መጽሐፈ፡መክብብ።

(ክለሳ.1.20020507)

_______________መጽሐፈ፡መክብብ፥ምዕራፍ፡1።______________
ምዕራፍ፡1።
1፤በኢየሩሳሌም፡የነገሠ፡የሰባኪው፡የዳዊት፡ልጅ፡ቃል።
2፤ሰባኪው፦ከንቱ፥ከንቱ፥የከንቱ፡ከንቱ፥ዅሉ፡ከንቱ፡ነው፡ይላል።
3፤ከፀሓይ፡በታች፡በሚደክምበት፡ድካም፡ዅሉ፡የሰው፡ትርፉ፡ምንድር፡ነው፧
4፤ትውልድ፡ይኼዳል፥ትውልድም፡ይመጣል፤ምድር፡ግን፡ለዘለዓለም፡ነው።
5፤ፀሓይ፡ትወጣለች፥ፀሓይም፡ትገባለች፥ወደምትወጣበትም፡ስፍራ፡ትቸኵላለች።
6፤ነፋስ፡ወደ፡ደቡብ፡ይኼዳል፥ወደ፡ሰሜንም፡ይዞራል፤ዘወትር፡በዙረቱ፡ይዞራል፥ነፋስም፡በዙረቱ፡ደግሞ፡ይመ ለሳል።
7፤ፈሳሾች፡ዅሉ፡ወደ፡ባሕር፡ይኼዳሉ፥ባሕሩ፡ግን፡አይሞላም፤ፈሳሾች፡ወደሚኼዱበት፡ስፍራ፡እንደ፡ገና፡ወደዚ ያ፡ይመለሳሉ።
8፤ነገር፡ዅሉ፡ያደክማል፡ሰው፡ይናገረው፡ዘንድ፡አይችልም፤ዐይን፡ከማየት፡አይጠግብም፥ዦሮም፡ከመስማት፡አይ ሞላም።
9፤የኾነው፡ነገር፡ርሱ፡የሚኾን፡ነው፥የተደረገውም፡ነገር፡ርሱ፡የሚደረግ፡ነው፤ከፀሓይም፡በታች፡ዐዲስ፡ነገ ር፡የለም።
10፤ማንም፦እንሆ፥ይህ፡ነገር፡ዐዲስ፡ነው፡ይል፡ዘንድ፡ይችላልን፧ርሱ፡ከእኛ፡በፊት፡በነበሩት፡ዘመናት፡ተደ ርጓል።
11፤ለፊተኛዎቹ፡ነገሮች፡መታሰቢያ፡የላቸውም፤ከዃለኛዎቹም፡ነገሮች፡ከነርሱ፡በዃላ፡በሚነሡት፡ሰዎች፡ዘንድ ፡መታሰቢያ፡አይገኝላቸውም።
12፤እኔ፡ሰባኪው፡በእስራኤል፡ላይ፡በኢየሩሳሌም፡ንጉሥ፡ነበርኹ።
13፤ከሰማይም፡በታች፡የተደረገውን፡ዅሉ፡በጥበብ፡እፈልግና፡እመረምር፡ዘንድ፡ልቤን፡አተጋኹ፤እግዚአብሔር፡ ይደክሙባት፡ዘንድ፡ይህችን፡ለሰው፡ልጆች፡የሰጠ፡ክፉ፡ጥረት፡ናት።
14፤ከፀሓይ፡በታች፡የተሠራውን፡ሥራ፡ዅሉ፡አየኹ፤እንሆም፥ዅሉ፡ከንቱ፡ነው፥ነፋስንም፡እንደ፡መከተል፡ነው።
15፤ጠማማ፡ይቀና፡ዘንድ፡አይችልም፤ጐደሎም፡ይቈጠር፡ዘንድ፡አይችልም።
16፤እኔ፡በልቤ፦እንሆ፥ከእኔ፡አስቀድመው፡በኢየሩሳሌም፡ላይ፡ከነበሩት፡ዅሉ፡ይልቅ፡ጥበብን፡አብዝቼ፡ጨመር ኹ፤ልቤም፡ብዙ፡ጥበብንና፡ዕውቀትን፡ተመለከተ፡ብዬ፡ተናገርኹ።
17፤ጥበብንና፡እብደትን፡ሞኝነትንም፡ዐውቅ፡ዘንድ፡ልቤን፡ሰጠኹ፤ይህም፡ደግሞ፡ነፋስን፡እንደ፡መከተል፡እን ደ፡ኾነ፡አስተዋልኹ።
18፤በጥበብ፡መብዛት፡ትካዜ፡ይበዛልና፤ዕውቀትንም፡የሚጨምር፡ሐዘንን፡ይጨምራልና።
_______________መጽሐፈ፡መክብብ፥ምዕራፍ፡2።______________
ምዕራፍ፡2።
1፤እኔ፡በልቤ፦ና፥በደስታም፡እፈትንኻለኹ፥መልካምንም፡ቅመስ፡አልኹ፤ይህም፡ደግሞ፥እንሆ፥ከንቱ፡ነበረ።
2፤ሣቅን፦እብድ፡ነኽ፤ደስታንም፦ምን፡ታደርጋለኽ፧አልኹት።
3፤የሰው፡ልጆች፡በሕይወታቸው፡ዘመን፡ዅሉ፡ከፀሓይ፡በታች፡ሊሠሩት፡መልካም፡ነገር፡ምን፡እንደ፡ኾነ፡እስካይ ፡ድረስ፥ልቤ፡በጥበብ፡እየመራኝ፥ሰውነቴን፡በወይን፡ጠጅ፡ደስ፡ለማሠኘት፥ስንፍናንም፡ለመያዝ፡በልቤ፡መረመ ርኹ።
4፤ትልቅ፡ሥራን፡ሠራኹ፥ቤቶችንም፡አደረግኹ፥ወይንም፡ተከልኹ፤
5፤አትክልትንና፡ገነትን፡አደረግኹ፥ልዩ፡ልዩ፡ፍሬ፡ያለባቸውንም፡ዛፎች፡ተከልኹባቸው፤
6፤በዱር፡የተተከሉትን፡ዛፎች፡አጠጣበት፡ዘንድ፡የውሃ፡ማጠራቀሚያ፡አደረግኹ።
7፤ወንዶችንና፡ሴቶችን፡ባሪያዎች፡ገዛኹ፥የቤት፡ውልድ፡ባሪያዎችም፡ነበሩኝ፤ከእኔ፡አስቀድመው፡በኢየሩሳሌም ፡ከነበሩት፡ዅሉ፡ይልቅ፡ብዙ፡ከብቶችና፡መንጋዎች፡ነበሩኝ።
8፤ብርንና፡ወርቅን፡የከበረውንም፡የነገሥታትና፡የአውራጃዎችን፡መዝገብ፡ሰበሰብኹ፤አዝማሪዎችንና፡አረኾዎች ን፡የሰዎች፡ልጆችንም፡ተድላ፡እጅግ፡የበዙ፡ሴቶችንም፡አከማቸኹ።
9፤ታላቅም፡ኾንኹ፥ከእኔም፡አስቀድመው፡በኢየሩሳሌም፡ከነበሩት፡ዅሉ፡ይልቅ፡ከበርኹ፤ደግሞም፡ጥበቤ፡ከእኔ፡ ጋራ፡ጸንታ፡ቀረች።
10፤ዐይኖቼንም፡ከፈለጉት፡ዅሉ፡አልከለከልዃቸውም፤ልቤም፡በድካሜ፡ዅሉ፡ደስ፡ይለው፡ነበርና፥ልቤን፡ከደስታ ፡ዅሉ፡አላራቅኹትም፥ከድካሜም፡ዅሉ፡ይህ፡ዕድል፡ፈንታዬ፡ኾነ።
11፤እጄ፡የሠራቻትን፡ሥራዬን፡ዅሉ፡የደከምኹበትንም፡ድካሜን፡ዅሉ፡ተመለከትኹ፤እንሆ፥ዅሉ፡ከንቱ፡ነፋስንም ፡እንደ፡መከተል፡ነበር፥ከፀሓይ፡በታችም፡ትርፍ፡አልነበረም።
12፤እኔም፡ጥበብን፡እብደትንና፡ስንፍናን፡አይ፡ዘንድ፡ተመለከትኹ፤በፊት፡ከተደረገው፡በቀር፥ከንጉሥ፡በዃላ ፡የሚመጣው፡ሰው፡ምን፡ያደርጋል፧
13፤እኔም፡ብርሃን፡ከጨለማ፡እንደሚበልጥ፡እንዲሁ፡ጥበብ፡ከስንፍና፡እንዲበልጥ፡አየኹ።
14፤የጠቢብ፡ዐይኖች፡በራሱ፡ላይ፡ናቸው፥ሰነፍ፡ግን፡በጨለማ፡ይኼዳል፤ደግሞ፡ለኹለቱ፡መጨረሻቸው፡አንድ፡እ ንደ፡ኾነ፡አስተዋልኹ።
15፤እኔም፡በልቤ፦ለሰነፍ፡የሚደርሰው፡ለኔም፡ይደርሳል፤ለምን፡እጅግ፡ጠቢብ፡ኾንኹ፧አልኹ።የዚያን፡ጊዜም፡ በልቤ፦ይህ፡ደግሞ፡ከንቱ፡ነው፡አልኹ።
16፤በሚመጣው፡ዘመን፡ነገር፡ዅሉ፡የተረሳ፡ይኾናልና፥ለዘለዓለም፡የሚኾን፡የጠቢብና፡የሰነፍ፡መታሰቢያ፡አይ ገኝም።አዬ፡ጕድ! ጠቢብ፡ከሰነፍ፡ጋራ፡እንዴት፡ይሞታል!
