መዠመሪያዪቱ፡የሐዋርያው፡ጳውሎስ፡መልእክት፡
ወደቆሮንቶስ፡ሰዎች።

(ክለሳ.1.20020507)

_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡1።______________
ምዕራፍ፡1፤
1፤በእግዚአብሔር፡ፈቃድ፡የኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ሐዋርያ፡ሊኾን፡የተጠራ፡ጳውሎስ፣ወንድሙም፡ሶስቴንስ፥
2፤በቆሮንቶስ፡ላለች፡ለእግዚአብሔር፡ቤተ፡ክርስቲያን፥በክርስቶስ፡ኢየሱስ፡ለተቀደሱት፥የእነርሱና፡የእኛ፡ ጌታ፡የኾነውን፡የጌታችንን፡የኢየሱስ፡ክርስቶስን፡ስም፡በየስፍራው፡ከሚጠሩት፡ዅሉ፡ጋራ፡ቅዱሳን፡ለመኾን፡ ለተጠሩት፤
3፤ከእግዚአብሔር፡ከአባታችን፡ከጌታም፡ከኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ጸጋና፡ሰላም፡ለእናንተ፡ይኹን።
4፤በክርስቶስ፡ኢየሱስ፡ስላመናችኹ፡በተሰጣችኹ፡በእግዚአብሔር፡ጸጋ፡ምክንያት፡ዅልጊዜ፡ስለ፡እናንተ፡አምላ ክን፡አመሰግናለኹ፤
5-6፤ለክርስቶስ፡መመስከሬ፡በእናንተ፡ዘንድ፡እንደ፡ጸና፥በነገር፡ዅሉ፣በቃልም፡ዅሉ፣በዕውቀትም፡ዅሉ፡በርሱ ፡ባለጠጋዎች፡እንድትኾኑ፡ተደርጋችዃልና።
7፤እንደዚህ፡የጌታችንን፡የኢየሱስ፡ክርስቶስን፡መገለጥ፡ስትጠባበቁ፡አንድ፡የጸጋ፡ስጦታ፡እንኳ፡አይጐድልባ ችኹም፤
8፤ርሱም፡ደግሞ፡በጌታችን፡በኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ቀን፡ያለነቀፋ፡እንድትኾኑ፡እስከ፡ፍጻሜ፡ድረስ፡ያጸናችዃል ።
9፤ወደልጁ፡ወደጌታችን፡ወደኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ኅብረት፡የጠራችኹ፡እግዚአብሔር፡የታመነ፡ነው።
10፤ነገር፡ግን፥ወንድሞች፡ሆይ፥ዅላችኹ፡አንድ፡ንግግር፡እንድትናገሩ፡ባንድ፡ልብና፡ባንድ፡ዐሳብም፡የተባበ ራችኹ፡እንድትኾኑ፡እንጂ፡መለያየት፡በመካከላችኹ፡እንዳይኾን፡በጌታችን፡በኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ስም፡እለምና ችዃለኹ።
11፤ወንድሞቼ፡ሆይ፥በመካከላችኹ፡ክርክር፡እንዳለ፡ስለ፡እናንተ፡የቀሎዔ፡ቤተ፡ሰዎች፡አስታውቀውኛልና።
12፤ይህንም፡እላለኹ፦እያንዳንዳችኹ፦እኔ፡የጳውሎስ፡ነኝ፥እኔስ፡የአጵሎስ፡ነኝ፥እኔ፡ግን፡የኬፋ፡ነኝ፥እኔ ስ፡የክርስቶስ፡ነኝ፡ትላላችኹ።
13፤ክርስቶስ፡ተከፍሏልን፧ጳውሎስስ፡ስለ፡እናንተ፡ተሰቀለን፧ወይስ፡በጳውሎስ፡ስም፡ተጠመቃችኹን፧
14-15፤በስሜ፡እንደ፡ተጠመቃችኹ፡ማንም፡እንዳይል፡ከቀርስጶስና፡ከጋይዮስ፡በቀር፡ከእናንተ፡አንድን፡እንኳ፡ ስላላጠመቅኹ፡እግዚአብሔርን፡አመሰግናለኹ።
16፤የእስጢፋኖስንም፡ቤተ፡ሰዎች፡ደግሞ፡አጥምቄያለኹ፤ጨምሬ፡ሌላ፡አጥምቄ፡እንደ፡ኾነ፡አላውቅም።
17፤ለማጥመቅ፡ክርስቶስ፡አልላከኝምና፥ወንጌልን፡ልሰብክ፡እንጂ፤የክርስቶስ፡መስቀል፡ከንቱ፡እንዳይኾን፡በ ቃል፡ጥበብ፡አይደለም።
18፤የመስቀሉ፡ቃል፡ለሚጠፉት፡ሞኝነት፥ለእኛ፡ለምንድን፡ግን፡የእግዚአብሔር፡ኀይል፡ነውና።
