ትንቢተ፡ዮናስ።

(ክለሳ.1.20020507)

______________ትንቢተ፡ዮናስ፥ምዕራፍ፡1።______________
ምዕራፍ፡1።
1፤የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደዐማቴ፡ልጅ፡ወደ፡ዮናስ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
2፤ተነሥተኽ፡ወደዚያች፡ወደ፡ታላቂቱ፡ከተማ፡ወደ፡ነነዌ፡ኺድ፥ክፋታቸውም፡ወደ፡ፊቴ፡ወጥቷልና፥በርሷ፡ላይ፡ ስበክ።
3፤ዮናስ፡ግን፡ከእግዚአብሔር፡ፊት፡ወደ፡ተርሴስ፡ይኰበልል፡ዘንድ፡ተነሣ፤ወደ፡ኢዮጴም፡ወረደ፥ወደ፡ተርሴስ ም፡የምታልፍ፡መርከብ፡አገኘ፤ከእግዚአብሔርም፡ፊት፡ኰብሎ፟፡ከነርሱ፡ጋራ፡ወደ፡ተርሴስ፡ይኼድ፡ዘንድ፡ዋጋ ፡ሰጥቶ፡ወደ፡ርሷ፡ገባ።
4፤እግዚአብሔርም፡በባሕሩ፡ላይ፡ታላቅ፡ነፋስን፡አመጣ፥በባሕርም፡ላይ፡ታላቅ፡ማዕበል፡ኾነ፥መርከቢቱም፡ልት ሰበር፡ቀረበች።
5፤መርከበኛዎቹም፡ፈሩ፥እያንዳንዱም፡ወደ፡አምላኩ፡ጮኸ፤መርከቢቱም፡እንድትቀል፟ላቸው፡በውስጧ፡የነበረውን ፡ዕቃ፡ወደ፡ባሕር፡ጣሉት፤ዮናስ፡ግን፡ወደ፡መርከቡ፡ውስጠኛው፡ክፍል፡ወርዶ፡ነበር፥በከባድ፡እንቅልፍም፡ተ ኝቶ፡ነበር።
6፤የመርከቡም፡አለቃ፡ወደ፡ርሱ፡ቀርቦ፦ምነው፡ተኝተኻል፧እንዳንጠፋ፡እግዚአብሔር፡ያስበን፡እንደ፡ኾነ፡ተነ ሥተኽ፡አምላክኽን፡ጥራ፡አለው።
7፤ርስ፡በርሳቸውም፦ይህ፡ክፉ፡ነገር፡በማን፡ምክንያት፡እንዳገኘን፡እናውቅ፡ዘንድ፡ኑ፥ዕጣ፡እንጣጣል፡ተባባ ሉ።ዕጣም፡ተጣጣሉ፥ዕጣውም፡በዮናስ፡ላይ፡ወደቀ።
8፤የዚያን፡ጊዜም፦ይህ፡ክፉ፡ነገር፡በማን፡ምክንያት፡እንዳገኘን፡እባክኽ፡ንገረን፤ሥራኽ፡ምንድር፡ነው፧ከወ ዴትስ፡መጣኽ፧አገርኽስ፡ወዴት፡ነው፧ወይስ፡ከማን፡ወገን፡ነኽ፧አሉት።
9፤ርሱም፦እኔ፡ዕብራዊ፡ነኝ፤ባሕሩንና፡የብሱን፡የፈጠረውን፡የሰማይን፡አምላክ፡እግዚአብሔርን፡አመልካለኹ፡ አላቸው።
10፤እነዚያም፡ሰዎች፡ከእግዚአብሔር፡ፊት፡እንደ፡ኰበለለ፡ርሱ፡ስለ፡ነገራቸው፡ዐውቀዋልና፥እጅግ፡ፈርተው፦ ይህ፡ያደረግኸው፡ምንድር፡ነው፧አሉት።