17፤ከፀሓይም፡በታች፡የተሠራው፡ሥራ፡ዅሉ፡ከብዶብኛልና፥ሕይወትን፡ጠላኹ፤ዅሉም፡ከንቱ፡ነፋስንም፡እንደ፡መ ከተል፡ነው።
18፤ከእኔ፡በዃላ፡ለሚመጣው፡ሰው፡እተወዋለኹና፡ከፀሓይ፡በታች፡የደከምኹበትን፡ዅሉ፡ጠላኹት።
19፤ጠቢብ፡ወይም፡ሰነፍ፡እንዲኾን፡የሚያውቅ፡ሰው፡ማን፡ነው፧ከፀሓይ፡በታች፡በደከምኹበትና፡ጠቢብ፡በኾንኹ በት፡በድካሜ፡ዅሉ፡ላይ፡ጌታ፡ይኾንበታል፤ይህም፡ደግሞ፡ከንቱ፡ነው።
20፤እኔም፡ተመልሼ፡ልቤን፡ከፀሓይ፡በታች፡በደከምኹበት፡ድካም፡ዅሉ፡ተስፋ፡አስቈረጥኹት።
21፤ሰው፡በጥበብና፡በዕውቀት፡በብልኀትም፡ከደከመ፡በዃላ፡ለሌላ፡ላልደከመበት፡ሰው፡ያወርሰዋልና፤ይህም፡ደ ግሞ፡ከንቱ፡ትልቅም፡መከራ፡ነው።
22፤ከፀሓይ፡በታች፡በደከመበት፡ድካም፡ዅሉና፡በልቡ፡ዐሳብ፡የሰው፡ጥቅም፡ምንድር፡ነው፧
23፤ዘመኑ፡ዅሉ፡ሐዘን፥ጥረትም፡ትካዜ፡ነው፤ልቡም፡በሌሊት፡አይተኛም፤ይህም፡ደግሞ፡ከንቱ፡ነው።
24፤ለሰው፡ከሚበላና፡ከሚጠጣ፡በድካሙም፡ደስ፡ከሚለው፡በቀር፡የሚሻለው፡ነገር፡የለም፤ይህም፡ደግሞ፡ከእግዚ አብሔር፡እጅ፡እንደ፡ተሰጠ፡አየኹ።
25፤ያለርሱ፡ፈቃድ፡የበላ፡ደስ፡ብሎትም፡ተድላን፡የቀመሰ፡ማን፡ነው፧
26፤ርሱም፡ደስ፡ለሚያሠኘው፡ሰው፡ጥበብንና፡ዕውቀትን፡ደስታንም፡ይሰጠዋል፤ለኀጢአተኛ፡ግን፡እግዚአብሔርን ፡ደስ፡ለሚያሠኘው፡ሰው፡ይሰጥ፡ዘንድ፡እንዲሰበስብና፡እንዲያከማች፡ጥረትን፡ይሰጠዋል።ይህም፡ደግሞ፡ከንቱ ፡ነፋስንም፡እንደ፡መከተል፡ነው።
_______________መጽሐፈ፡መክብብ፥ምዕራፍ፡3።______________
ምዕራፍ፡3።
1፤ለዅሉ፡ዘመን፡አለው፥ከሰማይ፡በታችም፡ለኾነ፡ነገር፡ዅሉ፡ጊዜ፡አለው።
2፤ለመወለድ፡ጊዜ፡አለው፥ለመሞትም፡ጊዜ፡አለው፤ለመትከል፡ጊዜ፡አለው፥የተተከለውንም፡ለመንቀል፡ጊዜ፡አለው ፤
3፤ለመግደል፡ጊዜ፡አለው፥ለመፈወስም፡ጊዜ፡አለው፤ለማፍረስ፡ጊዜ፡አለው፥ለመሥራትም፡ጊዜ፡አለው፤
4፤ለማልቀስ፡ጊዜ፡አለው፥ለመሣቅም፡ጊዜ፡አለው፤ዋይ፡ለማለት፡ጊዜ፡አለው፥ለመዝፈንም፡ጊዜ፡አለው፤
5፤ድንጋይን፡ለመጣል፡ጊዜ፡አለው፥ድንጋይንም፡ለመሰብሰብ፡ጊዜ፡አለው፤ለመተቃቀፍ፡ጊዜ፡አለው፥ከመተቃቀፍም ፡ለመራቅ፡ጊዜ፡አለው፤
6፤ለመፈለግ፡ጊዜ፡አለው፥ለማጥፋትም፡ጊዜ፡አለው፤ለመጠበቅ፡ጊዜ፡አለው፥ለመጣልም፡ጊዜ፡አለው፤
7፤ለመቅደድ፡ጊዜ፡አለው፥ለመስፋትም፡ጊዜ፡አለው፤ዝም፡ለማለት፡ጊዜ፡አለው፥ለመናገርም፡ጊዜ፡አለው፤
8፤ለመውደድ፡ጊዜ፡አለው፥ለመጥላትም፡ጊዜ፡አለው፤ለጦርነት፡ጊዜ፡አለው፥ለሰላምም፡ጊዜ፡አለው።
9፤ለሠራተኛ፡የድካሙ፡ትርፍ፡ምንድር፡ነው፧
10፤እግዚአብሔር፡ለሰው፡ልጆች፡ይደክሙበት፡ዘንድ፡የሰጣቸውን፡ጥረት፡አይቻለኹ።
11፤ነገርን፡ዅሉ፡በጊዜው፡ውብ፡አድርጎ፡ሠራው፤እግዚአብሔርም፡ከጥንት፡ዠምሮ፡እስከ፡ፍጻሜ፡ድረስ፡የሠራው ን፡ሥራ፡ሰው፡መርምሮ፡እንዳያገኝ፡ዘለዓለምነትን፡በልቡ፡ሰጠው።
12፤ሰው፡ደስ፡ከሚለውና፡በሕይወቱ፡ሳለ፡መልካምን፡ነገር፡ከሚያደርግ፡በቀር፡መልካም፡ነገር፡እንደሌለ፡ዐወ ቅኹ።
13፤ደግሞም፡ሰው፡ዅሉ፡ይበላና፡ይጠጣ፡ዘንድ፡በድካሙም፡ዅሉ፡ደስ፡ይለው፡ዘንድ፡የእግዚአብሔር፡ስጦታ፡ነው ።
14፤እግዚአብሔር፡ያደረገው፡ዅሉ፡ለዘለዓለም፡እንዲኖር፡ዐወቅኹ፤ሊጨመርበት፡ወይም፡ከርሱ፡ሊጐድል፡አይቻል ም፤እግዚአብሔርም፡በፊቱ፡ይፈሩ፡ዘንድ፡አደረገ።
15፤አኹን፡ያለው፡በፊት፡ነበረ፥የሚኾነውም፡በፊት፡ኾኖ፡ነበር፤እግዚአብሔርም፡ያለፈውን፡መልሶ፡ይሻዋል።
16፤ደግሞም፡ከፀሓይ፡በታች፡በፍርድ፡ስፍራ፡ኀጢአት፥በጽድቅም፡ስፍራ፡ኀጢአት፡እንዳለ፡አየኹ።
17፤እኔም፡በልቤ፦በዚያ፡ለነገር፡ዅሉና፡ለሥራ፡ዅሉ፡ጊዜ፡አለውና፡በጻድቅና፡በኀጢአተኛ፡ላይ፡እግዚአብሔር ፡ይፈርዳል፡አልኹ።
18፤እኔ፡በልቤ፡ስለሰው፡ልጆች፦እንደ፡እንስሳ፡መኾናቸውን፡እንዲያዩ፡እግዚአብሔር፡ይፈትናቸዋል፡አልኹ።
