ፡ወይፈን፥አንድ፡ሺሕም፡አውራ፡በጎች፥አንድ፡ሺሕም፡የበግ፡ጠቦቶች፥የመጠጥ፡ቍርባናቸውንም፥ስለ፡እስራኤል ም፡ዅሉ፡ብዙ፡መሥዋዕት፡አቀረቡ።
22፤በዚያም፡ቀን፡በታላቅ፡ደስታ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡በሉ፡ጠጡም።የዳዊትንም፡ልጅ፡ሰሎሞንን፡ኹለተኛ፡ጊዜ ፡አነገሡት፤ርሱንም፡አለቃ፡ይኾን፡ዘንድ፡ለእግዚአብሔር፡ቀቡት፥ሳዶቅንም፡ካህን፡ይኾን፡ዘንድ፡ቀቡት።
23፤ሰሎሞንም፡በአባቱ፡በዳዊት፡ዙፋን፡ላይ፡ተቀመጠ፥ተከናወነለትም፤እስራኤልም፡ዅሉ፡ታዘዙለት።
24፤አለቃዎቹም፡ዅሉ፥ኀያላኑም፥ደግሞም፡የንጉሡ፡የዳዊት፡ልጆች፡ዅሉ፡ለንጉሡ፡ለሰሎሞን፡እጅ፡ሰጡት።
25፤እግዚአብሔርም፡ሰሎሞንን፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ፊት፡እጅግ፡አገነነው፤ከርሱ፡በፊትም፡ለነበሩት፡ለእስራኤል ፡ነገሥታት፡ያልኾነውን፡የመንግሥት፡ክብር፡ሰጠው።
26፤የእሴይም፡ልጅ፡ዳዊት፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ላይ፡ነገሠ።
27፤በእስራኤልም፡ላይ፡የነገሠበት፡ዘመን፡አርባ፡ዓመት፡ነበረ፤ሰባት፡ዓመት፡በኬብሮን፡ነገሠ፥ሠላሳ፡ሦስት ም፡ዓመት፡በኢየሩሳሌም፡ነገሠ።
28፤ዕድሜም፥ባለጠግነትም፥ክብርም፡ጠግቦ፡በመልካም፡ሽምግልና፡ሞተ፤ልጁም፡ሰሎሞን፡በርሱ፡ፋንታ፡ነገሠ።
29፤የንጉሡም፡የዳዊት፡የፊተኛውና፡የዃለኛው፡ነገር፥እንሆ፥በባለራእዩ፡በሳሙኤል፡ታሪክ፥በነቢዩም፡በናታን ፡ታሪክ፥በባለራእዩም፡በጋድ፡ታሪክ፡ተጽፏል።
30፤እንደዚሁም፡የመንግሥቱ፡ነገርና፡ኀይሉ፡ዅሉ፡በርሱም፡በእስራኤልም፡በአገሮችም፡መንግሥታት፡ዅሉ፡ላይ፡ ያለፉት፡ዘመናት፡ተጽፈዋል፨

http://www.gzamargna.net