ትንቢተ፡ናሖም።

(ክለሳ.1.20020507)

_______________ትንቢተ፡ናሖም፥ምዕራፍ፡1።______________
ምዕራፍ፡1።
1፤ስለ፡ነነዌ፡የተነገረ፡ሸክም፤የኤልቆሻዊው፡የናሖም፡የራእዩ፡መጽሐፍ፡ይህ፡ነው።
2፤እግዚአብሔር፡ቀናተኛና፡ተበቃይ፡አምላክ፡ነው፤እግዚአብሔር፡ተበቃይና፡መዓትን፡የተሞላ፡ነው፤እግዚአብሔ ር፡ተቃዋሚዎቹን፡ይበቀላል፥ለጠላቶቹም፡ቍጣውን፡ይጠብቃል።
3፤እግዚአብሔር፡ትዕግሥተኛ፥ኀይሉም፡ታላቅ፡ነው፥በደለኛውንም፦ንጹሕ፡ነኽ፡አይልም፤እግዚአብሔር፡በወጀብና ፡በዐውሎ፡ነፋስ፡ውስጥ፡መንገድ፡አለው፥ደመናም፡የእግሩ፡ትቢያ፡ነው።
4፤ባሕሩንም፡ይገሥጻታል፥ያደርቃትማል፥ወንዞችንም፡ዅሉ፡ያደርቃል፤ባሳንና፡ቀርሜሎስም፡ላልተዋል፥የሊባኖስ ም፡አበባ፡ጠውልጓል።
5፤ተራራዎችም፡ከርሱ፡የተነሣ፡ታወኩ፥ኰረብታዎችም፡ቀለጡ፤ምድርና፡ዓለም፡የሚኖሩበትም፡ዅሉ፡ከፊቱ፡ተናወጡ ።
6፤በቍጣው፡ፊት፡የሚቆም፡ማን፡ነው፧የቍጣውንም፡ትኵሳት፡ማን፡ይታገሣል፧መዓቱ፡እንደ፡እሳት፡ይፈሳ፟ል፥ከር ሱም፡የተነሣ፡አለቶች፡ተሰነጠቁ።
7፤እግዚአብሔር፡መልካም፡ነው፥በመከራ፡ቀንም፡መሸሸጊያ፡ነው፤በርሱ፡የሚታመኑትንም፡ያውቃል።
8፤ስፍራዋን፡ግን፡በሚያጥለቀልቅ፡ጐርፍ፡ፈጽሞ፡ያጠፋታል፥ጠላቶቹንም፡ወደ፡ጨለማ፡ያሳድዳቸዋል።
9፤በእግዚአብሔር፡ላይ፡የምታስቡት፡ምንድር፡ነው፧ርሱ፡ፈጽሞ፡ያጠፋል፥መከራም፡ኹለተኛ፡አይነሣም።
10፤ርስ፡በርሳቸው፡እንደ፡ተመሰቃቀለ፡ሾኽ፡ቢኾኑ፥በመጠጣቸውም፡ቢሰክሩ፡እንደ፡ደረቅ፡ገለባ፡ፈጽመው፡ይጠ ፋሉ።
11፤በእግዚአብሔር፡ላይ፡በክፉ፡የሚያስብ፥ክፋትን፡የሚመክር፥ከአንተ፡ዘንድ፡ወጥቷል።
12፤እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ኀይለኛዎችና፡ብዙዎች፡ቢኾኑ፡እንዲሁ፡ይቈረጣሉ፥ርሱም፡ያልቃል።እኔም፡አ ስጨንቄኻለኹ፥ነገር፡ግን፥ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አላስጨንቅኽም።
13፤አኹንም፡ቀንበሩን፡ከአንተ፡እሰብራለኹ፥እስራትኽንም፡እበጥሳለኹ።
14፤እግዚአብሔርም፡ከስምኽ፡ማንም፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡እንዳይዘራ፡ስለ፡አንተ፡አዟ፟ል፤ከአምላኮችኽ፡ቤት፡ የተቀረጸውንና፡ቀልጦ፡የተሠራውን፡ምስል፡አጠፋለኹ፤አንተም፡የተጠቃኽ፡ነኽና፥መቃብርኽን፡እምሳለኹ።
15፤እንሆ፥የምሥራችን፡የሚያመጣ፡ሰላምንም፡የሚያወራ፡ሰው፡እግር፡በተራራዎች፡ላይ፡ነው! ይሁዳ፡ሆይ፥አጥፊው፡ፈጽሞ፡ጠፍቷልና፥ከእንግዲህም፡ወዲህ፡ባንተ፡ዘንድ፡አያልፍምና፡ዓመት፡በዓሎችኽን፡አ ድርግ፥ስእለቶችኽን፡ክፈል።