19፤የሰው፡ልጆችና፡የእንስሳ፡ዕድል፡ፈንታ፡አንድ፡ነው፤ድርሻቸውም፡ትክክል፡ነው፤አንዱ፡እንደሚሞት፡ሌላው ም፡እንዲሁ፡ይሞታል፤የዅሉም፡እስትንፋስ፡አንድ፡ነው፤ዅሉም፡ከንቱ፡ነውና፥ሰው፡ከእንስሳ፡ብልጫ፡የለውም።
20፤ዅሉ፡ወደ፡አንድ፡ቦታ፡ይኼዳል፤ዅሉ፡ከዐፈር፡ነው፥ዅሉም፡ወደ፡ዐፈር፡ይመለሳል።
21፤የሰው፡ልጆች፡ነፍስ፡ወደ፡ላይ፡እንደምትወጣ፥የእንስሳም፡ነፍስ፡ወደ፡ታች፡ወደ፡ምድር፡እንደምትወርድ፡ የሚያውቅ፡ማን፡ነው፧
22፤ያም፡ዕድል፡ፈንታው፡ነውና፥ሰው፡በሥራው፡ደስ፡ከሚለው፡በቀር፡ሌላ፡መልካም፡ነገር፡እንደሌለው፡አየኹ፤ ከርሱ፡በዃላስ፡የሚኾነውን፡ያይ፡ዘንድ፡የሚያመጣው፡ማን፡ነው፧
_______________መጽሐፈ፡መክብብ፥ምዕራፍ፡4።______________
ምዕራፍ፡4።
1፤እኔም፡ተመለስኹ፥ከፀሓይ፡በታችም፡የሚደረገውን፡ግፍ፡ዅሉ፡አየኹ፤እንሆም፥የተገፉት፡ሰዎች፡እንባ፡ነበረ ፤የሚያጽናናቸውም፡አልነበረም፤በሚገፏቸውም፡እጅ፡ኀይል፡ነበረ፥እነርሱን፡ግን፡የሚያጽናናቸው፡አልነበረም ።
2፤እኔም፡እስከ፡ዛሬ፡በሕይወት፡ካሉት፡ይልቅ፡በቀድሞ፡ዘመን፡የሞቱትን፡አመሰገንኹ፤
3፤ከነዚህም፡ከኹለቱ፡ይልቅ፡ገና፡ያልተወለደው፡ከፀሓይም፡በታች፡የሚደረገውን፡ግፍ፡ያላየው፡ይሻላል።
4፤ደግሞም፡የሰውን፡ድካምና፡የብልኀት፡ሥራውን፡ዅሉ፡ተመለከትኹ፥በባልንጀራውም፡ዘንድ፡ቅንአት፡እንዲያስነ ሣ፡አየኹ፤ይህም፡ደግሞ፡ከንቱ፡ነፋስንም፡እንደ፡መከተል፡ነው።
5፤ሰነፍ፡እጆቹን፡ኰርትሞ፡ይቀመጣል፤የገዛ፡ሥጋውንም፡ይበላል።
6፤በድካምና፡ነፋስን፡በመከተል፡ከኹለት፡እጅ፡ሙሉ፡ይልቅ፡አንድ፡እጅ፡ሙሉ፡በዕረፍት፡ይሻላል።
7፤እኔም፡ተመለስኹ፥ከፀሓይ፡በታችም፡ከንቱን፡ነገር፡አየኹ።
8፤አንድ፡ሰው፡ብቻውን፡አለ፥ኹለተኛም፡የለውም፡ልጅም፡ኾነ፡ወንድም፡የለውም፤ለድካሙ፡ግን፡መጨረሻ፡የለውም ፥ዐይኖቹም፡ከባለጠግነት፡አይጠግቡም፦ለማን፡እደክማለኹ፥ሰውነቴንስ፡መልካሙን፡ነገር፡ለምን፡እነፍጋታለኹ ፧ይላል።ይህም፡ደግሞ፡ከንቱ፡ነገር፣ክፉም፡ጥረት፡ነው።
9፤ድካማቸው፡መልካም፡ዋጋ፡አለውና፥አንድ፡ብቻ፡ከመኾን፡ኹለት፡መኾን፡ይሻላል።
10፤ቢወድቁ፡አንዱ፡ኹለተኛውን፡ያነሣዋልና፤አንዱ፡ብቻውን፡ኾኖ፡በወደቀ፡ጊዜ፡ግን፡የሚያነሣው፡ኹለተኛ፡የ ለውምና፡ወዮለት።
11፤ኹለቱም፡በአንድነት፡ቢተኙ፥ይሞቃቸዋል፤አንድ፡ብቻውን፡ግን፡እንዴት፡ይሞቀዋል፧
12፤አንዱም፡አንዱን፡ቢያሸንፍ፥ኹለቱ፡በፊቱ፡ይቆማሉ፤በሦስትም፡የተገመደ፡ገመድ፡ፈጥኖ፡አይበጠስም።
13፤ድኻና፡ጠቢብ፡ብላቴና፥ተግሣጽን፡መቀበል፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡ከማያውቅ፡ከሰነፍ፡ሽማግሌ፡ንጉሥ፡ይሻላል ።
14፤ምንም፡በመንግሥቱ፡አገር፡ደግሞ፡ችግረኛ፡ኾኖ፡ቢወለድ፥ከግዞቱ፡ቤት፡ወደ፡መንግሥት፡ወጥቷልና።
15፤ከፀሓይ፡በታች፡የሚኼዱትን፡ሕያዋን፡ዅሉ፡በርሱ፡ፋንታ፡ከሚነሣው፡ከሌላው፡ጐበዝ፡ጋራ፡ኾነው፡አየኹ።
16፤ከርሱ፡በፊት፡የተገዙለት፡ሕዝብ፡ዅሉ፡አይቈጠሩም፤በዃላ፡የሚመጡት፡ግን፡በርሱ፡ደስ፡አይላቸውም።ይህም ፡ደግሞ፡ከንቱ፡ነፋስንም፡እንደ፡መከተል፡ነው።
_______________መጽሐፈ፡መክብብ፥ምዕራፍ፡5።______________
ምዕራፍ፡5።
1፤ወደእግዚአብሔር፡ቤት፡በገባኽ፡ጊዜ፡እግርኽን፡ጠብቅ፤ለመስማት፡መቅረብ፡ከሰነፎች፡መሥዋዕት፡ይበልጣልና ፤እነርሱም፡ክፉ፡እንዲያደርጉ፡አያውቁምና።
2፤እግዚአብሔር፡በሰማይ፥አንተም፡በምድር፡ነኽና፥በአፍኽ፡አትፍጠን፥በእግዚአብሔርም፡ፊት፡ቃልን፡ይናገር፡ ዘንድ፡ልብኽ፡አይቸኵል፤ስለዚህም፡ቃልኽ፡ጥቂት፡ትኹን።
3፤ሕልም፡በሥራ፡ብዛት፡ይታያል፤እንዲሁም፡የሰነፍ፡ድምፅ፡በቃሉ፡ብዛት፡ይሰማል።
4፤ሰነፎች፡ደስ፡አያሠኙትምና፡ለእግዚአብሔር፡ስእለት፡በተሳልኽ፡ጊዜ፡ትፈጽመው፡ዘንድ፡አትዘግይ፤የተሳልኸ ውን፡ፈጽመው።
