ኦሪት፡ዘዳግም።

(ክለሳ.1.20020507)

_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡1።______________
ምዕራፍ፡1።
1፤በዮርዳኖስ፡ማዶ፡በምድረ፡በዳ፥በዐረባ፡ውስጥ፡በቀይ፡ባሕር፡ፊት፡ለፊት፥በፋራን፡በጦፌልም፡በላባንም ፡በሐጼሮትም፡በዲዛሃብም፡መካከል፡ሳሉ፥ሙሴ፡ለእስራኤል፡ዅሉ፡የነገራቸው፡ቃል፡ይህ፡ነው።
2፤በሴይር፡ተራራ፡መንገድ፡ከኰሬብ፡እስከ፡ቃዴስ፡በርኔ፡ድረስ፡የዐሥራ፡አንድ፡ቀን፡መንገድ፡ነው።
3፤4፤በአርባኛው፡ዓመት፡በዐሥራ፡አንደኛው፡ወር፡ከወሩም፡በመዠመሪያው፡ቀን፥ሙሴ፥በሐሴቦን፡ተቀምጦ፡የ ነበረውን፡የአሞራውያንን፡ንጉሥ፡ሴዎንን፥በዐስታሮትና፡በኤድራይ፡ተቀምጦ፡የነበረውን፡የባሳንን፡ንጉሥ፡ ዐግን፡ከመታ፡በዃላ፥እግዚአብሔር፡ስለ፡እነርሱ፡ያዘዘውን፡ዅሉ፡ለእስራኤል፡ልጆች፡ነገራቸው።
5፤በዮርዳኖስ፡ማዶ፡በሞዐብ፡ምድር፡ሙሴ፡እንዲህ፡ብሎ፡ይህችን፡ሕግ፡ይገልጥ፡ዠመር።
6፤አምላካችን፡እግዚአብሔር፡በኰሬብ፡እንዲህ፡ብሎ፡ተናገረን፦በዚህ፡ተራራ፡የተቀመጣችኹት፡በቃ፤
7፤ተመልሳችኹ፡ተጓዙ፤ወደ፡ተራራማው፡ወደአሞራውያን፡አገር፡ወደ፡ድንበሮቹም፡ዅሉ፥በዐረባም፡በደጋውም፡ በቈላውም፡በደቡብም፡በባሕርም፡ዳር፡ወዳሉ፡ወደከነዓናውያን፡ምድር፥ወደ፡ሊባኖስም፡እስከ፡ታላቁ፡ወንዝም ፡እስከ፡ኤፍራጥስ፡ድረስ፡ኺዱ።
8፤እንሆ፥ምድሪቱን፡በፊታችኹ፡አድርጌያለኹ፤ግቡ፥እግዚአብሔር፡ለእነርሱ፡ከነርሱም፡በዃላ፡ለዘራቸው፡ይ ሰጣት፡ዘንድ፡ለአባቶቻችኹ፡ለአብርሃምና፡ለይሥሐቅ፡ለያዕቆብም፡የማለላቸውንም፡ምድር፡ውረሱ።
9፤በዚያም፡ዘመን፡እንዲህ፡ብዬ፡ተናገርዃችኹ፦እኔ፡ብቻዬን፡ልሸከማችኹ፡አልችልም፤
10፤አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡አብዝቷችዃል፥እንሆም፥እናንተ፡ዛሬ፡እንደሰማይ፡ከዋክብት፡ብዛት፡ናችኹ።
11፤የአባቶቻችኹ፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡በዚህ፡ቍጥር፡ላይ፡እልፍ፡አእላፋት፡ይጨምር፥እንደ፡ተናገራችኹ ም፡ይባርካችኹ።
12፤እኔ፡ብቻዬን፡ድካማችኹን፣ሸክማችኹንም፣ክርክራችኹንም፡እሸከም፡ዘንድ፡እንዴት፡እችላለኹ፧
13፤ከእናንተ፡ከየነገዳችኹ፡ጥበበኛዎች፡አስተዋዮችም፡ዐዋቂዎችም፡የኾኑትን፡ሰዎች፡ምረጡ፥እኔም፡በላያ ችኹ፡አለቃዎች፡አደርጋቸዋለኹ።
14፤እናንተም፦እናደርገው፡ዘንድ፡የተናገርኸው፡ይህ፡ነገር፡መልካም፡ነው፡ብላችኹ፡መለሳችኹልኝ።
15፤ጥበበኛዎችና፡ዐዋቂዎች፡የኾኑትን፡የነገዶቻችኹን፡አለቃዎች፡መረጥኹ፥በእናንተም፡ላይ፡አለቃዎች፡የ ሻለቃዎችም፡የመቶ፡አለቃዎችም፡የዐምሳ፡አለቃዎችም፡የዐሥር፡አለቃዎችም፡ገዢዎችም፡በየነገዶቻቸው፡አደረ ግዃቸው።
16፤በዚያን፡ጊዜም፦የወንድሞቻችኹን፡ነገር፡ስሙ፤በሰውና፡በወንድሙ፡ከርሱም፡ጋራ፡ባለው፡መጻተኛ፡መካከ ል፡በጽድቅ፡ፍረዱ።
17፤በፍርድም፡አድልዎ፡አታድርጉ፤ታላቁን፡እንደምትሰሙ፥ታናሹንም፡እንዲሁ፡ስሙ፤ፍርድ፡ለእግዚአብሔር፡ ነውና፥ከሰው፡ፊት፡አትፍሩ፤ከነገርም፡አንድ፡ነገር፡ቢከብዳችኹ፡ርሱን፡ወደ፡እኔ፡አምጡት፥እኔም፡እሰማዋ ለኹ፡ብዬ፡ፈራጆቻችኹን፡አዘዝዃቸው።
18፤በዚያን፡ጊዜም፡ልታደርጉት፡የሚገ፟ባ፟ችኹን፡ነገር፡ዅሉ፡አዘዝዃችኹ።
19፤ከኰሬብም፡ተጓዝን፥አምላካችን፡እግዚአብሔር፡እንዳዘዘን፡በታላቁ፡እጅግም፡በሚያስፈራ፡በዚያ፡ባያች ኹት፡ምድረ፡በዳ፡ዅሉ፡በኩል፡በተራራማው፡በአሞራውያን፡መንገድ፡ኼድን፤ወደ፡ቃዴስ፡በርኔም፡መጣን።
20፤እኔም፦አምላካችን፡እግዚአብሔር፡ወደሚሰጠን፡ወደ፡ተራራማው፡ወደአሞራውያን፡አገር፡መጣችኹ፤
21፤እንሆ፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ምድሪቱን፡በፊትኽ፡አድርጓል፤የአባቶችኽ፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡እን ዳለኽ፥ውጣ፥ውረሳት፤አትፍራ፥አትደንግጥም፡አልዃችኹ።
22፤እናንተም፡ዅላችኹ፡ወደ፡እኔ፡ቀርባችኹ፦ምድሪቱን፡እንዲጐበኙልንና፡እንወጣበት፡ዘንድ፡የሚገ፟ባ፟ን ን፡የመንገዱንና፡የምንገባባቸውን፡የእነዚያን፡ከተማዎች፡ወሬ፡ተመልሰው፡እንዲነግሩን፡በፊታችን፡ሰዎች፡ እንስደድ፡አላችኹኝ።
23፤ያም፡ነገር፡ደስ፡አሠኘኝ፤ከእናንተም፡ዐሥራ፡ኹለት፡ሰው፡መረጥኹ፤ከየነገዱ፡ዅሉ፡አንድ፡አንድ፡ሰው ፡ነበረ።
24፤ኼዱም፥ወደ፡ተራራማውም፡ወጡ፥ወደኤሽኮልም፡ሸለቆ፡መጥተው፡ጐበኟት።
25፤ከምድሪቱም፡ፍሬ፡በእጃቸው፡ወሰዱ፥ወደ፡እኛም፡ይዘውት፡መጡ፦አምላካችን፡እግዚአብሔር፡የሚሰጠን፡ም ድር፡መልካም፡ናት፡ብለውም፡አወሩልን።
26፤በአምላካችኹ፡በእግዚአብሔር፡ትእዛዝ፡ላይ፡ዐመፃችኹ፡እንጂ፡ወደ፡ርሷ፡መውጣትን፡እንቢ፡አላችኹ፤
27፤በድንኳናችኹም፡ውስጥ፡እንዲህ፡እያላችኹ፡አጕረመረማችኹ፦እግዚአብሔር፡ስለ፡ጠላን፥እንዲያጠፋን፡በ አሞራውያን፡እጅ፡አሳልፎ፡ይሰጠን፡ዘንድ፥ከግብጽ፡ምድር፡አወጣን።
28፤ወዴት፡እንወጣለን፧ሕዝቡ፡ብዙ፡ነው፥ቁመቱም፡ከእኛ፡ይረዝማል፥ከተማዎቹም፡ታላላቆች፡የተመሸጉም፡እ ስከ፡ሰማይም፡የደረሱ፡ናቸው፥የዔናቅንም፡ልጆች፡ደግሞ፡በዚያ፡አየናቸው፡ብለው፡ወንድሞቻችን፡ልባችንን፡ አስፈሩት።
29፤እኔም፡አልዃችኹ፦አትደንግጡ፥ከነርሱም፡አትፍሩ፤
30፤በፊታችኹ፡የሚኼደው፡አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፥እናንተ፡ስታዩ፡በግብጽና፡በምድረ፡በዳ፡እንዳደረገላ ችኹ፡ዅሉ፥ስለ፡እናንተ፡ይዋጋል፤
31፤ወደዚህም፡ስፍራ፡እስክትመጡ፡ድረስ፡በኼዳችኹበት፡መንገድ፡ዅሉ፥ሰው፡ልጁን፡እንዲሸከም፡አምላክኽ፡ እግዚአብሔር፡አንደ፡ተሸከመኽ፡አንተ፡አይተኻል።
32፤33፤ዳሩ፡ግን፡ለሰፈራችኹ፡የሚገ፟ባ፟ውን፡ስፍራ፡እንዲፈልግላችኹ፥ትኼዱበት፡ዘንድ፡የሚገ፟ባ፟ውንም ፡መንገድ፡እንዲያሳያችኹ፡ሌሊት፡በእሳት፥ቀን፡በደመና፡በፊታችኹ፡በመንገድ፡ሲኼድ፡የነበረውን፡አምላካች ኹን፡እግዚአብሔርን፡በዚህ፡ነገር፡አላመናችኹም።
34፤እግዚአብሔርም፡የቃላችኹን፡ድምፅ፡ሰምቶ፡ተቈጣ።
35፤ለአባቶቻችኹ፡እሰጣት፡ዘንድ፡የማልኹላቸውን፡መልካሚቱን፡ምድር፡ከነዚህ፡ሰዎች፡ከዚህ፡ክፉ፡ትውልድ ፡ማንም፡አያይም፥
36፤ከዮፎኒ፡ልጅ፡ከካሌብ፡በቀር፡ርሱ፡ግን፡ያያታል፤እግዚአብሔርን፡ፈጽሞ፡ተከትሏልና፥የረገጣትን፡ምድ ር፡ለርሱ፡ለልጆቹም፡እሰጣለኹ፡ብሎ፡ማለ።
37፤እግዚአብሔርም፡ደግሞ፡በእናንተ፡ምክንያት፡በእኔ፡ተቈጣ፡እንዲህም፡አለ፦አንተ፡ደግሞ፡ወደዚያ፡አት ገባም፤
38፤በፊትኽ፡የሚቆም፡የነዌ፡ልጅ፡ኢያሱ፡ርሱ፡ወደዚያ፡ይገባል፤ርሱ፡ለእስራኤል፡ምድሪቱን፡ያወርሳልና፥ አደፋፍረው።
39፤ደግሞ፦ለምርኮ፡ይኾናሉ፡ያላችዃቸው፡ሕፃናታችኹ፥ዛሬም፡መልካሙን፡ከክፉ፡መለየት፡የማይችሉ፡ልጆቻች ኹ፥እነርሱ፡ወደዚያ፡ይገባሉ፥ምድሪቱንም፡ለእነርሱ፡እሰጣለኹ፥ይወርሷታልም።
40፤እናንተ፡ግን፡ተመልሳችኹ፡በቀይ፡ባሕር፡መንገድ፡ወደ፡ምድረ፡በዳ፡ኺዱ።
41፤እናንተም፦እግዚአብሔርን፡በድለናል፤አምላካችን፡እግዚአብሔር፡እንዳዘዘን፡ዅሉ፡እንወጣለን፥እንዋጋ ማለን፡ብላችኹ፡መለሳችኹልኝ።ከእናንተም፡ሰው፡ዅሉ፡የጦር፡መሣሪያውን፡ያዘ፥ወደ፡ተራራማውም፡አገር፡መው ጣትን፡አቀለላችኹት።
42፤እግዚአብሔርም፦እኔ፡በእናንተ፡መካከል፡አይደለኹምና፡በጠላቶቻችኹ፡ፊት፡እንዳትወድቁ፡አትውጡ፥አት ዋጉም፡በላቸው፡አለኝ።እኔም፡ተናገርዃችኹ፤
43፤እናንተ፡ግን፡በእግዚአብሔር፡ትእዛዝ፡ላይ፡ዐመፃችኹ፡እንጂ፡አልሰማችኹም፤በትዕቢታችኹም፡ወደ፡ተራ ራማው፡አገር፡ወጣችኹ።
44፤በዚያም፡በተራራማው፡አገር፡ይኖሩ፡የነበር፡አሞራውያን፡ወጥተው፡ተጋጠሟችኹ፥ንብ፡እንደምታሳድድም፡ አሳደዷችኹ፥እስከ፡ሔርማም፡ድረስ፡በሴይር፡መቷችኹ።
45፤ተመልሳችኹም፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡አለቀሳችኹ፤እግዚአብሔር፡ግን፡ድምፃችኹን፡አልሰማም፥ወደ፡እናን ተም፡አላዳመጠም።
46፤እንደተቀመጣችኹበትም፡ዘመን፡መጠን፡በቃዴስ፡ብዙ፡ቀን፡ተቀመጣችኹ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡2።______________
ምዕራፍ፡2።
1፤እግዚአብሔርም፡እንዳለኝ፡ተመልሰን፡በቀይ፡ባሕር፡መንገድ፡ወደ፡ምድረ፡በዳ፡ኼድን፤የሴይርንም፡ተራራ ፡ብዙ፡ቀን፡ዞርን።
2፤እግዚአብሔርም፡እንዲህ፡ብሎ፡ተናገረኝ።
3፤ይህን፡ተራራ፡መዞር፡ይበቃችዃል፤ተመልሳችኹ፡ወደ፡ሰሜን፡ኺዱ።
4፤ሕዝቡንም፡እንዲህ፡ብለኽ፡እዘዛቸው፦በሴይር፡ላይ፡በተቀመጡት፡በወንድሞቻችኹ፡በዔሳው፡ልጆች፡አገር፡ ታልፋላችኹ፥እነርሱም፡ይፈሯችዃል፤እንግዲህ፡እጅግ፡ተጠንቀቁ።
5፤የሴይርን፡ተራራ፡ለዔሳው፡ርስት፡አድርጌ፡ስለ፡ሰጠኹ፡እኔ፡ከምድራቸው፡የጫማ፡መርገጫ፡ታኽል፡እንኳ፡ አልሰጣችኹምና፡አትጣሏቸው።
6፤ከነርሱ፡በገንዘብ፡ምግብ፡ገዝታችኹ፡ትበላላችኹ፤ውሃም፡ደግሞ፡በገንዘብ፡ገዝታችኹ፡ትጠጣላችኹ።ብ፡ገ ዝታችኹ፡ትጠጣላችኹ።
7፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡የእጅኽን፡ሥራ፡ዅሉ፡ባርኮልኻልና፤በዚህ፡በታላቅ፡ምድረ፡በዳ፡መኼድኽን፡ዐው ቋል፤በዚህ፡አርባ፡ዓመት፡ውስጥ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከአንተ፡ጋራ፡ነበረ፥አንዳችም፡አላጣኽም።
8፤በሴይርም፡ከተቀመጡት፡ከወንድሞቻችን፡ከዔሳው፡ልጆች፡በዐረባ፡መንገድ፡ከኤላትና፡ከዔጽዮንጋብር፡ዐለ ፍን።ተመልሰንም፡በሞዐብ፡ምድረ፡በዳ፡መንገድ፡ዐለፍን።
9፤እግዚአብሔርም፡አለኝ፦እኔ፡ዔርን፡ለሎጥ፡ልጆች፡ርስት፡አድርጌ፡ስለ፡ሰጠኹ፡ከምድሩ፡ርስት፡አልሰጣች ኹምና፡ሞዐብን፡አትጣላ፡በሰልፍም፡አትውጋቸው።
10፤አስቀድሞ፡ታላቅና፡ብዙ፡ሕዝብ፡እንደ፡ዔናቅም፡ልጆች፡በቁመት፡የረዘሙ፡ኤሚማውያን፡በዚያ፡ይቀመጡ፡ ነበር።
11፤እነርሱም፡ደግሞ፡እንደ፡ዔናቅ፡ልጆች፡ራፋይም፡ይባሉ፡ነበር፤ሞዐባውያን፡ግን፡ኤሚም፡ይሏቸዋል።
12፤ሖራውያንም፡ደግሞ፡አስቀድሞ፡በሴይር፡ላይ፡ተቀምጠው፡ነበር፥የዔሳው፡ልጆች፡ግን፡አሳደዷቸው፤እግዚ አብሔርም፡በሰጠው፡በርስቱ፡ምድር፡እስራኤል፡እንዳደረገ፥ከፊታቸው፡አጠፏቸው፥በስፍራቸውም፡ተቀመጡ።
13፤እግዚአብሔርም፦ተነሡ፡የዘሬድንም፡ፈፋ፡ተሻገሩ፡አለ።
14፤የዘሬድንም፡ፈፋ፡ተሻገርን።የዘሬድንም፡ፈፋ፡እስከተሻገርንበት፡ድረስ፥እግዚአብሔር፡እንደ፡ማለባቸ ው፡የሰልፈኛዎች፡ትውልድ፡ዅሉ፡ከሰፈሩ፡መካከል፡እስከጠፉ፡ድረስ፥ከቃዴስ፡በርኔ፡የተጓዝንበት፡ዘመን፡ሠ ላሳ፡ስምንት፡ዓመት፡ኾነ።
15፤ከሰፈርም፡መካከል፡ተቈርጠው፡እስኪጠፉ፡ድረስ፡የእግዚአብሔር፡እጅ፡በላያቸው፡ነበረ።
16፤እንዲህም፡ኾነ፤ሰልፈኛዎቹ፡ከጠፉ፡ከሕዝቡም፡መካከል፡ከሞቱ፡በዃላ፥
17፤እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ብሎ፡ተናገረኝ።
18፤አንተ፡ዛሬ፡የሞዐብን፡ዳርቻ፡ዔርን፡ታልፋለኽ፤
19፤ለሎጥም፡ልጆች፡ርስት፡አድርጌ፡ስለ፡ሰጠኹ፡ከዐሞን፡ልጆች፡ምድር፡ርስት፡አልሰጥኽምና፡በዐሞን፡ልጆ ች፡አቅራቢያ፡ስትደርስ፡አትጣላቸው፡አትውጋቸውም።
20፤ያም፡ደግሞ፡የራፋይም፡ምድር፡ተብሎ፡ተቈጠረ፤ራፋይምም፡አስቀድሞ፡በዚያ፡ተቀምጠው፡ነበር፤አሞናውያ ን፡ግን፡ዘምዙማውያን፡ብለው፡ይጠሯቸዋል።
21፤ታላቅና፡ብዙም፡ሕዝብ፡እንደ፡ዔናቅም፡ልጆች፡ቁመታቸው፡የረዘመ፡ነበሩ፤እግዚአብሔር፡ከፊታቸው፡አጠ ፋቸው፤እነርሱንም፡አሳደ፟ው፡በስፍራቸው፡ተቀመጡ።
22፤ሖራውያንን፡ከፊታቸው፡አጥፍቶ፡በሴይር፡ለተቀመጡት፡ለዔሳው፡ልጆች፡እንዳደረገ፡እንዲሁ፡ለእነርሱ፡ አደረገ፤እነርሱንም፡አሳደ፟ው፡በስፍራቸው፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡ተቀመጡ።
23፤እስከ፡ጋዛም፡ድረስ፡በመንደሮች፡ተቀምጠው፡የነበሩትን፡ኤዋውያንን፡ከከፍቶር፡የወጡ፡ከፍቶራውያን፡ አጠፏቸው፥በስፍራቸውም፡ተቀመጡ።
24፤ደግሞም፡አለ፦ተነሥታችኹ፡ኺዱ፥የአርኖንንም፡ሸለቆ፡ተሻገሩ፤እንሆ፥አሞራዊውን፡የሐሴቦንን፡ንጉሥ፡ ሴዎንን፡ምድሩንም፡በእጅኽ፡አሳልፌ፡ሰጥቼኻለኹ፤ርሷን፡በመውረስ፡ዠምር፥ከርሱም፡ጋራ፡ተዋጋ።
25፤ከሰማይ፡በታች፡ባሉ፡አሕዛብ፡ዅሉ፡ላይ፡ማስደንገጥኽንና፡ማስፈራትኽን፡እሰድ፟፡ዘንድ፡ዛሬ፡እዠምራ ለኹ፤ወሬኽን፡በሰሙ፡ጊዜ፡በፊትኽ፡ይንቀጠቀጣሉ፥ድንጋጤም፡ይይዛቸዋል።
26፤ከቅዴሞትም፡ምድረ፡በዳ፡የሰላምን፡ቃል፡ይነግሩት፡ዘንድ፡ወደሐሴቦን፡ንጉሥ፡ወደ፡ሴዎን፡እንዲህ፡ብ ዬ፡መልእክተኛዎችን፡ላክኹ።በአገርኽ፡ላይ፡ልለፍ፤
27፤በአውራ፡ጐዳና፡እኼዳለኹ፥ወደ፡ቀኝም፡ወደ፡ግራም፡አልተላለፍም።
28፤29፤የምበላውን፡ምግብ፡በገንዘብ፡ሽጥልኝ፥የምጠጣውንም፡ውሃ፡በገንዘብ፡ስጠኝ፤በሴይር፡የተቀመጡ፡የ ዔሳው፡ልጆች፡በዔርም፡የተቀመጡ፡ሞዐባውያን፡እንዳደረጉልኝ፥አምላካችን፡እግዚአብሔር፡ወደሚሰጠን፡ምድር ፡ዮርዳኖስን፡እስክሻገር፡ድረስ፡ብቻ፡በእግሬ፡ልለፍ።
30፤የሐሴቦን፡ንጉሥ፡ሴዎን፡ግን፡ያሳልፈን፡ዘንድ፡አልፈቀደም፤እንደ፡ዛሬው፡ዅሉ፡በእጅኽ፡አሳልፎ፡ይሰ ጠው፡ዘንድ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡መንፈሱን፡አደንድኖታልና፥ልቡንም፡አጽንቶታልና።
31፤እግዚአብሔርም፦ሴዎንንና፡ምድሩን፡በእጅኽ፡አሳልፌ፡መስጠት፥እንሆ፥ዠመርኹ፤ምድሩን፡ትገዛት፡ዘንድ ፡መውረስ፡ዠምር፡አለኝ።
32፤ሴዎንም፡ሕዝቡም፡ዅሉ፡ሊጋጠሙን፡ወደ፡ያሀጽ፡ወጡ።
33፤አምላካችንም፡እግዚአብሔር፡ርሱን፡አሳልፎ፡ሰጠን፤ርሱንም፡ልጆቹንም፡ሕዝቡንም፡ዅሉ፡መታን።
34፤በዚያን፡ጊዜም፡ከተማዎቹን፡ዅሉ፡ወሰድን፡የተቀመጡባቸውንም፡ሰዎች፡ዅሉ፡ሴቶችንም፡ሕፃናትንም፡አጠ ፋን፤አንዳችም፡አላስቀረንም፥
35፤ከብቶቻቸውንና፡ከከተማዎቻቸው፡ያገኘነውን፡ብዝበዛ፡ለራሳችን፡ወሰድን፡እንጂ።
36፤በአርኖን፡ቈላ፡አጠገብ፡ካለችው፡ከዐሮዔር፡ከሸለቆውም፡ውስጥ፡ካለችው፡ከተማ፡ዠምረን፡እስከ፡ገለዓ ድ፡ድረስ፡ማናቸዪቱም፡ከተማ፡አልጠነከረችብንም፤አምላካችን፡እግዚአብሔር፡ዅሉን፡አሳልፎ፡ሰጠን።
37፤ዳሩ፡ግን፡አምላካችን፡እግዚአብሔር፡ወደከለከለን፡ዅሉ፥ወደዐሞን፡ልጆች፡ምድር፡በያቦቅም፡ወንዝ፡አ ጠገብ፡ወዳለው፡ስፍራ፡ዅሉ፡በተራራማውም፡አገር፡ወዳሉት፡ከተማዎች፡አልደረስንም።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡3።______________
ምዕራፍ፡3።
1፤ተመልሰን፡በባሳን፡መንገድ፡ወጣን፥የባሳን፡ንጉሥ፡ዐግም፡ሕዝቡም፡ዅሉ፡በኤድራይ፡ሊዋጉን፡ወጡ።
2፤እግዚአብሔርም፦ርሱንና፡ሕዝቡን፡ዅሉ፡ምድሩንም፡በእጅኽ፡አሳልፌ፡ሰጥቻለኹና፡አትፍራው፤በሐሴቦን፡ይ ኖር፡በነበረው፡በአሞራውያን፡ንጉሥ፡በሴዎን፡ላይ፡እንዳደረግኽ፡በርሱም፡ታደርግበታለኽ፡አለኝ።
3፤አምላካችን፡እግዚአብሔርም፡ደግሞ፡የባሳንን፡ንጉሥ፡ዐግን፡ሕዝቡንም፡ዅሉ፡በእጃችን፡አሳልፎ፡ሰጠን፤ እኛም፡መታነው፤አንድ፡ሰው፡እንኳ፡አምልጦ፡አልቀረለትም።
4፤በዚያን፡ጊዜም፡ከተማዎቹን፡ዅሉ፡ወሰድን፤አንድም፡ያልወሰድነው፡የለም፤በባሳን፡ያለውን፡የዐግን፡መን ግሥት፥የአርጎብን፡አገር፡ዅሉ፥ስድሳ፡ከተማዎችን፡ወሰድን።
5፤በቅጥር፡ካልተመሸጉት፡ከእጅግ፡ብዙ፡ከተማዎች፡ሌላ፥እነዚህ፡ከተማዎች፡ዅሉ፡ቁመቱ፡ረዥም፡በኾነ፡ቅጥ ር፡በመዝጊያና፡በመወርወሪያም፡የተመሸጉ፡ነበሩ።
6፤በሐሴቦንም፡ንጉሥ፡በሴዎን፡እንዳደረግን፡ፈጽሞ፡አጠፋናቸው፤ከተማዎቹን፡ዅሉ፡ከወንዶችና፡ከሴቶች፡ከ ሕፃናትም፡ጋራ፡አጠፋናቸው።
7፤ከብቶቹን፡ዅሉ፡የከተማዎቹንም፡ምርኮ፡ለእኛ፡በዘበዝን።
8፤በዚያም፡ዘመን፡ከአርኖን፡ሸለቆ፡ዠምሮ፡እስከአርሞንዔም፡ተራራ፡ድረስ፡ምድሪቱን፡በዮርዳኖስ፡ማዶ፡ከ ነበሩ፡ከኹለቱ፡ከአሞራውያን፡ነገሥታት፡እጅ፡ወሰድን፤
9፤ሲዶናውያን፡አርሞንዔምን፡ሢርዮን፡ብለው፡ይጠሩታል፥አሞራውያንም፡ሳኔር፡ብለው፡ይጠሩታል።
10፤በሜዳውም፡ያሉትን፡ከተማዎች፡ዅሉ፥ገለዓድንም፡ዅሉ፥በባሳንም፡ያሉትን፡የዐግን፡መንግሥት፡ከተማዎች ፡እስከ፡ሰልካና፡እስከ፡ኤድራይ፡ድረስ፡ባሳንን፡ዅሉ፡ወሰድን።
11፤ከራፋይም፡ወገን፡የባሳን፡ንጉሥ፡ዐግ፡ብቻውን፡ቀርቶ፡ነበር፤እንሆ፥ዐልጋው፡የብረት፡ዐልጋ፡ነበረ፤ ርሱ፡በዐሞን፡ልጆች፡አገር፡በነበረባት፡አለ፤ርዝመቱ፡ዘጠኝ፡ክንድ፡ወርዱም፡አራት፡ክንድ፡በሰው፡ክንድ፡ ልክ፡ነበረ።
12፤ይህችንም፡ምድር፡በዚያን፡ዘመን፡ወረስን፤በአርኖንም፡ሸለቆ፡አጠገብ፡ካለችው፡ከዐሮዔር፡ዠምሮ፡የገ ለዓድን፡ተራራማ፡አገር፡እኩሌታ፡ከተማዎቹንም፡ለሮቤልና፡ለጋድ፡ነገድ፡ሰጠዃቸው።
13፤ከገለዓድም፡የቀረውን፡የዐግንም፡መንግሥት፡ባሳንን፡ዅሉ፥የአርጎብንም፡ምድር፡ዅሉ፡ለምናሴ፡ነገድ፡ እኩሌታ፡ሰጠኹ፤ያችም፡ባሳን፡ዅሉ፡የራፋይም፡አገር፡ተብላ፡ተቈጠረች።
14፤የምናሴ፡ልጅ፡ኢያዕር፡እስከ፡ጌሹራውያንና፡እስከማዕካታውያን፡ዳርቻ፡ድረስ፡የአርጎብን፡ምድር፡ዅሉ ፡ወሰደ፤ይህችንም፡የባሳንን፡ምድር፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡በስሙ፡የኢያዕር፡መንደሮች፡ብሎ፡ጠራ።
15፤ለማኪርም፡ገልዓድን፡ሰጠኹት።
16፤ለሮቤል፡ነገድና፡ለጋድም፡ነገድ፡ከገለዓድ፡ዠምሮ፡እስከአርኖን፡ሸለቆ፡ድረስ፡የሸለቆውን፡እኩሌታ፡ ዳርቻውንም፥እስከዐሞን፡ልጆች፡ዳርቻ፡እስከያቦቅ፡ወንዝ፡ድረስ፥
17፤ከኪኔሬት፡እስከዐረባ፡ባሕር፡ርሱም፡የጨው፡ባሕር፡ድረስ፡ከፈስጋ፡ተራራ፡በታች፡ወደ፡ምሥራቅ፡ያለው ን፡ዐረባ፡ዮርዳኖስንም፡ዳሩንም፡ሰጠዃቸው።
18፤በዚያም፡ዘመን፡እንዲህ፡ብዬ፡አዘዝዃችኹ።አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡ይህችን፡ምድር፡ርስት፡አድርጎ፡ ሰጥቷችዃል፤መሣሪያችኹን፡ይዛችኹ፡እናንተ፡ዐርበኛዎች፡ዅሉ፡በወንድሞቻችኹ፡በእስራኤል፡ልጆች፡ፊት፡ትሻ ገራላችኹ።
19፤ነገር፡ግን፥እጅግ፡ከብቶች፡እንዳሏችኹ፡ዐውቃለኹና፡ሴቶቻችኹና፡ልጆቻችኹ፡ከብቶቻችኹም፡በሰጠዃችኹ ፡ከተማዎች፡ይቀመጣሉ፤
20፤ይኸውም፡እግዚአብሔር፡እናንተን፡እንዳሳረፈ፥ወንድሞቻችኹን፡እስኪያሳርፍ፡ድረስ፡እነርሱም፡ደግሞ፡ በዮርዳኖስ፡ማዶ፡አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡የሚሰጣቸውን፡ምድር፡እስኪወርሱ፡ድረስ፡ነው፤ከዚያም፡በዃላ፡ እናንተ፡ዅሉ፡ወደሰጠዃችኹ፡ርስት፡ትመለሳላችኹ።
21፤በዚያም፡ጊዜ፡ኢያሱን፦አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡በእነዚህ፡በኹለቱ፡ነገሥት፡ያደረገውን፡ዅሉ፡ዐይኖ ችኽ፡አይተዋል፤እንዲሁ፡በምታልፍባቸው፡መንግሥታት፡ዅሉ፡ላይ፡እግዚአብሔር፡ያደርጋል።
22፤አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡ርሱ፡ስለ፡እናንተ፡ይዋጋልና፥አትፍራቸውም፡ብዬ፡አዘዝኹት።
23፤በዚያም፡ዘመን፡እኔ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ብዬ፡ለመንኹ።
24፤ጌታ፡እግዚአብሔር፡ሆይ፥ታላቅነትኽን፡የጸናችውንም፡እጅኽን፡ለእኔ፡ለባሪያኽ፡ማሳየት፡ዠምረኻል፤በ ሰማይና፡በምድርም፡እንደ፡ሥራኽ፡እንደ፡ኀይልኽም፡ይሠራ፡ዘንድ፡የሚችል፡አምላክ፡ማን፡ነው፧
25፤እኔ፡ልሻገር፡በዮርዳኖስም፡ማዶ፡ያለችውን፡መልካሚቱን፡ምድር፡ያንም፡መልካሙን፡ተራራማውን፡አገር፡ ሊባኖስንም፡ልይ።
26፤እግዚአብሔር፡ግን፡በእናንተ፡ምክንያት፡ተቈጣኝ፡አልሰማኝምም፤እግዚአብሔርም፡አለኝ፦ይበቃኻል፤በዚ ህ፡ነገር፡ደግመኽ፡አትናገረኝ።
27፤ይህን፡ዮርዳኖስን፡አትሻገርምና፡ወደፈስጋ፡ራስ፡ውጣ፤ዐይንኽንም፡ወደ፡ምዕራብ፡ወደ፡ሰሜንም፡ወደ፡ ደቡብም፡ወደ፡ምሥራቅም፡አንሥተኽ፡በዐይንኽ፡ተመልከት።
28፤ኢያሱ፡በዚህ፡ሕዝብ፡ፊት፡ይሻገራልና፥አንተም፡የምታያትን፡ምድር፡ርሱ፡ያወርሳቸዋልና፥ኢያሱን፡እዘ ዘው፥አደፋፍረውም፥አጽናውም።
29፤በቤተ፡ፌጎርም፡ፊት፡ለፊት፡በሸለቆው፡ውስጥ፡ተቀመጥን።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡4።______________
ምዕራፍ፡4።
1፤አኹንም፥እስራኤል፡ሆይ፥እንድታደርጓቸው፡በሕይወትም፡እንድትኖሩ፥የአባቶቻችኹም፡አምላክ፡እግዚአብሔ ር፡ወደሚሰጣችኹ፡ምድር፡ገብታችኹ፡እንድትወርሱ፥የማስተምራችኹን፡ሥርዐትና፡ፍርድ፡ስሙ።
2፤እኔ፡ያዘዝዃችኹን፡የአምላካችኹን፡የእግዚአብሔርን፡ትእዛዝ፡ትጠብቃላችኹ፡እንጂ፡ባዘዝዃችኹ፡ቃል፡ላ ይ፡አትጨምሩም፥ከርሱም፡አታጐድሉም።
3፤ብዔልፌጎርን፡የተከተሉትን፡ሰዎች፡ዅሉ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከመካከላችኹ፡እንዳጠፋ፥እግዚአብሔር ፡በብዔልፌጎር፡ያደረገውን፡ዐይኖቻችኹ፡አይተዋል።
4፤እናንተ፡ግን፡አምላካችኹን፡እግዚአብሔርን፡የተከተላችኹ፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡ዅላችኹ፡በሕይወት፡ትኖራ ላችኹ።
5፤እንሆ፥እናንተ፡ገብታችኹ፡በምትወርሷት፡ምድር፡ውስጥ፡እንዲህ፡ታደርጉ፡ዘንድ፡አምላኬ፡እግዚአብሔር፡ እንዳዘዘኝ፡ሥርዐትንና፡ፍርድን፡አስተማርዃችኹ።
6፤ጠብቋት፡አድርጓትም፤ይህችን፡ሥርዐት፡ዅሉ፡ሰምተው።በእውነት፡ይህ፡ታላቅ፡ሕዝብ፡ጠቢብና፡አስተዋይ፡ ሕዝብ፡ነው፡በሚሉ፡በአሕዛብ፡ፊት፡ጥበባችኹና፡ማስተዋላችኹ፡ይህ፡ነውና፤
7፤አምላካችን፡እግዚአብሔር፡በምንጠራው፡ጊዜ፡ዅሉ፡እንደሚቀርበን፥አምላኩ፡ወደ፡ርሱ፡የቀረበው፡ታላቅ፡ ሕዝብ፡ማን፡ነው፧
8፤በዐይናችኹ፡ፊት፡ዛሬ፡እንደማኖራት፡እንደዚች፡ሕግ፡ዅሉ፡ጽድቅ፡የኾነች፡ሥርዐትና፡ፍርድ፡ያለው፡ታላ ቅ፡ሕዝብ፡ማን፡ነው፧
9፤10፤እግዚአብሔር፦ሕዝቡን፡ወደ፡እኔ፡ሰብስብ፥በምድርም፡በሕይወት፡በሚኖሩበት፡ዘመን፡ዅሉ፡እኔን፡መፍ ራት፡ይማሩ፡ዘንድ፥ልጆቻቸውንም፡ያስተምሩ፡ዘንድ፡ቃሌን፡አሰማቸዋለኹ፡ብሎ፡በተናገረኝ፡ጊዜ፥በአምላክኽ ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡በኰሬብ፡በቆምኽበት፡ቀን፡ዐይኖችኽ፡ያዩትን፡ነገር፡እንዳትረሳ፥በሕይወትኽም፡ዘመ ን፡ዅሉ፡ከልብኽ፡እንዳይወድቅ፡ተጠንቀቅ፥ነፍስኽንም፡በትጋት፡ጠብቅ፤ለልጆችኽም፡ለልጅ፡ልጆችኽም፡አስታ ውቀው።
