የጌታችን፡የኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ወንጌል፡
ቅዱስ፡ሉቃስ፡እንደ፡ጻፈው።

(ክለሳ.1.20020507)

______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡1።______________
ምዕራፍ፡1፤
1-4፤የከበርኽ፡ቴዎፍሎስ፡ሆይ፥ከመዠመሪያው፡በዐይን፡ያዩትና፡የቃሉ፡አገልጋዮች፡የኾኑት፡እንዳስተላለፉልን ፥በኛ፡ዘንድ፡ስለተፈጸመው፡ነገር፡ብዙዎች፡ታሪክን፡በየተራው፡ለማዘጋጀት፡ስለ፡ሞከሩ፥እኔ፡ደግሞ፡ስለተማ ርኸው፡ቃል፡ርግጡን፡እንድታውቅ፡በጥንቃቄ፡ዅሉን፡ከመዠመሪያው፡ተከትዬ፡በየተራው፡ልጽፍልኽ፡መልካም፡ኾኖ ፡ታየኝ።
5፤በይሁዳ፡ንጉሥ፡በሄሮድስ፡ዘመን፡ከአብያ፡ክፍል፡የኾነ፡ዘካርያስ፡የሚባል፡አንድ፡ካህን፡ነበረ፤ሚስቱም፡ ከአሮን፡ልጆች፡ነበረች፥ስሟም፡ኤልሳቤጥ፡ነበረ።
6፤ኹለቱም፡በጌታ፡ትእዛዝና፡ሕግጋት፡ዅሉ፡ያለነቀፋ፡እየኼዱ፥በእግዚአብሔር፡ፊት፡ጻድቃን፡ነበሩ።
7፤ኤልሳቤጥም፡መካን፡ነበረችና፡ልጅ፡አልነበራቸውም፤ኹለቱም፡በዕድሜያቸው፡አርጅተው፡ነበር።
8፤ርሱም፡በክፍሉ፡ተራ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ሲያገለግል፥
9፤እንደ፡ካህናት፡ሥርዐት፡ወደጌታ፡ቤተ፡መቅደስ፡ገብቶ፡ለማጠን፡ዕጣ፡ደረሰበት።
10፤በዕጣንም፡ጊዜ፡ሕዝቡ፡ዅሉ፡በውጭ፡ቆመው፡ይጸልዩ፡ነበር።
11፤የጌታም፡መልአክ፡በዕጣኑ፡መሠዊያ፡ቀኝ፡ቆሞ፡ታየው።
12፤ዘካርያስም፡ባየው፡ጊዜ፡ደነገጠ፥ፍርሀትም፡ወደቀበት።
13፤መልአኩም፡እንዲህ፡አለው፦ዘካርያስ፡ሆይ፥ጸሎትኽ፡ተሰምቶልኻልና፥አትፍራ፤ሚስትኽ፡ኤልሳቤጥም፡ወንድ፡ ልጅ፡ትወልድልኻለች፥ስሙንም፡ዮሐንስ፡ትለዋለኽ።
14፤ደስታና፡ተድላም፡ይኾንልኻል፥በመወለዱም፡ብዙዎች፡ደስ፡ይላቸዋል።
15፤በጌታ፡ፊት፡ታላቅ፡ይኾናልና፥የወይን፡ጠጅና፡የሚያሰክር፡መጠጥ፡አይጠጣም፤ገናም፡በእናቱ፡ማሕፀን፡ሳለ ፡መንፈስ፡ቅዱስ፡ይሞላበታል፤
16፤ከእስራኤልም፡ልጆች፡ብዙዎችን፡ወደ፡ጌታ፡ወደ፡አምላካቸው፡ይመልሳል።
17፤ርሱም፡የተዘጋጁትን፡ሕዝብ፡ለጌታ፡እንዲያሰናዳ፥የአባቶችን፡ልብ፡ወደ፡ልጆች፡የማይታዘዙትንም፡ወደጻድ ቃን፡ጥበብ፡ይመልስ፡ዘንድ፡በኤልያስ፡መንፈስና፡ኀይል፡በፊቱ፡ይኼዳል።
18፤ዘካርያስም፡መልአኩን፦እኔ፡ሽማግሌ፡ነኝ፥ሚስቴም፡በዕድሜዋ፡አርጅታለችና፥ይህን፡በምን፡ዐውቃለኹ፧አለ ው።
19፤መልአኩም፡መልሶ፦እኔ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡የምቆመው፡ገብርኤል፡ነኝ፥እንድናገርኽም፡ይህችንም፡የምሥራ ች፡እንድሰብክልኽ፡ተልኬ፡ነበር፤
20፤እንሆም፥በጊዜው፡የሚፈጸመውን፡ቃሌን፡ስላላመንኽ፥ይህ፡ነገር፡እስከሚኾን፡ቀን፡ድረስ፡ዲዳ፡ትኾናለኽ፡ መናገርም፡አትችልም፡አለው።
21፤ሕዝቡም፡ዘካርያስን፡ይጠብቁት፡ነበር፤በቤተ፡መቅደስም፡ውስጥ፡ስለ፡ዘገየ፡ይደነቁ፡ነበር።
22፤በወጣም፡ጊዜ፡ሊነግራቸው፡አልቻለም፥በቤተ፡መቅደስም፡ራእይ፡እንዳየ፡አስተዋሉ፤ርሱም፡ይጠቅሳቸው፡ነበ ር፤ድዳም፡ኾኖ፡ኖረ።
23፤የማገልገሉም፡ወራት፡ሲፈጸም፡ወደ፡ቤቱ፡ኼደ።
24-25፤ከዚህም፡ወራት፡በዃላ፡ሚስቱ፡ኤልሳቤጥ፡ፀነሰችና፦ነቀፌታዬን፡ከሰው፡መካከል፡ያስወግድልኝ፡ዘንድ፡ጌ ታ፡በተመለከተበት፡ወራት፡እንዲህ፡አድርጎልኛል፡ስትል፡ራሷን፡ዐምስት፡ወር፡ሰወረች።
26፤በስድስተኛውም፡ወር፡መልአኩ፡ገብርኤል፡ናዝሬት፡ወደምትባል፡ወደ፡ገሊላ፡ከተማ፥
27፤ከዳዊት፡ወገን፡ለኾነው፡ዮሴፍ፡ለሚባል፡ሰው፡ወደ፡ታጨች፡ወደ፡አንዲት፡ድንግል፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ ተላከ፥የድንግሊቱም፡ስም፡ማርያም፡ነበረ።
28፤መልአኩም፡ወደ፡ርሷ፡ገብቶ፦ደስ፡ይበልሽ፥ጸጋ፡የሞላብሽ፡ሆይ፥ጌታ፡ከአንቺ፡ጋራ፡ነው፤አንቺ፡ከሴቶች፡ መካከል፡የተባረክሽ፡ነሽ፡አላት።
29፤ርሷም፡ባየችው፡ጊዜ፡ከንግግሩ፡በጣም፡ደነገጠችና፦ይህ፡እንዴት፡ያለ፡ሰላምታ፡ነው፧ብላ፡ዐሰበች።
30፤መልአኩም፡እንዲህ፡አላት፦ማርያም፡ሆይ፥በእግዚአብሔር፡ፊት፡ጸጋ፡አግኝተሻልና፥አትፍሪ።
31፤እንሆም፥ትፀንሻለሽ፡ወንድ፡ልጅም፡ትወልጃለሽ፥ስሙንም፡ኢየሱስ፡ትዪዋለሽ።
32፤ርሱ፡ታላቅ፡ይኾናል፡የልዑል፡ልጅም፡ይባላል፥ጌታ፡አምላክም፡የአባቱን፡የዳዊትን፡ዙፋን፡ይሰጠዋል፤
33፤በያዕቆብ፡ቤትም፡ላይ፡ለዘለዓለም፡ይነግሣል፥ለመንግሥቱም፡መጨረሻ፡የለውም።
34፤ማርያምም፡መልአኩን፦ወንድ፡ስለማላውቅ፡ይህ፡እንዴት፡ይኾናል፧አለችው።
35፤መልአኩም፡መልሶ፡እንዲህ፡አላት፦መንፈስ፡ቅዱስ፡ባንቺ፡ላይ፡ይመጣል፥የልዑልም፡ኀይል፡ይጸልልሻል፡ስለ ዚህ፡ደግሞ፡ከአንቺ፡የሚወለደው፡ቅዱስ፡የእግዚአብሔር፡ልጅ፡ይባላል።
36፤እንሆም፡ዘመድሽ፡ኤልሳቤጥ፥ርሷ፡ደግሞ፡በእርጅናዋ፡ወንድ፡ልጅ፡ፀንሳለች፥ለርሷም፡መካን፡ትባል፡ለነበ ረችው፡ይህ፡ስድስተኛ፡ወር፡ነው፤
37፤ለእግዚአብሔር፡የሚሳነው፡ነገር፡የለምና።
38፤ማርያምም፦እንሆኝ፡የጌታ፡ባሪያ፡እንደ፡ቃልኽ፡ይኹንልኝ፡አለች።መልአኩም፡ከርሷ፡ኼደ።
39፤ማርያምም፡በዚያ፡ወራት፡ተነሥታ፡ወደ፡ተራራማው፡አገር፡ወደይሁዳ፡ከተማ፡ፈጥና፡ወጣች፥
40፤ወደዘካርያስም፡ቤት፡ገብታ፡ኤልሳቤጥን፡ተሳለመቻት።
41፤ኤልሳቤጥም፡የማርያምን፡ሰላምታ፡በሰማች፡ጊዜ፡ፅንሱ፡በማሕፀኗ፡ውስጥ፡ዘለለ፤በኤልሳቤጥም፡መንፈስ፡ቅ ዱስ፡ሞላባት፥
42፤በታላቅ፡ድምፅም፡ጮኻ፡እንዲህ፡አለች፦አንቺ፡ከሴቶች፡መካከል፡የተባረክሽ፡ነሽ፥የማሕፀንሽም፡ፍሬ፡የተ ባረከ፡ነው።
43፤የጌታዬ፡እናት፡ወደ፡እኔ፡ትመጣ፡ዘንድ፡እንዴት፡ይኾንልኛል፧
44፤እንሆ፥የሰላምታሽ፡ድምፅ፡በዦሮዬ፡በመጣ፡ጊዜ፡ፅንሱ፡በማሕፀኔ፡በደስታ፡ዘሏልና።
45፤ከጌታ፡የተነገረላት፡ቃል፡ይፈጸማልና፥ያመነች፡ብፅዕት፡ናት።
46፤ማርያምም፡እንዲህ፡አለች፦
47፤ነፍሴ፡ጌታን፡ታከብረዋለች፥መንፈሴም፡በአምላኬ፡በመድኀኒቴ፡ሐሴት፡ታደርጋለች፤
48፤የባሪያዪቱን፡ውርደት፡ተመልክቷልና።እንሆም፥ከዛሬ፡ዠምሮ፡ትውልድ፡ዅሉ፦ብፅዕት፡ይሉኛል፤
49፤ብርቱ፡የኾነ፡ርሱ፡በእኔ፡ታላቅ፡ሥራ፡አድርጓልና፤ስሙም፡ቅዱስ፡ነው።
50፤ምሕረቱም፡ለሚፈሩት፡እስከ፡ትውልድና፡ትውልድ፡ይኖራል።
51፤በክንዱ፡ኀይል፡አድርጓል፤ትዕቢተኛዎችን፡በልባቸው፡ዐሳብ፡በትኗል፤
52፤ገዢዎችን፡ከዙፋናቸው፡አዋርዷል፤ትሑታንንም፡ከፍ፡አድርጓል፤
53፤የተራቡትን፡በበጎ፡ነገር፡አጥግቧል፤ባለጠጋዎችንም፡ባዷቸውን፡ሰዷቸዋል።
54-55፤ለአባቶቻችን፡እንደ፡ተናገረ፥ለአብርሃምና፡ለዘሩ፡ለዘለዓለም፡ምሕረቱ፡ትዝ፡እያለው፡እስራኤልን፡ብላ ቴናውን፡ረድቷል።
56፤ማርያምም፡ሦስት፡ወር፡የሚያኽል፡በርሷ፡ዘንድ፡ተቀመጠች፡ወደ፡ቤቷም፡ተመለሰች።
57፤የኤልሳቤጥም፡የመውለጃዋ፡ጊዜ፡ደረሰ፥ወንድ፡ልጅም፡ወለደች።
58፤ጎረቤቶቿም፡ዘመዶቿም፡ጌታ፡ምሕረቱን፡እንዳገነነላት፡ሰምተው፡ከርሷ፡ጋራ፡ደስ፡አላቸው።
59፤በስምንተኛውም፡ቀን፡ሕፃኑን፡ሊገርዙት፡መጡ፥በአባቱም፡ስም፡ዘካርያስ፡ሊሉት፡ወደዱ።
60፤እናቱ፡ግን፡መልሳ፦አይኾንም፥ዮሐንስ፡ይባል፡እንጂ፡አለች።
61፤እነርሱም፦ከወገንሽ፡ማንም፡በዚህ፡ስም፡የተጠራ፡የለም፡አሏት።
62፤አባቱንም፡ማን፡ሊባል፡እንዲወድ፡ጠቀሱት።
63፤ብራናም፡ለምኖ፦ስሙ፡ዮሐንስ፡ነው፡ብሎ፡ጻፈ።ዅሉም፡አደነቁ።
64፤ያን፡ጊዜም፡አፉ፡ተከፈተ፥ምላሱም፡ተፈታ፥እግዚአብሔርንም፡እየባረከ፡ተናገረ።
65፤ለጎረቤቶቻቸውም፡ዅሉ፡ፍርሀት፡ኾነ፤ይህም፡ዅሉ፡ነገር፡በይሁዳ፡በተራራማው፡አገር፡ዅሉ፡ተወራ፤
66፤የሰሙትም፡ዅሉ፦እንኪያ፡ይህ፡ሕፃን፡ምን፡ይኾን፧እያሉ፡በልባቸው፡አኖሩት፤የጌታ፡እጅ፡ከርሱ፡ጋራ፡ነበ ረችና።
67፤አባቱ፡ዘካርያስም፡መንፈስ፡ቅዱስ፡ሞላበትና፡ትንቢት፡ተናገረ፡እንዲህም፡አለ።
68፤የእስራኤል፡ጌታ፡አምላክ፡ይባረክ፥ጐብኝቶ፡ለሕዝቡ፡ቤዛ፡አድርጓልና፤
69-70፤ከጥንት፡ዠምሮ፡በነበሩት፡በቅዱሳን፡ነቢያት፡አፍ፡እንደ፡ተናገረ፥በብላቴናው፡በዳዊት፡ቤት፡የመዳን፡ ቀንድን፡አስነሥቶልናል፤
71፤ማዳኑም፡ከወደረኛዎቻችንና፡ከሚጠሉን፡ዅሉ፡እጅ፡ነው፤
72-73፤እንደዚህ፡ለአባቶቻችን፡ምሕረት፡አደረገ፤ለአባታችን፡ለአብርሃምም፡የማለውን፡መሐላውን፡ቅዱሱን፡ኪዳ ን፡ዐሰበ፤
74-75፤በርሱም፡ከጠላቶቻችን፡እጅ፡ድነን፡በዘመናችን፡ዅሉ፡ያለፍርሀት፡በቅድስናና፡በጽድቅ፡በፊቱ፡እንድናገ ለግለው፡ሰጠን።
76፤ደግሞም፡አንተ፡ሕፃን፡ሆይ፥የልዑል፡ነቢይ፡ትባላለኽ፥መንገዱን፡ልትጠርግ፡በጌታ፡ፊት፡ትኼዳለኽና፤
77፤እንደዚህም፡የኀጢአታቸው፡ስርየት፡የኾነውን፡የመዳን፡ዕውቀት፡ለሕዝቡ፡ትሰጣለኽ፤
78፤ይህም፡ከላይ፡የመጣ፡ብርሃን፡በጐበኘበት፡በአምላካችን፡ምሕረትና፡ርኅራኄ፡ምክንያት፡ነው፤
79፤ብርሃኑም፡በጨለማና፡በሞት፡ጥላ፡ተቀምጠው፡ላሉት፡ያበራል፡እግሮቻችንንም፡በሰላም፡መንገድ፡ያቀናል።
80፤ሕፃኑም፡አደገ፡በመንፈስም፡ጠነከረ፥ለእስራኤልም፡እስከታየበት፡ቀን፡ድረስ፡በምድረ፡በዳ፡ኖረ።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡2።______________
ምዕራፍ፡2፤
1፤በዚያም፡ወራት፡ዓለሙ፡ዅሉ፡እንዲጻፍ፡ከአውግስጦስ፡ቄሳር፡ትእዛዝ፡ወጣች።
2፤ቄሬኔዎስ፡በሶርያ፡አገር፡ገዢ፡በነበረ፡ጊዜ፡ይህ፡የመዠመሪያ፡ጽሕፈት፡ኾነ።
3፤ዅሉም፡እያንዳንዱ፡ይጻፍ፡ዘንድ፡ወደ፡ከተማው፡ኼደ።
4-5፤ዮሴፍም፡ደግሞ፡ከዳዊት፡ቤትና፡ወገን፡ስለ፡ነበረ፡ከገሊላ፡ከናዝሬት፡ከተማ፡ተነሥቶ፡ቤተ፡ልሔም፡ወደም ትባል፡ወደዳዊት፡ከተማ፡ወደ፡ይሁዳ፥ፀንሳ፡ከነበረች፡ከዕጮኛው፡ከማርያም፡ጋራ፡ይጻፍ፡ዘንድ፡ወጣ።
6፤በዚያም፡ሳሉ፡የመውለጃዋ፡ወራት፡ደረሰ፥
7፤የበኵር፡ልጇንም፡ወለደች፥በመጠቅለያም፡ጠቀለለችው፤በእንግዳዎችም፡ማደሪያ፡ስፍራ፡ስላልነበራቸው፡በግር ግም፡አስተኛችው።
8፤በዚያም፡ምድር፡መንጋቸውን፡በሌሊት፡ሲጠብቁ፡በሜዳ፡ያደሩ፡እረኛዎች፡ነበሩ።
9፤እንሆም፥የጌታ፡መልአክ፡ወደ፡እነርሱ፡ቀረበ፡የጌታ፡ክብርም፡በዙሪያቸው፡አበራ፥ታላቅ፡ፍርሀትም፡ፈሩ።
10፤መልአኩም፡እንዲህ፡አላቸው፦እንሆ፥ለሕዝቡ፡ዅሉ፡የሚኾን፡ታላቅ፡ደስታ፡የምሥራች፡እነግራችዃለኹና፡አት ፍሩ፤
11፤ዛሬ፡በዳዊት፡ከተማ፡መድኀኒት፡ርሱም፡ክርስቶስ፡ጌታ፡የኾነ፡ተወልዶላችዃልና።
12፤ይህም፡ምልክት፡ይኾንላችዃል፤ሕፃን፡ተጠቅሎ፟፡በግርግምም፡ተኝቶ፡ታገኛላችኹ።
13፤ድንገትም፡ብዙ፡የሰማይ፡ሰራዊት፡ከመልአኩ፡ጋራ፡ነበሩ።እግዚአብሔርንም፡እያመሰገኑ።
14፤ክብር፡ለእግዚአብሔር፡በአርያም፡ይኹን፡ሰላምም፡በምድር፡ለሰውም፡በጎ፡ፈቃድ፡አሉ።
15፤መላእክትም፡ከነርሱ፡ተለይተው፡ወደ፡ሰማይ፡በወጡ፡ጊዜ፥እረኛዎቹ፡ርስ፡በርሳቸው።እንግዲህ፡እስከ፡ቤተ ፡ልሔም፡ድረስ፡እንኺድ፡እግዚአብሔርም፡የገለጠልንን፡ይህን፡የኾነውን፡ነገር፡እንይ፡ተባባሉ።
16፤ፈጥነውም፡መጡ፡ማርያምንና፡ዮሴፍን፡ሕፃኑንም፡በግርግም፡ተኝቶ፡አገኙ።
17፤አይተውም፡ስለዚህ፡ሕፃን፡የተነገረላቸውን፡ነገር፡ገለጡ።
18፤የሰሙትን፡ዅሉ፡እረኛዎቹ፡በነገሯቸው፡ነገር፡አደነቁ፤
19፤ማርያም፡ግን፡ይህን፡ነገር፡ዅሉ፡በልቧ፡እያሰበች፡ትጠብቀው፡ነበር።
20፤እረኛዎችም፡እንደ፡ተባለላቸው፡ስለ፡ሰሙትና፡ስላዩት፡ዅሉ፡እግዚአብሔርን፡እያመሰገኑና፡እያከበሩ፡ተመ ለሱ።
21፤ሊገርዙት፡ስምንት፡ቀን፡በሞላ፡ጊዜ፥በማሕፀን፡ሳይረገዝ፡በመልአኩ፡እንደ፡ተባለ፥ስሙ፡ኢየሱስ፡ተብሎ፡ ተጠራ።
22-24፤እንደ፡ሙሴም፡ሕግ፡የመንጻታቸው፡ወራት፡በተፈጸመ፡ጊዜ፥በጌታ፡ሕግ፦የእናቱን፡ማሕፀን፡የሚከፍት፡ወን ድ፡ዅሉ፡ለጌታ፡የተቀደሰ፡ይባላል፡ተብሎ፡እንደ፡ተጻፈ፡በጌታ፡ፊት፡ሊያቆሙት፥በጌታም፡ሕግ።ኹለት፡ዋሊያ፡ ወይም፡ኹለት፡የርግብ፡ጫጩቶች፡እንደ፡ተባለ፥መሥዋዕት፡ሊያቀርቡ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ወሰዱት።
25፤እንሆም፥በኢየሩሳሌም፡ስምዖን፡የሚባል፡ሰው፡ነበረ፥ይህም፡ሰው፡የእስራኤልን፡መጽናናት፡ይጠባበቅ፡ነበ ር፤ጻድቅና፡ትጉህም፡ነበረ፥መንፈስ፡ቅዱስም፡በርሱ፡ላይ፡ነበረ።
26፤በጌታም፡የተቀባውን፡ሳያይ፡ሞትን፡እንዳያይ፡በመንፈስ፡ቅዱስ፡ተረድቶ፡ነበር።
27፤በመንፈስም፡ወደ፡መቅደስ፡ወጣ፤ወላጆቹም፡እንደ፡ሕጉ፡ልማድ፡ያደርጉለት፡ዘንድ፡ሕፃኑን፡ኢየሱስን፡በአ ስገቡት፡ጊዜ፥
28፤ርሱ፡ደግሞ፡ተቀብሎ፡ዐቀፈው፡እግዚአብሔርንም፡እየባረከ፡እንዲህ፡አለ።
29፤ጌታ፡ሆይ፥አኹን፡እንደ፡ቃልኽ፡ባሪያኽን፡በሰላም፡ታሰናብተዋለኽ፤
30-31፤ዐይኖቼ፡በሰዎች፡ዅሉ፡ፊት፡ያዘጋጀኸውን፡ማዳንኽን፡አይተዋልና፤
32፤ይህም፡ለአሕዛብ፡ዅሉን፡የሚገልጥ፡ብርሃን፡ለሕዝብኽም፡ለእስራኤል፡ክብር፡ነው።
33፤ዮሴፍና፡እናቱም፡ስለ፡ርሱ፡በተባለው፡ነገር፡ይደነቁ፡ነበር።
34-35፤ስምዖንም፡ባረካቸው፡እናቱን፡ማርያምንም፦እንሆ፥የብዙዎች፡ልብ፡ዐሳብ፡ይገለጥ፡ዘንድ፥ይህ፡በእስራኤ ል፡ላሉት፡ለብዙዎቹ፡ለመውደቃቸውና፡ለመነሣታቸው፡ለሚቃወሙትም፡ምልክት፡ተሾሟል፥ባንቺም፡ደግሞ፡በነፍስሽ ፡ሰይፍ፡ያልፋል፡አላት።
36፤ከአሴር፡ወገንም፡የምትኾን፡የፋኑኤል፡ልጅ፡ሐና፡የምትባል፡አንዲት፡ነቢዪት፡ነበረች፤ርሷም፡ከድንግልና ዋ፡ዠምራ፡ከባሏ፡ጋራ፡ሰባት፡ዓመት፡ኖረች፤
37፤ርሷም፡ሰማንያ፡አራት፡ዓመት፡ያኽል፡መበለት፡ኾና፡በጣም፡አርጅታ፡ነበር፤በጾምና፡በጸሎትም፡ሌሊትና፡ቀ ን፡እያገለገለች፡ከመቅደስ፡አትለይም፡ነበር።
38፤በዚያችም፡ሰዓት፡ቀርባ፡እግዚአብሔርን፡አመሰገነች፤የኢየሩሳሌምንም፡ቤዛ፡ለሚጠባበቁ፡ዅሉ፡ስለ፡ርሱ፡ ትናገር፡ነበር።
39፤ዅሉንም፡እንደ፡ጌታ፡ሕግ፡ከፈጸሙ፡በዃላ፥ወደ፡ገሊላ፡ወደ፡ከተማቸው፡ወደ፡ናዝሬት፡ተመለሱ።
40፤ሕፃኑም፡አደገ፥ጥበብም፡ሞልቶበት፡በመንፈስ፡ጠነከረ፤የእግዚአብሔርም፡ጸጋ፡በርሱ፡ላይ፡ነበረ።
41፤ወላጆቹም፡በያመቱ፡በፋሲካ፡በዓል፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ይወጡ፡ነበር።
42፤የዐሥራ፡ኹለት፡ዓመት፡ልጅ፡በኾነ፡ጊዜ፥እንደ፡በዓሉ፡ሥርዐት፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ወጡ፤
43፤ቀኖቹንም፡ከፈጸሙ፡በዃላ፥ሲመለሱ፡ብላቴናው፡ኢየሱስ፡በኢየሩሳሌም፡ቀርቶ፡ነበር፥ዮሴፍም፡እናቱም፡አላ ወቁም፡ነበር።
44፤ከመንገደኛዎች፡ጋራ፡የነበረ፡ስለ፡መሰላቸው፡ያንድ፡ቀን፡መንገድ፡ኼዱ፥ከዘመዶቻቸውም፡ከሚያውቋቸውም፡ ዘንድ፡ፈለጉት፤
45፤ባጡትም፡ጊዜ፡እየፈለጉት፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ተመለሱ።
46፤ከሦስት፡ቀንም፡በዃላ፡በመምህራን፡መካከል፡ተቀምጦ፡ሲሰማቸውም፡ሲጠይቃቸውም፡በመቅደስ፡አገኙት፤
47፤የሰሙትም፡ዅሉ፡በማስተዋሉና፡በመልሱ፡ተገረሙ።
48፤ባዩትም፡ጊዜ፡ተገረሙ፥እናቱም፦ልጄ፡ሆይ፥ለምን፡እንዲህ፡አደረግኽብን፧እንሆ፥አባትኽና፡እኔ፡እየተጨነ ቅን፡ስንፈልግኽ፡ነበርን፡አለችው።
49፤ርሱም፦ስለ፡ምን፡ፈለጋችኹኝ፧በአባቴ፡ቤት፡እኾን፡ዘንድ፡እንዲገባኝ፡አላወቃችኹምን፧አላቸው።
50፤እነርሱም፡የተናገራቸውን፡ነገር፡አላስተዋሉም።
51፤ከነርሱም፡ጋራ፡ወርዶ፡ወደ፡ናዝሬት፡መጣ፥ይታዘዝላቸውም፡ነበር።እናቱም፡ይህን፡ነገር፡ዅሉ፡በልቧ፡ትጠ ብቀው፡ነበር።
52፤ኢየሱስም፡ደግሞ፡በጥበብና፡በቁመት፡በሞገስም፡በእግዚአብሔርና፡በሰው፡ፊት፡ያድግ፡ነበር።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡3።______________
ምዕራፍ፡3፤
1፤ጢባርዮስ፡ቄሳርም፡በነገሠ፡በዐሥራ፡ዐምስተኛዪቱ፡ዓመት፥ጰንጤናዊው፡ጲላጦስም፡በይሁዳ፡ሲገዛ፥ሄሮድስም ፡በገሊላ፡የአራተኛው፡ክፍል፡ገዢ፥ወንድሙ፡ፊልጶስም፡በኢጡርያስ፡በጥራኮኒዶስም፡አገር፡የአራተኛው፡ክፍል ፡ገዢ፥ሊሳኒዮስም፡በሳቢላኒስ፡የአራተኛው፡ክፍል፡ገዢ፡ኾነው፡ሳሉ፥
2፤ሐናና፡ቀያፋም፡ሊቃነ፡ካህናት፡ሳሉ፥የእግዚአብሔር፡ቃል፡ወደዘካርያስ፡ልጅ፡ወደ፡ዮሐንስ፡በምድረ፡በዳ፡ መጣ።
3-6፤በነቢዩ፡በኢሳይያስ፡ቃል፡መጽሐፍ፦የጌታን፡መንገድ፡አዘጋጁ፡ጥርጊያውንም፡አቅኑ፡እያለ፡በምድረ፡በዳ፡ የሚጮኽ፡ሰው፡ድምፅ፤ዐዘቅቱ፡ዅሉ፡ይሙላ፡ተራራውና፡ኰረብታውም፡ዅሉ፡ዝቅ፡ይበል፥ጠማማውም፡የቀና፡መንገድ ፡ይኹን፥ሻካራውም፡መንገድ፡ትክክል፡ይኹን፤ሥጋም፡የለበሰ፡ዅሉ፡የእግዚአብሔርን፡ማዳን፡ይይ፡ተብሎ፡እንደ ፡ተጻፈ፡ለኀጢአት፡ስርየት፡የንስሓን፡ጥምቀት፡እየሰበከ፡በዮርዳኖስ፡ዙሪያ፡ወዳለችው፡አገር፡ዅሉ፡መጣ።
7፤ስለዚህ፥ከርሱ፡ሊጠመቁ፡ለወጡት፡ሕዝብ፡እንዲህ፡ይላቸው፡ነበር፦እናንተ፡የእፍኝት፡ልጆች፥ከሚመጣው፡ቍጣ ፡እንድትሸሹ፡ማን፡አመለከታችኹ፧
8፤እንግዲህ፡ለንስሓ፡የሚገ፟ባ፟፡ፍሬ፡አድርጉ፤በልባችኹም፦አብርሃም፡አባት፡አለን፡ማለትን፡አትዠምሩ፤ከነ ዚህ፡ድንጋዮች፡ለአብርሃም፡ልጆች፡ሊያስነሣለት፡እግዚአብሔር፡እንዲችል፡እላችዃለኹና።
9፤አኹንስ፡ምሣር፡ደግሞ፡በዛፎች፡ሥር፡ተቀምጧል፤እንግዲህ፡መልካም፡ፍሬ፡የማያደርግ፡ዛፍ፡ዅሉ፡ይቈረጣል፡ ወደ፡እሳትም፡ይጣላል።
10፤ሕዝቡም፦እንግዲህ፡ምን፡እናድርግ፧ብለው፡ይጠይቁት፡ነበር።
11፤መልሶም፦ኹለት፡ልብስ፡ያለው፡ለሌለው፡ያካፍል፥ምግብም፡ያለው፡እንዲሁ፡ያድርግ፡ይል፡ነበር።
12፤ቀራጮችም፡ደግሞ፡ሊጠመቁ፡መጥተው፦መምህር፡ሆይ፥ምን፡እናድርግ፧አሉት።
13፤ከታዘዘላችኹ፡አብልጣችኹ፡አትውሰዱ፡አላቸው።
14፤ጭፍራዎችም፡ደግሞ፦እኛ፡ደግሞ፡ምን፡እናድርግ፧ብለው፡ይጠይቁት፡ነበር።ርሱም፦በማንም፡ግፍ፡አትሥሩ፡ማ ንንም፡በሐሰት፡አትክሰሱ፥ደመ፡ወዛችኹም፡ይብቃችኹ፡አላቸው።
15፤ሕዝቡም፡ሲጠብቁ፡ሳሉ፡ዅሉም፡በልባቸው፡ስለ፡ዮሐንስ፦ይህ፡ክርስቶስ፡ይኾንን፧ብለው፡ሲያስቡ፡ነበር፥
16፤ዮሐንስ፡መልሶ፦እኔስ፡በውሃ፡አጠምቃችዃለኹ፤ነገር፡ግን፥የጫማውን፡ጠፍር፡መፍታት፡ከማይገ፟ባ፟ኝ፡ከእ ኔ፡የሚበረታ፡ይመጣል፤ርሱ፡በመንፈስ፡ቅዱስና፡በእሳት፡ያጠምቃችዃል፤
17፤መንሹም፡በእጁ፡ነው፥ዐውድማውንም፡ፈጽሞ፡ያጠራል፥ስንዴውንም፡በጐተራው፡ይከታል፥ገለባውን፡ግን፡በማይ ጠፋ፡እሳት፡ያቃጥለዋል፡አላቸው።
18፤ስለዚህ፥ሕዝቡን፡በብዙ፡ሌላ፡ምክር፡እየመከራቸው፡ወንጌልን፡ይሰብክላቸው፡ነበር፤
19፤የአራተኛው፡ክፍል፡ገዢ፡ሄሮድስ፡ግን፥ስለ፡ሄሮድያዳ፡ስለ፡ወንድሙ፡ስለ፡ፊልጶስ፡ሚስትና፡ሄሮድስ፡ስላ ደረገው፡ሌላ፡ክፋት፡ዅሉ፡ዮሐንስ፡ስለ፡ገሠጸው፥
20፤ይህን፡ደግሞ፡ከዅሉ፡በላይ፡ጨምሮ፡ዮሐንስን፡በወህኒ፡አገባው።
21፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡ከተጠመቁ፡በዃላ፡ኢየሱስ፡ደግሞ፡ተጠመቀ።ሲጸልይም፡ሰማይ፡ተከፈተ፥