19፤የጥበበኛዎችን፡ጥበብ፡አጠፋለኹ፡የአስተዋዮችንም፡ማስተዋል፡እጥላለኹ፡ተብሎ፡ተጽፏልና።
20፤ጥበበኛ፡የት፡አለ፧ጻፊስ፡የት፡አለ፧የዚች፡ዓለም፡መርማሪስ፡የት፡አለ፧እግዚአብሔር፡የዚችን፡ዓለም፡ጥ በብ፡ሞኝነት፡እንዲኾን፡አላደረገምን፧
21፤በእግዚአብሔር፡ጥበብ፡ምክንያት፡ዓለም፡እግዚአብሔርን፡በጥበቧ፡ስላላወቀች፥በስብከት፡ሞኝነት፡የሚያም ኑትን፡ሊያድን፡የእግዚአብሔር፡በጎ፡ፈቃድ፡ኾኗልና።
22፤መቼም፡አይሁድ፡ምልክትን፡ይለምናሉ፡የግሪክ፡ሰዎችም፡ጥበብን፡ይሻሉ፥
23፤እኛ፡ግን፡የተሰቀለውን፡ክርስቶስን፡እንሰብካለን፤ይህም፡ለአይሁድ፡ማሰናከያ፡ለአሕዛብም፡ሞኝነት፡ነው ፥
24፤ለተጠሩት፡ግን፥አይሁድ፡ቢኾኑ፡የግሪክ፡ሰዎችም፡ቢኾኑ፥የእግዚአብሔር፡ኀይልና፡የእግዚአብሔር፡ጥበብ፡ የኾነው፡ክርስቶስ፡ነው።
25፤ከሰው፡ይልቅ፡የእግዚአብሔር፡ሞኝነት፡ይጠበባልና፥የእግዚአብሔርም፡ድካም፡ከሰው፡ይልቅ፡ይበረታልና።
26፤ወንድሞች፡ሆይ፥መጠራታችኹን፡ተመልከቱ፤እንደ፡ሰው፡ጥበብ፡ጥበበኛዎች፡የኾኑ፡ብዙዎች፥ኀያላን፡የኾኑ፡ ብዙዎች፥ባላባቶች፡የኾኑ፡ብዙዎች፡አልተጠሩም።
27፤ነገር፡ግን፥እግዚአብሔር፡ጥበበኛዎችን፡እንዲያሳፍር፡የዓለምን፡ሞኝ፡ነገር፡መረጠ፤ብርቱንም፡ነገር፡እ ንዲያሳፍር፡እግዚአብሔር፡የዓለምን፡ደካማ፡ነገር፡መረጠ፤
28፤እግዚአብሔርም፡የኾነውን፡ነገር፡እንዲያጠፋ፡የዓለምን፡ምናምንቴ፡ነገር፡የተናቀውንም፡ነገር፡ያልኾነው ንም፡ነገር፡መረጠ፥
29፤ሥጋን፡የለበሰ፡ዅሉ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡እንዳይመካ።
30-31፤ነገር፡ግን፦የሚመካ፡በእግዚአብሔር፡ይመካ፡ተብሎ፡እንደተጻፈው፡ይኾን፡ዘንድ፥ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ ጥበብና፡ጽድቅ፣ቅድስናም፣ቤዛነትም፡በተደረገልን፡በክርስቶስ፡ኢየሱስ፡የኾናችኹ፡ከርሱ፡ነው።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡2።______________
ምዕራፍ፡2፤
1፤እኔም፥ወንድሞች፡ሆይ፥ወደ፡እናንተ፡በመጣኹ፡ጊዜ፡በቃልና፡በጥበብ፡ብልጫ፡ለእግዚአብሔር፡ምስክርነቴን፡ ለእናንተ፡እየነገርኹ፡አልመጣኹም።
2፤በመካከላችኹ፡ሳለኹ፡ከኢየሱስ፡ክርስቶስ፡በቀር፥ርሱም፡አንደ፡ተሰቀለ፡ሌላ፡ነገር፡እንዳላውቅ፡ቈርጬ፡ነ በርና።
3፤እኔም፡በድካምና፡በፍርሀት፡በብዙ፡መንቀጥቀጥም፡በእናንተ፡ዘንድ፡ነበርኹ፤
4-5፤እምነታችኹም፡በእግዚአብሔር፡ኀይል፡እንጂ፡በሰው፡ጥበብ፡እንዳይኾን፥ቃሌም፡ስብከቴም፡መንፈስንና፡ኀይ ልን፡በመግለጥ፡ነበረ፡እንጂ፥በሚያባብል፡በጥበብ፡ቃል፡አልነበረም።
6፤በበሰሉት፡መካከል፡ግን፡ጥበብን፡እንናገራለን፥ነገር፡ግን፥የዚችን፡ዓለም፡ጥበብ፡አይደለም፡የሚሻሩትንም ፡የዚችን፡ዓለም፡ገዢዎች፡ጥበብ፡አይደለም፤
7፤ነገር፡ግን፥እግዚአብሔር፡አስቀድሞ፡ከዘመናት፡በፊት፡ለክብራችን፡የወሰነውን፥ተሰውሮም፡የነበረውን፡የእ ግዚአብሔርን፡ጥበብ፡በምስጢር፡እንናገራለን።