5፤ተስለኽ፡የማትፈጽም፡ብትኾን፡ባትሳል፡ይሻላል።
6፤ሥጋኽን፡በኀጢአት፡እንዳያስተው፡ለአፍኽ፡ሐራነት፡አትስጥ፥በመልአክም፡ፊት፦ስሕተት፡ነበረ፡አትበል፤እግ ዚአብሔር፡በቃልኽ፡ይቈጣ፡ዘንድ፡የእጅኽንም፡ሥራ፡ያጠፋ፡ዘንድ፡ስለ፡ምን፡ትሻለኽ፧
7፤ብዙ፡ሕልም፡ባለበት፡ዘንድ፥እንዲሁም፡ደግሞ፡ብዙ፡ቃል፡ባለበት፡ስፍራ፡በዚያ፡ብዙ፡ከንቱ፡ነገር፡አለ፤አ ንተ፡ግን፡እግዚአብሔርን፡ፍራ።
8፤ከፍ፡ካለው፡በላይ፡ከፍ፡ያለ፡ይመለከታልና፥ከነርሱም፡በላይ፡ደግሞ፡ሌላዎች፡ከፍ፡ይላሉና፡በአገሩ፡ድኻዎ ች፡ሲገፉ፥ፍርድና፡ጽድቅም፡ሲነጠቅ፡ባየኽ፡ጊዜ፡በዚህ፡ነገር፡አታድንቅ።
9፤በጠቅላላው፡ግን፡የአገሩ፡ጥቅም፡ዕርሻን፡የሚወድ፟፡ንጉሥ፡ቢኖር፡ነው።
10፤ብርን፡የሚወድ፟፡ሰው፡ብርን፡አይጠግብም፤ባለጠግነትንም፡የሚወድ፟፡ትርፉን፡አይጠግብም፤ይህም፡ደግሞ፡ ከንቱ፡ነው።
11፤ሀብት፡ሲበዛ፡የሚበሉት፡ይበዛሉ፤ሀብቱን፡በዐይኑ፡ብቻ፡ከማየት፡በቀር፡ለባለቤቱ፡ምን፡ይጠቅመዋል፧
12፤እጅግ፡ወይም፡ጥቂት፡ቢበላ፡የሠራተኛ፡እንቅልፍ፡ጣፋጭ፡ነው፥የባለጠጋ፡ጥጋብ፡ግን፡እንቅልፍን፡ይከለክ ለዋል።
13፤ከፀሓይ፡በታች፡የሚያሳዝን፡ክፉ፡ነገር፡አየኹ፤ለመከራው፡በባለቤቱ፡ዘንድ፡የተቈጠበች፡ባለጠግነት፡ናት ።
14፤ያችም፡ባለጠግነት፡በክፉ፡ነገር፡ትጠፋለች፤ልጅንም፡ቢወልድ፡በእጁ፡ምንም፡የለውም።
15፤ከእናቱ፡ሆድ፡ዕራቍቱን፡እንደ፡ወጣ፡እንዲሁ፡እንደመጣው፡ይመለሳል፤ከጥረቱም፡በእጁ፡ሊወስድ፡የሚችለው ን፡ምንም፡አያገኝም።
16፤ይህም፡ደግሞ፡የሚያሳዝን፡ክፉ፡ነገር፡ነው፤እንደ፡መጣ፡እንዲሁ፡ይኼዳል፤ድካሙም፡ለነፋስ፡ከኾነ፡ጥቅሙ ፡ምንድር፡ነው፧
17፤ዘመኑን፡ዅሉ፡በጨለማ፡በሐዘን፡በብስጭት፡በደዌና፡በቍጣ፡ነው።
18፤እንሆ፥እኔ፡ያየኹት፡መልካምና፡የተዋበ፡ነገር፡ሰው፡እግዚአብሔር፡በሰጠው፡በሕይወቱ፡ዘመን፡ዅሉ፡ይበላ ና፡ይጠጣ፡ዘንድ፥ከፀሓይ፡በታችም፡በሚደክምበት፡ድካም፡ዅሉ፡ደስ፡ይለው፡ዘንድ፡ነው፤ይህ፡ዕድል፡ፈንታው፡ ነውና።
19፤እግዚአብሔር፡ለሰው፡ዅሉ፡ባለጠግነትንና፡ሀብትን፡መስጠቱ፥ከርሷም፡ይበላና፡ዕድል፡ፈንታውን፡ይወስድ፡ ዘንድ፡በድካሙም፡ደስ፡ይለው፡ዘንድ፡ማሠልጠኑ፤ይህ፡የእግዚአብሔር፡ስጦታ፡ነው።
20፤እግዚአብሔር፡በልቡ፡ደስታን፡ስለ፡ሰጠው፡ርሱ፡የሕይወቱን፡ዘመን፡እጅግ፡አያስብም።
_______________መጽሐፈ፡መክብብ፥ምዕራፍ፡6።______________
ምዕራፍ፡6።
1፤ከፀሓይ፡በታች፡ያየኹት፡ክፉ፡ነገር፡አለ፥ርሱም፡በሰው፡ላይ፡እጅግ፡የከበደ፡ነው።
2፤እግዚአብሔር፡ለሰው፡ሀብትንና፡ጥሪትን፡ክብርንም፡ሰጠው፥ከወደደውም፡ዅሉ፡ለነፍሱ፡አልጐደለውም፤ነገር፡ ግን፥ሌላ፡ሰው፡ይበላዋል፡እንጂ፡ከርሱ፡ይበላ፡ዘንድ፡እግዚአብሔር፡አላሠለጠነውም፤ይህም፡ከንቱና፡ክፉ፡ደ ዌ፡ነው።
3፤ሰው፡መቶ፡ልጆች፡ቢወልድ፡እጅግ፡ዘመንም፡በሕይወት፡ቢኖር፡ዕድሜውም፡እጅግ፡ዓመት፡ቢኾን፥ነፍሱም፡መልካ ምን፡ባትጠግብ፡መቃብርንም፡ባያገኝ፥እኔ፡ስለ፡ርሱ፦ከርሱ፡ይልቅ፡ጭንጋፍ፡ይሻላል፡አልኹ።
4፤በከንቱ፡መጥቷል፡በጨለማ፡ይኼዳል፡ስሙም፡በጨለማ፡ይሸፈናል፤
5፤ደግሞም፡ፀሓይን፡አላየውም፡አላወቀውምም፤ለዚህም፡ከዚያ፡ይልቅ፡ዕረፍት፡አለው።
6፤ሺሕ፡ዓመት፡ኹለት፡ጊዜ፡በሕይወት፡ቢኖር፡መልካምንም፡ባያይ፥ዅሉ፡ወደ፡አንድ፡ስፍራ፡የሚኼድ፡አይደለምን ፧
7፤የሰው፡ድካም፡ዅሉ፡ለአፉ፡ነው፥ነፍሱ፡ግን፡አትጠግብም።
8፤ከሰነፍ፡ይልቅ፡ለጥበበኛ፡ጥቅም፡ምንድር፡ነው፧በሕያዋን፡ፊትስ፡መኼድ፡ለሚያውቅ፡ለድኻ፡ጥቅሙ፡ምንድር፡ ነው፧
9፤በዐይን፡ማየት፡በነፍስ፡ከመቅበዝበዝ፡ይሻላል፤ይህም፡ደግሞ፡ከንቱ፡ነፋስንም፡እንደ፡መከተል፡ነው።
10፤የኾነው፡ስሙ፡አስቀድሞ፡ተጠራ፥ሰውም፡እንደ፡ኾነ፡ታወቀ፤ከርሱ፡ከሚበረታው፡ጋራ፡ይፋረድ፡ዘንድ፡አይች ልም።