22፤መንፈስ፡ቅዱስም፡በአካል፡መልክ፡እንደ፡ርግብ፡በርሱ፡ላይ፡ወረደ፤የምወድኽ፡ልጄ፡አንተ፡ነኽ፥ባንተ፡ደ ስ፡ይለኛል፡የሚል፡ድምፅም፡ከሰማይ፡መጣ።
23፤ኢየሱስም፡ሊያስተምር፡ሲዠምር፡ዕድሜው፡ሠላሳ፡ዓመት፡ያኽል፡ኾኖት፡ነበር፤እንደመሰላቸው፡የዮሴፍ፡ልጅ ፡ኾኖ፥የኤሊ፡ልጅ፥
24፤የማቲ፡ልጅ፥የሌዊ፡ልጅ፥የሚልኪ፡ልጅ፥
25፤የዮና፡ልጅ፥የዮሴፍ፡ልጅ፥የማታትዩ፡ልጅ፥የዓሞጽ፡ልጅ፥የናሖም፡ልጅ፥የኤሲሊም፡ልጅ፡
26፤የናጌ፡ልጅ፥የማአት፡ልጅ፥የማታትዩ፡ልጅ፡የሴሜይ፡ልጅ፥የዮሴፍ፡ልጅ፥
27፤የዮዳ፡ልጅ፥የዮናን፡ልጅ፥የሬስ፡ልጅ፥የዘሩባቤል፡ልጅ፥የሰላትያል፡ልጅ፥የኔሪ፡ልጅ፥
28፤የሚልኪ፡ልጅ፥የሐዲ፡ልጅ፥የዮሳስ፡ልጅ፥የቆሳም፡ልጅ፥የኤልሞዳም፡ልጅ፥የኤር፡ልጅ፥
29፤የዮሴዕ፡ልጅ፥የኤልዓዘር፡ልጅ፡የዮራም፡ልጅ፥የማጣት፡ልጅ፥የሌዊ፡ልጅ፥
30፤የስምዖን፡ልጅ፥የይሁዳ፡ልጅ፥የዮሴፍ፡ልጅ፥
31፤የዮናን፡ልጅ፥የኤልያቄም፡ልጅ፥የሜልያ፡ልጅ፥የማይናን፡ልጅ፥የማጣት፡ልጅ፥የናታን፡ልጅ፡
32፤የዳዊት፡ልጅ፥የእሴይ፡ልጅ፥የኢዮቤድ፡ልጅ፥የቦዔዝ፡ልጅ፥የሰልሞን፡ልጅ፥
33፤የነአሶን፡ልጅ፥የዐሚናዳብ፡ልጅ፥የአራም፡ልጅ፥የአሮኒ፡ልጅ፥የኤስሮም፡ልጅ፥
34፤የፋሬስ፡ልጅ፥የይሁዳ፡ልጅ፥የያዕቆብ፡ልጅ፥የይሥሐቅ፡ልጅ፥የአብርሃም፡ልጅ፥የታራ፡ልጅ፥
35፤የናኮር፡ልጅ፥የሴሮህ፡ልጅ፥የራጋው፡ልጅ፥የፋሌቅ፡ልጅ፥የአቤር፡ልጅ፥የሳላ፡ልጅ፥
36፤የቃይንም፡ልጅ፥የአርፋክስድ፡ልጅ፥የሴም፡ልጅ፥የኖኅ፡ልጅ፥የላሜህ፡ልጅ፥
37፤የማቱሳላ፡ልጅ፥የሔኖክ፡ልጅ፥የያሬድ፡ልጅ፥
38፤የመላልኤል፡ልጅ፥የቃይናን፡ልጅ፥የሄኖስ፡ልጅ፥የሴት፡ልጅ፥የአዳም፡ልጅ፥የእግዚአብሔር፡ልጅ።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡4።______________
ምዕራፍ፡4፤
1፤ኢየሱስም፡መንፈስ፡ቅዱስ፡መልቶበት፡ከዮርዳኖስ፡ተመለሰ፥በመንፈስም፡ወደ፡ምድረ፡በዳ፡ተመርቶ፥
2፤አርባ፡ቀን፡ከዲያብሎስ፡ተፈተነ።በነዚያም፡ቀኖች፡ምንም፡አልበላም፥ከተጨረሱም፡በዃላ፡ተራበ።
3፤ዲያብሎስም፦የእግዚአብሔር፡ልጅ፡ከኾንኽ፥ይህን፡ድንጋይ፦እንጀራ፡ኹን፡ብለኽ፡እዘዝ፡አለው።
4፤ኢየሱስም፦ሰው፡በእግዚአብሔር፡ቃል፡ዅሉ፡እንጂ፡በእንጀራ፡ብቻ፡አይኖርም፡ተብሎ፡ተጽፏል፡ብሎ፡መለሰለት ።
5፤ዲያብሎስም፡ረዥም፡ወደ፡ኾነ፡ተራራ፡አውጥቶ፡የዓለምን፡መንግሥታት፡ዅሉ፡በቅጽበት፡አሳየው።
6፤ዲያብሎስም፦ይህ፡ሥልጣን፡ዅሉ፡ክብራቸውም፡ለእኔ፡ተሰጥቷል፡ለምወደ፟ውም፡ለማንም፡እሰጠዋለኹና፡ለአንተ ፡እሰጥኻለኹ፤
7፤ስለዚህ፥አንተ፡በእኔ፡ፊት፡ብትሰግድ፥ዅሉ፡ለአንተ፡ይኾናል፡አለው።
8፤ኢየሱስም፡መልሶ፦ለጌታ፡ለአምላክኽ፡ስገድ፡ርሱንም፡ብቻ፡አምልክ፡ተብሎ፡ተጽፏል፡አለው።
9-11፤ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ደግሞ፡ወሰደው፤በመቅደስም፡ጫፍ፡ላይ፡አቁሞ፦ይጠብቁኽ፡ዘንድ፡መላእክቱን፡ስለ፡አን ተ፡ያዝ፟ልኻል፥እግርኽንም፡በድንጋይ፡ከቶ፡እንዳትሰናከል፡በእጃቸው፡ያነሡኻል፡ተብሎ፡ተጽፏልና፥የእግዚአ ብሔር፡ልጅስ፡ከኾንኽ፥ከዚህ፡ወደ፡ታች፡ራስኽን፡ወርውር፡አለው።
12፤ኢየሱስም፡መልሶ፦ጌታን፡አምላክኽን፡አትፈታተነው፡ተብሏል፡አለው።
13፤ዲያብሎስም፡ፈተናውን፡ዅሉ፡ከጨረሰ፡በዃላ፡እስከ፡ጊዜው፡ከርሱ፡ተለየ።
14፤ኢየሱስም፡በመንፈስ፡ኀይል፡ወደ፡ገሊላ፡ተመለሰ፤ስለ፡ርሱም፡በዙሪያው፡ባለችው፡አገር፡ዅሉ፡ዝና፡ወጣ።
15፤ርሱም፡በምኵራባቸው፡ያስተምር፥ዅሉም፡ያመሰግኑት፡ነበር።
16፤ወዳደገበትም፡ወደ፡ናዝሬት፡መጣ፤እንደ፡ልማዱም፡በሰንበት፡ቀን፡ወደ፡ምኵራብ፡ገባ፥ሊያነብም፡ተነሣ።
17-19፤የነቢዩንም፡የኢሳይያስን፡መጽሐፍ፡ሰጡት፥መጽሐፉንም፡በተረተረ፡ጊዜ፦የጌታ፡መንፈስ፡በእኔ፡ላይ፡ነው ፥ለድኻዎች፡ወንጌልን፡እሰብክ፡ዘንድ፡ቀብቶኛልና፤ለታሰሩትም፡መፈታትን፡ለዕውሮችም፡ማየትን፡እሰብክ፡ዘን ድ፥የተጠቁትንም፡ነጻ፡አወጣ፡ዘንድ፡የተወደደችውንም፡የጌታን፡ዓመት፡እሰብክ፡ዘንድ፡ልኮኛል፡ተብሎ፡የተጻ ፈበትን፡ስፍራ፡አገኘ።
20፤መጽሐፉንም፡ጠቅሎ፟፡ለአገልጋዩ፡ሰጠውና፡ተቀመጠ፤በምኵራብም፡የነበሩት፡ዅሉ፡ትኵር፡ብለው፡ይመለከቱት ፡ነበር።
21፤ርሱም፦ዛሬ፡ይህ፡መጽሐፍ፡በዦሯችኹ፡ተፈጸመ፡ይላቸው፡ዠመር።
22፤ዅሉም፡ይመሰክሩለት፡ነበር፡ከአፉም፡ከሚወጣው፡ከጸጋው፡ቃል፡የተነሣ፡እየተደነቁ፦ይህ፡የዮሴፍ፡ልጅ፡አ ይደለምን፧ይሉ፡ነበር።
23፤ርሱም፦ያለጥርጥር፡ይህን፡ምሳሌ፦ባለመድኀኒት፡ሆይ፥ራስኽን፡ፈውስ፤በቅፍርናሖም፡እንዳደረግኸው፡የሰማ ነውን፡ዅሉ፡በዚህ፡በገዛ፡አገርኽ፡ደግሞ፡አድርግ፡ትሉኛላችኹ፡አላቸው።
24፤እንዲህም፡አለ፦እውነት፡እላችዃለኹ፥ነቢይ፡በገዛ፡አገሩ፡ከቶ፡አይወደድም።
25፤ነገር፡ግን፥እውነት፡እላችዃለኹ፥በኤልያስ፡ዘመን፡ሦስት፡ዓመት፡ከስድስት፡ወር፡ሰማይ፡ተዘግቶ፡ሳለ፡በ ምድር፡ዅሉ፡ብርቱ፡ራብ፡በነበረ፡ጊዜ፥በእስራኤል፡ብዙ፡መበለቶች፡ነበሩ፤
26፤ኤልያስም፡በሲዶና፡አገር፡ወዳለች፡ወደ፡ሰራጵታ፣ወደ፡አንዲት፡መበለት፡እንጂ፥ከነርሱ፡ወደ፡አንዲቱ፡አ ልተላከም።
27፤በነቢዩ፡በኤልሳዕ፡ዘመንም፡በእስራኤል፡ብዙ፡ለምጻሞች፡ነበሩ፥ከሶርያዊው፡ከንዕማን፡በቀር፡ከነርሱ፡አ ንድ፡ስንኳ፡አልነጻም።
28፤በምኵራብም፡የነበሩ፡ዅሉ፡ይህን፡ሰምተው፡ቍጣ፡ሞላባቸው፥ተነሥተውም፡ከከተማ፡ወደ፡ውጭ፡አወጡት፥
29፤ይጥሉትም፡ዘንድ፡ከተማቸው፡ተሠርታባት፡ወደነበረች፡ወደተራራው፡አፋፍ፡ወሰዱት፤
30፤ርሱ፡ግን፡በመካከላቸው፡ዐልፎ፡ኼደ።
31፤ወደገሊላ፡ከተማም፡ወደ፡ቅፍርናሖም፡ወረደ።በሰንበትም፡ያስተምራቸው፡ነበር፤
32፤ቃሉ፡በሥልጣን፡ነበርና፥በትምህርቱ፡ተገረሙ።
33፤በምኵራብም፡የርኩስ፡ጋኔን፡መንፈስ፡ያደረበት፡ሰው፡ነበረ፥በታላቅ፡ድምፅም፡ጮኾ፦
34፤ተው፥የናዝሬቱ፡ኢየሱስ፡ሆይ፥ከአንተ፡ጋራ፡ምን፡አለን፧ልታጠፋን፡መጣኽን፧ማን፡እንደ፡ኾንኽ፡ዐውቄኻለ ኹ፥አንተ፡የእግዚአብሔር፡ቅዱሱ፡አለ።
35፤ኢየሱስም፦ዝም፡በል፡ከርሱም፡ውጣ፡ብሎ፡ገሠጸው።ጋኔኑም፡በመካከላቸው፡ጥሎት፡ሳይጐዳው፡ከርሱ፡ወጣ።
36፤ዅሉንም፡መደነቅ፡ያዛቸው፥ርስ፡በርሳቸውም፦ይህ፡ቃል፡ምንድር፡ነው፧በሥልጣንና፡በኀይል፡ርኩሳን፡መናፍ ስትን፡ያዛ፟ልና፥ይወጡማል፡ብለው፡ተነጋገሩ።
37፤ዝናም፡በዙሪያው፡ባለች፡አገር፡ወደ፡ስፍራው፡ዅሉ፡ስለ፡ርሱ፡ወጣ።
38፤በምኵራብም፡ተነሥቶ፡ወደስምዖን፡ቤት፡ገባ።የስምዖንም፡ዐማት፡በብርቱ፡ንዳድ፡ታማ፡ነበር፡ስለ፡ርሷም፡ ለመኑት።
39፤በአጠገቧም፡ቆሞ፡ንዳዱን፡ገሠጸውና፡ለቀቃት፤ያን፡ጊዜውንም፡ተነሥታ፡አገለገለቻቸው።
40፤ፀሓይም፡በገባ፡ጊዜ፡በልዩ፡ልዩ፡ደዌ፡የተያዙ፡በሽተኛዎችን፡ዅሉ፡ወደ፡ርሱ፡አመጧቸው፤ርሱም፡በያንዳን ዳቸው፡ላይ፡እጁን፡ጭኖ፡ፈወሳቸው።
41፤አጋንንትም፡ደግሞ፦አንተ፡ክርስቶስ፡የእግዚአብሔር፡ልጅ፡ነኽ፡እያሉ፡እየጮኹም፡ከብዙዎች፡ይወጡ፡ነበር ፤ገሠጻቸውም፡ክርስቶስም፡እንደ፡ኾነ፡ዐውቀውት፡ነበርና፥እንዲናገሩ፡አልፈቀደላቸውም።
42፤በጸባም፡ጊዜ፡ወጥቶ፡ወደ፡ምድረ፡በዳ፡ኼደ፤ሕዝቡም፡ይፈልጉት፡ነበር፤ወደ፡ርሱም፡መጡ፥ከነርሱም፡ተለይ ቶ፡እንዳይኼድ፡ሊከለክሉት፡ወደዱ።
43፤ርሱ፡ግን፦ስለዚህ፡ተልኬያለኹና፡ለሌላዎቹ፡ከተማዎች፡ደግሞ፡የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡ወንጌል፡እሰብ ክ፡ዘንድ፡ይገ፟ባ፟ኛል፡አላቸው።
44፤በገሊላም፡ምኵራቦች፡ይሰብክ፡ነበር።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡5።______________
ምዕራፍ፡5፤
1፤ሕዝቡም፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡እየሰሙ፡ሲያስጠብቡት፡ሳሉ፥ርሱ፡ራሱ፡በጌንሳሬጥ፡ባሕር፡ዳር፡ቆሞ፡ነበር ፤
2፤በባሕር፡ዳርም፡ቆመው፡የነበሩትን፡ኹለት፡ታንኳዎች፡አየ፤ዓሣ፡አጥማጆች፡ግን፡ከነርሱ፡ውስጥ፡ወጥተው፡መ ረቦቻቸውን፡ያጥቡ፡ነበር።
3፤ከታንኳዎቹም፡የስምዖን፡ወደነበረች፡ወደ፡አንዲቱ፡ገብቶ፡ከምድር፡ጥቂት፡ፈቀቅ፡እንዲያደርጋት፡ለመነው፤ በታንኳዪቱም፡ተቀምጦ፡ሕዝቡን፡ያስተምር፡ነበር።
4፤ነገሩንም፡ከጨረሰ፡በዃላ፥ስምዖንን፦ወደ፡ጥልቁ፡ፈቀቅ፡በል፡መረቦቻችኹንም፡ለማጥመድ፡ጣሉ፡አለው።
5፤ስምዖንም፡መልሶ፦አቤቱ፥ሌሊቱን፡ዅሉ፡ዐድረን፡ስንደክም፡ምንም፡አልያዝንም፤ነገር፡ግን፥በቃልኽ፡መረቦቹ ን፡እጥላለኹ፡አለው።
6፤ይህንም፡ባደረጉ፡ጊዜ፡እጅግ፡ብዙ፡ዓሣ፡ያዙ፤መረቦቻቸውም፡ተቀደዱ።
7፤በሌላ፡ታንኳም፡የነበሩትን፡ጓደኛዎቻቸውን፡መጥተው፡እንዲያግዟቸው፡ጠቀሱ፤መጥተውም፡ኹለቱ፡ታንኳዎች፡እ ስኪሰጥሙ፡ድረስ፡ሞሏቸው።
8፤ስምዖን፡ጴጥሮስ፡ግን፡ባየ፡ጊዜ፡በኢየሱስ፡ጕልበት፡ላይ፡ወድቆ፦ጌታ፡ሆይ፥እኔ፡ኀጢአተኛ፡ነኝና፡ከእኔ፡ ተለይ፡አለው።
9፤ስላጠመዱት፡ዓሣ፡ርሱ፡ከርሱ፡ጋራም፡የነበሩ፡ዅሉ፡ተደንቀዋልና፥
10፤እንዲሁም፡ደግሞ፡የስምዖን፡ባልንጀራዎች፡የነበሩ፡የዘብዴዎስ፡ልጆች፡ያዕቆብና፡ዮሐንስም፡ተደነቁ።ኢየ ሱስም፡ስምዖንን፦አትፍራ፤ከእንግዲህ፡ወዲህ፡ሰውን፡የምታጠምድ፡ትኾናለኽ፡አለው።
11፤ታንኳዎችንም፡ወደ፡ምድር፡አድርሰው፡ዅሉን፡ትተው፡ተከተሉት።
12፤ከከተማዎችም፡በአንዲቱ፡ሳለ፥እንሆ፥ለምጽ፡የሞላበት፡ሰው፡ነበረ፤ኢየሱስንም፡አይቶ፡በፊቱ፡ወደቀና፦ጌ ታ፡ሆይ፥ብትወድስ፥ልታነጻኝ፡ትችላለኽ፡ብሎ፡ለመነው።
13፤እጁንም፡ዘርግቶ፡ዳሰሰውና፦እወዳለኹ፥ንጻ፡አለው፤ወዲያውም፡ለምጹ፡ለቀቀው።
14፤ርሱም፡ለማንም፡እንዳይናገር፡አዘዘው፥ነገር፡ግን፦ኼደኽ፡ራስኽን፡ለካህን፡አሳይ፥ለእነርሱም፡ምስክር፡ እንዲኾን፡ስለ፡መንጻትኽ፡ሙሴ፡እንዳዘዘ፡መሥዋዕት፡አቅርብ፡አለው።
15፤ወሬው፡ግን፡አብዝቶ፡ወጣ፥ብዙ፡ሕዝብም፡ሊሰሙትና፡ከደዌያቸው፡ሊፈወሱ፡ይሰበሰቡ፡ነበር፤
16፤ነገር፡ግን፥ርሱ፡ወደ፡ምድረ፡በዳ፡ፈቀቅ፡ብሎ፡ይጸልይ፡ነበር።
17፤አንድ፡ቀንም፡ያስተምር፡ነበር፤ከገሊላና፡ከይሁዳ፡መንደሮችም፡ዅሉ፡ከኢየሩሳሌምም፡መጥተው፡የነበሩ፡ፈ ሪሳውያንና፡የሕግ፡መምህራን፡ይቀመጡ፡ነበር፤ርሱም፡እንዲፈውስ፡የጌታ፡ኀይል፡ኾነለት።
18፤እንሆም፥አንድ፡ሽባ፡በዐልጋ፡ተሸክመው፡አመጡ፤አግብተውም፡በፊቱ፡ሊያኖሩት፡ይሹ፡ነበር።
19፤ስለ፡ሕዝቡም፡ብዛት፡እንዴት፡አድርገው፡እንዲያገቡት፡ሲያቅታቸው፥ወደ፡ሰገነቱ፡ወጡ፡የጣራውንም፡ጡብ፡ አሳልፈው፡በመካከል፡በኢየሱስ፡ፊት፡ከነዐልጋው፡አወረዱት።
20፤እምነታቸውንም፡አይቶ፦አንተ፡ሰው፥ኀጢአትኽ፡ተሰረየችልኽ፡አለው።
21፤ጻፊዎችና፡ፈሪሳውያንም፦ይህ፡የሚሳደብ፡ማን፡ነው፧ከአንዱ፡ከእግዚአብሔር፡በቀር፡ኀጢአት፡ሊያስተሰርይ ፡ማን፡ይችላል፧ብለው፡ያስቡ፡ዠመር።
22፤ኢየሱስም፡ዐሳባቸውን፡እያወቀ፡መልሶ፦በልባችኹ፡ምን፡ታስባላችኹ፧
23፤ኀጢአትኽ፡ተሰረየችልኽ፡ከማለት፡ወይስ፦ተነሣና፡ኺድ፡ከማለት፡ማናቸው፡ይቀላል፧
24፤ነገር፡ግን፥በምድር፡ላይ፡ኀጢአት፡ሊያስተሰርይ፡ለሰው፡ልጅ፡ሥልጣን፡እንዳለው፡እንድታውቁ፡ብሎ፥ሽባው ን፦አንተን፡እልኻለኹ፥ተነሣ፥ዐልጋኽን፡ተሸክመኽ፡ወደ፡ቤትኽ፡ኺድ፡አለው።
25፤በዚያን፡ጊዜም፡በፊታቸው፡ተነሣ፥ተኝቶበትም፡የነበረውን፡ተሸክሞ፡እግዚአብሔርን፡እያመሰገነ፡ወደ፡ቤቱ ፡ኼደ።
26፤ዅሉንም፡መገረም፡ያዛቸው፥እግዚአብሔርንም፡አመስግነው።ዛሬስ፡ድንቅ፡ነገር፡አየን፡እያሉ፡ፍርሀት፡ሞላ ባቸው።
27፤ከዚህም፡በዃላ፡ወጥቶ፡ሌዊ፡የሚባል፡ቀራጭ፡በመቅረጫው፡ተቀምጦ፡ተመለከተና፦ተከተለኝ፡አለው።
28፤ዅሉንም፡ተወ፤ተነሥቶም፡ተከተለው።
29፤ሌዊም፡በቤቱ፡ታላቅ፡ግብዣ፡አደረገለት፤ከነርሱም፡ጋራ፡በማእዱ፡ተቀምጠው፡የነበሩ፡ከቀራጮችና፡ከሌላዎ ች፡ሰዎች፡ብዙ፡ሕዝብ፡ነበሩ።
30፤ፈሪሳውያንና፡ጻፊዎቻቸውም፡በደቀ፡መዛሙርቱ፡ላይ፦ስለ፡ምን፡ከቀራጮችና፡ከኀጢአተኛዎች፡ጋራ፡ትበላላች ኹ፡ትጠጡማላችኹ፧ብለው፡አንጐራጐሩ።
31፤ኢየሱስም፡መልሶ፦ሕመምተኛዎች፡እንጂ፡ባለጤናዎች፡ባለመድኀኒት፡አያስፈልጋቸውም፤
32፤ኀጢአተኛዎችን፡ወደ፡ንስሓ፡እንጂ፡ጻድቃንን፡ልጠራ፡አልመጣኹም፡አላቸው።
33፤እነርሱም፦የዮሐንስ፡ደቀ፡መዛሙርት፡ስለ፡ምን፡ብዙ፡ይጦማሉ፡ጸሎትስ፡ስለ፡ምን፡ያደርጋሉ፥ደግሞም፡የፈ ሪሳውያን፡ደቀ፡መዛሙርት፡ስለ፡ምን፡እንደዚሁ፡ያደርጋሉ፤የአንተ፡ደቀ፡መዛሙርት፡ግን፡ይበላሉ፡ይጠጣሉም፧ አሉት።
34፤ኢየሱስም፦ሙሽራው፡ከነርሱ፡ጋራ፡ሳለ፡ሚዜዎችን፡ልታስጦሙ፡ትችላላችኹን፧
35፤ነገር፡ግን፥ወራት፡ይመጣል፥ሙሽራውም፡ከነርሱ፡ሲወሰድ፡ያን፡ጊዜ፥በዚያ፡ወራት፡ይጦማሉ፡አላቸው።
36፤ደግሞም፡ምሳሌ፡እንዲህ፡ሲል፡ነገራቸው፦የዐዲስ፡ልብስ፡ዕራፊ፡ባረጀ፡ልብስ፡ላይ፡የሚያኖር፡የለም፤ቢደ ረግ፡ግን፡ዐዲሱን፡ይቀደዋል፡ደግሞም፡ዐዲስ፡ዕራፊ፡ለአሮጌው፡አይስማማውም።
37፤ባረጀ፡አቍማዳም፡ዐዲስ፡የወይን፡ጠጅ፡የሚያኖር፡የለም፤ቢደረግ፡ግን፡ዐዲሱ፡የወይን፡ጠጅ፡አቍማዳውን፡ ያፈነዳል፥ርሱም፡ይፈሳል፡አቍማዳውም፡ይጠፋል።
38፤ዐዲሱን፡የወይን፡ጠጅ፡ግን፡በዐዲስ፡አቍማዳ፡ማኖር፡ይገ፟ባ፟ል፥ኹለቱም፡ይጠባበቃሉ።
39፤አሮጌ፡የወይን፡ጠጅ፡ሲጠጣ፡ዐዲሱን፡የሚሻ፡ማንም፡የለም፤አሮጌው፡ይጣፍጣል፡ይላልና።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡6።______________
ምዕራፍ፡6፤
1፤በሰንበትም፡በዕርሻ፡መካከል፡ያልፍ፡ነበር፡ደቀ፡መዛሙርቱም፡እሸት፡ይቀጥፉ፡በእጃቸውም፡እያሹ፡ይበሉ፡ነ በር።
2፤ከፈሪሳውያን፡ግን፡አንዳንዶቹ፦በሰንበት፡ሊያደርግ፡ያልተፈቀደውን፡ስለ፡ምን፡ታደርጋላችኹ፧አሏቸው።
3-4፤ኢየሱስም፡ለእነርሱ፡መልሶ፦ዳዊት፡በተራበ፡ጊዜ፡ርሱ፡ዐብረውት፡ከነበሩ፡ጋራ፡ያደረገውን፥ወደእግዚአብ ሔር፡ቤት፡እንደ፡ገባ፡ከካህናት፡ብቻ፡በቀር፡መብላቱ፡ያልተፈቀደውን፡የመሥዋዕትን፡እንጀራ፡ይዞ፡እንደ፡በ ላ፥ከርሱም፡ጋራ፡ለነበሩት፡ደግሞ፡እንደ፡ሰጣቸው፡ይህን፡አላነበባችኹምን፧አለ።
5፤የሰው፡ልጅ፡የሰንበት፡ጌታ፡ነው፡አላቸውም።
6፤በሌላው፡ሰንበትም፡ወደ፡ምኵራብ፡ገብቶ፡አስተማረ፤በዚያም፡ቀኝ፡እጁ፡የሰለለች፡ሰው፡ነበረ፤
7፤ጻፊዎችና፡ፈሪሳውያንም፡መክሰሻ፡ሊያገኙበት፡በሰንበት፡ይፈውስ፡እንደ፡ኾነ፡ይጠባበቁት፡ነበር።
8፤ርሱ፡ግን፡ዐሳባቸውን፡ዐውቆ፡እጁ፡የሰለለችውን፡ሰው፦ተነሣና፡በመካከል፡ቁም፡አለው፤ተነሥቶም፡ቆመ።
9፤ኢየሱስም፦እጠይቃችዃለኹ፤በሰንበት፡በጎ፡ማድረግ፡ተፈቅዷልን፡ወይስ፡ክፉ፧ነፍስ፡ማዳንን፡ወይስ፡መግደል ፧አላቸው።
10፤ኹላቸውንም፡ዙሪያውን፡አየና፡ሰውዬውን፦እጅኽን፡ዘርጋ፡አለው።ርሱም፡እንዲህ፡አደረገ፥እጁም፡እንደ፡ኹ ለተኛዪቱ፡ዳነች።
11፤እነርሱም፡ቍጣ፡ሞላባቸው፥በኢየሱስም፡ምን፡እንዲያደርጉበት፡ርስ፡በርሳቸው፡ተባባሉ።
12፤በነዚህም፡ወራት፡ይጸልይ፡ዘንድ፡ወደ፡ተራራ፡ወጣ፥ሌሊቱንም፡ዅሉ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ሲጸልይ፡ዐደረ።
13፤በነጋም፡ጊዜ፡ደቀ፡መዛሙርቱን፡ጠራ፥ከነርሱም፡ዐሥራ፡ኹለት፡መረጠ፡ደግሞም፡ሐዋርያት፡ብሎ፡ሰየማቸው፤
14፤እነርሱም፥ጴጥሮስ፡ብሎ፡እንደ፡ገና፡የሰየመው፡ስምዖን፥ወንድሙም፡እንድርያስ፥ያዕቆብም፡ዮሐንስም፥ፊል ጶስም፡በርተሎሜዎስም፥
15፤ማቴዎስም፡ቶማስም፥የእልፍዮስ፡ልጅ፡ያዕቆብም፡ቀናተኛ፡የሚባለው፡ስምዖንም፥
16፤የያዕቆብ፡ይሁዳም፥አሳልፎ፡የሰጠውም፡የአስቆሮቱ፡ይሁዳ፡ናቸው።
17፤ከነርሱም፡ጋራ፡ወርዶ፡በተካከለ፡ስፍራ፡ቆመ፥ከደቀ፡መዛሙርቱም፡ወገን፡ብዙ፡ሕዝብ፡ነበረ፥ደግሞም፡ሊሰ ሙትና፡ከደዌያቸው፡ሊፈወሱ፡ከይሁዳ፡ዅሉ፡ከኢየሩሳሌምም፡ከጢሮስና፡ከሲዶና፡ባሕር፡ዳርም፡የመጡ፡ብዙ፡ሰዎ ች፡ነበሩ፤
18፤ከርኩሳንም፡መናፍስት፡ይሠቃዩ፡የነበሩት፡ተፈወሱ፤
19፤ከርሱም፡ኀይል፡ወጥቶ፡ዅሉን፡ይፈውስ፡ነበርና፥ሕዝቡ፡ዅሉ፡ሊዳስሱት፡ይሹ፡ነበር።
20፤ርሱም፡ወደ፡ደቀ፡መዛሙርቱ፡ዐይኑን፡አነሣ፡እንዲህም፡አላቸው፦እናንተ፡ድኻዎች፡ብፁዓን፡ናችኹ፥የእግዚ አብሔር፡መንግሥት፡የእናንተ፡ነውና።
21፤እናንተ፡አኹን፡የምትራቡ፡ብፁዓን፡ናችኹ፥ትጠግባላችኹና።እናንተ፡አኹን፡የምታለቅሱ፡ብፁዓን፡ናችኹ፥ት ሥቃላችኹና።
22፤ሰዎች፡ስለሰው፡ልጅ፡ሲጠሏችኹ፡ሲለይዋችኹም፡ሲነቅፏችኹም፡ስማችኹንም፡እንደ፡ክፉ፡ሲያወጡ፥ብፁዓን፡ና ችኹ።
23፤እንሆ፥ዋጋችኹ፡በሰማይ፡ታላቅ፡ነውና፥በዚያን፡ቀን፡ደስ፡ይበላችኹ፡ዝለሉም፤አባቶቻቸው፡ነቢያትን፡እን ዲህ፡ያደርጉባቸው፡ነበርና።
24፤ነገር፡ግን፥እናንተ፡ባለጠጋዎች፡ወዮላችኹ፥መጽናናታችኹን፡ተቀብላችዃልና።
25፤እናንተ፡አኹን፡የጠገባችኹ፡ወዮላችኹ፥ትራባላችኹና።እናንተ፡አኹን፡የምትሥቁ፡ወዮላችኹ፥ታዝናላችኹና፡ ታለቅሱማላችኹ።
26፤ሰዎች፡ዅሉ፡መልካም፡ሲናገሩላችኹ፥ወዮላችኹ፤አባቶቻቸው፡ለሐሰተኛዎች፡ነቢያት፡እንዲሁ፡ያደርጉላቸው፡ ነበርና።
27፤ነገር፡ግን፥ለእናንተ፡ለምትሰሙ፡እላችዃለኹ፥ጠላቶቻችኹን፡ውደዱ፥ለሚጠሏችኹ፡መልካም፡አድርጉ፥
28፤የሚረግሟችኹንም፡መርቁ፥ስለሚበድሏችኹም፡ጸልዩ።
29፤ጕንጭኽን፡ለሚመታኽ፡ደግሞ፡ኹለተኛውን፡ስጠው፥መጐናጸፊያኽንም፡ለሚወስድ፡እጀ፡ጠባብኽን፡ደግሞ፡አትከ ልክለው።
30፤ለሚለምንኽ፡ዅሉ፡ስጥ፥ገንዘብኽንም፡የሚወስድ፡እንዲመልስ፡አትጠይቀው።
31፤ሰዎችም፡ሊያደርጉላችኹ፡እንደምትወዱ፡እናንተ፡ደግሞ፡እንዲሁ፡አድርጉላቸው።
32፤የሚወዷ፟ችኹንማ፡ብትወዱ፥ምን፡ምስጋና፡አላችኹ፧ኀጢአተኛዎች፡ደግሞ፡የሚወዷ፟ቸውን፡ይወዳሉና።
33፤መልካምም፡ለሚያደርጉላችኹ፡መልካም፡ብታደርጉ፥ምን፡ምስጋና፡አላችኹ፧ኀጢአተኛዎች፡ደግሞ፡ያን፡ያደርጋ ሉና።
34፤እንድትወስዱባቸው፡ተስፋ፡ለምታደርጓቸው፡ብታበድሩ፥ምን፡ምስጋና፡አላችኹ፧ኀጢአተኛዎች፡ደግሞ፡በትክክ ል፡እንዲቀበሉ፡ለኀጢአተኛዎች፡ያበድራሉ።
35፤ነገር፡ግን፥ጠላቶቻችኹን፡ውደዱ፤መልካም፡አድርጉ፤ምንም፡ተስፋ፡ሳታደርጉም፡አበድሩ፥ዋጋችኹም፡ታላቅ፡ ይኾናል፥የልዑልም፡ልጆች፡ትኾናላችኹ፥ርሱ፡ለማያመሰግኑ፡ለክፉዎችም፡ቸር፡ነውና።
36፤አባታችኹ፡ርኅሩኅ፡እንደ፡ኾነ፡ርኅሩኆች፡ኹኑ።
37፤አትፍረዱ፡አይፈረድባችኹምም፤አትኰንኑ፡አትኰነኑምም።ይቅር፡በሉ፡ይቅርም፡ትባላላችኹ።
38፤ስጡ፡ይሰጣችኹማል፤በምትሰፍሩበት፡መስፈሪያ፡ተመልሶ፡ይሰፈርላችዃልና፥የተጨቈነና፡የተነቀነቀ፡የተትረ ፈረፈም፡መልካም፡መስፈሪያ፡በዕቅፋችኹ፡ይሰጣችዃል።
39፤ምሳሌም፡አላቸው፦ዕውር፡ዕውርን፡ሊመራ፡ይችላልን፧ኹለቱ፡በጕድጓድ፡አይወድቁምን፧
40፤ደቀ፡መዝሙር፡ከመምህሩ፡አይበልጥም፤ፈጽሞ፡የተማረ፡ዅሉ፡ግን፡እንደ፡መምህሩ፡ይኾናል።
41፤በወንድምኽም፡ዐይን፡ያለውን፡ጕድፍ፡ስለ፡ምን፡ታያለኽ፥በራስኽ፡ዐይን፡ግን፡ያለውን፡ምሰሶ፡ስለ፡ምን፡ አትመለከትም፧