11፤እናንተም፡ቀርባችኹ፡ከተራራው፡በታች፡ቆማችኹ፡ነበር፤እስከ፡ሰማይም፡መካከል፡ድረስ፡እሳት፡በተራራ ው፡ላይ፡ይነድ፟፡ነበር፤ጨለማና፡ደመና፡ድቅድቅ፡ጨለማም፡ነበረ።
12፤እግዚአብሔርም፡በእሳት፡ውስጥ፡ኾኖ፡ተናገራችኹ፤የቃልን፡ድምፅ፡ሰማችኹ፥መልክ፡ግን፡አላያችኹም፤ድ ምፅን፡ብቻ፡ሰማችኹ።
13፤ታደርጉትም፡ዘንድ፡ያዘዛችኹን፡ቃል፡ኪዳን፡ዐሥሩን፡ቃላት፡ነገራችኹ፤በኹለቱም፡በድንጋይ፡ጽላቶች፡ ላይ፡ጻፋቸው።
14፤ትወርሷት፡ዘንድ፡ተሻግራችኹ፡በምትገቡባት፡ምድር፡የምታደርጓትን፡ሥርዐትና፡ፍርድ፡አስተምራችኹ፡ዘ ንድ፡እግዚአብሔር፡በዚያን፡ጊዜ፡አዘዘኝ።
15፤እግዚአብሔር፡በኰሬብ፡በእሳት፡ውስጥ፡ኾኖ፡በተናገራችኹ፡ጊዜ፡መልክ፡ከቶ፡አላያችኹምና፡እጅግ፡ተጠ ንቀቁ፤
16፤እንዳትረክሱ፥የተቀረጸውን፡ምስል፡የማናቸውንም፡ነገር፡ምሳሌ፥በወንድ፡ወይም፡በሴት፡መልክ፡የተሠራ ውን፥
17፤በምድር፡ላይ፡ያለውን፡የእንስሳን፡ዅሉ፡ምሳሌ፥በሰማይም፡በታች፡የሚበረ፟ውን፡የወፍን፡ዅሉ፡ምሳሌ፥
18፤በምድርም፡ላይ፡የሚሽከረከረውን፡ዅሉ፡ምሳሌ፥ከምድርም፡በታች፡በውሃ፡ውስጥ፡የሚኖረውን፡የዓሣን፡ዅ ሉ፡ምሳሌ፡እንዳታደርጉ፥
19፤ዐይኖችኽን፡ወደ፡ሰማይ፡አንሥተኽ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከሰማይ፡ዅሉ፡በታች፡ላሉት፡አሕዛብ፡ዅሉ ፡የሰጣቸውን፡ፀሓይንና፡ጨረቃን፡ከዋክብትንና፡የሰማይን፡ሰራዊት፡ዅሉ፡ባየኽ፡ጊዜ፥ሰግደኽላቸው፡አምልከ ኻቸውም፡እንዳትስት፡ተጠንቀቅ።
20፤እናንተን፡ግን፡እንደ፡ዛሬው፡ዅሉ፡የርስቱ፡ሕዝብ፡ትኾኑለት፡ዘንድ፡እግዚአብሔር፡ወስዶ፡ከብረት፡እ ቶን፡ከግብጽ፡አወጣችኹ።
21፤እግዚአብሔርም፡በእናንተ፡ምክንያት፡ተቈጣኝ፥ዮርዳኖስንም፡እንዳልሻገር፥አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ ርስት፡አድርጎ፡ወደሚሰጥኽ፡ወደ፡መልካሚቱ፡ምድር፡እንዳልገባ፡ማለ።
22፤እኔ፡ግን፡በዚች፡ምድር፡እሞታለኹ፥ዮርዳኖስንም፡አልሻገርም፤እናንተ፡ግን፡ትሻገራላችኹ፥ያችንም፡መ ልካሚቱን፡ምድር፡ትወርሳላችኹ።
23፤አምላካችኹም፡እግዚአብሔር፡ከእናንተ፡ጋራ፡የተማማለውን፡ቃል፡ኪዳን፡እንዳትረሱ፥አምላክኽም፡እግዚ አብሔር፡የከለከለውን፡በማናቸውም፡ቅርጽ፡የተቀረጸውን፡ምስል፡እንዳታደርጉ፡ተጠንቀቁ።
24፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡የሚበላ፡እሳት፡ቀናተኛም፡አምላክ፡ነውና።
25፤ልጆችን፡የልጅ፡ልጆችንም፥በወለዳችኹ፡ጊዜ፡በምድሪቱም፡ብዙ፡ዘመን፡በተቀመጣችኹ፡ጊዜ፥በረከሳችኹም ፡ጊዜ፥በማናቸውም፡ቅርጽ፡የተቀረጸውን፡ምስል፡ባደረጋችኹ፡ጊዜ፥ታስቈጡትም፡ዘንድ፡በአምላካችኹ፡በእግዚ አብሔር፡ፊት፡ክፉ፡የኾነውን፡ነገር፡በሠራችኹ፡ጊዜ፥
26፤ትወርሷት፡ዘንድ፡ዮርዳኖስን፡ተሻግራችኹ፡ከምትገቡባት፡ምድር፡ፈጥናችኹ፡እንድትጠፉ፡እኔ፡ዛሬ፡ሰማ ይንና፡ምድርን፡በእናንተ፡አስመሰክራለኹ፤ፈጽሞም፡ትጠፋላችኹ፡እንጂ፡ረዥም፡ዘመን፡አትቀመጡባትም።
27፤እግዚአብሔርም፡በአሕዛብ፡መካከል፡ይበትናችዃል፥እግዚአብሔር፡በውስጣቸው፡በሚያኖራችኹ፡በአሕዛብ፡ መካከልም፡ጥቂቶች፡ኾናችኹ፡ትቀራላችኹ።
28፤በዚያም፡የማያዩትን፡የማይሰሙትንም፡የማይበሉትንም፡የማያሸቱትንም፥በሰው፡እጅ፡ከዕንጨትና፡ከድንጋ ይ፡የተሠሩትን፡አማልክት፡ታመልካላችኹ።
29፤ነገር፡ግን፥ከዚያ፡አምላካችኹን፡እግዚአብሔርን፡ትሻላችኹ፤በልብኽም፡ዅሉ፡በነፍስኽም፡ዅሉ፡የፈለግ ኸው፡እንደ፡ኾነ፡ታገኘዋለኽ።
30፤ይህም፡ዅሉ፡በደረሰብኽ፡ጊዜ፥ስትጨነቅ፥በዘመኑ፡ፍጻሜ፡ወደ፡አምላክኽ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ትመለሳለ ኽ፥ቃሉንም፡ትሰማለኽ።
31፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡መሓሪ፡አምላክ፡ነውና፥አይተውኽም፥አያጠፋኽምም፥ለአባቶችኽም፡የማለላቸውን ፡ቃል፡ኪዳኑን፡አይረሳም።
32፤እግዚአብሔር፡ሰውን፡በምድር፡ላይ፡ከፈጠረው፡ዠምሮ፥ከሰማይ፡ዳር፡እስከ፡ዳርቻዋ፡ድረስ፡ከቶ፡እንዲ ህ፡ያለ፡ታላቅ፡ነገር፡ወይም፡እንደ፡ርሱ፡ያለ፡ተሰምቶ፡እንደ፡ኾነ፡ከአንተ፡በፊት፡የነበረውን፡የቀደመው ን፡ዘመን፡ጠይቅ።
33፤አንተ፡ከእሳት፡ውስጥ፡ኾኖ፡ሲናገር፡የእግዚአብሔርን፡ድምፅ፡እንደ፡ሰማኽ፥ሌላ፡ሕዝብ፡ሰምቶ፡በሕይ ወት፡ይኖራልን፧
34፤አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡በዐይናችኹ፡ፊት፡በግብጽ፡ለእናንተ፡እንደ፡ሠራው፡ዅሉ፥በፈተናና፡በተኣም ራት፥በድንቅና፡በሰልፍ፥በጸናች፡እጅና፡በተዘረጋ፡ክንድ፡በታላቅም፡ማስፈራት፡እግዚአብሔር፡ከሌላ፡ሕዝብ ፡መካከል፡ገብቶ፡ለርሱ፡ሕዝብን፡ይወስድ፡ዘንድ፡ሞክሮ፡ነበርን፧
35፤እግዚአብሔርም፡አምላክ፡እንደ፡ኾነ፡ታውቅ፡ዘንድ፡ይህ፡ለአንተ፡ተገለጠ፤ከርሱም፡ሌላ፡አምላክ፡የለ ም።
36፤ያስተምርኽ፡ዘንድ፡ከሰማይ፡ድምፁን፡አሰማኽ፤በምድርም፡ላይ፡ታላቁን፡እሳት፡አሳየኽ፤ከእሳትም፡ውስ ጥ፡ቃሉን፡ሰማኽ።
37፤38፤አባቶችኽን፡ወዷ፟ልና፥ከነርሱ፡በዃላ፡ዘራቸውን፡መረጠ፥ዛሬ፡እንደኾነው፡ዅሉ፡ከአንተ፡የጸኑትን ፡ታላላቆችን፡አሕዛብ፡በፊትኽ፡እንዲያወጣ፥አንተንም፡እንዲያገባኽ፥ምድራቸውንም፡ርስት፡አድርጎ፡እንዲሰ ጥኽ፥ከአንተ፡ጋራ፡ኾኖ፡በታላቅ፡ኀይሉ፡ከግብጽ፡አወጣኽ።
39፤እንግዲህ፡እግዚአብሔር፡በላይ፡በሰማይ፡በታችም፡በምድር፡አምላክ፡እንደ፡ኾነ፥ሌላም፡እንደሌለ፡ዛሬ ፡ዕወቅ፥በልብኽም፡ያዝ።
40፤ለአንተ፡ከአንተም፡በዃላ፡ለልጆችኽ፡መልካም፡ይኾን፡ዘንድ፥አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ለዘለዓለም፡በ ሚሰጥኽ፡ምድር፡ዕድሜኽ፡ይረዝም፡ዘንድ፥እኔ፡ዛሬ፡የማዝ፟ኽን፡ሥርዐቱንና፡ትእዛዙን፡ጠብቅ።
41፤42፤በዚያን፡ጊዜ፡ሙሴ፡ትናንት፡ከትናንት፡በስቲያም፡ጠላቱ፡ያልኾነውን፡ባልንጀራውን፡ሳያውቅ፡የገደ ለ፡ገዳዩ፡ይሸሽባቸው፡ዘንድ፥ከነዚህም፡ከተማዎች፡ወደ፡አንዲቱ፡ሸሽቶ፡በሕይወት፡ይኖር፡ዘንድ፡በምሥራቅ ፡በኩል፡በዮርዳኖስ፡ማዶ፡ሦስት፡ከተማዎች፡ለየ።
43፤ከተማዎቹም፡ለሮቤል፡ነገድ፡በምድረ፡በዳ፡በደልዳላ፡ስፍራ፡ያለ፡ቦሶር፥ለጋድም፡ነገድ፡በገለዓድ፡ያ ለ፡ራሞት፥ለምናሴም፡ነገድ፡በባሳን፡ያለ፡ጎላን፡ነበሩ።
44፤ሙሴም፡በእስራኤል፡ልጆች፡ፊት፡ያኖራት፡ሕግ፡ይህች፡ናት፤
45፤46፤ሙሴና፡የእስራኤል፡ልጆች፡ከግብጽ፡ከወጡ፡በዃላ፡በመቱት፥በሐሴቦን፡ተቀምጦ፡በነበረው፡በአሞራው ያን፡ንጉሥ፡በሴዎን፡ምድር፥በቤተ፡ፌጎር፡አንጻር፡ባለው፡ሸለቆ፡በዮርዳኖስ፡ማዶ፥ከግብጽ፡በወጡ፡ጊዜ፡ሙ ሴ፡ለእስራኤል፡ልጆች፡የተናገረው፡ምስክርና፡ሥርዐት፡ፍርድም፡ይህ፡ነው።
47፤የርሱንና፡የባሳንን፡ንጉሥ፡የዐግን፡ምድር፥በምሥራቅ፡በኩል፡በዮርዳኖስ፡ማዶ፡የነበሩትን፡የኹለቱን ፡የአሞራውያንን፡ነገሥታት፡ምድር፥
48፤በአርኖን፡ወንዝ፡ዳር፡ካለችው፡ከዐሮዔር፡ዠምሮ፡እስከሲዎን፡ተራራ፡እስከ፡አርሞንዔም፡ድረስ፥
49፤በምሥራቅ፡በኩል፡በዮርዳኖስ፡ማዶ፡ከፈስጋ፡ተራራ፡በታች፡ያለውን፡ዐረባ፡ዅሉ፡እስከዐረባ፡ባሕር፡ድ ረስ፡ወሰዱ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡5።______________
ምዕራፍ፡5።
1፤ሙሴም፡እስራኤልን፡ዅሉ፡ጠርቶ፡አላቸው፦እስራኤል፡ሆይ፥እንድትማሯት፡በማድረግም፡እንድትጠብቋት፡ዛሬ ፡በዦሯችኹ፡የምናገራትን፡ሥርዐትና፡ፍርድ፡ስሙ።
2፤አምላካችን፡እግዚአብሔር፡በኰሬብ፡ከእኛ፡ጋራ፡ቃል፡ኪዳን፡አደረገ።
3፤እግዚአብሔር፡ዛሬ፡በዚህ፡በሕይወት፡ካለነው፡ከእኛ፡ከዅላችን፡ጋራ፡እንጂ፡ከአባቶቻችን፡ጋራ፡ይህችን ፡ቃል፡ኪዳን፡አላደረገም።
4፤በተራራው፡ላይ፡በእሳት፡ውስጥ፡ኾኖ፡እግዚአብሔር፡ፊት፡ለፊት፡ተናገራችኹ።
5፤እኔ፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡እነግራችኹ፡ዘንድ፡በዚያን፡ጊዜ፡በእግዚአብሔርና፡በእናንተ፡መካከል፡ቆሜ ፡ነበር፤እናንተ፡በእሳቱ፡ምክንያት፡ፈርታችዃልና፥ወደ፡ተራራውም፡አልወጣችኹምና።ርሱም፡አለ፦
6፤ከግብጽ፡ምድር፡ከባርነት፡ቤት፡ያወጣኹኽ፡እግዚአብሔር፡አምላክኽ፡እኔ፡ነኝ።
7፤ከእኔ፡በቀር፡ሌላዎች፡አማልክት፡አይኹኑልኽ።
8፤በላይ፡በሰማይ፡ካለው፥በታችም፡በምድር፡ካለው፥ከምድርም፡በታች፡በውሃ፡ካለው፡ነገር፡የማናቸውንም፡ም ሳሌ፡የተቀረጸውንም፡ምስል፡ለአንተ፡አታድርግ፤
9፤10፤በሚጠሉኝ፡እስከ፡ሦስተኛና፡እስከ፡አራተኛ፡ትውልድ፡ድረስ፡የአባቶችን፡ኀጢአት፡በልጆች፡ላይ፡የማ መጣ፤ለሚወዱኝ፡ትእዛዜንም፡ለሚጠብቁ፡እስከ፡ሺሕ፡ትውልድ፡ድረስ፡ምሕረትን፡የማደርግ፡እኔ፡እግዚአብሔር ፡አምላክኽ፡ቀናተኛ፡አምላክ፡ነኛና፡አትስገድላቸው፥አታምልካቸውም።
11፤የእግዚአብሔርን፡የአምላክኽን፡ስም፡በከንቱ፡አትጥራ፤እግዚአብሔር፡ስሙን፡በከንቱ፡የሚጠራውን፡ከበ ደል፡አያነጻውምና።
12፤እግዚአብሔር፡አምላክኽ፡እንዳዘዘኽ፡የሰንበትን፡ቀን፡ትቀድሰው፡ዘንድ፡ጠብቅ።
13፤ስድስት፡ቀን፡ሥራ፡ተግባርኽንም፡ዅሉ፡አድርግ፥
14፤ሰባተኛው፡ቀን፡ግን፡ለእግዚአብሔር፡አምላክኽ፡ሰንበት፡ነው፤አንተ፡እንደምታርፍ፡ሎሌኽና፡ገረድኽ፡ ያርፉ፡ዘንድ፥አንተ፡ወንድ፡ልጅኽም፡ሴት፡ልጅኽም፡ሎሌኽም፡ገረድኽም፡በሬኽም፡አህያኽም፡ከብትኽም፡ዅሉ፡ በደጆችኽም፡ውስጥ፡ያለ፡እንግዳ፡በርሱ፡ምንም፡ሥራ፡አትሥሩ።
15፤አንተም፡በግብጽ፡ባሪያ፡እንደ፡ነበርኽ፡ዐስብ፤እግዚአብሔር፡አምላክኽ፡በጸናች፡እጅና፡በተዘረጋ፡ክ ንድ፡ከዚያ፡አወጣኽ፤ስለዚህ፥እግዚአብሔር፡አምላክኽ፡የሰንበትን፡ቀን፡ትጠብቅ፡ዘንድ፡አዘዘኽ።
16፤እግዚአብሔር፡አምላክኽ፡እንዳዘዘኽ፡አባትኽንና፡እናትኽን፡አክብር፤እግዚአብሔር፡አምላክኽ፡በሚሰጥ ኽ፡ምድር፡ላይ፡ዕድሜኽ፡እንዲረዝም፥መልካምም፡እንዲኾንልኽ።
17፤አትግደል።
18፤አታመንዝር።
19፤አትስረቅ።
20፤በባልንጀራኽ፡ላይ፡በሐሰት፡አትመስክር።
21፤የባልንጀራኽን፡ሚስት፡አትመኝ፤የባልንጀራኽንም፡ቤት፡ዕርሻውንም፡ሎሌውንም፡ገረዱንም፡በሬውንም፡አ ህያውንም፥ከባልንጀራኽ፡ገንዘብ፡ዅሉ፡ማናቸውንም፡አትመኝ።
22፤እግዚአብሔር፡በተራራው፡ላይ፡በእሳትና፡በደመናው፡በጨለማውም፡ውስጥ፡ኾኖ፡በታላቅ፡ድምፅ፡እነዚህን ፡ቃሎች፡ለጉባኤያችኹ፡ዅሉ፡ተናገረ፤ምንም፡ምን፡አልጨመረም።በኹለቱም፡የድንጋይ፡ጽላቶች፡ላይ፡ጻፋቸው፥ ለኔም፡ሰጣቸው።
23፤ተራራው፡በእሳት፡ሲነድ፟፡ከጨለማው፡ውስጥ፡ድምፁን፡በሰማችኹ፡ጊዜ፥እናንተ፥የነገዶቻችኹ፡አለቃዎች ፡ሽማግሌዎቻችኹም፥ወደ፡እኔ፡ቀረባችኹ፤
24፤አላችኹም፦እንሆ፥አምላካችን፡እግዚአብሔር፡ክብሩንና፡ታላቅነቱን፡አሳይቶናል፥ከእሳቱም፡ውስጥ፡ድም ፁን፡ሰምተናል፤እግዚአብሔርም፡ከሰው፡ጋራ፡ሲነጋገር፡ሰውዮውም፡በሕይወት፡ሲኖር፡ዛሬ፡አይተናል።
25፤አኹን፡እንግዲህ፡ይህች፡ታላቂቱ፡እሳት፡ታቃጥለናለችና፡ለምን፡እንሞታለን፧እኛ፡የአምላካችንን፡የእ ግዚአብሔርን፡ድምፅ፡ደግሞ፡ብንሰማ፡እንሞታለን።
26፤ከሥጋ፡ለባሽ፡ዅሉ፡እኛ፡እንደ፡ሰማን፡በእሳት፡ውስጥ፡ኾኖ፡ሲናገር፡የሕያው፡አምላክን፡ድምፅ፡ሰምቶ ፡በሕይወቱ፡የኖረ፡ማን፡ነው፧
27፤አንተ፡ቅረብ፥አምላካችን፡እግዚአብሔር፡የሚለውን፡ዅሉ፡ስማ፤አምላካችን፡እግዚአብሔርም፡ለአንተ፡የ ሚናገረውን፡ዅሉ፡ለእኛ፡ንገረን፤እኛም፡ሰምተን፡እናደርገዋለን።
28፤በተናገራችኹኝም፡ጊዜ፡እግዚአብሔር፡የእናንተን፡ቃል፡ድምፅ፡ሰማ፤እግዚአብሔርም፡አለኝ፦ይህ፡ሕዝብ ፡የተናገሩኽን፡ቃል፡ድምፅ፡ሰምቻለኹ፤የተናገሩኽ፡ዅሉ፡መልካም፡ነገር፡ነው።
29፤ለእነርሱም፡ለዘለዓለምም፡ለልጆቻቸው፡መልካም፡ይኾንላቸው፡ዘንድ፥እንዲፈሩኝ፡ዅልጊዜም፡ትእዛዜን፡ ዅሉ፡እንዲጠብቁ፡እንዲህ፡ያለ፡ልብ፡ምነው፡በኾነላቸው!
30፤ኼደኽ፦ወደ፡ድንኳናችኹ፡ተመለሱ፡በላቸው።
31፤አንተ፡ግን፡በዚህ፡በእኔ፡ዘንድ፡ቁም፥ርስት፡አድርጌ፡በምሰጣቸውም፡ምድር፡ላይ፡ያደርጓት፡ዘንድ፡የ ምታስተምራቸውን፡ትእዛዜንና፡ሥርዐቴን፡ፍርዴንም፡ዅሉ፡እነግርኻለኹ።
32፤እግዚአብሔር፡አምላካችኹ፡እንዳዘዛችኹ፡ታደርጉ፡ዘንድ፡ጠብቁ፤ከርሱም፡ወደ፡ቀኝም፡ወደ፡ግራም፡ፈቀ ቅ፡አትበሉ።
33፤በሕይወት፡እንድትኖሩ፥መልካምም፡እንዲኾንላችኹ፥በምትወርሷትም፡ምድር፡ዕድሜያችኹ፡እንዲረዝም፥እግ ዚአብሔር፡አምላካችኹ፡ባዘዛችኹ፡መንገድ፡ዅሉ፡ኺዱ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡6።______________
ምዕራፍ፡6።
1፤2፤አንተ፡ልጅኽም፡የልጅ፡ልጅኽም፡በዕድሜያችኹ፡ዅሉ፡ልትወርሷት፡በምትገቡባት፡ምድር፡ታደርጓት፡ዘን ድ፥አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡ፈርተኽ፡እኔ፡ለአንተ፡ያዘዝኹትን፡ሥርዐቱንና፡ትእዛዙን፡ዅሉ፡ትጠብቅ፡ዘ ንድ፥ዕድሜኽም፡ይረዝም፡ዘንድ፥አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡እንዳስተምራችኹ፡ያዘዛት፡ትእዛዝና፡ሥርዐት፡ፍ ርድም፡ይህች፡ናት።
3፤እንግዲህ፥እስራኤል፡ሆይ፥ስማ፤መልካምም፡እንዲኾንልኽ፥የአባቶችኽም፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ተ ናገረ፡ወተትና፡ማር፡በምታፈሰ፟ው፡ምድር፡እጅግ፡እንድትበዛ፥ታደርጋት፡ዘንድ፡ጠብቅ።
4፤እስራኤል፡ሆይ፥ስማ፤አምላካችን፡እግዚአብሔር፡አንድ፡እግዚአብሔር፡ነው፤
5፤አንተም፡አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡በፍጹም፡ልብኽ፡በፍጹምም፡ነፍስኽ፡በፍጹምም፡ኀይልኽ፡ውደድ።
6፤እኔም፡ዛሬ፡አንተን፡የማዘ፟ውን፡ይህን፡ቃል፡በልብኽ፡ያዝ።
7፤ለልጆችኽም፡አስተምረው፥በቤትኽም፡ስትቀመጥ፥በመንገድም፡ስትኼድ፥ስትተኛም፥ስትነሣም፡ተጫወተው።
8፤በእጅኽም፡ምልክት፡አድርገኽ፡እሰረው፤በዐይኖችኽም፡መካከል፡እንደክታብ፡ይኹንልኽ።
9፤በቤትኽም፡መቃኖች፡በደጃፍኽም፡በሮች፡ላይ፡ጻፈው።
10፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ለአንተ፡ሊሰጣት፡ለአባቶችኽ፡ለአብርሃምና፡ለይሥሐቅ፡ለያዕቆብም፡ወደ፡ማለ ላቸው፡ምድር፡ባገባኽ፡ጊዜ፤ያልሠራኻቸውንም፡ታላቅና፡መልካም፡ከተማዎች፥
11፤ያልሞላኻቸውንም፡ሀብትን፡የሞሉ፡ቤቶች፥ያልማስኻቸውንም፡የተማሱ፡ጕድጓዶች፥ያልተከልኻቸውንም፡ወይ ንና፡ወይራ፡በሰጠኽ፡ጊዜ፥በበላኽና፡በጠገብኽም፡ጊዜ፤
12፤በዚያን፡ጊዜ፡ከግብጽ፡ምድር፡ከባርነት፡ቤት፡ያወጣኽን፡እግዚአብሔርን፡እንዳትረሳ፡ተጠንቀቅ።
13፤አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡ፍራ፤ርሱንም፡አምልክ፤በስሙም፡ማል።
14፤15፤በመካከልኽ፡ያለው፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ቀናተኛ፡አምላክ፡ነውና፥የአምላክኽ፡የእግዚአብሔር፡ ቍጣ፡እንዳይነድ፟ብኽ፡ከምድርም፡ፊት፡እንዳያጠፋኽ፥በዙሪያችኹ፡ያሉት፡አሕዛብ፡የሚያመልኳቸውን፡ሌላዎች ን፡አማልክት፡አትከተሉ።
16፤በማሣህ፡እንደ፡ፈተናችኹት፡አምላካችኹን፡እግዚአብሔርን፡አትፈታተኑት።
17፤ለእናንተ፡ያዘዘውን፡የአምላካችኹን፡የእግዚአብሔርን፡ትእዛዝ፡ምስክሩንም፡ሥርዐቱንም፡አጥብቃችኹ፡ ጠብቁ።
18፤19፤መልካምም፡ይኾንልኽ፡ዘንድ፥እግዚአብሔርም፡ለአባቶችኽ፡ወደማለላቸው፡ወደመልካሚቱ፡ምድር፡ገብተ ኽ፡ርሷን፡ትወርስ፡ዘንድ፥እግዚአብሔርም፡እንደ፡ተናገረ፡ጠላቶችኽን፡ዅሉ፡ከፊትኽ፡ያወጣልኽ፡ዘንድ፥በእ ግዚአብሔር፡ፊት፡ቅኑንና፡መልካሙን፡አድርግ።
20፤በዃለኛው፡ዘመንም፡ልጅኽ፦አምላካችን፡እግዚአብሔር፡ያዘዛችኹ፡ምስክርና፡ሥርዐት፡ፍርድስ፡ምንድር፡ ነው፧ብሎ፡በጠየቀኽ፡ጊዜ፥
21፤አንተ፡ልጅኽን፡በለው፦በግብጽ፡የፈርዖን፡ባሪያዎች፡ነበርን፤እግዚአብሔርም፡በጽኑ፡እጅ፡ከግብጽ፡አ ወጣን፤
22፤እግዚአብሔርም፡ከግብጽና፡በፈርዖን፡በቤቱም፡ዅሉ፡ላይ፡እኛ፡እያየን፡ታላቅና፡ክፉ፡ምልክት፡ተኣምራ ትም፡አደረገ።
23፤ለአባቶቻችን፡ወደማለላቸው፡ምድር፡አግብቶ፡ርሷን፡ይሰጠን፡ዘንድ፡ከዚያ፡አወጣን።
24፤እንደ፡ዛሬም፡በሕይወት፡እንዲያኖረን፥ዅልጊዜም፡መልካም፡እንዲኾንልን፥አምላካችንን፡እግዚአብሔርን ፡እንፈራ፡ዘንድ፥ይህችንም፡ሥርዐት፡ዅሉ፡እናደርግ፡ዘንድ፡እግዚአብሔር፡አዘዘን።
25፤ርሱም፡እንዳዘዘን፡በአምላካችን፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡እናደርጋት፡ዘንድ፡ይህችን፡ትእዛዝ፡ዅሉ፡ብን ጠብቅ፡ለእኛ፡ጽድቅ፡ይኾንልናል።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡7።______________
ምዕራፍ፡7።
1፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ልትወርሳት፡ወደምትገባባት፡ምድር፡ባመጣኽ፡ጊዜ፥ከፊትኽም፡ብዙ፡አሕዛብን፥ከ አንተ፡የበለጡትን፡የበረቱትንም፡ሰባቱን፡አሕዛብ፥ኬጢያዊውን፡ጌርጌሳዊውንም፡አሞራዊውንም፡ከነዓናዊውን ም፡ፌርዛዊውንም፡ዔዊያዊውንም፡ኢያቡሳዊውንም፡ባወጣ፡ጊዜ፥
2፤አምላክኽ፡እግዚአብሔርም፡በእጅኽ፡አሳልፎ፡በሰጣቸው፡በመታኻቸውም፡ጊዜ፥ፈጽመኽ፡አጥፋቸው፤ከነርሱም ፡ጋራ፡ቃል፡ኪዳን፡አታድርግ፥አትማራቸውም፤
3፤ከነርሱም፡ጋራ፡አትጋባ፤ሴት፡ልጅኽን፡ለወንድ፡ልጁ፡አትስጥ፥ሴት፡ልጁንም፡ለወንድ፡ልጅኽ፡አትውሰድ።
4፤እንዳይከተለኝ፡ሌላዎችንም፡አማልክት፡እንዲያመልክ፡ልጅኽን፡ያስታልና፤የእግዚአብሔርም፡ቍጣ፡ይነድ፟ ባችዃል፥ፈጥኖም፡ያጠፋችዃል።
5፤ነገር፡ግን፥እንዲህ፡አድርጉባቸው፤መሠዊያቸውን፡አፍርሱ፥ሐውልቶቻቸውንም፡ሰባብሩ፥የማምለኪያ፡ዐጸዶ ቻቸውንም፡ቍረጡ፥የተቀረጸውን፡ምስላቸውንም፡በእሳት፡አቃጥሉ።
6፤ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡አንተ፡ቅዱስ፡ሕዝብ፡ነኽና፤በምድር፡ፊት፡ከሚኖሩ፡አሕዛብ፡ዅሉ፡ይልቅ፡ለ ርሱ፡ለራሱ፡ሕዝብ፡ትኾንለት፡ዘንድ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡መረጠኽ።
7፤እግዚአብሔርም፡የወደዳችኹና፡የመረጣችኹ፡ከአሕዛብ፡ዅሉ፡በቍጥር፡ስለ፡በዛችኹ፡አይደለም፤እናንተ፡ከ አሕዛብ፡ዅሉ፡በቍጥር፡ጥቂቶች፡ነበራችኹና፤
8፤ነገር፡ግን፥እግዚአብሔር፡ስለ፡ወደዳችኹ፡ለአባቶቻችኹም፡የማለላቸውን፡መሐላ፡ስለ፡ጠበቀ፥ስለዚህ፡እ ግዚአብሔር፡በጽኑ፡እጅ፡አወጣችኹ፥ከባርነትም፡ቤት፡ከግብጽ፡ንጉሥ፡ከፈርዖን፡እጅ፡አዳናችኹ።
9፤አንተም፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ርሱ፡አምላክ፡እንደ፡ኾነ፥ለሚወዱትም፡ትእዛዙንም፡ለሚጠብቁ፡ቃል፡ኪ ዳኑንና፡ምሕረቱን፡እስከ፡ሺሕ፡ትውልድ፡ድረስ፡የሚጠብቅ፡የታመነ፡አምላክ፡እንደ፡ኾነ፡ዕወቅ፤
10፤የሚጠሉትን፡ለማጥፋት፡በፊታቸው፡ብድራት፡ይመልስባቸዋል፤ለሚጠላው፡አይዘገይም፥ነገር፡ግን፥በፊቱ፡ ብድራት፡ይመልስበታል።
11፤እንግዲህ፡ታደርጋት፡ዘንድ፡እኔ፡ዛሬ፡ለአንተ፡የማዛ፟ትን፡ትእዛዝና፡ሥርዐት፡ፍርድንም፡ጠብቅ።
12፤እንዲህም፡ይኾናል፤ይህችን፡ፍርድ፡ሰምተኽ፡ብትጠብቃት፡ብታደርጋትም፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ለአባ ቶችኽ፡የማለውን፡ቃል፡ኪዳንና፡ምሕረት፡ለአንተ፡ይጠብቅልኻል፤
13፤ይወድ፟ኽማል፥ይባርክኽማል፥ያበዛኽማል፤ይሰጥኽም፡ዘንድ፡ለአባቶችኽ፡በማለላቸው፡ምድር፡የሆድኽን፡ ፍሬ፡የመሬትኽንም፡ፍሬ፥እኽልኽን፡ወይንኽንም፡ዘይትኽንም፥የከብትኽንም፡ብዛት፡የበግኽንም፡መንጋ፡ይባር ክልኻል።
14፤ከአሕዛብም፡ዅሉ፡ይልቅ፡የተባረክኽ፡ትኾናለኽ፤በሰውኽና፡በከብትኽም፡ዘንድ፡ወንድ፡ቢኾን፡ወይም፡ሴ ት፡ብትኾን፡መካን፡አይኾንብኽም።
15፤እግዚአብሔርም፡ሕማምን፡ዅሉ፡ከአንተ፡ያርቃል፤የምታውቀውንም፡ክፉውን፡የግብጽ፡በሽታ፡ዅሉ፡ባንተ፡ ላይ፡አያደርስብኽም፥በጠላቶችኽም፡ዅሉ፡ላይ፡ያመጣባቸዋል።
16፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡በእጅኽ፡አሳልፎ፡የሚጥላቸውን፡አሕዛብን፡ዅሉ፡ታጠፋቸዋለኽ፤ዐይንኽም፡አ ታዝንላቸውም፤ያም፡ወጥመድ፡ይኾንብኻልና፥አማልክታቸውን፡አታምልካቸው።
17፤በልብኽም፦እነዚህ፡አሕዛብ፡ከእኔ፡ይልቅ፡ይበዛሉና፡አወጣቸው፡ዘንድ፡እንዴት፡እችላለኹ፧ብትል፥አት ፍራቸው፤
18፤ነገር፡ግን፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በፈርዖንና፡በግብጽ፡ዅሉ፡ያደረገውን፥
19፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፥ዐይንኽ፡እያየች፥ታላቅን፡መቅሠፍት፡ምልክትንም፡ተኣምራትንም፡የጸናችውን፡ እጅ፡የተዘረጋውንም፡ክንድ፡አድርጎ፡እንዳወጣኽ፥ዐስብ፤እንዲሁ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡አንተ፡በምትፈራ ቸው፡በአሕዛብ፡ዅሉ፡ላይ፡ያደርጋል።
20፤ደግሞም፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡የቀሩት፡ከፊትኽም፡የተሸሸጉት፡እስኪጠፉ፡ድረስ፡ተርብ፡ይሰድ፟ባቸ ዋል።
21፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፥ታላቅና፡የሚያስፈራ፡አምላክ፥በመካከልኽ፡ነውና፥ከነርሱ፡የተነሣ፡አትደንግ ጥ።
22፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡እነዚህን፡አሕዛብ፡በጥቂት፡በጥቂቱ፡ከፊትኽ፡ያወጣቸዋል፤የምድረ፡በዳ፡አ ራዊት፡እንዳይበዙብኽ፡አንድ፡ጊዜ፡ታጠፋቸው፡ዘንድ፡አይገ፟ባ፟ኽም።
23፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ግን፡እነርሱን፡በእጅኽ፡አሳልፎ፡ይሰጣቸዋል፥እስኪጠፉም፡ድረስ፡በታላቅ፡ድ ንጋጤ፡ያስደነግጣቸዋል።
24፤ነገሥታታቸውንም፡በእጅኽ፡አሳልፎ፡ይሰጣቸዋል፥ስማቸውንም፡ከሰማይ፡በታች፡ታጠፋለኽ፤እስክታጠፋቸው ፡ድረስ፡ማንም፡በፊትኽ፡ይቆም፡ዘንድ፡አይችልም።