8፤ከዚችም፡ዓለም፡ገዢዎች፡አንዱ፡እንኳ፡ይህን፡ጥበብ፡አላወቀም፤ዐውቀውስ፡ቢኾኑ፡የክብርን፡ጌታ፡ባልሰቀሉ ትም፡ነበር፤
9፤ነገር፡ግን፦ዐይን፡ያላየችው፡ዦሮም፡ያልሰማው፡በሰውም፡ልብ፡ያልታሰበው፡እግዚአብሔር፡ለሚወዱት፡ያዘጋጀ ው፡ተብሎ፡አንደ፡ተጻፈ፥እንዲህ፡እንናገራለን።
10፤መንፈስም፡የእግዚአብሔርን፡ጥልቅ፡ነገር፡ስንኳ፡ሳይቀር፡ዅሉን፡ይመረምራልና፥ለእኛ፡እግዚአብሔር፡በመ ንፈሱ፡በኩል፡ገለጠው።
11፤በርሱ፡ውስጥ፡ካለው፡ከሰው፡መንፈስ፡በቀር፡ለሰው፡ያለውን፡የሚያውቅ፡ሰው፡ማን፡ነው፧እንዲሁም፡ደግሞ፡ ከእግዚአብሔር፡መንፈስ፡በቀር፡ለእግዚአብሔር፡ያለውን፡ማንም፡አያውቅም።
12፤እኛ፡ግን፡ከእግዚአብሔር፡እንዲያው፡የተሰጠንን፡እናውቅ፡ዘንድ፡ከእግዚአብሔር፡የኾነውን፡መንፈስ፡እን ጂ፡የዓለምን፡መንፈስ፡አልተቀበልንም።
13፤መንፈሳዊውን፡ነገር፡ከመንፈሳዊው፡ነገር፡ጋራ፡አስተያይተን፡መንፈስ፡በሚያስተምረን፡ቃል፡ይህን፡ደግሞ ፡እንናገራለን፡እንጂ፡የሰው፡ጥበብ፡በሚያስተምረን፡ቃል፡አይደለም።
14፤ለፍጥረታዊ፡ሰው፡የእግዚአብሔር፡መንፈስ፡ነገር፡ሞኝነት፡ነውና፥አይቀበለውም፤በመንፈስም፡የሚመረመር፡ ስለ፡ኾነ፡ሊያውቀው፡አይችልም።
15፤መንፈሳዊ፡ሰው፡ግን፡ዅሉን፡ይመረምራል፡ራሱ፡ግን፡በማንም፡አይመረመርም።
16፤እንዲያስተምረው፡የጌታን፡ልብ፡ማን፡ዐውቆት፡ነው፧እኛ፡ግን፡የክርስቶስ፡ልብ፡አለን።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡3።______________
ምዕራፍ፡3፤
1፤እኔም፥ወንድሞች፡ሆይ፥የሥጋ፡እንደ፡መኾናችኹ፥በክርስቶስም፡ሕፃናት፡እንደ፡መኾናችኹ፡እንጂ፡መንፈሳውያ ን፡እንደ፡መኾናችኹ፡ልናገራችኹ፡አልቻልኹም።
2፤ገና፡ጽኑ፡መብል፡ለመብላት፡አትችሉም፡ነበርና፥ወተት፡ጋትዃችኹ፤
3፤ገና፡ሥጋውያን፡ናችኹና፥እስከ፡አኹን፡ድረስ፡ገና፡አትችሉም።ቅናትና፡ክርክር፡ስለሚገኝባችኹ፡ሥጋውያን፡ መኾናችኹ፡አይደላችኹምን፧እንደ፡ሰው፡ልማድስ፡አትመላለሱምን፧
4፤አንዱ፦እኔ፡የጳውሎስ፡ነኝ፥ኹለተኛውም፦እኔ፡የአጵሎስ፡ነኝ፡ቢል፡ሰዎች፡ብቻ፡መኾናችኹ፡አይደለምን፧
5፤አጵሎስ፡እንግዲህ፡ምንድር፡ነው፧ጳውሎስስ፡ምንድር፡ነው፧በእነርሱ፡እጅ፡ያመናችኹ፡አገልጋዮች፡ናቸው፤ለ ያንዳንዳቸውም፡ጌታ፡እንደ፡ሰጣቸው፡ያገለግላሉ።
6፤እኔ፡ተከልኹ፡አጵሎስም፡አጠጣ፥ነገር፡ግን፥እግዚአብሔር፡ያሳድግ፡ነበር፤
7፤እንግዲያስ፡የሚያሳድግ፡እግዚአብሔር፡እንጂ፡የሚተክል፡ቢኾን፡ወይም፡የሚያጠጣ፡ቢኾን፡አንዳች፡አይደለም ።
8፤የሚተክልና፡የሚያጠጣ፡አንድ፡ናቸው፥ነገር፡ግን፥እያንዳንዱ፡እንደ፡ራሱ፡ድካም፡መጠን፡የራሱን፡ደመ፡ወዝ ፡ይቀበላል።
9፤የእግዚአብሔር፡ዕርሻ፡ናችኹ፤የእግዚአብሔር፡ሕንፃ፡ናችኹ፤ከርሱ፡ጋራ፡ዐብረን፡የምንሠራ፡ነንና።
10፤የእግዚአብሔር፡ጸጋ፡እንደተሰጠኝ፡መጠን፡እንደ፡ብልኀተኛ፡የዐናጺ፡አለቃ፡መሠረትን፡መሠረትኹ፥ሌላውም ፡በላዩ፡ያንጻል።እያንዳንዱ፡ግን፡በርሱ፡ላይ፡እንዴት፡እንዲያንጽ፡ይጠንቀቅ።