11፤ባሕሩንም፡ሞገዱ፡አጥብቆ፡ያናውጠው፡ነበርና፦ባሕሩ፡ከእኛ፡ዘንድ፡ጸጥ፡እንዲል፡ምን፡እናድርግብኽ፧አሉ ት።
12፤ርሱም፦ይህ፡ታላቅ፡ማዕበል፡በእኔ፡ምክንያት፡እንዳገኛችኹ፡ዐውቃለኹና፡አንሥታችኹ፡ወደ፡ባሕር፡ጣሉኝ፥ ባሕሩም፡ጸጥ፡ይልላችዃል፡አላቸው።
13፤ሰዎቹ፡ግን፡ወደ፡ምድሩ፡ሊመለሱ፡አጥብቀው፡ቀዘፉ፤ዳሩ፡ግን፡ባሕሩ፡እጅግ፡አብዝቶ፡ይናወጥባቸው፡ነበር ና፥አልቻሉም።
14፤ስለዚህ፥ወደ፡እግዚአብሔር፡ጮኸው፦አቤቱ፥እንደ፡ወደድኽ፡አድርገኻልና፥እንለምንኻለን፤አቤቱ፥ስለዚህ፡ ሰው፡ነፍስ፡እንዳንጠፋ፡ንጹሕም፡ደም፡በእኛ፡ላይ፡እንዳታደርግ፡እንለምንኻለን፡አሉ።
15፤ዮናስንም፡ወስደው፡ወደ፡ባሕሩ፡ጣሉት፤ባሕሩም፡ከመናወጡ፡ጸጥ፡አለ።
16፤ሰዎችም፡እግዚአብሔርን፡እጅግ፡ፈሩ፥ለእግዚአብሔርም፡መሥዋዕትን፡አቀረቡ፥ስእለትንም፡ተሳሉ።
_______________ትንቢተ፡ዮናስ፥ምዕራፍ፡2።______________
ምዕራፍ፡2።
1፤እግዚአብሔርም፡ዮናስን፡የሚውጥ፡ታላቅ፡ዓሣ፡አሰናዳ፤ዮናስም፡ሦስት፡ቀንና፡ሦስት፡ሌሊት፡በዓሣው፡ሆድ፡ ውስጥ፡ነበረ።
2፤ዮናስም፡በዓሣው፡ሆድ፡ውስጥ፡ኾኖ፡ወደ፡አምላኩ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ጸለየ፥እንዲህም፡አለ፦
3፤በመከራዬ፡ሳለኹ፡ወደ፡አምላኬ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ጮኽኹ፥ርሱም፡ሰማኝ፤በሲኦልም፡ሆድ፡ውስጥ፡ኾኜ፡ጮኽኹ ፥ቃሌንም፡አዳመጥኽ።
4፤ወደ፡ጥልቁ፡ወደ፡ባሕሩ፡ውስጥ፡ጣልኸኝ፥ፈሳሾችም፡በዙሪያዬ፡ነበሩ፤ማዕበልኽና፡ሞገድኽ፡ዅሉ፡በላዬ፡ዐለ ፉ።
5፤እኔም፦ከዐይንኽ፡ፊት፡ተጣልኹ፤ነገር፡ግን፥ወደ፡ቅዱስ፡መቅደስኽ፡ደግሞ፡እመለከታለኹ፡አልኹ።
6፤ውሃዎችም፡እስከ፡ነፍሴ፡ድረስ፡ከበቡኝ፤ጥልቁ፡ባሕር፡በዙሪያዬ፡ነበረ፤የባሕሩ፡ሣር፡በራሴ፡ተጠምጥሞ፡ነ በር።
7፤ወደተራራዎች፡መሠረት፡ወረድኹ፤በምድርና፡በመወርወሪያዎቿ፡ለዘለዓለም፡ተዘጋኹ፤አንተ፡ግን፥አቤቱ፡አምላ ኬ፥ሕይወቴን፡ከጕድጓዱ፡አወጣኽ።