11፤ከንቱን፡የሚያበዛ፡ብዙ፡ነገር፡አለና፡ለሰው፡ጥቅሙ፡ምንድር፡ነው፧
12፤ሰው፡በከንቱ፡ወራቱ፡ቍጥርና፡እንደ፡ጥላ፡በሚያሳልፈው፡ዘመኑ፡በሕይወቱ፡ሳለ፡ለሰው፡የሚሻለውን፡የሚያ ውቅ፡ማነው፧ወይስ፡ለሰው፡ከፀሓይ፡በታች፡ከርሱ፡በዃላ፡የሚኾነውን፡ማን፡ይነግረዋል፧
_______________መጽሐፈ፡መክብብ፥ምዕራፍ፡7።______________
ምዕራፍ፡7።
1፤ከመልካም፡ሽቱ፡መልካም፡ስም፥ከመወለድ፡ቀንም፡የሞት፡ቀን፡ይሻላል።
2፤ወደግብዣ፡ቤት፡ከመኼድ፡ወደልቅሶ፡ቤት፡መኼድ፡ይሻላል፤ርሱ፡የሰው፡ዅሉ፡ፍጻሜ፡ነውና፥ሕያውም፡የኾነ፡በ ልቡ፡ያኖረዋልና።
3፤ከሣቅ፡ሐዘን፡ይሻላል፥ከፊት፡ሐዘን፡የተነሣ፡ልብ፡ደስ፡ይሠኛልና።
4፤የጠቢባን፡ልብ፡በልቅሶ፡ቤት፡ነው፤የሰነፎች፡ልብ፡ግን፡በደስታ፡ቤት፡ነው።
5፤ሰው፡የሰነፎችን፡ዜማ፡ከሚሰማ፡ይልቅ፡የጠቢባንን፡ተግሣጽ፡መስማት፡ይሻለዋል።
6፤ከድስት፡በታች፡እንደሚቃጠል፡ሾኽ፡ድምፅ፡የሰነፍ፡ሣቅ፡እንዲሁ፡ነው፤ይህም፡ደግሞ፡ከንቱ፡ነው።
7፤ግፍ፡ጠቢቡን፡ያሳብደዋል፤ጕቦም፡ልቡን፡ያጠፋዋል።
8፤የነገር፡ፍጻሜ፡ከመዠመሪያው፡ይሻላል፤ታጋሽም፡ከትዕቢተኛ፡ይሻላል።
9፤በነፍስኽ፡ለቍጣ፡ችኵል፡አትኹን፡ቍጣ፡በሰነፍ፡ብብት፡ያርፋልና።
10፤ከዚህ፡ዘመን፡ይልቅ፡ያለፈው፡ዘመን፡ለምን፡ተሻለ፧ብለኽ፡አትናገር፤የዚህን፡ነገር፡በጥበብ፡አትጠይቅም ና።
11፤ጥበብ፡ከርስት፡ጋራ፡መልካም፡ነው፤ፀሓይንም፡ለሚያዩ፡ሰዎች፡ትርፍን፡ይሰጣል።
12፤የጥበብ፡ጥላ፡እንደ፡ገንዘብ፡ጥላ፡ናትና፤የዕውቀትም፡ብልጫዋ፡ጥበብ፡ገንዘብ፡ላደረጋት፡ሕይወትን፡እን ድትሰጥ፡ነው።
13፤የእግዚአብሔርን፡ሥራ፡ተመልከት፤ርሱ፡ጠማማ፡ያደረገውን፡ማን፡ሊያቀናው፡ይችላል፧
14፤በመልካም፡ቀን፡ደስ፡ይበልኽ፤በክፉም፡ቀን፡ተመልከት፤ሰው፡ከርሱ፡በዃላ፡መርምሮ፡ምንም፡እንዳያገኝ፡እ ግዚአብሔር፡ይህንም፡ያንም፡እንደዚያ፡ሠርቷል።
15፤ጻድቅ፡በጽድቁ፡ሲጠፋ፡ኃጥእም፡በክፋቱ፡እጅግ፡ዘመን፡ሲኖር፥ይህን፡ዅሉ፡ከንቱ፡በኾነ፡ዘመኔ፡አየኹ።
16፤እጅግ፡ጻድቅ፡አትኹን፥እጅግ፡ጠቢብም፡አትኹን፥እንዳትጠፋ።
17፤እጅግ፡ክፉ፡አትኹን፥እልከኛም፡አትኹን፥ጊዜኽ፡ሳይደርስ፡እንዳትሞት።
18፤እግዚአብሔርን፡የሚፈራ፡ከዅሉ፡ይወጣልና፥ይህን፡ብትይዝ፡ከዚያም፡ደግሞ፡እጅኽን፡ባታርቅ፡መልካም፡ነው ።
19፤በከተማ፡ከሚኖሩ፡ከዐሥር፡ገዢዎች፡ይልቅ፡ጥበብ፡ጠቢብን፡ታበረታለች።
20፤በምድር፡ላይ፡መልካምን፡የሚሠራ፡ኀጢአትንም፡የማያደርግ፡ጻድቅ፡አይገኝምና።
21፤ባሪያኽ፡ሲረግምኽ፡እንዳትሰማ፡በሚጫወቱበት፡ቃል፡ዅሉ፡ልብኽን፡አትጣል፤
22፤አንተ፡ደግሞ፡ሌላዎችን፡እንደ፡ረገምኽ፡ልብኽ፡ያውቃልና።
23፤ይህን፡ዅሉ፡በጥበብ፡ፈተንኹ፤ጠቢብ፡እኾናለኹ፡አልኹ፥ርሷ፡ግን፡ከእኔ፡ራቀች።
24፤የኾነው፡ራቀ፡እጅግም፡ጠለቀ፤መርምሮ፡የሚያገኘውስ፡ማን፡ነው፧
25፤ዐውቅና፡እመረምር፡ዘንድ፥ጥበብንና፡የነገሩን፡ዅሉ፡መደምደሚያ፡እፈልግ፡ዘንድ፥ኀጢአትም፡ስንፍና፥ስን ፍናም፡እብደት፡እንደ፡ኾነች፡ዐውቅ፡ዘንድ፡እኔ፡በልቤ፡ዞርኹ።
26፤እኔም፡ከሞት፡ይልቅ፡የመረረ፡ነገር፡መርምሬ፡አገኘኹ፤ርሷም፡ልቧ፡ወጥመድና፡መርበብ፡የኾነ፥እጆቿም፡እ ግር፡ብረት፡የኾኑ፡ሴት፡ናት፤በእግዚአብሔር፡ፊት፡መልካም፡የኾነ፡ከርሷ፡ያመልጣል፥ኀጢአተኛ፡ግን፡ይጠመድ ባታል።
27፤አንዱን፡በአንዱ፡ላይ፡ጨምሬ፡ወደ፡ነገሩ፡ዅሉ፡መደምደሚያ፡እደርስ፡ዘንድ፥እንሆ፥ይህን፡ነገር፡አገኘኹ ፡ይላል፡ሰባኪው፤
28፤ነፍሴ፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡ትሻታለች፥ነገር፡ግን፥አላገኘኹም፤ከሺሕ፡ወንዶች፡አንድ፡አገኘኹ፥ከነዚያ፡ዅ ሉ፡መካከል፡ግን፡አንዲት፡ሴት፡አላገኘኹም።
29፤እግዚአብሔር፡ሰዎችን፡ቅኖች፡አድርጎ፡እንደ፡ሠራቸው፥እንሆ፥ይህን፡ብቻ፡አገኘኹ፤እነርሱ፡ግን፡ብዙ፡ብ ልኀትን፡ፈለጉ።