11፤ከተመሠረተው፡በቀር፡ማንም፡ሌላ፡መሠረት፡ሊመሠርት፡አይችልምና፥ርሱም፡ኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ነው።
12፤ማንም፡ግን፡በዚህ፡መሠረት፡ላይ፡በወርቅ፡ቢኾን፡በብርም፡በከበረ፡ድንጋይም፡በዕንጨትም፡በሣርም፡ወይም ፡በአገዳ፡ቢያንጽ፥የያንዳንዱ፡ሥራ፡ይገለጣል፤
13፤በእሳት፡ስለሚገለጥ፡ያ፡ቀን፡ያሳያልና፥የያንዳንዱም፡ሥራ፡እንዴት፡መኾኑን፡እሳቱ፡ይፈትነዋል።
14፤ማንም፡በርሱ፡ላይ፡ያነጸው፡ሥራ፡ቢጸናለት፡ደመ፡ወዙን፡ይቀበላል፤
15፤የማንም፡ሥራ፡የተቃጠለበት፡ቢኾን፡ይጐዳበታል፥ርሱ፡ራሱ፡ግን፡ይድናል፥ነገር፡ግን፥በእሳት፡እንደሚድን ፡ይኾናል።
16፤የእግዚአብሔር፡ቤተ፡መቅደስ፡እንደ፡ኾናችኹ፡የእግዚአብሔርም፡መንፈስ፡እንዲኖርባችኹ፡አታውቁምን፧
17፤ማንም፡የእግዚአብሔርን፡ቤተ፡መቅደስ፡ቢያፈርስ፡እግዚአብሔር፡ርሱን፡ያፈርሰዋል፤የእግዚአብሔር፡ቤተ፡ መቅደስ፡ቅዱስ፡ነውና፥ያውም፡እናንተ፡ናችኹ።
18፤ማንም፡ራሱን፡አያታል፟፤ከእናንተ፡ማንም፡በዚች፡ዓለም፡ጥበበኛ፡የኾነ፡ቢመስለው፡ጥበበኛ፡ይኾን፡ዘንድ ፡ሞኝ፡ይኹን።
19-20፤የዚች፡ዓለም፡ጥበብ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ሞኝነት፡ነውና፦ርሱ፡ጥበበኛዎችን፡በተንኰላቸው፡የሚይዝ፤ደ ግሞም፦ጌታ፡የጥበበኛዎችን፡ዐሳብ፡ከንቱ፡እንደ፡ኾነ፡ያውቃል፡ተብሎ፡ተጽፏልና።
21፤ስለዚህም፡ማንም፡በሰው፡አይመካ።ነገር፡ዅሉ፡የእናንተ፡ነውና፤
22፤ጳውሎስ፡ቢኾን፡አጵሎስም፡ቢኾን፡ኬፋም፡ቢኾን፡ዓለምም፡ቢኾን፡ሕይወትም፡ቢኾን፡ሞትም፡ቢኾን፡ያለውም፡ ቢኾን፡የሚመጣውም፡ቢኾን፥
23፤ዅሉ፡የእናንተ፡ነው፥እናንተም፡የክርስቶስ፡ናችኹ፡ክርስቶስም፡የእግዚአብሔር፡ነው።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡4።______________
ምዕራፍ፡4፤
1፤እንዲሁ፡ሰው፡እኛን፡እንደክርስቶስ፡ሎሌዎችና፡እንደእግዚአብሔር፡ምስጢር፡መጋቢዎች፡ይቍጠረን።
2፤እንደዚህም፡ሲኾን፥በመጋቢዎች፡ዘንድ፡የታመነ፡ኾኖ፡መገኘት፡ይፈለጋል።
3፤ነገር፡ግን፥በእናንተ፡ዘንድ፡ወይም፡በሌላ፡ሰው፡ዘንድ፡ብፈረድ፡ለእኔ፡ምንም፡አይደለም፤እኔም፡በራሴ፡እ ንኳ፡አልፈርድም፤
4፤በራሴ፡ላይ፡ምንም፡አላውቅምና፥ነገር፡ግን፥በዚህ፡አልጸድቅም፤እኔን፡የሚፈርድ፡ግን፡ጌታ፡ነው።
5፤ስለዚህም፡በጨለማ፡የተሰወረውን፡ደግሞ፡ወደ፡ብርሃን፡የሚያወጣ፡የልብንም፡ምክር፡የሚገልጥ፡ጌታ፡እስኪመ ጣ፡ድረስ፡ጊዜው፡ሳይደርስ፡አንዳች፡አትፍረዱ፤በዚያን፡ጊዜም፡ለያንዳንዱ፡ምስጋናው፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ ፡ይኾናል።
6፤ወንድሞች፡ሆይ፥ስለ፡አንዱ፡በአንዱ፡ላይ፡አንዳችኹም፡እንዳይ(ት)ታበዩ፦ከተጻፈው፡አትለፍ፡የሚለውን፡በእኛ፡ትማሩ፡ዘንድ፥ይህን፡በእናንተ፡ምክንያት፡ስለ፡ራሴና፡ስለ፡አጵ ሎስ፡እንደ፡ምሳሌ፡ተናገርኹ።
7፤አንተ፡እንድትበልጥ፡ማን፡አድርጎኻል፧ያልተቀበልኸውስ፡ምን፡አለኽ፧የተቀበልኽ፡ከኾንኽ፡ግን፡እንዳልተቀ በልኽ፡የምትመካ፡ስለ፡ምንድር፡ነው፧