8፤ነፍሴ፡በዛለችብኝ፡ጊዜ፡እግዚአብሔርን፡ዐሰብኹት፤ጸሎቴም፡ወዳንተ፡ወደ፡ቅዱስ፡መቅደስኽ፡ገባች።
9፤ከንቱነትንና፡ሐሰትን፡የሚጠብቁ፡ምሕረታቸውን፡ትተዋል።
10፤እኔ፡ግን፡በምስጋና፡ቃል፡እሠዋልኻለኹ፤የተሳልኹትንም፡እከፍላለኹ።ደኅንነት፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ነ ው።
11፤እግዚአብሔርም፡ዓሣውን፡አዘዘው፥ርሱም፡ዮናስን፡በየብስ፡ላይ፡ተፋው።
_______________ትንቢተ፡ዮናስ፥ምዕራፍ፡3።______________
ምዕራፍ፡3።
1፤የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ኹለተኛ፡ወደ፡ዮናስ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
2፤ተነሥተኽ፡ወደዚያች፡ወደ፡ታላቂቱ፡ከተማ፡ወደ፡ነነዌ፡ኺድ፥የምነግርኽንም፡ስብከት፡ስበክላት፡አለው።
3፤ዮናስም፡ተነሥቶ፡እንደእግዚአብሔር፡ቃል፡ወደ፡ነነዌ፡ኼደ፤ነነዌም፡የሦስት፡ቀን፡መንገድ፡ያኽል፡እጅግ፡ ታላቅ፡ከተማ፡ነበረች።
4፤ዮናስም፡የአንድ፡ቀን፡መንገድ፡ያኽል፡ወደ፡ከተማዪቱ፡ውስጥ፡ሊገባ፡ዠመረ፤ጮኾም፦በሦስት፡ቀን፡ውስጥ፡ነ ነዌ፡ትገለበጣለች፡አለ።
5፤የነነዌም፡ሰዎች፡እግዚአብሔርን፡አመኑ፤ለጾም፡ዐዋጅ፡ነገሩ፥ከታላቁም፡ዠምሮ፡እስከ፡ታናሹ፡ድረስ፡ማቅ፡ ለበሱ።
6፤ወሬውም፡ወደነነዌ፡ንጉሥ፡ደረሰ፤ርሱም፡ከዙፋኑ፡ተነሥቶ፡መጐናጸፊያውን፡አወለቀ፡ማቅም፡ለበሰ፥በዐመድም ፡ላይ፡ተቀመጠ።
7፤ዐዋጅም፡አስነገረ፥በነነዌም፡ውስጥ፡የንጉሡንና፡የመኳንንቱን፡ትእዛዝ፡አሳወጀ፥እንዲህም፡አለ፦ሰዎችና፡ እንስሳዎች፡ላሞችና፡በጎች፡አንዳችን፡አይቅመሱ፤አይሰማሩም፡ውሃንም፡አይጠጡ፤
8፤ሰዎችና፡እንስሳዎችም፡በማቅ፡ይከደኑ፥ወደ፡እግዚአብሔርም፡በብርቱ፡ይጩኹ፤ሰዎችም፡ዅሉ፡ከክፉ፡መንገዳቸ ውና፡በእጃቸው፡ካለው፡ግፍ፡ይመለሱ።
9፤እኛ፡እንዳንጠፋ፡እግዚአብሔር፡ተመልሶ፡ይጸጸት፡እንደ፡ኾነ፥ከጽኑ፡ቍጣውም፡ይመለስ፡እንደ፡ኾነ፡ማን፡ያ ውቃል፧