_______________መጽሐፈ፡መክብብ፥ምዕራፍ፡8።______________
ምዕራፍ፡8።
1፤እንደ፡ጠቢብ፡የኾነ፡ሰው፡ማን፡ነው፧ነገርንስ፡መተርጐም፡የሚያውቅ፡ማን፡ነው፧የሰው፡ጥበብ፡ፊቱን፡ታበራ ለች፥የፊቱንም፡ድፍረት፡ትለውጣለች።
2፤እኔ፦በእግዚአብሔር፡መሐላ፡ምክንያት፡የንጉሥን፡ትእዛዝ፡ጠብቅ፡እልኻለኹ።
3፤የወደደውን፡ዅሉ፡ያደርጋልና፥ከፊቱ፡ትወገድ፡ዘንድ፡አትቸኵል፥ክፉንም፡በማድረግ፡አትጽና።
4፤የንጉሥ፡ቃል፡ኀይለኛ፡ነውና፤ይህንስ፡ለምን፡ታደርጋለኽ፧ማን፡ይለዋል፧
5፤ትእዛዝን፡የሚጠብቅ፡ክፉን፡ነገር፡አያውቅም፤የጠቢብም፡ልብ፡ጊዜንና፡ፍርድን፡ያውቃል።
6፤የሰው፡መከራ፡በርሱ፡ላይ፡እጅግ፡ስለ፡ኾነ፡ለነገር፡ዅሉ፡ጊዜና፡ፍርድ፡አለውና።
7፤የሚኾነውንም፡አያውቅም፤እንዴትስ፡እንደሚኾን፡የሚነግረው፡ማን፡ነው፧
8፤መንፈስን፡ለማስቀረት፡በመንፈስ፡ላይ፡ሥልጣን፡ያለው፡ሰው፡የለም፤በሞቱም፡ቀን፡ሥልጣን፡የለውም፤በሰልፍ ም፡ስንብቻ፡የለም፥ኀጢአትም፡ሠሪውን፡አያድነውም።
9፤ይህን፡ዅሉ፡አየኹ፥ከፀሓይም፡በታች፡ወደተደረገው፡ሥራ፡ዅሉ፡ልቤን፡ሰጠኹ፤ሰው፡ሰውን፡ለመጕዳት፡ገዢ፡የ ሚኾንበት፡ጊዜ፡አለ።
10፤እንዲሁም፡ኃጥኣን፡ተቀብረው፡አየኹ፥ወደ፡ዕረፍትም፡ገቡ፤ነገር፡ግን፥ቅን፡አድራጊዎች፡ከቅድስት፡ስፍራ ፡ወጡ፥በከተማዪቱም፡ውስጥ፡ተረሱ፤ይህም፡ደግሞ፡ከንቱ፡ነው።
11፤በክፉ፡ሥራ፡ላይ፡ፈጥኖ፡ፍርድ፡አይፈረድምና፡ስለዚህ፡በሰው፡ልጆች፡ውስጥ፡ልባቸው፡ክፉን፡ለመሥራት፡ጠ ነከረ።
12፤ኀጢአተኛ፡መቶ፡ጊዜ፡ክፉን፡ቢሠራ፡ዘመኑም፡ረዥም፡ቢኾን፥እግዚአብሔርን፡ለሚፈሩት፡በፊቱም፡ለሚፈሩት፡ ደኅንነት፡እንዲኾን፡ዐውቃለኹ፤
13፤ለኃጥእ፡ግን፡ደኅንነት፡የለውም፥በእግዚአብሔርም፡ፊት፡አይፈራምና፡ዘመኑ፡እንደ፡ጥላ፡አትረዝምም።
14፤በምድር፡የሚደረግ፡ከንቱ፡ነገር፡አለ፤በኃጥኣን፡የሚደረገው፡ሥራ፡የሚደርስባቸው፡ጻድቃን፡አሉ፥ለጻድቃ ንም፡የሚደረገው፡ሥራ፡የሚደርስላቸው፡ኃጥኣን፡አሉ፤ይህም፡ደግሞ፡ከንቱ፡ነው፡አልኹ።
15፤ከሚበላውና፡ከሚጠጣው፡ደስም፡ከሚለው፡በቀር፡ለሰው፡ከፀሓይ፡በታች፡ሌላ፡መልካም፡ነገር፡የለውምና፥እኔ ፡ደስታን፡አመሰገንኹ፤ከፀሓይም፡በታች፡ከድካሙ፡እግዚአብሔር፡በሰጠው፡በሕይወቱ፡ዘመን፡ይህ፡ደስታው፡ከር ሱ፡ጋራ፡ይኖራል።
16፤ጥበብን፡ዐውቅ፡ዘንድ፡በምድር፡የሚኾነውንም፡ድካም፡አይ፡ዘንድ፡ልቤን፡ሰጠኹ፥በቀንና፡በሌሊት፡እንቅል ፍን፡በዐይኑ፡የማያይ፡አለና፤
17፤ከፀሓይም፡በታች፡የተደረገውን፡ሥራ፡መርምሮ፡ያገኝ፡ዘንድ፡ለሰው፡እንዳይቻለው፡የእግዚአብሔርን፡ሥራ፡ ዅሉ፡አየኹ።ሰውም፡ሊፈልግ፡እጅግ፡ቢደክም፥መርምሮ፡አያገኘውም፤ደግሞ፡ጠቢብ፡ሰው፦ይህን፡ዐወቅኹ፡ቢል፥ር ሱ፡ያገኘው፡ዘንድ፡አይችልም።
_______________መጽሐፈ፡መክብብ፥ምዕራፍ፡9።______________
ምዕራፍ፡9።
1፤ጻድቃንና፡ጠቢባን፡ሥራዎቻቸውም፡በእግዚአብሔር፡እጅ፡እንደ፡ኾኑ፥ይህን፡ዅሉ፡እመረምር፡ዘንድ፡በልቤ፡አ ኖርኹ፤ፍቅር፡ወይም፡ጥል፡ቢኾን፡ሰው፡አያውቅም፤ዅሉ፡ወደ፡ፊታቸው፡ነው።
2፤የጻድቁና፡የበደለኛው፥የመልካሙና፡የክፉው፥የንጹሑና፡የርኩሱ፥መሥዋዕትን፡የሚሠዋውና፡የማይሠዋው፥የሰው ፡ዅሉ፡ድርሻው፡አንድ፡ነው፤እንደ፡መልካሙ፡ሰው፡እንዲሁ፡ኀጢአተኛው፥እንደ፡መሐለኛው፡ሰው፡እንዲሁ፡መሐላ ን፡የሚፈራው፡ነው።
3፤አንድ፡ድርሻ፡ዅሉን፡እንዲያገኝ፡ከፀሓይ፡በታች፡በተደረገው፡ዅሉ፡ይህ፡ነገር፡ክፉ፡ነው፤ደግሞም፡የሰው፡ ልጆች፡ልብ፡ክፋትን፡ትሞላለች፥በሕይወታቸውም፡ሳሉ፡እብደት፡በልባቸው፡ነው፥ከዚያም፡በዃላ፡ወደ፡ሙታን፡ይ ወርዳሉ።
4፤ያልሞተ፡ውሻ፡ከሞተ፡አንበሳ፡ይሻላልና፥ሰው፡ከሕያዋን፡ዅሉ፡ጋራ፡በአንድነት፡ቢኖር፡ተስፋ፡አለው።
5፤ሕያዋን፡እንዲሞቱ፡ያውቃሉና፤ሙታን፡ግን፡አንዳች፡አያውቁም፤መታሰቢያቸውም፡ተረስቷልና፥ከዚያ፡በዃላ፡ዋ ጋ፡የላቸውም።