25፤የተቀረጸውንም፡የአምላኮቻቸውን፡ምስል፡በእሳት፡ታቃጥላለኽ፤የተሠራባቸውን፡ብርና፡ወርቅ፡አትመኝ፤ በአምላክኽም፡በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ርኩስ፡ነውና፥እንዳትጠመድበት፡ከርሱ፡ምንም፡አትውሰድ።
26፤እንደ፡ርሱም፡ርጉም፡እንዳትኾን፡ርኩስን፡ነገር፡ወደ፡ቤትኽ፡አታግባ፤ርጉም፡ነውና፥ተጸየፈው፥ጥላው ም።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡8።______________
ምዕራፍ፡8።
1፤በሕይወት፡እንድትኖሩ፥እንድትበዙም፥እግዚአብሔርም፡ለአባቶቻችኹ፡ወደማለላቸው፡ምድር፡ገብታችኹ፡እን ድትወርሷት፥ዛሬ፡ለአንተ፡የማዘ፟ውን፡ትእዛዝ፡ዅሉ፡ታደርጉ፡ዘንድ፡ጠብቁ።
2፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ይፈትንኽ፡ዘንድ፥በልብኽም፡ያለውን፡ትእዛዙን፡ትጠብቅ፡ወይም፡አትጠብቅ፡እን ደ፡ኾነ፡ያውቅ፡ዘንድ፥ሊያስጨንቅኽ፡በእነዚህ፡በአርባ፡ዓመታት፡በምድረ፡በዳ፡የመራኽን፡መንገድ፡ዅሉ፡ዐ ስብ።
3፤ሰውም፡ከእግዚአብሔር፡አፍ፡በሚወጣ፡ነገር፡ዅሉ፡በሕይወት፡እንዲኖር፡እንጂ፡ሰው፡በእንጀራ፡ብቻ፡በሕ ይወት፡እንዳይኖር፡ያስታውቅኽ፡ዘንድ፡አስጨነቀኽ፥አስራበኽም፥አንተም፡ያላወቅኸውን፡አባቶችኽም፡ያላወቁ ትን፡መና፟፡አበላኽ።
4፤በእነዚህ፡አርባ፡ዓመታት፡የለበስኸው፡ልብስ፡አላረጀም፥እግርኽም፡አላበጠም።
5፤ሰውም፡ልጁን፡እንደሚገሥጽ፡እንዲሁም፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡አንተን፡እንዲገሥጽ፡በልብኽ፡አስተውል ።
6፤በመንገዱም፡እንድትኼድ፡ርሱንም፡እንድትፈራ፡የአምላክኽን፡የእግዚአብሔርን፡ትእዛዝ፡ጠብቅ።
7፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ወደ፡መልካም፡ምድር፥ከሸለቆና፡ከኰረብታ፡የሚመነጩ፡የውሃ፡ጅረቶችና፡ፈሳሾች ፡ምንጮችም፡ወዳሉባት፡ምድር፥
8፤ስንዴ፡ገብስም፡ወይንም፡በለስም፡ሮማንም፡ወይራም፡ማርም፡ወደሞሉባት፡ምድር፥
9፤ሳይጐድልኽ፡እንጀራን፡ወደምትበላባት፡አንዳችም፡ወደማታጣባት፡ምድር፥ድንጋይዋ፡ብረት፡ወደ፡ኾነ፥ከተ ራራዋም፡መዳብ፡ወደሚማስባት፡ምድር፡ያገባኻል።
10፤ትበላማለኽ፥ትጠግብማለኽ፥ስለሰጠኽም፡ስለመልካሚቱ፡ምድር፡አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡ትባርካለኽ።
11፤ዛሬ፡እኔ፡አንተን፡የማዘ፟ውን፡ትእዛዙንና፡ፍርዱን፡ሥርዐቱንም፡ባለመጠበቅ፡አምላክኽን፡እግዚአብሔ ርን፡እንዳትረሳ፡ተጠንቀቅ፤
12፤ከበላኽና፡ከጠገብኽ፡በዃላ፥መልካምም፡ቤት፡ሠርተኽ፡ከተቀመጥኽበት፡በዃላ፥
13፤የላምና፡የበግ፡መንጋ፡ከበዛልኽ፡በዃላ፥ብርኽና፡ወርቅኽም፡ያለኽም፡ዅሉ፡ከበዛልኽ፡በዃላ፥ልብኽ፡እ ንዳይጓደድ፤
14፤ከግብጽም፡ምድር፡ከባርነት፡ቤት፡ያወጣኽን፥
15፤እባብና፡ጊንጥ፡ጥማትም፡ባለባት፥ውሃም፡በሌለባት፥በታላቂቱና፡በምታስፈራው፡ምድረ፡በዳ፡የመራኽን፥ ከጭንጫ፡ድንጋይም፡ውሃን፡ያወጣልኽን፥
16፤በመጨረሻም፡ዘመን፡መልካም፡ያደርግልኽ፡ዘንድ፡ሊፈትንኽ፡ሊያዋርድኽም፡አባቶችኽ፡ያላወቁትን፡መና፟ ፡በምድረ፡በዳ፡ያበላኽን፡አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡እንዳትረሳ፤
17፤በልብኽም፦ጕልበቴ፡የእጄም፡ብርታት፡ይህን፡ሀብት፡አመጣልኝ፡እንዳትል።
18፤ነገር፡ግን፥ዛሬ፡እንደ፡ኾነ፡ለአባቶችኽ፡የማለውን፡ቃል፡ኪዳን፡ያጸና፡ዘንድ፥ሀብት፡ለማከማቸት፡ር ሱ፡ጕልበት፡ሰጥቶኻልና፥አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡ዐስብ።
19፤አምላክኽንም፡እግዚአብሔርን፡ብትረሳ፥ሌላዎችንም፡አማልክት፡ብትከተል፡ብታመልካቸውም፡ብትሰግድላቸ ውም፥ፈጽሞ፡እንድትጠፉ፡እኔ፡ዛሬውኑ፡እመሰክርባችዃለኹ።
20፤የአምላካችኹን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ስላልሰማችኹ፡እግዚአብሔር፡ከፊታችኹ፡እንደሚያጠፋቸው፡እንደ ፡አሕዛብ፡እንዲሁ፡እናንተ፡ትጠፋላችኹ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡9።______________
ምዕራፍ፡9።
1፤እስራኤል፡ሆይ፥ስማ፤ከአንተ፡የበለጡትንና፡የበረቱትን፡አሕዛብ፥እስከ፡ሰማይም፡ድረስ፡የተመሸጉትን፡ ታላላቆች፡ከተማዎች፡ለመውረስ፡ትገቡ፡ዘንድ፡ዛሬ፡ዮርዳኖስን፡ትሻገረዋለኽ።
2፤አንተም፡የምታውቃቸው፡ስለ፡እነርሱም፦በዔናቅ፡ልጆች፡ፊት፡መቆም፡ማን፡ይችላል፧ሲባል፡የሰማኸው፡ታላ ቁና፡ረዥሙ፡ሕዝብ፡የዔናቅ፡ልጆች፡ናቸው።
3፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡እንደሚበላ፡እሳት፡ኾኖ፡በፊትኽ፡እንዲያልፍ፡ዛሬ፡ዕወቅ፤ርሱ፡ያጠፋቸዋል፥ በፊትኽም፡ያዋርዳቸዋል፤እግዚአብሔርም፡እንደ፡ነገረኽ፡አንተ፡ታሳድዳቸዋለኽ፥ፈጥነኽም፡ታጠፋቸዋለኽ።
4፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከፊትኽ፡ካወጣቸው፡በዃላ፦ስለ፡ጽድቄ፡እወርሳት፡ዘንድ፡ወደዚች፡ምድር፡እግዚ አብሔር፡አገባኝ፡ስትል፡በልብኽ፡አትናገር፤እነዚህን፡አሕዛብ፡ስለ፡ኀጢአታቸው፡እግዚአብሔር፡ከፊትኽ፡ያ ወጣቸዋል።
5፤ምድራቸውን፡ትወርሳት፡ዘንድ፡የምትገባው፡ስለ፡ጽድቅኽና፡ስለ፡ልብኽ፡ቅንነት፡አይደለም፤ነገር፡ግን፥ አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከፊትኽ፡በሚያጠፋቸው፡በእነዚያ፡አሕዛብ፡ኀጢአት፡ምክንያትና፡ለአባቶችኽ፡ለአብ ርሃምና፡ለይሥሐቅ፡ለያዕቆብም፡የማለላቸውን፡ቃል፡ይፈጽም፡ዘንድ፡ነው።
6፤እንግዲህ፡አንተ፡ዐንገተ፡ደንዳና፡ሕዝብ፡ነኽና፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ይህችን፡መልካም፡ምድር፡ርስ ት፡አድርጎ፡የሰጠኽ፡ስለ፡ጽድቅኽ፡እንዳይደለ፡ዕወቅ።
7፤አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡በምድረ፡በዳ፡እንዳስቈጣኸው፤ከግብጽ፡አገር፡ከወጣኽበት፡ቀን፡ዠምሮ፡ወደ ዚህ፡ስፍራ፡እስከመጣችኹ፡ድረስ፡በእግዚአብሔር፡ላይ፡እንዳመፃችኹ፡ዐስብ፥አትርሳ።
8፤በኰሬብ፡ደግሞ፡እግዚአብሔርን፡አስቈጣችኹ፤እግዚአብሔርም፡ሊያጠፋችኹ፡ተቈጣባችኹ።
9፤የድንጋዩን፡ጽላቶች፥እግዚአብሔር፡ከእናንተ፡ጋራ፡የተማማለባቸውን፡የቃል፡ኪዳን፡ጽላቶች፥እቀበል፡ዘ ንድ፡ወደ፡ተራራ፡በወጣኹ፡ጊዜ፥በተራራው፡አርባ፡ቀንና፡አርባ፡ሌሊት፡ተቀምጬ፡ነበር፤እንጀራ፡አልበላኹም ፥ውሃም፡አልጠጣኹም።
10፤እግዚአብሔርም፡በእግዚአብሔር፡ጣት፡የተጻፉትን፡ኹለት፡የድንጋይ፡ጽላቶች፡ሰጠኝ፤ስብሰባ፡ተደርጎ፡ በነበረበትም፡ቀን፡እግዚአብሔር፡በተራራው፡ላይ፡በእሳት፡ውስጥ፡ኾኖ፡የነገራችኹ፡ቃል፡ዅሉ፡ተጽፎባቸው፡ ነበር።
11፤ከአርባ፡ቀንና፡ከአርባ፡ሌሊትም፡በዃላ፡እግዚአብሔር፡ኹለቱን፡የድንጋይ፡ጽላቶች፥የቃል፡ኪዳኑን፡ጽ ላቶች፥ሰጠኝ።
12፤እግዚአብሔርም፦ተነሥተኽ፡ከዚህ፡ፈጥነኽ፡ውረድ፤ከግብጽ፡ያወጣኻቸው፡ሕዝብኽ፡ረክሰዋል፤ፈጥነው፡ካ ዘዝዃቸው፡መንገድ፡ፈቀቅ፡ብለዋል፥ቀልጦ፡የተሠራ፡ምስልም፡ለራሳቸው፡አድርገዋል፡አለኝ።
13፤እግዚአብሔርም፦ይህ፡ሕዝብ፡ዐንገተ፡ደንዳና፡ሕዝብ፡እንደ፡ኾነ፡አይቻለኹ፤
14፤አጠፋቸው፡ዘንድ፥ስማቸውንም፡ከሰማይ፡በታች፡እደመስስ፡ዘንድ፡ተወኝ፤አንተንም፡ከነርሱ፡ለሚበረታና ፡ለሚበዛ፡ሕዝብ፡አደርግኻለኹ፡ብሎ፡ተናገረኝ።
15፤እኔም፡ተመልሼ፡ከተራራው፡ወረድኹ፥ተራራውም፡በእሳት፡ይነድ፟፡ነበር፤ኹለቱም፡የቃል፡ኪዳን፡ጽላቶች ፡በኹለቱ፡እጆቼ፡ነበሩ።
16፤ተመለከትኹም፤እንሆ፥አምላካችኹን፡እግዚአብሔርን፡በድላችኹ፡ነበር፥ለእናንተም፡ቀልጦ፡የተሠራ፡የጥ ጃ፡ምስል፡ሠርታችኹ፡ነበር፤እግዚአብሔር፡ካዘዛችኹ፡መንገድ፡ፈጥናችኹ፡ፈቀቅ፡ብላችኹ፡ነበር።
17፤ኹለቱንም፡ጽላቶች፡ያዝኹ፥ከኹለቱም፡እጆቼ፡ጣልዃቸው፥እናንተም፡ስታዩ፡ሰበርዃቸው።
18፤19፤ስለሠራችኹት፡ኀጢአት፡ዅሉ፥ርሱንም፡ለማስቈጣት፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ክፉ፡የኾነውን፡ነገር፡ስላ ደረጋችኹ፥እግዚአብሔር፡ሊያጠፋችኹ፡ከተቈጣባችኹ፡ከቍጣውና፡ከመዓቱ፡የተነሣ፡ስለ፡ፈራኹ፥እንደ፡ፊተኛው ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡አርባ፡ቀንና፡አርባ፡ሌሊት፡ወደቅኹ፤እንጀራ፡አልበላኹም፥ውሃም፡አልጠጣኹም።እግዚ አብሔርም፡በዚያን፡ጊዜ፡ደግሞ፡ሰማኝ።
20፤እግዚአብሔርም፡አሮንን፡ሊያጠፋው፡እጅግ፡ተቈጣው፤ስለ፡አሮንም፡ደግሞ፡በዚያን፡ጊዜ፡ጸለይኹ።
21፤ያደረጋችኹትንም፡ኀጢአት፡ጥጃውን፡ወሰድኹ፥በእሳትም፡አቃጠልኹት፥አደቀቅኹትም፥እንደ፡ትቢያም፡እስ ኪኾን፡ድረስ፡ፈጨኹት፤ትቢያውንም፡ከተራራ፡በሚወርድ፡ወንዝ፡ጣልኹት።
22፤በተቤራም፣በማሣህም፣በምኞት፡መቃብርም፡እግዚአብሔርን፡አስቈጣችኹት።
23፤እግዚአብሔርም፦ውጡ፥የሰጠዃችኹንም፡ምድር፡ውረሱ፡ብሎ፡ከቃዴስ፡በርኔ፡በላካችኹ፡ጊዜ፥በአምላካችኹ ፡በእግዚአብሔር፡ቃል፡ዐመፃችኹ፥በርሱም፡አላመናችኹም፥ድምፁንም፡አልሰማችኹም።
24፤እናንተን፡ካወቅኹበት፡ቀን፡ዠምሮ፡በእግዚአብሔር፡ዐመፀኛዎች፡ነበራችኹ።
25፤እግዚአብሔርም፦አጠፋችዃለኹ፡ብሎ፡ስለ፡ተናገረ፡በወደቅኹበት፡ዘመን፡አርባ፡ቀንና፡አርባ፡ሌሊት፡በ እግዚአብሔር፡ፊት፡ወደቅኹ።
26፤በእግዚአብሔርም፡ፊት፡እንዲህ፡ብዬ፡ጸለይኹ፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡ሆይ፥በታላቅነትኽ፡የተቤዠኸውን፥በ ጠነከረችውም፡እጅ፡ከግብጽ፡ያወጣኸውን፡ሕዝብኽንና፡ርስትኽን፡አታጥፋ።
27፤ባሪያዎችኽን፡አብርሃምንና፡ይሥሐቅን፣ያዕቆብንም፡ዐስብ፤የዚህን፡ሕዝብ፡ደንዳናነት፣ክፋቱንም፣ኀጢ አቱንም፡አትመልከት፤
28፤ከርሷ፡እኛን፡ያወጣኽባት፡ምድር፡ሰዎች፦እግዚአብሔር፡ተስፋ፡ወደሰጣቸው፡ምድር፡ያገባቸው፡ዘንድ፡አ ልቻለምና፥ጠልቷቸውማልና፥ስለዚህ፡በምድረ፡በዳ፡ሊገድላቸው፡አወጣቸው፡እንዳይሉ።
29፤እነርሱም፡በታላቅ፡ኀይልኽ፡በተዘረጋውም፡ክንድኽ፡ያወጣኻቸው፡ሕዝብኽና፡ርስትኽ፡ናቸው።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡10።______________
ምዕራፍ፡10።
1፤በዚያን፡ጊዜ፡እግዚአብሔር፦እንደ፡ፊተኛዎች፡ያሉትን፡ኹለት፡የድንጋይ፡ጽላቶች፡ጠርበኽ፡ወደ፡እኔ፡ወ ደ፡ተራራው፡ውጣ፥ለአንተም፡የዕንጨት፡ታቦት፡ሥራ፤
2፤በሰበርኻቸውም፡በፊተኛዎቹ፡ጽላቶች፡የነበሩትን፡ቃሎች፡በእነዚህ፡ጽላቶች፡እጽፋለኹ፥በታቦቱም፡ውስጥ ፡ታደርጋቸዋለኽ፡አለኝ።
3፤ከግራርም፡ዕንጨት፡ታቦትን፡ሠራኹ፥እንደ፡ፊተኛዎችም፡ኹለት፡የድንጋይ፡ጽላቶች፡ጠረብኹ፤ኹለቱንም፡ጽ ላቶች፡በእጄ፡ይዤ፡ወደ፡ተራራው፡ወጣኹ።
4፤ስብሰባ፡ተደርጎ፡በነበረበትም፡ቀን፡እግዚአብሔር፡በተራራው፡ላይ፡በእሳት፡ውስጥ፡ኾኖ፡የተናገራችኹን ፡ዐሠርቱን፡ቃላት፡ቀድሞ፡ተጽፈው፡እንደ፡ነበረ፡በጽላቶቹ፡ላይ፡ጻፈ፤እግዚአብሔርም፡እነርሱን፡ለእኔ፡ሰ ጠኝ።
5፤ተመልሼም፡ከተራራው፡ወረድኹ፥ጽላቶችንም፡በሠራኹት፡ታቦት፡ውስጥ፡አደረግዃቸው፤እግዚአብሔርም፡እንዳ ዘዘኝ፡በዚያ፡ኖሩ።
6፤የእስራኤልም፡ልጆች፡ከብኤሮት፡ብኔያዕቃን፡ወደ፡ሞሴራ፡ተጓዙ፤በዚያም፡አሮን፡ሞተ፡በዚያም፡ተቀበረ፤ በርሱም፡ፋንታ፡ልጁ፡አልዓዛር፡ካህን፡ኾነ።
7፤ከዚያም፡ወደ፡ጕድጐዳ፡ተጓዙ፤ከጕድጐዳም፡ወደ፡ውሃ፡ፈሳሾች፡ምድር፡ወደ፡ዮጥባታ፡ተጓዙ።
8፤በዚያን፡ጊዜ፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡ይሸከም፡ዘንድ፥ርሱንም፡ለማገልገል፡በእግዚአብሔር ፡ፊት፡ይቆም፡ዘንድ፥በስሙም፡ይባርክ፡ዘንድ፡እግዚአብሔር፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡የሌዊን፡ነገድ፡ለየ።
9፤ስለዚህ፥ለሌዊ፡ከወንድሞቹ፡ጋራ፡ክፍልና፡ርስት፡የለውም፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ተናገረው፥እ ግዚአብሔር፡ርስቱ፡ነው።
10፤እኔም፡እንደ፡ፊተኛው፡ጊዜ፡አርባ፡ቀንና፡አርባ፡ሌሊት፡በተራራው፡ላይ፡ተቀመጥኹ፤እግዚአብሔርም፡በ ዚህ፡ጊዜ፡ደግሞ፡ሰማኝ፤እግዚአብሔር፡ሊያጠፋኽ፡አልወደደም።
11፤እግዚአብሔርም፦ተነሥተኽ፡በሕዝቡ፡ፊት፡ተጓዝ፤ለአባቶቻቸውም፡ልሰጣቸው፡ወደማልኹላቸው፡ምድር፡ይግ ቡ፡ይውረሷትም፡አለኝ።
12፤13፤እስራኤል፡ሆይ፥አኹንስ፡አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡ትፈራ፡ዘንድ፥በመንገዱም፡ዅሉ፡ትኼድ፡ዘንድ ፥አምላክኽንም፡እግዚአብሔርን፡ትወድ፟፡ዘንድ፥በፍጹምም፡ልብኽ፡በፍጹምም፡ነፍስኽ፡ታመልከው፡ዘንድ፥መል ካምም፡እንዲኾንልኽ፡ዛሬ፡ለአንተ፡የማዘ፟ውን፡የእግዚአብሔርን፡ትእዛዝና፡ሥርዐት፡ትጠብቅ፡ዘንድ፡ነው፡ እንጂ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከአንተ፡የሚፈልገው፡ምንድር፡ነው፧
14፤እንሆ፥ሰማይ፡ሰማየ፡ሰማያትም፥ምድርም፡በርሷም፡ያለው፡ዅሉ፡የአምላክኽ፡የእግዚአብሔር፡ነው።
15፤ብቻ፡እግዚአብሔር፡ስለ፡አባቶችኽ፡ደስ፡ብሎታል፥እነርሱንም፡ወዷ፟ል፤ከነርሱም፡በዃላ፡እናንተን፡ዘ ራቸውን፡እንደ፡ዛሬው፡ዅሉ፡ከአሕዛብ፡ዅሉ፡መካከል፡መረጠ።
16፤17፤እንግዲህ፡አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡የአማልክት፡አምላክ፣የጌታዎችም፡ጌታ፥ታላቅ፡አምላክ፣ኀያል ም፡የሚያስፈራም፥በፍርድ፡የማያደላ፥መማለጃም፡የማይቀበል፡ነውና፥እናንተ፡የልባችኹን፡ሸለፈት፡ግረዙ፥ከ እንግዲህ፡ወዲህም፡ዐንገተ፡ደንዳና፡አትኹኑ።
18፤ለድኻ፡አደጉና፡ለመበለቲቱ፡ይፈርዳል፥መብልና፡ልብስም፡ይሰጠው፡ዘንድ፡ስደተኛውን፡ይወዳ፟ል።
19፤እናንተ፡በግብጽ፡አገር፡ስደተኛዎች፡ነበራችኹና፡ስለዚህ፡ስደተኛውን፡ውደዱ።
20፤አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡ፍራ፥ርሱንም፡አምልክ፤ከርሱም፡ተጣበቅ፥በስሙም፡ማል።
21፤ዐይኖችኽ፡ያዩትን፡እነዚህን፡ታላላቆች፡የሚያስፈሩትንም፡ነገሮች፡ያደረገልኽ፡ርሱ፡ክብርኽ፡ነው፥ር ሱም፡አምላክኽ፡ነው።
22፤አባቶችኽ፡ሰባ፡ነፍስ፡ኾነው፡ወደ፡ግብጽ፡ወረዱ፤አኹንም፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ብዛትኽን፡እንደሰ ማይ፡ከዋክብት፡አደረገ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡11።______________
ምዕራፍ፡11።
1፤እንግዲህ፡አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡ውደድ፥ሕጉንም፡ሥርዐቱንም፡ፍርዱንም፡ትእዛዙንም፡ዅል፡ጊዜ፡ጠ ብቅ።
2፤የአምላካችኹን፡የእግዚአብሔርን፡ተግሣጽ፥ታላቅነቱንም፥የጸናችም፡እጁን፥የተዘረጋውንም፡ክንዱን፥
3፤በግብጽም፡መካከል፡በንጉሡ፡በፈርዖንና፡በአገሩ፡ዅሉ፡ላይ፡ያደረጋትን፡ተኣምራቱንና፡ሥራውን፥
4፤በተከተሏችኹም፡ጊዜ፡በቀይ፡ባሕር፡ውሃ፡እንዳሰጠማቸው፥እግዚአብሔርም፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡እንዳጠፋቸ ው፥በግብጽ፡ጭፍራ፡በፈረሶቻቸውም፡በሠረገላዎቻቸውም፡ያደረገውን፥
5፤ወደዚህ፡ስፍራ፡እስክትመጡ፡ድረስ፡በምድረ፡በዳ፡ያደረገላችኹን፥
6፤በእስራኤልም፡ዅሉ፡መካከል፡ምድር፡አፏን፡ከፍታ፡እነርሱንና፡ቤተ፡ሰቦቻቸውን፡ድንኳኖቻቸውንም፡ለእነ ርሱም፡የነበራቸውን፡ዅሉ፡በዋጠቻቸው፡በሮቤል፡ልጅ፡በኤልያብ፡ልጆች፡በዳታንና፡በአቤሮን፡ያደረገውን፡ላ ላወቁትና፡ላላዩት፡ልጆቻችኹ፡አልነግራቸውምና፡እናንተ፡ዛሬ፡ዕወቁ።
7፤ነገር፡ግን፥እግዚአብሔር፡ያደረጋትን፡ታላቂቱን፡ሥራ፡ዅሉ፡ዐይኖቻችኹ፡አይተዋል።
8፤9፤እንግዲህ፡እንድትጠነክሩ፥ትወርሷትም፡ዘንድ፡ወደምትሻገሩባት፡ምድር፡እንድትገቡ፡እንድትወርሷትም ፥እግዚአብሔርም፡ለእነርሱና፡ለዘራቸው፡ይሰጣት፡ዘንድ፡በማለላቸው፡ወተትና፡ማርም፡በምታፈሰ፟ው፡ምድር፡ ዕድሜያችኹ፡እንዲረዝም፥ዛሬ፡ለእናንተ፡የማዘ፟ውን፡ትእዛዝ፡ዅሉ፡ጠብቁ።
10፤ትወርሳት፡ዘንድ፡የምትገባባት፡ምድር፥በአትክልት፡ስፍራ፡እንደሚዘሩ፡ዘርኽን፡እንደዘራኽባት፥በእግ ርኽም፡እንዳጠጣኻት፥እንደ፡ወጣኽባት፡እንደ፡ግብጽ፡ምድር፡አይደለችም።
11፤ነገር፡ግን፥ትወርሷት፡ዘንድ፡ተሻግራችኹ፡የምትገቡባት፡ምድር፡ኰረብታና፡ሸለቆ፡ያለባት፡አገር፡ናት ፤በሰማይ፡ዝናብ፡ውሃ፡ትረካለች።
12፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡የሚጐበኛት፡አገር፡ናት፤ከዓመቱ፡መዠመሪያ፡እስከዓመቱ፡መጨረሻ፡ድረስ፡የአ ምላክኽ፡የእግዚአብሔር፡ዐይን፡ዅል፡ጊዜ፡በርሷ፡ላይ፡ነው።
13፤እንዲህም፡ይኾናል፤እናንተ፡አምላካችኹን፡እግዚአብሔርን፡ትወዱ፡ዘንድ፥በፍጹምም፡ልባችኹ፡በፍጹምም ፡ነፍሳችኹ፡ታመልኩት፡ዘንድ፡ዛሬ፡ለእናንተ፡የማዘ፟ውን፡ትእዛዜን፡ፈጽማችኹ፡ብትሰሙ፥
14፤እኽልኽን፡ወይንኽንም፡ዘይትኽንም፡ትሰበስብ፡ዘንድ፡በየጊዜው፡የበልጉን፡ዝናብና፡የክረምቱን፡ዝናብ ፡ለምድራችኹ፡አወርዳለኹ።
15፤በሜዳ፡ለእንስሳዎችኽ፡ሣርን፡እሰጣለኹ፥ትበላማለኽ፥ትጠግብማለኽ።
16፤ልባችኹ፡እንዳይስት፥ፈቀቅ፡እንዳትሉ፥ሌላዎችንም፡አማልክት፡እንዳታመልኩ፥እንዳትሰግዱላቸውም፥
17፤የእግዚአብሔርም፡ቍጣ፡እንዳይነድ፟ባችኹ፥ዝናብም፡እንዳይዘንብ፡ምድሪቱም፡ፍሬዋን፡እንዳትሰጥ፡ሰማ ይን፡እንዳይዘጋባችኹ፤እግዚአብሔርም፡ከሚሰጣችኹ፡ከመልካሚቱ፡ምድር፡ፈጥናችኹ፡እንዳትጠፉ፡ተጠንቀቁ።
18፤እንግዲህ፡እነዚህን፡ቃሎች፡በልባችኹና፡በነፍሳችኹ፡አኑሩ፤እነርሱንም፡ለምልክት፡በእጃችኹ፡ላይ፡እ ሰሯቸው፥በዐይኖቻችኹም፡መካከል፡እንደክታብ፡ይኹኑ።
19፤ልጆቻችኹንም፡አስተምሯቸው፥በቤትኽም፡ስትቀመጥ፥በመንገድም፡ስትኼድ፥ስትተኛም፡ስትነሣም፡አጫውቷቸ ው።
20፤21፤ርሷንም፡እንዲሰጣቸው፡እግዚአብሔር፡ለአባቶቻችኹ፡በማለላቸው፡ምድር፥እንደሰማይ፡ዘመን፡በምድር ፡ላይ፥ዘመናችኹ፡የልጆቻችኹም፡ዘመን፡ይረዝም፡ዘንድ፡በቤትኽ፡መቃኖችና፡በደጃፍኽም፡በሮች፡ላይ፡ጻፈው።
22፤አምላካችኹን፡እግዚአብሔርን፡ትወዱ፡ዘንድ፥በመንገዱም፡ዅሉ፡ትኼዱ፡ዘንድ፥ከርሱም፡ጋራ፡ትጣበቁ፡ዘ ንድ፥ዛሬ፡ለእናንተ፡የማዘ፟ውን፡ትእዛዝ፡ዅሉ፡ብትጠብቁ፡ብታደርጓትም፥
23፤እግዚአብሔር፡እነዚህን፡አሕዛብ፡ዅሉ፡ከፊታችኹ፡ያወጣል፥ከእናንተም፡የሚበልጡትን፡የሚበረቱትንም፡ አሕዛብ፡ትወርሳላችኹ።
24፤የእግራችኹ፡ጫማ፡የምትረግጣት፡ስፍራ፡ዅሉ፡ለእናንተ፡ትኾናለች፤ከምድረ፡በዳም፡ከሊባኖስም፡ከታላቁ ም፡ከኤፍራጥስ፡ወንዝ፡ዠምሮ፡እስከምዕራብ፡ባሕር፡ድረስ፡ዳርቻችኹ፡ይኾናል።
25፤በእናንተም፡ፊት፡ማንም፡መቆም፡አይችልም፤አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፥ርሱ፡እንደ፡ተናገራችኹ፥ማስፈራ ታችኹን፡ማስደንገጣችኹንም፡በምትረግጧት፡ምድር፡ዅሉ፡ላይ፡ያኖራል።
26፤እንሆ፥እኔ፡ዛሬ፡በፊታችኹ፡በረከትንና፡መርገምን፡አኖራለኹ፤
27፤በረከትም፥እኔ፡ዛሬ፡ለእናንተ፡የማዘ፟ውን፡የአምላካችኹን፡የእግዚአብሔርን፡ትእዛዝ፡ብትሰሙ፤
28፤መርገምም፥የአምላካችኹን፡የእግዚአብሔርን፡ትእዛዝ፡ባትሰሙ፥ዛሬም፡ካዘዝዃችኹ፡መንገድ፡ፈቀቅ፡ብት ሉ፥ሌላዎችንም፡የማታውቋቸውን፡አማልክት፡ብትከተሉ፡ነው።
29፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ትወርሳት፡ዘንድ፡አንተን፡ወደምትኼድባት፡ምድር፡ባገባኽ፡ጊዜ፥በረከቱን፡ በገሪዛን፡ተራራ፥መርገሙንም፡በጌባል፡ተራራ፡ታኖራለኽ።
30፤እነርሱም፡በዮርዳኖስ፡ማዶ፥ከፀሓይ፡መግቢያ፡ካለችው፡መንገድ፡በዃላ፥በዐረባ፡በተቀመጡት፡በከነዓና ውያን፡ምድር፥በገልገላ፡ፊት፡ለፊት፡በሞሬ፡የአድባር፡ዛፍ፡አጠገብ፡ናቸው።
31፤አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡የሚሰጣችኹን፡ምድር፡ትወርሱ፡ዘንድ፡ዮርዳኖስን፡ትሻገራላችኹ፥ትወርሷታላ ችኹም፥ትቀመጡባታላችኹም።
32፤እኔም፡ዛሬ፡በፊታችኹ፡የማኖራትን፡ሥርዐትና፡ፍርድ፡ዅሉ፡ታደርጉ፡ዘንድ፡ጠብቁ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡12።______________
ምዕራፍ፡12።
1፤በምድር፡ላይ፡በምትኖሩበት፡ዘመን፡ዅሉ፡የአባቶቻችኹ፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡ለመውረስ፡በሰጣችኹ፡አገ ር፥የምትጠብቋትና፡የምታደርጓት፡ሥርዐትና፡ፍርድ፡እነዚህ፡ናቸው።
2፤እናንተ፡የምትወርሷቸው፡አሕዛብ፡አማልክታቸውን፡ያመለኩባቸውን፡በረዥም፡ተራራዎች፡በኰረብታዎችም፡ላ ይ፡ከለምለምም፡ዛፍ፡በታች፡ያለውን፡ስፍራ፡ዅሉ፡ፈጽማችኹ፡አጥፏቸው፤
3፤መሠዊያቸውንም፡አፍርሱ፥ሐውልቶቻቸውንም፡ሰባብሩ፥የማምለኪያ፡ዐጸዶቻቸውንም፡በእሳት፡አቃጥሉ፥የአማ ልክታቸውንም፡የተቀረጹ፡ምስሎች፡አንከታክቱ፤ከዚያም፡ስፍራ፡ስማቸውን፡አጥፉ።
4፤ለአምላካችኹ፡ለእግዚአብሔር፡እንዲህ፡ያለ፡ሥራ፡አትሥሩ።
5፤ነገር፡ግን፥አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡ከነገዶቻችኹ፡ዅሉ፡ስሙን፡በዚያ፡ያኖር፡ዘንድ፡ወደዚያ፡ወደመረ ጠው፡ስፍራ፡ትመጣላችኹ፥ማደሪያውንም፡ትሻላችኹ።
6፤ወደዚያም፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕታችኹን፥ሌላ፡መሥዋዕታችኹንም፥ዐሥራታችኹንም፥በእጃችኹም፡ያነሣችኹት ን፡ቍርባን፥ስእለታችኹንም፥በፈቃዳችኹ፡የምታቀርቡትን፥የላማችኹንና፡የበጋችኹንም፡በኵራት፡ውሰዱ።
7፤በዚያም፡በአምላካችኹ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ብሉ፥እጃችኹንም፡በምትዘረጉበት፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ በባረከኽ፡ነገር፡ዅሉ፥እናንተና፡ቤተ፡ሰባችኹ፡ደስ፡ይበላችኹ።