8፤አኹን፡ጠግባችዃል፤አኹንስ፡ባለጠጋዎች፡ኾናችዃል፤ያለእኛ፡ነግሣችዃል፤እኛ፡ደግሞ፡ከእናንተ፡ጋራ፡እንድ ንነግሥ፡ብትነግሡ፡መልካም፡ይኾን፡ነበር።
9፤ለዓለም፡ለመላእክትም፡ለሰዎችም፡መጫወቻ፡ኾነናልና፤እግዚአብሔር፡እኛን፡ሐዋርያቱን፡ሞት፡እንደተፈረደባ ቸው፡ሰዎች፡ከዅሉ፡ይልቅ፡የዃለኛዎች፡እንዳደረገን፡ይመስለኛልና።
10፤እኛ፡ስለ፡ክርስቶስ፡ሞኞች፡ነን፡እናንተ፡ግን፡በክርስቶስ፡ልባሞች፡ናችኹ፤እኛ፡ደካማዎች፡ነን፡እናንተ ፡ግን፡ኀይለኛዎች፡ናችኹ፤እናንተ፡የከበራችኹ፡ናችኹ፡እኛ፡ግን፡የተዋረድን፡ነን።
11፤እስከዚህ፡ሰዓት፡ድረስ፡እንራባለን፥እንጠማለን፥እንራቈታለን፥እንጐሰማለን፥እንንከራተታለን፥
12፤በገዛ፡እጃችን፡እየሠራን፡እንደክማለን፤ሲሰድቡን፡እንመርቃለን፥ሲያሳድዱን፡እንታገሣለን፥ክፉ፡ሲናገሩ ን፡እንማልዳለን፤
13፤እስከ፡አኹን፡ድረስ፡የዓለም፡ጥራጊ፡የዅሉም፡ጕድፍ፡ኾነናል።
14፤እንደምወዳችኹ፡ልጆቼ፡አድርጌ፡ልገሥጻችኹ፡እንጂ፡ላሳፍራችኹ፡ይህን፡አልጽፍም።
15፤በክርስቶስ፡አእላፍ፡ሞግዚቶች፡ቢኖሯችኹ፡ብዙ፡አባቶች፡የሏችኹም፡እኔ፡በክርስቶስ፡ኢየሱስ፡በወንጌል፡ ወልጃችዃለኹና።
16፤እንግዲህ፡እኔን፡የምትመስሉ፡ኹኑ፡ብዬ፡እለምናችዃለኹ።
17፤ስለዚህ፥የምወደ፟ውንና፡የታመነውን፥በጌታ፡ልጄ፡የኾነውን፥ጢሞቴዎስን፡ልኬላችዃለኹ፤እኔም፡በየስፍራው ፡በአብያተ፡ክርስቲያናት፡ዅሉ፡እንደማስተምር፥በክርስቶስ፡ኢየሱስ፡የሚኾነውን፡መንገዴን፡ርሱ፡ያሳስባችዃ ል።
18፤አንዳንዱ፡ግን፡ወደ፡እናንተ፡የማልመጣ፡እየመሰላቸው፡የታበዩ፡አሉ፤
19፤ነገር፡ግን፥ጌታ፡ቢፈቅድ፡ፈጥኜ፡ወደ፡እናንተ፡እመጣለኹ፥የትዕቢተኛዎችንም፡ኀይል፡ዐውቃለኹ፡እንጂ፡ቃ ላቸውን፡አይደለም፤
20፤የእግዚአብሔር፡መንግሥት፡በኀይል፡ነው፡እንጂ፡በቃል፡አይደለምና።
21፤ምን፡ትወዳላችኹ፧በበትር፡ወይስ፡በፍቅርና፡በየውሀት፡መንፈስ፡ልምጣባችኹን፧
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡5።______________
ምዕራፍ፡5፤
1፤በዐጪር፡ቃል፡በእናንተ፡መካከል፡ዝሙት፡እንዳለ፡ይወራል፡የዚያም፡ዐይነት፡ዝሙት፡በአሕዛብስ፡እንኳ፡የማ ይገኝ፡ነው፥የአባቱን፡ሚስት፡ያገባ፡ሰው፡ይኖራልና።
2፤እናንተም፡ታብያችዃል፤ይልቅስ፡እንድታዝኑ፡አይገ፟ባ፟ችኹምን፧ይህን፡ሥራ፡የሠራው፡ከመካከላችኹ፡ይወገድ ።
3-4፤እኔ፡ምንም፡እንኳ፡በሥጋ፡ከእናንተ፡ጋራ፡ባልኾን፥በመንፈስ፡ከእናንተ፡ጋራ፡ነኝ፥ከእናንተም፡ጋራ፡እን ዳለኹ፡ኾኜ፡ይህን፡እንደዚህ፡በሠራው፡ላይ፡በጌታችን፡በኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ስም፡አኹን፡ፈርጄበታለኹ፤እናን ተና፡መንፈሴም፡ከጌታችን፡ከኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ኀይል፡ጋራ፡ተሰብስበን፥
5፤መንፈሱ፡በጌታ፡በኢየሱስ፡ቀን፡ትድን፡ዘንድ፡እንደዚህ፡ያለው፡ለሥጋው፡ጥፋት፡ለሰይጣን፡እንዲሰጥ፡ፍርዴ ፡ነው።
6፤መመካታችኹ፡መልካም፡አይደለም።ጥቂት፡ርሾ፡ሊጡን፡ዅሉ፡እንዲያቦካ፡አታውቁምን፧