42፤በዐይንኽ፡ያለውን፡ምሰሶ፡ራስኽ፡ሳታይ፥እንዴት፡ወንድምኽን፦ወንድሜ፡ሆይ፥በዐይንኽ፡ያለውን፡ጕድፍ፡ላ ውጣ፡ፍቀድልኝ፡ልትል፡ትችላለኽ፧አንተ፡ግብዝ፥አስቀድመኽ፡ከዐይንኽ፡ምሰሶውን፡አውጣ፡ከዚያም፡በዃላ፡በወ ንድምኽ፡ዐይን፡ያለውን፡ጕድፍ፡ታወጣ፡ዘንድ፡አጥርተኽ፡ታያለኽ።
43፤ክፉ፡ፍሬ፡የሚያደርግ፡መልካም፡ዛፍ፡የለምና፥እንዲሁም፡መልካም፡ፍሬ፡የሚያደርግ፡ክፉ፡ዛፍ፡የለም።
44፤ዛፍ፡ዅሉ፡ከፍሬው፡ይታወቃልና፤ከሾኽ፡በለስ፡አይለቅሙም፥ከዐጣጥ፡ቍጥቋጦም፡ወይን፡አይቈርጡም።
45፤በልብ፡ሞልቶ፡ከተረፈው፡አፉ፡ይናገራልና፥መልካም፡ሰው፡ከልብ፡መልካም፡መዝገብ፡መልካሙን፡ያወጣል፥ክፉ ፡ሰውም፡ከልብ፡ክፉ፡መዝገብ፡ክፉውን፡ያወጣል።
46፤ስለ፡ምን፦ጌታ፡ሆይ፥ጌታ፡ሆይ፥ትሉኛላችኹ፥የምለውንም፡አታደርጉም፧
47፤ወደ፡እኔ፡የሚመጣ፡ዅሉ፡ቃሌንም፡ሰምቶ፡የሚያደርገው፥ማንን፡እንዲመስል፡አሳያችዃለኹ።
48፤ቤት፡ሲሠራ፡አጥልቆ፡የቈፈረ፡በአለት፡ላይም፡የመሠረተ፡ሰውን፡ይመስላል፤ጐርፍም፡በመጣ፡ጊዜ፡ወንዙ፡ያ ን፡ቤት፡ገፋው፥በአለት፡ላይም፡ስለ፡ተመሠረተ፡ሊያናውጠው፡አልቻለም።
49፤ሰምቶ፡የማያደርገው፡ግን፡ያለመሠረት፡በምድር፡ላይ፡ቤቱን፡የሠራ፡ሰውን፡ይመስላል፤ወንዙም፡ገፋው፡ወዲ ያውም፡ወደቀ፡የዚያ፡ቤት፡አወዳደቅም፡ታላቅ፡ኾነ።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡7።______________
ምዕራፍ፡7፤
1፤ቃሉን፡ዅሉ፡በሕዝብ፡ዦሮዎች፡በጨረሰ፡ጊዜ፡ወደ፡ቅፍርናሖም፡ገባ።
2፤አንድ፡የመቶ፡አለቃም፡ነበረ፤የሚወደ፟ውም፡ባሪያው፡ታሞ፡ሊሞት፡ቀርቦ፡ነበር።
3፤ስለ፡ኢየሱስም፡በሰማ፡ጊዜ፡የአይሁድን፡ሽማግሌዎች፡ወደ፡ርሱ፡ላከና፡መጥቶ፡ባሪያውን፡እንዲያድን፡ለመነ ው።
4፤እነርሱም፡ወደ፡ኢየሱስ፡መጥተው፦ይህን፡ልታደርግለት፡ይገ፟ባ፟ዋል፤
5፤ሕዝባችንን፡ይወዳልና፥ምኵራብም፡ራሱ፡ሠርቶልናል፡ብለው፡አጽንተው፡ለመኑት።
6፤ኢየሱስም፡ከነርሱ፡ጋራ፡ኼደ።አኹንም፡ወደ፡ቤቱ፡በቀረበ፡ጊዜ፡የመቶው፡አለቃ፡ወዳጆቹን፡ወደ፡ርሱ፡ላከ፤ አለውም፦ጌታ፡ሆይ፡በቤቴ፡ጣራ፡በታች፡ልትገባ፡አይገ፟ባ፟ኝምና፥አትድከም፤
7፤ስለዚህም፡ወዳንተ፡ልመጣ፡እንዲገባኝ፡ሰውነቴን፡አልቈጠርኹትም፤ነገር፡ግን፥ቃል፡ተናገር፥ብላቴናዬም፡ይ ፈወሳል።
8፤እኔ፡ደግሞ፡ከሌላዎች፡በታች፡የምገዛ፡ሰው፡ነኝ፥ከእኔም፡በታች፡ወታደሮች፡አሉኝ፥አንዱንም፦ኺድ፡ብለው፡ ይኼዳል፥ሌላውንም፦ና፡ብለው፡ይመጣል፥ባሪያዬንም፦ይህን፡አድርግ፡ብለው፡ያደርጋል።
9፤ኢየሱስም፡ይህን፡ሰምቶ፡በርሱ፡ተደነቀ፥ዘወርም፡ብሎ፡ለተከተሉት፡ሕዝብ፦እላችዃለኹ፥በእስራኤልስ፡እንኳ ፡እንዲህ፡ያለ፡ትልቅ፡እምነት፡አላገኘኹም፡አላቸው።
10፤የተላኩትም፡ወደ፡ቤት፡ተመልሰው፡ባሪያውን፡ባለጤና፡ኾኖ፡አገኙት።
11፤በነገውም፡ናይን፡ወደምትባል፡ወደ፡አንዲት፡ከተማ፡ኼደ፥ደቀ፡መዛሙርቱም፡ብዙ፡ሕዝብም፡ከርሱ፡ጋራ፡ዐብ ረው፡ኼዱ።
12፤ወደ፡ከተማዪቱም፡በር፡በቀረበ፡ጊዜ፥እንሆ፥የሞተ፡ሰው፡ተሸክመው፡አወጡ፤ርሱም፡ለእናቱ፡አንድ፡ልጅ፡ነ በረ፥ርሷም፡መበለት፡ነበረች፥ብዙም፡የከተማ፡ሕዝብ፡ከርሷ፡ጋራ፡ዐብረው፡ነበሩ።
13፤ጌታም፡ባያት፡ጊዜ፡ዐዘነላትና፦አታልቅሺ፡አላት።
14፤ቀርቦም፡ቃሬዛውን፡ነካ፥የተሸከሙትም፡ቆሙ፤አለውም፦አንተ፡ጐበዝ፥እልኻለኹ፥ተነሣ።
15፤የሞተውም፡ቀና፡ብሎ፡ተቀመጠ፡ሊናገርም፡ዠመረ፥ለእናቱም፡ሰጣት።
16፤ዅሉንም፡ፍርሀት፡ያዛቸውና፦ታላቅ፡ነቢይ፡በእኛ፡መካከል፡ተነሥቷል፥ደግሞ፦እግዚአብሔር፡ሕዝቡን፡ጐበኘ ፡እያሉ፡እግዚአብሔርን፡አመሰገኑ።
17፤ይህም፡ዝና፡ስለ፡ርሱ፡በይሁዳ፡ዅሉ፡በዙሪያውም፡ባለች፡አገር፡ዅሉ፡ወጣ።
18፤ደቀ፡መዛሙርቱም፡ለዮሐንስ፡እነዚህን፡ዅሉ፡አወሩ።
19፤ዮሐንስም፡ከደቀ፡መዛሙርቱ፡ኹለት፡ወደ፡ርሱ፡ጠርቶ፦የሚመጣው፡አንተ፡ነኽን፡ወይስ፡ሌላውን፡እንጠብቅ፧ ብሎ፡ወደ፡ኢየሱስ፡ላከ።
20፤ሰዎቹም፡ወደ፡ርሱ፡መጥተው፦መጥምቁ፡ዮሐንስ፦የሚመጣው፡አንተ፡ነኽን፡ወይስ፡ሌላውን፡እንጠብቅ፧ብሎ፡ወ ዳንተ፡ላከን፡አሉት።
21፤በዚያች፡ሰዓት፡ከደዌና፡ከሥቃይ፡ከክፉዎች፡መናፍስትም፡ብዙዎችን፡ፈወሰ፥ለብዙ፡ዕውሮችም፡ማየትን፡ሰጠ ።
22፤ኢየሱስም፡መልሶ፦ኼዳችኹ፡ያያችኹትን፡የሰማችኹትንም፡ለዮሐንስ፡አውሩለት፤ዕውሮች፡ያያሉ፥ዐንካሳዎችም ፡ይኼዳሉ፥ለምጻሞችም፡ይነጻሉ፥ደንቈሮዎችም፡ይሰማሉ፥ሙታንም፡ይነሣሉ፥ለድኻዎችም፡ወንጌል፡ይሰበካል፤
23፤በእኔም፡የማይሰናከለው፡ዅሉ፡ብፁዕ፡ነው፡አላቸው።
24፤የዮሐንስ፡መልክተኛዎችም፡ከኼዱ፡በዃላ፥ለሕዝቡ፡ስለ፡ዮሐንስ፡ይናገር፡ዠመር፡እንዲህም፡አለ፦ምን፡ልታ ዩ፡ወደ፡ምድረ፡በዳ፡ወጣችኹ፧ነፋስ፡የሚወዘውዘውን፡ሸምበቆን፧ወይስ፡ምን፡ልታዩ፡ወጣችኹ፧
25፤ቀጭን፡ልብስ፡የለበሰውን፡ሰውን፧እንሆ፥ጌጠኛ፡ልብስ፡የሚለብሱና፡በቅምጥልነት፡የሚኖሩ፡በነገሥታት፡ቤ ት፡አሉ።
26፤ወይስ፡ምን፡ልታዩ፡ወጣችኹ፧ነቢይን፧አዎን፡እላችዃለኹ፥ከነቢይም፡የሚበልጠውን።
27፤እንሆ፥መንገድኽን፡በፊትኽ፡የሚጠርግ፡መልክተኛዬን፡በፊትኽ፡እልካለኹ፡ተብሎ፡የተጻፈለት፡ይህ፡ነው።
28፤እላችዃለኹ፥ከሴቶች፡ከተወለዱት፡መካከል፡ከመጥምቁ፡ዮሐንስ፡የሚበልጥ፡ማንም፡የለም፤በእግዚአብሔር፡መ ንግሥት፡ግን፡ከዅሉ፡የሚያንሰው፡ይበልጠዋል።
29፤የሰሙትም፡ሕዝብ፡ዅሉ፡ቀራጮች፡እንኳ፡ሳይቀሩ፡በዮሐንስ፡ጥምቀት፡ተጠምቀው፡እግዚአብሔርን፡አጸደቁ፤
30፤ፈሪሳውያንና፡ሕግ፡ዐዋቂዎች፡ግን፡በርሱ፡ስላልተጠመቁ፡የእግዚአብሔርን፡ምክር፡ከራሳቸው፡ጣሉ።
31፤እንግዲህ፡የዚችን፡ትውልድ፡ሰዎች፡በምን፡አስመስላቸዋለኹ፧ማንንስ፡ይመስላሉ፧
32፤በገበያ፡የሚቀመጡትን፡ልጆች፡ይመስላሉ፥ርስ፡በርሳቸውም፡እየተጠራሩ።እንቢልታ፡ነፋንላችኹ፡አልዘፈናች ኹምም፤ሙሾ፡አወጣንላችኹ፡አላለቀሳችኹምም፡ይላል።
33፤መጥምቁ፡ዮሐንስ፡እንጀራ፡ሳይበላ፡የወይን፡ጠጅም፡ሳይጠጣ፡መጥቶ፡ነበርና፦ጋኔን፡አለበት፡አላችኹት።
34፤የሰው፡ልጅ፡እየበላና፡እየጠጣ፡መጥቷልና፦እንሆ፥በላተኛና፡የወይን፡ጠጅ፡ጠጪ፥የቀራጮችና፡የኀጢአተኛዎ ች፡ወዳጅ፡አላችኹት።
35፤ጥበብም፡ለልጆቿ፡ዅሉ፡ጸደቀች።
36፤ከፈሪሳውያንም፡አንድ፡ከርሱ፡ጋራ፡ይበላ፡ዘንድ፡ለመነው፤በፈሪሳዊው፡ቤትም፡ገብቶ፡በማእዱ፡ተቀመጠ።
37፤እንሆም፡በዚያች፡ከተማ፡ኀጢአተኛ፡የነበረች፡አንዲት፡ሴት፤በፈሪሳዊው፡ቤት፡በማእዱ፡እንደ፡ተቀመጠ፡ባ ወቀች፡ጊዜ፥ሽቱ፡የሞላበት፡የአልባስጥሮስ፡ቢልቃጥ፡አመጣች።
38፤በስተዃላውም፡በእግሩ፡አጠገብ፡ቆማ፡እያለቀሰች፡በእንባዋ፡እግሩን፡ታርስ፡ዠመር፥በራስ፡ጠጕሯም፡ታብሰ ው፡እግሩንም፡ትስመው፡ሽቱም፡ትቀባው፡ነበር።
39፤የጠራው፡ፈሪሳዊም፡አይቶ፦ይህስ፡ነቢይ፡ቢኾን፥ይህች፡የምትዳስሰው፡ሴት፡ማን፡እንደ፡ኾነች፡እንዴትስ፡ እንደ፡ነበረች፡ባወቀ፡ነበር፥ኀጢአተኛ፡ናትና፥ብሎ፡በልቡ፡ዐሰበ።
40፤ኢየሱስም፡መልሶ፦ስምዖን፡ሆይ፥የምነግርኽ፡ነገር፡አለኝ፡አለው።ርሱም፦መምህር፡ሆይ፥ተናገር፡አለ።
41፤ላንድ፡አበዳሪ፡ኹለት፡ተበዳሪዎች፡ነበሩት፡በአንዱ፡ዐምስት፡መቶ፡ዲናር፡ነበረበት፡በኹለተኛውም፡ዐምሳ ።
42፤የሚከፍሉትም፡ቢያጡ፡ለኹለቱም፡ተወላቸው።እንግዲህ፡ከነርሱ፡አብልጦ፡የሚወደ፟ው፡ማንኛው፡ነው፧
43፤ስምዖንም፡መልሶ፦ብዙ፡የተወለቱ፡ይመስለኛል፡አለ።ርሱም፦በእውነት፡ፈረድኽ፡አለው።
44፤ወደ፡ሴቲቱም፡ዘወር፡ብሎ፡ስምዖንን፡እንዲህ፡አለው፦ይህችን፡ሴት፡ታያለኽን፧እኔ፡ወደ፡ቤትኽ፡ገባኹ፥ው ሃ፡ስንኳ፡ለእግሬ፡አላቀረብኽልኝም፤ርሷ፡ግን፡በእንባዋ፡እግሬን፡አራሰች፡በጠጕሯም፡አበሰች።
45፤አንተ፡አልሳምኸኝም፤ርሷ፡ግን፡ከገባኹ፡ዠምራ፡እግሬን፡ከመሳም፡አላቋረጠችም።
46፤አንተ፡ራሴን፡ዘይት፡አልቀባኸኝም፤ርሷ፡ግን፡እግሬን፡ሽቱ፡ቀባች።
47፤ስለዚህ፥እልኻለኹ፥እጅግ፡ወዳ፟ለችና፥ብዙ፡ያለው፡ኀጢአቷ፡ተሰርዮላታል፤ጥቂት፡ግን፡የሚሰረይለት፡ጥቂ ት፡ይወዳል።
48፤ርሷንም፦ኀጢአትሽ፡ተሰርዮልሻል፡አላት።
49፤ከርሱም፡ጋራ፡በማእዱ፡ተቀምጠው፡የነበሩት፡በልባቸው፦ኀጢአትን፡እንኳ፡የሚያስተሰርይ፡ይህ፡ማን፡ነው፧ ይሉ፡ዠመር።
50፤ሴቲቱንም፦እምነትሽ፡አድኖሻል፤በሰላም፡ኺጂ፡አላት።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡8።______________
ምዕራፍ፡8፤
1፤ከዚህም፡በዃላ፡እየሰበከና፡ስለእግዚአብሔር፡መንግሥት፡የምሥራች፡እየተናገረ፡በየከተማዪቱ፡በየመንደሩም ፡ያልፍ፡ነበር፤
2፤ዐሥራ፡ኹለቱም፡ከርሱ፡ጋራ፡ነበሩ፥ከክፉዎች፡መናፍስትና፡ከደዌም፡ተፈውሰው፡የነበሩ፡አንዳንድ፡ሴቶች፤እ ነርሱም፡ሰባት፡አጋንንት፡የወጡላት፡መግደላዊት፡የምትባል፡ማርያም፥
3፤የሄሮድስ፡አዛዥ፡የኩዛ፡ሚስት፡ዮሐናም፡ሶስናም፡ብዙዎች፡ሌላዎችም፡ኾነው፡በገንዘባቸው፡ያገለግሉት፡ነበ ር።
4፤ብዙ፡ሕዝብም፡በተሰበሰቡ፡ጊዜ፡ከከተማዎችም፡ዅሉ፡ወደ፡ርሱ፡በመጡ፡ጊዜ፡በምሳሌ፡እንዲህ፡ሲል፡ተናገራቸ ው፦
5፤ዘሪ፡ዘሩን፡ሊዘራ፡ወጣ።ሲዘራም፡አንዳንዱ፡በመንገድ፡ዳር፡ወደቀ፡ተረገጠም፥የሰማይ፡ወፎችም፡በሉት።
6፤ሌላውም፡በአለት፡ላይ፡ወደቀ፥በበቀለም፡ጊዜ፡ርጥበት፡ስላልነበረው፡ደረቀ።
7፤ሌላውም፡በሾኽ፡መካከል፡ወደቀ፥ሾኹም፡ዐብሮ፡በቀለና፡ዐነቀው።
8፤ሌላውም፡በመልካም፡መሬት፡ላይ፡ወደቀ፤በበቀለም፡ጊዜ፡መቶ፡ዕጥፍ፡አፈራ።ይህን፡በተናገረ፡ጊዜ፦የሚሰማ፡ ዦሮ፡ያለው፡ይስማ፡ብሎ፡ጮኸ።
9፤ደቀ፡መዛሙርቱም፦ይህ፡ምሳሌ፡ምንድር፡ነው፧ብለው፡ጠየቁት።
10፤ርሱም፡እንዲህ፡አለ፦ለእናንተ፡የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡ምስጢር፡ማወቅ፡ተሰጥቷችዃል፤ለሌላዎች፡ግን ፡እያዩ፡እንዳያዩ፡እየሰሙም፡እንዳያስተውሉ፡በምሳሌ፡ነው።
11፤ምሳሌው፡ይህ፡ነው።ዘሩ፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ነው።
12፤በመንገድ፡ዳርም፡ያሉት፡የሚሰሙ፡ናቸው፤ከዚህ፡በዃላም፡ዲያብሎስ፡ይመጣል፡አምነውም፡እንዳይድኑ፡ቃሉን ፡ከልባቸው፡ይወስዳል።
13፤በአለት፡ላይም፡ያሉት፡ሲሰሙ፡ቃሉን፡በደስታ፡የሚቀበሉ፡ናቸው፤እነርሱም፡ለጊዜው፡ብቻ፡ያምናሉ፡እንጂ፡ በፈተና፡ጊዜ፡የሚክዱ፡ሥር፡የሌላቸው፡ናቸው።
14፤በሾኽ፡መካከልም፡የወደቀ፡እነዚህ፡የሚሰሙት፡ናቸው፤መንገዳቸውንም፡ኼደው፡በሕይወት፡ዘመን፡በዐሳብና፡ በባለጠግነት፡ምቾት፡ይታነቃሉ፥ሙሉ፡ፍሬም፡አያፈሩም።
15፤በመልካም፡መሬት፡ላይም፡የወደቀ፡እነርሱ፡በመልካምና፡በበጎ፡ልብ፡ቃሉን፡ሰምተው፡የሚጠብቁት፡በመጽናት ም፡ፍሬ፡የሚያፈሩ፡ናቸው።
16፤መብራትንም፡አብርቶ፡በዕቃ፡የሚከድነው፡ወይም፡ከዐልጋ፡በታች፡የሚያኖረው፡የለም፥የሚገቡት፡ሰዎች፡ብር ሃኑን፡እንዲያዩ፡በመቅረዝ፡ላይ፡ያኖረዋል፡እንጂ።
17፤የማይገለጥ፡የተሰወረ፡የለምና፥የማይታወቅም፡ወደ፡ግልጥም፡የማይመጣ፡የተሸሸገ፡የለም።
18፤እንግዲህ፡እንዴት፡እንድትሰሙ፡ተጠበቁ፤ላለው፡ዅሉ፡ይሰጠዋልና፥ከሌለውም፡ዅሉ፥ያው፡ያለው፡የሚመስለው ፡እንኳ፡ይወሰድበታል።
19፤እናቱና፡ወንድሞቹም፡ወደ፡ርሱ፡መጡ፥ከሕዝቡም፡ብዛት፡የተነሣ፡ሊያገኙት፡አልተቻላቸውም።
20፤እናትኽና፡ወንድሞችኽ፡ሊያዩኽ፡ወደ፟ው፡በውጭ፡ቆመዋል፡ብለው፡ነገሩት።
21፤ርሱም፡መልሶ፦እናቴና፡ወንድሞቼስ፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ሰምተው፡የሚያደርጉት፡እነዚህ፡ናቸው፡አላቸው ።
22፤ከዕለታቱም፡በአንዱ፡ርሱ፡ከደቀ፡መዛሙርቱ፡ጋራ፡ወደ፡ታንኳ፡ገብቶ፦ወደባሕር፡ማዶ፡እንሻገር፡አላቸው፤ ተነሡም።
23፤ሲኼዱም፡አንቀላፋ።ዐውሎ፡ነፋስም፡በባሕር፡ላይ፡ወረደ፥ውሃውም፡ታንኳዪቱን፡ይሞላ፡ነበርና፥ይጨነቁ፡ነ በር።
24፤ቀርበውም፦አቤቱ፥አቤቱ፡ጠፋን፡እያሉ፡አስነሡት።ርሱም፡ነቅቶ፡ነፋሱንና፡የውሃውን፡ማዕበል፡ገሠጻቸው፤ ተዉም፥ጽጥታም፡ኾነ።
25፤ርሱም፦እምነታችኹ፡የት፡ነው፧አላቸው።ፈርተውም፡ተደነቁ፥ርስ፡በርሳቸውም፦እንዲህ፡ነፋሳትንና፡ውሃን፡ እንኳ፡የሚያዝ፡ለርሱም፡የሚታዘዙለት፡ይህ፡ማን፡ነው፧አሉ።
26፤በገሊላም፡አንጻር፡ወዳለችው፡ወደጌርጌሴኖን፡አገር፡በታንኳ፡ደረሱ።
27፤ወደ፡ምድርም፡በወጣ፡ጊዜ፡አጋንንት፡ያደሩበት፡አንድ፡ሰው፡ከከተማ፡ወጥቶ፡ተገናኘው፥ከብዙ፡ዘመንም፡ዠ ምሮ፡ልብስ፡ሳይለብስ፡በመቃብር፡እንጂ፡በቤት፡አይኖርም፡ነበር።
28፤ኢየሱስንም፡ባየ፡ጊዜ፡ጮኾ፡በፊቱ፡ተደፋ፡በታላቅ፡ድምፅም፦የልዑል፡እግዚአብሔር፡ልጅ፡ኢየሱስ፡ሆይ፥ከ አንተ፡ጋራ፡ምን፡አለኝ፧እንዳትሣቀየኝ፡እለምንኻለኹ፡አለ።
29፤ርኩሱን፡መንፈስ፡ከሰውዬው፡እንዲወጣ፡ያዘ፟ው፡ነበርና።ብዙ፡ዘመንም፡ይዞት፡ነበርና፥በሰንሰለትና፡በእ ግር፡ብረትም፡ታስሮ፡ይጠበቅ፡ነበር፤እስራቱንም፡ሰብሮ፡በጋኔኑ፡ወደ፡ምድረ፡በዳ፡ይነዳ፡ነበር።
30፤ኢየሱስም፦ስምኽ፡ማን፡ነው፧ብሎ፡ጠየቀው።ርሱም፡ብዙዎች፡አጋንንት፡ገብተውበት፡ነበርና፦ሌጌዎን፡አለው ።
31፤ወደ፡ጥልቁም፡ሊኼዱ፡እንዳያዛቸው፡ለመኑት።
32፤በዚያም፡በተራራው፡የብዙ፡ዕሪያ፡መንጋ፡ይሰማሩ፡ነበር፤ወደ፡እነርሱም፡ሊገቡ፡እንዲፈቅድላቸው፡ለመኑት ፤ፈቀደላቸውም።
33፤አጋንንትም፡ከሰውዬው፡ወጥተው፡ወደ፡ዕሪያዎች፡ገቡ፥መንጋውም፡ከአፋፉ፡ወደ፡ባሕር፡ተጣደፉና፡ሰጠሙ።
34፤እረኛዎችም፡የኾነውን፡ባዩ፡ጊዜ፡ሸሽተው፡በከተማውና፡በአገሩ፡አወሩት።
35፤የኾነውን፡ነገር፡ሊያዩ፡ወጥተውም፡ወደ፡ኢየሱስ፡መጡ፥አጋንንትም፡የወጡለትን፡ሰው፡ለብሶ፡ልቡም፡ተመል ሶ፡በኢየሱስ፡እግር፡አጠገብ፡ተቀምጦ፡አገኙትና፡ፈሩ።
36፤ያዩትም፡ደግሞ፡አጋንንት፡ያደሩበት፡ሰው፡እንዴት፡እንደ፡ዳነ፡አወሩላቸው።
37፤በዙሪያውም፡በጌርጌሴኖን፡አገር፡ያሉት፡ሕዝብ፡ዅሉ፡ታላቅ፡ፍርሀት፡ይዟቸዋልና፥ከነርሱ፡እንዲኼድ፡ለመ ኑት፡በታንኳም፡ገብቶ፡ተመለሰ።
38፤አጋንንት፡የወጡለት፡ሰውም፡ከርሱ፡ጋራ፡ይኖር፡ዘንድ፡ለመነው፤
39፤ነገር፡ግን፦ወደ፡ቤትኽ፡ተመለስ፥እግዚአብሔር፡እንዴት፡ያለ፡ታላቅ፡ነገር፡እንዳደረገልኽ፡ንገር፡ብሎ፡ አሰናበተው።ኢየሱስም፡እንዴት፡ያለ፡ታላቅ፡ነገር፡እንዳደረገለት፡በከተማው፡ዅሉ፡እየሰበከ፡ኼደ።
40፤ኢየሱስም፡በተመለሰ፡ጊዜ፡ዅሉ፡ይጠብቁት፡ነበርና፥ሕዝቡ፡ተቀበሉት።
41፤እንሆም፥ኢያኢሮስ፡የሚባል፡ሰው፡መጣ፥ርሱም፡የምኵራብ፡አለቃ፡ነበረ፡በኢየሱስም፡እግር፡ላይ፡ወድቆ፡ወ ደ፡ቤቱ፡እንዲገባ፡ለመነው፤
42፤ዐሥራ፡ኹለት፡ዓመት፡የኾናት፡አንዲት፡ሴት፡ልጅ፡ነበረችውና፤ርሷም፡ለሞት፡ቀርባ፡ነበር።ሲኼድም፡ሕዝቡ ፡ያጨናንቁት፡ነበር።
43፤ከዐሥራ፡ኹለት፡ዓመትም፡ዠምሮ፡ደም፡የሚፈሳ፟ት፡ሴት፡ነበረች፥ትዳሯንም፡ዅሉ፡ለባለመድኀኒቶች፡ከስራ፥ ማንም፡ሊፈውሳት፡አልተቻለውም።
44፤በዃላውም፡ቀርባ፡የልብሱን፡ጫፍ፡ዳሰሰች፥የደሟም፡ፈሳሽ፡በዚያን፡ጊዜ፡ቆመ።
45፤ኢየሱስም፦የዳሰሰኝ፡ማን፡ነው፧አለ።ዅሉም፡በካዱ፡ጊዜ፥ጴጥሮስና፡ከርሱ፡ጋራ፡የነበሩት፦አቤቱ፥ሕዝቡ፡ ያጫንቁኻልና፥ያጋፉኽማል፤የዳሰሰኝ፡ማን፡ነው፡ትላለኽን፧አሉ።
46፤ኢየሱስ፡ግን፦አንድ፡ሰው፡ዳሶ፟ኛል፥ኀይል፡ከእኔ፡እንደ፡ወጣ፡እኔ፡ዐውቃለኹና፡አለ።
47፤ሴቲቱም፡እንዳልተሰወረች፡ባየች፡ጊዜ፡እየተንቀጠቀጠች፡መጥታ፡በፊቱ፡ተደፋች፥በምን፡ምክንያትም፡እንደ ፡ዳሰሰችው፡ፈጥናም፡እንደ፡ተፈወሰች፡በሕዝቡ፡ዅሉ፡ፊት፡አወራች።
48፤ርሱም፦ልጄ፡ሆይ፥እምነትሽ፡አድኖሻል፤በሰላም፡ኺጂ፡አላት።
49፤ርሱም፡ገና፡ሲናገር፡አንድ፡ሰው፡ከምኵራብ፡አለቃው፡ቤት፡መጥቶ፦ልጅኽ፡ሞታለች፤እንግዲህ፡መምህሩን፡አ ታድክም፡አለ።
50፤ኢየሱስ፡ግን፡ሰምቶ፦አትፍራ፤እመን፡ብቻ፡ትድንማለች፡ብሎ፡መለሰለት።
51፤ወደ፡ቤትም፡ሲገባ፡ከጴጥሮስና፡ከያዕቆብ፡ከዮሐንስም፡ከብላቴናዪቱም፡አባትና፡እናት፡በቀር፡ማንም፡ከር ሱ፡ጋራ፡ይገባ፡ዘንድ፡አልፈቀደም።
52፤ዅሉም፡እያለቀሱላት፡ዋይ፡ዋይ፡ይሉ፡ነበር።ርሱ፡ግን፦አታልቅሱ፤ተኝታለች፡እንጂ፡አልሞተችም፡አለ።
53፤እንደ፡ሞተችም፡ዐውቀው፡በጣም፡ሣቁበት።
54፤ርሱ፡ግን፡እጇን፡ይዞ፦አንቺ፡ብላቴና፥ተነሺ፡ብሎ፡ጮኸ።
55፤ነፍሷም፡ተመለሰች፥ፈጥናም፡ቆመች፥የምትበላውንም፡እንዲሰጧት፡አዘዘ።
56፤ወላጆቿም፡ተገረሙ፤ርሱ፡ግን፡የኾነውን፡ለማንም፡እንዳይነግሩ፡አዘዛቸው።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡9።______________
ምዕራፍ፡9፤
1፤ዐሥራ፡ኹለቱንም፡ሐዋርያት፡በአንድነት፡ወደ፡ርሱ፡ጠርቶ፡በአጋንንት፡ዅሉ፡ላይ፡ደዌንም፡ይፈውሱ፡ዘንድ፡ ኀይልና፡ሥልጣን፡ሰጣቸው፤
2፤የእግዚአብሔርንም፡መንግሥት፡እንዲሰብኩና፡ድውዮችን፡እንዲፈውሱ፡ላካቸው፥
3፤እንዲህም፡አላቸው፦በትርም፡ቢኾን፥ከረጢትም፡ቢኾን፥እንጀራም፡ቢኾን፥ብርም፡ቢኾን፡ለመንገድ፡ምንም፡አት ያዙ፥ኹለት፡እጀ፡ጠባብም፡አይኹንላችኹ።
4፤በማናቸውም፡በምትገቡበት፡ቤት፡በዚያ፡ተቀመጡ፡ከዚያም፡ውጡ።
5፤ማናቸውም፡የማይቀበሏችኹ፡ቢኾኑ፥ከዚያ፡ከተማ፡ወጥታችኹ፡ምስክር፡እንዲኾንባቸው፡ከእግራችኹ፡ትቢያ፡አራ ግፉ።
6፤ወጥተውም፡ወንጌልን፡እየሰበኩና፡በስፍራው፡ዅሉ፡እየፈወሱ፡በየመንደሩ፡ያልፉ፡ነበር።
7፤የአራተኛው፡ክፍል፡ገዢ፡ሄሮድስም፡የተደረገውን፡ነገር፡ዅሉ፡ሰምቶ፥አንዳንድ፡ሰዎች፦
8፤ዮሐንስ፡ከሙታን፡ተነሣ፥ሌላዎችም፦ኤልያስ፡ተገለጠ፥ሌላዎችም፦ከቀደሙት፡ነቢያት፡አንዱ፡ተነሥቷል፡ይሉ፡ ስለ፡ነበር፡አመነታ።
9፤ሄሮድስም፦ዮሐንስንስ፡እኔ፡ራሱን፡አስቈረጥኹት፤ይህ፡እንዲህ፡ያለ፡ነገር፡የምሰማበት፡ማን፡ነው፧አለ።ሊ ያየውም፡ይሻ፡ነበር።
10፤ሐዋርያትም፡ተመልሰው፡ያደረጉትን፡ዅሉ፡ነገሩት።ከርሱ፡ጋራም፡ወስዷቸው፡ቤተ፡ሳይዳ፡ከምትባል፡ከተማ፡ አጠገብ፡ወደ፡ምድረ፡በዳ፡ለብቻው፡ፈቀቅ፡አለ።
11፤ሕዝቡም፡ዐውቀው፡ተከተሉት፤ተቀብሏቸውም፡ስለእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ይነግራቸው፡ነበር፥መፈወስ፡ያስፈ ለጋቸውንም፡ፈወሳቸው።
12፤ቀኑም፡ይመሽ፡ዠመር፤ዐሥራ፡ኹለቱም፡ቀርበው፦በዚህ፡በምድረ፡በዳ፡ነንና፡በዙሪያችን፡ወዳሉ፡መንደሮችና ፡ገጠሮች፡ኼደው፡እንዲያድሩና፡ምግብ፡እንዲያገኙ፡ሕዝቡን፡አሰናብት፡አሉት።
13፤ርሱ፡ግን፦እናንተ፡የሚበሉትን፡ስጧቸው፡አላቸው።እነርሱም፦ኼደን፡ለዚህ፡ዅሉ፡ሕዝብ፡ምግብ፡ካልገዛን፥ ከዐምስት፡እንጀራና፡ከኹለት፡ዓሣ፡የሚበልጥ፡የለንም፡አሉት፤ዐምስት፡ሺሕ፡ሰዎች፡ያኽሉ፡ነበርና።
14፤ለደቀ፡መዛሙርቱ፦በየክፍሉ፡ዐምሳ፡ዐምሳውን፡አስቀምጧቸው፡አላቸው።
15፤እንዲህም፡አደረጉ፡ዅሉንም፡አስቀመጧቸው።
16፤ዐምስቱንም፡እንጀራና፡ኹለቱን፡ዓሣ፡ይዞ፥ወደ፡ሰማይ፡አሻቅቦ፡አየና፡ባረካቸው፡ቈርሶም፡ለሕዝቡ፡እንዲ ያቀርቡ፡ለደቀ፡መዛሙርቱ፡ሰጠ።
17፤ዅሉም፡በልተው፡ጠገቡ፥ከነርሱም፡የተረፈውን፡ቍርስራሽ፡ዐሥራ፡ኹለት፡መሶብ፡ወሰዱ።
18፤ለብቻውም፡ሲጸልይ፡ደቀ፡መዛሙርቱ፡ከርሱ፡ጋራ፡ነበሩና፦ሕዝቡ፡እኔ፡ማን፡እንደ፡ኾንኹ፡ይላሉ፧ብሎ፡ጠየ ቃቸው።