8፤ሰው፡ዅሉ፡በፊቱ፡መልካም፡መስሎ፡የታየውን፥እኛ፡በዚህ፡ዛሬ፡የምናደርገውን፡ዅሉ፡አታደርጉም፤
9፤አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡ወደሚሰጣችኹ፡ዕረፍትና፡ርስት፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡አልገባችኹምና።
10፤ዮርዳኖስን፡ግን፡በተሻገራችኹ፡ጊዜ፥አምላካችኹም፡እግዚአብሔር፡በሚያወርሳችኹ፡ምድር፡በተቀመጣችኹ ፡ጊዜ፥ያለፍርሀትም፡እንድትኖሩ፡ከከበቧችኹ፡ጠላቶች፡ዅሉ፡ዕረፍት፡በሰጣችኹ፡ጊዜ፥
11፤በዚያን፡ጊዜ፡አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡ስሙ፡ይጠራበት፡ዘንድ፡ወደዚያ፡ወደመረጠው፡ስፍራ፥እኔ፡የማ ዛ፟ችኹን፡ዅሉ፥የሚቃጠለውን፡መሥዋዕታችኹን፥ሌላ፡መሥዋዕታችኹንም፥ዐሥራታችኹንም፥በእጃችኹ፡ያነሣችኹት ንም፡ቍርባን፥ለእግዚአብሔርም፡ተስላችኹ፡የመረጣችኹትን፡ስእለታችኹን፡ዅሉ፡ውሰዱ።
12፤እናንተም፥ወንዶች፡ልጆቻችኹና፡ሴቶች፡ልጆቻችኹም፥ባሪያዎቻችኹም፥ገረዶቻችኹም፥ከእናንተ፡ጋራ፡ክፍ ልና፡ርስት፡ስለሌለው፡በደጆቻችኹ፡ውስጥ፡የተቀመጠው፡ሌዋዊም፡በአምላካችኹ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ደስ፡ይ በላችኹ።
13፤የሚቃጠለውን፡መሥዋዕትኽን፡በሚታይኽ፡ስፍራ፡ዅሉ፡እንዳታቀርብ፡ተጠንቀቅ።
14፤ነገር፡ግን፥እግዚአብሔር፡ከነገዶችኽ፡ከአንዱ፡ዘንድ፡በመረጠው፡ስፍራ፡በዚያ፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕ ትኽን፡አቅርብ፥በዚያም፡የማዝ፟ኽን፡ዅሉ፡አድርግ።
15፤ነገር፡ግን፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ሰጠኽ፡በረከት፥ሰውነትኽ፡እንደ፡ፈቀደ፥በደጆችኽ፡ዅሉ፡ ውስጥ፡ዐርደኽ፡ብላ፤ንጹሕ፡ሰው፡ንጹሕም፡ያልኾነ፡ሰው፡እንደ፡ሚዳቋና፡እንደ፡ዋላ፡ያለውን፡ይብላው።
16፤ደሙን፡ግን፡እንደ፡ውሃ፡በምድር፡ላይ፡አፍሰ፟ው፡እንጂ፡አትብላው።
17፤የእኽልኽን፡የወይን፡ጠጅኽን፡የዘይትኽንም፡ዓሥራት፥የላምኽንና፡የበግኽንም፡በኵራት፥የተሳልኸውንም ፡ስእለት፡ዅሉ፥በፈቃድኽም፡ያቀረብኸውን፥በእጅኽም፡ያነሣኸውን፡ቍርባን፡በደጆችኽ፡ውስጥ፡መብላት፡አትች ልም።
18፤ነገር፡ግን፥አንተ፥ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆችኽም፥ባሪያዎችኽና፡ገረዶችኽም፥በአገርኽም፡ደጅ፡ያለው፡ሌ ዋዊ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በመረጠው፡ስፍራ፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ብሉት፤እጅኽንም፡በምትዘ ረጋበት፡ነገር፡ዅሉ፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ደስ፡ይበልኽ።
19፤በምድርኽ፡ላይ፡በምትኖርበት፡ዘመን፡ዅሉ፡ሌዋዊውን፡ቸል፡እንዳትል፡ተጠንቀቅ።
20፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ነገረኽ፡አገርኽን፡ባሰፋ፡ጊዜ፥ሰውነትኽም፡ሥጋ፡መብላት፡ስለ፡ወደደ ች፦ሥጋ፡ልብላ፡ስትል፥እንደ፡ሰውነትኽ፡ፈቃድ፡ሥጋን፡ብላ።
21፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በዚያ፡ስሙን፡ያኖር፡ዘንድ፡የመረጠው፡ስፍራ፡ከአንተ፡ሩቅ፡ቢኾንም፥እግዚአ ብሔር፡ከሰጠኽ፡ከላምና፡ከበግ፡መንጋኽ፡እንዳዘዝኹኽ፡ዕረድ፥እንደ፡ሰውነትኽም፡ፈቃድ፡ዅሉ፡በአገርኽ፡ደ ጅ፡ውስጥ፡ብላው።
22፤ሚዳቋና፡ዋላ፡እንደሚበሉ፡እንዲሁ፡ብላው፤ንጹሕ፡ሰው፡ንጹሕም፡ያልኾነ፡ይብላው።
23፤ነገር፡ግን፥ደሙ፡ነፍሱ፡ነውና፥ነፍሱንም፡ከሥጋው፡ጋራ፡መብላት፡አይገ፟ባ፟ኽምና፡ደሙን፡እንዳትበላ ፡ተጠንቀቅ።
24፤በምድር፡ላይ፡እንደ፡ውሃ፡አፍሰ፟ው፡እንጂ፡አትብላው።
25፤በእግዚአብሔር፡ፊት፡መልካም፡የኾነውን፡ነገር፡ስታደርግ፡ለአንተ፡ከአንተም፡በዃላ፡ለልጆችኽ፡መልካ ም፡እንዲኾንላችኹ፥አትብላው።
26፤ነገር፡ግን፥የተቀደሰውን፡ነገርኽን፡ስእለትኽንም፡ይዘኽ፡እግዚአብሔር፡ወደመረጠው፡ስፍራ፡ኺድ።
27፤የሚቃጠለውንም፡መሥዋዕትኽን፥ሥጋውንና፡ደሙን፥በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡መሠዊያ፡ላይ፡አቅርብ፤የ መሥዋዕትኽም፡ደም፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡መሠዊያ፡ላይ፡ይፍሰስ፥ሥጋውንም፡ብላው።
28፤በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡መልካምና፡ቅን፡የኾነውን፡ነገር፡ስታደርግ፡ለአንተ፡ከአንተም፡በዃ ላ፡ለልጆችኽ፡ለዘለዓለም፡መልካም፡ይኾንላችኹ፡ዘንድ፡እኔ፡የማዝ፟ኽን፡እነዚህን፡ቃሎች፡ዅሉ፡ሰምተኽ፡ጠ ብቅ።
29፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ትወርሳቸው፡ዘንድ፡የምትኼድባቸውን፡አሕዛብን፡በፊትኽ፡ባጠፋ፡ጊዜ፥አንተም ፡በወረስኻቸው፡ጊዜ፥
30፤በምድራቸውም፡በተቀመጥኽ፡ጊዜ፥ከፊትኽ፡ከጠፉ፡በዃላ፡እነርሱን፡ለመከተል፡እንዳትጠመድ፦እነዚህስ፡ አሕዛብ፡አማልክታቸውን፡ያመለኩት፡እንዴት፡ነው፧እንዲሁ፡ደግሞ፡እኔ፡አደርጋለኹ፡ብለኽ፡ስለ፡አማልክታቸ ው፡እንዳትጠይቅ፡ተጠንቀቅ።
31፤እግዚአብሔር፡የሚጠላውን፡ርኵሰት፡ዅሉ፡እነርሱ፡ለአማልክታቸው፡አድርገዋልና፥ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆ ቻቸውን፡ደግሞ፡ለአማልክታቸው፡በእሳት፡ያቃጥሏቸዋልና፥አንተ፡ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡እንዲሁ፡አታድ ርግ።
32፤እኔ፡የማዝ፟ኽን፡ነገር፡ዅሉ፡ታደርገው፡ዘንድ፡ጠብቅ፤ምንም፡በርሱ፡ላይ፡አትጨምር፥ከርሱም፡ምንም፡ አታጕድል።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡13።______________
ምዕራፍ፡13።
1፤በመካከልኽም፡ነቢይ፡ወይም፡ሕልም፡ዐላሚ፡ቢነሣ፥ምልክትም፡ተኣምራትም፡ቢሰጥኽ፥
2፤እንደ፡ነገረኽም፡ምልክቱ፡ተኣምራቱም፡ቢፈጸም፥ርሱም፦ኼደን፡የማታውቃቸውን፡ሌላዎች፡አማልክት፡እንከ ተል፡እናምልካቸውም፡ቢልኽ፥
3፤አምላካችኹን፡እግዚአብሔርን፡በፍጹም፡ልባችኹ፡በፍጹምም፡ነፍሳችኹ፡ትወዱት፡እንደ፡ኾነ፡ያውቅ፡ዘንድ ፡አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡ሊፈትናችኹ፡ነውና፥የዚያን፡ነቢይ፡ቃል፡ወይም፡ያን፡ሕልም፡ዐላሚ፡አትስማ።
4፤አምላካችኹን፡እግዚአብሔርን፡ተከተሉ፥ርሱንም፡ፍሩ፥ትእዛዙንም፡ጠብቁ፥ቃሉንም፡ስሙ፥ርሱንም፡አምልኩ ፥ከርሱም፡ጋራ፡ተጣበቁ።
5፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ትኼድባት፡ዘንድ፡ካዘዘኽ፡መንገድ፡ሊያወጣኽ፥ከግብጽ፡ምድር፡ካወጣችኹ፡ከባር ነትም፡ቤት፡ካዳናችኹ፡ከአምላካችኹ፡ከእግዚአብሔር፡ሊያስታችኹ፡ተናግሯልና፥ያ፡ነቢይ፡ወይም፡ያ፡ሕልም፡ ዐላሚ፡ይገደል፤እንዲሁም፡ክፉውን፡ነገር፡ከመካከልኽ፡አርቅ።
6፤7፤የእናትኽ፡ልጅ፡ወንድምኽ፡ወይም፡ወንድ፡ልጅኽ፡ወይም፡ሴት፡ልጅኽ፡ወይም፡በብብትኽ፡ያለች፡ሚስትኽ ፡ወይም፡እንደ፡ነፍስኽ፡ያለ፡ወዳጅኽ፡በስውር፦ና፥ኼደን፡ከምድር፡ዳር፡ዠምሮ፡እስከምድር፡ዳር፡ድረስ፡ወ ዳንተ፡የቀረቡት፡ከአንተም፡የራቁት፡አንተን፡ከበ፟ውኽ፡ያሉ፡አሕዛብ፡ከሚያመልኳቸው፡አማልክት፥አንተም፡ አባቶችኽም፡የማታውቋቸውን፡ሌላዎች፡አማልክት፡እናምልክ፡ብሎ፡ቢያስትኽ፥ዕሺ፡አትበለው፥
8፤አትስማውም፤ዐይንኽም፡አይራራለት፥አትማረውም፥አትሸሽገውም፤
9፤ነገር፡ግን፥ፈጽመኽ፡ግደለው፤ርሱን፡ለመግደል፡በፊት፡የአንተ፡እጅ፥ከዚያም፡በዃላ፡የሕዝቡ፡ዅሉ፡እጅ ፡በላዩ፡ትኹን።
10፤ከግብጽ፡ምድር፡ከባርነት፡ቤት፡ካወጣኽ፡ከአምላክኽ፡ከእግዚአብሔር፡ሊያርቅኽ፡ወዷ፟ልና፥እስኪሞት፡ ድረስ፡በድንጋይ፡ውገረው።
11፤እስራኤልም፡ዅሉ፡ሰምተው፡ይፈራሉ፥እንዲህም፡ያለ፡ክፉ፡ሥራ፡እንደ፡ገና፡ባንተ፡መካከል፡አያደርጉም ።
12፤13፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ልትኖርባት፡በሚሰጥኽ፡በአንዲቱ፡ከተማኽ፦ክፋተኛዎች፡ሰዎች፡ከእናንተ፡ ዘንድ፡ወጥተው፦ኼደን፡የማታውቋቸውን፡ሌላዎችን፡አማልክት፡እናምልክ፡ብለው፡የከተማቸውን፡ሰዎች፡አሳቱ፡ ሲሉ፡ወሬ፡ብትሰማ፥
14፤ትፈልጋለኽ፥ትመረምራለኽም፥ትጠይቃለኽም፤እንሆም፥እውነት፡ቢኾን፥ይህም፡ክፉ፡ነገር፡በመካከልኽ፡እ ንደ፡ተደረገ፡ርግጥ፡ኾኖ፡ቢገኝ፥
15፤የዚያችን፡ከተማ፡ሰዎች፡በሰይፍ፡ስለት፡ፈጽሞ፡ትመታቸዋለኽ፤ከተማዪቱን፥በርሷም፡ያለውን፡ዅሉ፥እን ስሳውንም፡በሰይፍ፡ስለት፡ታጠፋቸዋለኽ።
16፤ዕቃዋንም፡ዅሉ፡ወደ፡አደባባይዋ፡ትሰበሰባለኽ፥ከተማዪቱንም፡ዕቃዋንም፡ዅሉ፡ለአምላክኽ፡ለእግዚአብ ሔር፡በእሳት፡ፈጽመኽ፡ታቃጥላለኽ፤ለዘለዓለምም፡ወና፡ትኾናለች፥ደግሞም፡አትሠራም።
17፤18፤ዛሬም፡እኔ፡የማዝ፟ኽን፡ትእዛዝ፡ዅሉ፡ትጠብቅ፡ዘንድ፥በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ደስ፡የሚ ያሠኘውን፡ታደርግ፡ዘንድ፡የአምላክኽን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ስትሰማ፥የእግዚአብሔር፡መቅሠፍት፡ቍጣ፡ይ መለስ፡ዘንድ፥ለአባቶችኽም፡እንደ፡ማለላቸው፡ይምርኽ፡ዘንድ፥ይራራልኽም፡ዘንድ፥ያበዛኽም፡ዘንድ፥ዕርም፡ ከኾነው፡አንዳች፡ነገር፡በእጅኽ፡አይንጠልጠልብኽ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡14።______________
ምዕራፍ፡14።
1፤2፤እናንተ፡የአምላካችኹ፡የእግዚአብሔር፡ልጆች፡ናችኹ፤ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡አንተ፡ቅዱስ፡ሕዝ ብ፡ነኽና፥በምድርም፡ላይ፡ከሚኖሩ፡አሕዛብ፡ዅሉ፡ይልቅ፡ለርሱ፡ለራሱ፡ሕዝብ፡ትኾንለት፡ዘንድ፡እግዚአብሔ ር፡አንተን፡መርጧልና፥ስለሞተው፡ሰው፡አካላችኹን፡አትንጩ፥በዐይኖቻችኹም፡መካከል፡ራሳችኹን፡አትላጩ።
3፤4፤ርኩስን፡ነገር፡ዅሉ፡አትብላ።የምትበሏቸው፡እንስሳዎች፡እነዚህ፡ናቸው፤በሬ፥
5፤በግ፥ፍየል፥ዋላ፥ሚዳቋ፥የበረሓ፡ፍየል፥አጋዘን፥አጭ፥በራይሌ፥ድኵላ።
6፤ከእንስሳዎች፡ሰኰናው፡የተሰነጠቀውን፥ጥፍሩም፡ከኹለት፡የተከፈለውን፥የሚያመሰኳውንም፡እንስሳ፡ዅሉ፡ ትበላለኽ።
7፤ነገር፡ግን፥ከሚያመሰኩ፡ወይም፡ሰኰናቸው፡ከተሰነጠቀ፡እነዚህን፡አትበሉም፤ግመልን፥ጥንቸልን፥ሽኮኮን ፡አትበሉም።ያመሰኳሉና፥ነገር፡ግን፥ሰኰናቸው፡አልተሰነጠቀምና፡እነዚህ፡ለእናንተ፡ርኩሶች፡ናቸው።
8፤ዕሪያም፥ሰኰናው፡ስለ፡ተሰነጠቀ፥ነገር፡ግን፥ስላላመሰኳ፡ርሱ፡ለእናንተ፡ርኩስ፡ነው፤ሥጋውን፡አትብሉ ፥በድኑንም፡አትንኩ።
9፤በውሃዎች፡ውስጥ፡ከሚኖሩት፡ዅሉ፡የምትበሏቸው፡እነዚህ፡ናቸው፤ክንፍና፡ቅርፊት፡ያላቸውን፡ትበላላችኹ ።
10፤ክንፍና፡ቅርፊትም፡የሌላቸውን፡አትበሉም፤ለእናንተ፡ርኩስ፡ናቸው።
11፤ንጹሕ፡የኾኑትን፡ወፎች፡ዅሉ፡ብሉ።
12፤ሊበሉ፡የማይገ፟ባ፟ቸው፡ግን፡እነዚህ፡ናቸው፤
13፤ንስር፥ገዴ፥ዓሣ፡አውጭ፥ጭልፊት፥ጭላት፡በየወገኑ፥
14፤15፤ቍራም፡ዅሉ፡በየወገኑ፥ሰጐን፥
16፤ጠላቋ፥ዝዪ፥በቋል፡በየወገኑ፥ጕጕት፥
17፤ጋጋኖ፥የውሃ፡ዶሮ፥ይብራ፥ጥምብ፡አንሣ፡አሞራ፥
18፤እርኩም፥ሽመላ፥ሳቢሳ፡በየወገኑ፥ጃንጁላቴ፡ወፍ፥የሌሊት፡ወፍ።
19፤የሚበር፟ም፡ተንቀሳቃሽ፡ዅሉ፡ለእናንተ፡ርኩስ፡ነው፤አይበላም።
20፤ንጹሕ፡የኾኑትን፡ወፎች፡ዅሉ፡ብሉ።
21፤አንተ፡ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡የተቀደሰ፡ሕዝብ፡ነኽና፥የበከተውን፡ዅሉ፡አትብላ፤ይበላው፡ዘንድ ፡በአገርኽ፡ደጅ፡ለተቀመጠ፡መጻተኛ፡ትሰጠዋለኽ፥ወይም፡ለእንግዳ፡ትሸጠዋለኽ።የፍየሉን፡ጠቦት፡በእናቱ፡ ወተት፡አትቀቅል።
22፤ከዕርሻኽ፡በየዓመቱ፡ከምታገኘው፡ከዘርኽ፡ፍሬ፡ዅሉ፡ዓሥራት፡ታወጣለኽ።
23፤ዅል፡ጊዜ፡አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡መፍራት፡ትማር፡ዘንድ፥ስሙ፡እንዲጠራበት፡በመረጠው፡ስፍራ፡በ አምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡የእኽልኽን፡የወይን፡ጠጅኽንም፡የዘይትኽንም፡ዓሥራት፡የላምኽንና፡የበግኽ ንም፡በኵራት፡ብላ።
24፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በባረከኽ፡ጊዜ፥መንገዱ፡ሩቅ፡ቢኾን፥አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ስሙን፡ያኖር በት፡ዘንድ፡የመረጠው፡ስፍራ፡ቢርቅብኽ፥ይህን፡ወደዚያ፡ለመሸከም፡ባትችል፥ትሸጠዋለኽ፥
25፤የዋጋውንም፡ገንዘብ፡በእጅኽ፡ይዘኽ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ወደመረጠው፡ስፍራ፡ትኼዳለኽ።
26፤በዚያም፡በገንዘቡ፡ሰውነትኽ፡የፈለገውን፥በሬ፡ወይም፡በግ፡ወይም፡የወይን፡ጠጅ፡ወይም፡ብርቱ፡መጠጥ ፡ሰውነትኽም፡የሚሻውን፡ዅሉ፡ትገዛለኽ፤በዚያም፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ትበላዋለኽ፥አንተና፡ቤ ተ፡ሰብኽም፡ደስ፡ይላችዃል።
27፤ድርሻና፡ርስት፡ከአንተ፡ጋራ፡ስለሌለው፡በአገርኽ፡ደጅ፡ውስጥ፡ያለውን፡ሌዋዊ፡ቸል፡አትበል።
28፤በየሦስተኛው፡ዓመት፡መጨረሻ፡በዚያ፡ዓመት፡የፍሬኽን፡ዓሥራት፡ዅሉ፡አምጥተኽ፡በአገርኽ፡ደጅ፡ውስጥ ፡ታኖረዋለኽ፤
29፤ሌዋዊውም፥ከአንተ፡ጋራ፡ክፍልና፡ርስት፡የለውምና፥በአገርኽም፡ደጅ፡ያለ፡መጻተኛ፡ድኻ፡አደግም፡መበ ለትም፡መጥተው፡ይበላሉ፡ይጠግባሉም፤ይኸውም፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በምታደርገው፡በእጅኽ፡ሥራ፡ዅሉ፡ይ ባርክኽ፡ዘንድ፡ነው።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡15።______________
ምዕራፍ፡15።
1፤በየሰባቱ፡ዓመት፡መጨረሻ፡የዕዳ፡ምሕረት፡ታደርጋለኽ።
2፤ለምሕረቱም፡የሚገ፟ባ፟፡ወግ፡ይህ፡ነው፤አበዳሪ፡ዅሉ፡ለባልንጀራው፡ያበደረውን፡ይተዋል፤የእግዚአብሔ ር፡ይቅርታ፡ታውጇልና፥ያበደረውን፡ከባልንጀራው፡ወይም፡ከወንድሙ፡አይሻ።
3፤ከእንግዳ፡ላይ፡ያበደርኸውን፡መፈለግ፡ትችላለኽ፤በወንድምኽ፡ላይ፡ያለውን፡ዅሉ፡ግን፡እጅኽ፡ይተወዋል ።
4፤5፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ትወርሳት፡ዘንድ፡ርስት፡አድርጎ፡በሰጠኽ፡ምድር፡ላይ፡እግዚአብሔር፡በእ ውነት፡ይባርክኻልና፥አንተ፡የአምላክኽን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ፈጽመኽ፡ብትሰማ፥ታደርጋትም፡ዘንድ፡ዛሬ ፡የማዝ፟ኽን፡ይህችን፡ትእዛዝ፡ዅሉ፡ብትጠብቅ፥በመካከልኽ፡ድኻ፡አይኖርም።
6፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ተስፋ፡እንደ፡ሰጠኽ፡ይባርክኻል፤ለብዙ፡አሕዛብም፡ታበድራለኽ፥አንተ፡ግን፡ አትበደርም፤ብዙ፡አሕዛብንም፡ትገዛለኽ፥አንተን፡ግን፡አይገዙኽም።
7፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በሰጠኽ፡በአገርኽ፡ደጅ፡ውስጥ፡ከሚኖሩ፡ከወንድሞችኽ፡አንዱ፡ቢደኸይ፥ልብኽን ፡አታጽና፥በድኻው፡ወንድምኽ፡ላይ፡እጅኽን፡አትጨብጥ።
8፤ነገር፡ግን፥እጅኽን፡ለርሱ፡ክፈት፥የለመነኽንም፡አስፈላጊውን፡ነገር፡አበድረው።
9፤ሰባተኛው፡ዓመት፡የዕዳ፡ምሕረት፡ዓመት፡ቀርቧል፡ብለኽ፡ክፉ፡ዐሳብ፡በልብኽ፡እንዳታስብ፥ለድኻውም፡ወ ንድምኽ፡አንዳች፡የማትሰጥ፡እንዳትኾን፥ዐይንኽም፡በርሱ፡ላይ፡ክፉ፡እንዳይኾን፥ርሱም፡ወደ፡እግዚአብሔር ፡ባንተ፡ላይ፡እንዳይጮኽ፥ኀጢአትም፡እንዳይኾንብኽ፡ተጠንቀቅ።
10፤እጅኽን፡በምትጥልበት፡ዅሉ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ስለዚህ፡በሥራኽ፡ዅሉ፡ይባርክኻልና፥ፈጽመኽ፡ስ ጠው፥በሰጠኸውም፡ጊዜ፡በልብኽ፡አትጸጸት።
11፤ድኻዎች፡ከምድሪቱ፡ላይ፡አያልቁምና፡ስለዚህ፡እኔ፦በአገርኽ፡ውስጥ፡ላለው፡ድኻ፡ለተቸገረውም፡ወንድ ምኽ፡እጅኽን፡ትከፍታለኽ፡ብዬ፡አዝ፟ኻለኹ።
12፤አንተም፡ወንድምኽን፡ዕብራዊውን፡ወይም፡ዕብራዊቱን፡ብትገዛ፡ስድስት፡ዓመት፡ያገልግሉኽ፤በሰባተኛው ም፡ዓመት፡ከአንተ፡ዘንድ፡ሐራነት፡አውጣው።
13፤ከአንተም፡ዘንድ፡ሐራነት፡ባወጣኸው፡ጊዜ፡ባዶውን፡አትስደደው፤
14፤ነገር፡ግን፥ከመንጋኽ፥ከዐውድማኽም፥ከወይንኽም፡መጥመቂያ፡ትለግስለታለኽ፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ እንደ፡ባረከኽ፡መጠን፡ትሰጠዋለኽ።
15፤አንተም፡በግብጽ፡ምድር፡ባሪያ፡እንደ፡ነበርኽ፡አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡እንዳዳነኽ፡ዐስብ፤ስለዚህ ፥እኔ፡ዛሬ፡ይህን፡ነገር፡አዝ፟ኻለኹ።
16፤ርሱ፡ግን፡አንተንና፡ቤትኽን፡ስለ፡ወደደ፥ከአንተም፡ጋራ፡መልካም፡ስለ፡ኾነለት፦ልወጣ፡አልወድ፟ም፡ ቢል፥
17፤አንተ፡ወስፌ፡ወስደኽ፡በቤትኽ፡በር፡ላይ፡ዦሮውን፡ትበሳዋለኽ፥ለዘለዓለምም፡ባሪያ፡ይኾንልኻል።በሴ ት፡ባሪያኽ፡ደግሞ፡እንዲሁ፡ታደርጋለኽ።
18፤ርሱንም፡ሐራነት፡ባወጣኸው፡ጊዜ፡የምንደኝነቱን፡ሥራ፡ኹለት፡ዕጥፍ፡አድርጎ፡ስድስት፡ዓመት፡አገልግ ሎኻልና፥አይክበድኽ፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡በምትሠራው፡ዅሉ፡ይባርክኻል።
19፤ላምኽና፡በግኽ፡የወለዱትን፡ተባት፡የኾነውን፡በኵራት፡ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡ትቀድሳለኽ፤በበሬ ኽ፡በኵራት፡አትሥራበት፥የበግኽንም፡በኵራት፡አትሸልት።
20፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በመረጠው፡ስፍራ፡አንተና፡ቤተ፡ሰብኽ፡በየዓመቱ፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር ፡ፊት፡ብሏቸው።
21፤ነውረኛ፡ወይም፡ዐንካሳ፡ወይም፡ዕውር፡ቢኾን፥ወይም፡አንዳች፡ክፉ፡ነውር፡ቢኖረው፥ለአምላክኽ፡ለእግ ዚአብሔር፡አትሠዋው።
22፤በአገርኽ፡ደጅ፡ውስጥ፡ትበላዋለኽ፤ንጹሕ፡ሰው፡ንጹሕም፡ያልኾነ፡ሚዳቋና፡ዋላ፡እንደሚበሉ፡ይበሉታል ።
23፤ነገር፡ግን፥ደሙን፡እንደ፡ውሃ፡በምድር፡ላይ፡አፍሰ፟ው፡እንጂ፡አትብላው።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡16።______________
ምዕራፍ፡16።
1፤በአቢብ፡ወር፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በሌሊት፡ከግብጽ፡ስላወጣኽ፡የአቢብን፡ወር፡ጠብቅ፥የአምላክኽን ም፡የእግዚአብሔርን፡ፋሲካ፡አድርግበት።
2፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በዚያ፡ስሙ፡ይጠራበት፡ዘንድ፡በመረጠው፡ስፍራ፡ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡ከ በግና፡ከላም፡መንጋ፡ፋሲካ፡ሠዋ።
3፤የቦካውን፡እንጀራ፡ከርሱ፡ጋራ፡አትብላ፤ከግብጽ፡አገር፡በችኰላ፡ስለ፡ወጣኽ፡ከግብጽ፡አገር፡የወጣኽበ ትን፡ቀን፡በዕድሜኽ፡ዅሉ፡ታስብ፡ዘንድ፡የመከራን፡እንጀራ፥ቂጣ፡እንጀራ፥ሰባት፡ቀን፡ከርሱ፡ጋራ፡ብላ።
4፤ሰባት፡ቀንም፡በአገርኽ፡ዅሉ፡ርሾ፡አይታይም፤በመዠመሪያው፡ቀን፡ማታ፡ከሠዋኸው፡ሥጋ፡እስከ፡ነገ፡ድረ ስ፡ምንም፡አይደር።
5፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከሰጠኽ፡ከአገርኽ፡ደጆች፡በማንኛዪቱም፡ፋሲካን፡ትሠዋ፡ዘንድ፡አይገ፟ባ፟ኽም ።
6፤ነገር፡ግን፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ስሙ፡ይጠራበት፡ዘንድ፡በመረጠው፡በዚያ፡ስፍራ፡ከግብጽ፡በወጣኽበ ት፡ወራት፥ፀሓይ፡ሲገባ፥ማታ፡ፋሲካን፡ሠዋ።
7፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በመረጠው፡ስፍራ፡ታበስለዋለኽ፥ትበላውማለኽ፤በነጋውም፡ተነሥተኽ፡ወደ፡ድንኳ ንኽ፡ትኼዳለኽ።
8፤ስድስት፡ቀን፡ቂጣ፡እንጀራ፡ብላ፤በሰባተኛውም፡ቀን፡ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡ጉባኤ፡ይኹን፤ሥራን፡ ዅሉ፡አታድርግበት።
9፤ሰባት፡ሳምንትም፡ትቈጥራለኽ፤መከሩን፡ማጨድ፡ከምትዠምርበት፡ቀን፡ዠምሮ፡ሰባት፡ሳምንት፡መቍጠር፡ትዠ ምራለኽ።
10፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በባረከኽ፡መጠን፡በፈቃድኽ፡የምታቀርበውን፡አምጥተኽ፡ለአምላክኽ፡ለእግዚአ ብሔር፡የሰባቱ፡ሱባዔ፡በዓል፡ታደርጋለኽ።
11፤አንተ፥ወንድ፡ልጅኽና፡ሴት፡ልጅኽ፥ወንድ፡ባሪያኽና፡ሴት፡ባሪያኽ፥በአገርኽም፡ደጅ፡ውስጥ፡ያለው፡ሌ ዋዊ፥በመካከልኽም፡ያሉት፡መጻተኛና፡ድኻ፡አደግ፡መበለትም፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በዚያ፡ስሙ፡ይጠራበት ፡ዘንድ፡በሚመርጠው፡ስፍራ፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ደስ፡ይበላችኹ።
12፤አንተም፡በግብጽ፡ባሪያ፡እንደ፡ነበርኽ፡ዐስብ፤ይህንንም፡ሥርዐት፡ጠብቅ፥አድርገውም።
13፤ከዐውድማኽና፡ከመጥመቂያኽ፡ፍሬኽን፡በሰበሰብኽ፡ጊዜ፡የዳስ፡በዓል፡ሰባትን፡ቀን፡ትጠብቃለኽ።
14፤አንተም፥ወንድ፡ልጅኽና፡ሴት፡ልጅኽ፥ወንድ፡ባሪያኽና፡ሴት፡ባሪያኽ፥በአገርኽም፡ደጅ፡ውስጥ፡ያለ፡ሌ ዋዊና፡መጻተኛ፥ድኻ፡አደግና፡መበለትም፡በበዓል፡ደስ፡ይበላችኹ።
15፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በፍሬኽ፡ዅሉ፡በእጅኽም፡ሥራ፡ዅሉ፡ይባርክኻልና፥እግዚአብሔር፡በመረጠው፡ስ ፍራ፡ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡ሰባት፡ቀን፡በዓል፡ታደርጋለኽ፤አንተም፡ፈጽሞ፡ደስ፡ይልኻል።
16፤በዓመት፡ሦስት፡ጊዜ፥በቂጣ፡በዓል፥በሰባቱ፡ሱባዔም፡በዓል፥በዳስም፡በዓል፡ወንዶችኽ፡ዅሉ፡በአምላክ ኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ርሱ፡በመረጠው፡ስፍራ፡ይታዩ፤በእግዚአብሔርም፡ፊት፡ባዶ፡እጃቸውን፡አይታዩ።
17፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በረከት፡እንደ፡ሰጠኽ፡መጠን፡እያንዳንዱ፡ሰው፡እንደ፡ችሎታው፡ይስጥ።
18፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በሚሰጥኽ፡በአገርኽ፡ደጅ፡ዅሉ፡በየነገዶችኽ፡ፈራጆችንና፡አለቃዎችን፡ሹም፤ ለሕዝቡም፡ቅን፡ፍርድ፡ይፍረዱ።
19፤ፍርድን፡አታጣ፟ም፟፤ፊት፡አይተኽም፡አታድላ፤ጕቦ፡የጥበበኛዎችን፡ዐይን፡ያሳውራልና፥የጻድቃንንም፡ ቃል፡ያጣምማልና፥ጕቦ፡አትቀበል።
20፤በሕይወት፡ትኖር፡ዘንድ፥አምላክኽ፡እግዚአብሔርም፡የሚሰጥኽን፡ምድር፡ትወርስ፡ዘንድ፡እውነተኛውን፡ ፍርድ፡ተከተል።
21፤ለአንተ፡በምትሠራው፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡መሠዊያ፡አጠገብ፡ከማናቸውም፡ዛፍ፡የማምለኪያ፡ዐጸ ድ፡አድርገኽ፡አትትከል።
22፤አምላክኽ፡እግዚአብሔርም፡የሚጠላውን፡ሐውልት፡ለአንተ፡አታቁም።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡17።______________
ምዕራፍ፡17።
1፤በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡የተጠላ፡ነውና፥ነውር፡ወይም፡ክፉ፡ነገር፡ያለበትን፡በሬ፡ወይም፡በግ ፡ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡አትሠዋ።
2፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከሰጠኽ፡ከአገርኽ፡ደጆች፡በማንኛዪቱም፡ውስጥ፡ወንድ፡ወይም፡ሴት፡ቢኾን፡ቃል ፡ኪዳኑን፡በማፍረስ፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ክፋት፡የሠራ፡ቢገኝ፥
3፤ኼዶም፡ሌላዎች፡አማልክትን፡ያመለከ፥እኔ፡ላላዘዝዃቸው፡ለፀሓይና፡ለጨረቃ፡ለሰማይም፡ሰራዊት፡ዅሉ፡የ ሰገደ፡ቢገኝ፥
4፤ቢያወሩልኽም፡ብትሰማም፥ያንን፡ፈጽመኽ፡መርምር፤እንሆም፥እውነት፡ቢኾን፥በእስራኤልም፡መካከል፡እንዲ ህ፡ያለ፡ርኵሰት፡እንደ፡ተሠራ፡ርግጥ፡ኾኖ፡ቢገኝ፥
5፤ይህን፡ክፉ፡ነገር፡የሠሩትን፡ያን፡ወንድ፡ወይም፡ያችን፡ሴት፡ወደ፡በርኽ፡ታመጣቸዋለኽ፥እስኪሞቱም፡ድ ረስ፡በድንጋይ፡ትወግራቸዋለኽ።
6፤በኹለት፡ወይም፡በሦስት፡ምስክሮች፡አፍ፡ሞት፡የሚገ፟ባ፟ው፡ይገደል፤ባንድ፡ምስክር፡አፍ፡አይገደል።
7፤ርሱን፡ለመግደል፡በመዠመሪያ፡የምስክሮች፡እጅ፡በዃላም፡የሕዝቡ፡ዅሉ፡እጅ፡ትኹንበት፤እንዲሁም፡ክፋቱ ን፡ከመካከልኽ፡አስወግድ።
8፤በደምና፡በደም፥በፍርድና፡በፍርድ፥በመቍሰልና፡በመቍሰል፡መካከል፡በአገርኽ፡ደጅ፡ውስጥ፡ሰዎች፡ስለሚ ከራከሩበት፡ክርክር፡የሚሳንኽ፡የፍርድ፡ነገር፡ቢነሣ፥አንተ፡ተነሥተኽ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ወደ፡መረ ጠው፡ስፍራ፡ትወጣለኽ፤
9፤ወደ፡ሌዋውያን፡ካህናት፡በዚያም፡ዘመን፡ወደተሾመው፡ፈራጅ፡መጥተኽ፡ትጠይቃለኽ፤እነርሱም፡የፍርዱን፡ ነገር፡ይነግሩኻል።
10፤እግዚአብሔር፡በመረጠው፡ስፍራ፡የነገሩኽን፡የፍርድ፡ነገር፡ታደርጋለኽ፤እንዳስተማሩኽም፡ታደርግ፡ዘ ንድ፡ጠብቅ።
11፤እንዳስተማሩኽም፡ሕግ፥እንደ፡ነገሩኽም፡ፍርድ፡አድርግ፤ከነገሩኽ፡ፍርድ፡ወደ፡ቀኝም፡ወደ፡ግራም፡አ ትበል።
12፤ማናቸውም፡ሰው፡ቢኰራ፥በዚያም፡አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡ለማገልገል፡የሚቆመውን፡ካህኑን፡ወይም፡ ፈራጁን፡ለመስማት፡ባይወድ፟፥ያ፡ሰው፡ይሙት፥ከእስራኤልም፡ዘንድ፡ክፋትን፡አስወግድ፤
13፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡ሰምቶ፡ይፈራል፥ከዚያም፡ወዲያ፡አይኰራም።
14፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ወደሚሰጥኽ፡ምድር፡በገባኽ፥በወረስኻትም፡ጊዜ፥በተቀመጥኽባትም፡ጊዜ፦በዙሪ ያዬ፡እንዳሉት፡አሕዛብ፡ዅሉ፡በላዬ፡ንጉሥ፡አነግሣለኹ፡ስትል፥
15፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡የመረጠውን፡በላይኽ፡ታነግሣለኽ፤ከወንድሞችኽ፡መካከል፡የኾነውን፡ባንተ፡ላ ይ፡ንጉሥ፡ታነግሣለኽ፤ወንድምኽ፡ያልኾነውን፡ከሌላ፡ወገን፡ሰው፡በላይኽ፡ንጉሥ፡ታደርግ፡ዘንድ፡አይገ፟ባ ፟ኽም።
16፤ነገር፡ግን፥ለርሱ፡ፈረሶችን፡አያበዛም፤እግዚአብሔር፦በዚያ፡መንገድ፡ደግማችኹ፡አትመለሱም፡ብሏችዃ ልና፥ፈረሶችን፡ለማብዛት፡ሕዝቡን፡ወደ፡ግብጽ፡አይመልስም።
17፤ልቡም፡እንዳይስት፡ሚስቶችን፡ለርሱ፡አያበዛም፤ወርቅና፡ብርም፡ለርሱ፡እጅግ፡አያበዛም።
18፤በመንግሥቱም፡ዙፋን፡በተቀመጠ፡ጊዜ፡ከሌዋውያን፡ካህናት፡ወስዶ፡ይህን፡ሕግ፡ለራሱ፡በመጽሐፍ፡ይጻፍ ።
19፤21፤አምላኩን፡እግዚአብሔርን፡መፍራት፡ይማር፡ዘንድ፥የዚህን፡ሕግ፡ቃል፡ዅሉ፡ይህችንም፡ሥርዐት፡ጠብ ቆ፡ያደርግ፡ዘንድ፥ልቡ፡በወንድሞቹ፡ላይ፡እንዳይኰራ፡ከትእዛዙም፡ቀኝና፡ግራ፡እንዳይል፥ርሱም፡ልጆቹም፡ በእስራኤል፡ልጆች፡መካከል፡ረዥም፡ዘመን፡ይነግሡ፡ዘንድ፡መጽሐፉ፡ከርሱ፡ጋራ፡ይኑር፥ዕድሜውንም፡ዅሉ፡ያ ንብበው።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡18።______________
ምዕራፍ፡18።
1፤ለሌዋውያን፡ካህናት፥ለሌዊም፡ነገድ፡ዅሉ፡ከእስራኤል፡ጋራ፡ድርሻና፡ርስት፡አይኾንላቸውም፤በእሳት፡ለ እግዚአብሔር፡የሚቀርበውን፡መሥዋዕቱንና፡ርስቱን፡ይበላሉ።
2፤በወንድሞቻቸውም፡መካከል፡ርስት፡አይኾንላቸውም፤ርሱ፡አንደ፡ተናገራቸው፡ርስታቸው፡እግዚአብሔር፡ነው ።
3፤በሬ፡ወይም፡በግ፡ለመሥዋዕት፡ከሚያቀርቡት፡ሕዝብ፡የካህናቱ፡ወግ፡ይህ፡ይኾናል፤ወርቹንና፡ኹለቱን፡ጕ ንጮቹን፡ጨጓራውንም፡ለካህኑ፡ይሰጣሉ።
4፤የእኽልኽን፡የወይን፡ጠጅኽን፡የዘይትኽንም፡በኵራት፥አስቀድሞም፡የተሸለተውን፡የበግኽን፡ጠጕር፡ለርሱ ፡ትሰጣለኽ።
5፤ርሱ፡ከልጆቹ፡ጋራ፡ተነሥቶ፡በእግዚአብሔር፡ስም፡ለዘለዓለም፡ያገለግል፡ዘንድ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር ፡ከነገዶችኽ፡ዅሉ፡ስለ፡መረጠው፡ነው።
6፤አንድ፡ሌዋዊ፡ሰው፡ከሚቀመጥባቸው፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ዘንድ፡ካሉት፡ከአገር፡ደጆች፡ከአንዲቱ፡ቢወጣ፥በ ፍጹም፡ፈቃድም፡እግዚአብሔር፡ወደ፡መረጠው፡ስፍራ፡ቢመጣ፥
7፤በእግዚአብሔር፡ፊት፡እንደሚቆሙት፡እንደ፡ወንድሞቹ፡እንደ፡ሌዋውያን፡ዅሉ፡በአምላኩ፡በእግዚአብሔር፡ ስም፡ያገለግላል።
8፤ከተሸጠው፡ከአባቶቹ፡ከብት፡ዋጋ፡ሌላ፡እንደ፡ባልንጀራዎቹ፡ከመብል፡ድርሻውን፡ይወስዳል።
9፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ወደሚሰጥኽ፡ምድር፡በገባኽ፡ጊዜ፡እነዚያ፡አሕዛብ፡የሚያደርጉትን፡ርኵሰት፡ታ ደርግ፡ዘንድ፡አትማር።
10፤ወንድ፡ልጁን፡ሴት፡ልጁን፡በእሳት፡የሚያሳልፍ፥ሟርተኛም፥ሞራ፡ገላጭም፥
11፤አስማተኛም፥መተተኛም፥በድግምት፡የሚጠነቍልም፥መናፍስትንም፡የሚጠራ፥ጠንቋይም፥ሙታን፡ሳቢም፡ባንተ ፡ዘንድ፡አይገኝ።
12፤ይህንም፡የሚያደርግ፡ዅሉ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡የተጠላ፡ነው፤ስለዚህም፡ርኵሰት፡አምላክኽ፡እግዚአብ ሔር፡ከፊትኽ፡ያሳድዳቸዋል።
13፤አንተ፡ግን፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ፍጹም፡ኹን።
14፤የምትወርሳቸው፡እነዚህ፡አሕዛብ፡ሞራ፡ገላጮችንና፡ሟርተኛዎችን፡ያዳምጣሉ፤አንተ፡ግን፡እንዲሁ፡ታደ ርግ፡ዘንድ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከልክሎኻል።
15፤16፤አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡በኰሬብ፡ስብሰባ፡ተደርጎ፡በነበረበት፡ቀን፦እንዳልሞት፡የአምላኬን፡ የእግዚአብሔርን፡ድምፅ፡ደግሞ፡አልስማ፥ይህችን፡ታላቅ፡እሳት፡ደግሞ፡አልይ፡ብለኽ፡እንደ፡ለመንኸው፡ዅሉ ፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከአንተ፡መካከል፡ከወንድሞችኽ፡እንደ፡እኔ፡ያለ፡ነቢይ፡ያስነሣልኻል፤ርሱንም፡ ታደምጣለኽ።
17፤እግዚአብሔርም፡አለኝ፦የተናገሩት፡መልካም፡ነው፤
18፤ከወንድሞቻቸው፡መካከል፡እንደ፡አንተ፡ያለ፡ነቢይ፡አስነሣላቸዋለኹ፤ቃሌንም፡በአፉ፡አደርጋለኹ፥ያዘ ዝኹትንም፡ቃል፡ዅሉ፡ይነግራቸዋል፤
19፤በስሜም፡የሚናገረውን፡ቃሌን፡የማይሰማውን፡ሰው፡እኔ፡እበቀልለታለኹ።
20፤ነገር፡ግን፥ይናገር፡ዘንድ፡ያላዘዝኹትን፡በስሜ፡በድፍረት፡የሚናገር፡ወይም፡በሌላ፡አማልክት፡ስም፡ የሚናገር፡ነቢይ፥ርሱ፡ይገደል።
21፤በልብኽም፦እግዚአብሔር፡ያልተናገውን፡ቃል፡እናውቅ፡ዘንድ፡እንዴት፡ይቻለናል፧ብትል፥
22፤ነቢዩ፡በእግዚአብሔር፡ስም፡በተናገረ፡ጊዜ፡የተናገረው፡ነገር፡ባይኾን፡ባይመጣም፥ያ፡ነገር፡እግዚአ ብሔር፡ያልተናገረው፡ነው፤ነቢዩ፡በድፍረቱ፡ተናግሮታል፡ርሱን፡አትፍራው።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡19።______________
ምዕራፍ፡19።
1፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ምድራቸውን፡የሚሰጥኽን፡አሕዛብ፡ባጠፋ፡ጊዜ፥በወረስኻትም፡ጊዜ፥በከተማዎቻቸ ውና፡በቤቶቻቸውም፡በተቀመጥኽ፡ጊዜ፥
2፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ርስት፡አድርጎ፡በሚሰጥኽ፡በምድርኽ፡መካከል፡ሦስት፡ከተማዎችን፡ለራስኽ፡ትለ ያለኽ።
3፤ነፍሰ፡ገዳይ፡ይሸሽባቸው፡ዘንድ፡ወደ፡እነርሱ፡የሚወስደውን፡መንገድ፡ታዘጋጃለኽ፥አምላክኽም፡እግዚአ ብሔር፡የሚያወርስኽን፡ምድር፡ከሦስት፡አድርገኽ፡ትከፍላለኽ።
4፤የነፍሰ፡ገዳይ፡ወግ፡ይህ፡ነው፤አስቀድሞ፡ጠላቱ፡ሳይኾን፡ባልንጀራውን፡ሳያስብ፡የገደለ፡ወደዚያ፡ሸሽ ቶ፡በሕይወት፡ይኑር።
5፤6፤ሰው፡ከባልንጀራው፡ጋራ፡ዕንጨት፡ሊቈርጥ፡ወደ፡ዱር፡ቢኼድ፥ዛፉንም፡ሊቈርጥ፡ምሣሩን፡ሲያነሣ፡ብረ ቱ፡ከእጀታው፡ቢወልቅ፥ባልንጀራውንም፡እስኪሞት፡ድረስ፡ቢመታው፥ደም፡ተበቃዩ፡ነፍሰ፡ገዳዩን፡በልቡ፡ተና ዶ፟፡እንዳያሳድደው፡መንገዱም፡ሩቅ፡ስለ፡ኾነ፡አግኝቶ፡እንዳይገድለው፥ከነዚህ፡ከተማዎች፡ወደ፡አንዲቱ፡ ሸሽቶ፡በሕይወት፡ይኖራል፤አስቀድሞ፡ጠላቱ፤አልነበረምና፡ሞት፡አይገ፟ባ፟ውም።
7፤ስለዚህ፥እኔ፦ለአንተ፡ሦስት፡ከተማዎችን፡ለይ፡ብዬ፡አዝዤኻለኹ።
8፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ለአባቶችኽ፡እንደ፡ማለላቸው፡ዳርቻኽን፡ቢያሰፋ፥ይሰጣቸውም፡ዘንድ፡ለአባቶ ችኽ፡የተናገረውን፡ምድር፡ዅሉ፡ቢሰጥኽ፥
9፤10፤አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡ትወድ፟፡ዘንድ፥ዅልጊዜም፡በመንገዱ፡ትኼድ፡ዘንድ፥ዛሬ፡የማዝ፟ኽን፡ይ ህችን፡ትእዛዝ፡ዅሉ፡
ታደርጋት፡ዘንድ፡ብትጠብቅ፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ትወርሳት፡ዘንድ፡በሚሰጥኽ፡ምድር፡ውስጥ፡ንጹሕ፡ደም ፡እንዳይፈስ፟፡ደምም፡ባንተ፡ላይ፡እንዳይኾን፥በእነዚህ፡በሦስት፡ከተማዎች፡ላይ፡ሌላዎች፡ሦስት፡ከተማዎ ችን፡ትጨምራለኽ።
11፤ሰው፡ግን፡ባልንጀራውን፡ቢጠላ፥ቢሸምቅበትም፥ተነሥቶም፡እስኪሞት፡ድረስ፡ቢመታው፥ከነዚህም፡ከተማዎ ች፡ወደ፡አንዲቱ፡ቢሸሽ፥
12፤የከተማው፡ሽማግሌዎች፡ይልካሉ፥ከተማጠነበትም፡ከተማ፡ይነጥቁታል፥እንዲሞትም፡በደም፡ተበቃዩ፡እጅ፡ አሳልፈው፡ይሰጡታል።
13፤ዐይንኽ፡አትራራለት፤ነገር፡ግን፥መልካም፡ይኾንልኽ፡ዘንድ፡ንጹሑን፡ደም፡ከእስራኤል፡ታስወግዳለኽ።
14፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ትወርሳት፡ዘንድ፡በሚሰጥኽ፡ምድር፡በምትወርሳት፡ርስትኽ፡የቀደሙ፡ሰዎች፡የ ተከሉትን፡የባልንጀራኽን፡የድንበር፡ምልክት፡አትንቀል።
15፤ስለ፡በደል፡ዅሉ፥ክፉ፡በማድረግም፡ስለሠራት፡ኀጢአት፡ዅሉ፡በማንም፡ላይ፡አንድ፡ምስክር፡አይቁም፤በ ኹለት፡ምስክሮች፡ወይም፡በሦስት፡ምስክሮች፡አፍ፡ነገር፡ዅሉ፡ይጸናል።
16፤በዐመፃ፡ይከሰ፟ው፡ዘንድ፡በሰው፡ላይ፡ሐሰተኛ፡ምስክር፡ቢቆም፥
17፤ኹለቱ፡ጠበኛዎች፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡በካህናቱና፡በዚያ፡ዘመን፡በሚፈርዱ፡ፈራጆች፡ፊት፡ይቆማሉ፤
18፤ፈራጆቹም፡አጥብቀው፡ይመረምራሉ፤ያም፡ምስክር፡ሐሰተኛ፡ምስክር፡ኾኖ፡በወንድሙ፡ላይ፡በሐሰት፡ተናግ ሮ፡ቢገኝ፥
19፤በወንድሙ፡ላይ፡ያደርገው፡ዘንድ፡ያሰበውን፡በርሱ፡ላይ፡ትመልሱበታላችኹ፤እንዲሁም፡ከአንተ፡መካከል ፡ክፋቱን፡ታስወግዳለኽ።
20፤የቀሩትም፡ሰምተው፡ይፈራሉ፥እንደዚህ፡ያለውንም፡ክፋት፡ከመካከልኽ፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡ደግሞ፡አያደ ርጉም።
21፤ዐይንኽም፡አትራራለት፤ነፍስ፡በነፍስ፥ዐይን፡በዐይን፥ጥርስ፡በጥርስ፥እጅ፡በእጅ፥እግር፡በእግር፥ይ መለሳል።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡20።______________
ምዕራፍ፡20።
1፤ጠላቶችኽን፡ለመውጋት፡በወጣኽ፡ጊዜ፥ፈረሶችንና፡ሠረገላዎችን፡ሕዝቡንም፡ከአንተ፡ይልቅ፡በዝተው፡ባየ ኽ፡ጊዜ፥ከግብጽ፡አገር፡ያወጣኽ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከአንተ፡ጋራ፡ነውና፥አትፍራቸው።
2፤ወደ፡ሰልፍም፡በቀረባችኹ፡ጊዜ፡ካህኑ፡ይቅረብ፡ለሕዝቡም፡እንዲህ፡ብሎ፡ይንገራቸው፦
3፤እስራኤል፡ሆይ፥ስሙ፤ዛሬ፡ጠላቶቻችኹን፡ለመውጋት፡ትቀርባላችኹ፤ልባችኹ፡አይታወክ፥አትፍሩ፥አትንቀጥ ቀጡ፥በፊታቸውም፡አትደንግጡ፤
4፤ከእናንተ፡ጋራ፡የሚኼድ፥ያድናችኹም፡ዘንድ፡ጠላቶቻችኹን፡ስለ፡እናንተ፡የሚወጋ፡አምላካችኹ፡እግዚአብ ሔር፡ነውና።
5፤አለቃዎችም፡ለሕዝቡ፡እንዲህ፡ብለው፡ይናገሩ፦ዐዲስ፡ቤት፡ሠርቶ፡ያላስመረቀ፡ሰው፡ቢኖር፡በሰልፍ፡እን ዳይሞት፡ሌላም፡ሰው፡እንዳያስመርቀው፡ወደ፡ቤቱ፡ተመልሶ፡ይኺድ።
6፤ወይንም፡ተክሎ፡ፍሬውንም፡ያልበላ፡ሰው፡ቢኖር፡በሰልፍ፡እንዳይሞት፡ሌላም፡ሰው፡ፍሬውን፡እንዳይበላ፡ ወደ፡ቤቱ፡ተመልሶ፡ይኺድ።
7፤ሚስትም፡ዐጭቶ፡ያላገባትም፡ሰው፡ቢኖር፡በሰልፍ፡እንዳይሞት፡ሌላም፡ሰው፡እንዳያገባት፡ወደ፡ቤቱ፡ተመ ልሶ፡ይኺድ።
8፤አለቃዎቹም፡ደግሞ፡ጨምረው።ማንም፡ፈሪና፡ድንጉጥ፡ሰው፡ቢኾን፡ርሱ፡ፈርቶ፡የወንድሞቹን፡ልብ፡ደግሞ፡ እንዳያስፈራ፡ወደ፡ቤቱ፡ተመልሶ፡ይኺድ፡ብለው፡ለሕዝቡ፡ይናገሩ።
9፤አለቃዎቹም፡ለሕዝቡ፡ነግረው፡በጨረሱ፡ጊዜ፡በየጭፍራው፡በሕዝቡ፡ላይ፡የጦር፡አለቃዎችን፡ይሹሙ።
10፤ለመዋጋት፡ወደ፡አንዲት፡ከተማ፡በደረስኽ፡ጊዜ፡አስቀድመኽ፡በዕርቅ፡ቃል፡ጥራቸው።
11፤የዕርቅ፡ቃልም፡ቢመልሱልኽ፡ደጅም፡ቢከፍቱልኽ፥በከተማ፡ውስጥ፡ያለው፡ሕዝብ፡ዅሉ፡ይገብሩልኽ፡ያገል ግሉኽም።
12፤የዕርቅ፡ቃልም፡ባይመልሱልኽ፡ከአንተም፡ጋራ፡መዋጋት፡ቢወዱ፥አንተ፡ከተማዪቱን፡ትከባ፟ለኽ፡ታስጨን ቃትማለኽ፤
13፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡በእጅኽ፡አሳልፎ፡በሰጣት፡ጊዜ፥በርሷ፡ያሉትን፡ወንዶች፡ዅሉ፡በሰይፍ፡ስለ ት፡ትገድላቸዋለኽ፤
14፤ነገር፡ግን፥ሴቶቹንና፡ሕፃናትን፡እንስሳዎቹንም፡በከተማዪቱም፡ያለውን፡ምርኮ፡ዅሉ፡በዝብዘኽ፡ለአን ተ፡ትወስዳለኽ፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡የሚሰጥኽን፡የጠላቶችኽን፡ምርኮ፡ትበላለኽ።
15፤የእነዚህ፡አሕዛብ፡ከተማዎች፡ባይደሉት፡ከአንተ፡እጅግ፡በራቁት፡ከተማዎች፡ዅሉ፡እንዲሁ፡ታደርጋለኽ ።
16፤ነገር፡ግን፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ርስት፡አድርጎ፡ከሚሰጥኽ፡ከነዚህ፡አሕዛብ፡ከተማዎች፡ምንም፡ነ ፍስ፡አታድንም።
17፤18፤ነገር፡ግን፥ለአማልክታቸው፡ያደረጉትን፡ርኵሰት፡ዅሉ፡ታደርጉ፡ዘንድ፡እንዳያስተምሯችኹ፥በአምላ ካችኹም፡በእግዚአብሔር፡ላይ፡ኀጢአት፡እንዳትሠሩ፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡እንዳዘዘኽ፡ኬጢያዊውን፡አሞራ ዊውንም፡ከነዓናዊውንም፡ፌርዛዊውንም፡ዔዊያዊውንም፡ኢያቡሳዊውንም፡ፈጽመኽ፡ታጠፋቸዋለኽ።
19፤ከተማዪቱን፡ለመውሰድ፡በመውጋት፡ብዙ፡ቀን፡ከበ፟ኽ፡ባስጨነቅኻት፡ጊዜ፥ምሣርኽን፡አንሥተኽ፡ዛፎቿን ፡አትቍረጥ፤ከነርሱ፡ትበላለኽና፡አትቍረጣቸው፤ከበ፟ኽ፡የምታጠፋው፡የምድር፡ዛፍ፡ሰው፡መኾኑ፡ነውን፧
20፤ለመብል፡የማይኾኑትን፡የምታውቃቸውን፡ዛፎች፡ታጠፋቸዋለኽ፥ትቈርጣቸውማለኽ፤እስክታሸንፋትም፡ድረስ ፡በምትዋጋኽ፡ከተማ፡ላይ፡ምሽግ፡ትመሽጋለኽ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡21።______________
ምዕራፍ፡21።
1፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ትወርሳት፡ዘንድ፡በሚሰጥኽ፡ምድር፡የተገደለ፡ሰው፡በሜዳ፡ወድቆ፡ቢገኝ፥
2፤ገዳዩም፡ባይታወቅ፥ሽማግሌዎችኽና፡ፈራጆችኽ፡ወጥተው፡በተገደለው፡ሰው፡ዙሪያ፡እስካሉት፡ከተማዎች፡ድ ረስ፡በስፍር፡ይለኩ፤
3፤ወደተገደለውም፡ሰው፡አቅራቢያ፡የኾነችው፡የከተማዪቱ፡ሽማግሌዎች፡ለሥራ፡ያልደረሰችውን፡ቀንበርም፡ያ ልተጫነባትን፡ጊደር፡ይውሰዱ፤
4፤የዚያችም፡ከተማ፡ሽማግሌዎች፡ጊደሪቱን፡ይዘው፡ፈሳሽ፡ውሃ፡ወዳለበት፡ወዳልታረሰና፡ዘርም፡ወዳልተዘራ በት፡ሸለቆ፡ይኼዳሉ፤በዚያም፡በሸለቆው፡ውስጥ፡የጊደሪቱን፡ዐንገት፡ይሰብራሉ።
5፤የሌዊ፡ልጆች፡ካህናትም፡ይቀርባሉ፤በፊቱ፡እንዲያገለግሉ፥በስሙም፡እንዲባርኩ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር ፡መርጧቸዋልና፥በእነርሱም፡ቃል፡ክርክር፡ዅሉ፡ጕዳትም፡ዅሉ፡ይቈረጣልና፤
6፤ወደተገደለው፡ሰው፡አቅራቢያ፡የኾነችው፡የከተማዪቱ፡ሽማግሌዎች፡ዅሉ፡በሸለቆው፡ውስጥ፡ዐንገቷ፡በተሰ በረው፡ጊደር፡ላይ፡እጃቸውን፡ሲታጠቡ።
7፤እጃችን፡ይህን፡ደም፡አላፈሰሰችም፥ዐይናችንም፡አላየችም፤
8፤አቤቱ፥የተቤዠኸውን፡ሕዝብኽን፡እስራኤልን፡ይቅር፡በል፤በሕዝብኽም፡በእስራኤል፡ላይ፡የንጹሑን፡ደም፡ በደል፡አትቍጠር፡ብለው፡ይናገራሉ።ስለ፡ደሙም፡ይሰረይላቸዋል።
9፤አንተም፡በእግዚአብሔር፡ዐይን፡የቀናውን፡ባደረግኽ፡ጊዜ፡የንጹሑን፡ደም፡በደል፡ከመካከልኽ፡ታርቃለኽ ።
10፤ጠላቶችኽን፡ልትወጋ፡በወጣኽ፡ጊዜ፥አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡በእጅኽ፡አሳልፎ፡በሰጣቸው፡በማረክኻቸ ውም፡ጊዜ፥
11፤በተማረኩት፡መካከል፡የተዋበች፡ሴት፡ብታይ፥ብትመኛትም፡ሚስትም፡ልታደርጋት፡ብትወድ፟፥ወደ፡ቤትኽ፡ ታመጣታለኽ፤
12፤ርሷም፡ራሷን፡ትላጫለች፥ጥፍሯንም፡ትቈረጣለች፤
13፤የተማረከችበትንም፡ልብስ፡ታወልቃለች፥በቤትኽም፡ተቀምጣ፡ስለ፡አባቷና፡ስለ፡እናቷ፡አንድ፡ወር፡ሙሉ ፡ታለቅሳለች፤ከዚያም፡በዃላ፡ትደርስባታለኽ፥ባልም፡ትኾናታለኽ፥ርሷም፡ሚስት፡ትኾንልኻለች።
14፤ከዚያም፡በዃላ፡በርሷ፡ደስ፡ባይልኽ፡ሐራነት፡አውጥተኽ፡ወደወደደችው፡ትሰድዳታለኽ፤በዋጋ፡ግን፡አት ሸጣትም፤ዕፍረት፡አድርገኽባታልና፥እንደ፡ባሪያ፡አትቈጥራትም።
15፤ላንድ፡ሰው፡አንዲቱ፡የተወደደች፡አንዲቱም፡የተጠላች፡ኹለት፡ሚስቶች፡ቢኖሩት፥ለርሱም፡የተወደደችው ፡ደግሞም፡የተጠላችው፡ልጆችን፡ቢወልዱ፥በኵሩም፡ከተጠላችው፡ሚስት፡የተወለደው፡ልጅ፡ቢኾን፥
16፤ለልጆቹ፡ከብቱን፡በሚያወርስበት፡ቀን፡ከተጠላችው፡ሚስት፡በተወለደው፡በበኵሩ፡ፊት፡ከተወደደችው፡ሚ ስት፡የተወለደውን፡ልጅ፡በኵር፡ያደርገው፡ዘንድ፡አይገ፟ባ፟ውም፤
17፤ነገር፡ግን፥ከከብቱ፡ኹለት፡ዕጥፍ፡ለርሱ፡በመስጠት፡ከተጠላችው፡ሚስት፡የተወለደው፡ልጅ፡በኵር፡እን ደ፡ኾነ፡ያስታውቅ።የኀይሉ፡መዠመሪያ፡ነውና፥በኵርነቱ፡የርሱ፡ነው።
18፤ማንም፡ሰው፡ለአባቱ፡ቃልና፡ለእናቱ፡ቃል፡የማይታዘዝ፡ቢቀጡትም፡የማይሰማቸው፡እልከኛና፡ዐመፀኛ፡ል ጅ፡ቢኖረው፥
19፤አባቱና፡እናቱ፡ይዘው፡ወደከተማው፡ሽማግሌዎች፡ወደሚኖሩበትም፡ስፍራ፡በር፡ያምጡት፤
20፤የከተማውንም፡ሽማግሌዎች፦ይህ፡ልጃችን፡እልከኛና፡ዐመፀኛ፡ነው፥ለቃላችንም፡አይታዘዝም፡ሥሥታምና፡ ሰካራም፡ነው፡ይበሏቸው።
21፤የከተማውም፡ሰዎች፡ዅሉ፡እስኪሞት፡ድረስ፡በድንጋይ፡ይውገሩት፤እንዲህም፡ክፉውን፡ነገር፡ከመካከልኽ ፡ታርቃለኽ፥እስራኤልም፡ዅሉ፡ሰምተው፡ይፈራሉ።
22፤ማንም፡ሰው፡ለሞት፡የሚያበቃውን፡ኀጢአት፡ቢሠራ፥እንዲሞትም፡ቢፈረድበት፥በዕንጨትም፡ላይ፡ብትሰቅለ ው፥
23፤በዕንጨት፡ላይ፡የተሰቀለ፡በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡የተረገመ፡ነውና፥ሬሳው፡በዕንጨት፡ላይ፡አይደር፤ነ ገር፡ግን፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ርስት፡አድርጎ፡የሰጠኽን፡ምድር፡እንዳታረክስ፡በርግጥ፡በዚያው፡ቀን፡ ቅበረው።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡22።______________