7፤እንግዲህ፡ያለርሾ፡እንዳላችኹ፡ዐዲሱን፡ሊጥ፡ትኾኑ፡ዘንድ፡አሮጌውን፡ርሾ፡አስወግዱ።ፋሲካችን፡ክርስቶስ ፡ታርዷልና፤
8፤ስለዚህ፥በቅንነትና፡በእውነት፡ቂጣ፡በዓልን፡እናድርግ፡እንጂ፥በአሮጌ፡ርሾ፣በክፋትና፡በግፍ፡ርሾም፡አይ ደለም።
9፤ከሴሰኛዎች፡ጋራ፡እንዳትተባበሩ፡በመልእክቴ፡ጻፍኹላችኹ።
10፤በጠቅላላው፡የዚህን፡ዓለም፡ሴሰኛዎችን፥ወይም፡ገንዘብን፡የሚመኙትን፡ነጣቂዎችንም፥ወይም፡ጣዖትን፡የሚ ያመልኩትን፡አላልኹም፤ይህስ፡ቢኾን፡ከዓለም፡ልትወጡ፡ይገ፟ባ፟ችኹ፡ነበር።
11፤አኹን፡ግን፡ወንድሞች፡ከሚባሉት፡አንዱ፡ሴሰኛ፡ወይም፡ገንዘብን፡የሚመኝ፡ወይም፡ጣዖትን፡የሚያመልክ፡ወ ይም፡ተሳዳቢ፡ወይም፡ሰካር፡ወይም፡ነጣቂ፡ቢኾን፡ከርሱ፡ጋራ፡እንዳትተባበሩ፡እጽፍላችዃለኹ፤እንደነዚህ፡ካ ለው፡ጋራ፡መብል፡እንኳን፡አትብሉ።
12፤በውጭ፡ባሉ፡ሰዎች፡ላይ፡መፍረድ፡ምን፡አግዶኝ፧በውስጥ፡ባሉ፡ሰዎች፡ላይ፡እናንተ፡አትፈርዱምን፧
13፤በውጭ፡ባሉቱ፡ግን፡እግዚአብሔር፡ይፈርድባቸዋል።ክፉውን፡ከመካከላችኹ፡አውጡት።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡6።______________
ምዕራፍ፡6፤
1፤ከእናንተ፡አንዱ፡ከባልንጀራው፡ጋራ፡ሙግት፡ቢኖረው፡በቅዱሳን፡ፊት፡በመፋረድ፡ፋንታ፡በዐመፀኛዎች፡ፊት፡ ሊፋረድ፡ይደፍራልን፧
2፤ቅዱሳን፡በዓለም፡ላይ፡እንዲፈርዱ፡አታውቁምን፧በዓለምስ፡ላይ፡ብትፈርዱ፡ከዅሉ፡ይልቅ፡ትንሽ፡ስለሚኾን፡ ነገር፡ልትፈርዱ፡አትበቁምን፧
3፤የትዳር፡ጕዳይ፡ይቅርና፡በመላእክት፡እንኳ፡እንድንፈርድ፡አታውቁምን፧
4፤እንግዲህ፡ስለትዳር፡ጕዳይ፡የፍርድ፡ቤት፡ቢያስፈልጋችኹ፡በቤተ፡ክርስቲያን፡የተናቁትን፡ሰዎች፡ፈራጆች፡ አድርጋችኹ፡ታስቀምጣላችኹን፧
5፤አሳፍራችኹ፡ዘንድ፡ይህን፡እላለኹ፦እንደዚህ፡ነውን፧በወንድሞች፡መካከል፡ሽማግሌ፡ሊኾን፡የሚችል፡አንድ፡ አስተዋይ፡ሰው፡በእናንተ፡ዘንድ፡አይገኝምን፧
6፤ነገር፡ግን፥ወንድም፡ወንድሙን፡ይከሳል፥ይህም፡በማያምኑ፡ፊት፡ይደረጋልን፧
7፤እንግዲህ፡ፈጽሞ፡የርስ፡በርስ፡ሙግት፡እንዳለባችኹ፡በእናንተ፡ጕድለት፡ነው።ብትበደሉ፡አይሻልምን፧ብትታ ለሉስ፡አይሻልምን፧
8፤ነገር፡ግን፥እናንተ፡ትበድላላችኹ፡ታታልሉማላችኹ፥ያውም፡ወንድሞቻችኹን።
9፤ወይስ፡ዐመፀኛዎች፡የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡እንዳይወርሱ፡አታውቁምን፧አትሳቱ፤ሴሰኛዎች፡ቢኾን፡ወይም ፡ጣዖትን፡የሚያመልኩ፡ወይም፡አመንዝራዎች፡ወይም፡ቀላጮች፡ወይም፡ከወንድ፡ጋራ፡ዝሙት፡የሚሠሩ፡
10፤ወይም፡ሌባዎች፡ወይም፡ገንዘብን፡የሚመኙ፡ወይም፡ሰካሮች፡ወይም፡ተሳዳቢዎች፡ወይም፡ነጣቂዎች፡የእግዚአ ብሔርን፡መንግሥት፡አይወርሱም።
11፤ከእናንተም፡አንዳንዶቹ፡እንደ፡እነዚህ፡ነበራችኹ፤ነገር፡ግን፥በጌታ፡በኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ስም፡በአምላ ካችንም፡መንፈስ፡ታጥባችዃል፥ተቀድሳችዃል፥ጸድቃችዃል።