6፤ፍቅራቸውና፡ጥላቸው፡ቅንአታቸውም፡በአንድነት፡ጠፍቷል፥ከፀሓይ፡በታችም፡በሚሠራው፡ነገር፡ለዘለዓለም፡ዕ ድል፡ፈንታ፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡የላቸውም።
7፤እግዚአብሔር፡ሥራኽን፡ተቀብሎታልና፥ኺድ፤እንጀራኽን፡በደስታ፡ብላ፥የወይን፡ጠጅኽንም፡በተድላ፡ጠጣ።
8፤ዅልጊዜ፡ልብስኽ፡ነጭ፡ይኹን፤ቅባትም፡ከራስኽ፡ላይ፡አይታጣ።
9፤በሕይወትኽ፥አንተም፡ከፀሓይ፡በታች፡በምትደክምበት፡ድካም፡ይህ፡ዕድል፡ፈንታኽ፡ነውና፥ከንቱ፡በኾነ፡በሕ ይወትኽ፡ዘመን፡ዅሉ፥ከፀሓይ፡በታች፡በሰጠኽ፥በከንቱ፡ዘመንኽ፡ዅሉ፥ከምትወዳ፟ት፡ሚስትኽ፡ጋራ፡ደስ፡ይበል ኽ።
10፤አንተ፡በምትኼድበት፡በሲኦል፡ሥራና፡ዐሳብ፡ዕውቀትና፡ጥበብ፡አይገኙምና፡እጅኽ፡ለማድረግ፡የምታገኘውን ፡ዅሉ፡እንደ፡ኀይልኽ፡አድርግ።
11፤እኔም፡ተመለስኹ፥ከፀሓይ፡በታችም፡ሩጫ፡ለፈጣኖች፥ሰልፍም፡ለኀያላን፥እንጀራም፡ለጠቢባን፥ባለጠግነትም ፡ለአስተዋዮች፥ሞገስም፡ለዐዋቂዎች፡እንዳልኾነ፡አየኹ፤ጊዜና፡ዕድል፡ግን፡ዅሉን፡ይገናኛቸዋል።
12፤ሰውም፡ጊዜውን፡አያውቅም፤በክፉ፡መረብ፡እንደ፡ተጠመዱ፡ዓሣዎች፥በወጥመድም፡እንደ፡ተያዙ፡ወፎች፥እንዲ ሁ፡የሰው፡ልጆች፡በክፉ፡ጊዜ፡በድንገት፡ሲወድቅባቸው፡ይጠመዳሉ።
13፤ከፀሓይ፡በታችም፡ይህን፡ጥበብ፡አየኹ፥ርሷም፡በእኔ፡ዘንድ፡ታላቅ፡መሰለችኝ።
14፤ታናሽ፡ከተማ፡ነበረች፥ጥቂቶች፡ሰዎችም፡ነበሩባት፤ታላቅ፡ንጉሥም፡መጣባት፡ከበባትም፥ታላቅ፡ግንብም፡ሠ ራባት።
15፤ጠቢብ፡ድኻ፡ሰውም፡ተገኘባት፥ያችንም፡ከተማ፡በጥበቡ፡አዳናት፤ያን፡ድኻ፡ሰው፡ግን፡ማንም፡አላሰበውም።
16፤እኔም።ከኀይል፡ይልቅ፡ጥበብ፡ትበልጣለች፤የድኻው፡ጥበብ፡ግን፡ተናቀች፡ቃሉም፡አልተሰማችም፡አልኹ።
17፤በሰነፎች፡መካከል፡ከሚጮኽ፡ከገዢው፡ጩኸት፡ይልቅ፡የጠቢባን፡ቃል፡በጸጥታ፡ትሰማለች።
18፤ከጦር፡መሣሪያዎች፡ይልቅ፡ጥበብ፡ትሻላለች፤አንድ፡ኀጢአተኛ፡ግን፡ብዙ፡መልካምን፡ያጠፋል።
_______________መጽሐፈ፡መክብብ፥ምዕራፍ፡10።______________
ምዕራፍ፡10።
1፤የሞቱ፡ዝንቦች፡የተቀመመውን፡የዘይት፡ሽቱ፡ያገሙታል፤እንዲሁም፡ትንሽ፡ስንፍና፡ጥበብንና፡ክብርን፡ያጠፋ ል።
2፤የጠቢብ፡ልብ፡በስተቀኙ፡ነው፥የሰነፍ፡ልብ፡ግን፡በስተግራው፡ነው።
3፤ደግሞም፡ሰነፍ፡በመንገድ፡ሲመላለስ፡ርሱ፡ልብ፡ይጐድለዋል፥የሚያስበውም፡ዅሉ፡ስንፍና፡ነው።
4፤ትዕግሥት፡ታላቁን፡ኀጢአት፡ጸጥ፡ያደርጋልና፥የገዢ፡ቍጣ፡የተነሣብኽ፡እንደ፡ኾነ፡ስፍራኽን፡አትልቀቅ።
5፤ከፀሓይ፡በታች፡ያየኹት፡ክፉ፡ነገር፡አለ፥ርሱም፡ከገዢ፡የሚወጣ፡ስሕተት፡ነው፤
6፤ሰነፍ፡በታላቅ፡ማዕርግ፡ተሾመ፥ባለጠጋዎች፡ግን፡በተዋረደ፡ስፍራ፡ተቀመጡ።
7፤ባሪያዎች፡በፈረስ፡ላይ፡ሲቀመጡ፡መሳፍንትም፡እንደ፡ባሪያዎች፡በምድር፡ላይ፡ሲኼዱ፡አየኹ።
8፤ጕድጓድን፡የሚምስ፡ይወድቅበታል፥ቅጥርንም፡የሚያፈርስን፡እባብ፡ትነድፈዋለች።
9፤ድንጋይን፡የሚፈነቅል፡ይታመምበታል፥ዕንጨትንም፡የሚፈልጥ፡ይጐዳበታል።
10፤ብረት፡ቢደነዝዝ፡ሰውም፡ባይስለው፡ኀይልን፡ሊያበዛ፡ይገ፟ባ፟ዋል፤ጥበብ፡ግን፡ሥራውን፡ለማከናወን፡ትጠ ቅመዋለች።
11፤ደጋሚ፡ሳይደግምባት፡እባብ፡ብትነድፍ፡ለደጋሚው፡ትርፍ፡የለውም።
12፤የጠቢብ፡ሰው፡የአፉ፡ቃል፡ሞገስ፡ናት፤የሰነፍ፡ከንፈሮች፡ግን፡ራሱን፡ይውጡታል።
13፤የአፉ፡ቃል፡መዠመሪያ፡ስንፍና፡ነው፥የንግግሩ፡ፍጻሜም፡ክፉ፡እብደት፡ነው።
14፤ሰነፍ፡ቃሉን፡ያበዛል፤ሰው፡ግን፡የሚኾነውን፡አያውቅም፤ከርሱስ፡በዃላ፡የሚኾነውን፡ማን፡ይነግረዋል፧
15፤የሰነፍ፡ሥራ፡ያደክመዋል፡ወደ፡ከተማ፡መኼድ፡አያውቅምና።
16፤ንጉሥሽ፡ሕፃን፡የኾነ፥መኳንንቶችሽም፡ማልደው፡የሚበሉ፥አንቺ፡አገር፡ሆይ፥ወዮልሽ!