ምዕራፍ፡22።
1፤የወንድምኽ፡በሬ፡ወይም፡በግ፡ጠፍቶ፡ብታይ፡ቸል፡አትበል፤ወደ፡ወንድምኽ፡መልሰው።
2፤ወንድምኽም፡በአቅራቢያኽ፡ባይኾን፡ወይም፡ባታውቀው፡ይዘኽ፡ወደ፡ቤትኽ፡ትገባለኽ፤ወንድምኽ፡እስኪሻው ፡ድረስ፡ባንተ፡ዘንድ፡ይቀመጣል፥ለርሱም፡ትመልሰዋለኽ።
3፤እንዲህም፡በአህያው፡ወይም፡በልብሱ፡ታደርጋለኽ፤እንዲህም፡በወንድምኽ፡በጠፋበት፡ነገር፡ዅሉ፡ባገኘኸ ው፡ጊዜ፡ታደርጋለኽ፤ቸል፡ልትለው፡አይገ፟ባ፟ኽም።
4፤የወንድምኽ፡አህያ፡ወይም፡በሬው፡በመንገድ፡ወድቆ፡ብታይ፡ከርሱ፡ጋራ፡ኾነኽ፡አነሣሣው፡እንጂ፡ቸል፡አ ትበለው።
5፤ሴት፡የወንድ፡ልብስ፡አትልበስ፥ወንድም፡የሴት፡ልብስ፡አይልበስ፤ይህን፡የሚያደርግ፡በአምላክኽ፡በእግ ዚአብሔር፡ዘንድ፡የተጠላ፡ነውና።
6፤በመንገድ፡ስትኼድ፡በዛፍ፡ወይም፡በመሬት፡ላይ፡እናቲቱ፡በጫጩቶቿ፡ወይም፡በዕንቍላሎቿ፡ላይ፡ተኝታ፡ሳ ለች፡የወፍ፡ጐዦ፡ብታገኝ፥እናቲቱን፡ከጫጩቷ፡ጋራ፡አትውሰድ።
7፤ነገር፡ግን፥መልካም፡ይኾንልኽ፡ዘንድ፡ዕድሜኽም፡ይረዝም፡ዘንድ፡እናቲቱን፡ስደድ፥ጫጩቶችንም፡ለአንተ ፡ውሰድ።
8፤ዐዲስ፡ቤት፡በሠራኽ፡ጊዜ፡ማንም፡ከርሱ፡ወድቆ፡ደሙን፡በቤትኽ፡ላይ፡እንዳታመጣ፡በጣራው፡ዙሪያ፡መከታ ፡አድርግለት።
9፤የዘራኸው፡ዘርና፡ከወይኑ፡የወጣው፡አንድ፡ኾነው፡እንዳይጠፉብኽ፡በወይንኽ፡ቦታ፡ላይ፡ኹለት፡ዐይነት፡ ዘር፡አትዝራ።
10፤በበሬና፡በአህያ፡በአንድነት፡አትረስ።
11፤ከተልባ፡እግርና፡ከበግ፡ጠጕር፡በአንድነት፡የተሠራ፡ልብስ፡አትልበስ።
12፤በምትለብሰው፡በልብስኽ፡በአራቱ፡ማእዘን፡ዘርፍ፡አድርግ።
13፤ማናቸውም፡ሰው፡ሚስት፡ቢያገባ፥ከደረሰባትም፡በዃላ፡ቢጠላት፥
14፤የነውር፡ነገር፡አውርቶ፦እኔ፡ይህችን፡ሴት፡ሚስት፡አድርጌ፡አገባዃት፥በደርስኹባትም፡ጊዜ፡ድንግልና ዋን፡አላገኘኹባትም፡ብሎ፡በክፉ፡ስም፡ቢያሳጣት፥
15፤የብላቴናዪቱ፡አባትና፡እናት፡የድንግልናዋን፡ምልክት፡ወስደው፡በበሩ፡በአደባባይ፡ወደተቀመጡ፡ወደከ ተማ፡ሽማግሌዎች፡ያምጡት፤
16፤የብላቴናዪቱም፡አባት፡ሽማግሌዎቹን፦እኔ፡ለዚህ፡ሰው፡ልጄን፡ዳርኹለት፡ርሱም፡ጠላት፤
17፤እንሆም፦በልጅኽ፡ድንግልና፡አላገኘኹባትም፡ብሎ፡የነውር፡ነገር፡አወራባት፤የልጄም፡ምልክት፡ይኸው፡ ይላቸዋል።በከተማም፡ሽማግሌዎች፡ፊት፡ልብሱን፡ይዘረጋሉ።
18፤የዚያችም፡ከተማ፡ሽማግሌዎች፡ያንን፡ሰው፡ወስደው፡ይግረፉት፤
19፤በእስራኤል፡ድንግል፡ላይ፡ክፉ፡ስም፡አምጥቷልና፥መቶ፡የብር፡ሰቅል፡ያስከፍሉት፥ለብላቴናዪቱም፡አባ ት፡ይስጡት፤ርሷም፡ሚስት፡ትኹነው፥በዕድሜውም፡ዘመን፡ዅሉ፡ሊፈታት፡አይገ፟ባ፟ውም።
20፤ነገሩ፡ግን፡እውነት፡ቢኾን፥በብላቴናዪቱም፡ድንግልናዋ፡ባይገኝ፥
21፤ብላቴናዪቱን፡ወዳባቷ፡ቤት፡ደጅ፡ያውጧት፥በእስራኤልም፡ዘንድ፡የማይገ፟ባ፟ውን፡ነገር፡አድርጋለችና ፥በአባቷም፡ቤት፡አመንዝራለችና፡የከተማዋ፡ሰዎች፡እስክትሞት፡ድረስ፡በድንጋይ፡ይውገሯት፤እንዲሁም፡ክፉ ውን፡ነገር፡ከመካከልኽ፡ታስወግዳለኽ።
22፤ማናቸውም፡ሰው፡ከሌላ፡ሰው፡ሚስት፡ጋራ፡ተኝቶ፡ቢገኝ፥አመንዝራውና፡አመንዝራዪቱ፡ኹለታቸው፡ይሙቱ፤ እንዲሁም፡ክፉውን፡ነገር፡ከእስራኤል፡ታስወግዳለኽ።
23፤ማናቸውም፡ሰው፡ድንግልና፡ያላትን፡ልጃገረድ፡ቢያጭ፥ሌላ፡ሰውም፡በከተማ፡ውስጥ፡አግኝቶ፡ከርሷ፡ጋራ ፡ቢተኛ፥
24፤ኹለቱን፡ወደዚያች፡ከተማ፡በር፡አውጧቸው፤ብላቴናዪቱ፡በከተማ፡ውስጥ፡ሳለች፡አልጮኸችምና፥ሰውዮውም ፡የባልንጀራውን፡ሚስት፡አስነውሯልና፥እስኪሞቱ፡ድረስ፡በድንጋይ፡ውገሯቸው፤እንዲሁም፡ክፉውን፡ነገር፡ከ መካከልኽ፡ታስወግዳለኽ።
25፤ነገር፡ግን፥ሰው፡የታጨችውን፡ልጃገረድ፡በሜዳ፡ቢያገኛት፥በግድ፡አሸንፎም፡ቢደርስባት፥ያ፡የደረሰባ ት፡ሰው፡ብቻውን፡ይገደል።
26፤በብላቴናዪቱ፡ላይ፡ግን፡ምንም፡አታድርጉ፡በብላቴናዪቱ፡ላይ፡ለሞት፡የሚያበቃ፡ኀጢአት፡የለባትም፤ሰ ው፡በባልንጀራው፡ላይ፡ተነሥቶ፡እንደሚገድለው፡ይህ፤ነገር፡ደግሞ፡እንደዚሁ፡ነውና፤
27፤በሜዳ፡ባገኛት፡ጊዜ፡የታጨችው፡ልጃገረድ፡ጮኻለችና፥የሚታደጋትም፡አልነበረምና።
28፤ማናቸውም፡ሰው፡ድንግልና፡ያላትን፡ያልታጨች፡ልጃገረድ፡ቢያገኝ፥ወስዶም፡ቢደርስባት፥ቢያገኙትም፥
29፤ያ፡የደረሰባት፡ሰው፡ዐምሳ፡የብር፡ሰቅል፡ለብላቴናዪቱ፡አባት፡ይስጥ፤አስነውሯታልና፥ሚስት፡ትኹነው ፤በዕድሜውም፡ዘመን፡ዅሉ፡ሊፈታት፡አይገ፟ባ፟ውም።
30፤ማናቸውም፡ሰው፡የአባቱን፡ሚስት፡አይውሰድ፥የአባቱንም፡ልብስ፡ጫፍ፡አይግለጥ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡23።______________
ምዕራፍ፡23።
1፤ቍላው፡የተቀጠቀጠ፡ብልቱም፡የተቈረጠ፡ወደእግዚአብሔር፡ጉባኤ፡አይግባ።
2፤ዲቃላ፡ወደእግዚአብሔር፡ጉባኤ፡አይግባ፤እስከ፡ዐሥር፡ትውልድ፡ድረስ፡ወደእግዚአብሔር፡ጉባኤ፡አይግባ ።
3፤4፤ከግብጽ፡በወጣችኹ፡ጊዜ፡እንጀራና፡ውሃ፡ይዘው፡በመንገድ፡ላይ፡አልተቀበሏችኹምና፥በመስጴጦምያ፡ካ ለው፡ከፋቱራ፡የቢዖርን፡ልጅ፡በለዓምን፡ዋጋ፡ሰጥተው፡ይረግምኽ፡ዘንድ፡አምጥተውብኻልና፥አሞናዊና፡ሞዐባ ዊ፡ወደእግዚአብሔር፡ጉባኤ፡አይግባ፡እስከ፡ዐሥር፡ትውልድ፡ድረስ፡ለዘለዓለም፡ወደእግዚአብሔር፡ጉባኤ፡አ ይግባ።
5፤ነገር፡ግን፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በለዓምን፡ይሰማ፡ዘንድ፡አልወደደም፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ወ ዶ፟ኻልና፥ርግማኑን፡በረከት፡አደረገልኽ።
6፤በዘመንኽ፡ዅሉ፡ለዘለዓለም፡ሰላምና፡ልማት፡ለእነርሱ፡አትሻ።
7፤ኤዶማዊው፡ወንድምኽ፡ነውና፥አትጸየፈው፤ግብጻዊውንም፡በአገሩ፡ስደተኛ፡ነበርኽና፡አትጸየፈው።
8፤ከነርሱም፡በሦስተኛው፡ትውልድ፡የሚወለዱ፡ልጆች፡ወደእግዚአብሔር፡ጉባኤ፡ይግቡ።
9፤ጠላቶችኽን፡ልትወጋ፡በወጣኽ፡ጊዜ፡ከክፉ፡ነገር፡ዅሉ፡ሰውነትኽን፡ጠብቅ።
10፤በእናንተ፡መካከል፡ሌሊት፡በሚኾነው፡ርኵሰት፡የረከስ፡ሰው፡ቢኖር፥ከሰፈር፡ወደ፡ውጭ፡ይውጣ፥ወደ፡ሰ ፈርም፡አይግባ።
11፤በመሸም፡ጊዜ፡በውሃ፡ይታጠብ፤ፀሓይም፡በገባ፡ጊዜ፡ወደ፡ሰፈር፡ይመለስ።
12፤ወደ፡ሜዳም፡ትወጣበት፡ዘንድ፡ከሰፈር፡ውጭ፡ቦታ፡ይኹንልኽ።
13፤ከመሣሪያኽም፡ጋራ፡መቈፈሪያ፡ያዝ፤በሜዳም፡በተቀመጥኽ፡ጊዜ፡ትምስበታለኽ፥ዞረኽም፡ከአንተ፡የወጣው ን፡በዐፈር፡ትከድነዋለኽ።
14፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ሊያድንኽ፡ጠላቶችኽንም፡በእጅኽ፡አሳልፎ፡ሊሰጥ፡በሰፈርኽ፡መካከል፡ይኼዳል ና፥ስለዚህ፡ነውረኛ፡ነገር፡እንዳያይብኽ፥ፊቱንም፡ከአንተ፡እንዳይመልስ፡ሰፈርኽ፡የተቀደስ፡ይኹን።
15፤ከጌታው፡ኰብሎ፟፡ወዳንተ፡የመጣውን፡ባሪያ፡ለጌታው፡አሳልፈኽ፡አትስጥ።
16፤ከደጆችኽ፡በሚመርጣት፡በአንዲቱ፡በሚወዳ፟ት፡ስፍራ፡ከአንተ፡ጋራ፡በመካከልኽ፡ይቀመጥ፥አንተም፡አታ ስጨንቀው።
17፤ከእስራኤል፡ሴቶች፡ልጆች፡ሴት፡ጋለሞታ፡አትገኝ፥ከእስራኤልም፡ወንዶች፡ልጆች፡ወንድ፡ጋለሞታ፡አይገ ኝ።
18፤ስለተሳልኸው፡ስእለት፡ዅሉ፡የጋለሞታዪቱን፡ዋጋና፡የውሻውን፡ዋጋ፡ወደ፡አምላክኽ፡ወደእግዚአብሔር፡ ቤት፡አታቅርብ፤ኹለቱም፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡የሚያጸይፉ፡ናቸውና።
19፤ለወንድምኽ፡በወለድ፡አታበድር፤የብር፡ወይም፡የእኽል፡ወይም፡የማናቸውንም፡ነገር፡ዅሉ፡ወለድ፡አትው ሰድ።
20፤ለእንግዳው፡በወለድ፡አበድረው፤ነገር፡ግን፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ልትወርሳት፡በምትገባባት፡ምድር ፡በሥራኽ፡ዅሉ፡ይባርክኽ፡ዘንድ፡ለወንድምኽ፡በወለድ፡አታበድር።
21፤ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡ስእለት፡በተሳልኽ፡ጊዜ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከአንተ፡ፈጽሞ፡ይሻዋል ና፥ኀጢአትም፡ይኾንብኻልና፥መክፈሉን፡አታዘግይ።
22፤ባትሳል፡ግን፡ኀጢአት፡የለብኽም።
23፤በአፍኽ፡የተናገርኸውን፡ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡በፈቃድኽ፡ተስለኻልና፥ከከንፈርኽ፡የወጣውን፡ታ ደርግ፡ዘንድ፡ጠብቅ።
24፤ወደባልንጀራኽ፡ወይን፡ቦታ፡በገባኽ፡ጊዜ፡እስክትጠግብ፡ድረስ፡ከወይኑ፡ብላ፤ወደ፡ዕቃኽ፡ግን፡ከርሱ ፡ምንም፡አታግባ።
25፤ወደባልንጀራኽ፡ዕርሻ፡በገባኽ፡ጊዜ፡እሸቱን፡በእጅኽ፡ቀጥፈኽ፡ብላ፤ወዳልታጨደው፡ወደባልንጀራኽ፡እ ኽል፡ግን፡ማጭድ፡አታግባ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡24።______________
ምዕራፍ፡24።
1፤ሰው፡ሴትን፡ወስዶ፡ቢያገባ፥የዕፍረት፡ነገር፡ስላገኘባት፡በርሱ፡ዘንድ፡ሞገስ፡ባታገኝ፥የፍቿን፡ጽሕፈ ት፡ጽፎ፡በእጇ፡ይስጣት፥ከቤቱም፡ይስደዳት።
2፤ከቤቱም፡ከወጣች፡በዃላ፡ሌላ፡ወንድ፡ብታገባ፥
3፤ኹለተኛውም፡ባል፡ቢጠላት፥የፍቿንም፡ጽሕፈት፡ጽፎ፡በእጇ፡ቢሰጣት፥ከቤቱም፡ቢሰዳ፟ት፥ወይም፡ሚስት፡አ ድርጎ፡ያገባት፡ኹለተኛው፡ባሏ፡ቢሞት፥
4፤የሰደዳት፡የቀድሞ፡ባሏ፡ከረከሰች፡በዃላ፡ደግሞ፡ያገባት፡ዘንድ፡አይገ፟ባ፟ውም፤ያ፡በእግዚአብሔር፡የ ተጠላ፡ነው፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ርስት፡አድርጎ፡የሰጠኽን፡ምድር፡አታርክስ።
5፤ዐዲስ፡ሚስትም፡ያገባ፡ሰው፡ወደ፡ጦርነት፡አይኺድ፥ነገርም፡አይጫኑበት፤ነገር፡ግን፥አንድ፡ዓመት፡በቤ ቱ፡በፈቃዱ፡ይቀመጥ፥የወሰዳትንም፡ሚስቱን፡ደስ፡ያሠኛት።
6፤የሰውን፡ነፍስ፡እንደ፡መውሰድ፡ነውና፥ወፍጮ፡ወይም፡መጅ፡ስለ፡መያዣ፡ማንም፡አይውሰድ።
7፤ማንም፡ሰው፡ከእስራኤል፡ልጆች፡ከወንድሞቹ፡አንዱን፡ሰርቆ፡እንደ፡ባሪያ፡ሲያደርግበት፡ወይም፡ሲሸጠው ፡ቢገኝ፥ያ፡ሌባ፡ይሙት፤እንዲሁም፡ክፉውን፡ነገር፡ከመካከልኽ፡ታስወግዳለኽ።
8፤በለምጽ፡ደዌ፡ሌዋውያን፡ካህናት፡ያስተማሩኽን፡ዅሉ፡ፈጽመኽ፡እንድትጠብቅ፡እንድታደርግም፡ተጠንቀቅ፤ እኔ፡ያዘዝዃቸውን፡እንዲሁ፡ታደርግ፡ዘንድ፡ጠብቅ።
9፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከግብጽ፡በወጣችኹ፡ጊዜ፡በመንገድ፡ሳላችኹ፡በማርያም፡ላይ፡ያደረገውን፡ዐስብ ።
10፤ለባልንጀራኽ፡ባበደርኸው፡ጊዜ፡መያዣውን፡ልትወስድ፡ወደ፡ቤቱ፡አትግባ።
11፤አንተ፡በውጭ፡ቁም፡ያበደርኸውም፡ሰው፡መያዣውን፡ያውጣልኽ።
12፤ያም፡ሰው፡ድኻ፡ቢኾን፡መያዣውን፡ባንተ፡ዘንድ፡አታሳድር።
13፤ለብሶት፡እንዲተኛ፡እንዲባርክኽም፡ፀሓይ፡ሳይገባ፡መያዣውን፡ፈጽመኽ፡መልስለት፤በአምላክኽም፡በእግ ዚአብሔር፡ፊት፡ጽድቅ፡ይኾንልኻል፡
14፤ድኻና፡ችግረኛ፡የኾነውን፡ምንደኛ፥ከወንድሞችኽ፡ወይም፡በምድርኽ፡በአገርኽ፡ደጅ፡ውስጥ፡ከሚቀመጡት ፡መጻተኛዎች፡ቢኾን፥አታስጨንቀው።
15፤ድኻ፡ነውና፥ነፍሱም፡ጠንክራ፡ትፈልገዋለችና፡ወደ፡እግዚአብሔር፡እንዳይጮኽብኽ፡ኀጢአትም፡እንዳይኾ ንብኽ፡ደመ፡ወዙን፡ፀሓይ፡ሳይገባ፡በቀኑ፡ስጠው።
16፤አባቶች፡ስለ፡ልጆች፡አይገደሉ፥ልጆችም፡ስለ፡አባቶች፡አይገደሉ፤ነገር፡ግን፥ዅሉ፡እያንዳንዱ፡በኀጢ አቱ፡ይገደል።
17፤የመጻተኛውንና፡የድኻ፡አደጉን፡ፍርድ፡አታጣ፟ም፟ባቸው፤የመበለቲቱን፡ልብስ፡ለመያዣ፡አትውሰድባት።
18፤አንተም፡በግብጽ፡ባሪያ፡እንደ፡ነበርኽ፥አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ከዚያ፡እንዳዳነኽ፡ዐስብ፤ስለዚህ ፥ይህን፡ነገር፡ታደርግ፡ዘንድ፡አዝዤኻለኹ።
19፤የዕርሻኽን፡መከር፡ባጨድኽ፡ጊዜ፡ነዶም፡ረስተኽ፡በዕርሻኽ፡ብታስቀር፥ትወስደው፡ዘንድ፡አትመለስ፤አ ምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በእጅኽ፡ሥራ፡ዅሉ፡እንዲባርክኽ፥ለመጻተኛና፡ለድኻ፡አደግ፡ለመበለትም፡ተወው።
20፤የወይራኽን፡ፍሬ፡ባረገፍኽ፡ጊዜ፡ከቅርንጫፎቹ፡ላይ፡ማርገፉን፡ለማጣራት፡አትመለስ፤ለመጻተኛና፡ለድ ኻ፡አደግ፡ለመበለትም፡ይኹን።
21፤የወይንኽን፡ፍሬ፡በቈረጥኽ፡ጊዜ፡ቃርሚያውን፡አትልቀመው፤ለመጻተኛና፡ለድኻ፡አደግ፡ለመበለትም፡ይኹ ን።
22፤አንተም፡በግብጽ፡አገር፡ባሪያ፡እንደ፡ነበርኽ፡ዐስብ፤ስለዚህ፥ይህን፡ታደርግ፡ዘንድ፡አዝዤኻለኹ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡25።______________
ምዕራፍ፡25።
1፤በሰዎች፡መካከል፡ጠብ፡ቢኾን፥ወደ፡ፍርድም፡ቢመጡ፥ፈራጆችም፡ቢፈርዱባቸው፥ጻድቁን፦ደኅና፡ነኽ፥የበደ ለውንም፦በደለኛ፡ነኽ፡ይበሏቸው።
2፤በደለኛውም፡መገረፍ፡ቢገባው፡እንዲገረፍ፡ፈራጁ፡በፊቱ፡በምድር፡ላይ፡ያጋድመው፤የግርፋቱም፡ቍጥር፡እ ንደ፡ኀጢአቱ፡መጠን፡ይኹን።
3፤ግርፋቱም፡አርባ፡ይኹን፤ከዚህ፡በላይ፡ጨምሮ፡ብዙ፡ግርፋት፡ቢገርፈው፥ወንድምኽ፡በፊትኽ፡ነውረኛ፡ይኾ ናልና፥ከዚህ፡በላይ፡አይጨመርበት።
4፤እኽል፡የሚያበራየውን፡በሬ፡አፉን፡አትሰር።
5፤ወንድማማቾች፡በአንድነት፡ቢቀመጡ፥አንዱም፡ልጅ፡ሳይኖረው፡ቢሞት፥የሞተው፡ሰው፡ሚስት፡ሌላ፡ሰው፡ታገ ባ፡ዘንድ፡ወደ፡ውጭ፡አትኺድ፤ነገር፡ግን፥የባሏ፡ወንድም፡ወደ፡ርሷ፡ገብቶ፡ርሷን፡ያግባ፥ከርሷም፡ጋራ፡ይ ኑር።
6፤የሟቹ፡ስም፡ከእስራኤል፡ዘንድ፡እንዳይጠፋ፡ከርሷ፡የሚወለደው፡በኵር፡ልጅ፡በሞተው፡በወንድሙ፡ስም፡ይ ጠራ።
7፤ያም፡ሰው፡የወንድሙን፡ሚስት፡ማግባት፡ባይወድ፟፥ዋርሳዪቱ፡በበሩ፡አደባባይ፡ወደሚቀመጡ፡ሽማግሌዎች፡ ኼዳ።ዋርሳዬ፡በእስራኤል፡ዘንድ፡ለወንድሙ፡ስም፡ማቆም፡እንቢ፡አለ፤ከእኔ፡ጋራ፡ሊኖርም፡አልወደደም፡ትበ ላቸው።
8፤የከተማውም፡ሽማግሌዎች፡ጠርተው፡ይጠይቁት፤ርሱም፡በዚያ፡ቆሞ፦አገባት፡ዘንድ፡አልወድ፟ም፡ቢል፥
9፤ዋርሳዪቱ፡በሽማግሌዎቹ፡ፊት፡ወደ፡ርሱ፡ቀርባ፦የወንድሙን፡ቤት፡በማይሠራ፡ሰው፡ላይ፡እንዲህ፡ይደረግ በታል፡ስትል፡ጫማውን፡ከእግሩ፡ታውጣ፥በፊቱም፡እንትፍ፡ትበልበት።
10፤በእስራኤልም፡ዘንድ፡ስሙ፡የጫማ፡ፈቱ፡ቤት፡ተብሎ፡ይጠራ።
11፤ኹለት፡ሰዎች፡ርስ፡በርሳቸው፡ቢጣሉ፥የአንደኛውም፡ሚስት፡ባሏን፡ከሚመታው፡ሰው፡እጅ፡ታድነው፡ዘንድ ፡ብትቀርብ፥እጇንም፡ዘርግታ፡ብልቱን፡ብትይዝ፥
12፤እጇን፡ቍረጥ፥ዐይንኽም፡አትራራላት።
13፤በከረጢትኽ፡ውስጥ፡ታላቅና፡ታናሽ፡የኾነ፡ኹለት፡ዐይነት፡ሚዛን፡አይኑርልኽ።
14፤በቤትኽ፡ውስጥ፡ታላቅና፡ታናሽ፡የኾነ፡ኹለት፡ዐይነት፡መስፈሪያ፡አይኑርልኽ።
15፤16፤ይህን፡የሚያደርግ፡ዅሉ፡ክፋትንም፡የሚያደርግ፡ዅሉ፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡የተጠላ፡ ነውና፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡በሚሰጥኽ፡ምድር፡ላይ፡ዕድሜኽ፡ይረዝም፡ዘንድ፡እውነተኛና፡ፍጹም፡ሚዛን፡ ይኹንልኽ፤እውነተኛና፡ፍጹም፡መስፈሪያም፡ይኹንልኽ።
17፤ከግብጽ፡በወጣችኹ፡ጊዜ፡ዐማሌቅ፡በመንገድ፡ላይ፡ያደረገብኽን፡ዐስብ፤
18፤በመንገድ፡ላይ፡እንደ፡ተቃወመኽ፥አንተም፡ተስኖኽ፡ደክመኽም፡ሳለኽ፡ከአንተ፡በዃላ፡ደክመው፡የነበሩ ትን፡ዅሉ፡እንደ፡መታ፤እግዚአብሔርንም፡አልፈራም።
19፤ስለዚህ፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ትወርሳት፡ዘንድ፡በሚሰጥኽ፡ምድር፡ከሚከቡ፟ኽ፡ጠላቶችኽ፡ዅሉ፡አም ላክኽ፡እግዚአብሔር፡ባሳረፈኽ፡ጊዜ፥የዐማሌቅን፡ዝክረ፡ስሙን፡ከሰማይ፡በታች፡አጥፋው፤ይህንን፡አትርሳ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡26።______________
ምዕራፍ፡26።
1፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ርስት፡አድርጎ፡ወደሚሰጥኽ፡ምድር፡በገባኽም፡ጊዜ፥በወረስኻትም፡በኖርኽባትም ፡ጊዜ፥
2፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከሚሰጥኽ፡ምድር፡ከምትሰበስበው፡ፍሬ፡ዅሉ፡በኵራት፡ውሰድ፡በእንቅብም፡አድር ገው፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ስሙ፡ይጠራበት፡ዘንድ፡ወደመረጠውም፡ስፍራ፡ይዘኽ፡ኺድ።
3፤በዚያም፡ወራት፡ወደሚኾነው፡ካህን፡መጥተኽ፦እግዚአብሔር፡ይሰጠን፡ዘንድ፡ለአባቶቻችን፡ወደማለላቸው፡ ምድር፡እንደ፡ገባኹ፡ዛሬ፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡አስታውቃለኹ፡በለው።
4፤ካህኑም፡እንቅቡን፡ከእጅኽ፡ወስዶ፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡መሠዊያ፡ፊት፡ያኑረው።
5፤በአምላክኽም፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡እንዲህ፡ብለኽ፡ተናገር፦አባቴ፡የተቅበዘበዘ፡ሶርያዊ፡ነበረ፤በቍጥ ር፡ጥቂት፡ሳለ፡ወደ፡ግብጽ፡ወረደ፡በዚያም፡ተቀመጠ፤ታላቅ፡የኾነ፡የበረታም፡ቍጥሩም፡የበዛ፡ሕዝብ፡ኾነ።
6፤ግብጻውያንም፡ክፉ፡ነገር፡አደረጉብን፥አስጨነቁንም፥በላያችንም፡ጽኑ፡ከባድ፡ሥራን፡ጫኑብን፤
7፤ወዳባቶቻችንም፡አምላክ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ጮኽን፤እግዚአብሔርም፡ድምፃችንን፡ሰማ፥ጭንቀታችንንም፡ድ ካማችንንም፡ግፋችንንም፡አየ፤
8፤እግዚአብሔርም፡በጸናች፡እጅና፡በተዘረጋ፡ክንድ፥በታላቅም፡ድንጋጤ፥በተኣምራትም፥በድንቅም፡ከግብጽ፡ አወጣን፤
9፤ወደዚህም፡ስፍራ፡አገባን፥ወተትና፡ማር፡የምታፈሰ፟ውንም፡ይህችን፡ምድር፡ሰጠን።
10፤አኹንም፥እንሆ፥አቤቱ፥አንተ፡የሰጠኸኝን፡የምድሪቱን፡ፍሬ፡በኵራት፡አቅርቤያለኹ።አንተም፡በአምላክ ኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡አኑረው፥በአምላክኽም፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ስገድ።
11፤አንተም፡በመካከልኽም፡ያለ፡ሌዋዊና፡መጻተኛ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ለአንተና፡ለቤትኽ፡በሰጠው፡ቸ ርነት፡ዅሉ፡ደስ፡ይበላችኹ።
12፤ዓሥራት፡በምታወጣበት፡በሦስተኛው፡ዓመት፡የፍሬኽን፡ዅሉ፡ዓሥራት፡አውጥተኽ፡በፈጸምኽ፡ጊዜ፥በአገር ኽ፡ደጅ፡ውስጥ፡ይበሉ፡ዘንድ፡ይጠግቡም፡ዘንድ፡ለሌዋዊው፡ለመጻተኛውም፡ለድኻ፡አደጉም፡ለመበለቲቱም፡ስጣ ቸው።
13፤በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡እንዲህ፡በል፦የተቀደሰውን፡ነገር፡ከቤቴ፡ወስጄ፡ለሌዋዊው፡ለመጻተ ኛውም፡ለድኻ፡አደጉም፡ለመበለቲቱም፡እንዳዘዝኸኝ፡ትእዛዝ፡ዅሉ፡ሰጥቻለኹ፤ትእዛዝኽን፡ምንም፡አላፈረስኹ ም፥አልረሳኹምም፤
14፤በሐዘኔ፡ጊዜ፡እኔ፡ከርሱ፡አልበላኹም፥ለርኩስነቴም፡ከርሱ፡አላወጣኹም፥ከርሱም፡አንዳች፡ለሞተ፡ሰው ፡አልሰጠኹም፤የአምላኬንም፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ሰምቻለኹ፥ያዘዝኸኝንም፡ዅሉ፡አድርጌያለኹ።
15፤ከቅዱስ፡ማደሪያኽ፡ከሰማይ፡ጐብኝ፥ሕዝብኽንም፡እስራኤልን፡ለአባቶቻችን፡እንደ፡ማልኽላቸው፡የሰጠኸ ንንም፡ወተትና፡ማር፡የምታፈሰ፟ውን፡አገር፡ባርክ።
16፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ይህን፡ሥርዐትና፡ፍርድ፡ታደርግ፡ዘንድ፡ዛሬ፡አዞ፟ኻል፤አንተም፡በፍጹም፡ል ብኽና፡በፍጹም፡ነፍስኽ፡ጠብቀው፥አድርገውም።
17፤አንተ፡በመንገዱ፡ትኼድ፡ዘንድ፥ሥርዐቱንና፡ትእዛዙን፡ፍርዱንም፡ትጠብቅ፡ዘንድ፥ቃሉንም፡ትሰማ፡ዘን ድ፡እግዚአብሔር፡ርሱ፡አምላክኽ፡መኾኑን፡ዛሬ፡አስታውቀኻል።
18፤እግዚአብሔርም፡እንደ፡ሰጠኽ፡ተስፋ፡ገንዘቡና፡ሕዝቡ፡መኾንኽን፥ትእዛዙንም፡ዅሉ፡ትጠብቅ፡ዘንድ፥
19፤ከፈጠራቸውም፡አሕዛብ፡ዅሉ፡በምስጋና፡በስም፡በክብር፡ከፍ፡ያደርግኽ፡ዘንድ፥ርሱም፡እንደ፡ተናገረ፡ ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡የተቀደሰ፡ሕዝብ፡ትኾን፡ዘንድ፡ዛሬ፡አስታውቋል።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡27።______________
ምዕራፍ፡27።
1፤ሙሴና፡የእስራኤል፡ሽማግሌዎችም፡እንዲህ፡ብለው፡ሕዝቡን፡አዘዙ፦ዛሬ፡ያዘዝዃችኹን፡ትእዛዝ፡ዅሉ፡ጠብ ቁ።
2፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ወደሚሰጥኽ፡ምድር፡ዮርዳኖስን፡በተሻገርኽ፡ጊዜ፡ታላላቅ፡ድንጋዮችን፡ለአንተ ፡አቁም፥በኖራም፡ምረጋቸው።
3፤የአባቶችኽ፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡ተስፋ፡እንደ፡ሰጠኽ፥ወተትና፡ማር፡ወደምታፈስ፟፡ምድር፥አምላክኽ፡ እግዚአብሔር፡ወደሚሰጥኽ፡ምድር፡ትገባ፡ዘንድ፡በተሻገርኽ፡ጊዜ፥የዚህን፡ሕግ፡ቃሎች፡ዅሉ፡ጻፍባቸው።
4፤ዮርዳኖስንም፡በተሻገርኽ፡ጊዜ፥ዛሬ፡እንዳዘዝኹኽ፥እነዚህን፡ድንጋዮች፡በጌባል፡ተራራ፡አቁም፥በኖራም ፡ምረጋቸው።
5፤በዚያም፡ለአምላክኽ፡ለእግዚአብሔር፡መሠዊያ፡ሥራ፤መሠዊያውም፡ብረት፡ካልነካው፡ድንጋይ፡ይኹን።
6፤ካልተጠረበም፡ድንጋይ፡የአምላክኽን፡የእግዚአብሔርን፡መሠዊያ፡ሥራ፤ለአምላክም፡ለእግዚአብሔር፡የሚቃ ጠለውን፡መሥዋዕትኽን፡አቅርብበት፤
7፤የደኅንነትም፡መሥዋዕት፡ሠዋበት፥በዚያም፡ብላ፤በአምላክኽም፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ደስ፡ይበልኽ።
8፤የዚህንም፡ሕግ፡ቃሎች፡ዅሉ፡የተገለጠ፡አድርገኽ፡በድንጋዮቹ፡ላይ፡ጻፍ።
9፤ሙሴና፡ሌዋውያን፡ካህናት፡ለእስራኤል፡ዅሉ፡እንዲህ፡ብለው፡ተናገሩ።እስራኤል፡ሆይ፥ዝም፡ብላችኹ፡አድ ምጡ፤ዛሬ፡የአምላክኽ፡የእግዚአብሔር፡ሕዝብ፡ኾነኻል።
10፤ለአምላክኽም፡ለእግዚአብሔር፡ቃል፡ታዘዝ፥ዛሬም፡የማዝ፟ኽን፡ትእዛዙንና፡ሥርዐቱን፡አድርግ።
11፤ሙሴም፡በዚያን፡ቀን፡እንዲህ፡ብሎ፡ሕዝቡን፡አዘዘ።
12፤ዮርዳኖስን፡በተሻገራችኹ፡ጊዜ፡ሕዝቡን፡ይባርኩ፡ዘንድ፡እነዚህ፥ስምዖንና፡ሌዊ፡ይሁዳና፡ይሳኮር፡ዮ ሴፍና፡ብንያም፥በገሪዛን፡ተራራ፡ላይ፡ይቁሙ።