_______________ትንቢተ፡ናሖም፥ምዕራፍ፡2።______________
ምዕራፍ፡2።
1፤የሚቀጠቅጥ፡ባንተ፡ላይ፡ወጥቷል፤ምሽግን፡ጠብቅ፥መንገድንም፡ሰልል፤ወገብኽን፡አጽና፥ኀይልኽንም፡እጅግ፡ አበርታ።
2፤ዘራፊዎች፡ዘርፈዋቸዋልና፥የወይናቸውንም፡ዐረግ፡አጥፍተዋልና፥እግዚአብሔር፡የያዕቆብን፡ክብር፡እንደ፡እ ስራኤል፡ክብር፡ይመልሳል።
3፤የኀያላኑ፡ጋሻ፡ቀልቷል፥ጽኑዓንም፡ቀይ፡ልብስ፡ለብሰዋል።ርሱም፡በሚያዘጋጅበት፡ቀን፡ሠረገላዎች፡እንደ፡ እሳት፡ይንቦገቦጋሉ፤የጦሩም፡ሶማያ፡ይወዛወዛል።
4፤ሠረገላዎች፡በመንገድ፡ላይ፡ይነጕዳሉ፥አደባባይም፡ይጋጫሉ፤መልካቸው፡እንደ፡ፋና፡ነው፥እንደ፡መብረቅም፡ ይከንፋሉ።
5፤መሳፍንቱን፡ያስባል፤በአረማመዳቸው፡ይሰናከላሉ፤ፈጥነው፡በቅጥሯ፡ላይ፡ይወጣሉ፥መጠጊያም፡ተዘጋጀለት።
6፤የወንዞቹም፡መዝጊያዎች፡ተከፈቱ፥የንጉሡ፡ቤትም፡ቀለጠች።
7፤ንግሥት፡ተገለጠች፥ተማረከችም፥ሴቶች፡ባሪያዎቿም፡እንደ፡ርግብ፡እየጮኹና፡ደረታቸውን፡እየመቱ፡ዋይ፡ዋይ ፡ይላሉ።
8፤ነነዌ፡ግን፡ከዱሮ፡ዘመን፡ዠምራ፡እንደ፡ተከማቸ፡ውሃ፡ነበረች፤አኹን፡ግን፡ይሸሻሉ፤እነርሱም፦ቁሙ፥ቁሙ፡ ይላሉ፥ነገር፡ግን፥የሚመለስ፡የለም።
9፤መዝገቧ፡መጨረሻ፡የለውምና፥የከበረውም፡የዕቃዋ፡ዅሉ፡ብዛት፡አይቈጠርምና፡ብሩን፡በዝብዙ፥ወርቁንም፡በዝ ብዙ።
10፤ባዶና፡ባድማ፡ምድረ፡በዳም፡ኾናለች፤ልብ፡ቀልጧል፥ጕልበቶችም፡ተብረክርከዋል፤በወገብም፡ዅሉ፡ሕማም፡አ ለ፥የሰዎችም፡ዅሉ፡ፊት፡ጠቍሯል።
11፤የአንበሳዎችም፡መደብ፥የአንበሳዎችም፡ደቦል፡የሚሰማራበት፥አንበሳውና፡አንበሳዪቱ፡ግልገሉም፡ሳይፈሩ፡ የሚኼዱት፡ስፍራ፡ወዴት፡ነው፧
12፤አንበሳው፡ለልጆቹ፡የሚበቃውን፡ነጠቀ፥ለእንስቶቹም፡ሰበረላቸው፡ዋሻውን፡በንጥቂያ፥መደቡንም፡በቅሚያ፡ ሞልቶታል።
13፤እንሆ፥ባንቺ፡ላይ፡ነኝ፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፤ሠረገላዎቿንም፡አቃጥዬ፡አጤሳለኹ፥ሰይፍም ፡የአንበሳ፡ደቦሎችሽን፡ይበላቸዋል፤ንጥቂያሽንም፡ከምድር፡አጠፋለኹ፥የመልክተኛዎችሽን፡ድምፅ፡ከእንግዲህ ፡ወዲህ፡አይሰማም።
_______________ትንቢተ፡ናሖም፥ምዕራፍ፡3።______________
ምዕራፍ፡3።
1፤ለደም፡ከተማ፡ወዮላት! በዅለንተናዋ፡ሐሰትና፡ቅሚያ፡ሞልቶባታል፤ንጥቂያ፡ከርሷ፡አያልቅም።
2፤የዐለንጋ፡ድምፅ፥የመንኰራኵርም፡ድምፅ፥የፈረሶችም፡ኰቴ፥የፈጣን፡ሠረገላም፡ጩኸት፡ተሰምቷል፤
3፤ፈረሰኛው፡ይጋልባል፥ሰይፍም፡ይንቦገቦጋል፥ጦርም፡ይብለጨለጫል፤የተገደሉትም፡ይበዛሉ፥በድኖችም፡በክምር ፡ይከመራሉ፥ሬሳቸውም፡አይቈጠርም፤በሬሳቸውም፡ይሰናከላሉ።