10፤እግዚአብሔርም፡ከክፉ፡መንገዳቸው፡እንደተመለሱ፡ሥራቸውን፡አየ፤እግዚአብሔርም፡ያደርግባቸው፡ዘንድ፡በ ተናገረው፡ክፉ፡ነገር፡ተጸጽቶ፡አላደረገውም።
_______________ትንቢተ፡ዮናስ፥ምዕራፍ፡4።______________
ምዕራፍ፡4።
1፤ይህም፡ዮናስን፡ከቶ፡ደስ፡አላሠኘውም፥ርሱም፡ተቈጣ።
2፤ወደ፡እግዚአብሔርም፡ጸለየና፦አቤቱ፥እለምንኻለኹ፤በአገሬ፡ሳለኹ፡የተናገርኹት፡ይህ፡አልነበረምን፧አንተ ፡ቸርና፡ይቅር፡ባይ፥ታጋሽም፥ምሕረትኽም፡የበዛ፥ከክፉው፡ነገርም፡የተነሣ፡የምትጸጸት፡አምላክ፡እንደ፡ኾን ኽ፡ዐውቄ፡ነበርና፥ስለዚህ፡ወደ፡ተርሴስ፡ለመኰብለል፡ፈጥኜ፡ነበር።
3፤አኹንም፥አቤቱ፥ከሕይወት፡ሞት፡ይሻለኛልና፥እባክኽ፥ነፍሴን፡ከእኔ፡ውሰድ፡አለው።
4፤እግዚአብሔርም፦በእውኑ፡ትቈጣ፡ዘንድ፡ይገ፟ባ፟ኻልን፧አለ።
5፤ዮናስም፡ከከተማዪቱ፡ወጣ፥ከከተማዪቱም፡በስተምሥራቅ፡በኩል፡ተቀመጠ፤ከተማዪቱንም፡የሚያገኛትን፡እስኪያ ይ፡ድረስ፡በዚያ፡ለራሱ፡ዳስ፡ሠርቶ፡ከጥላው፡በታች፡ተቀመጠ።
6፤እግዚአብሔር፡አምላክም፡ቅል፡አዘጋጀ፥ከጭንቀቱም፡ታድነው፡ዘንድ፡በራሱ፡ላይ፡ጥላ፡እንድትኾን፡በዮናስ፡ ላይ፡ከፍ፡ከፍ፡አደረጋት፤ዮናስም፡ስለ፡ቅሊቱ፡እጅግ፡ደስ፡አለው።
7፤በነጋው፡ግን፡ወገግ፡ባለ፡ጊዜ፡እግዚአብሔር፡ትልን፡አዘጋጀ፥ርሷም፡ቅሊቱን፡እስክትደርቅ፡ድረስ፡መታቻት ።
8፤ፀሓይም፡በወጣች፡ጊዜ፡እግዚአብሔር፡ትኵስ፡የምሥራቅ፡ነፋስ፡አዘጋጀ፡ዮናስ፡እስኪዝል፡ድረስም፡ፀሓይ፡ራ ሱን፡መታው፤ለራሱም፡ሞትን፡ፈለገና፦ከሕይወት፡ሞት፡ይሻለኛል፡አለ።
9፤እግዚአብሔርም፡ዮናስን፦በእውኑ፡ስለዚች፡ቅል፡ትቈጣ፡ዘንድ፡ይገ፟ባ፟ኻልን፧አለው።ርሱም፦እስከ፡ሞት፡ድ ረስ፡እቈጣ፡ዘንድ፡ይገ፟ባ፟ኛል፡አለ።
10፤እግዚአብሔርም፦አንተ፡ትበቅል፡ዘንድ፡ላልደከምኽባት፡ላላሳደግኻትም፥ባንድ፡ሌሊት፡ለበቀለች፥ባንድ፡ሌ ሊትም፡ለደረቀችው፡ቅል፡አዝነኻል።
11፤እኔስ፡ቀኛቸውንና፡ግራቸውን፡የማይለዩ፡ከመቶ፡ኻያ፡ሺሕ፡የሚበልጡ፡ሰዎችና፡ብዙ፡እንስሳዎች፡ላሉባት፡ ለታላቂቱ፡ከተማ፡ለነነዌ፡አላዝንምን፧አለው፨

http://www.gzamargna.net