13፤ይረግሙም፡ዘንድ፡እነዚህ፥ሮቤልና፡ጋድ፡አሴርና፡ዛብሎን፡ዳንና፡ንፍታሌም፥በጌባል፡ተራራ፡ላይ፡ይቁ ሙ።
14፤ሌዋውያንም፡ከፍ፡ባለች፡ድምፅ፡ለእስራኤል፡ሰዎች፡ዅሉ፡እንዲህ፡ብለው፡ይናገራሉ።
15፤በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡የተጠላ፡የሠራተኛ፡እጅ፡ሥራን፡የተቀረጸ፡ወይም፡ቀልጦ፡የተሠራ፡ምስልን፡የሚ ያደርግ፥በስውርም፡የሚያቆመው፡ሰው፡ርጉም፡ይኹን፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡መልሰው፡አሜን፡ይላሉ።
16፤አባቱን፡ወይም፡እናቱን፡የሚያቃልል፡ርጉም፡ይኹን፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡አሜን፡ይላሉ።
17፤የባልንጀራውን፡የድንበር፡ምልክት፡የሚገፋ፡ርጉም፡ይኹን፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡አሜን፡ይላሉ።
18፤ዕውሩን፡ከመንገድ፡ፈቀቅ፡የሚያደርግ፡ርጉም፡ይኹን፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡አሜን፡ይላሉ።
19፤በመጻተኛ፡በድኻ፡አደጉም፡በመበለቲቱም፡ላይ፡ፍርድን፡የሚያጣምም፡ርጉም፡ይኹን፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡አሜን ፡ይላሉ።
20፤ከአባቱ፡ሚስት፡ጋራ፡የሚተኛ፡የአባቱን፡ልብስ፡ገልጧልና፥ርጉም፡ይኹን፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡አሜን፡ይላሉ።
21፤ከማናቸዪቱም፡እንስሳ፡ጋራ፡የሚተኛ፡ርጉም፡ይኹን፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡አሜን፡ይላሉ።
22፤ከአባቱ፡ወይም፡ከእናቱ፡ልጅ፡ከእኅቱ፡ጋራ፡የሚተኛ፡ርጉም፡ይኹን፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡አሜን፡ይላሉ።
23፤ከዐማቱ፡ጋራ፡የሚተኛ፡ርጉም፡ይኹን፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡አሜን፡ይላሉ።
24፤ባልንጀራውን፡በስውር፡የሚመታ፡ርጉም፡ይኹን፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡አሜን፡ይላሉ።
25፤የንጹሑን፡ሰው፡ነፍስ፡ለመግደል፡ጕቦ፡የሚቀበል፡ርጉም፡ይኹን፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡አሜን፡ይላሉ።
26፤የዚህን፡ሕግ፡ቃሎች፡ያደርግ፡ዘንድ፡የማያጸና፡ርጉም፡ይኹን፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡አሜን፡ይላሉ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡28።______________
ምዕራፍ፡28።
1፤እንዲህም፡ይኾናል፤የአምላክኽን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ብትሰማ፥ዛሬም፡ያዘዝኹኽን፡ትእዛዙን፡ዅሉ፡ብ ታደርግ፡ብትጠብቅም፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከምድር፡አሕዛብ፡ዅሉ፡ላይ፡ከፍ፡ከፍ፡ያደርግኻል።
2፤የአምላክኽንም፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ብትሰማ፡እነዚህ፡በረከቶች፡ዅሉ፡ይመጡልኻል፤ያገኙኽማል።
3፤አንተ፡በከተማ፡ቡሩክ፡ትኾናለኽ፥በዕርሻም፡ቡሩክ፡ትኾናለኽ።
4፤የሆድኽ፡ፍሬ፥የምድርኽም፡ፍሬ፥የከብትኽም፡ፍሬ፥የላምኽም፡ርቢ፥የበግኽም፡ርቢ፡ቡሩክ፡ይኾናል።
5፤እንቅብኽና፡ቡሓቃኽ፡ቡሩክ፡ይኾናል።
6፤አንተም፡በመግባትኽ፡ቡሩክ፡ትኾናለኽ፥በመውጣትኽም፡ቡሩክ፡ትኾናለኽ።
7፤እግዚአብሔርም፡በላይኽ፡የሚቆሙትን፡ጠላቶችኽን፡በፊትኽ፡የተመቱ፡ያደርጋቸዋል፤ባንድ፡መንገድ፡ይመጡ ብኻል፥በሰባትም፡መንገድ፡ከፊትኽ፡ይሸሻሉ።
8፤እግዚአብሔር፡በረከቱ፡ባንተ፡ላይ፡በጐተራኽ፡በእጅኽም፡ሥራ፡ዅሉ፡እንዲወርድ፡ያዛ፟ል፤አምላክኽ፡እግ ዚአብሔር፡በሚሰጥኽም፡ምድር፡ይባርክኻል።
9፤የአምላክኽን፡የእግዚአብሔርን፡ትእዛዝ፡ብትጠብቅ፥በመንገዱም፡ብትኼድ፥እግዚአብሔር፡እንደ፡ማለልኽ፡ ለርሱ፡የተቀደሰ፡ሕዝብ፡አድርጎ፡ያቆምኻል።
10፤የምድር፡አሕዛብም፡ዅሉ፡የእግዚአብሔር፡ስም፡ባንተ፡ላይ፡እንደ፡ተጠራ፡አይተው፡ይፈሩኻል።
11፤እግዚአብሔርም፡ርሷን፡ይሰጥኽ፡ዘንድ፡ለአባቶችኽ፡በማለላቸው፡በምድርኽ፡ላይ፥በሆድኽ፡ፍሬ፥በከብት ኽ፡ፍሬ፥በዕርሻኽም፡ፍሬ፥እግዚአብሔር፡በጎነቱን፡በላይኽ፡ያበዛል።
12፤እግዚአብሔርም፡ለምድርኽ፡በወራቱ፡ዝናብ፡ይሰጥ፡ዘንድ፥የእጅኽንም፡ሥራ፡ዅሉ፡ይባርክ፡ዘንድ፡መልካ ሙን፡መዝገብ፡ሰማዩን፡ይከፍትልኻል፤ለብዙ፡አሕዝብም፡ታበድራለኽ፥አንተ፡ግን፡ከማንም፡አትበደርም።
13፤14፤ዛሬም፡ያዘዝኹኽን፡የአምላክኽን፡የእግዚአብሔርን፡ትእዛዝ፡ሰምተኽ፡ብትጠብቃት፡ብታደርጋትም፥ዛ ሬም፡ካዘዝኹኽ፡ከነዚህ፡ቃሎች፡ወደ፡ቀኝ፡ወደ፡ግራም፡ፈቀቅ፡ባትል፥ታመልካቸውም፡ዘንድ፡ሌላዎችን፡አማል ክት፡ባትከተል፥እግዚአብሔር፡ራስ፡ያደርግኻል፡እንጂ፡ዥራት፡አያደርግኽም፤ዅልጊዜም፡በላይ፡እንጂ፡በታች ፡አትኾንም።
15፤ነገር፡ግን፥የአምላክኽን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ባትሰማ፥ዛሬም፡ያዘዝኹኽን፡ሥርዐቱንና፡ትእዛዙን፡ ዅሉ፡ባትጠብቅ፡ባታደርግም፥እነዚህ፡መርገሞች፡ዅሉ፡ይመጡብኻል፡ያገኙኽማል።
16፤በከተማ፡ርጉም፡ትኾናለኽ፥በዕርሻም፡ርጉም፡ትኾናለኽ።
17፤እንቅብኽና፡ቡሓቃኽ፡ርጉም፡ይኾናል።
18፤የሆድኽ፡ፍሬ፥የምድርኽም፡ፍሬ፥የላምኽም፡ርቢ፥የበግኽም፡ርቢ፡ርጉም፡ይኾናል።
19፤አንተ፡በመግባትኽ፡ርጉም፡ትኾናለኽ፥በመውጣትኽም፡ርጉም፡ትኾናለኽ።
20፤እኔን፡ስለ፡ተውኸኝ፥ስለሥራኽ፡ክፋት፥እስክትጠፋ፡ፈጥነኽም፡እስክታልቅ፡ድረስ፡በምትሠራው፡ሥራ፡ዅ ሉ፡እግዚአብሔር፡መርገምን፥ሽሽትን፥ተግሣጽን፡ይሰድ፟ብኻል።
21፤እግዚአብሔር፡ትወርሳት፡ዘንድ፡ከምትገባባት፡ምድር፡እስኪያጠፋኽ፡ድረስ፡ቸነፈርን፡ያጣብቅብኻል።
22፤እግዚአብሔር፡በክሳት፥በንዳድም፥በጥብሳትም፥በትኵሳትም፥በድርቅም፥በዋግም፥በዐረማሞም፡ይመታኻል፤ እስክትጠፋም፡ድረስ፡ያሳድዱኻል።
23፤በራስኽም፡ላይ፡ሰማይ፡ናስ፡ይኾንብኻል፥ከእግርኽም፡በታች፡ምድሪቱ፡ብረት፡ትኾንብኻለች።
24፤እግዚአብሔር፡የምድርኽን፡ዝናብ፡ትቢያና፡ዐፈር፡ያደርጋል፤እስክትጠፋ፡ድረስ፡ከሰማይ፡ይወርድብኻል ።
25፤እግዚአብሔር፡ከጠላቶችኽ፡ፊት፡የተመታኽ፡ያደርግኻል፤ባንድ፡መንገድ፡ትወጣባቸዋለኽ፥በሰባት፡መንገ ድ፡ከነርሱ፡ትሸሻለኽ፤ለምድርም፡መንግሥታት፡ዅሉ፡ድንጋጤ፡ትኾናለኽ።
26፤ሬሳኽ፡ለሰማይ፡ወፎች፡ዅሉ፡ለምድርም፡አራዊት፡መብል፡ይኾናል፥የሚያስፈራቸውም፡የለም።
27፤እግዚአብሔር፡ፈውስ፡በሌለው፡በግብጽ፡ቍስል፡በዕባጭም፡በቋቍቻም፡በችፌም፡ይመታኻል።
28፤እግዚአብሔር፡በእብደት፥በዕውርነት፥በድንጋጤም፡ይመታኻል።
29፤በቀትርም፡ጊዜ፡ዕውር፡በጨለማ፡እንደሚርመሰመስ፡ትርመሰመሳለኽ፥መንገድኽም፡የቀና፡አይኾንም፤በዘመ ንኽም፡ዅሉ፡የተጨነቅኽ፡የተዘረፍኽም፡ትኾናለኽ፥የሚያድንኽም፡የለም።
30፤ሚስት፡ታጫለኽ፥ሌላም፡ሰው፡ከርሷ፡ጋራ፡ይተኛል፤ቤት፡ትሠራለኽ፥አትቀመጥበትም፤ወይን፡ትተክላለኽ፥ ከርሱም፡አትበላም።
31፤በሬኽ፡በፊትኽ፡ይታረዳል፥ከርሱም፡አትበላም፤አህያኽ፡ከእጅኽ፡በግድ፡ይወሰዳል፥ወዳንተም፡አይመለስ ም፤በግኽ፡ለጠላቶችኽ፡ትሰጣለች፥የሚያድንኽም፡አታገኝም።
32፤ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆችኽ፡ለሌላ፡ሕዝብ፡ይሰጣሉ፥ዐይኖችኽም፡ያያሉ፥ዅልጊዜም፡ስለ፡እነርሱ፡ሲባክኑ ፡ያልቃሉ፤በእጅኽም፡ኀይል፡ምንም፡አይገኝም።
33፤የምድርኽን፡ፍሬ፡ድካምኽንም፡ዅሉ፡የማታውቀው፡ሕዝብ፡ይበላዋል፤አንተም፡ዅል፡ጊዜ፡የተጨነቅኽ፡የተ ገፋኽም፡ትኾናለኽ።
34፤ዐይኖችኽም፡ከሚያዩት፡የተነሣ፡እብድ፡ትኾናለኽ።
35፤እግዚአብሔር፡ፈውስ፡በሌለው፡በክፉ፡ቍስል፡ጕልበትኽንና፡ጭንኽን፡ከእግርኽ፡ጫማ፡እስከ፡ዐናትኽ፡ድ ረስ፡ይመታኻል።
36፤እግዚአብሔርም፡አንተን፡ባንተም፡ላይ፡የምታነግሠውን፡ንጉሥ፡አንተና፡አባቶችኽ፡ወዳላወቃችዃቸው፡ሕ ዝብ፡ይወስድኻል፤በዚያም፡ሌላዎችን፡የዕንጨትና፡የድንጋይ፡አማልክት፡ታመልካለኽ።
37፤እግዚአብሔርም፡በሚያገባኽ፡በአሕዛብ፡መካከል፡ዅሉ፡ድንጋጤ፡ምሳሌም፡ተረትም፡ትኾናለኽ።
38፤እጅግ፡ዘር፡ወደ፡ዕርሻ፡ታወጣለኽ፤አንበጣም፡ይበላዋልና፥ጥቂት፡ትሰበስባለኽ።
39፤ወይን፡ትተክላለኽ፡ታበጀውማለኽ፤ትልም፡ይበላዋልና፥ከርሱ፡ምንም፡አትሰበስብም፥የወይን፡ጠጁንም፡አ ትጠጣም።
40፤የወይራ፡ዛፍ፡በአገርኽ፡ዅሉ፡ይኾንልኻል፤ወይራኽም፡ይረግፋልና፥ዘይቱን፡አትቀባም።
41፤ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆች፡ይወለዱልኻል፤በምርኮም፡ይኼዳሉና፡ለአንተ፡አይኾኑልኽም።
42፤ዛፍኽን፡ዅሉ፡የምድርኽንም፡ፍሬ፡ኵብኵባ፡ይወርሰዋል።
43፤ባንተ፡መካከል፡ያለ፡መጻተኛ፡ባንተ፡ላይ፡ከፍ፡ከፍ፡ይላል፥አንተም፡ዝቅ፡ዝቅ፡ትላለኽ።
44፤ርሱ፡ያበድርኻል፥አንተ፡ግን፡አታበድረውም፤ርሱ፡ራስ፡ይኾናል፥አንተም፡ዥራት፡ትኾናለኽ።
45፤የአምላክኽንም፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ስላልሰማኽ፥ያዘዘኽንም፡ትእዛዙንና፡ሥርዐቱን፡ስላልጠበቅኽ፥ እስክትጠፋ፡ድረስ፡እነዚህ፡መርገሞች፡ዅሉ፡ይወርዱብኻል፥ያሳድዱኽማል፥ያገኙኽማል።
46፤ባንተም፡በልጅ፡ልጅኽም፡ላይ፡ለዘለዓለም፡ለምልክትና፡ለድንቅ፡ይኾናሉ።
47፤ዅሉን፡አብዝቶ፡ስለ፡ሰጠኽ፡አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡በፍሥሓና፡በሐሤት፡አላመለክኽምና፡
48፤በራብና፡በጥማት፡በዕራቍትነትም፡ዅሉንም፡በማጣት፡እግዚአብሔር፡ለሚልክብኽ፡ለጠላቶችኽ፡ትገዛለኽ፤ እስኪያጠፋኽም፡ድረስ፡በዐንገትኽ፡ላይ፡የብረት፡ቀንበር፡ይጭናል።
49፤50፤እግዚአብሔር፡ቋንቋቸውን፡የማታውቀውን፥ፊታቸው፡የደነደነውን፥ሽማግሌውንም፡የማያፍሩትን፥ሕፃኑ ንም፡የማይምሩትን፡ሕዝብ፡ንስር፡እንደሚበር፟፡ከሩቅ፡አገር፡ከምድር፡ዳር፡ያመጣብኻል።
51፤እስክትጠፋ፡ድረስ፡የከብትኽን፡ፍሬ፡የምድርኽንም፡ፍሬ፡ይበላሉ፤እስኪያጠፉኽም፡ድረስ፡እኽልን፡የወ ይንም፡ጠጅ፡ዘይትንም፡የላምኽንና፡የበግኽን፡ርቢ፡አይተዉልኽም።
52፤በአገርኽ፡ዅሉ፡ያሉ፥ትታመንባቸው፡የነበሩ፥የረዘሙ፡የጸኑም፡ቅጥሮች፡እስኪፈርሱ፡ድረስ፥በከተማዎች ኽ፡ደጆች፡ዅሉ፡ከበ፟ው፡ያስጭንቁኻል፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡በሰጠኽ፡ምድር፡ዅሉ፡በደጆች፡ዅሉ፡ከበ፟ ው፡ያስጨንቁኻል።
53፤ጠላቶችኽም፡ከበ፟ው፡ባስጨነቁኽና፡መከራ፡ባሳዩኽ፡ጊዜ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡የሚሰጥኽን፡የሆድኽ ን፡ፍሬ፡የወንዶችና፡የሴቶች፡ልጆችኽን፡ሥጋ፡ትበላለኽ።
54፤ባንተ፡ዘንድ፡የተለሳለሰና፡በቅምጥልነት፡ዅል፡ጊዜ፡ይኖር፡የነበረ፡ሰው፡በወንድሙ፥ዐቅፋውም፡በምት ተኛ፡በሚስቱ፥በቀሩትም፡ልጆች፡ይቀናል፤
55፤በደጆችኽ፡ዅሉ፡ውስጥ፡ጠላቶችኽ፡ከበ፟ው፡ባስጨነቁኽና፡መከራ፡ባሳዩኽ፡ጊዜ፡ሌላ፡ነገር፡የቀረው፡የ ለምና፡ከሚበላው፡ከልጆቹ፡ሥጋ፡ለአንዱ፡አይሰጥም።
56፤ባንተ፡ዘንድ፡ያለችው፡የተለሳለሰችና፡በቅምጥልነት፡ዅል፡ጊዜ፡ትኖር፡የነበረችው፥ከልስላሴና፡ከቅም ጥልነት፡የተነሣ፡የእግር፡ጫማዋን፡በምድር፡ላይ፡ያላደረገችው፡ሴት፥ዐቅፋ፡በተኛችው፡ባሏ፥
57፤በወንድና፡በሴት፡ልጇም፥በእግሯ፡መካከል፡በሚወጣው፡በእንግዴ፡ልጅ፥በምትወልዳቸውም፡ልጆች፡ትቀናለ ች፤በደጆችኽም፡ውስጥ፡ጠላቶችኽ፡ከበ፟ው፡ባስጨነቁኽና፡መከራ፡ባሳዩኽ፡ጊዜ፡ዅሉን፡ስላጣች፡በስውር፡ትበ ላቸዋለች።
58፤በዚህ፡መጽሐፍ፡የተጻፉትን፡የዚህን፡ሕግ፡ቃሎች፡ዅሉ፡ታደርግ፡ዘንድ፡ባትጠብቅ፥ይህንንም፡‟አምላክ ኽ፡እግዚአብሔር”፡የተባለውን፡የተመሰገነውንና፡የተፈራውን፡ስም፡ባትፈራ፥
59፤እግዚአብሔር፡መቅሠፍትኽን፥የዘርኽንም፡መቅሠፍት፥ብዙ፡ዘመንም፡የሚኖረውን፡ታላቅ፡መቅሠፍት፥ብዙ፡ ዘመን፡የሚኖረውንም፡ክፉ፡ደዌ፡ያደርግብኻል።
60፤የፈራኸውንም፡የግብጽ፡ደዌ፡ዅሉ፡እንደ፡ገና፡ያመጣብኻል፥ይጣበቅብኽማል።
61፤ደግሞም፡ይህ፡ሕግ፡ባለበት፡መጽሐፍ፡ውስጥ፡ያልተጻፈውን፡ደዌ፡ዅሉ፡መቅሠፍትም፡ዅሉ፡እስክትጠፋ፡ድ ረስ፡እግዚአብሔር፡ያመጣብኻል።
62፤የአምላካችኹን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡አልሰማችኹምና፡ከብዛታችኹ፡የተነሣ፡እንደሰማይ፡ከዋክብት፡የ ነበረው፡ቍጥራችኹ፡ጥቂት፡ኾኖ፡ይቀራል።
63፤እግዚአብሔርም፡በጎ፡ያደርግላችኹ፡ዘንድ፡ያበዛችኹም፡ዘንድ፡ደስ፡ይለው፡እንደ፡ነበረ፥እንዲሁ፡እግ ዚአብሔር፡ሲያጠፋችኹ፡ሲያፈርሳችኹም፡ደስ፡ይለዋል፤ትወርሷትም፡ዘንድ፡ከምትገቡባት፡ምድር፡ትነቀላላችኹ ።
64፤እግዚአብሔርም፡ከምድር፡ዳር፡እስከ፡ዳርቻዋ፡ድረስ፡ወዳሉ፡አሕዛብ፡ዅሉ፡ይበትንኻል፤በዚያም፡አንተ ና፡አባቶችኽ፡ያላወቃችዃቸውን፡ሌላዎችን፡አማልክት፥ዕንጨትንና፡ድንጋይን፥ታመልካለኽ።
65፤በእነዚያም፡አሕዛብ፡መካከል፡ዕረፍት፡አታገኝም፥ለእግርኽም፡ጫማ፡ማረፊያ፡አይኾንም፤በዚያም፡እግዚ አብሔር፡ተንቀጥቃጭ፡ልብ፥ፈዛዛ፡ዐይን፥ደካማም፡ነፍስ፡ያመጣብኻል።
66፤ነፍስኽም፡ታመነታለች፤ሌሊትና፡ቀንም፡ትፈራለኽ፥በሕይወትኽም፡አትታመንም፤
67፤አንተ፡ስለፈራኽበት፡ስለልብኽ፡ፍርሀት፥በዐይንኽም፡ስለምታየው፡አስተያየት፥ማለዳ፦መቼ፡ይመሻል፧ት ላለኽ፤ማታም፦መቼ፡ይነጋል፧ትላለኽ።
68፤ከእንግዲህ፡ወዲህ፡ተመልሰኽ፡አታያትም፡ባልኹኽ፡መንገድም፡እግዚአብሔር፡በመርከብ፡ወደ፡ግብጽ፡ይመ ልስኻል፤በዚያም፡ወንዶችና፡ሴቶች፡ባሪያዎች፡ትኾኗቸው፡ዘንድ፡ለጠላቶቻችኹ፡ራሳችኹን፡ትሸጣላችኹ፤የሚገ ዛችኹም፡አይገኝም።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡29።______________
ምዕራፍ፡29።
1፤እግዚአብሔር፡በኰሬብ፡ካደረገው፡ቃል፡ኪዳን፡ሌላ፡በሞዐብ፡ምድር፡ከእስራኤል፡ልጆች፡ጋራ፡ያደርገው፡ ዘንድ፡ሙሴን፡ያዘዘው፡የቃል፡ኪዳኑ፡ቃሎች፡እነዚህ፡ናቸው።
2፤ሙሴም፡የእስራኤልን፡ልጆች፡ዅሉ፡ጠርቶ፡አላቸው፦እግዚአብሔር፡በፊታችኹ፡በግብጽ፡ምድር፡በፈርዖንና፡ በባሪያዎቹ፡ዅሉ፡በምድሩም፡ዅሉ፡ያደረገውን፡ዅሉ፥
3፤ዐይኖቻችኹ፡ያይዋቸውን፡ታላላቆች፡ፈተናዎች፥ታላላቆች፡ተኣምራትና፡ድንቆች፥አይታችዃል፤
4፤እግዚአብሔር፡ግን፡አስተዋይ፡ልብ፥የሚያዩ፡ዐይኖች፥የሚሰሙም፡ዦሮዎች፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡አልሰጣችኹ ም።
5፤አርባ፡ዓመት፡በምድረ፡በዳ፡መራዃችኹ፤ልብሳችኹም፡አላረጀባችኹም፥ጫማችኹም፡በእግራችኹ፡ላይ፡አላረጀ ም።
6፤እኔ፡አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ኾንኹ፡ታውቁ፡ዘንድ፡እንጀራ፡አልበላችኹም፥የወይን፡ጠጅና፡የሚ ያሰክረውን፡መጠጥ፡አልጠጣችኹም።
7፤ወደዚህም፡ስፍራ፡በመጣችኹ፡ጊዜ፡የሐሴቦን፡ንጉሥ፡ሴዎን፡የባሳንም፡ንጉሥ፡ዐግ፡ሊወጉን፡ወጡብን፥እኛ ም፡መታናቸው፤
8፤ምድራቸውንም፡ወስደን፡ለሮቤልና፡ለጋድ፡ለምናሴም፡ነገድ፡እኩሌታ፡ርስት፡አድርገን፡ሰጠናቸው።
9፤ስለዚህ፥በምታደርጉት፡ዅሉ፡ትከናወኑ፡ዘንድ፡የዚህን፡ቃል፡ኪዳን፡ቃሎች፡ጠብቁ፡አድርጉም።
10፤11፤ዅላችኹ፥አለቃዎቻችኹም፡ነገዶቻችኹም፡ሽማግሌዎቻችኹም፡ሹማምቶቻችኹም፥የእስራኤል፡ሰዎች፡ዅሉ፡ ልጆቻችኹም፡ሴቶቻችኹም፡በሰፈራችኹም፡ያለ፡ዕንጨትኽን፡የሚቈርጥ፡ውሃኽንም፡የሚቀዳ፡መጻተኛ፥ዛሬ፡በአም ላካችኹ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ቆማችዃል፤
12፤13፤ይኸውም፡ዛሬ፡ለርሱ፡ሕዝብ፡አድርጎ፡ያስነሣኽ፡ዘንድ፥ርሱም፡ለአንተ፡እንደ፡ተናገረ፡ለአባቶችኽ ም፡ለአብርሃምና፡ለይሥሐቅ፡ለያዕቆብም፡እንደ፡ማለ፡አምላክ፡ይኾንልኽ፡ዘንድ፥አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከ አንተ፡ጋራ፡ዛሬ፡በሚያደርገው፡ቃል፡ኪዳን፡ትገባ፡ዘንድና፡የአምላክኽን፡የእግዚአብሔርን፡መሐላ፡ትሰማ፡ ዘንድ፡ነው።
14፤እኔም፡ይህን፡ቃል፡ኪዳንና፡ይህን፡መሐላ፡የማደርገው፡ከእናንተ፡ጋራ፡ብቻ፡አይደለም፤
15፤ነገር፡ግን፥ዛሬ፡በአምላካችን፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ከእኛ፡ጋራ፡በዚህ፡ከሚቆም፡ሰው፡ጋራ፥ዛሬም፡ከ እኛ፡ጋራ፡በዚህ፡ከሌለ፡ሰው፡ጋራ፡ነው፡እንጂ፤
16፤ነገር፡ግን፥እኛ፡በግብጽ፡ምድር፡እንደ፡ተቀመጥን፡በመካከላቸውም፡ባለፋችኹባቸው፡አሕዛብ፡መካከል፡ እንዳለፍን፡ዐውቃችዃልና፥
17፤ርኩስነታቸውንም፡በእነርሱም፡ዘንድ፡የነበሩትን፡የዕንጨትና፡የድንጋይ፡የብርና፡የወርቅም፡ጣዖቶቻቸ ውን፡አይታችዃልና፥
18፤ኼዶ፡የእነዚያን፡አሕዛብ፡አማልክት፡ያመልክ፡ዘንድ፡ከአምላኩ፡ከእግዚአብሔር፡ልቡን፡ዛሬ፡የሚያስት ፡ወንድ፡ወይም፡ሴት፡ወይም፡ወገን፡ወይም፡ነገድ፡አይኑርባችኹ፤ሐሞትና፡ሬትም፡የሚያበቅል፡ሥር፡አይኹንባ ችኹ።
19፤የዚህንም፡ርግማን፡ቃሎች፡የሰማ፡ሰው፦ምንም፡እንኳ፡በልቤ፡ደንዳናነት፡ብኼድ፥ለጥማቴም፡ስካር፡ብጨ ምር፥ሰላም፡ይኾንልኛል፡ብሎ፡ሰውነቱን፡በልቡ፡የሚባርክ፡ቢኖር፥
20፤የእግዚአብሔር፡ቍጣ፡ቅንአቱም፡በዚያ፡ሰው፡ላይ፡ይጤሳል፡እንጂ፡እግዚአብሔር፡ይቅርታ፡አያደርግለት ም፤በዚህም፡መጽሐፍ፡የተጻፈው፡ርግማን፡ዅሉ፡በላዩ፡ይኖራል፥እግዚአብሔርም፡ስሙን፡ከሰማይ፡በታች፡ይደመ ስሰዋል።
21፤እግዚአብሔርም፡በዚህ፡ሕግ፡መጽሐፍ፡እንደተጻፈው፡እንደ፡ቃል፡ኪዳኑ፡ርግማን፡ዅሉ፡ከእስራኤል፡ነገ ዶች፡ዅሉ፡ለጥፋት፡ይለየዋል።
22፤ከዚያም፡በዃላ፡የሚነሣ፡ትውልድ፡ከእናንተም፡በዃላ፡የሚኾኑ፡ልጆቻችኹ፡ከሩቅ፡አገርም፡የሚመጣ፡እን ግዳ፥የዚህን፡አገር፡መቅሠፍት፥እግዚአብሔርም፡በርሷ፡ያደረገውን፡ሥቃይዋን፥
23፤ምድርም፡በዅለንተናዋ፡ዲንና፡ጨው፡መቃጠልም፡እንደ፡ኾነባት፥እንዳትዘራም፡እንዳታበቅልም፥ማናቸውም ፡ሣርና፡ልምላሜም፡እንዳይወጣባት፥እግዚአብሔር፡በቍጣውና፡በመዓቱ፡እንደ፡ገለባበጣቸው፡እንደ፡ሰዶምና፡ ገሞራ፡እንደ፡አዳማና፡እንደ፡ሲባዮ፡እንደ፡ኾነች፡ባዩ፡ጊዜ፥
24፤አሕዛብ፡ዅሉ፦እግዚአብሔር፡በዚች፡ምድር፡ስለ፡ምን፡እንደዚህ፡አደረገ፧ይህስ፡የቍጣው፡ታላቅ፡መቅሠ ፍት፡ምንድር፡ነው፧ይላሉ።
25፤ሰዎችም፡እንዲህ፡ይላሉ፦የአባቶቻቸው፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡ከግብጽ፡ምድር፡ባወጣቸው፡ጊዜ፡ከነርሱ ፡ጋራ፡ያደረገውን፡ቃል፡ኪዳን፡ስለ፡ተዉ፥
26፤ኼደውም፡የማያውቋቸውንና፡ያልታዘዙትን፡ሌላዎችን፡አማልክት፡ስላመለኩና፡ስለ፡ሰገዱላቸው፥
27፤ስለዚህ፥በዚህ፡መጽሐፍ፡የተጻፈውን፡መርገም፡ዅሉ፡ያወርድባት፡ዘንድ፡የእግዚአብሔር፡ቍጣ፡በዚች፡ም ድር፡ነደደ፤
28፤ዛሬም፡እንዳሉ፡እግዚአብሔር፡በቍጣና፡በመቅሠፍት፡በታላቅም፡መዓት፡ከምድራቸው፡ነቀላቸው፥ወደ፡ሌላ ም፡ምድር፡ጣላቸው።
29፤ምስጢሩ፡ለአምላካችን፡ለእግዚአብሔር፡ነው፤የተገለጠው፡ግን፡የዚህን፡ሕግ፡ቃሎች፡ዅሉ፡እናደርግ፡ዘ ንድ፡ለእኛ፡ለዘለዓለምም፡ለልጆቻችን፡ነው።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡30።______________
ምዕራፍ፡30።
1፤እንዲህም፡ይኾናል፤እኔ፡በፊትኽ፡ያኖርኹት፡ይህ፡ነገር፡ዅሉ፥በረከቱና፡መርገሙ፥በወረደብኽ፡ጊዜ፥አም ላክኽም፡እግዚአብሔር፡በሚበትንኽ፡በአሕዛብ፡ዅሉ፡መካከል፡ኾነኽ፡በልብኽ፡ባሰብኸው፡ጊዜ፥
2፤ወደ፡አምላክኽም፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ተመልሰኽ፡እኔ፡ዛሬ፡እንደማዝ፟ኽ፡ዅሉ፡አንተና፡ልጆችኽ፡በፍጹም ፡ልብና፡በፍጹም፡ነፍስ፡ለቃሉ፡በታዘዝኽ፡ጊዜ፥
3፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ምርኮኽን፡ይመልሳል፡ይራራልኽማል፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡አንተን፡ከበተነ በት፡ከአሕዛብ፡ዅሉ፡መካከል፡መልሶ፡ይሰበስብኻል።
4፤ሰዎችኽም፡እስከሰማይ፡ዳርቻ፡ድረስ፡ፈልሰው፡እንደ፡ኾነ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ከዚያ፡ይሰበስብኻል ፥ከዚያም፡ያመጣኻል።
5፤አባቶችኽም፡ወደወረሷት፡ምድር፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ያጋባኻል፥ትወርሳትማለኽ፤መልካምም፡ያደርግል ኻል፥ከአባቶችኽም፡ይልቅ፡ያበዛኻል።
6፤በሕይወትም፡እንድትኖር፥አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡በፍጹም፡ልብኽ፡በፍጹምም፡ነፍስኽ፡እንድትወድ፟፡ አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ልብኽን፡የዘርኽንም፡ልብ፡ይገርዛል።
7፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ይህችን፡መርገም፡ዅሉ፡በጠላቶችኽና፡በሚጠሉኽ፡በሚያሳድዱኽም፡ላይ፡ያመጣታ ል።
8፤አንተም፡ተመልሰኽ፡የአምላክኽን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ትሰማለኽ፥ዛሬም፡እኔ፡የማዝ፟ኽን፡ትእዛዙን፡ ዅሉ፡ታደርጋለኽ።
9፤10፤የአምላክኽንም፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ብትሰማ፥በዚህም፡ሕግ፡መጽሐፍ፡የተጻፉትን፡ትእዛዙንና፡ሥር ዐቱን፡ብትጠብቅ፥በፍጹምም፡ልብኽ፡በፍጹምም፡ነፍስኽ፡ወደ፡አምላክኽ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ብትመለስ፥እግዚ አብሔር፡በአባቶችኽ፡ደስ፡እንዳለው፡በመልካሙ፡ነገር፡ዅሉ፡እንደ፡ገና፡ባንተ፡ደስ፡ይለዋልና፥አምላክኽ፡ እግዚአብሔር፡በእጅኽ፡ሥራ፡ዅሉ፡በሆድኽም፡ፍሬ፡በከብትኽም፡ፍሬ፡በዕርሻኽም፡ፍሬ፡እጅግ፡ይባርክኻል።