19፤እነርሱም፡መልሰው፦መጥምቁ፡ዮሐንስ፥ሌላዎችም፦ኤልያስ፥ሌላዎችም፦ከቀደሙት፡ነቢያት፡አንዱ፡ተነሥቷል፡ ይላሉ፡አሉት።
20፤እናንተስ፡እኔ፡ማን፡እንደ፡ኾንኹ፡ትላላችኹ፧አላቸው።ጴጥሮስም፡መልሶ፦ከእግዚአብሔር፡የተቀባኽ፡ነኽ፡ አለ።
21-22፤ርሱ፡ግን፦የሰው፡ልጅ፡ብዙ፡መከራ፡ሊቀበል፡በሽማግሌዎችም፡በካህናት፡አለቃዎችም፡በጻፊዎችም፡ሊጣል፡ ሊገደልም፡በሦስተኛውም፡ቀን፡ሊነሣ፡ይገ፟ባ፟ዋል፡ብሎ፡ለማንም፡ይህን፡እንዳይናገሩ፡አስጠንቅቆ፡አዘዘ።
23፤ለዅሉም፡እንዲህ፡አላቸው፦በዃላዬ፡ሊመጣ፡የሚወድ፡ቢኖር፥ራሱን፡ይካድ፡መስቀሉንም፡ዕለት፡ዕለት፡ተሸክ ሞ፡ይከተለኝ።
24፤ነፍሱን፡ሊያድን፡የሚወድ፡ዅሉ፡ያጠፋታልና፤ስለ፡እኔ፡ነፍሱን፡የሚያጠፋ፡ዅሉ፡ግን፡ርሱ፡ያድናታል።
25፤ሰው፡ዓለሙን፡ዅሉ፡አትርፎ፡ራሱን፡ቢያጠፋ፡ወይም፡ቢያጐድል፡ምን፡ይጠቅመዋል፧
26፤በእኔና፡በቃሌ፡የሚያፍር፡ዅሉ፥የሰው፡ልጅ፡በክብሩ፡በአባቱና፡በቅዱሳን፡መላእክቱ፡ክብርም፡ሲመጣ፡በር ሱ፡ያፍርበታል።
27፤እውነት፡እላችዃለኹ፥በዚህ፡ከሚቆሙት፡ሰዎች፡የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡እስኪያዩ፡ድረስ፡ሞትን፡የማይ ቀምሱ፡አንዳንድ፡አሉ።
28፤ከዚህም፡ቃል፡በዃላ፡ስምንት፡ቀን፡ያኽል፡ቈይቶ፡ጴጥሮስንና፡ዮሐንስን፡ያዕቆብንም፡ይዞ፡ሊጸልይ፡ወደ፡ ተራራ፡ወጣ።
29፤ሲጸልይም፡የፊቱ፡መልክ፡ተለወጠ፤ልብሱም፡ተብለጭልጮ፡ነጭ፡ኾነ።
30፤እንሆም፥ኹለት፡ሰዎች፡እነርሱም፡ሙሴና፡ኤልያስ፡ከርሱ፡ጋራ፡ይነጋገሩ፡ነበር፤
31፤በክብርም፡ታይተው፡በኢየሩሳሌም፡ሊፈጽም፡ስላለው፡ስለ፡መውጣቱ፡ይናገሩ፡ነበር።
32፤ነገር፡ግን፥ጴጥሮስንና፡ከርሱ፡ጋራ፡የነበሩት፡እንቅልፍ፡ከበደባቸው፤ነቅተው፡ግን፡ክብሩንና፡ከርሱ፡ጋ ራ፡ቆመው፡የነበሩትን፡ኹለት፡ሰዎች፡አዩ።
33፤ከርሱም፡ሲለ፟ዩ፥ጴጥሮስ፡ኢየሱስን፦አቤቱ፥በዚህ፡መኾን፡ለእኛ፡መልካም፡ነውና፥አንድ፡ለአንተ፡አንድም ፡ለሙሴ፡አንድም፡ለኤልያስ፡ሦስት፡ዳሶች፡እንሥራ፡አለው፤የሚለውንም፡አያውቅም፡ነበር።
34፤ይህንም፡ሲናገር፡ደመና፡መጣና፡ጋረዳቸው፤ወደ፡ደመናውም፡ሲገቡ፡ሳሉ፡ፈሩ።
35፤ከደመናውም፦የመረጥኹት፡ልጄ፡ይህ፡ነው፥ርሱን፡ስሙት፡የሚል፡ድምፅ፡መጣ።
36፤ድምፁም፡ከመጣ፡በዃላ፡ኢየሱስ፡ብቻውን፡ኾኖ፡ተገኘ።እነርሱም፡ዝም፡አሉ፥ካዩትም፡ነገር፡በዚያ፡ወራት፡ ምንም፡ለማንም፡አላወሩም።
37፤በነገውም፡ከተራራ፡ሲወርዱ፡ብዙ፡ሕዝብ፡ተገናኙት።
38፤እንሆም፥ከሕዝቡ፡አንድ፡ሰው፡እንዲህ፡እያለ፡ጮኸ፦መምህር፡ሆይ፥ለእኔ፡አንድ፡ልጅ፡ነውና፥ልጄን፡እንድ ታይልኝ፡እለምንኻለኹ።
39፤እንሆም፥ጋኔን፡ይይዘዋል፥ድንገትም፡ይጮኻል፡ዐረፋም፡እያስደፈቀው፡ያንፈራግጠዋል፥እየቀጠቀጠም፡በጭን ቅ፡ይለቀዋል፤
40፤ደቀ፡መዛሙርትኽንም፡እንዲያወጡት፡ለመንኹ፥አልቻሉምም።
41፤ኢየሱስም፡መልሶ፦እናንተ፡የማታምን፡ጠማማ፡ትውልድ፥እስከ፡መቼ፡ከእናንተ፡ጋራ፡እኖራለኹ፧እስከ፡መቼስ ፡እታገሣችዃለኹ፧ልጅኽን፡ወደዚህ፡አምጣው፡አለ።
42፤ሲቀርብም፡ጋኔኑ፡ጣለውና፡አንፈራገጠው፤ኢየሱስ፡ግን፡ርኩሱን፡መንፈስ፡ገሥጾ፡ብላቴናውን፡ፈወሰው፡ለአ ባቱም፡መለሰው።
43፤ዅሉም፡ከእግዚአብሔር፡ታላቅነት፡የተነሣ፡ተገረሙ።ዅሉም፡ኢየሱስ፡ባደረገው፡ዅሉ፡ሲደነቁ፥
44፤ለደቀ፡መዛሙርቱ፦የሰው፡ልጅ፡በሰው፡እጅ፡ይሰጥ፡ዘንድ፡አለውና፥እናንተ፡ይህን፡ቃል፡በዦሯችኹ፡አኑሩ፡ አለ።
45፤እነርሱ፡ግን፡ይህን፡ነገር፡አላስተዋሉም፥እንዳይገባቸውም፡ተሰውሮባቸው፡ነበር፤ስለዚህ፡ነገርም፡እንዳ ይጠይቁት፡ፈሩ።
46፤ከነርሱም፡ማን፡እንዲበልጥ፡ክርክር፡ተነሣባቸው።
47፤ኢየሱስም፡የልባቸውን፡ዐሳብ፡ዐውቆ፡ሕፃንን፡ያዘ፤በአጠገቡም፡አቁሞ፦
48፤ማንም፡ይህን፡ሕፃን፡በስሜ፡የሚቀበል፡እኔን፡ይቀበላል፤የሚቀበለኝም፡ዅሉ፡የላከኝን፡ይቀበላል፤ከኹላች ኹ፡የሚያንስ፡ርሱ፡ታላቅ፡ነውና፥አላቸው።
49፤ዮሐንስም፡መልሶ፦አቤቱ፥አንድ፡ሰው፡በስምኽ፡አጋንንትን፡ሲያወጣ፡አየነው፥ከእኛ፡ጋራም፡ስለማይከተል፡ ከለከልነው፡አለው።
50፤ኢየሱስ፡ግን፦የማይቃወማችኹ፡ከእናንተ፡ጋራ፡ነውና፥አትከልክሉት፡አለው።
51፤የሚወጣበትም፡ወራት፡በቀረበ፡ጊዜ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ለመኼድ፡ፊቱን፡አቀና፥
52፤በፊቱም፡መልክተኛዎችን፡ሰደደ።ኼደውም፡ሊያሰናዱለት፡ወደ፡አንድ፡ወደሳምራውያን፡መንደር፡ገቡ፤
53፤ፊቱም፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡እንደሚኼድ፡ስለ፡ነበር፥አልተቀበሉትም።
54፤ደቀ፡መዛሙርቱም፡ያዕቆብና፡ዮሐንስ፡አይተው፦ጌታ፡ሆይ፥ኤልያስ፡ደግሞ፡እንዳደረገ፡እሳት፡ከሰማይ፡ወር ዶ፡ያጥፋቸው፡እንል፡ዘንድ፡ትወዳለኽን፧አሉት።
55፤ርሱ፡ግን፡ዘወር፡ብሎ፡ገሠጻቸውና፦ምን፡ዐይነት፡መንፈስ፡እንደ፡ኾነላችኹ፡አታውቁም፤
56፤የሰው፡ልጅ፡የሰውን፡ነፍስ፡ሊያድን፡እንጂ፡ሊያጠፋ፡አልመጣም፡አለ።ወደ፡ሌላ፡መንደርም፡ኼዱ።
57፤እነርሱም፡በመንገድ፡ሲኼዱ፡አንድ፡ሰው፦ጌታ፡ሆይ፥ወደምትኼድበት፡ዅሉ፡እከተልኻለኹ፡አለው።
58፤ኢየሱስም፦ለቀበሮዎች፡ጕድጓድ፡ለሰማይም፡ወፎች፡መሳፈሪያ፡አላቸው፥ለሰው፡ልጅ፡ግን፡ራሱን፡የሚያስጠጋ በት፡የለውም፡አለው።
59፤ሌላውንም፦ተከተለኝ፡አለው።ርሱ፡ግን፦ጌታ፡ሆይ፥አስቀድሜ፡ልኺድና፡አባቴን፡እቀብር፡ዘንድ፡ፍቀድልኝ፡ አለ።
60፤ኢየሱስም፦ሙታናቸውን፡እንዲቀብሩ፡ሙታንን፡ተዋቸው፤አንተስ፡ኼደኽ፡የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡ስበክ፡ አለው።
61፤ደግሞ፡ሌላው፦ጌታ፡ሆይ፥እከተልኻለኹ፤ነገር፡ግን፥አስቀድሜ፡ከቤቴ፡ሰዎች፡እንድሰናበት፡ፍቀድልኝ፡አለ ።
62፤ኢየሱስ፡ግን፦ማንም፡ዕርፍ፡በእጁ፡ይዞ፡ወደ፡ዃላ፡የሚመለከት፡ለእግዚአብሔር፡መንግሥት፡የተገባ፡አይደ ለም፡አለው።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡10።______________
ምዕራፍ፡10፤
1፤ከዚህም፡በዃላ፡ጌታ፡ሌላዎቹን፡ሰብዓ፡ሾመ፥ኹለት፡ኹለትም፡አድርጎ፡ርሱ፡ሊኼድበት፡ወዳለው፡ከተማና፡ስፍ ራ፡ዅሉ፡በፊቱ፡ላካቸው።
2፤አላቸውም፦መከሩስ፡ብዙ፡ነው፥ሠራተኛዎች፡ግን፡ጥቂቶች፡ናቸው፤እንግዴህ፡የመከሩን፡ጌታ፡ለመከሩ፡ሠራተኛ ዎች፡እንዲልክ፡ለምኑት።
3፤ኺዱ፤እንሆ፥እንደ፡በጎች፡በተኵላዎች፡መካከል፡እልካችዃለኹ።
4፤ኰረጆም፡ከረጢትም፡ጫማም፡አትያዙ፤በመንገድም፡ለማንም፡እጅ፡አትንሡ።
5፤ወደምትገቡበት፡ቤት፡ዅሉ፡አስቀድማችኹ፦ሰላም፡ለዚህ፡ቤት፡ይኹን፡በሉ።
6፤በዚያም፡የሰላም፡ልጅ፡ቢኖር፥ሰላማችኹ፡ያድርበታል፤አለዚያም፡ይመለስላችዃል።
7፤በዚያም፡ቤት፡ከነርሱ፡ዘንድ፡ካለው፡እየበላችኹና፡እየጠጣችኹ፡ተቀመጡ፤ለሠራተኛ፡ደመ፡ወዙ፡ይገ፟ባ፟ዋል ና።ከቤት፡ወደ፡ቤት፡አትተላለፉ።
8፤ወደምትገቡባትም፡ከተማ፡ዅሉ፡ቢቀበሏችኹ፥ያቀረቡላችኹን፡ብሉ፤
9፤በርሷም፡ያሉትን፡ድውዮችን፡ፈውሱና፦የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ወደ፡እናንተ፡ቀረበች፡በሏቸው።
10፤ነገር፡ግን፥ወደምትገቡባት፡ከተማ፡ዅሉ፡ባይቀበሏችኹ፥ወደ፡አደባባይዋ፡ወጥታችኹ።
11፤ከከተማችኹ፡የተጣበቀብንን፡ትቢያ፡እንኳን፡እናራግፍላችዃለን፤የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ግን፡ወደ፡እና ንተ፡እንደ፡ቀረበች፡ይህን፡ዕወቁ፡በሉ።
12፤እላችዃለኹ፥በዚያን፡ቀን፡ከዚያች፡ከተማ፡ይልቅ፡ለሰዶም፡ይቀልላታል።
13፤ወዮልሽ፡ኮራዚን፥ወዮልሽ፡ቤተ፡ሳይዳ፤በእናንተ፡የተደረገው፡ተኣምራት፡በጢሮስና፡በሲዶና፡ተደርጎ፡ቢኾ ን፥ማቅ፡ለብሰው፡በዐመድም፡ተቀምጠው፡ከብዙ፡ጊዜ፡በፊት፡ንስሓ፡በገቡ፡ነበር።
14፤ነገር፡ግን፥በፍርድ፡ከእናንተ፡ይልቅ፡ለጢሮስና፡ለሲዶና፡ይቀልላቸዋል።
15፤አንቺም፡ቅፍርናሖም፥እስከ፡ሰማይ፡ከፍ፡አልሽን፧ወደ፡ሲኦል፡ትወርጃለሽ።
16፤የሚሰማችኹ፡እኔን፡ይሰማል፥እናንተንም፡የጣለ፡እኔን፡ይጥላል፤እኔንም፡የጣለ፡የላከኝን፡ይጥላል።
17፤ሰብዓውም፡በደስታ፡ተመልሰው፦ጌታ፡ሆይ፥አጋንንት፡ስንኳ፡በስምኽ፡ተገዝተውልናል፡አሉት።
18፤እንዲህም፡አላቸው፡ሰይጣንን፡እንደ፡መብረቅ፡ከሰማይ፡ሲወድቅ፡አየኹ።
19፤እንሆ፥እባቡንና፡ጊንጡን፡ትረግጡ፡ዘንድ፥በጠላትም፡ኀይል፡ዅሉ፡ላይ፡ሥልጣን፡ሰጥቻችዃለኹ፥የሚጐዳችኹ ም፡ምንም፡የለም።
20፤ነገር፡ግን፥መናፍስት፡ስለ፡ተገዙላችኹ፡በዚህ፡ደስ፡አይበላችኹ፥ስማችኹ፡ግን፡በሰማያት፡ሰለ፡ተጻፈ፡ደ ስ፡ይበላችኹ።
21፤በዚያን፡ሰዓት፡ኢየሱስ፡በመንፈስ፡ቅዱስ፡ሐሤት፡አደረገና፦የሰማይና፡የምድር፡ጌታ፡አባት፡ሆይ፥ይህን፡ ከጥበበኛዎችና፡ከአስተዋዮች፡ሰውረኽ፡ለሕፃናት፡ስለ፡ገለጥኽላቸው፥አመሰግናለኹ፤አዎን፡አባት፡ሆይ፥ፈቃድ ኽ፡በፊትኽ፡እንዲህ፡ኾኗልና።
22፤ዅሉ፡ከአባቴ፡ዘንድ፡ተሰጥቶኛል፥ወልድንም፡ማን፡እንደ፡ኾነ፡ከአብ፡በቀር፡የሚያውቅ፡የለም፥አብንም፡ማ ን፡እንደ፡ኾነ፡ከወልድ፡በቀር፡ወልድም፡ሊገልጥለት፡ከሚፈቅድ፡በቀር፡የሚያውቅ፡የለም፡አለ።
23፤ወደ፡ደቀ፡መዛሙርቱም፡ዘወር፡ብሎ፡ለብቻቸው፦የምታዩትን፡የሚያዩ፡ዐይኖች፡ብፁዓን፡ናቸው።
24፤እላችዃለኹና፥እናንተ፡የምታዩትን፡ብዙዎች፡ነቢያትና፡ነገሥታት፡ሊያዩ፡ወደዱ፡አላዩምም፥የምትሰሙትንም ፡ሊሰሙ፡ወደ፟ው፡አልሰሙም፡አለ።
25፤እንሆም፥አንድ፡ሕግ፡ዐዋቂ፡ሊፈትነው፡ተነሥቶ፦መምህር፡ሆይ፥የዘለዓለምን፡ሕይወት፡እንድወርስ፡ምን፡ላ ድርግ፧አለው።
26፤ርሱም፡በሕግ፡የተጻፈው፡ምንድር፡ነው፧እንዴትስ፡ታነባለኽ፧አለው።
27፤ርሱም፡መልሶ፦ጌታ፡አምላክኽን፡በፍጹም፡ልብኽ፡በፍጹም፡ነፍስኽም፡በፍጹም፡ኀይልኽም፡በፍጹም፡ዐሳብኽም ፡ውደድ፥ባልንጀራኽንም፡እንደ፡ራስኽ፡ውደድ፡አለው።
28፤ኢየሱስም፦እውነት፡መለስኽ፤ይህን፡አድርግ፡በሕይወትም፡ትኖራለኽ፡አለው።
29፤ርሱ፡ግን፡ራሱን፡ሊያጸድቅ፡ወዶ፟፡ኢየሱስን፦ባልንጀራዬስ፡ማን፡ነው፧አለው።
30፤ኢየሱስም፡መልሶ፡እንዲህ፡አለ፦አንድ፡ሰው፡ከኢየሩሳሌም፡ወደ፡ኢያሪኮ፡ወረደ፡በወንበዴዎችም፡እጅ፡ወደ ቀ፤እነርሱም፡ደግሞ፡ገፈፉት፡ደበደቡትም፡በሕይወትና፡በሞት፡መካከልም፡ትተውት፡ኼዱ።
31፤ድንገትም፡አንድ፡ካህን፡በዚያ፡መንገድ፡ወረደ፥አይቶትም፡ገለል፡ብሎ፡ዐለፈ።
32፤እንዲሁም፡ደግሞ፡አንድ፡ሌዋዊ፡ወደዚያ፡ስፍራ፡መጣና፡አይቶት፥ገለል፡ብሎ፡ዐለፈ።
33፤አንድ፡ሳምራዊ፡ግን፡ሲኼድ፡ወደ፡ርሱ፡መጣ፥አይቶትም፡ዐዘነለት፤
34፤ቀርቦም፡ዘይትና፡የወይን፡ጠጅ፡በቍስሎቹ፡ላይ፡አፍሶ፟፡አሰራቸው፤በራሱ፡አህያም፡ላይ፡አስቀምጦት፡ወደ እንግዳዎች፡ማደሪያ፡ወሰደው፥ጠበቀውም።
35፤በማግስቱም፡ኹለት፡ዲናር፡አውጥቶ፡ለባለቤቱ፡ሰጠና፦ጠብቀው፥ከዚህም፡በላይ፡የምትከስረውን፡ዅሉ፡እኔ፡ ስመለስ፡እከፍልኻለኹ፡አለው።
36፤እንግዲህ፡ከነዚህ፡ከሦስቱ፡በወንበዴዎች፡እጅ፡ለወደቀው፡ባልንጀራ፡የኾነው፡ማንኛው፡ይመስልኻል፧
37፤ርሱም፦ምሕረት፡ያደረገለት፡አለ።ኢየሱስም፦ኺድ፥አንተም፡እንዲሁ፡አድርግ፡አለው።
38፤ሲኼዱም፡ርሱ፡ወደ፡አንዲት፡መንደር፡ገባ፤ማርታ፡የተባለች፡አንዲት፡ሴትም፡በቤቷ፡ተቀበለችው።
39፤ለርሷም፡ማርያም፡የምትባል፡እኅት፡ነበረቻት፥ርሷም፡ደግሞ፡ቃሉን፡ልትሰማ፡በኢየሱስ፡እግር፡አጠገብ፡ተ ቀምጣ፡ነበር።
40፤ማርታ፡ግን፡አገልግሎት፡ስለ፡በዛባት፡ባከነች፤ቀርባም፦ጌታ፡ሆይ፥እኔ፡እንድሠራ፡እኅቴ፡ብቻዬን፡ስትተ ወኝ፡አይገድኽምን፧እንኪያስ፡እንድታግዘኝ፡ንገራት፡አለችው።
41፤ኢየሱስም፡መልሶ፦ማርታ፥ማርታ፥በብዙ፡ነገር፡ትጨነቂያለሽ፡ትታወኪማለሽ፥
42፤የሚያስፈልገው፡ግን፡ጥቂት፡ወይም፡አንድ፡ነገር፡ነው፤ማርያምም፡መልካም፡ዕድልን፡መርጣለች፡ከርሷም፡አ ይወሰድባትም፡አላት።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡11።______________
ምዕራፍ፡11፤
1፤ርሱም፡ባንድ፡ስፍራ፡ይጸልይ፡ነበር፥በጨረሰም፡ጊዜ፡ከደቀ፡መዛሙርቱ፡አንዱ፦ጌታ፡ሆይ፥ዮሐንስ፡ደቀ፡መዛ ሙርቱን፡እንዳስተማረ፡እንጸልይ፡ዘንድ፡አስተምረን፡አለው።
2፤አላቸውም፦ስትጸልዩ፡እንዲህ፡በሉ፦በሰማያት፡የምትኖር፡አባታችን፡ሆይ፤ስምኽ፡ይቀደስ፤መንግሥትኽ፡ትምጣ ፤ፈቃድኽ፡በሰማይ፡እንደ፡ኾነች፡እንዲሁ፡በምድር፡ትኹን፤
3፤የዕለት፡እንጀራችንን፡ዕለት፡ዕለት፡ስጠን፤
4፤ኀጢአታችንንም፡ይቅር፡በለን፥እኛ፡ደግሞ፡የበደሉንን፡ዅሉ፡ይቅር፡ብለናልና፤ከክፉ፡አድነን፡እንጂ፡ወደ፡ ፈተና፡አታግባን።
5፤እንዲህም፡አላቸው፦ከእናንተ፡ማናቸውም፡ወዳጅ፡ያለው፥በእኩል፡ሌሊትስ፡ወደ፡ርሱ፡ኼዶ፦ወዳጄ፡ሆይ፥ሦስት ፡እንጀራ፡አበድረኝ፥
6፤አንድ፡ወዳጄ፡ከመንገድ፡ወደ፡እኔ፡መጥቶ፡የማቀርብለት፡የለኝምና፡ይላልን፧
7፤ያም፡ከውስጥ፡መልሶ፦አታድክመኝ፤አኹን፡ደጁ፡ተቈልፏል፡ልጆቼም፡ከእኔ፡ጋራ፡በዐልጋ፡ላይ፡አሉ፤ተነሥቼ፡ ልሰጥኽ፡አልችልም፡ይላልን፧
8፤እላችዃለኹ፥ወዳጅ፡ስለ፡ኾነ፡ተነሥቶ፡ባይሰጠው፡እንኳ፥ስለ፡ንዝነዛው፡ተነሥቶ፡የሚፈልገውን፡ዅሉ፡ይሰጠ ዋል።
9፤እኔም፡እላችዃለኹ፦ለምኑ፥ይሰጣችኹማል፤ፈልጉ፥ታገኙማላችኹ፤መዝጊያን፡አንኳኩ፥ይከፍትላችኹማል።
10፤የሚለምን፡ዅሉ፡ይቀበላልና፥የሚፈልግም፡ያገኛል፥መዝጊያውንም፡ለሚያንኳኳው፡ይከፈትለታል።
11፤አባት፡ከኾናችኹ፡ከእናንተ፡ከማንኛችኹም፡ልጁ፡እንጀራ፡ቢለምነው፥ርሱም፡ድንጋይ፡ይሰጠዋልን፧ዓሣ፡ደግ ሞ፡ቢለምነው፡በዓሣ፡ፋንታ፡እባብ፡ይሰጠዋልን፧
12፤ወይስ፡ዕንቍላል፡ቢለምነው፡ጊንጥ፡ይሰጠዋልን፧
13፤እንኪያስ፡እናንተ፡ክፉዎች፡ስትኾኑ፡ለልጆቻችኹ፡መልካም፡ስጦታ፡መስጠት፡ካወቃችኹ፥በሰማይ፡ያለው፡አባ ት፡ለሚለምኑት፡እንዴት፡አብልጦ፡መንፈስ፡ቅዱስን፡ይሰጣቸው፧
14፤ዲዳውንም፡ጋኔን፡ያወጣ፡ነበር፤ጋኔኑም፡ከወጣ፡በዃላ፡ዲዳው፡ተናገረ፡ሕዝቡም፡ተደነቁ፤
15፤ነገር፡ግን፥ከነርሱ፡አንዳንዱ፦በብዔል፡ዜቡል፡በአጋንንት፡አለቃ፡አጋንንትን፡ያወጣል፡አሉ።
16፤ሌላዎችም፡ሲፈትኑት፡ከሰማይ፡ምልክት፡ከርሱ፡ይፈልጉ፡ነበር።
17፤ርሱ፡ግን፡ዐሳባቸውን፡ዐውቆ፡እንዲህ፡አላቸው፦ርስ፡በርሷ፡የምትለያይ፡መንግሥት፡ዅሉ፡ትጠፋለች፤ቤትም ፡በቤት፡ላይ፡ይወድቃል።
18፤እኔ፡አጋንንትን፡በብዔል፡ዜቡል፡እንዳወጣ፡ትላላችኹና፡ሰይጣን፡ደግሞ፡ርስ፡በርሱ፡ከተለያየ፡መንግሥቱ ፡እንዴት፡ትቆማለች፧
19፤እኔስ፡በብዔል፡ዜቡል፡አጋንንትን፡የማወጣ፡ከኾንኹ፥ልጆቻችኹ፡በማን፡ያወጧቸዋል፧ስለዚህ፡እነርሱ፡ፈራ ጆች፡ይኾኑባችዃል።
20፤እኔ፡ግን፡በእግዚአብሔር፡ጣት፡አጋንንትን፡የማወጣ፡ከኾንኹ፥እንግዲህ፡የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ወደ፡ እናንተ፡ደርሳለች።
21፤ኀይለኛ፡ሰው፡ጋሻና፡ጦር፡ይዞ፡የራሱን፡ግቢ፡ቢጠብቅ፥ያለው፡ገንዘቡ፡በሰላም፡ይኾናል፤
22፤ከርሱ፡ይልቅ፡የሚበረታ፡መጥቶ፡ሲያሸንፈው፡ግን፥ታምኖበት፡የነበረውን፡ጋሻና፡ጦር፡ይወስድበታል፡ምርኮ ውንም፡ያካፍላል።
23፤ከእኔ፡ጋራ፡ያልኾነ፡ይቃወመኛል፥ከእኔ፡ጋራም፡የማያከማች፡ይበትናል።
24፤ርኩስ፡መንፈስ፡ከሰው፡በወጣ፡ጊዜ፡ዕረፍትን፡እየፈለገ፡ውሃ፡በሌለበት፡ቦታ፡ያልፋል፤ባያገኝም፦ወደወጣ ኹበት፡ቤቴ፡እመለሳለኹ፡ይላል፤
25፤ሲመጣም፡ተጠርጎ፡አጊጦም፡ያገኘዋል።
26፤ከዚያ፡ወዲያ፡ይኼድና፡ከርሱ፡የከፉትን፡ሌላዎችን፡ሰባት፡አጋንንት፡ከርሱ፡ጋራ፡ይይዛል፥ገብተውም፡በዚ ያ፡ይኖራሉ፤ለዚያም፡ሰው፡ከፊተኛው፡ይልቅ፡የዃለኛው፡ይብስበታል።
27፤ይህንም፡ሲናገር፥ከሕዝቡ፡አንዲት፡ሴት፡ድምፇን፡ከፍ፡አድርጋ፦የተሸከመችኽ፡ማሕፀንና፡የጠባኻቸው፡ጡቶ ች፡ብፁዓን፡ናቸው፡አለችው።
28፤ርሱ፡ግን፦አዎን፥ብፁዓንስ፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ሰምተው፡የሚጠብቁት፡ናቸው፡አለ።
29፤ብዙ፡ሕዝብም፡በተሰበሰቡ፡ጊዜ፡እንዲህ፡ይል፡ዠመር፦ይህ፡ትውልድ፡ክፉ፡ነው፤ምልክት፡ይፈልጋል፥ከነቢዩ ም፡ከዮናስ፡ምልክት፡በቀር፡ምልክት፡አይሰጠውም።
30፤ዮናስ፡ለነነዌ፡ሰዎች፡ምልክት፡እንደ፡ኾናቸው፥እንዲሁ፡ደግሞ፡የሰው፡ልጅ፡ለዚህ፡ትውልድ፡ምልክት፡ይኾ ናል።
31፤ንግሥተ፡አዜብ፡በፍርድ፡ከዚህ፡ትውልድ፡ሰዎች፡ጋራ፡ተነሥታ፡ትፈርድባቸዋለች፤የሰሎሞንን፡ጥበብ፡ለመስ ማት፡ከምድር፡ዳር፡መጥታለችና፥እንሆም፥ከሰሎሞን፡የሚበልጥ፡ከዚህ፡አለ።
32፤የነነዌ፡ሰዎች፡በፍርድ፡ከዚህ፡ትውልድ፡ጋራ፡ተነሥተው፡ይፈርዱበታል፤በዮናስ፡ስብከት፡ንስሓ፡ገብተዋል ና፥እንሆም፥ከዮናስ፡የሚበልጥ፡ከዚህ፡አለ።
33፤መብራትንም፡አብርቶ፡በስውር፡ወይም፡በእንቅብ፡በታች፡የሚያኖረው፡የለም፥የሚገቡ፡ሰዎች፡ብርሃኑን፡እን ዲያዩ፡በመቅረዝ፡ላይ፡ያኖረዋል፡እንጂ።
34፤የሰውነትኽ፡መብራት፡ዐይንኽ፡ናት።ዐይንኽ፡ጤናማ፡በኾነች፡ጊዜ፡ሰውነትኽ፡ዅሉ፡ደግሞ፡ብሩህ፡ይኾናል። ዐይንኽ፡ታማሚ፡በኾነች፡ጊዜ፡ግን፡ሰውነትኽ፡ደግሞ፡የጨለመ፡ይኾናል።
35፤እንግዲህ፡ባንተ፡ያለው፡ብርሃን፡ጨለማ፡እንዳይኾን፡ተመልከት።
36፤እንግዲህ፡ሰውነትኽ፡ዅሉ፡የጨለማ፡ቍራጭ፡የሌለበት፡ብሩህ፡ቢኾን፥መብራት፡በደመቀ፡ብርሃን፡እንደሚያበ ራልኽ፡በጭራሽ፡ብሩህ፡ይኾናል።
37፤ይህንንም፡ሲናገር፡አንድ፡ፈሪሳዊ፡ከርሱ፡ጋራ፡ምሳ፡ይበላ፡ዘንድ፡ለመነው፡ገብቶም፡ተቀመጠ።
38፤ከምሳም፡በፊት፡አስቀድሞ፡እንዳልታጠበ፡ባየው፡ጊዜ፥ፈሪሳዊው፡ተደነቀ።
39፤ጌታም፡እንዲህ፡አለው፦አኹን፡እናንተ፡ፈሪሳውያን፡የጽዋውንና፡የወጭቱን፡ውጭ፡ታጠራላችኹ፥ውስጣችኹ፡ግ ን፡ቅሚያና፡ክፋት፡ሞልቶበታል፡
40፤እናንት፡ደንቈሮዎች፥የውጩን፡የፈጠረ፡የውስጡን፡ደግሞ፡አልፈጠረምን፧
41፤ነገር፡ግን፥በውስጥ፡ያለውን፡ምጽዋት፡አድርጋችኹ፡ስጡ፥እንሆም፥ዅሉ፡ንጹሕ፡ይኾንላችዃል።
42፤ነገር፡ግን፥እናንተ፡ፈሪሳውያን፥ከአዝሙድና፡ከጤና፡አዳም፡ከአትክልትም፡ዅሉ፡ዓሥራት፡ስለምታወጡ፥ፍር ድንና፡እግዚአብሔርን፡መውደድ፡ስለምትተላለፉ፥ወዮላችኹ፤ነገር፡ግን፥ሌላውን፡ሳትተዉ፡ይህን፡ልታደርጉት፡ ይገ፟ባ፟ችኹ፡ነበር።
43፤እናንተ፡ፈሪሳውያን፥በምኵራብ፡የከበሬታ፡ወንበር፡በገበያም፡ሰላምታ፡ስለምትወዱ፥ወዮላችኹ።
44፤እናንተ፡ግብዞች፡ጻፊዎችና፡ፈሪሳውያን፥ሰዎች፡ሳያውቁ፡በላዩ፡የሚኼዱበት፡የተሰወረ፡መቃብር፡ስለምትመ ስሉ፥ወዮላችኹ።
45፤ከሕግ፡ዐዋቂዎችም፡አንዱ፡መልሶ፦መምህር፡ሆይ፥ይህን፡ማለትኽ፡እኛን፡ደግሞ፡መስደብኽ፡ነው፡አለው።
46፤ርሱም፡እንዲህ፡አለ፦እናንተ፡ደግሞ፡ሕግ፡ዐዋቂዎች፥አስቸጋሪ፡ሸክም፡ለሰዎች፡ስለምታሸክሙ፥ራሳችኹም፡ በአንዲት፡ጣታችኹ፡ስንኳ፡ሸክሙን፡ስለማትነኩት፥ወዮላችኹ።
47፤አባቶቻችኹ፡የገደሏቸውን፡የነቢያትን፡መቃብር፡ስለምትሠሩ፥ወዮላችኹ።