4፤ስለተዋበችው፡ጋለሞታ፡ግልሙትና፡ብዛት፡ይህ፡ኾኗል፤ርሷም፡በመተቷ፡እጅግ፡በለጠች፥አሕዛብንም፡በግልሙት ናዋ፥ወገኖችንም፡በመተቷ፡ሸጠች።
5፤እንሆ፥ባንቺ፡ላይ፡ነኝ፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፥ልብስሽን፡በፊትሽ፡እገልጣለኹ፤ኅፍረተ፡ሥጋ ሽንም፡ለአሕዛብ፥ነውርሽንም፡ለመንግሥታት፡አሳያለኹ።
6፤ርኵሰትንም፡በላይሽ፡እጥላለኹ፥እንቅሽማለኹ፥ማላገጫም፡አደርግሻለኹ።
7፤የሚያይሽም፡ዅሉ፡ከአንቺ፡ሸሽቶ፦ነነዌ፡ባድማ፡ኾናለች፤የሚያለቅስላትስ፡ማን፡ነው፧የሚያጽናናትንስ፡ከወ ዴት፡እፈልጋለኹ፧ይላል።
8፤አንቺ፡በመስኖች፡መካከል፡ከተቀመጠችው፥ውሃም፡በዙሪያዋ፡ከነበራት፥ምሽጓም፡ባሕር፡ከነበረ፥ቅጥሯም፡በባ ሕር፡ውስጥ፡ከነበረ፡ከኖእ፡ዐሞን፡ትበልጫለሽን፧
9፤ኢትዮጵያና፡ግብጽ፡የማይቈጠር፡ኀይሏ፡ነበሩ፤ፉጥና፡ልብያ፡ረዳቶቿ፡ነበሩ።
10፤ርሷ፡ግን፡ተማርካ፡ፈለሰች፤ሕፃናቷ፡በመንገድ፡ዅሉ፡ራስ፡ላይ፡ተፈጠፈጡ፤በከበርቴዎቿም፡ላይ፡ዕጣ፡ተጣ ጣሉ፥ታላላቆቿም፡ዅሉ፡በሰንሰለት፡ታሰሩ።
11፤አንቺም፡ትሰክሪያለሽ፡ወራዳም፡ትኾኛለሽ፤አንቺ፡ደግሞ፡ከጠላት፡የተነሣ፡መጠጊያን፡ትፈልጊያለሽ።
12፤ዐምባሽ፡ዅሉ፡የመዠመሪያውን፡የበሰለ፡ፍሬ፡እንደ፡ያዙ፡እንደ፡በለስ፡ዛፎች፡ነው፤ቢወዛወዝ፡በሚበላው፡ አፍ፡ውስጥ፡ይወድቃል።
13፤እንሆ፥በመካከልሽ፡ያሉ፡ሕዝብሽ፡ሴቶች፡ናቸው፤የአገርሽ፡በሮች፡ለጠላቶችሽ፡ፈጽሞ፡ተከፍተዋል፥እሳትም ፡መወርወሪያዎችኽን፡በልቷል።
14፤ከበ፟ው፡ያስጨንቁሻልና፥ውሃን፡ቅጂ፤ዐምባሽን፡አጠንክሪ፤ወደ፡ጭቃ፡ገብተሽ፡ርገጪ፤የጡብን፡መሠሪያ፡ያ ዢ።
15፤በዚያ፡እሳት፡ይበላሻል፥ሰይፍ፡ያጠፋሻል፥እንደ፡ደጐብያ፡ይበላሻል፤እንደ፡ደጐብያ፡ብዢ፥እንደ፡አንበጣ ም፡ተባዢ።
16፤ነጋዴዎችሽን፡ከሰማይ፡ከዋክብት፡ይልቅ፡አበዛሽ፤ደጐብያ፡ተዘረጋ፥በረረም።
17፤ባንቺ፡ዘንድ፡ዘውድ፡የጫኑት፡እንደ፡አንበጣ፥አለቃዎችሽም፡እንደሚንቀሳቀሱ፡ኵብኵባዎች፡ናቸው፤በብርድ ፡ቀን፡በቅጥር፡ውስጥ፡ይቀመጣሉ፥ፀሓይም፡በወጣች፡ጊዜ፡ያኰበኵባሉ፤ስፍራቸው፡በየት፡እንደ፡ኾነ፡አይታወቅ ም።
18፤የአሶር፡ንጉሥ፡ሆይ፥እረኛዎችኽ፡አንቀላፍተዋል፤መኳንንቶችኽም፡ዐርፈዋል፤ሕዝብኽም፡በተራራዎች፡ላይ፡ ተበትኗል፥የሚሰበስበውም፡የለም።
19፤ስብራትኽ፡አይፈወስም፥ቍስልኽም፡ክፉ፡ነው፤ወሬኽንም፡የሚሰሙ፡ዅሉ፡እጃቸውን፡ባንተ፡ላይ፡ያጨበጭባሉ፤ ክፋትኽ፡ዅልጊዜ፡ያላለፈችበት፡ሰው፡ማን፡ነውና፨

http://www.gzamargna.net