12፤ዅሉ፡ተፈቅዶልኛል፥ዅሉ፡ግን፡አይጠቅምም።ዅሉ፡ተፈቅዶልኛል፥በእኔ፡ላይ፡ግን፡አንድ፡ነገር፡እንኳ፡አይ ሠለጥንብኝም።
13፤መብል፡ለሆድ፡ነው፥ሆድም፡ለመብል፡ነው፤እግዚአብሔር፡ግን፡ይህንም፡ያንም፡ያጠፋቸዋል።ሥጋ፡ግን፡ለጌታ ፡ነው፡እንጂ፡ለዝሙት፡አይደለም፤ጌታም፡ለሥጋ፡ነው፤
14፤እግዚአብሔርም፡ጌታንም፡አስነሣ፡እኛንም፡በኀይሉ፡ያስነሣናል።
15፤ሥጋችኹ፡የክርስቶስ፡ብልቶች፡እንደ፡ኾነ፡አታውቁምን፧እንግዲህ፡የክርስቶስን፡ብልቶች፡ወስጄ፡የጋለሞታ ፡ብልቶች፡ላድርጋቸውን፧አይገ፟ባ፟ም።
16፤ወይስ፡ከጋለሞታ፡ጋራ፡የሚተባበር፡አንድ፡ሥጋ፡እንዲኾን፡አታውቁምን፧ኹለቱ፡አንድ፡ሥጋ፡ይኾናሉ፡ተብሏ ልና።
17፤ከጌታ፡ጋራ፡የሚተባበር፡ግን፡አንድ፡መንፈስ፡ነው።
18፤ከዝሙት፡ሽሹ።ሰው፡የሚያደርገው፡ኀጢአት፡ዅሉ፡ከሥጋ፡ውጭ፡ነው፤ዝሙትን፡የሚሠራ፡ግን፡በገዛ፡ሥጋው፡ላ ይ፡ኀጢአትን፡ይሠራል።
19-20፤ወይስ፡ሥጋችኹ፡ከእግዚአብሔር፡የተቀበላችኹት፡በእናንተ፡የሚኖረው፡የመንፈስ፡ቅዱስ፡ቤተ፡መቅደስ፡እ ንደ፡ኾነ፡አታውቁምን፧በዋጋ፡ተገዝታችዃልና፥ለራሳችኹ፡አይደላችኹም፤ስለዚህ፥በሥጋችኹ፡እግዚአብሔርን፡አ ክብሩ።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡7።______________
ምዕራፍ፡7፤
1፤ስለጻፋችኹልኝስ፡ነገር፥ከሴት፡ጋራ፡አለመገናኘት፡ለሰው፡መልካም፡ነው።
2፤ነገር፡ግን፥ስለዝሙት፡ጠንቅ፡ለያንዳንዱ፡ለራሱ፡ሚስት፡ትኑረው፥ለያንዳንዲቱ፡ደግሞ፡ለራሷ፡ባል፡ይኑራት ።
3፤ባል፡ለሚስቱ፡የሚገ፟ባ፟ትን፡ያድርግላት፥እንደዚሁም፡ደግሞ፡ሚስቲቱ፡ለባሏ።
4፤ሚስት፡በገዛ፡ሥጋዋ፡ላይ፡ሥልጣን፡የላትም፥ሥልጣን፡ለባሏ፡ነው፡እንጂ፤እንዲሁም፡ደግሞ፡ባል፡በገዛ፡ሥጋ ው፡ላይ፡ሥልጣን፡የለውም፥ሥልጣን፡ለሚስቱ፡ነው፡እንጂ።
5፤ለጸሎት፡ትተጉ፡ዘንድ፡ተስማምታችኹ፡ለጊዜው፡ካልኾነ፡በቀር፥ርስ፡በርሳችኹ፡አትከላከሉ፤ራሳችኹን፡ስለ፡ አለመግዛት፡ሰይጣን፡እንዳይፈታተናችኹ፡ደግሞ፡ዐብራችኹ፡ኹኑ።
6፤ዳሩ፡ግን፡ይህን፡እንደ፡ፈቃድ፡እላለኹ፡እንጂ፡እንደ፡ትእዛዝ፡አይደለም።
7፤ሰው፡ዅሉ፡እንደ፡እኔ፡ሊኾን፡እወዳለኹና፤ነገር፡ግን፥እያንዳንዱ፡ከእግዚአብሔር፡ለራሱ፡የጸጋ፡ስጦታ፡አ ለው፥አንዱ፡እንደዚህ፡ኹለተኛውም፡እንደዚያ።
8፤ላላገቡና፡ለመበለቶች፡ግን፡እላለኹ፦እንደ፡እኔ፡ቢኖሩ፡ለእነርሱ፡መልካም፡ነው፤
9፤ነገር፡ግን፥በምኞት፡ከመቃጠል፡መጋባት፡ይሻላልና፥ራሳቸውን፡መግዛት፡ባይችሉ፡ያግቡ።
10-11፤ሚስትም፡ከባሏ፡አትለያይ፥ብትለያይ፡ግን፡ሳታገባ፡ትኑር፡ወይም፡ከባሏ፡ትታረቅ፥ባልም፡ሚስቱን፡አይተ ዋት፡ብዬ፡የተጋቡትን፡አዛቸዋለኹ፥እኔ፡ግን፡አላዝም፥ጌታ፡እንጂ።
12፤ሌላዎችንም፡እኔ፡እላለኹ፥ጌታም፡አይደለም፤ከወንድሞች፡ወገን፡ያላመነች፡ሚስት፡ያለችው፡ቢኖር፡ርሷም፡ ከርሱ፡ጋራ፡ልትቀመጥ፡ብትስማማ፥አይተዋት፤
13፤ያላመነ፡ባል፡ያላት፡ሚስትም፡ብትኖር፡ይህ፡ከርሷ፡ጋራ፡ሊቀመጥ፡ቢስማማ፥አትተወው።
14፤ያላመነ፡ባል፡በሚስቱ፡ተቀድሷልና፥ያላመነችም፡ሚስት፡በባሏ፡ተቀድሳለች፤አለዚያ፡ልጆቻችኹ፡ርኩሳን፡ና ቸው፤አኹን፡ግን፡የተቀደሱ፡ናቸው።