11፤እኔ፡ዛሬ፡የማዝ፟ኽ፡ይህች፡ትእዛዝ፡ከባድ፡አይደለችም፥ከአንተም፡የራቀች፡አይደለችም።
12፤ሰምተን፡እናደርጋት፡ዘንድ፡ስለ፡እኛ፡ወደ፡ሰማይ፡ወጥቶ፡ርሷን፡የሚያመጣልን፡ማን፡ነው፧እንዳትል፡ በሰማይ፡አይደለችም።
13፤ሰምተን፡እናደርጋት፡ዘንድ፡ስለ፡እኛ፡ባሕሩን፡ተሻግሮ፡ርሷን፡የሚያመጣልን፡ማን፡ነው፧እንዳትል፡ከ ባሕሩ፡ማዶ፡አይደለችም።
14፤ነገር፡ግን፥ታደርገው፡ዘንድ፡ቃሉ፡በአፍኽና፡በልብኽ፡ውስጥ፡ለአንተ፡እጅግ፡ቅርብ፡ነው።
15፤ተመልከት፤ዛሬ፡በፊትኽ፡ሕይወትንና፡መልካምነትን፥ሞትንና፡ክፋትን፡አኑሬያለኹ።
16፤በሕይወትም፡እንድትኖር፡እንድትባዛም፥አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ልትወርሳት፡በምትገባባት፡ምድር፡እ ንዲባርክኽ፥አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡ትወድ፟፡ዘንድ፥በመንገዱም፡ትኼድ፡ዘንድ፡ትእዛዙንና፡ሥርዐቱን፡ ፍርዱንም፡ትጠብቅ፡ዘንድ፡ዛሬ፡እኔ፡አዝ፟ኻለኹ።
17፤ልብኽ፡ግን፡ቢስት፡አንተም፡ባትሰማ፥ብትታለልም፥ለሌላዎችም፡አማልክት፡ብትሰግድ፡ብታመልካቸውም፥
18፤ፈጽማችኹ፡እንድትጠፉ፡እኔ፡ዛሬ፡እነግራችዃለኹ፤ዮርዳኖስን፡ተሻግረኽ፡ትወርሳት፡ዘንድ፡በምትገባባ ት፡ምድር፡ዘመናችኹን፡አታስረዝሙም።
19፤በፊታችኹ፡ሕይወትንና፡ሞትን፡በረከትንና፡መርገምን፡እንዳስቀመጥኹ፡እኔ፡ዛሬ፡ሰማይንና፡ምድርን፡ባ ንተ፡ላይ፡አስመሰክራለኹ፤እንግዲህ፡አንተና፡ዘርኽ፡በሕይወት፡ትኖሩ፡ዘንድ፡ሕይወትን፡ምረጥ፤
20፤እግዚአብሔርም፡ለአባቶችኽ፡ለአብርሃምና፡ለይሥሐቅ፡ለያዕቆብም፡እንዲሰጣቸው፡በማለላቸው፡በምድሪቱ ፡ትቀመጥ፡ዘንድ፥ርሱ፡ሕይወትኽ፡የዘመንኽም፡ርዝመት፡ነውና፥አምላክኽን፡እግዚአብሔርን፡ትወደ፟ው፡ትጠባ በቀውም፡ቃሉንም፡ትሰማ፡ዘንድ፡ምረጥ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡31።______________
ምዕራፍ፡31።
1፤ሙሴም፡ኼዶ፡ይህንን፡ቃል፡ለእስራኤል፡ዅሉ፡ነገረ።
2፤አላቸውም፦እኔ፡ዛሬ፡መቶ፡ኻያ፡ዓመት፡ኾኖኛል፤ከዚህ፡በዃላ፡እወጣና፡እገባ፡ዘንድ፡አልችልም፤እግዚአ ብሔርም፦ይህን፡ዮርዳኖስን፡አትሻገርም፡ብሎኛል።
3፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ርሱ፡በፊትኽ፡ያልፋል፤ርሱ፡እነዚህን፡አሕዛብ፡ከፊትኽ፡ያጠፋቸዋል፡ትወርሳቸ ውማለኽ፤እግዚአብሔርም፡እንደ፡ተናገረ፡ኢያሱ፡በፊትኽ፡ይሻገራል።
4፤እግዚአብሔርም፡ባጠፋቸው፡በአሞራውያን፡ነገሥታት፡በሴዎንና፡በዐግ፡በምድራቸውም፡እንዳደረገ፡ያደርግ ባቸዋል።
5፤እግዚአብሔርም፡በፊታችኹ፡አሳልፎ፡ይጥላቸዋል፥እንዳዘዝዃችኹም፡ትእዛዝ፡ዅሉ፡ታደርጉባቸዋላችኹ።
6፤ጽኑ፥አይዟችኹ፥አትፍሩ፥ከፊታቸውም፡አትደንግጡ፤አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ርሱ፡ከአንተ፡ጋራ፡ይኼዳል፤ አይጥልኽም፥አይተውኽም።
7፤ሙሴም፡ኢያሱን፡ጠርቶ፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ፊት፦አንተ፡ከዚህ፡ሕዝብ፡ጋራ፡እግዚአብሔር፡ለአባቶቻቸው፡እ ንዲሰጥ፡ወደማለላቸው፡ምድር፡ትገባለኽና፥ርሷንም፡ለእነርሱ፡ታወርሳለኽና፡ጽና፥አይዞኽ።
8፤በፊትኽም፡የሚኼድ፡ርሱ፡እግዚአብሔር፡ነው፤ከአንተ፡ጋራ፡ይኾናል፥አይጥልኽም፥አይተውኽም፤አትፍራ፥አ ትደንግጥ፡አለው።
9፤ሙሴም፡ይህችን፡ሕግ፡ጻፈ፥የእግዚአብሔርንም፡የቃል፡ኪዳኑን፡ታቦት፡ይሸከሙ፡ለነበሩት፡ለሌዊ፡ልጆች፡ ለካህናቱ፡ለእስራኤልም፡ሽማግሌዎች፡ዅሉ፡ሰጣት።
10፤ሙሴም፡እንዲህ፡ብሎ፡አዘዛቸው።በሰባተኛው፡ዓመት፡መጨረሻ፥በዕዳ፡ምሕረት፡ዘመን፥በዳስ፡በዓል፥
11፤እስራኤል፡ዅሉ፡በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ይታይ፡ዘንድ፡ርሱ፡በመረጠው፡ስፍራ፡ሲከማች፥ይህን ፡ሕግ፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ፊት፡በዦሮው፡አንበ፟ው።
12፤ይሰሙና፡ይማሩ፡ዘንድ፥አምላካችኹንም፡እግዚአብሔርን፡ይፈሩ፡ዘንድ፥የዚህንም፡ሕግ፡ቃሎች፡ዅሉ፡ጠብ ቀው፡ያደርጉ፡ዘንድ፡ሕዝቡን፡ወንዶችንና፡ሴቶችን፡ሕፃናትንም፡በአገራችኹ፡ደጅ፡ያለውንም፡መጻተኛ፡ሰብስ ብ።
13፤የሕግ፡ቃላት፡የማያውቁ፡ልጆቻቸውም፡ዮርዳኖስን፡ተሻግራችኹ፡ልትወርሷት፡በምትኼዱባት፡ምድር፡በምት ኖሩበት፡ዘመን፡ዅሉ፡ይስሙ፥አምላካችኹን፡እግዚአብሔርንም፡መፍራት፡ይማሩ።
14፤እግዚአብሔርም፡ሙሴን፦የምትሞትበት፡ቀን፥እንሆ፥ቀረበ፤ኢያሱን፡ጠርተኽ፡ርሱን፡አዘ፟ው፡ዘንድ፡በመ ገናኛው፡ድንኳን፡ውስጥ፡ከርሱ፡ጋራ፡ቁም፡አለው።ሙሴና፡ኢያሱም፡ኼደው፡በመገናኛው፡ድንኳን፡ውስጥ፡ቆሙ።
15፤እግዚአብሔርም፡በድንኳኑ፡ውስጥ፡በደመና፡ዐምድ፡ተገለጠ፤የደመናውም፡ዐምድ፡በድንኳኑ፡ደጃፍ፡ላይ፡ ቆመ።
16፤እግዚአብሔርም፡ሙሴን፡አለው፦እንሆ፥ከአባቶችኽ፡ጋራ፡ትተኛለኽ፤ይህም፡ሕዝብ፡ይነሣል፥ይቀመጥባትም ፡ዘንድ፡በሚኼድባት፡ምድር፡መካከል፡ያሉትን፡ሌላዎችን፡አማልክት፡ተከትሎ፡ያመነዝራል፥እኔንም፡ይተወኛል ፥ከነርሱም፡ጋራ፡ያደረግኹትን፡ቃል፡ኪዳን፡ያፈርሳሉ።
17፤በዚያም፡ቀን፡ቍጣዬ፡ይነድ፟ባቸዋል፥እተዋቸውማለኹ፥ፊቴንም፡እሰውርባቸዋለኹ፥ለአሕዛብ፡መብል፡ይኾ ናሉ፤በዚያም፡ቀን፦በእውነት፡እግዚአብሔር፡በእኛ፡መካከል፡የለምና፡ይህ፡ክፉ፡ነገር፡ዅሉ፡አገኘን፡እስኪ ሉ፡ድረስ፡ብዙ፡ክፉ፡ነገርና፡ጭንቀት፡ይደርስባቸዋል።
18፤ሌላዎችን፡አማልክት፡ተከትለዋልና፥ስላደረጉት፡ክፋት፡ዅሉ፡እኔ፡በዚያ፡ቀን፡ፈጽሜ፡ፊቴን፡እሰውራለ ኹ።
19፤አኹንም፡ይህችን፡መዝሙር፡ለእናንተ፡ጻፉ፥ለእስራኤልም፡ልጆች፡አስተምሯቸው፤ይህችም፡መዝሙር፡በእስ ራኤል፡ላይ፡ምስክር፡ትኾንልኝ፡ዘንድ፡በአፋቸው፡አድርጓት።
20፤ለአባቶቻቸው፡ወደማልኹላቸው፥ወተትና፡ማር፡ወደምታፈሰ፟ው፡ምድር፡ካገባዃቸው፡በዃላ፥ከበሉም፡ከጠገ ቡም፡ከደነደኑም፡በዃላ፥ሌላዎችን፡አማልክት፡ተከትለው፡ያመልካሉ፥እኔንም፡ይንቃሉ፥ቃል፡ኪዳኔንም፡ያፈር ሳሉ።
21፤ዛሬ፡ወደማልኹላቸው፡ምድር፡ገና፡ሳላገባቸው፡የሚያስቡትን፡ዐሳብ፡ዐውቃለኹና፥ከልጆቻቸውም፡አፍ፡አ ትረሳምና፡ብዙ፡ክፉ፡ነገርና፡ጭንቀት፡በደረሰባቸው፡ጊዜ፡ይህች፡መዝሙር፡ምስክር፡ኾና፡በፊታቸው፡ትመሰክ ራለች።
22፤ሙሴም፡በዚያ፡ቀን፡ይህችን፡መዝሙር፡ጻፈ፥ለእስራኤልም፡ልጆች፡አስተማራት።
23፤የነዌንም፡ልጅ፡ኢያሱን፦የእስራኤልን፡ልጆች፡ወደማልኹላቸው፡ምድር፡ታገባለኽና፡ጽና፥አይዞኽ፤እኔም ፡ከአንተ፡ጋራ፡እኾናለኹ፡ብሎ፡አዘዘው።
24፤እንዲህም፡ኾነ፤ሙሴ፡የዚህን፡ሕግ፡ቃሎች፡በመጽሐፍ፡ከጻፈ፡ከፈጸመም፡በዃላ፥
25፤ሙሴ፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡የሚሸከሙትን፡ሌዋውያንን፡እንዲህ፡ብሎ፡አዘዘ።
26፤ይህን፡የሕግ፡መጽሐፍ፡ውሰዱ፥በዚያም፡በእናንተ፡ላይ፡ምስክር፡እንዲኾን፡በአምላካችኹ፡በእግዚአብሔ ር፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡አጠገብ፡አኑሩት።
27፤እኔ፡ዐመፃችኹንና፡የዐንገታችኹን፡ድንዳኔ፡ዐውቃለኹና፤እኔም፡ዛሬ፡ከእናንተ፡ጋራ፡ገና፡በሕይወት፡ ሳለኹ፡እናንተ፡በእግዚአብሔር፡ላይ፡ዐምፃችዃል፤ይልቁንስ፡ከሞትኹ፡በዃላ፡እንዴት፡ይኾናል፧
28፤ይህን፡ቃል፡በዦሯቸው፡እናገር፡ዘንድ፥ሰማይንና፡ምድርንም፡አስመሰክርባቸው፡ዘንድ፡የነገዶቻችኹን፡ ሽማግሌዎች፡ዅሉ፡አለቃዎቻችኹንም፡ሰብስቡልኝ፤
29፤ከሞትኹ፡በዃላ፡ፈጽማችኹ፡እንድትረክሱ፥ካዘዝዃችኹም፡መንገድ፡ፈቀቅ፡እንድትሉ፡ዐውቃለኹና።በእጃች ኹም፡ሥራ፡ታስቈጡት፡ዘንድ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ክፉ፡ስላደረጋችኹ፡በዃለኛው፡ዘመን፡ክፉ፡ነገር፡ያገኛች ዃል።
30፤ሙሴም፡በእስራኤል፡ጉባኤ፡ዅሉ፡ዦሮ፡የዚች፡መዝሙር፡ቃሎች፡እስኪፈጸሙ፡ድረስ፡ተናገረ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡32።______________
ምዕራፍ፡32።
1፤ሰማያት፡ሆይ፥አድምጡ፥እኔም፡እናገራለኹ፤
ምድርም፡የአፌን፡ቃሎች፡ትስማ።
2፤ትምህርቴ፡እንደ፡ዝናብ፡ትፈሳ፟ለች፥
ነገሬ፡እንደ፡ጠል፡ትንጠባጠባለች፤
በልምላሜ፡ላይ፡እንደ፡ጤዛ፥
በሣርም፡ላይ፡እንደ፡ካፊያ።
3፤የእግዚአብሔርን፡ስም፡እጠራለኹና፤
ለአምላካችን፡ታላቅነትን፡ስጡ።
4፤ርሱ፡አምላክ፡ነው፤ሥራውም፡ፍጹም፡ነው፤
መንገዱም፡ዅሉ፡የቀና፡ነው፤
የታመነ፡አምላክ፥ክፋትም፡የሌለበት፥
ርሱ፡እውነተኛና፡ቅን፡ነው።
5፤እነርሱ፡ረከሱ፤ልጆቹም፡አይደሉም፤
ነውርም፡አለባቸው፤ጠማማና፡ገልበጥባጣ፡ትውልድ፡ናቸው።
6፤ደንቈሮ፡ብልኀተኛም፡ያልኾንኽ፡ሕዝብ፡ሆይ፥
ለእግዚአብሔር፡ይህንን፡ትመልሳለኽ፧
የገዛኽ፡አባትኽ፡አይደለምን፧
የፈጠረኽና፡ያጸናኽ፡ርሱ፡ነው።
7፤የዱሮውን፡ዘመን፡ዐስብ፥
የብዙ፡ትውልድንም፡ዓመታት፡አስተውል፤
አባትኽን፡ጠይቅ፥ያስታውቅኽማል፤
ሽማግሌዎችኽን፡ጠይቅ፥ይነግሩኽማል።
8፤ልዑል፡ለአሕዛብ፡ርስታቸውን፡ባወረሰ፡ጊዜ፥
የአዳምን፡ልጆች፡በለየ፡ጊዜ፥
እንደ፡እስራኤል፡ልጆች፡ቍጥር፡
የአሕዛብን፡ድንበር፡አቆመ።
9፤የእግዚአብሔር፡ዕድል፡ፈንታ፡ሕዝቡ፡ነው፤
ያዕቆብም፡የርስቱ፡ገመድ፡ነው።
10፤በምድረ፡በዳ፡በጥማት፥
የነፋስ፡ጩኸትም፡በሞላበት፡ውድማ፡አገኘው፤
ከበበው፡ተጠነቀቀለትም፤
እንደ፡ዐይን፡ብሌን፡ጠበቀው።
11፤ንስር፡ጫጩቶቹን፡እንደሚያወጣ፥
በእነርሱም፡ላይ፡እንደሚሰፍ፟፥
ክንፎቹን፡ዘርግቶ፡ወሰዳቸው፥
በክንፎቹም፡ዐዘላቸው።
12፤እግዚአብሔር፡ብቻውን፡መራው፤
ከርሱም፡ጋራ፡ሌላ፡አምላክ፡አልነበረም።
13፤በምድር፡ከፍታ፡ላይ፡አወጣው፤
የዕርሻውን፡ፍሬ፡በላ፤
ከአለትም፡ድንጋይ፡በሚገኝ፡ማር፥
ከጭንጫውም፡ድንጋይ፡በሚገኝ፡ዘይት፡አጠባው፤
14፤የላሙንም፡ቅቤ፥የመንጋውም፡ወተት፥
ከጠቦት፡ስብ፡ጋራ፥
የባሳንንም፡አውራ፡በግ፥ፍየሉንም፥
ከስንዴ፡እሸት፡ጋራ፡በላኽ፤
ከወይኑም፡ደም፡ያለውን፡ጠጅ፡ጠጣኽ።
15፤ይሹሩን፡ወፈረ፥ረገጠ፤
[ቍ.15፤በዕብራይስጥ፡'ይሹሩን'፡የሚለውን፡ግእዙ፡'ያዕቆብ'፡ይለዋል።]
ወፈረ፥ደነደነ፥ሰባ፤
የፈጠረውንም፡እግዚአብሔርን፡ተወ፤
የመድኀኒቱንም፡አምላክ፡ናቀ።
16፤በሌላዎች፡አማልክት፡አስቀኑት፥
በርኵሰታቸውም፡አስቈጡት።
17፤እግዚአብሔር፡ላልኾኑ፡አጋንንት፥
ለማያውቋቸውም፡አማልክት፥
በቅርብ፡ጊዜ፡ለተነሡ፡ለዐዲሶች፡
አባቶቻቸውም፡ላልፈሯቸው፡አማልክት፡ሠዉ።
18፤የወለደኽን፡አምላክ፡ተውኽ፥
ያሳደገኽን፡እግዚአብሔርን፡ረሳኽ።
19፤ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆችም፡ስላስቈጡት፡
እግዚአብሔር፡አይቶ፡ጣላቸው።
20፤ርሱም፡አለ፦ፊቴን፡እሰውርባቸዋለኹ፤
ፍጻሜያቸው፡ምን፡እንደ፡ኾነ፡አያለኹ፤
ጠማማ፡ትውልድ፥
ያልታመኑም፡ልጆች፡ናቸው።
21፤አምላክ፡ባልኾነው፡አስቀኑኝ፤
በምናምንቴዎቻቸውም፡አስቈጡኝ፤
እኔም፡ሕዝብ፡ባልኾነው፡አስቀናቸዋለኹ፤
በማያስተውል፡ሕዝብ፡አስቈጣቸዋለኹ።
22፤እሳት፡ከቍጣዬ፡ትነዳ፟ለችና፥
እስከ፡ሲኦል፡ድረስ፡ታቃጥላለች፥
ምድርንም፡ከፍሬዋ፡ጋራ፡ትበላለች፥
የተራራዎችን፡መሠረት፡ታነዳ፟ለች።
23፤መከራን፡እጨምርባቸዋለኹ፤
በፍላጻዎቼም፡እወጋቸዋለኹ።
24፤በራብ፡በንዳድ፡ይጠፋሉ፤
በንዳድና፡በመራራ፡ጥፋት፡ያልቃሉ፤
የአራዊትን፡ጥርስ፥
የምድርንም፡እባብ፡መርዝ፡እሰድ፟ባቸዋለኹ።
25፤ጕልማሳውን፡ከድንግል፥ሕፃኑንም፡ከሽማግሌ፡ጋራ፥
በሜዳ፡ሰይፍ፥በቤትም፡ውስጥ፡ድንጋጤ፡ያጠፋቸዋል።
26፤እበትናቸዋለኹ፡አልኹ፤
ከሰዎችም፡መካከል፡መታሰቢያቸውን፡አጠፋለኹ።
27፤ነገር፡ግን፥ጠላቶቻቸው፡እንዳይታበዩ።
እጃችን፡ከፍ፡ከፍ፡አለች፡እንጂ፡
እግዚአብሔር፡ይህን፡ዅሉ፡አላደረገም፡
እንዳይሉ፥
ስለጠላቱ፡ቍጣ፡ፈራኹ።
28፤ምክር፡ያጡ፡ሕዝብ፡ናቸው፥
ማስተዋልም፡የላቸውም።
29፤አእምሮ፡ቢኖራቸው፥
ይህንን፡ያስተውሉ፡ነበር፥
ፍጻሜያቸውንም፡ያስቡ፡ነበር።
30፤ርሱ፡አምላካቸው፡ካልሸጣቸው፥
እግዚአብሔርም፡አሳልፎ፡ካልሰጣቸው፥
አንድ፡ሰው፡እንዴት፡ሺሕን፡ያሳድድ፡ነበር፧
ኹለቱሳ፡እንዴት፡ዐሥሩን፡ሺሕ፡ያሸሹ፡ነበር፧
31፤አምላካችን፡እንደ፡አማልክታቸው፡አይደለም፤
ጠላቶቻችንም፡ሰነፎች፡ናቸው።
32፤ወይናቸው፡ከሰዶም፡ወይን፥
ከገሞራም፡ዕርሻ፡ነው፤
ፍሬያቸው፡ሐሞት፡ነው፤
ዘለላውም፡መራራ፡ነው።
33፤የወይን፡ጠጃቸው፡የእባብ፡መርዝ፥
የእፍኝትም፡ሥራይ፡ነው።
34፤ይህ፡በእኔ፡ዘንድ፡ተጠብቆ፡የለምን፧
በመዝገቤስ፡የታተመ፡አይደለምን፧
35፤የጥፋታቸው፡ቀን፡ቀርቧልና፥
የሚመጣባቸውም፡ነገር፡ይፈጥናልና፥
እግራቸው፡ሲሰናከል፡
በቀልና፡ፍርድ፡የእኔ፡ነው።
36፤ኀይላቸውም፡እንደ፡ደከመ፥
የተዘጋ፡የተለቀቀም፡እንደሌለ፡ባየ፡ጊዜ፡
እግዚአብሔር፡ለሕዝቡ፡ይፈርዳል፥
ስለ፡ባሪያዎቹም፡ያዝናል።
37፤ርሱም፡ይላል፦አማልክታቸው፡የት፡ናቸው፧
ይታመኑባቸው፡የነበሩት፡አማልክት፧
38፤የመሥዋዕታቸውን፡ስብ፡የበሉ፥
የመጠጥ፡ቍርባናቸውንም፡የወይን፡ጠጅ፡የጠጡ፧
እነርሱ፡ይነሡ፥ይርዷችኹም፥
መጠጊያም፡ይኹኑላችኹ።
39፤አኹንም፡እኔ፡ብቻዬን፡እኔ፡እንደ፡ኾንኹ፥
ከእኔም፡በቀር፡አምላክ፡እንደሌለ፡እዩ፤
እኔ፡እገድላለኹ፥አድንማለኹ፤
እኔ፡እመታለኹ፥እፈውስማለኹ፤
ከእጄም፡የሚያድን፡የለም።
40፤እጄን፡ወደ፡ሰማይ፡እዘረጋለኹና፥
እንዲህም፡እላለኹ፦ለዘለዓለም፡እኔ፡ሕያው፡ነኝና፡
41፤የሚንቦገቦግ፡ሰይፌን፡እስለዋለኹ፥
እጄም፡ፍርድን፡ትይዛለች፥
ጠላቶቼንም፡እበቀላለኹ፥
ለሚጠሉኝም፡ፍዳቸውን፡እከፍላለኹ።
42፤ከተወጉት፡ከተማረኩትም፡ደም፥
ፍላጻዎቼን፡በደም፡አሰክራለኹ፤
ከጠላት፡አለቃዎችም፡ራስ፡
ሰይፌ፡ሥጋ፡ይበላል።
43፤የባሪያዎቹን፡ደም፡ይበቀላልና፥
ጠላቶቹንም፡ይበቀላቸዋልና፥
ምድሪቱንና፡ሕዝቡን፡ይክሳልና፥
እናንተ፡አሕዛብ፡ሆይ፥ከሕዝቡ፡ጋራ፡ደስ፡ይበላችኹ።
44፤ሙሴም፡የነዌም፡ልጅ፡ኢያሱ፡የዚችን፡መዝሙር፡ቃሎች፡ዅሉ፡በሕዝቡ፡ዦሮ፡ተናገሩ።
45፤ሙሴም፡ይህን፡ቃል፡ዅሉ፡ለእስራኤል፡ዅሉ፡ተናግሮ፡ፈጸመ።
46፤ርሱም፡እንዲህ፡አላቸው፦የዚህን፡ሕግ፡ቃሎች፡ዅሉ፡ይጠብቁና፡ያደርጉ፡ዘንድ፡ልጆቻችኹን፡እንድታዙ፟ በት፡ዛሬ፡የምመሰክርላችኹን፡ቃል፡ዅሉ፡በልባችኹ፡አኑሩት።
47፤ይህ፡ነገር፡ሕይወታችኹ፡ነው፡እንጂ፡ለእናንተ፡ከንቱ፡አይደለምና፤በዚህም፡ነገር፡ትወርሷት፡ዘንድ፡ ዮርዳኖስን፡ተሻግራችኹ፡በምትገቡባት፡ምድር፡ረዥም፡ዘመን፡ትቀመጣላችኹ።
48፤በዚያም፡ቀን፡እግዚአብሔር፡ሙሴን፡እንዲህ፡ብሎ፡ተናገረው፦
49፤ወደዚህ፡በኢያሪኮ፡አንጻር፡በሞዐብ፡ምድር፡በዓባሪም፡ተራራ፡ውስጥ፡ወዳለው፡ወደናባው፡ተራራ፡ውጣ፥ ለእስራኤልም፡ልጆች፡ርስት፡አድርጌ፡የምሰጣቸውን፡የከነዓንን፡ምድር፡እይ፤
50፤ወንድምኽም፡አሮን፡በሖር፡ተራራ፡እንደ፡ሞተ፡ወደ፡ወገኖቹም፡እንደ፡ተከማቸ፥በወጣኽበት፡ተራራ፡ሙት ፥ወደ፡ወገኖችኽም፡ተከማች፤
51፤በእስራኤል፡ልጆች፡መካከል፡በጺን፡ምድረ፡በዳ፡በቃዴስ፡ባለው፡በመሪባ፡ውሃ፡ስለ፡በደላችኹኝ፥በእስ ራኤልም፡ልጆች፡መካከል፡ስላልቀደሳችኹኝ፥
52፤ምድሪቱን፡ፊት፡ለፊት፡ታያለኽ፡እንጂ፡ወደዚያች፡እኔ፡ለእስራኤል፡ልጆች፡ወደምሰጣቸው፡ምድር፡አትገ ባም።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡33።______________
ምዕራፍ፡33።
1፤የእግዚአብሔር፡ሰው፡ሙሴ፡ሳይሞት፡የእስራኤልን፡ልጆች፡የባረከባት፡በረከት፡ይህች፡ናት።
2፤እንዲህም፡አለ፦
እግዚአብሔር፡ከሲና፡መጣ፥
በሴይርም፡ተገለጠ፤
ከፋራን፡ተራራ፡አበራላቸው፥
ከአእላፋትም፡ቅዱሳኑ፡መጣ፤
በስተቀኙም፡የእሳት፡ሕግ፡ነበረላቸው።
3፤ሕዝቡንም፡ወደዳቸው፤
ቅዱሳኑ፡ዅሉ፡በእጅኽ፡ናቸው፤
በእግሮችኽም፡አጠገብ፡ተቀመጡ፤
ቃሎችኽን፡ይቀበላሉ።
4፤ሙሴ፡ለያዕቆብ፡ጉባኤ፡ርስት፡የኾነውን፡
ሕግ፡አዘዘን።
5፤የሕዝቡ፡አለቃዎች፡ከእስራኤል፡ነገዶች፡
ዅሉ፡ጋራ፡በተከማቹ፡ጊዜ፥
ንጉሥ፡በይሹሩን፡ነበረ።
6፤ሮቤል፡በሕይወት፡ይኑር፥አይሙት፤
ሰዎቹም፡በቍጥር፡ብዙ፡ይኹኑ።
7፤የይሁዳ፡በረከት፡ይህ፡ነው፤እንዲህም፡አለ፦
አቤቱ፥የይሁዳን፡ድምፅ፡ስማ፥
ወደ፡ወገኖቹም፡አግባው፤
እጆቹ፡ይጠንክሩለት፤
በጠላቶቹ፡ላይ፡ረዳት፡ትኾነዋለኽ።
8፤ስለ፡ሌዊም፡እንዲህ፡አለ፥
ቱሚምኽና፡ኡሪምኽ፡ለቅዱስኽ፡ሰው፡ነው፥
በማሣህ፡ለፈተንኸው፥
በመሪባ፡ውሃም፡ለተከራከርኸው፤
9፤ስለ፡አባቱና፡ስለ፡እናቱ፦አላየኹም፡ላለ፥
ወንድሞቹንም፡ላላስተዋለ፥
ልጆቹንም፡ላላወቀ፤
ቃልኽን፡አደረጉ፥
ቃል፡ኪዳንኽንም፡ጠበቁ።
10፤ፍርድኽን፡ለያዕቆብ፥
ሕግኽንም፡ለእስራኤል፡ያስተምራሉ፤
በፊትኽ፡ዕጣንን፥
በመሠዊያኽም፡የሚቃጠል፡መሥዋዕት፡ይሠዋሉ።
11፤አቤቱ፥ሀብቱን፡ባርክ፥
የእጁንም፡ሥራ፡ተቀበል፤
የሚነሣበትን፡ወገብ፡ውጋው፥
የሚጠሉትም፡አይነሡ።
12፤ስለ፡ብንያምም፡እንዲህ፡አለ፦
በእግዚአብሔር፡የተወደደ፡በርሱ፡
ዘንድ፡ተማምኖ፡ይኖራል፤
ቀኑን፡ዅሉ፡ይጋርደዋል፥
በትከሻውም፡መካከል፡ያድራል።
13፤ስለ፡ዮሴፍም፡እንዲህ፡አለ፦
ምድሩ፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡የተባረከ፡ይኹን፤
በሰማያት፡ገናንነት፡በጠል፥
በታችኛውም፡ቀላይ፥
14፤በፀሓዩ፡ፍሬያት፡ገናንነት፥
በጨረቃውም፡መውጣት፡ገናንነት፡
15፤በቀደሙትም፡ተራራዎች፡ከፍተኛነት፥
በዘለዓለሙም፡ኰረብታዎች፡ገናንነት፥
16፤በምድሪቱም፡ገናንነትና፡ሞላዋ፥
በቍጥቋጦው፡ውስጥ፡ከነበረው፡በረከት፡
በዮሴፍ፡ራስ፡ላይ፥ከወንድሞቹም፡በተለየው፡ራስ፡ዐናት፡ላይ፡ይውረድ።
17፤ለላሞች፡በኵር፡ግርማ፡ይኾናል፤
ቀንዶቹ፡አንድ፡ቀንድ፡እንዳለው፡ናቸው፤
በእነርሱ፡እስከምድር፡ዳርቻ፡ያሉትን፡
አሕዛብ፡ዅሉ፡ይወጋል፤
የኤፍሬም፡እልፍ፡አእላፋት፥
የምናሴም፡አእላፋት፡እነርሱ፡ናቸው።
18፤ስለ፡ዛብሎንም፡እንዲህ፡አለ፦ዛብሎን፡ሆይ፥በመውጣትኽ፥
ይሳኮር፡ሆይ፥በድንኳንኽ፡ውስጥ፡ደስ፡ይበላችኹ።
19፤የተሰወረውን፡የአሸዋውን፡መዝገብ፥
የባሕሩንም፡ባለጠግነት፡ይጠባሉና፡
አሕዛብን፡ወደ፡ተራራው፡ይጠራሉ፤
በዚያ፡የጽድቅ፡መሥዋዕት፡ይሠዋሉ።
20፤ስለ፡ጋድም፡እንዲህ፡አለ፦
ጋድን፡ሰፊ፡ያደረገ፡ቡሩክ፡ይኹን፤
እንደ፡አንበሳዪቱ፡ዐርፏል፤
ክንድንና፡ራስን፡ይቀጠቅጣል።
21፤በዚያ፡የአለቃ፡ዕድል፡ፈንታ፡ቀርቷልና፥
የመዠመሪያውን፡ክፍል፡ለራሱ፡መረጠ፤
ወደሕዝብ፡አለቃዎችም፡መጣ፤
የእግዚአብሔርንም፡ጽድቅ፥
ፍርዱንም፡ከእስራኤል፡ጋራ፡አደረገ።
22፤ስለ፡ዳንም፡እንዲህ፡አለ፦
ዳን፡የአንበሳ፡ደቦል፡ነው፤
ከባሳን፡ዘሎ፟፡ይወጣል።
23፤ስለ፡ንፍታሌምም፡እንዲህ፡አለ፦
ንፍታሌም፡በሞገስ፡ጠግቧል፥
የእግዚአብሔርንም፡በረከት፡ተሞልቷል፤
ባሕሩንና፡ደቡቡን፡ይወርሳል።
24፤ስለ፡አሴርም፡እንዲህ፡አለ፦
አሴር፡በልጆች፡የተባረከ፡ይኹን፤
በወንድሞቹ፡የተወደደ፡ይኹን፤እግሩንም፡በዘይት፡ውስጥ፡ያጥልቅ።
25፤ጫማኽ፡ብረትና፡ናስ፡ይኾናል፤
እንደ፡ዕድሜኽ፡እንዲሁ፡ኀይልኽ፡ይኾናል።
26፤ይሹሩን፡ሆይ፥በሰማያት፡ላይ፡ለረድኤትኽ፥
በደመናትም፡ላይ፡በታላቅነት፡እንደሚኼድ፡
እንደ፡እግዚአብሔር፡ያለ፡ማንም፡የለም።
27፤መኖሪያኽ፡የዘለዓለም፡አምላክ፡ነው፥
የዘለዓለምም፡ክንዶች፡ከአንተ፡በታች፡ናቸው፤
ጠላትኽን፡ከፊትኽ፡አውጥቶ፦
አጥፋው፡ይላል።
28፤እስራኤልም፡ተማምኖ፥
የያዕቆብም፡ምንጭ፡ብቻውን፥
እኽልና፡የወይን፡ጠጅ፡ባለባት፡ምድር፡ይኖራል፤
ሰማያቱም፡ጠልን፡ያንጠባጥባሉ።
29፤እስራኤል፡ሆይ፥ምስጉን፡ነኽ፤
በእግዚአብሔር፡የዳነ፡ሕዝብ፡እንደ፡አንተ፡ማን፡ነው፧
ርሱ፡የረድኤትኽ፡ጋሻ፥
የከፍተኛነትኽም፡ሰይፍ፡ነው።
ጠላቶችኽም፡ይገዙልኻል፤
አንተም፡ከፍታቸውን፡ትረግጣለኽ።
_______________ኦሪት፡ዘዳግም፥ምዕራፍ፡34።______________
ምዕራፍ፡34።
1፤ሙሴም፡ከሞዐብ፡ሜዳ፡በኢያሪኮ፡ፊት፡ለፊት፡ወዳለው፡ወደናባው፡ተራራ፡ወደፈስጋ፡ራስ፡ወጣ፤እግዚአብሔ ርም፡እስከ፡ዳን፡ድረስ፡ያለውን፡የገለዓድን፡ምድር፥
2፤የንፍታሌምንም፡ምድር፡ዅሉ፥የኤፍሬምንና፡የምናሴንም፡ምድር፥እስከምዕራብም፡ባሕር፡ድረስ፡ያለውን፡የ ይሁዳን፡ምድር፡ዅሉ፥ደቡብንም፥
3፤እስከ፡ዞዓር፡ድረስ፡ያለውንም፡የዘንባባ፡ዛፎች፡ያሉባትን፡ከተማ፡የኢያሪኮን፡ሸለቆ፡ሜዳ፡አሳየው።
4፤እግዚአብሔርም፦ለዘርኽ፡እሰጣታለኹ፡ብዬ፡ለአብርሃምና፡ለይሥሐቅ፡ለያዕቆብም፡የማልኹላቸው፡ምድር፡ይ ህች፡ናት፤በዐይንኽ፡እንድታያት፡አደረግኹኽ፥ነገር፡ግን፥ወደዚያች፡አትሻገርም፡አለው።
5፤የእግዚአብሔር፡ባሪያም፡ሙሴ፡እንደእግዚአብሔር፡ቃል፡በዚያ፡በሞዐብ፡ምድር፡ሞተ።
6፤በቤተ፡ፌጎርም፡ፊት፡ለፊት፡በሞዐብ፡ምድር፡በሸለቆው፡ውስጥ፡ተቀበረ፤እስከ፡ዛሬም፡ድረስ፡መቃብሩን፡ ማንም፡አላወቀም።
7፤ሙሴም፡በሞተ፡ጊዜ፡ዕድሜው፡መቶ፡ኻያ፡ዓመት፡ነበረ፤ዐይኑ፡አልፈዘዘም፥ጕልበቱም፡አልደነገዘም።
8፤የእስራኤልም፡ልጆች፡በሞዐብ፡ሜዳ፡ሠላሳ፡ቀን፡ለሙሴ፡አለቀሱለት፤ለሙሴም፡ያለቀሱለት፡የልቅሶው፡ወራ ት፡ተፈጸመ።
9፤ሙሴም፡እጆቹን፡ስለጫነበት፡የነዌ፡ልጅ፡ኢያሱ፡የጥበብን፡መንፈስ፡ተሞላ፤የእስራኤልም፡ልጆች፡ታዘዙለ ት፥እግዚአብሔርም፡ሙሴን፡እንዳዘዘው፡አደረጉ።
10፤እግዚአብሔርን፡ፊት፡ለፊት፡እንዳወቀው፡እንደ፡ሙሴ፡ያለ፡ነቢይ፡ከዚያ፡ወዲህ፡በእስራኤል፡ዘንድ፡አ ልተነሣም፤
11፤በግብጽ፡ምድር፡በፈርዖንና፡በባሪያዎቹ፡ዅሉ፡ላይ፡በምድሪቱም፡ዅሉ፡ላይ፡ምልክትንና፡ድንቅን፡ያደር ግ፡ዘንድ፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ላከው፡ያለ፥
12፤በእስራኤል፡ዅሉ፡ፊት፡በጸናች፡እጅ፡ዅሉና፡በታላቅ፡ማስደንገጥ፡ዅሉ፡እንዳደረገው፡እንደ፡ሙሴ፡ያለ ፡አልተነሣም፨

http://www.gzamargna.net