48፤እንግዲህ፡ለአባቶቻችኹ፡ሥራ፡ትመሰክራላችኹ፡ትስማማላችኹም፤እነርሱ፡ገድለዋቸዋልና፥እናንተም፡መቃብራ ቸውን፡ትሠራላችኹ።
49፤ስለዚህ፡ደግሞ፥የእግዚአብሔር፡ጥበብ፡እንዲህ፡አለች፦ወደ፡እነርሱ፡ነቢያትንና፡ሐዋርያትን፡እልካለኹ፥ ከነርሱም፡ይገድላሉ፥ያሳድዱማል፥
50፤ዓለም፡ከተፈጠረ፡ዠምሮ፡የፈሰሰው፡የነቢያት፡ዅሉ፡ደም፥
51፤ከአቤል፡ደም፡ዠምሮ፡በመሠዊያውና፡በቤተ፡መቅደስ፡መካከል፡እስከ፡ጠፋው፥እስከ፡ዘካርያስ፡ደም፡ድረስ፥ ከዚህ፡ትውልድ፡እንዲፈለግ፡አዎን፡እላችዃለኹ፥ከዚህ፡ትውልድ፡ይፈለጋል።
52፤እናንተ፡ሕግ፡ዐዋቂዎች፥የዕውቀትን፡መክፈቻ፡ስለ፡ወሰዳችኹ፥ወዮላችኹ፡ራሳችኹ፡አልገባችኹም፡የሚገቡት ንም፡ከለከላችኹ።
53-54፤ይህንም፡ሲናገራቸው፥ጻፊዎችና፡ፈሪሳውያን፡በአፉ፡የተናገረውን፡ሊነጥቁ፡ሲያደቡ፥እጅግ፡ይቃወሙና፡ስ ለ፡ብዙ፡ነገር፡እንዲናገር፡ያነሣሡ፡ዠመር።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡12።______________
ምዕራፍ፡12፤
1፤በዚያን፡ጊዜ፡የሕዝብ፡አእላፍ፡ርስ፡በርሳቸው፡እስኪረጋገጡ፡ድረስ፡ተሰብስበው፡ሳሉ፥ለደቀ፡መዛሙርቱ፡እ ንዲህ፡ይል፡ዠመር።አስቀድማችኹ፡ከፈሪሳውያን፡ርሾ፡ተጠበቁ፥ርሱም፡ግብዝነት፡ነው።
2፤ነገር፡ግን፥የማይገለጥ፡የተከደነ፥የማይታወቅም፡የተሰወረ፡ምንም፡የለም።
3፤ስለዚህ፥በጨለማ፡የምትናገሩት፡ዅሉ፡በብርሃን፡ይሰማል፥በዕልፍኝም፡ውስጥ፡በዦሮ፡የምትናገሩት፡በሰገነት ፡ላይ፡ይሰበካል።
4፤ለእናንተም፡ለወዳጆቼ፡እላችዃለኹ፥ሥጋን፡የሚገድሉትን፡በዃላም፡አንድ፡ስንኳ፡የሚበልጥ፡ሊያደርጉ፡የማይ ችሉትን፡አትፍሩ።
5፤እኔ፡ግን፡የምትፈሩትን፡አሳያችዃለኹ፤ከገደለ፡በዃላ፡ወደ፡ገሃነም፡ለመጣል፡ሥልጣን፡ያለውን፡ፍሩ።አዎን ፡እላችዃለኹ፥ርሱን፡ፍሩ።
6፤ዐምስት፡ድንቢጦች፡በዐሥር፡ሳንቲም፡ይሸጡ፡የለምን፧ከነርሱም፡አንዲቱ፡ስንኳ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡አትረ ሳም።
7፤ነገር፡ግን፥የእናንተ፡የራሳችኹ፡ጠጕር፡ዅሉ፡እንኳ፡የተቈጠረ፡ነው፤እንግዲያስ፡አትፍሩ፡ከብዙ፡ድንቢጦች ፡ትበልጣላችኹ።
8፤እላችኹማለኹ፥በሰው፡ፊት፡የሚመሰክርልኝ፡ዅሉ፥የሰው፡ልጅ፡ደግሞ፡በእግዚአብሔር፡መላእክት፡ፊት፡ይመሰክ ርለታል፤
9፤በሰውም፡ፊት፡የሚክደኝ፡በእግዚአብሔር፡መላእክት፡ፊት፡ይካዳል።
10፤በሰው፡ልጅም፡ላይ፡ቃል፡የሚናገር፡ዅሉ፡ይሰረይለታል፤መንፈስ፡ቅዱስን፡የሚሰድብ፡ግን፡አይሰረይለትም።
11፤ወደ፡ምኵራቦችና፡ወደ፡መኳንንቶችም፡ወደ፡ገዢዎችም፡ሲጐትቷችኹ፥እንዴት፡ወይም፡ምን፡እንድትመልሱ፡ወይ ም፡እንድትናገሩ፡አትጨነቁ፤
12፤መንፈስ፡ቅዱስ፡በዚያች፡ሰዓት፡ልትናገሩ፡የሚገ፟ባ፟ችኹን፡ያስተምራችዃልና።
13፤ከሕዝቡም፡አንድ፡ሰው፦መምህር፡ሆይ፥ርስቱን፡ከእኔ፡ጋራ፡እንዲካፈል፡ለወንድሜ፡ንገረው፡አለው።
14፤ርሱም፦አንተ፡ሰው፥ፈራጅና፡አካፋይ፡በላያችኹ፡እንድኾን፡ማን፡ሾመኝ፧አለው።
15፤የሰው፡ሕይወት፡በገንዘቡ፡ብዛት፡አይደለምና፡ተጠንቀቁ፥ከመጐምዠትም፡ዅሉ፡ተጠበቁ፡አላቸው።
16፤ምሳሌም፡ነገራቸው፡እንዲህ፡ሲል፦አንድ፡ባለጠጋ፡ሰው፡ዕርሻ፡እጅግ፡ፍሬያም፡ኾነችለት።
17፤ርሱም፦ፍሬዬን፡የማከማችበት፡ስፍራ፡ዐጥቻለኹና፡ምን፡ላድርግ፧ብሎ፡በልቡ፡ዐሰበ።
18፤እንዲህ፡አደርጋለኹ፤ጐተራዬን፡አፍርሼ፡ሌላ፡የሚበልጥ፡እሠራለኹ፥በዚያም፡ፍሬዬንና፡በረከቴን፡ዅሉ፡አ ከማቻለኹ፤
19፤ነፍሴንም፦አንቺ፡ነፍሴ፥ለብዙ፡ዘመን፡የሚቀር፡ብዙ፡በረከት፡አለሽ፤ዕረፊ፥ብዪ፥ጠጪ፥ደስ፡ይበልሽ፡እላ ታለኹ፡አለ።
20፤እግዚአብሔር፡ግን፦አንተ፡ሰነፍ፥በዚች፡ሌሊት፡ነፍስኽን፡ከአንተ፡ሊወስዷት፡ይፈልጓታል፤ይህስ፡የሰበሰ ብኸው፡ለማን፡ይኾናል፧አለው።
21፤ለራሱ፡ገንዘብ፡የሚያከማች፥በእግዚአብሔር፡ዘንድም፡ባለጠጋ፡ያልኾነ፡እንዲህ፡ነው።
22፤ለደቀ፡መዛሙርቱም፡እንዲህ፡አለ፦ስለዚህ፡እላችዃለኹ፥ለነፍሳችኹ፡በምትበሉት፡ወይም፡ለሰውነታችኹ፡በም ትለብሱት፡አትጨነቁ።
23፤ነፍስ፡ከመብል፡ሰውነትም፡ከልብስ፡ይበልጣልና።
24፤ቍራዎችን፡ተመልከቱ፤አይዘሩም፡አያጭዱምም፥ዕቃ፡ቤትም፡ወይም፡ጐተራ፡የላቸውም፥እግዚአብሔርም፡ይመግባ ቸዋል፤እናንተስ፡ከወፎች፡እንዴት፡ትበልጣላችኹ፧
25፤ከእናንተ፡ተጨንቆ፡በቁመቱ፡ላይ፡አንድ፡ክንድ፡መጨመር፡የሚችል፡ማን፡ነው፧
26፤እንግዲህ፡ትንሹን፡ነገር፡ስንኳ፡የማትችሉ፡ከኾናችኹ፥ስለ፡ምን፡በሌላ፡ትጨነቃላችኹ፧
27፤አበባዎችን፡እንዴት፡እንዲያድጉ፡ተመልከቱ፤አይደክሙም፡አይፈትሉምም፤ነገር፡ግን፥እላችዃለኹ፥ሰሎሞንስ ፡እንኳ፡በክብሩ፡ዅሉ፡ከነዚህ፡እንደ፡አንዲቱ፡አለበሰም።
28፤እግዚአብሔር፡ግን፡ዛሬ፡ያለውን፡ነገም፡ወደ፡እቶን፡የሚጣለውን፡በሜዳ፡የኾነውን፡ሣር፡እንዲህ፡የሚያለ ብሰው፡ከኾነ፥እናንተ፡እምነት፡የጐደላችኹ፥እናንተንማ፡ይልቁን፡እንዴት፧
29፤እናንተም፡የምትበሉትን፡የምትጠጡትንም፡አትፈልጉ፥አታወላውሉም፤
30፤ይህንስ፡ዅሉ፡በዓለም፡ያሉ፡አሕዛብ፡ይፈልጉታልና፤የእናንተም፡አባት፡ይህ፡እንዲያስፈልጋችኹ፡ያውቃል።
31፤ዳሩ፡ግን፡መንግሥቱን፡ፈልጉ፡ይህም፡ዅሉ፡ይጨመርላችዃል።
32፤አንተ፡ታናሽ፡መንጋ፥መንግሥትን፡ሊሰጣችኹ፡የአባታችኹ፡በጎ፡ፈቃድ፡ነውና፥አትፍሩ።
33፤ያላችኹን፡ሽጡ፡ምጽዋትም፡ስጡ፤ሌባ፡በማይቀርብበት፡ብልም፡በማያጠፋበት፡በሰማያት፡የማያልቅ፡መዝገብ፡ የሚኾኑትን፡የማያረጁትንም፡ኰረጆዎች፡ለራሳችኹ፡አድርጉ፤
34፤መዝገባችኹ፡ባለበት፡ልባችኹ፡ደግሞ፡በዚያ፡ይኾናልና።
35፤ወገባችኹ፡የታጠቀ፡መብራታችኹም፡የበራ፡ይኹን፤
36፤እናንተም፡ጌታቸው፡መጥቶ፡ደጁን፡ሲያንኳኳ፡ወዲያው፡እንዲከፍቱለት፡ከሰርግ፡እስኪመለስ፡ድረስ፡የሚጠብ ቁ፡ሰዎችን፡ምሰሉ፡
37፤ጌታቸው፡በመጣ፡ጊዜ፡ሲተጉ፡የሚያገኛቸው፡እነዚያ፡ባሪያዎች፡ብፁዓን፡ናቸው፤እውነት፡እላችዃለኹ፥ታጥቆ ፡በማእዱ፡ያስቀምጣቸዋል፡ቀርቦም፡ያገለግላቸዋል።
38፤ከሌሊቱም፡በኹለተኛው፡ወይም፡በሦስተኛው፡ክፍል፡መጥቶ፡እንዲሁ፡ቢያገኛቸው፥እነዚያ፡ባሪያዎች፡ብፁዓን ፡ናቸው።
39፤ይህን፡ግን፡ዕወቁ፡ባለቤት፡በምን፡ሰዓት፡ሌባ፡እንዲመጣ፡ቢያውቅ፡ኖሮ፥በነቃ፥ቤቱም፡እንዲቈፈር፡ባልፈ ቀደም፡ነበር።
40፤እናንተ፡ደግሞ፡ተዘጋጅታችኹ፡ኑሩ፥የሰው፡ልጅ፡በማታስቡበት፡ሰዓት፡ይመጣልና።
41፤ጴጥሮስም፦ጌታ፡ሆይ፥ይህን፡ምሳሌ፡ለእኛ፡ወይስ፡ደግሞ፡ለዅሉ፡ትናገራለኽን፧አለው።
42፤ጌታም፡አለ፦እንኪያስ፡ምግባቸውን፡በጊዜው፡ይሰጣቸው፡ዘንድ፡ጌታው፡በቤተ፡ሰዎቹ፡ላይ፡የሚሾመው፡ታማኝ ና፡ልባም፡መጋቢ፡ማን፡ነው፧
43፤ጌታው፡መጥቶ፡እንዲህ፡ሲያደርግ፡የሚያገኘው፡ያ፡ባሪያ፡ብፁዕ፡ነው።
44፤እውነት፡እላችዃለኹ፥ባለው፡ዅሉ፡ላይ፡ይሾመዋል።
45፤ያ፡ባሪያ፡ግን፦ጌታዬ፡እስኪመጣ፡ይዘገያል፡ብሎ፡በልቡ፡ቢያስብ፡ሎሌዎችንና፡ገረዶችንም፡ይመታ፡ይበላም ፡ይጠጣም፡ይሰክርም፡ዘንድ፡ቢዠምር፥
46፤የዚያ፡ባሪያ፡ጌታ፡ባልጠበቃት፡ቀን፡ባላወቃትም፡ሰዓት፡ይመጣል፥ከኹለትም፡ይሰነጥቀዋል፡ዕድሉንም፡ከማ ይታመኑ፡ጋራ፡ያደርጋል።
47፤የጌታውንም፡ፈቃድ፡ዐውቆ፡ያልተዘጋጀ፡እንደ፡ፈቃዱም፡ያላደረገ፡ያ፡ባሪያ፡እጅግ፡ይገረፋል፤
48፤ያላወቀ፡ግን፥መገረፍ፡የሚገ፟ባ፟ውንም፡ያደረገ፡ጥቂት፡ይገረፋል።ብዙም፡ከተሰጠው፡ሰው፡ዅሉ፡ከርሱ፡ብ ዙ፡ይፈለግበታል፥ብዙ፡ዐደራም፡ከተሰጠው፡ከርሱ፡አብዝተው፡ይሹበታል።
49፤በምድር፡ላይ፡እሳት፡ልጥል፡መጣኹ፥አኹንም፡የነደደ፡ከኾነ፡ዘንድ፡ምን፡እፈልጋለኹ፧
50፤ነገር፡ግን፥የምጠመቃት፡ጥምቀት፡አለችኝ፥እስክትፈጸምም፡ድረስ፡እንዴት፡እጨነቃለኹ፧
51፤በምድር፡ላይ፡ሰላምንም፡ለመስጠት፡የመጣኹ፡ይመስላችዃልን፧እላችዃለኹ፥አይደለም፥መለያየትን፡እንጂ።
52፤ካኹን፡ዠምሮ፡በአንዲት፡ቤት፡ዐምስት፡ሰዎች፡ይኖራሉና፤ሦስቱም፡በኹለቱ፡ላይ፡ኹለቱም፡በሦስቱ፡ላይ፡ተ ነሥተው፡ይለያያሉ።
53፤አባት፡በልጁ፡ላይ፡ልጅም፡በአባቱ፡ላይ፥እናት፡በልጇ፡ላይ፡ልጇም፡በእናቷ፡ላይ፥ዐማት፡በምራቷ፡ላይ፡ም ራትም፡በአማቷ፡ላይ፡ተነሥተው፡ይለያያሉ።
54፤ደግሞም፡ሕዝቡን፡እንዲህ፡አለ፦ደመና፡ከምዕራብ፡ሲወጣ፡ባያችኹ፡ጊዜ፥ወዲያው።ዝናብ፡ይመጣል፡ትላላችኹ ፥እንዲሁም፡ይኾናል፤
55፤በአዜብም፡ነፋስ፡ሲነፍስ፦ትኵሳት፡ይኾናል፡ትላላችኹ፥ይኾንማል።
56፤እናንት፡ግብዞች፥የምድሩንና፡የሰማዩን፡ፊት፡ልትመረምሩ፡ታውቃላችኹ፥ነገር፡ግን፥ይህን፡ዘመን፡የማትመ ረምሩ፡እንዴት፡ነው፧
57፤ራሳችኹ፡ደግሞ፡ጽድቅን፡የማትፈርዱ፡ስለ፡ምን፡ነው፧
58፤ከባላጋራኽ፡ጋራ፡ወደ፡ሹም፡ብትኼድ፥ወደ፡ዳኛ፡እንዳይጐትትኽ፡ዳኛውም፡ለሎሌው፡አሳልፎ፡እንዳይሰጥኽ፡ ሎሌውም፡በወህኒ፡እንዳይጥልኽ፥ገና፡በመንገድ፡ሳለኽ፡ከባላጋራኽ፡እንድትታረቅ፡ትጋ።
59፤እልኻለኹ፥የመጨረሻዋን፡ግማሽ፡ሳንቲም፡እስክትከፍል፡ድረስ፡ከዚያ፡ከቶ፡አትወጣም።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡13።______________
ምዕራፍ፡13፤
1፤በዚያን፡ጊዜም፡ሰዎች፡መጥተው፡ጲላጦስ፡ደማቸውን፡ከመሥዋዕታቸው፡ጋራ፡ስላደባለቀው፡ስለገሊላ፡ሰዎች፡አ ወሩለት።
2፤ኢየሱስም፡መልሶ፡እንዲህ፡አላቸው፦እነዚህ፡የገሊላ፡ሰዎች፡ይህ፡ስለ፡ደረሰባቸው፥ከገሊላ፡ሰዎች፡ዅሉ፡ይ ልቅ፡ኀጢአተኛዎች፡የኾኑ፡ይመስሏችዃልን፧
3፤እላችዃለኹ፥አይደለም፤ነገር፡ግን፥ንስሓ፡ባትገቡ፡ዅላችኹ፡እንዲሁ፡ትጠፋላችኹ።
4፤ወይስ፡በሰሌሆም፡ግንቡ፡የወደቀባቸውና፡የገደላቸው፡እነዚያ፡ዐሥራ፡ስምንት፡ሰዎች፡በኢየሩሳሌም፡ከሚኖሩ ት፡ዅሉ፡ይልቅ፡በደለኛዎች፡ይመስሏችዃልን፧አይደለም፥እላችዃለኹ፤
5፤ነገር፡ግን፥ንስሓ፡ባትገቡ፡ዅላችኹ፡እንደዚሁ፡ትጠፋላችኹ።
6፤ይህንም፡ምሳሌ፡አለ፦ላንድ፡ሰው፡በወይኑ፡አትክልት፡የተተከለች፡በለስ፡ነበረችው፥ፍሬም፡ሊፈልግባት፡መጥ ቶ፡ምንም፡አላገኘም።
7፤የወይን፡አትክልት፡ሠራተኛውንም፦እንሆ፥ከዚች፡በለስ፡ፍሬ፡ልፈልግ፡ሦስት፡ዓመት፡እየመጣኹ፡ምንም፡አላገ ኘኹም፤ቍረጣት፤ስለ፡ምን፡ደግሞ፡መሬቱን፡ታጐሳቍላለች፧አለው።
8፤ርሱ፡ግን፡መልሶ፦ጌታ፡ሆይ፥ዙሪያዋን፡እስክኰተኵትላትና፡ፋንድያ፡እስካፈስላት፡ድረስ፡በዚች፡ዓመት፡ደግ ሞ፡ተዋት።
9፤ወደ፡ፊትም፡ብታፈራ፥ደኅና፡ነው፤ያለዚያ፡ግን፡ትቈርጣታለኽ፡አለው።
10፤በሰንበትም፡ባንድ፡ምኵራብ፡ያስተምር፡ነበር።
11፤እንሆም፥ከዐሥራ፡ስምንት፡ዓመት፡ዠምሮ፡የድካም፡መንፈስ፡ያደረባት፡ሴት፡ነበረች፥ርሷም፡ጐባጣ፡ነበረች ፥ቀንታም፡ልትቆም፡ከቶ፡አልተቻላትም።
12፤ኢየሱስም፡ባያት፡ጊዜ፡ጠራትና፦አንቺ፡ሴት፥ከድካምሽ፡ተፈተ፟ሻል፡አላት፥እጁንም፡ጫነባት፤
13፤ያን፡ጊዜም፡ቀጥ፡አለች፥እግዚአብሔርንም፡አመሰገነች።
14፤የምኵራብ፡አለቃ፡ግን፡ኢየሱስ፡በሰንበት፡ስለ፡ፈወሰ፡ተቈጥቶ፡መለሰና፡ሕዝቡን፦ሊሠራባቸው፡የሚገ፟ባ፟ ፡ስድስት፡ቀኖች፡አሉ፤እንግዲህ፡በእነርሱ፡መጥታችኹ፡ተፈወሱ፡እንጂ፡በሰንበት፡አይደለም፡አለ።
15፤ጌታም፡መልሶ፦እናንተ፡ግብዞች፥ከእናንተ፡እያንዳንዱ፡በሰንበት፡በሬውን፡ወይስ፡አህያውን፡ከግርግሙ፡ፈ ቶ፟፡ውሃ፡ሊያጠጣው፡ይወስደው፡የለምን፧
16፤ይህችም፡የአብርሃም፡ልጅ፡ኾና፡ከዐሥራ፡ስምንት፡ዓመት፡ዠምሮ፡ሰይጣን፡ያሰራት፡በሰንበት፡ቀን፡ከዚህ፡ እስራት፡ልትፈታ፡አይገ፟ባ፟ምን፧አለው።
17፤ይህንም፡ሲናገር፡ሳለ፡የተቃወሙት፡ዅሉ፡ዐፈሩ፤ከርሱም፡በተደረገው፡ድንቅ፡ዅሉ፡ሕዝቡ፡ዅሉ፡ደስ፡አላቸ ው።
18፤ርሱም፦የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ምን፡ትመስላለች፥በምንስ፡አስመስላታለኹ፧
19፤ሰው፡ወስዶ፡በአትክልቱ፡የጣላትን፡የሰናፍጭ፡ቅንጣት፡ትመስላለች፤አደገችም፡ታላቅ፡ዛፍም፡ኾነች፥የሰማ ይ፡ወፎችም፡በቅርንጫፎቿ፡ሰፈሩ፡አለ።
20፤ደግሞም፥የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡በምን፡አስመስላታለኹ፧
21፤ሴት፡ወስዳ፡ዅሉ፡እስኪቦካ፡ድረስ፡በሦስት፡መስፈሪያ፡ዱቄት፡የሸሸገችውን፡ርሾ፡ትመስላለች፡አለ።
22፤ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ሲኼድ፡ከተማዎችንና፡መንደሮችን፡እያስተማረ፡ያልፍ፡ነበር።
23፤አንድ፡ሰውም፦ጌታ፡ሆይ፥የሚድኑ፡ጥቂቶች፡ናቸውን፧አለው።ርሱም፡እንዲህ፡አላቸው፦
24፤በጠበበው፡በር፡ለመግባት፡ተጋደሉ፤እላችዃለኹና፥ብዙዎች፡ሊገቡ፡ይፈልጋሉ፡አይችሉምም።
25፤ባለቤቱ፡ተነሥቶ፡በሩን፡ከቈለፈ፡በዃላ፥እናንተ፡በውጭ፡ቆማችኹ፦ጌታ፡ሆይ፥ጌታ፡ሆይ፥ክፈትልን፡እያላች ኹ፡በሩን፡ልታንኳኩ፡ትዠምራላችኹ፡ርሱም፡መልሶ፦ከወዴት፡እንደ፡ኾናችኹ፡አላውቃችኹም፡ይላችዃል።
26፤በዚያን፡ጊዜም፦በፊትኽ፡በላን፡ጠጣንም፡በአደባባያችንም፡አስተማርኽ፡ልትሉ፡ትዠምራላችኹ፤
27፤ርሱም፦እላችዃለኹ፥ከወዴት፡እንደ፡ኾናችኹ፡አላውቃችኹም፤ዅላችኹ፡ዐመፀኛዎች፥ከእኔ፡ራቁ፡ይላችዃል።
28፤አብርሃምንና፡ይሥሐቅን፡ያዕቆብንም፡ነቢያትንም፡ዅሉ፡በእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ባያችኹ፡ጊዜ፥እናንተ፡ ግን፡ወደ፡ውጭ፡ተጥላችኹ፡ስትቀሩ፥በዚያ፡ልቅሶና፡ጥርስ፡ማፋጨት፡ይኾናል።
29፤ከምሥራቅና፡ከምዕራብም፡ከሰሜንና፡ከደቡብም፡ይመጣሉ፥በእግዚአብሔርም፡መንግሥት፡በማእዱ፡ይቀመጣሉ።
30፤እንሆም፥ከዃለኛዎች፡ፊተኛዎች፡የሚኾኑ፡አሉ፥ከፊተኛዎችም፡ዃለኛዎች፡የሚኾኑ፡አሉ።
31፤በዚያን፡ሰዓት፡ከፈሪሳውያን፡አንዳንዱ፡ቀርበው፦ሄሮድስ፡ሊገድልኽ፡ይወዳልና፥ከዚህ፡ውጣና፡ኺድ፡አሉት ።
32፤እንዲህም፡አላቸው፦ኼዳችኹ፡ለዚያች፡ቀበሮ፦እንሆ፥ዛሬና፡ነገ፡አጋንንትን፡አወጣለኹ፡በሽተኛዎችንም፡እ ፈውሳለኹ፥በሦስተኛውም፡ቀን፡እፈጸማለኹ፡በሏት።
33፤ዳሩ፡ግን፡ነቢይ፡ከኢየሩሳሌም፡ውጭ፡ይጠፋ፡ዘንድ፡አይገ፟ባ፟ውምና፥ዛሬና፡ነገ፣ከነገ፡በስቲያም፡ልኼድ ፡ያስፈልገኛል።
34፤ኢየሩሳሌም፥ኢየሩሳሌም፥ነቢያትን፡የምትገድል፡ወደ፡ርሷ፡የተላኩትንም፡የምትወግር፥ዶሮ፡ጫጩቶቿን፡በክ ንፎቿ፡በታች፡እንደምትሰበስብ፡ልጆችሽን፡እሰበስብ፡ዘንድ፡ስንት፡ጊዜ፡ወደድኹ፥እናንተም፡አልወደዳችኹም።
35፤እንሆ፥ቤታችኹ፡የተፈታ፡ኾኖ፡ይቀርላችዃል።እላችዃለኹም፦በጌታ፡ስም፡የሚመጣ፡የተባረከ፡ነው፡እስክትሉ ፡ድረስ፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አታዩኝም።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡14።______________
ምዕራፍ፡14፤
1፤በሰንበትም፡ከፈሪሳውያን፡አለቃዎች፡ወደ፡አንዱ፡ቤት፡እንጀራ፡ሊበላ፡በገባ፡ጊዜ፡እነርሱ፡ይጠባበቁት፡ነ በር።
2፤እንሆም፥ሆዱ፡የተነፋ፡ሰው፡በፊቱ፡ነበረ።
3፤ኢየሱስም፡መልሶ፦በሰንበት፡መፈወስ፡ተፈቅዷልን፡ወይስ፡አልተፈቀደም፧ብሎ፡ለሕግ፡ዐዋቂዎችና፡ለፈሪሳውያ ን፡ተናገረ።
4፤እነርሱ፡ግን፡ዝም፡አሉ።ይዞም፡ፈወሰውና፡አሰናበተው።
5፤ከእናንተ፡አህያው፡ወይስ፡በሬው፡በጕድጓድ፡ቢወድቅ፡በሰንበት፡ወዲያው፡የማያወጣው፡ማን፡ነው፧አላቸው።
6፤ስለዚህ፡ነገርም፡ሊመልሱለት፡አልተቻላቸውም።
7፤የታደሙትንም፡የከበሬታ፡ስፍራ፡እንደ፡መረጡ፡ተመልክቶ፡ምሳሌ፡ነገራቸው፡እንዲህ፡ሲል፦
8፤ማንም፡ለሰርግ፡ቢጠራኽ፡በከበሬታ፡ስፍራ፡አትቀመጥ፤ምናልባት፡ከአንተ፡ይልቅ፡የከበረ፡ተጠርቶ፡ይኾናልና ፥አንተን፡ርሱንም፡የጠራ፡መጥቶ፦
9፤ለዚህ፡ስፍራ፡ተውለት፡ይልኻል፥በዚያን፡ጊዜም፡እያፈርኽ፡በዝቅተኛው፡ስፍራ፡ልትኾን፡ትዠምራለኽ።
10፤ነገር፡ግን፥በተጠራኽ፡ጊዜ፥የጠራኽ፡መጥቶ፦ወዳጄ፡ሆይ፥ወደ፡ላይ፡ውጣ፡እንዲልኽ፥ኼደኽ፡በዝቅተኛው፡ስ ፍራ፡ተቀመጥ፤ያን፡ጊዜም፡ከአንተ፡ጋራ፡በተቀመጡት፡ዅሉ፡ፊት፡ክብር፡ይኾንልኻል።
11፤ራሱን፡ከፍ፡የሚያደርግ፡ዅሉ፡ይዋረዳልና፥ራሱንም፡የሚያዋርድ፡ከፍ፡ይላል።
12፤የጠራውንም፡ደግሞ፡እንዲህ፡አለው፦ምሳ፡ወይም፡እራት፡ባደረግኽ፡ጊዜ፥እነርሱ፡ደግሞ፡በተራቸው፡ምናልባ ት፡እንዳይጠሩኽ፡ብድራትም፡እንዳይመልሱልኽ፥ወዳጆችኽንና፡ወንድሞችኽን፡ዘመዶችኽንም፡ባለጠጋዎች፡ጎረቤቶ ችኽንም፡አትጥራ።
13፤ነገር፡ግን፥ግብዣ፡ባደረግኽ፡ጊዜ፡ድኻዎችንና፡ጕንድሾችን፡ዐንካሳዎችንም፡ዕውሮችንም፡ጥራ፤
14፤የሚመልሱት፡ብድራት፡የላቸውምና፡ብፁዕ፡ትኾናለኽ፤በጻድቃን፡ትንሣኤ፡ይመለስልኻልና።
15፤ከተቀመጡትም፡አንዱ፡ይህን፡ሰምቶ፦በእግዚአብሔር፡መንግሥት፡እንጀራ፡የሚበላ፡ብፁዕ፡ነው፡አለው።
16፤ርሱ፡ግን፡እንዲህ፡አለው፦አንድ፡ሰው፡ታላቅ፡እራት፡አድርጎ፡ብዙዎችን፡ጠራ፤
17፤በእራትም፡ሰዓት፡የታደሙትን፦አኹን፡ተዘጋጅቷልና፥ኑ፡እንዲላቸው፡ባሪያውን፡ላከ።
18፤ዅላቸውም፡በአንድነት፡ያመካኙ፡ዠመር።የፊተኛው፦መሬት፡ገዝቻለኹ፡ወጥቼም፡ላየው፡በግድ፡ያስፈልገኛል፤ ይቅር፡እንድትለኝ፡እለምንኻለኹ፡አለው።
19፤ሌላውም፦ዐምስት፡ጥምድ፡በሬዎች፡ገዝቻለኹ፡ልፈትናቸውም፡እኼዳለኹ፤ይቅር፡እንድትለኝ፡እለምንኻለኹ፡አ ለው።
20፤ሌላውም፦ሚስት፡አግብቻለኹ፡ስለዚህም፡ልመጣ፡አልችልም፡አለው።
21፤ባሪያውም፡ደርሶ፡ይህን፡ለጌታው፡ነገረው።በዚያን፡ጊዜ፡ባለቤቱ፡ተቈጥቶ፡ባሪያውን፦ወደከተማ፡ጐዳናና፡ ወደ፡ስላች፡ፈጥነኽ፡ውጣ፡ድኻዎችንና፡ጕንድሾችን፡ዐንካሳዎችንና፡ዕውሮችንም፡ወደዚህ፡አግባ፡አለው።
22፤ባሪያውም፦ጌታ፡ሆይ፥እንዳዘዝኸኝ፡ተደርጓል፥ገናም፡ስፍራ፡አለ፡አለው።
23፤ጌታውም፡ባሪያውን፦ቤቴ፡እንዲሞላ፡ወደ፡መንገድና፡ወደ፡ቅጥር፡ውጣና፡ይገቡ፡ዘንድ፡ግድ፡በላቸው፤
24፤እላችዃለኹና፥ከታደሙት፡ከነዚያ፡ሰዎች፡አንድ፡ስንኳ፡እራቴን፡አይቀምስም፡አለው።
25፤ብዙም፡ሕዝብ፡ከርሱ፡ጋራ፡ይኼዱ፡ነበር፥ዘወር፡ብሎም፡እንዲህ፡አላቸው፦
26፤ማንም፡ወደ፡እኔ፡የሚመጣ፡ቢኖር፡አባቱንና፡እናቱን፡ሚስቱንም፡ልጆቹንም፡ወንድሞቹንም፡እኅቶቹንም፡የራ ሱን፡ሕይወት፡ስንኳ፡ሳይቀር፡ባይጠላ፥ደቀ፡መዝሙሬ፡ሊኾን፡አይችልም።
27፤ማንም፡መስቀሉን፡ተሸክሞ፡በዃላዬ፡የማይመጣ፥ደቀ፡መዝሙሬ፡ሊኾን፡አይችልም።
28፤ከእናንተ፡ግንብ፡ሊሠራ፡የሚወድ፡ለመደምደሚያ፡የሚበቃ፡ያለው፡እንደ፡ኾነ፡አስቀድሞ፡ተቀምጦ፡ከሳራውን ፡የማይቈጥር፡ማን፡ነው፧
29፤ያለዚያ፡መሠረቱን፡ቢመሠርት፥ሊደመድመውም፡ቢያቅተው፥ያዩት፡ዅሉ፦
30፤ይህ፡ሰው፡ሊሠራ፡ዠምሮ፡ሊደመድመው፡አቃተው፡ብለው፡ሊዘብቱበት፡ይዠምራሉ።
31፤ወይም፡ሌላውን፡ንጉሥ፡በጦርነት፡ሊጋጠም፡የሚኼድ፥ከኹለት፡እልፍ፡ጋራ፡የሚመጣበትን፡ባንድ፡እልፍ፡ሊገ ናኝ፡የሚችል፡እንደ፡ኾነ፡አስቀድሞ፡ተቀምጦ፡የማያስብ፡ንጉሥ፡ማን፡ነው፧
32፤ባይኾንስ፡ሌላው፡ገና፡ሩቅ፡ሳለ፡መልክተኛዎች፡ልኮ፡ዕርቅ፡ይለምናል።
33፤እንግዲህ፡እንደዚሁ፡ማንም፡ከእናንተ፡ያለውን፡ዅሉ፡የማይተው፡ደቀ፡መዝሙሬ፡ሊኾን፡አይችልም።