17፤ንጉሥሽ፡የከበረ፡ልጅ፡የኾነ፥ለብርታት፡እንጂ፡ለስካር፡ያይደለ፡በጊዜ፡የሚበሉ፡መኳንንት፡ያሉሽ፥አንቺ ፡አገር፡ሆይ፥የተመሰገንሽ፡ነሽ።
18፤ተግባር፡በመፍታት፡ጣራው፡ይዘብጣል፥በእጅም፡መታከት፡ቤት፡ያፈሳ፟ል።
19፤እንጀራን፡ለሣቅ፡የወይን፡ጠጅንም፡ለሕይወት፡ደስታ፡ያደርጉታል፥ዅሉም፡ለገንዘብ፡ይገዛል።
20፤የሰማይ፡ወፍ፡ቃሉን፡ይወስደዋልና፥ባለክንፎችም፡ነገሩን፡ይናገራሉና፡በልብኽ፡ዐሳብ፡እንኳ፡ቢኾን፡ንጉ ሥን፡አትስደብ፥በመኝታ፡ቤትኽም፡ባለጠጋን፡አትስደብ።
_______________መጽሐፈ፡መክብብ፥ምዕራፍ፡11።______________
ምዕራፍ፡11።
1፤እንጀራኽን፡በውሃ፡ፊት፡ላይ፡ጣለው፥ከብዙ፡ቀን፡በዃላ፡ታገኘዋለኽና።
2፤ለሰባት፡ደግሞም፡ለስምንት፡ዕድል፡ፈንታን፡ክፈል፥በምድር፡ላይ፡የሚኾነውን፡ክፉ፡ነገር፡ምን፡እንደ፡ኾነ ፡አታውቅምና።
3፤ደመናት፡ዝናብ፡በሞሉ፡ጊዜ፡በምድር፡ላይ፡ያፈሱ፟ታል፤ዛፍም፡ወደ፡ደቡብ፡ወይም፡ወደ፡ሰሜን፡ቢወድቅ፥ዛፉ ፡በወደቀበት፡ስፍራ፡በዚያ፡ይኖራል።
4፤ነፋስን፡የሚጠባበቅ፡አይዘራም፥ደመናንም፡የሚመለከት፡አያጭድም።
5፤የነፋስ፡መንገድ፡እንዴት፡እንደ፡ኾነች፡ዐጥንትም፡በእርጉዝ፡ሆድ፡እንዴት፡እንድትዋደድ፡እንደማታውቅ፥እ ንዲሁም፡ዅሉን፡የሚሠራውን፡የእግዚአብሔርን፡ሥራ፡አታውቅም።
6፤ወይም፡ይህ፡ወይም፡ያ፡ማናቸው፡እንዲበቅል፡ወይም፡ኹለቱ፡መልካም፡እንዲኾኑ፡አታውቅምና፡በማለዳ፡ዘርኽን ፡ዝራ፥በማታም፡እጅኽን፡አትተው።
7፤ብርሃን፡ጣፋጭ፡ነው፥ፀሓይንም፡ማየት፡ለዐይን፡መልካም፡ነው።
8፤ሰው፡ብዙ፡ዘመን፡በሕይወት፡ቢኖር፡በዅሉም፡ደስ፡ይበለው፤ኾኖም፡የጨለማውን፡ዘመን፡ያስብ፥ብዙ፡ቀን፡ይኾ ናልና።የሚመጣው፡ነገር፡ዅሉ፡ከንቱ፡ነው።
9፤አንተ፡ጐበዝ፥በጕብዝናኽ፡ደስ፡ይበልኽ፥በጕብዝናኽም፡ወራት፡ልብኽን፡ደስ፡ይበለው፥በልብኽም፡መንገድ፡ዐ ይኖችኽም፡በሚያዩት፡ኺድ፤ዳሩ፡ግን፡ስለዚህ፡ነገር፡ዅሉ፡እግዚአብሔር፡ወደ፡ፍርድ፡እንዲያመጣኽ፡ዕወቅ።
10፤ሕፃንነትና፡ጕብዝና፡ከንቱዎች፡ናቸውና፥ከልብኽ፡ሐዘንን፡አርቅ፥ከሰውነትኽም፡ክፉን፡ነገር፡አስወግድ።
_______________መጽሐፈ፡መክብብ፥ምዕራፍ፡12።______________
ምዕራፍ፡12።
1፤የጭንቀት፡ቀን፡ሳይመጣ፡በጕብዝናኽ፡ወራት፡ፈጣሪኽን፡ዐስብ፤ደስ፡አያሠኙም፡የምትላቸውም፡ዓመታት፡ሳይደ ርሱ፤
2፤ፀሓይና፡ብርሃን፡ጨረቃና፡ከዋክብትም፡ሳይጨልሙ፥ደመናትም፡ከዝናብ፡በዃላ፡ሳይመለሱ፤
3፤ቤት፡ጠባቂዎች፡በሚንቀጠቀጡበት፥ኀያላን፡ሰዎችም፡በሚጐብጡበት፥ጥቂቶች፡ኾነዋልና፥ፈጪታዎች፡ሥራ፡በሚፈ ቱበት፥በመስኮትም፡ኾነው፡የሚመለከቱ፡በሚጨልሙበት፥በአደባባይም፡ደጆቹ፡በሚዘጉበት፡ቀን፤
4፤የወፍጮ፡ድምፅ፡ሲላሽ፥ከወፍ፡ድምፅ፡የተነሣ፡ሰው፡ሲነሣ፥ዜማም፡የሚጮኹ፡ሴቶች፡ልጆች፡ዅሉ፡ዝግ፡ሲሉ፤
5፤ከፍ፡ያለውን፡ደግሞ፡ሲፈሩ፥ድንጋጤም፡በመንገድ፡ላይ፡ሲኾን፤ለውዝም፡ሲያብብ፥አንበጣም፡እንደ፡ሸክም፡ሲ ከብድ፥ፈቃድም፡ሲጠፋ፤ሰው፡ወደዘለዓለም፡ቤት፡ሲኼድ፥አልቃሾችም፡በአደባባይ፡ሲዞሩ፤
6፤የብር፡ድሪ፡ሳይበጠስ፥የወርቅም፡ኵስኵስት፡ሳይሰበር፥ማድጋውም፡በምንጭ፡አጠገብ፡ሳይከሰከስ፥መንኰራኵሩ ም፡በጕድጓድ፡ላይ፡ሳይሰበር፥
7፤ዐፈርም፡ወደነበረበት፡ምድር፡ሳይመለስ፥ነፍስም፡ወደሰጠው፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ሳይመለስ፡ፈጣሪኽን፡ዐስብ ።
8፤ሰባኪው፦ከንቱ፥ከንቱ፤ዅሉ፡ከንቱ፡ነው፡ይላል።
9፤ሰባኪውም፡ጠቢብ፡ስለ፡ኾነ፡ለሕዝቡ፡ዕውቀትን፡አስተማረ፤ርሱም፡ብዙ፡ምሳሌዎችን፡መረመረና፡ፈላለገ፡አስ ማማም።
10፤ሰባኪው፡ያማረውን፡በቅንም፡የተጻፈውን፡እውነተኛውን፡ቃል፡መርምሮ፡ለማግኘት፡ፈለገ።
11፤የጠቢባን፡ቃል፡እንደ፡በሬ፡መውጊያ፡ነው፥የተሰበሰቡትም፡ካንድ፡እረኛ፡የተሰጡት፡ቃላት፡እንደ፡ተቸነከ ሩ፡ችንካሮች፡ናቸው።
12፤ከዚህም፡ዅሉ፡በላይ፥ልጄ፡ሆይ፥ተግሣጽን፡ስማ፤ብዙ፡መጻሕፍትን፡ማድረግ፡ፍጻሜ፡የለውም፥እጅግም፡ምርም ር፡ሰውነትን፡ያደክማል።
13፤የነገሩን፡ዅሉ፡ፍጻሜ፡እንስማ፤ይህ፡የሰው፡ዅለንተናው፡ነውና፤እግዚአብሔርን፡ፍራ፥ትእዛዙንም፡ጠብቅ።
14፤እግዚአብሔር፡ሥራን፡ዅሉ፡የተሰወረውንም፡ነገር፡ዅሉ፥መልካምም፡ቢኾን፡ክፉም፡ቢኾን፥ወደ፡ፍርድ፡ያመጣ ዋልና፨

http://www.gzamargna.net