34፤ጨው፡መልካም፡ነው፤ጨው፡ዐልጫ፡ቢኾን፡ግን፡በምን፡ይጣፈጣል፧
35፤ለምድር፡ቢኾን፡ለፍግ፡መቈለያም፡ቢኾን፡አይረባም፤ወደ፡ውጭ፡ይጥሉታል።የሚሰማ፡ዦሮ፡ያለው፡ይስማ።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡15።______________
ምዕራፍ፡15፤
1፤ቀራጮችና፡ኀጢአተኛዎችም፡ዅሉ፡ሊሰሙት፡ወደ፡ርሱ፡ይቀርቡ፡ነበር።
2፤ፈሪሳውያንና፡ጻፊዎችም፦ይህስ፡ኀጢአተኛዎችን፡ይቀበላል፡ከነርሱም፡ጋራ፡ይበላል፡ብለው፡ርስ፡በርሳቸው፡ አንጐራጐሩ።
3፤ይህንም፡ምሳሌ፡ነገራቸው፡እንዲህ፡ሲል፦
4፤መቶ፡በግ፡ያለው፡ከነርሱም፡አንዱ፡ቢጠፋ፥ዘጠና፡ዘጠኙን፡በበረሓ፡ትቶ፡የጠፋውን፡እስኪያገኘው፡ድረስ፡ሊ ፈልገው፡የማይኼድ፡ከእናንተ፡ማን፡ነው፧
5፤ባገኘውም፡ጊዜ፡ደስ፡ብሎት፡በጫንቃው፡ይሸከመዋል፤
6፤ወደ፡ቤትም፡በመጣ፡ጊዜ፡ወዳጆቹንና፡ጎረቤቶቹን፡በአንድነት፡ጠርቶ፦የጠፋውን፡በጌን፡አግኝቼዋለኹና፡ከእ ኔ፡ጋራ፡ደስ፡ይበላችኹ፡ይላቸዋል።
7፤እላችዃለኹ፥እንዲሁ፡ንስሓ፡ከማያስፈልጋቸው፡ከዘጠና፡ዘጠኝ፡ጻድቃን፡ይልቅ፡ንስሓ፡በሚገባ፡ባንድ፡ኀጢአ ተኛ፡በሰማይ፡ደስታ፡ይኾናል።
8፤ወይም፡ዐሥር፡ድሪም፡ያላት፡አንድ፡ድሪም፡ቢጠፋባት፥መብራት፡አብርታ፡ቤቷንም፡ጠርጋ፡እስክታገኘው፡ድረስ ፡አጥብቃ፡የማትፈልግ፡ሴት፡ማን፡ናት፧
9፤ባገኘችውም፡ጊዜ፡ወዳጆቿንና፡ጎረቤቶቿን፡በአንድነት፡ጠርታ፦የጠፋውን፡ድሪሜን፡አግኝቼዋለኹና፡ከእኔ፡ጋ ራ፡ደስ፡ይበላችኹ፡ትላቸዋለች።
10፤እላችዃለኹ፥እንዲሁ፡ንስሓ፡በሚገባ፡ባንድ፡ኀጢአተኛ፡በእግዚአብሔር፡መላእክት፡ፊት፡ደስታ፡ይኾናል።
11፤እንዲህም፡አለ፦አንድ፡ሰው፡ኹለት፡ልጆች፡ነበሩት።
12፤ከነርሱም፡ታናሹ፡አባቱን፦አባቴ፡ሆይ፥ከገንዘብኽ፡የሚደርሰኝን፡ክፍል፡ስጠኝ፡አለው።ገንዘቡንም፡አካፈ ላቸው።
13፤ከጥቂት፡ቀንም፡በዃላ፡ታናሹ፡ልጅ፡ገንዘቡን፡ዅሉ፡ሰብስቦ፡ወደ፡ሩቅ፡አገር፡ኼደ፥ከዚያም፡እያባከነ፡ገ ንዘቡን፡በተነ።
14፤ዅሉንም፡ከከሰረ፡በዃላ፡በዚያች፡አገር፡ጽኑ፡ራብ፡ኾነ፥ርሱም፡ይጨነቅ፡ዠመር።
15፤ኼዶም፡ከዚያች፡አገር፡ሰዎች፡ከአንዱ፡ጋራ፡ተዳበለ፥ርሱም፡ዕሪያ፡ሊያሰማራ፡ወደ፡ሜዳ፡ሰደደው።
16፤ዕሪያዎችም፡ከሚበሉት፡ዐሠር፡ሊጠግብ፡ይመኝ፡ነበር፥የሚሰጠውም፡አልነበረም።
17፤ወደ፡ልቡም፡ተመልሶ፡እንዲህ፡አለ፦እንጀራ፡የሚተርፋቸው፡የአባቴ፡ሞያተኛዎች፡ስንት፡ናቸው፧እኔ፡ግን፡ ከዚህ፡በራብ፡እጠፋለኹ።
18፤ተነሥቼም፡ወደ፡አባቴ፡እኼዳለኹና፦አባቴ፡ሆይ፥በሰማይና፡በፊትኽ፡በደልኹ፥
19፤ወደ፡ፊትም፡ልጅኽ፡ልባል፡አይገ፟ባ፟ኝም፤ከሞያተኛዎችኽ፡እንደ፡አንዱ፡አድርገኝ፡እለዋለኹ።
20፤ተነሥቶም፡ወደ፡አባቱ፡መጣ።ርሱም፡ገና፡ሩቅ፡ሳለ፡አባቱ፡አየውና፡ዐዘነለት፥ሮጦም፡ዐንገቱን፡ዐቀፈውና ፡ሳመው።
21፤ልጁም፦አባቴ፡ሆይ፥በሰማይና፡በፊትኽ፡በደልኹ፥ወደ፡ፊትም፡ልጅኽ፡ልባል፡አይገ፟ባ፟ኝም፡አለው።
22፤አባቱ፡ግን፡ባሪያዎቹን፡አለ፦ፈጥናችኹ፡ከዅሉ፡የተሻለ፡ልብስ፡አምጡና፡አልብሱት፥ለእጁ፡ቀለበት፡ለእግ ሩም፡ጫማ፡ስጡ፤
23፤የሰባውን፡ፊሪዳ፡አምጥታችኹ፡ዕረዱት፥እንብላም፡ደስም፡ይበለን፤
24፤ይህ፡ልጄ፡ሞቶ፡ነበርና፥ደግሞም፡ሕያው፡ኾኗል፤ጠፍቶም፡ነበር፡ተገኝቷልም።ደስም፡ይላቸው፡ዠመር።
25፤ታላቁ፡ልጁ፡በዕርሻ፡ነበረ፤መጥቶም፡ወደ፡ቤት፡በቀረበ፡ጊዜ፡የመሰንቆና፡የዘፈን፡ድምፅ፡ሰማ፤
26፤ከብላቴናዎችም፡አንዱን፡ጠርቶ፦ይህ፡ምንድር፡ነው፧ብሎ፡ጠየቀ።
27፤ርሱም፦ወንድምኽ፡መጥቷልና፥በደኅና፡ስላገኘው፥አባትኽ፡የሰባውን፡ፊሪዳ፡ዐረደለት፡አለው።
28፤ተቈጣም፡ሊገባም፡አልወደደም፤አባቱም፡ወጥቶ፡ለመነው።
29፤ርሱ፡ግን፡መልሶ፡አባቱን፦እንሆ፥ይህን፡ያኽል፡ዓመት፡እንደ፡ባሪያ፡ተገዝቼልኻለኹ፡ከትእዛዝኽም፡ከቶ፡ አልተላለፍኹም፤ለኔም፡ከወዳጆቼ፡ጋራ፡ደስ፡እንዲለኝ፡አንድ፡ጥቦት፡ስንኳ፡አልሰጠኸኝም፤
30፤ነገር፡ግን፥ገንዘብኽን፡ከጋለሞታዎች፡ጋራ፡በልቶ፡ይህ፡ልጅኽ፡በመጣ፡ጊዜ፥የሰባውን፡ፊሪዳ፡ዐረድኽለት ፡አለው።
31፤ርሱ፡ግን፦ልጄ፡ሆይ፥አንተ፡ዅልጊዜ፡ከእኔ፡ጋራ፡ነኽ፥ለኔም፡የኾነ፡ዅሉ፡የአንተ፡ነው፤
32፤ዳሩ፡ግን፡ይህ፡ወንድምኽ፡ሞቶ፡ነበረ፡ሕያው፡ስለ፡ኾነ፡ጠፍቶም፡ነበር፡ስለ፡ተገኘ፡ደስ፡እንዲለን፡ፍሥ ሓም፡እንድናደርግ፡ይገ፟ባ፟ናል፡አለው።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡16።______________
ምዕራፍ፡16፤
1፤ደግሞም፡ለደቀ፡መዛሙርቱ፡እንዲህ፡አለ፦መጋቢ፡የነበረው፡አንድ፡ባለጠጋ፡ሰው፡ነበረ፥በርሱ፡ዘንድ፦ይህ፡ ሰው፡ያለኽን፡ይበትናል፡ብለው፡ከሰሱት።
2፤ጠርቶም፦ይህ፡የምሰማብኽ፡ምንድር፡ነው፧ወደ፡ፊት፡ለእኔ፡መጋቢ፡ልትኾን፡አትችልምና፡የመጋቢነትኽን፡ሒሳ ብ፡አስረክበኝ፡አለው።
3፤መጋቢውም፡በልቡ፦ጌታዬ፡መጋቢነቱን፡ከእኔ፡ይወስዳልና፥ምን፡ላድርግ፧ለመቈፈር፡ኀይል፡የለኝም፥መለመንም ፡ዐፍራለኹ።
4፤ከመጋቢነቱ፡ብሻር፡በቤታቸው፡እንዲቀበሉኝ፡የማደርገውን፡ዐውቃለኹ፡አለ።
5፤የጌታውንም፡ባለዕዳዎች፡እያንዳንዳቸውን፡ጠርቶ፡የፊተኛውን፦ለጌታዬ፡ምን፡ያኽል፡ዕዳ፡አለብኽ፧አለው።
6፤ርሱም፦መቶ፡ማድጋ፡ዘይት፡አለ።ደብዳቤኽን፡እንካ፡ፈጥነኽም፡ተቀምጠኽ፡ዐምሳ፡ብለኽ፡ጻፍ፡አለው።
7፤በዃላም፡ሌላውን፦አንተስ፡ስንት፡ዕዳ፡አለብኽ፧አለው።ርሱም፦መቶ፡ጫን፡ስንዴ፡አለ።ደብዳቤኽን፡እንካ፡ሰ ማንያ፡ብለኽም፡ጻፍ፡አለው።
8፤ጌታውም፡ዐመፀኛውን፡መጋቢ፡በልባምነት፡ስላደረገ፡አመሰገነው፡የዚህ፡ዓለም፡ልጆች፡ለትውልዳቸው፡ከብርሃ ን፡ልጆች፡ይልቅ፡ልባሞች፡ናቸውና።
9፤እኔም፡እላችዃለኹ፥የዐመፃ፡ገንዘብ፡ሲያልቅ፡በዘለዓለም፡ቤቶች፡እንዲቀበሏችኹ፥በርሱ፡ወዳጆችን፡ለራሳች ኹ፡አድርጉ።
10፤ከዅሉ፡በሚያንስ፡የታመነ፡በብዙ፡ደግሞ፡የታመነ፡ነው፥ከዅሉ፡በሚያንስም፡የሚያምፅ፡በብዙ፡ደግሞ፡ዐመፀ ኛ፡ነው።
11፤እንግዲያስ፡በዐመፃ፡ገንዘብ፡ካልታመናችኹ፥እውነተኛውን፡ገንዘብ፡ማን፡ዐደራ፡ይሰጣችዃል፧
12፤በሌላ፡ሰው፡ገንዘብ፡ካልታመናችኹ፥የእናንተን፡ማን፡ይሰጣችዃል፧
13፤ለኹለት፡ጌታዎች፡መገዛት፡የሚቻለው፡ባሪያ፡ማንም፡የለም፤ወይም፡አንዱን፡ይጠላልና፥ኹለተኛውንም፡ይወዳ ል፥ወይም፡ወደ፡አንዱ፡ይጠጋል፡ኹለተኛውንም፡ይንቃል።ለእግዚአብሔርና፡ለገንዘብ፡መገዛት፡አትችሉም።
14፤ገንዘብንም፡የሚወዱ፡ፈሪሳውያን፡ይህን፡ዅሉ፡ሰምተው፡ያፌዙበት፡ነበር።
15፤እንዲህም፡አላቸው፦ራሳችኹን፡በሰው፡ፊት፡የምታጸድቁ፡እናንተ፡ናችኹ፥ነገር፡ግን፥እግዚአብሔር፡ልባችኹ ን፡ያውቃል፤በሰው፡ዘንድ፡የከበረ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ርኵሰት፡ነውና።
16፤ሕግና፡ነቢያት፡እስከ፡ዮሐንስ፡ነበሩ፤ከዚያ፡ዠምሮ፡የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ይሰበካል፤ዅሉም፡ወደ፡ር ሷ፡በኀይል፡ይገቡባታል።
17፤ነገር፡ግን፥ከሕግ፡አንዲት፡ነጥብ፡ከምትወድቅ፡ሰማይና፡ምድር፡ሊያልፍ፡ይቀላል።
18፤ሚስቱንም፡የሚፈታ፡ዅሉ፡ሌላዪቱንም፡የሚያገባ፡ያመነዝራል፥ከባሏም፡የተፈታችውን፡የሚያገባ፡ያመነዝራል ።
19፤ቀይ፡ልብስና፡ቀጭን፡የተልባ፡እግር፡የለበሰ፡አንድ፡ባለጠጋ፡ሰው፡ነበረ፥ዕለት፡ዕለትም፡እየተመቸው፡በ ደስታ፡ይኖር፡ነበር።
20፤አልዓዛርም፡የሚባል፡አንድ፡ድኻ፡በቍስል፡ተወርሶ፡በደጁ፡ተኝቶ፡ነበር፥
21፤ከባለጠጋውም፡ማእድ፡ከሚወድቀው፡ፍርፋሪ፡ሊጠግብ፡ይመኝ፡ነበር፤ውሻዎች፡እንኳ፡መጥተው፡ቍስሎቹን፡ይል ሱ፡ነበር።
22፤ድኻውም፡ሞተ፥መላእክትም፡ወደአብርሃም፡ዕቅፍ፡ወሰዱት፤ባለጠጋው፡ደግሞ፡ሞተና፡ተቀበረ።
23፤በሲኦልም፡በሥቃይ፡ሳለ፡አሻቅቦ፡አብርሃምን፡በሩቅ፡አየ፡አልዓዛርንም፡በዕቅፉ።
24፤ርሱም፡እየጮኸ፦አብርሃም፡አባት፡ሆይ፥ማረኝ፥በዚህ፡ነበልባል፡እሣቀያለኹና፡የጣቱን፡ጫፍ፡በውሃ፡ነክሮ ፡ምላሴን፡እንዲያበርድልኝ፡አልዓዛርን፡ስደድልኝ፡አለ።
25፤አብርሃም፡ግን፦ልጄ፡ሆይ፥አንተ፡በሕይወትኽ፡ሳለኽ፡መልካም፡እንደ፡ተቀበልኽ፡ዐስብ፡አልዓዛርም፡እንዲ ሁ፡ክፉ፤አኹን፡ግን፡ርሱ፡በዚህ፡ይጽናናል፡አንተም፡ትሣቀያለኽ።
26፤ከዚህም፡ዅሉ፡ጋራ፡ከዚህ፡ወደ፡እናንተ፡ሊያልፉ፡የሚፈልጉ፡እንዳይችሉ፥ወዲያ፡ያሉ፡ደግሞ፡ወደ፡እኛ፡እ ንዳይሻገሩ፡በእኛና፡በእናንተ፡መካከል፡ታላቅ፡ገደል፡ተደርጓል፡አለ።
27፤ርሱም፦እንኪያስ፥አባት፡ሆይ፥ወዳባቴ፡ቤት፡እንድትሰደው፡እለምንኻለኹ፤ዐምስት፡ወንድሞች፡አሉኝና፤
28፤እነርሱ፡ደግሞ፡ወደዚህ፡ሥቃይ፡ስፍራ፡እንዳይመጡ፡ይመስክርላቸው፡አለ።
29፤አብርሃም፡ግን፦ሙሴና፡ነቢያት፡አሏቸው፤እነርሱን፡ይስሙ፡አለው።
30፤ርሱም፦አይደለም፥አብርሃም፡አባት፡ሆይ፥ነገር፡ግን፥ከሙታን፡አንዱ፡ቢኼድላቸው፡ንስሓ፡ይገባሉ፡አለ።
31፤ሙሴንና፡ነቢያትንም፡የማይሰሙ፡ከኾነ፥ከሙታንም፡እንኳ፡አንድ፡ቢነሣ፡አያምኑም፡አለው።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡17።______________
ምዕራፍ፡17፤
1፤ለደቀ፡መዛሙርቱም፡እንዲህ፡አለ፦መሰናክል፡ግድ፡ሳይመጣ፡አይቀርም፥ነገር፡ግን፥መሰናክሉን፡ለሚያመጣው፡ ወዮለት፤
2፤ከነዚህ፡ከታናናሾች፡አንዱን፡ከማሰናከል፡ይልቅ፡የወፍጮ፡ድንጋይ፡በዐንገቱ፡ታስሮ፡ወደ፡ባሕር፡ቢጣል፡ይ ጠቅመው፡ነበር።
3፤ለራሳችኹ፡ተጠንቀቁ።ወንድምኽ፡ቢበድልኽ፡ገሥጸው፥ቢጸጸትም፡ይቅር፡በለው።
4፤በቀንም፡ሰባት፡ጊዜ፡እንኳ፡ቢበድልኽ፡በቀንም፡ሰባት፡ጊዜ፦ተጸጸትኹ፡እያለ፡ወዳንተ፡ቢመለስ፥ይቅር፡በለ ው።
5፤ሐዋርያትም፡ጌታን፦እምነት፡ጨምርልን፡አሉት።
6፤ጌታም፡አለ፦የሰናፍጭ፡ቅንጣት፡የሚያኽል፡እምነት፡ቢኖራችኹ፥ይህን፡ሾላ፦ተነቅለኽ፡ወደ፡ባሕር፡ተተከል፡ ብትሉት፥ይታዘዝላችኹ፡ነበር።
7፤ከእናንተም፡የሚያርስ፡ወይም፡ከብትን፡የሚጠብቅ፡ባሪያ፡ያለው፥ከዕርሻ፡ሲመለስ፦ወዲያው፡ቅረብና፡በማእዱ ፡ተቀመጥ፡የሚለው፡ማን፡ነው፧
8፤የምበላውን፡እራቴን፡አሰናዳልኝ፥እስክበላና፡እስክጠጣ፡ድረስ፡ታጥቀኽ፡አገልግለኝ፥በዃላም፡አንተ፡ብላና ፡ጠጣ፡የሚለው፡አይደለምን፧
9፤ያንን፡ባሪያ፡ያዘዘውን፡ስላደረገ፡ያመሰግነዋልን፧
10፤እንዲሁ፡እናንተ፡ደግሞ፡የታዘዛችኹትን፡ዅሉ፡ባደረጋችኹ፡ጊዜ፦የማንጠቅም፡ባሪያዎች፡ነን፥ልናደርገው፡ የሚገ፟ባ፟ንን፡አድርገናል፡በሉ።
11፤ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡ሲኼድ፡በገሊላና፡በሰማርያ፡መካከል፡ዐለፈ።
12፤ወደ፡አንዲት፡መንደርም፡ሲገባ፡በሩቅ፡የቆሙት፡ዐሥር፡ለምጻሞች፡ተገናኙት፤
13፤እነርሱም፡እየጮኹ፦ኢየሱስ፡ሆይ፥አቤቱ፥ማረን፡አሉ።
14፤አይቶም፦ኺዱ፥ራሳችኹን፡ለካህናት፡አሳዩ፡አላቸው።
15፤እንሆም፥ሲኼዱ፡ነጹ።ከነርሱም፡አንዱ፡እንደ፡ተፈወሰ፡ባየ፡ጊዜ፡በታላቅ፡ድምፅ፡እግዚአብሔርን፡እያከበ ረ፡ተመለሰ፥
16፤እያመሰገነውም፡በእግሩ፡ፊት፡በግንባሩ፡ወደቀ፤ርሱም፡ሳምራዊ፡ነበረ።
17፤ኢየሱስም፡መልሶ፦ዐሥሩ፡አልነጹምን፧ዘጠኙስ፡ወዴት፡አሉ፧
18፤ከዚህ፡ከልዩ፡ወገን፡በቀር፡እግዚአብሔርን፡ሊያከብሩ፡የተመለሱ፡አልተገኙም፡አለ።
19፤ርሱንም፦ተነሣና፡ኺድ፤እምነትኽ፡አድኖኻል፡አለው።
20፤ፈሪሳውያንም፦የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡መቼ፡ትመጣለች፡ብለው፡ቢጠይቁት፥መልሶ፦የእግዚአብሔር፡መንግሥ ት፡በመጠባበቅ፡አትመጣም፤
21፤ደግሞም፦እንዃት፡በዚህ፡ወይም፦እንዃት፡በዚያ፡አይሏትም።እንሆ፥የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡በመካከላችኹ ፡ናትና፥አላቸው።
22፤ለደቀ፡መዛሙርቱም፡እንዲህ፡አለ፦ከሰው፡ልጅ፡ቀኖች፡አንዱን፡ልታዩ፡የምትመኙበት፡ወራት፡ይመጣል፡አታዩ ትምም።
23፤እነርሱም፦እንሆ፥በዚህ፥ወይም፦እንሆ፥በዚያ፡ይሏችዃል፤አትኺዱ፡አትከተሏቸውም።
24፤መብረቅ፡በርቆ፡ከሰማይ፡በታች፡ካለ፡ካንድ፡አገር፡ከሰማይ፡በታች፡ወዳለው፡ወደ፡ሌላ፡አገር፡እንደሚያበ ራ፥የሰው፡ልጅ፡በቀኑ፡እንዲህ፡ይኾናል።
25፤አስቀድሞ፡ግን፡ብዙ፡መከራ፡እንዲቀበል፥ከዚህም፡ትውልድ፡እንዲጣል፡ይገ፟ባ፟ዋል።
26፤በኖኅ፡ዘመንም፡እንደ፡ኾነ፥በሰው፡ልጅ፡ዘመን፡ደግሞ፡እንዲሁ፡ይኾናል።
27፤ኖኅ፡ወደ፡መርከብ፡እስከገባበት፡ቀን፡ድረስ፥ይበሉና፡ይጠጡ፡ያገቡና፡ይጋቡም፡ነበር፥የጥፋት፡ውሃም፡መ ጣ፡ዅሉንም፡አጠፋ።
28፤እንዲሁ፡በሎጥ፡ዘመን፡እንደ፡ኾነ፤ይበሉ፡ይጠጡም፡ይገዙም፡ይሸጡም፡ይተክሉም፡ቤትም፡ይሠሩ፡ነበር፤
29፤ሎጥ፡ከሰዶም፡በወጣበት፡ቀን፡ግን፡ከሰማይ፡እሳትና፡ዲን፡ዘነበ፡ዅሉንም፡አጠፋ።
30፤የሰው፡ልጅ፡በሚገለጥበት፡ቀን፡እንዲሁ፡ይኾናል።
31፤በዚያም፡ቀን፡በሰገነት፡ያለ፡በቤቱ፡ያለውን፡ዕቃ፡ሊወስድ፡አይውረድ፥እንዲሁም፡በዕርሻ፡ያለ፡ወደ፡ዃላ ው፡አይመለስ።
32፤የሎጥን፡ሚስት፡ዐስቧት።
33፤ነፍሱን፡ሊያድን፡የሚፈልግ፡ዅሉ፡ያጠፋታል፥ነፍሱንም፡የሚያጠፋ፡ዅሉ፡በሕይወት፡ይጠብቃታል።
34፤እላችዃለኹ፥በዚያች፡ሌሊት፡ኹለት፡ሰዎች፡ባንድ፡ዐልጋ፡ይኾናሉ፤አንዱ፡ይወሰዳል፡ኹለተኛውም፡ይቀራል።
35፤ኹለት፡ሴቶች፡ባንድ፡ወፍጮ፡ይፈጫሉ፤አንዲቱ፡ትወሰዳለች፡ኹለተኛዪቱም፡ትቀራለች።
36፤ኹለት፡ሰዎች፡በዕርሻ፡ይኾናሉ፤አንዱ፡ይወሰዳል፡ኹለተኛውም፡ይቀራል።
37፤መልሰውም፦ጌታ፡ሆይ፥ወዴት፡ነው፧አሉት።ርሱም፦ሥጋ፡ወዳለበት፡በዚያ፡አሞራዎች፡ይሰበሰባሉ፡አላቸው።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡18።______________
ምዕራፍ፡18፤
1፤ሳይታክቱም፡ዘወትር፡ሊጸልዩ፡እንዲገባቸው፡የሚል፡ምሳሌን፡ነገራቸው፥
2፤እንዲህ፡ሲል፦በአንዲት፡ከተማ፡እግዚአብሔርን፡የማይፈራ፡ሰውንም፡የማያፍር፡አንድ፡ዳኛ፡ነበረ።
3፤በዚያችም፡ከተማ፡አንዲት፡መበለት፡ነበረች፥ወደ፡ርሱም፡እየመጣች፦ከባላጋራዬ፡ፍረድልኝ፡ትለው፡ነበር።
4፤ዐያሌ፡ቀንም፡አልወደደም፤ከዚህ፡በዃላ፡ግን፡በልቡ፦ምንም፡እግዚአብሔርን፡ባልፈራ፡ሰውንም፡ባላፍር፥
5፤ይህች፡መበለት፡ስለምታደክመኝ፡ዅልጊዜም፡እየመጣች፡እንዳታውከኝ፡እፈርድላታለኹ፡አለ።
6፤ጌታም፡አለ፦ዐመፀኛው፡ዳኛ፡ያለውን፡ስሙ።
7፤እግዚአብሔር፡እንኪያስ፡ቀንና፡ሌሊት፡ወደ፡ርሱ፡ለሚጮኹ፡ለሚታገሣቸውም፡ምርጦቹ፡አይፈርድላቸውምን፧
8፤እላችዃለኹ፥ፈጥኖ፡ይፈርድላቸዋል።ነገር፡ግን፥የሰው፡ልጅ፡በመጣ፡ጊዜ፡በምድር፡እምነትን፡ያገኝ፡ይኾንን ፧
9፤ጻድቃን፡እንደ፡ኾኑ፡በራሳቸው፡ለሚታመኑና፡ሌላዎቹን፡ዅሉ፡በጣም፡ለሚንቁ፡ይህን፡ምሳሌ፡ነገራቸው፥
10፤እንዲህ፡ሲል፦ኹለት፡ሰዎች፡ሊጸልዩ፡ወደ፡መቅደስ፡ወጡ፥አንዱ፡ፈሪሳዊ፡ኹለተኛውም፡ቀራጭ።
11፤ፈሪሳዊም፡ቆሞ፡በልቡ፡ይህን፡ሲጸልይ፦እግዚአብሔር፡ሆይ፥እንደ፡ሌላ፡ሰው፡ዅሉ፥ቀማኛዎችና፡ዐመፀኛዎች ፡አመንዝራዎችም፥ወይም፡እንደዚህ፡ቀራጭ፡ስላልኾንኹ፡አመሰግንኻለኹ፤
12፤በየሳምንቱ፡ኹለት፡ጊዜ፡እጦማለኹ፥ከማገኘውም፡ዅሉ፡ዓሥራት፡አወጣለኹ፡አለ።
13፤ቀራጩ፡ግን፡በሩቅ፡ቆሞ፡ዐይኖቹን፡ወደ፡ሰማይ፡ሊያነሣ፡እንኳ፡አልወደደም፥ነገር፡ግን፦አምላክ፡ሆይ፥እ ኔን፡ኀጢአተኛውን፡ማረኝ፡እያለ፡ደረቱን፡ይደቃ፡ነበር።
14፤እላችዃለኹ፥ከዚያ፡ይልቅ፡ይህ፡ጻድቅ፡ኾኖ፡ወደ፡ቤቱ፡ተመለሰ፤ራሱን፡ከፍ፡የሚያደርግ፡ዅሉ፡ይዋረዳልና ፥ራሱን፡ግን፡የሚያዋርድ፡ከፍ፡ይላል።
15፤እንዲዳስሳቸውም፡ሕፃናትን፡ደግሞ፡ወደ፡ርሱ፡አመጡ፤ደቀ፡መዛሙርቱም፡አይተው፡ገሠጿቸው።
16፤ኢየሱስ፡ግን፡ሕፃናትን፡ወደ፡ርሱ፡ጠርቶ፦ሕፃናት፡ወደ፡እኔ፡ይመጡ፡ዘንድ፡ተዉአቸው፡አትከልክሏቸውም፤ የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡እንደ፡እነዚህ፡ላሉት፡ናትና።
17፤እውነት፡እላችዃለኹ፥የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡እንደ፡ሕፃን፡የማይቀበላት፡ዅሉ፡ከቶ፡አይገባባትም፡አ ለ።
18፤ከአለቃዎችም፡አንዱ፦ቸር፡መምህር፥የዘለዓለምን፡ሕይወት፡እንድወርስ፡ምን፡ላድርግ፧ብሎ፡ጠየቀው።
19፤ኢየሱስም፦ስለ፡ምን፡ቸር፡ትለኛለኽ፧ከአንዱ፡ከእግዚአብሔር፡በቀር፡ቸር፡ማንም፡የለም።
20፤ትእዛዛቱን፡ታውቃለኽ፥አታመንዝር፥አትግደል፥አትስረቅ፥በሐሰት፡አትመስክር፥አባትኽንና፡እናትኽን፡አክ ብር፡አለው።
21፤ርሱም፦ይህን፡ዅሉ፡ከሕፃንነቴ፡ዠምሬ፡ጠብቄያለኹ፡አለ።
22፤ኢየሱስም፡ይህን፡ሰምቶ፦አንዲት፡ገና፡ቀርታኻለች፤ያለኽን፡ዅሉ፡ሽጠኽ፡ለድኻዎች፡ስጥ፥በሰማይም፡መዝገ ብ፡ታገኛለኽ፥መጥተኽም፡ተከተለኝ፡አለው።
23፤ርሱ፡ግን፡ይህን፡ሰምቶ፡እጅግ፡ባለጠጋ፡ነበርና፥ብዙ፡ዐዘነ።
24፤ኢየሱስም፡ብዙ፡እንዳዘነ፡አይቶ፦ገንዘብ፡ላላቸው፡ወደእግዚአብሔር፡መንግሥት፡መግባት፡እንዴት፡ጭንቅ፡ ይኾናል።
25፤ባለጠጋ፡ወደእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ከሚገባ፡ይልቅ፡ግመል፡በመርፌ፡ቀዳዳ፡ሊገባ፡ይቀላል፡አለ።
26፤የሰሙትም፦እንግዲህ፡ማን፡ሊድን፡ይችላል፧አሉ።
27፤ርሱ፡ግን፦በሰው፡ዘንድ፡የማይቻል፡በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ይቻላል፡አለ።
28፤ጴጥሮስም፦እንሆ፥እኛ፡ዅሉን፡ትተን፡ተከተልንኽ፡አለ።
29፤ርሱም፦እውነት፡እላችዃለኹ፥ስለእግዚአብሔር፡መንግሥት፡ቤትን፡ወይም፡ወላጆችን፡ወይም፡ወንድሞችን፡ወይ ም፡ሚስትን፡ወይም፡ልጆችን፡የተወ፥
30፤በዚህ፡ዘመን፡ብዙ፡ዕጥፍ፡በሚመጣውም፡ዓለም፡የዘለዓለምን፡ሕይወት፡የማይቀበል፡ማንም፡የለም፡አላቸው።
31፤ዐሥራ፡ኹለቱንም፡ወደ፡ርሱ፡አቅርቦ፡እንዲህ፡አላቸው፦እንሆ፥ወደ፡ኢየሩሳሌም፡እንወጣለን፥ስለሰው፡ልጅ ም፡በነቢያት፡የተጻፈው፡ዅሉ፡ይፈጸማል።
32፤ለአሕዛብ፡አሳልፈው፡ይሰጡታልና፥ይዘብቱበትማል፡ያንገላቱትማል፡ይተፉበትማል፤
33፤ከገረፉትም፡በዃላ፡ይገድሉታል፥በሦስተኛውም፡ቀን፡ይነሣል።
34፤እነርሱም፡ከዚህ፡ነገር፡ምንም፡አላስተዋሉም፥ይህም፡ቃል፡ተሰውሮባቸው፡ነበር፥የተናገረውንም፡አላወቁም ።
35፤ወደ፡ኢያሪኮም፡በቀረበ፡ጊዜ፡አንድ፡ዕውር፡እየለመነ፡በመንገድ፡ዳር፡ተቀምጦ፡ነበር።
36፤ሕዝብም፡ሲያልፍ፡ሰምቶ፦ይህ፡ምንድር፡ነው፧ብሎ፡ጠየቀ።
37፤እነርሱም፦የናዝሬቱ፡ኢየሱስ፡ያልፋል፡ብለው፡አወሩለት።
38፤ርሱም፦የዳዊት፡ልጅ፥ኢየሱስ፡ሆይ፥ማረኝ፡እያለ፡ጮኸ።
39፤በስተፊት፡ይኼዱ፡የነበሩትም፡ዝም፡እንዲል፡ገሠጹት፤ርሱ፡ግን፦የዳዊት፡ልጅ፡ሆይ፥ማረኝ፡እያለ፡አብዝቶ ፡ጮኸ።
40፤ኢየሱስም፡ቆሞ፡ወደ፡ርሱ፡እንዲያመጡት፡አዘዘ።በቀረበም፡ጊዜ፦ምን፡ላደርግልኽ፡ትወዳለኽ፧ብሎ፡ጠየቀው ።
41፤ርሱም፦ጌታ፡ሆይ፥አይ፡ዘንድ፡ነው፡አለው።
42፤ኢየሱስም፦እይ፤እምነትኽ፡አድኖኻል፡አለው።
43፤በዚያን፡ጊዜም፡አየ፥እግዚአብሔርም፡እያከበረ፡ተከተለው።ሕዝቡም፡ዅሉ፡አይተው፡እግዚአብሔርን፡አመሰገ ኑ።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡19።______________
ምዕራፍ፡19፤
1-2፤ወደ፡ኢያሪኮም፡ገብቶ፡ያልፍ፡ነበር።እንሆም፡ዘኬዎስ፡የሚባል፡ሰው፥ርሱም፡የቀራጮች፡አለቃ፡ነበረ፥ባለ ጠጋም፡ነበረ።
3፤ኢየሱስንም፡የትኛው፡እንደ፡ኾነ፡ሊያይ፡ይፈልግ፡ነበር፤ቁመቱም፡ዐጪር፡ነበረና፡ስለሕዝቡ፡ብዛት፡አቃተው ።
4፤በዚያችም፡መንገድ፡ያልፍ፡ዘንድ፡አለውና፡ያየው፡ዘንድ፡ወደ፡ፊት፡ሮጦ፡ባንድ፡ሾላ፡ላይ፡ወጣ።
5፤ኢየሱስም፡ወደዚያ፡ስፍራ፡በደረሰ፡ጊዜ፥አሻቅቦ፡አየና፦ዘኬዎስ፡ሆይ፥ዛሬ፡በቤትኽ፡እውል፡ዘንድ፡ይገ፟ባ ፟ኛልና፥ፈጥነኽ፡ውረድ፡አለው።
6፤ፈጥኖም፡ወረደ፡በደስታም፡ተቀበለው።
7፤ዅሉም፡አይተው፦ከኀጢአተኛ፡ሰው፡ጋራ፡ሊውል፡ገባ፡ብለው፡አንጐራጐሩ።
8፤ዘኬዎስ፡ግን፡ቆሞ፡ጌታን፦ጌታ፡ሆይ፥ካለኝ፡ዅሉ፡እኩሌታውን፡ለድኻዎች፡እሰጣለኹ፤ማንንም፡በሐሰት፡ከስሼ ፡እንደ፡ኾንኹ፡አራት፡ዕጥፍ፡እመልሳለኹ፡አለው።
9፤ኢየሱስም፦ርሱ፡ደግሞ፡የአብርሃም፡ልጅ፡ነውና፥ዛሬ፡ለዚህ፡ቤት፡መዳን፡ኾኖለታል፤
10፤የሰው፡ልጅ፡የጠፋውን፡ሊፈልግና፡ሊያድን፡መጥቷልና፥አለው።
11፤እነርሱም፡ይህን፡ሲሰሙ፥ወደ፡ኢየሩሳሌም፡መቅረቡ፡ስለ፡ኾነ፡የእግዚአብሔርም፡መንግሥት፡ፈጥኖ፡ሊገለጥ ፡እንዳለው፡ስለ፡መሰላቸው፡ምሳሌ፡ጭምር፡ተናገረ።
12፤ስለዚህም፡እንዲህ፡አላቸው፦አንድ፡መኰንን፡ለራሱ፡መንግሥትን፡ይዞ፡ሊመለስ፡ወደ፡ሩቅ፡አገር፡ኼደ።
13፤ዐሥር፡ባሪያዎችንም፡ጠርቶ፡ዐሥር፡ምናን፡ሰጣቸውና፦እስክመጣ፡ድረስ፡ነግዱ፡አላቸው።
14፤የአገሩ፡ሰዎች፡ግን፡ይጠሉት፡ነበርና፦ይህ፡በላያችን፡ሊነግሥ፡አንወድም፡ብለው፡በዃላው፡መልክተኛዎችን ፡ላኩ።
15፤መንግሥትንም፡ይዞ፡በተመለሰ፡ጊዜ፥ገንዘብ፡የሰጣቸውን፡እነዚህን፡ባሪያዎች፡ነግደው፡ምን፡ያኽል፡እንዳ ተረፉ፡ያውቅ፡ዘንድ፡እንዲጠሩለት፡አዘዘ።
16፤የፊተኛውም፡ደርሶ፦ጌታ፡ሆይ፥ምናንኽ፡ዐሥር፡ምናን፡አተረፈ፡አለው።
17፤ርሱም፦መልካም፥አንተ፡በጎ፡ባሪያ፥በጥቂት፡የታመንኽ፡ስለ፡ኾንኽ፡በዐሥር፡ከተማዎች፡ላይ፡ሥልጣን፡ይኹ ንልኽ፡አለው።
18፤ኹለተኛውም፡መጥቶ፦ጌታ፡ሆይ፥ምናንኽ፡ዐምስት፡ምናን፡አተረፈ፡አለው።
19፤ይህንም፡ደግሞ፦አንተም፡በዐምስት፡ከተማዎች፡ላይ፡ኹን፡አለው።
20፤ሌላውም፡መጥቶ፦ጌታ፡ሆይ፥በጨርቅ፡ጠቅልዬ፡የጠበቅዃት፡ምናንኽ፡እንሆ፤
21፤ፈርቼኻለኹና፥ጨካኝ፡ሰው፡ስለ፡ኾንኽ፤ያላኖርኸውን፡ትወስዳለኽ፡ያልዘራኸውንም፡ታጭዳለኽ፡አለው።
22፤ርሱም፦አንተ፡ክፉ፡ባሪያ፥አፍኽ፡በተናገረው፡እፈርድብኻለኹ።እኔ፡ያላኖርኹትን፡የምወስድና፡ያልዘራኹት ን፡የማጭድ፡ጨካኝ፡ሰው፡እንደ፡ኾንኹ፡ዐወቅኽ፤ምን፡ነው፡ገንዘቤን፡ለለዋጮች፡ዐደራ፡ያልሰጠኸው፧
23፤እኔም፡መጥቼ፡ከትርፉ፡ጋራ፡እወስደው፡ነበር፡አለው።
24፤በዚያም፡ቆመው፡የነበሩትን፦ምናኑን፡ውሰዱበት፡ዐሥሩ፡ምናን፡ላለውም፡ስጡት፡አላቸው።
25፤እነርሱም፦ጌታ፡ሆይ፥ዐሥር፡ምናን፡አለው፡አሉት።
26፤እላችዃለኹ፥ላለው፡ዅሉ፡ይሰጠዋል፥ከሌለው፡ግን፡ያው፡ያለው፡ስንኳ፡ይወሰድበታል።
27፤ነገር፡ግን፥እነዚያን፡በላያቸው፡ልነግሥ፡ያልወደዱትን፡ጠላቶቼን፡ወደዚህ፡አምጧቸው፡በፊቴም፡ዕረዷቸው ።
28፤ይህንም፡ከተናገረ፡በዃላ፥ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ሲወጣ፡ይቀድማቸው፡ነበር።
29፤ደብረ፡ዘይትም፡በሚባል፡ተራራ፡አጠገብ፡ወዳሉት፡ወደ፡ቤተ፡ፋጌና፡ወደ፡ቢታንያ፡በቀረበ፡ጊዜ፥ከደቀ፡መ ዛሙርቱ፡ኹለቱን፡ላከና፦
30፤በፊታችኹ፡ወዳለችው፡መንደር፡ኺዱ፥ወደ፡ርሷም፡ገብታችኹ፡ከሰው፡ማንም፡ገና፡ያልተቀመጠበት፡ውርንጫ፡ታ ስሮ፡ታገኛላችኹ፥ፈታ፟ችኹም፡አምጡት።
31፤ማንም፦ስለ፡ምን፡ትፈቱታላችኹ፧ብሎ፡ቢጠይቃችኹ፥እንዲሁ፦ለጌታ፡ያስፈልገዋል፡በሉ፡አላቸው።
32፤የተላኩትም፡ኼደው፡እንዳላቸው፡አገኙ።
33፤እነርሱም፡ውርንጫውን፡ሲፈቱ፡ጌታዎቹ፦ውርንጫውን፡ስለ፡ምን፡ትፈቱታላችኹ፧አሏቸውም፡
34፤እነርሱም፦ለጌታ፡ያስፈልገዋል፡አሉ።
35፤ወደ፡ኢየሱስም፡አመጡት፥በውርንጫውም፡ላይ፡ልብሳቸውን፡ጭነው፡ኢየሱስን፡አስቀመጡት።
36፤ሲኼድም፡ልብሳቸውን፡በመንገድ፡ያነጥፉ፡ነበር።
37፤ወደ፡ደብረ፡ዘይት፡ቍልቍለትም፡አኹን፡በቀረበ፡ጊዜ፥ደቀ፡መዛሙርቱ፡ዅላቸው፡ደስ፡እያላቸው፡ተኣምራትን ፡ዅሉ፡ስላዩ፡በታላቅ፡ድምፅ፡እግዚአብሔርን፡ሊያመሰግኑ፡ዠምረው።
38፤በጌታ፡ስም፡የሚመጣ፡ንጉሥ፡የተባረከ፡ነው፤በሰማይ፡ሰላም፡በአርያምም፡ክብር፡አሉ።
39፤ከሕዝብም፡መካከል፡ከፈሪሳውያን፡አንዳንዱ፦መምህር፡ሆይ፥ደቀ፡መዛሙርትኽን፡ገሥጻቸው፡አሉት።
40፤መልሶም፦እላችዃለኹ፥እነዚህ፡ዝም፡ቢሉ፡ድንጋዮች፡ይጮኻሉ፡አላቸው።
41፤ሲቀርብም፡ከተማዪቱን፡አይቶ፡አለቀሰላት፥
42፤እንዲህ፡እያለ፦ለሰላምሽ፡የሚኾነውን፡በዚህ፡ቀን፡አንቺስ፡ስንኳ፡ብታውቂ፤አኹን፡ግን፡ከዐይንሽ፡ተሰው ሯል።
43፤ወራት፡ይመጣብሻልና፥ጠላቶችሽም፡ቅጥር፡ይቀጥሩብሻል፡ይከቡሻልም፡በየበኵሉም፡ያስጨንቁሻል፤
44፤አንቺንም፡ባንቺም፡ውስጥ፡የሚኖሩትን፡ልጆችሽን፡ወደ፡ታች፡ይጥላሉ፥ባንቺ፡ውስጥም፡ድንጋይ፡በድንጋይ፡ ላይ፡አይተዉም፥የመጐ፟ብኘትሽን፡ዘመን፡አላወቅሺምና።
45፤ወደ፡መቅደስም፡ገብቶ፡በርሱ፡የሚሸጡትን፡የሚገዙትንም፡ያወጣ፡ዠመር፤
46፤ርሱም፦ቤቴ፡የጸሎት፡ቤት፡ይኾናል፡ተብሎ፡ተጽፏል፤እናንተ፡ግን፡የወንበዴዎች፡ዋሻ፡አደረጋችኹት፡አላቸ ው።
47፤ዕለት፡ዕለትም፡በመቅደስ፡ያስተምር፡ነበር፤ነገር፡ግን፥የካህናት፡አለቃዎችና፡ጻፊዎች፡የሕዝቡ፡ታላላቆ ችም፡ሊገድሉት፡ይፈልጉ፡ነበር፥
48፤የሚያደርጉበትንም፡ዐጡ፤ሕዝቡ፡ዅሉ፡ሲሰሙት፡ተንጠልጥለውበት፡ነበርና።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡20።______________
ምዕራፍ፡20፤
1፤አንድ፡ቀንም፡ሕዝቡን፡በመቅደስ፡ሲያስተምር፡ወንጌልንም፡ሲሰብክላቸው፥የካህናት፡አለቃዎችና፡ጻፊዎች፡ከ ሽማግሌዎች፡ጋራ፡ወደ፡ርሱ፡ቀረቡና፦
2፤እስኪ፡ንገረን፤እነዚህን፡በምን፡ሥልጣን፡ታደርጋለኽ፡ወይስ፡ይህን፡ሥልጣን፡የሰጠኽ፡ማን፡ነው፧ብለው፡ተ ናገሩት።
3፤መልሶም፦እኔ፡ደግሞ፡አንዲት፡ነገር፡እጠይቃችዃለኹ፥እናንተም፡ንገሩኝ፤
4፤የዮሐንስ፡ጥምቀት፡ከሰማይ፡ነበረችን፡ወይስ፡ከሰው፧አላቸው።
5፤ርስ፡በርሳቸውም፡ሲነጋገሩ፦ከሰማይ፡ብንል፦ስለ፡ምን፡አላመናችኹበትም፧ይለናል፤
6፤ከሰው፡ብንል፡ግን፡ሕዝቡ፡ዅሉ፡ይወግሩናል፤ዮሐንስ፡ነቢይ፡እንደ፡ነበረ፡ዅሉ፡ያምኑ፡ነበርና፥አሉ።
7፤መልሰውም፦ከወዴት፡እንደ፡ኾነ፡አናውቅም፡አሉት።
8፤ኢየሱስም፦እኔም፡በምን፡ሥልጣን፡እነዚህን፡እንዳደርግ፡አልነግራችኹም፡አላቸው።
9፤ይህንም፡ምሳሌ፡ለሕዝቡ፡ይላቸው፡ዠመር፦አንድ፡ሰው፡የወይን፡አትክልት፡ተከለ፡ለገበሬዎችም፡አከራይቶ፡ለ ብዙ፡ዘመን፡ወደ፡ሌላ፡አገር፡ኼደ።
10፤በጊዜውም፡ከወይኑ፡አትክልት፡ፍሬ፡እንዲሰጡት፡አንድ፡ባሪያ፡ወደ፡ገበሬዎች፡ላከ፤ገበሬዎቹ፡ግን፡ደበደ ቡት፡ባዶውንም፡ሰደዱት።
11፤ጨምሮም፡ሌላውን፡ባሪያ፡ላከ፤እነርሱም፡ያን፡ደግሞ፡ደበደቡት፡አዋርደውም፡ባዶውን፡ሰደዱት።
12፤ጨምሮም፡ሦስተኛውን፡ላከ፤እነርሱም፡ይህን፡ደግሞ፡አቍስለው፡አወጡት።
13፤የወይኑም፡አትክልት፡ጌታ፦ምን፡ላድርግ፧የምወደ፟ውን፡ልጄን፡እልካለኹ፤ምናልባት፡ርሱን፡አይተው፡ያፍሩ ታል፡አለ።
14፤ገበሬዎቹ፡ግን፡አይተውት፡ርስ፡በርሳቸው፡ሲነጋገሩ፦ወራሹ፡ይህ፡ነው፤ርስቱ፡ለእኛ፡እንዲኾን፡ኑ፡እንግ ደለው፡አሉ።
15፤ከወይኑም፡አትክልት፡ወደ፡ውጭ፡አውጥተው፡ገደሉት።እንግዲህ፡የወይኑ፡አትክልት፡ጌታ፡ምን፡ያደርጋቸዋል ፧
16፤ይመጣል፡እነዚህንም፡ገበሬዎች፡ያጠፋል፥የወይኑንም፡አትክልት፡ለሌላዎች፡ይሰጣል።ይህንም፡በሰሙ፡ጊዜ፦ ይህስ፡አይኹን፡አሉ።
17፤ርሱ፡ግን፡ወደ፡እነርሱ፡ተመልክቶ፦እንግዲህ፦ግንበኛዎች፡የናቁት፡ድንጋይ፡ርሱ፡የማእዘን፡ራስ፡ኾነ፡ተ ብሎ፡የተጻፈው፡ይህ፡ምንድር፡ነው፧
18፤በዚያም፡ድንጋይ፡ላይ፡የሚወድቅ፡ዅሉ፡ይቀጠቀጣል፤የሚወድቅበትን፡ዅሉ፡ግን፡ይፈጨዋል፡አለ።
19፤የካህናት፡አለቃዎችና፡ጻፊዎችም፡ይህን፡ምሳሌ፡በእነርሱ፡ላይ፡እንደ፡ተናገረ፡ዐውቀው፡በዚያች፡ሰዓት፡ እጃቸውን፡ሊጭኑበት፡ፈለጉ፥ነገር፡ግን፥ሕዝቡን፡ፈሩ።
20፤ሲጠባበቁም፡ወደገዢ፡ግዛትና፡ሥልጣን፡አሳልፈው፡እንዲሰጡት፡ጻድቃን፡መስለው፡በቃሉ፡የሚያጠምዱትን፡ሸ ማቂዎች፡ሰደዱበት።
21፤ጠይቀውም፦መምህር፡ሆይ፥እውነትን፡እንድትናገርና፡እንድታስተምር፡ለሰው፡ፊትም፡እንዳታደላ፡እናውቃለን ፥በእውነት፡የእግዚአብሔርን፡መንገድ፡ታስተምራለኽ፡እንጂ፤
22፤ለቄሳር፡ግብር፡ልንሰጥ፡ተፈቅዷልን፧ወይስ፡አልተፈቀደም፧አሉት።
23፤ርሱ፡ግን፡ተንኰላቸውንም፡ተመልክቶ፦ስለ፡ምን፡ትፈትኑኛላችኹ፧አንድ፡ዲናር፡አሳዩኝ፤
24፤መልኩ፡ጽሕፈቱስ፡የማን፡ነው፧አላቸው።መልሰውም፦የቄሳር፡ነው፡አሉት።
25፤ርሱም፦እንኪያስ፡የቄሳርን፡ለቄሳር፡የእግዚአብሔርንም፡ለእግዚአብሔር፡አስረክቡ፡አላቸው።
26፤በሕዝቡም፡ፊት፡በቃሉ፡ሊያጠምዱት፡አልቻሉም፡በመልሱም፡እየተደነቁ፡ዝም፡አሉ።
27፤ትንሣኤ፡ሙታንንም፡የሚክዱ፡ከሰዱቃውያን፡አንዳንዶቹ፡ቀርበው፡ጠየቁት፥
28፤እንዲህ፡ሲሉ፦መምህር፡ሆይ፥ሙሴ፦ሚስት፡ያለችው፡የአንድ፡ሰው፡ወንድም፡ልጅ፡ሳይወልድ፡ቢሞት፥ወንድሙ፡ ሚስቱን፡አግብቶ፡ለወንድሙ፡ዘር፡ይተካ፡ብሎ፡ጻፈልን።
29፤እንግዲያስ፡ሰባት፡ወንድማማች፡ነበሩ፤የፊተኛውም፡ሚስት፡አግብቶ፡ልጅ፡ሳይወልድ፡ሞተ፤
30-31፤ኹለተኛውም፡አገባት፥ሦስተኛውም፥እንዲሁም፡ሰባቱ፡ደግሞ፡ልጅ፡ሳይተዉ፡ሞቱ።
32፤ከዅሉም፡በዃላ፡ሴቲቱ፡ደግሞ፡ሞተች።
33፤እንግዲህ፡ሰባቱ፡አግብተዋታልና፥ሴቲቱ፡በትንሣኤ፡ከነርሱ፡ለማንኛቸው፡ሚስት፡ትኾናለች፧
34፤ኢየሱስም፡መልሶ፡እንዲህ፡አላቸው፦የዚህ፡ዓለም፡ልጆች፡ያገባሉ፡ይጋባሉም፥
35፤ያን፡ዓለምና፡ከሙታን፡ትንሣኤ፡ሊያገኙ፡የሚገ፟ባ፟ቸው፡እነዚያ፡ግን፡አያገቡም፡አይጋቡምም፥እንደ፡መላ እክት፡ናቸውና፥
36፤ሊሞቱም፡ወደ፡ፊት፡አይቻላቸውም፥የትንሣኤም፡ልጆች፡ስለ፡ኾኑ፡የእግዚአብሔር፡ልጆች፡ናቸው።
37፤ሙታን፡እንዲነሡ፡ግን፡ሙሴ፡ደግሞ፡በቍጥቋጦው፡ዘንድ፡ጌታን፡የአብርሃም፡አምላክ፡የይሥሐቅም፡አምላክ፡ የያዕቆብም፡አምላክ፡በማለቱ፡አስታወቀ፤
38፤ዅሉ፡ለርሱ፡ሕያዋን፡ስለ፡ኾኑ፥የሕያዋን፡አምላክ፡ነው፡እንጂ፡የሙታን፡አይደለም።
39፤ከጻፊዎችም፡አንዳንዶቹ፡መልሰው፦መምህር፡ሆይ፥መልካም፡ተናገርኽ፡አሉት።
40፤ወደ፡ፊትም፡አንድ፡ነገር፡ስንኳ፡ሊጠይቁት፡አልደፈሩም።
41፤እንዲህም፡አላቸው፦ክርስቶስ፡የዳዊት፡ልጅ፡ነው፡እንዴት፡ይላሉ፧
42-43፤ዳዊትም፡ራሱ፡በመዝሙራት፡መጽሐፍ፦ጌታ፡ጌታዬን፦ጠላቶችኽን፡ለእግርኽ፡መርገጫ፡እስካደርግልኽ፡ድረስ ፡በቀኜ፡ተቀመጥ፡አለው፡ይላል።
44፤እንግዲህ፡ዳዊት፦ጌታ፡ብሎ፡ይጠራዋል፥እንዴትስ፡ልጁ፡ይኾናል፧
45፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡ሲሰሙ፡ደቀ፡መዛሙርቱን፦
46፤ረዣዥም፡ልብስ፡ለብሰው፡መዞር፡ከሚፈልጉ፥በገበያም፡ሰላምታ፥በምኵራብም፡የከበሬታ፡ወንበር፥በምሳም፡የ ከበሬታ፡ስፍራ፡ከሚወዱ፡ከጻፊዎች፡ተጠበቁ፤
47፤የመበለቶችን፡ቤት፡የሚበሉ፡ጸሎታቸውንም፡በማስረዘም፡የሚያመካኙ፥እነዚህ፡የባሰ፡ፍርድ፡ይቀበላሉ፡አለ ።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡21።______________
ምዕራፍ፡21፤
1፤ዐይኑንም፡አንሥቶ፡መባቸውን፡በመዝገብ፡የሚጥሉ፡ባለጠጋዎችን፡አየ።
2፤አንዲትም፡ድኻ፡መበለት፡ኹለት፡ሳንቲም፡በዚያ፡ስትጥል፡አየና፦
3፤እውነት፡እላችዃለኹ፥ይህች፡ድኻ፡መበለት፡ከዅሉ፡ይልቅ፡አብልጣ፡ጣለች፤
4፤እነዚህ፡ዅሉ፡ከትርፋቸው፡ወደእግዚአብሔር፡መዝገብ፡ጥለዋልና፤ይህች፡ግን፡ከጕድለቷ፡የነበራትን፡ትዳሯን ፡ዅሉ፡ጣለች፡አለ።
5፤አንዳንዶቹም፡ስለ፡መቅደስ፡በመልካም፡ድንጋይና፡በተሰጠው፡ሽልማት፡እንዳጌጠ፡ሲነጋገሩ፦ይህማ፡የምታዩት ፡ዅሉ፥
6፤ድንጋይ፡በድንጋይ፡ላይ፡ሳይፈርስ፡በዚህ፡የማይቀርበት፡ዘመን፡ይመጣል፡አለ።
7፤እነርሱም፦መምህር፡ሆይ፥እንግዲህ፡ይህ፡መቼ፡ይኾናል፧ይህስ፡ይኾን፡ዘንድ፡እንዳለው፡ምልክቱ፡ምንድር፡ነ ው፧ብለው፡ጠየቁት።
8፤እንዲህም፡አለ፦እንዳትስቱ፡ተጠንቀቁ፤ብዙዎች፦እኔ፡ነኝ፥ዘመኑም፡ቀርቧል፡እያሉ፡በስሜ፡ይመጣሉና፤እነር ሱን፡ተከትላችኹ፡አትኺዱ።
9፤ጦርንና፡ሁከትንም፡በሰማችኹ፡ጊዜ፡አትደንግጡ፤ይህ፡አስቀድሞ፡ይኾን፡ዘንድ፡ግድ፡ነውና፥ነገር፡ግን፥መጨ ረሻው፡ወዲያው፡አይኾንም።
10፤በዚያን፡ጊዜ፡እንዲህ፡አላቸው፦ሕዝብ፡በሕዝብ፡ላይ፥መንግሥትም፡በመንግሥት፡ላይ፡ይነሣል፤
11፤ታላቅም፡የምድር፡መናወጥና፡በልዩ፡ልዩ፡ስፍራ፡ቸነፈር፡ራብም፡ይኾናል፤የሚያስፈራም፡ነገር፡ከሰማይም፡ ታላቅ፡ምልክት፡ይኾናል።
12፤ከዚህም፡ዅሉ፡በፊት፡እጃቸውን፡በላያችኹ፡ይጭናሉ፡ያሳድዷችኹማል፤ስለ፡ስሜም፡ወደ፡ምኵራብና፡ወደ፡ወህ ኒ፡አሳልፈው፡ይሰጧችዃል፥ወደ፡ነገሥታትና፡ወደ፡ገዢዎችም፡ይወስዷችዃል፤
13፤ይህም፡ለምስክርነት፡ይኾንላችዃል።
14፤ሰለዚህ፡እንዴት፡እንድትመልሱ፡አስቀድማችኹ፡እንዳታስቡ፡በልባችኹ፡አኑሩት፤
15፤ወደረኛዎቻችኹ፡ዅሉ፡ሊቃወሙና፡ሊከራከሩ፡የማይችሉትን፡አፍና፡ጥበብ፡እሰጣችዃለኹና።
16፤ወላጆችም፡ስንኳ፡ወንድሞችም፡ዘመዶችም፡ወዳጆችም፡አሳልፈው፡ይሰጧችዃል፥ከእናንተም፡አንዳንዱን፡ይገድ ላሉ፤
17፤በዅሉም፡ስለ፡ስሜ፡የተጠላችኹ፡ትኾናላችኹ።
18፤ከራሳችኹም፡አንዲት፡ጠጕር፡ስንኳ፡አትጠፋም፤
19፤በመታገሣችኹም፡ነፍሳችኹን፡ታገኛላችኹ።
20፤ኢየሩሳሌም፡ግን፡በጭፍራ፡ተከባ፡ስታዩ፡በዚያን፡ጊዜ፡ጥፋቷ፡እንደ፡ቀረበ፡ዕወቁ።
21፤የዚያን፡ጊዜ፡በይሁዳ፡ያሉ፡ወደ፡ተራራዎች፡ይሽሹ፥በመካከሏም፡ያሉ፡ከርሷ፡ፈቀቅ፡ይበሉ፥በገጠር፡ያሉም ፡ወደ፡ርሷ፡አይግቡ፤
22፤የተጻፈው፡ዅሉ፡እንዲፈጸም፡ይህ፡የበቀል፡ጊዜ፡ነውና።
23፤በዚያን፡ወራት፡ለእርጕዞችና፡ለሚያጠቡ፡ወዮላቸው፤ታላቅ፡ችግር፡በምድር፡ላይ፥በዚህም፡ሕዝብ፡ላይ፡ቍጣ ፡ይኾናልና፤
24፤በሰይፍ፡ስለትም፡ይወድቃሉ፤ወደ፡አሕዛብ፡ዅሉም፡ይማረካሉ፤የአሕዛብም፡ዘመን፡እስኪፈጸም፡ድረስ፡ኢየሩ ሳሌም፡በአሕዛብ፡የተረገጠች፡ትኾናለች።
25፤በፀሓይና፡በጨረቃም፡በከዋክብትም፡ምልክት፡ይኾናል፤በምድር፡ላይም፡አሕዛብ፡ከባሕሩና፡ከሞገዱም፡ድምፅ ፡የተነሣ፡እያመነቱ፡ይጨነቃሉ፤
26፤ሰዎችም፡ከፍርሀትና፡በዓለም፡የሚመጣበትን፡ከመጠበቅ፡የተነሣ፡ይደክማሉ፤የሰማያት፡ኀይላት፡ይናወጣሉና ።
27፤በዚያን፡ጊዜም፡የሰው፡ልጅ፡በኀይልና፡በብዙ፡ክብር፡በደመና፡ሲመጣ፡ያዩታል።
28፤ይህም፡ሊኾን፡ሲዠምር፡ቤዛችኹ፡ቀርቧልና፥አሻቅባችኹ፡ራሳችኹን፡አንሡ።
29፤ምሳሌንም፡ነገራቸው፡እንዲህ፡ሲል፦በለስንና፡ዛፎችን፡ዅሉ፡እዩ፤
30፤ሲያቈጠቍጡ፡ተመልክታችኹ፡በጋ፡አኹን፡እንደ፡ቀረበ፡ራሳችኹ፡ታውቃላችኹ።
31፤እንዲሁ፡ደግሞ፡እናንተ፡ይህ፡ዅሉ፡መኾኑን፡ስታዩ፡የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡እንደ፡ቀረበች፡ዕወቁ።
32፤እውነት፡እላችዃለኹ፥ይህ፡ዅሉ፡እስኪኾን፡ድረስ፡ይህ፡ትውልድ፡አያልፍም።
33፤ሰማይና፡ምድር፡ያልፋሉ፡ቃሌ፡ግን፡አያልፍም።
34፤ነገር፡ግን፥ልባችኹ፡በመጠጥ፡ብዛትና፡በስካር፡ስለ፡ትዳርም፡በማሰብ፡እንዳይከብድ፥ያ፡ቀንም፡በድንገት ፡እንዳይመጣባችኹ፡ለራሳችኹ፡ተጠንቀቁ፤
35፤በምድር፡ዅሉ፡ላይ፡በሚቀመጡ፡ዅሉ፡እንደ፡ወጥመድ፡ይደርስባቸዋልና።
36፤እንግዲህ፡ሊመጣ፡ካለው፡ከዚህ፡ዅሉ፡ለማምለጥ፥በሰው፡ልጅም፡ፊት፡ለመቆም፡እንድትችሉ፡ስትጸልዩ፡ዅል፡ ጊዜ፡ትጉ።
37፤ዕለት፡ዕለትም፡በመቅደስ፡ያስተምር፡ነበር፥ሌሊት፡ግን፡ደብረ፡ዘይት፡ወደምትባል፡ተራራ፡ወጥቶ፡ያድር፡ ነበር።
38፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡ይሰሙት፡ዘንድ፡ማልደው፡በመቅደስ፡ወደ፡ርሱ፡ይመጡ፡ነበር።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡22።______________
ምዕራፍ፡22፤
1፤ፋሲካም፡የሚባለው፡የቂጣ፡በዓል፡ቀረበ።
2፤የካህናት፡አለቃዎችና፡ጻፊዎችም፡እንዴት፡እንዲያጠፉት፡ይፈልጉ፡ነበር፤ሕዝቡን፡ይፈሩ፡ነበርና።
3፤ሰይጣንም፡ከዐሥራ፡ኹለቱ፡ቍጥር፡አንዱ፡በነበረው፡የአስቆሮቱ፡በሚባለው፡በይሁዳ፡ገባ፤
4፤ኼዶም፡እንዴት፡አሳልፎ፡እንዲሰጣቸው፡ከካህናት፡አለቃዎችና፡ከመቅደስ፡አዛዦች፡ጋራ፡ተነጋገረ።
5፤እነርሱም፡ደስ፡አላቸው፥ገንዘብም፡ሊሰጡት፡ተዋዋሉ።
6፤ዕሺም፡አለ፥ሕዝብም፡በሌለበት፡አሳልፎ፡እንዲሰጣቸው፡ምቹ፡ጊዜ፡ይፈልግ፡ነበር።
7፤ፋሲካንም፡ሊያርዱበት፡የሚገ፟ባ፟ው፡የቂጣ፡በዓል፡ደረሰ፤
8፤ጴጥሮስንና፡ዮሐንስንም፦ፋሲካን፡እንድንበላ፡ኼዳችኹ፡አዘጋጁልን፡ብሎ፡ላካቸው።
9፤እነርሱም፦ወዴት፡እናዘጋጅ፡ዘንድ፡ትወዳለኽ፧አሉት።
10፤ርሱም፡አላቸው፦እንሆ፥ወደ፡ከተማ፡ስትገቡ፡ማድጋ፡ውሃ፡የተሸከመ፡ሰው፡ይገናኛችዃል፤ወደሚገባበት፡ቤት ፡ተከተሉት፤
11፤ለባለቤቱም፦መምህሩ፦ከደቀ፡መዛሙርቴ፡ጋራ፡ፋሲካን፡የምበላበት፡የእንግዳ፡ቤት፡ክፍል፡ወዴት፡ነው፧ይል ኻል፡በሉት፤
12፤ያም፡በደርብ፡ላይ፡ያለውን፡የተነጠፈ፡ታላቅ፡አዳራሽ፡ያሳያችዃል፤በዚያም፡አሰናዱልን።
13፤ኼደውም፡እንዳላቸው፡አገኙና፡ፋሲካን፡አሰናዱ።
14፤ሰዓቱም፡በደረሰ፡ጊዜ፡ከዐሥራ፡ኹለቱ፡ሐዋርያት፡ጋራ፡በማእዱ፡ተቀመጠ።
15፤ርሱም፦ከመከራዬ፡በፊት፡ከእናንተ፡ጋራ፡ይህን፡ፋሲካ፡ልበላ፡እጅግ፡እመኝ፡ነበር፤
16፤እላችዃለኹና፥በእግዚአብሔር፡መንግሥት፡እስኪፈጸም፡ድረስ፥ወደ፡ፊት፡ከዚህ፡አልበላም፡አላቸው።
17፤ጽዋንም፡ተቀበለ፡አመስግኖም፦ይህን፡እንካችኹ፥በመካከላችኹም፡ተካፈሉት፤
18፤እላችዃለኹና፥የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡እስክትመጣ፡ድረስ፡ካኹን፡ዠምሮ፡ከወይኑ፡ፍሬ፡አልጠጣም፡አለ።
19፤እንጀራንም፡አንሥቶ፡አመሰገነ፡ቈርሶም፡ሰጣቸውና፦ስለ፡እናንተ፡የሚሰጠው፡ሥጋዬ፡ይህ፡ነው፤ይህን፡ለመ ታሰቢያዬ፡አድርጉት፡አለ።
20፤እንዲሁም፡ከእራት፡በዃላ፡ጽዋውን፡አንሥቶ፡እንዲህ፡አለ፦ይህ፡ጽዋ፡ስለ፡እናንተ፡በሚፈሰው፡በደሜ፡የሚ ኾን፡ዐዲስ፡ኪዳን፡ነው።
21፤ነገር፡ግን፥አሳልፎ፡የሚሰጠኝ፡እጅ፥እንሆ፥በማእዱ፡ከእኔ፡ጋራ፡ናት።
22፤የሰው፡ልጅስ፡እንደተወሰነው፡ይኼዳል፥ነገር፡ግን፥ዐልፎ፡ለሚሰጥበት፡ለዚያ፡ሰው፡ወዮለት።
23፤ከነርሱም፡ይህን፡ሊያደርግ፡ያለው፡ማን፡እንደ፡ኾነ፡ርስ፡በርሳቸው፡ይጠያየቁ፡ዠመር።
24፤ደግሞም፡ማናቸውም፡ታላቅ፡ኾኖ፡እንዲቈጠር፡በመካከላቸው፡ክርክር፡ኾነ።
25፤እንዲህም፡አላቸው፦የአሕዛብ፡ነገሥታት፡ይገዟቸዋል፥በላያቸውም፡የሚሠለጥኑት፡ቸርነት፡አድራጊዎች፡ይባ ላሉ።
26፤እናንተ፡ግን፡እንዲህ፡አትኹኑ፤ነገር፡ግን፥ከእናንተ፡ታላቅ፡የኾነ፡በመካከላችኹ፡እንደ፡ታናሽ፥የሚገዛ ም፡እንደሚያገለግል፡ይኹን።
27፤በማእዱ፡የተቀመጠ፡ወይስ፡የሚያገለግል፡ማናቸው፡ታላቅ፡ነው፧የተቀመጠው፡አይደለምን፧እኔ፡ግን፡በመካከ ላችኹ፡እንደሚያገለግል፡ነኝ።
28፤ነገር፡ግን፥እናንተ፡በፈተናዎቼ፡ከእኔ፡ጋራ፡ጸንታችኹ፡የኖራችኹ፡ናችኹ፤
29-30፤አባቴ፡እኔን፡እንደ፡ሾመኝ፡እኔ፡ደግሞ፡በመንግሥቴ፡ከማእዴ፡ትበሉና፡ትጠጡ፡ዘንድ፥በዐሥራ፡ኹለቱ፡በ እስራኤል፡ነገድ፡ስትፈርዱ፡በዙፋኖች፡ትቀመጡ፡ዘንድ፡ለመንግሥት፡እሾማችዃለኹ።
31፤ጌታም፦ስምዖን፡ስምዖን፡ሆይ፥እንሆ፥ሰይጣን፡እንደ፡ስንዴ፡ሊያበጥራችኹ፡ለመነ፤
32፤እኔ፡ግን፡እምነትኽ፡እንዳይጠፋ፡ስለ፡አንተ፡አማለድኹ፤አንተም፡በተመለስኽ፡ጊዜ፡ወንድሞችኽን፡አጽና፡ አለ።
33፤ርሱም፦ጌታ፡ሆይ፥ወደ፡ወህኒም፡ወደ፡ሞትም፡ከአንተ፡ጋራ፡ለመኼድ፡የተዘጋጀኹ፡ነኝ፡አለው።
34፤ርሱ፡ግን፦ጴጥሮስ፡ሆይ፥እልኻለኹ፥እንዳታውቀኝ፡ሦስት፡ጊዜ፡እስክትክደኝ፡ድረስ፡ዛሬ፡ዶሮ፡አይጮኽም፡ አለው።
35፤ደግሞም፦ያለኰረጆና፡ያለከረጢት፡ያለጫማም፡በላክዃችኹ፡ጊዜ፥አንዳች፡ጐደለባችኹን፧አላቸው።እነርሱም፦ አንዳች፡እንኳ፡አሉ።
36፤ርሱም፦አኹን፡ግን፡ኰረጆ፡ያለው፡ከርሱ፡ጋራ፡ይውሰድ፥ከረጢትም፡ያለው፡እንዲሁ፤የሌለውም፡ልብሱን፡ሽጦ ፡ሰይፍ፡ይግዛ።
37፤እላችዃለኹና፥ይህ፦ከዐመፀኛዎች፡ጋራ፡ተቈጠረ፡ተብሎ፡የተጻፈው፡በእኔ፡ሊፈጸም፡ግድ፡ነው፤አዎን፥ስለ፡ እኔ፡የሚኾነው፡አኹን፡ይፈጸማልና፥አላቸው።
38፤እነርሱም፦ጌታ፡ሆይ፥እንሆ፥በዚህ፡ኹለት፡ሰይፎች፡አሉ፡አሉት።ርሱም፦ይበቃል፡አላቸው።
39፤ወጥቶም፡እንደ፡ልማዱ፡ወደ፡ደብረ፡ዘይት፡ኼደ፤ደቀ፡መዛሙርቱም፡ደግሞ፡ተከተሉት።
40፤ወደ፡ስፍራውም፡ደርሶ፦ወደ፡ፈተና፡እንዳትገቡ፡ጸልዩ፡አላቸው።
41፤ከነርሱም፡የድንጋይ፡ውርወራ፡የሚያኽል፡ራቀ፥ተንበርክኮም፦አባት፡ሆይ፥
42፤ብትፈቅድ፡ይህችን፡ጽዋ፡ከእኔ፡ውሰድ፤ነገር፡ግን፥የእኔ፡ፈቃድ፡አይኹን፡የአንተ፡እንጂ፡እያለ፡ይጸልይ ፡ነበር።
43፤ከሰማይም፡መጥቶ፡የሚያበረታ፡መልአክ፡ታየው።
44፤በፍርሀትም፡ሲጣጣር፡አጽንቶ፡ይጸልይ፡ነበር፤ወዙም፡በምድር፡ላይ፡እንደሚወርድ፡እንደ፡ደም፡ነጠብጣብ፡ ነበረ።
45፤ከጸሎትም፡ተነሥቶ፡ወደ፡ደቀ፡መዛሙርቱ፡መጣና፡ከሐዘን፡የተነሣ፡ተኝተው፡ሲያገኛቸው።
46፤ስለ፡ምን፡ትተኛላችኹ፧ወደ፡ፈተና፡እንዳትገቡ፡ተነሥታችኹ፡ጸልዩ፡አላቸው።
47፤ገናም፡ሲናገር፥እንሆ፥ሰዎች፡መጡ፤ከዐሥራ፡ኹለቱ፡አንዱም፡ይሁዳ፡የሚባለው፡ይቀድማቸው፡ነበር፥ሊስመው ም፡ወደ፡ኢየሱስ፡ቀረበ።
48፤ኢየሱስ፡ግን፦ይሁዳ፡ሆይ፥በመሳም፡የሰውን፡ልጅ፡አሳልፈኽ፡ትሰጣለኽን፧አለው።
49፤በዙሪያውም፡የነበሩት፡የሚኾነውን፡ባዩ፡ጊዜ፦ጌታ፡ሆይ፥በሰይፍ፡እንምታቸውን፧አሉት።
50፤ከነርሱም፡አንዱ፡የሊቀ፡ካህናቱን፡ባሪያ፡መቶ፟፡ቀኝ፡ዦሮውን፡ቈረጠው።
51፤ኢየሱስ፡ግን፡መልሶ፦ይህንስ፡ፍቀዱ፡አለ፤ዦሮውንም፡ዳሶ፟፡ፈወሰው።
52፤ኢየሱስም፡ወደ፡ርሱ፡ለመጡበት፡ለካህናት፡አለቃዎችና፡ለመቅደስ፡አዛዦች፡ለሽማግሌዎችም፦ወንበዴን፡እን ደምትይዙ፡ሰይፍና፡ጐመድ፡ይዛችኹ፡ወጣችኹን፧
53፤በመቅደስ፡ዕለት፡ዕለት፡ከእናንተ፡ጋራ፡ስኾን፡እጆቻችኹን፡አልዘረጋችኹብኝም፤ይህ፡ግን፡ጊዜያችኹና፡የ ጨለማው፡ሥልጣን፡ነው፡አላቸው።
54፤ይዘውም፡ወሰዱት፡ወደሊቀ፡ካህናት፡ቤትም፡አገቡት፤ጴጥሮስም፡ርቆ፡ይከተለው፡ነበር።
55፤በግቢ፡መካከልም፡እሳት፡አንድደው፡በአንድነት፡ተቀምጠው፡ሳሉ፡ጴጥሮስ፡በመካከላቸው፡ተቀመጠ።
56፤በብርሃኑም፡በኩል፡ተቀምጦ፡ሳለ፡አንዲት፡ገረድ፡አየችውና፡ትኵር፡ብላ፦ይህ፡ደግሞ፡ከርሱ፡ጋራ፡ነበረ፡ አለች።
57፤ርሱ፡ግን፦አንቺ፡ሴት፥አላውቀውም፡ብሎ፡ካደ።
58፤ከጥቂት፡ጊዜም፡በዃላ፡ሌላው፡አይቶት፦አንተ፡ደግሞ፡ከነርሱ፡ወገን፡ነኽ፡አለው።ጴጥሮስ፡ግን፦አንተ፡ሰ ው፥እኔ፡አይደለኹም፡አለ።
59፤አንድ፡ሰዓትም፡የሚያኽል፡ቈይቶ፡ሌላው፡አስረግጦ፦ርሱ፡የገሊላ፡ሰው፡ነውና፥በእውነት፡ይህ፡ደግሞ፡ከር ሱ፡ጋራ፡ነበረ፡አለ።
60፤ጴጥሮስ፡ግን፦አንተ፡ሰው፥የምትለውን፡አላውቅም፡አለ።ያን፡ጊዜም፡ገና፡ሲናገር፡ዶሮ፡ጮኸ።
61፤ጌታም፡ዘወር፡ብሎ፡ጴጥሮስን፡ተመለከተው፤ጴጥሮስም፦ዛሬ፡ዶሮ፡ሳይጮኽ፡ሦስት፡ጊዜ፡ትክደኛለኽ፡እንዳለ ው፡የጌታ፡ቃል፡ትዝ፡አለው።
62፤ጴጥሮስም፡ወደ፡ውጭ፡ወጥቶ፡ምርር፡ብሎ፡አለቀሰ።
63፤ኢየሱስንም፡የያዙት፡ሰዎች፡ይዘብቱበትና፡ይደበድቡት፡ነበር፤
64፤ሸፍነውም፡ፊቱን፡ይመቱት፡ነበርና፦በጥፊ፡የመታኽ፡ማን፡ነው፧ትንቢት፡ተናገር፡እያሉ፡ይጠይቁት፡ነበር።
65፤ሌላም፡ብዙ፡ነገር፡እየተሳደቡ፡በርሱ፡ላይ፡ይናገሩ፡ነበር።
66፤በነጋም፡ጊዜ፡የሕዝቡ፡ሽማግሌዎችና፡የካህናት፡አለቃዎች፡ጻፊዎችም፡ተሰብስበው፡ወደሸንጓቸው፡ወሰዱትና ፡
67፤ክርስቶስ፡አንተ፡ነኽን፧ንገረን፡አሉት።ርሱ፡ግን፡እንዲህ፡አላቸው፦ብነግራችኹ፡አታምኑም፤
68፤ብጠይቅም፡አትመልሱልኝም፡አትፈቱኝምም።
69፤ነገር፡ግን፥ካኹን፡ዠምሮ፡የሰው፡ልጅ፡በእግዚአብሔር፡ኀይል፡ቀኝ፡ይቀመጣል።
70፤ዅላቸውም፦እንግዲያስ፡አንተ፡የእግዚአብሔር፡ልጅ፡ነኽን፧አሉት።ርሱም፦እኔ፡እንደ፡ኾንኹ፡እናንተ፡ትላ ላችኹ፡አላቸው።
71፤እነርሱም፦ራሳችን፡ከአፉ፡ሰምተናልና፥ከእንግዲህ፡ወዲህ፡ምን፡ምስክር፡ያስፈልገናል፧አሉ።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡23።______________
ምዕራፍ፡23፤
1፤ዅሉም፡በሞላው፡ተነሥተው፡ወደ፡ጲላጦስ፡ወሰዱትና፦
2፤ይህ፡ሕዝባችንን፡ሲያጣምም፡ለቄሳርም፡ግብር፡እንዳይሰጥ፡ሲከለክል፡ደግሞም፦እኔ፡ክርስቶስ፡ንጉሥ፡ነኝ፡ ሲል፡አገኘነው፡ብለው፡ይከሱት፡ዠመር።
3፤ጲላጦስም፦አንተ፡የአይሁድ፡ንጉሥ፡ነኽን፧ብሎ፡ጠየቀው።ርሱም፡መልሶ፦አንተ፡አልኽ፡አለው።
4፤ጲላጦስም፡ለካህናት፡አለቃዎችና፡ለሕዝቡ፦በዚህ፡ሰው፡አንድ፡በደል፡ስንኳ፡አላገኘኹበትም፡አለ።
5፤እነርሱ፡ግን፡አጽንተው፦ከገሊላ፡ዠምሮ፡እስከዚህ፡ድረስ፡በይሁዳ፡ዅሉ፡እያስተማረ፡ሕዝቡን፡ያውካል፡አሉ ።
6፤ጲላጦስ፡ግን፦ገሊላ፡ሲሉ፡በሰማ፡ጊዜ፦የገሊላ፡ሰው፡ነውን፧ብሎ፡ጠየቀ፤
7፤ከሄሮድስም፡ግዛት፡እንደ፡ኾነ፡ባወቀ፡ጊዜ፡ወደ፡ሄሮድስ፡ሰደደው፤ርሱ፡ደግሞ፡በዚያ፡ጊዜ፡በኢየሩሳሌም፡ ነበረና።
8፤ሄሮድስም፡ኢየሱስን፡ባየው፡ጊዜ፡እጅግ፡ደስ፡አለው፤ስለ፡ርሱ፡ስለ፡ሰማ፡ከብዙ፡ጊዜ፡ዠምሮ፡ሊያየው፡ይመ ኝ፡ነበርና፥ምልክትም፡ሲያደርግ፡ሊያይ፡ተስፋ፡ያደርግ፡ነበር።
9፤በብዙ፡ቃልም፡ጠየቀው፤ርሱ፡ግን፡አንድ፡ስንኳ፡አልመለሰለትም።
10፤የካህናት፡አለቃዎችና፡ጻፊዎችም፡አጽንተው፡ሲከሱት፡ቆመው፡ነበር።
11፤ሄሮድስም፡ከሰራዊቱ፡ጋራ፡ናቀው፡ዘበተበትም፥የጌጥ፡ልብስም፡አልብሶ፡ወደ፡ጲላጦስ፡መልሶ፡ሰደደው።
12፤ሄሮድስና፡ጲላጦስም፡በዚያን፡ቀን፡ርስ፡በርሳቸው፡ወዳጆች፡ኾኑ፥ቀድሞ፡በመካከላቸው፡ጥል፡ነበረና።
13፤ጲላጦስም፥የካህናትን፡አለቃዎችና፡መኳንንትን፡ሕዝቡንም፡በአንድነት፡ጠርቶ፡እንዲህ፡አላቸው።
14፤ሕዝቡን፡ያጣምማል፡ብላችኹ፡ይህን፡ሰው፡ወደ፡እኔ፡አመጣችኹት፤እንሆም፥በፊታችኹ፡መርምሬ፡ከምትከሱበት ፡ነገር፡አንድ፡በደል፡ስንኳ፡በዚህ፡ሰው፡አላገኘኹበትም።
15፤ሄሮድስም፡ደግሞ፡ምንም፡አላገኘም፤ወደ፡እኛ፡መልሶታልና፤እንሆም፥ለሞት፡የሚያደርሰው፡ምንም፡አላደረገ ም፤
16-17፤እንግዲያስ፡ቀጥቼ፡እፈታዋለኹ።በበዓሉ፡አንድ፡ይፈታላቸው፡ዘንድ፡ግድ፡ነበረና።
18፤ዅላቸውም፡በአንድነት፦ይህን፡አስወግድ፥በርባንንም፡ፍታልን፡እያሉ፡ጮኹ፤
19፤ርሱም፡ሁከትን፡በከተማ፡አንሥቶ፡ሰውን፡ስለ፡ገደለ፡በወህኒ፡ታስሮ፡ነበር።
20፤ጲላጦስም፡ኢየሱስን፡ሊፈታ፡ወዶ፟፡ዳግመኛ፡ተናገራቸው፤
21፤ነገር፡ግን፥እነርሱ፦ስቀለው፡ስቀለው፡እያሉ፡ይጮኹ፡ነበር።
22፤ሦስተኛም፦ምን፡ነው፧ያደረገውስ፡ክፋት፡ምንድር፡ነው፧ለሞት፡የሚያደርሰው፡በደል፡አላገኘኹበትም፤ስለዚ ህ፥ቀጥቼ፡እፈታዋለኹ፡አላቸው።
23፤እነርሱ፡ግን፡እንዲሰቀል፡በታላቅ፡ድምፅ፡አጽንተው፡ለመኑት።የእነርሱ፡ጩኸትና፡የካህናት፡አለቃዎችም፡ ቃል፡በረታ።
24፤ጲላጦስም፡ልመናቸው፡እንዲኾንላቸው፡ፈረደበት።
25፤ያንን፡የለመኑትንም፥ስለ፡ሁከት፡ሰውንም፡ስለ፡መግደል፡በወህኒ፡ታስሮ፡የነበረውን፡አስፈታላቸው፥ኢየሱ ስን፡ግን፡ለፈቃዳቸው፡አሳልፎ፡ሰጠው።
26፤በወሰዱትም፡ጊዜ፡ስምዖን፡የተባለ፡የቀሬናን፡ሰው፡ከገጠር፡ሲመጣ፡ይዘው፡ከኢየሱስ፡በዃላ፡መስቀሉን፡እ ንዲሸከም፡ጫኑበት።
27፤ዋይ፡ዋይ፡ከሚሉና፡ሙሾ፡ከሚያወጡ፡ሴቶችና፡ከሕዝቡ፡እጅግ፡ብዙዎች፡ተከተሉት።
28-29፤ኢየሱስ፡ግን፡ወደ፡እነርሱ፡ዘወር፡ብሎ፡እንዲህ፡አለ፦እናንተ፡የኢየሩሳሌም፡ልጆች፥ለኔስ፡አታልቅሱል ኝ፤ዳሩ፡ግን፦መካኖችና፡ያልወለዱ፡ማሕፀኖች፡ያላጠቡ፡ጡቶችም፡ብፁዓን፡ናቸው፡የሚሉበት፡ጊዜ፥እንሆ፥ይመጣ ልና፥ለራሳችኹና፡ለልጆቻችኹ፡አልቅሱ።
30፤በዚያን፡ጊዜ፡ተራራዎችን፦በላያችን፡ውደቁ፥ኰረብታዎችንም፦ሰውሩን፡ይሉ፡ዘንድ፡ይዠምራሉ፤
31፤በርጥብ፡ዕንጨት፡እንዲህ፡የሚያደርጉ፡ከኾኑ፥በደረቀውስ፡እንዴት፡ይኾን፧
32፤ሌላዎችንም፡ኹለት፡ክፉ፡አድራጊዎች፡ደግሞ፡ከርሱ፡ጋራ፡ይገድሉ፡ዘንድ፡ወሰዱ።
33፤ቀራንዮም፡ወደሚባል፡ስፍራ፡በደረሱ፡ጊዜ፥በዚያ፡ርሱን፡ክፉ፡አድራጊዎቹንም፡አንዱን፡በቀኝ፡ኹለተኛውን ም፡በግራ፡ሰቀሉ።
34፤ኢየሱስም፦አባት፡ሆይ፥የሚያደርጉትን፡አያውቁምና፡ይቅር፡በላቸው፡አለ።ልብሱንም፡ተካፍለው፡ዕጣ፡ተጣጣ ሉበት።
35፤ሕዝቡም፡ቆመው፡ይመለከቱ፡ነበር።መኳንንቱም፡ደግሞ፦ሌላዎችን፡አዳነ፤ርሱ፡በእግዚአብሔር፡የተመረጠው፡ ክርስቶስ፡ከኾነ፥ራሱን፡ያድን፡እያሉ፡ያፌዙበት፡ነበር።
36፤ጭፍራዎችም፡ደግሞ፡ወደ፡ርሱ፡ቀርበው፡ሖምጣጤም፡አምጥተው፦
37፤አንተስ፡የአይሁድ፡ንጉሥ፡ከኾንኽ፥ራስኽን፡አድን፡እያሉ፡ይዘብቱበት፡ነበር፦
38፤ይህ፡የአይሁድ፡ንጉሥ፡ነው፡ተብሎ፡በግሪክና፡በሮማይስጥ፡በዕብራይስጥም፡ፊደል፡የተጻፈ፡ጽሕፈት፡ደግሞ ፡በርሱ፡ላይ፡ነበረ።
39፤ከተሰቀሉት፡ከክፉ፡አድራጊዎቹም፡አንዱ፦አንተስ፡ክርስቶስ፡አይደለኽምን፧ራስኽንም፡እኛንም፡አድን፡ብሎ ፡ሰደበው።
40፤ኹለተኛው፡ግን፡መልሶ፦አንተ፡እንደዚህ፡ባለ፡ፍርድ፡ሳለኽ፡እግዚአብሔርን፡ከቶ፡አትፈራውምን፧
41፤ስላደረግነውም፡የሚገ፟ባ፟ንን፡እንቀበላለንና፡በእኛስ፡እውነተኛ፡ፍርድ፡ነው፤ይህ፡ግን፡ምንም፡ክፋት፡ አላደረገም፡ብሎ፡ገሠጸው።
42፤ኢየሱስንም፦ጌታ፡ሆይ፥በመንግሥትኽ፡በመጣኽ፡ጊዜ፡ዐስበኝ፡አለው።
43፤ኢየሱስም፦እውነት፡እልኻለኹ፥ዛሬ፡ከእኔ፡ጋራ፡በገነት፡ትኾናለኽ፡አለው።
44፤ስድስት፡ሰዓትም፡ያኽል፡ነበረ፥ጨለማም፡እስከ፡ዘጠኝ፡ሰዓት፡በምድር፡ዅሉ፡ላይ፡ኾነ፥ፀሓይም፡ጨለመ፥
45፤የቤተ፡መቅደስም፡መጋረጃ፡ከመካከሉ፡ተቀደደ።
46፤ኢየሱስም፡በታላቅ፡ድምፅ፡ጮኾ፦አባት፡ሆይ፥ነፍሴን፡በእጅኽ፡ዐደራ፡እሰጣለኹ፡አለ።ይህንም፡ብሎ፡ነፍሱ ን፡ሰጠ።
47፤የመቶ፡አለቃውም፡የኾነውን፡ነገር፡ባየ፡ጊዜ፦ይህ፡ሰው፡በእውነት፡ጻድቅ፡ነበረ፡ብሎ፡እግዚአብሔርን፡አ ከበረ።
48፤ይህንም፡ለማየት፡ተከማችተው፡የነበሩ፡ሕዝብ፡ዅሉ፥የኾነውን፡ባዩ፡ጊዜ፥ደረታቸውን፡እየደቁ፡ተመለሱ።
49፤የሚያውቁቱ፡ግን፡ዅሉ፡ከገሊላ፡የተከተሉት፡ሴቶችም፡ይህን፡እያዩ፡በሩቅ፡ቆመው፡ነበር።
50፤እንሆም፥በጎና፡ጻድቅ፡ሰው፡የሸንጎ፡አማካሪም፡የኾነ፡ዮሴፍ፡የሚባል፡ሰው፡ነበረ፤
51፤ይህም፡በምክራቸውና፡በሥራቸው፡አልተባበረም፡ነበር፤አርማትያስም፡ከምትባል፡ከአይሁድ፡ከተማ፡ኾኖ፡ርሱ ፡ደግሞ፡የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡ይጠባበቅ፡ነበር።
52፤ይኸውም፡ወደ፡ጲላጦስ፡ቀርቦ፡የኢየሱስን፡ሥጋ፡ለመነው፤
53፤አውርዶም፡በተልባ፡እግር፡ልብስ፡ከፈነው፥ማንም፡ገና፡ባልተቀበረበት፡ከአለትም፡በተወቀረ፡መቃብር፡አኖ ረው።
54፤የመዘጋጀት፡ቀንም፡ነበረ፤ሰንበትም፡ሊዠምር፡ነበረ።
55፤ከገሊላም፡ከርሱ፡ጋራ፡የመጡት፡ሴቶች፡ተከትለው፡መቃብሩን፡ሥጋውንም፡እንዴት፡እንዳኖሩት፡አዩ።
56፤ተመልሰውም፡ሽቱና፡ቅባት፡አዘጋጁ።በሰንበትም፡እንደ፡ትእዛዙ፡ዐረፉ።
_______________የሉቃስ፡ወንጌል፥ምዕራፍ፡24።______________
ምዕራፍ፡24፤
1፤ነገር፡ግን፥ከሳምንቱ፡በመዠመሪያው፡ቀን፡ያዘጋጁትን፡ሽቱ፡ይዘው፡ከነርሱም፡ጋራ፡አንዳንዶቹ፡ወደ፡መቃብ ሩ፡እጅግ፡ማልደው፡መጡ።
2፤ድንጋዩንም፡ከመቃብሩ፡ተንከባሎ፡አገኙት፥
3፤ገብተውም፡የጌታን፡የኢየሱስን፡ሥጋ፡አላገኙም።
4፤እነርሱም፡በዚህ፡ሲያመነቱ፥እንሆ፥ኹለት፡ሰዎች፡የሚያንጸባርቅ፡ልብስ፡ለብሰው፡ወደ፡እነርሱ፡ቀረቡ፤
5፤ፈርተውም፡ፊታቸውን፡ወደ፡ምድር፡አቀርቅረው፡ሳሉ፥እንዲህ፡አሏቸው፦ሕያውን፡ከሙታን፡መካከል፡ስለ፡ምን፡ ትፈልጋላችኹ፧ተነሥቷል፡እንጂ፡በዚህ፡የለም።
6-7፤የሰው፡ልጅ፡በኀጢአተኛዎች፡እጅ፡ዐልፎ፡ሊሰጥና፡ሊሰቀል፡በሦስተኛውም፡ቀን፡ሊነሣ፡ግድ፡ነው፡እያለ፡ገ ና፡በገሊላ፡ሳለ፡ለእናንተ፡እንደ፡ተናገረ፡ዐስቡ።
8-9፤ቃሎቹንም፡ዐሰቡ፥ከመቃብሩም፡ተመልሰው፡ይህን፡ዅሉ፡ለዐሥራ፡አንዱና፡ለሌላዎች፡ዅሉ፡ነገሯቸው።
10፤ይህንም፡ለሐዋርያት፡የነገሯቸው፡መግደላዊት፡ማርያምና፡ዮሐና፡የያዕቆብም፡እናት፡ማርያም፡ከነርሱም፡ጋ ራ፡የነበሩት፡ሌላዎች፡ሴቶች፡ነበሩ።
11፤ይህም፡ቃል፡ቅዠት፡መስሎ፡ታያቸውና፡አላመኗቸውም።
12፤ጴጥሮስ፡ግን፡ተነሥቶ፡ወደ፡መቃብር፡ሮጠ፤በዚያም፡ዝቅ፡ብሎ፡ሲመለከት፡የተልባ፡እግር፡ልብስን፡ብቻ፡አ የ፤በኾነውም፡ነገር፡እየተደነቀ፡ወደ፡ቤቱ፡ኼደ።
13፤እንሆም፥ከነርሱ፡ኹለቱ፡በዚያ፡ቀን፡ከኢየሩሳሌም፡ስድሳ፡ምዕራፍ፡ያኽል፡ወደሚርቅ፡ኤማሁስ፡ወደሚባል፡ መንደር፡ይኼዱ፡ነበር፤
14፤ስለዚህም፡ስለኾነው፡ነገር፡ዅሉ፡ርስ፡በርሳቸው፡ይነጋገሩ፡ነበር።
15፤ሲነጋገሩና፡ሲመራመሩም፥ኢየሱስ፡ራሱ፡ቀርቦ፡ከነርሱ፡ጋራ፡ይኼድ፡ነበር፤
16፤ነገር፡ግን፥እንዳያውቁት፡ዐይናቸው፡ተይዞ፡ነበር።
17፤ርሱም፦እየጠወለጋችኹ፡ስትኼዱ፥ርስ፡በርሳችኹ፡የምትነጋገሯቸው፡እነዚህ፡ነገሮች፡ምንድር፡ናቸው፧አላቸ ው።
18፤ቀለዮጳ፡የሚባልም፡አንዱ፡መልሶ፦አንተ፡በኢየሩሳሌም፡እንግዳ፡ኾነኽ፡ለብቻኽ፡ትኖራለኽን፧በእነዚህ፡ቀ ኖች፡በዚያ፡የኾነውን፡ነገር፡አታውቅምን፧አለው።
19፤ርሱም፦ይህ፡ምንድር፡ነው፧አላቸው።እነርሱም፡እንዲህ፡አሉት፦በእግዚአብሔርና፡በሕዝቡ፡ዅሉ፡ፊት፡በሥራ ና፡በቃል፡ብርቱ፡ነቢይ፡ስለነበረው፡ስለናዝሬቱ፡ስለ፡ኢየሱስ፤
20፤ርሱንም፡የካህናት፡አለቃዎችና፡መኳንንቶቻችን፡ለሞት፡ፍርድ፡እንዴት፡አሳልፈው፡እንደ፡ሰጡትና፡እንደ፡ ሰቀሉት፡ነው።
21፤እኛ፡ግን፡እስራኤልን፡እንዲቤዥ፡ያለው፡ርሱ፡እንደ፡ኾነ፡ተስፋ፡አድርገን፡ነበር፤ደግሞም፡ከዚህ፡ዅሉ፡ ጋራ፡ይህ፡ከኾነ፡ዛሬ፡ሦስተኛው፡ቀን፡ነው።
22፤ደግሞም፡ከእኛ፡ውስጥ፡ማልደው፡ከመቃብሩ፡ዘንድ፡የነበሩት፡አንዳንድ፡ሴቶች፡አስገረሙን፤
23፤ሥጋውንም፡ባጡ፡ጊዜ፦ሕያው፡ነው፡የሚሉ፡የመላእክትን፡ራእይ፡ደግሞ፡አየን፡ሲሉ፡መጥተው፡ነበር።
24፤ከእኛም፡ጋራ፡ከነበሩት፡ወደ፡መቃብር፡ኼደው፡ሴቶች፡እንደ፡ተናገሩት፡ኾኖ፡አገኙት፥ርሱን፡ግን፡አላዩት ም።
25፤ርሱም፦እናንተ፡የማታስተውሉ፥ነቢያትም፡የተናገሩትን፡ዅሉ፡ልባችኹ፡ከማመን፡የዘገየ፤
26፤ክርስቶስ፡ይህን፡መከራ፡ይቀበል፡ዘንድና፡ወደ፡ክብሩ፡ይገባ፡ዘንድ፡ይገ፟ባ፟ው፡የለምን፧አላቸው።
27፤ከሙሴና፡ከነቢያት፡ዅሉ፡ዠምሮ፡ስለ፡ርሱ፡በመጻሕፍት፡ዅሉ፡የተጻፈውን፡ተረጐመላቸው።
28፤ወደሚኼዱበትም፡መንደር፡ቀረቡ፥ርሱም፡ሩቅ፡የሚኼድ፡መሰላቸው።
29፤እነርሱ፦ከእኛ፡ጋራ፡ዕደር፥ማታ፡ቀርቧልና፥ቀኑም፡ሊመሽ፡ዠምሯል፡ብለው፡ግድ፡አሉት፤ከነርሱም፡ጋራ፡ሊ ያድር፡ገባ።
30፤ከነርሱም፡ጋራ፡በማእዱ፡ተቀምጦ፡ሳለ፡እንጀራውን፡አንሥቶ፡ባረከው፥ቈርሶም፡ሰጣቸው፤
31፤ዐይናቸውም፡ተከፈተ፥ዐወቁትም፤ርሱም፡ከነርሱ፡ተሰወረ።
32፤ርስ፡በርሳቸውም፦በመንገድ፡ሲናገረን፡መጻሕፍትንም፡ሲከፍትልን፡ልባችን፡ይቃጠልብን፡አልነበረምን፧ተባ ባሉ።
33-34፤በዚያችም፡ሰዓት፡ተነሥተው፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ተመለሱ፥ዐሥራ፡አንዱና፡ከነርሱ፡ጋራ፡የነበሩትም፦ጌታ፡ በእውነት፡ተነሥቷል፡ለስምዖንም፡ታይቷል፡እያሉ፡በአንድነት፡ተሰብስበው፡አገኟቸው።
35፤እነርሱም፡በመንገድ፡የኾነውን፡እንጀራውንም፡በቈረሰ፡ጊዜ፡እንዴት፡እንደ፡ታወቀላቸው፡ተረኩላቸው።
36፤ይህንም፡ሲነጋገሩ፡ኢየሱስ፡ራሱ፡በመካከላቸው፡ቆሞ፦ሰላም፡ለእናንተ፡ይኹን፡አላቸው።
37፤ነገር፡ግን፥ደነገጡና፡ፈሩ፡መንፈስም፡ያዩ፡መሰላቸው።
38፤ርሱም፦ስለ፡ምን፡ትደነግጣላችኹ፧ስለ፡ምንስ፡ዐሳብ፡በልባችኹ፡ይነሣል፧
39፤እኔ፡ራሴ፡እንደ፡ኾንኹ፡እጆቼንና፡እግሮቼን፡እዩ፤በእኔ፡እንደምታዩት፥መንፈስ፡ሥጋና፡ዐጥንት፡የለውም ና፡እኔን፡ዳስሳችኹ፡እዩ፡አላቸው።
40፤ይህንም፡ብሎ፡እጆቹንና፡እግሮቹን፡አሳያቸው።
41፤እነርሱም፡ከደስታ፡የተነሣ፡ገና፡ስላላመኑ፡ሲደነቁ፡ሳሉ፦በዚህ፡አንዳች፡የሚበላ፡አላችኹን፧አላቸው።
42፤እነርሱም፡ከተጠበሰ፡ዓሣ፡አንድ፡ቍራጭ፥ከማር፡ወለላም፡ሰጡት፤
43፤ተቀብሎም፡በፊታቸው፡በላ።
44፤ርሱም፦ከእናንተ፡ጋራ፡ሳለኹ፡በሙሴ፡ሕግና፡በነቢያት፡በመዝሙራትም፡ስለ፡እኔ፡የተጻፈው፡ዅሉ፡ይፈጸም፡ ዘንድ፡ይገ፟ባ፟ል፡ብዬ፡የነገርዃችኹ፡ቃሌ፡ይህ፡ነው፡አላቸው።
45፤በዚያን፡ጊዜም፡መጻሕፍትን፡ያስተውሉ፡ዘንድ፡አእምሯቸውን፡ከፈተላቸው፤
46፤እንዲህም፡አላቸው፦ክርስቶስ፡መከራ፡ይቀበላል፡በሦስተኛውም፡ቀን፡ከሙታን፡ይነሣል፥
47፤በስሙም፡ንስሓና፡የኀጢአት፡ስርየት፡ከኢየሩሳሌም፡ዠምሮ፡በአሕዛብ፡ዅሉ፡ይሰበካል፡ተብሎ፡እንዲሁ፡ተጽ ፏል።
48፤እናንተም፡ለዚህ፡ምስክሮች፡ናችኹ።
49፤እንሆም፥አባቴ፡የሰጠውን፡ተስፋ፡እኔ፡እልክላችዃለኹ፤እናንተ፡ግን፡ከላይ፡ኀይል፡እስክትለብሱ፡ድረስ፡ በኢየሩሳሌም፡ከተማ፡ቈዩ።
50፤እስከ፡ቢታንያም፡አወጣቸው፡እጆቹንም፡አንሥቶ፡ባረካቸው።
51፤ሲባርካቸውም፡ከነርሱ፡ተለየ፡ወደ፡ሰማይም፡ዐረገ።
52፤እነርሱም፤ሰገዱለትና፡በብዙ፡ደስታ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ተመለሱ፥
53፤ዘወትርም፡እግዚአብሔርን፡እያመሰገኑና፡እየባረኩ፡በመቅደስ፡ኖሩ፨

http://www.gzamargna.net