15፤የማያምን፡ግን፡ቢለይ፡ይለይ፤ወንድም፡ቢኾን፡ወይም፡እኅት፡እንዲህ፡በሚመስል፡ነገር፡አይገዙም፤እግዚአ ብሔር፡ግን፡በሰላም፡ጠርቶናል።
16፤አንቺ፡ሴት፥ባልሽን፡ታድኚ፡እንደ፡ኾንሽ፡ምን፡ታውቂያለሽ፧ወይስ፡አንተ፡ሰው፥ሚስትኽን፡ታድን፡እንደ፡ ኾንኽ፡ምን፡ታውቃለኽ፧
17፤ብቻ፡ለያንዳንዱ፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ከፈለለት፡እያንዳንዱም፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ጠራው፡እንዲሁ፡ይመ ላለስ።እንዲሁም፡በአብያተ፡ክርስቲያናት፡ዅሉ፡እደነግጋለኹ።
18፤ማንም፡ተገርዞ፡ሳለ፡ተጠርቶ፡እንደ፡ኾነ፥ወደ፡አለመገረዝ፡አይመለስ፤ማንም፡ሳይገረዝ፡ተጠርቶ፡እንደ፡ ኾነ፡አይገረዝ።
19፤መገረዝ፡ቢኾን፡አለመገረዝም፡ቢኾን፡ከንቱ፡ነው፥የእግዚአብሔርን፡ትእዛዝ፡መጠበቅ፡ነው፡እንጂ።
20፤እያንዳንዱ፡በተጠራበት፡መጠራት፡እንደዚሁ፡ይኑር።
21፤ባሪያ፡ኾነኽ፡ተጠርተኽ፡እንደ፡ኾነ፡አይገድኽም፤ሐራነት፡ልትወጣ፡ቢቻልኽ፡ግን፡ሐራነትን፡ተቀበል።
22፤ባሪያ፡ኾኖ፡በጌታ፡የተጠራ፡የጌታ፡ነጻ፡ነውና፤እንዲሁም፡ነጻ፡ኾኖ፡የተጠራ፡የክርስቶስ፡ባሪያ፡ነው።
23፤በዋጋ፡ተገዝታችዃል፤የሰው፡ባሪያዎች፡አትኹኑ።
24፤ወንድሞች፡ሆይ፥እያንዳንዱ፡በተጠራበት፡እንደዚሁ፡ኾኖ፡በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ይኑር።
25፤ስለ፡ደናግልም፡የጌታ፡ትእዛዝ፡የለኝም፥ነገር፡ግን፥የታመንኹ፡እኾን፡ዘንድ፡ከጌታ፡ምሕረትን፡የተቀበል ኹ፡እንደ፡መኾኔ፡ምክር፡እመክራለኹ።
26፤እንግዲህ፡ስላኹኑ፡ችግር፡ይህ፡መልካም፡ይመስለኛል፤ሰው፡እንዲህ፡ኾኖ፡ቢኖር፡መልካም፡ነው።
27፤በሚስት፡ታስረኽ፡እንደ፡ኾንኽ፡መፋታትን፡አትሻ፤በሚስት፡አልታሰርኽ፡እንደ፡ኾንኽ፡ሚስትን፡አትሻ።
28፤ብታገባ፡ግን፡ኀጢአት፡አትሠራም፡ድንግሊቱም፡ብታገባ፡ኀጢአት፡አትሠራም፤ነገር፡ግን፥እንዲህ፡በሚያደር ጉ፡በሥጋቸው፡ላይ፡መከራ፡ይኾንባቸዋል፥እኔም፡እራራላችኹ፡ነበር።
29፤ዳሩ፡ግን፥ወንድሞች፡ሆይ፥ይህን፡እናገራለኹ፤ዘመኑ፡ዐጪር፡ኾኗል፤ከእንግዲህ፡ወዲህ፡ሚስቶች፡ያሏቸው፡ እንደሌላቸው፡ይኹኑ፥
30፤የሚያለቅሱም፡እንደማያለቅሱ፥ደስ፡የሚላቸውም፡ደስ፡እንደማይላቸው፥
31፤የሚገዙም፡ምንም፡እንደሌላቸው፥በዚችም፡ዓለም፡የሚጠቀሙ፡በሙሉ፡እንደማይጠቀሙባት፡ይኹኑ፤የዚች፡ዓለም ፡መልክ፡ዐላፊ፡ነውና።
32፤ነገር፡ግን፥ያለዐሳብ፡ልትኖሩ፡እወዳለኹ።ያላገባው፡ጌታን፡እንዴት፡ደስ፡እንዲያሠኘው፡የጌታን፡ነገር፡ ያስባል፤
33፤ያገባው፡ግን፡ሚስቱን፡እንዴት፡ደስ፡እንዲያሠኛት፡የዓለምን፡ነገር፡ያስባል፥ልቡም፡ተከፍሏል።
34፤ያልተጋባች፡ሴትና፡ድንግል፡በሥጋም፡በነፍስም፡እንዲቀደሱ፡የጌታን፡ነገር፡ያስባሉ፤የተጋባች፡ግን፡ባሏ ን፡እንዴት፡ደስ፡እንድታሠኘው፡የዓለምን፡ነገር፡ታስባለች።
35፤ይህንም፡ለራሳችኹ፡ጥቅም፡እላለኹ፤በአገባብ፡እንድትኖሩ፡ሳትባክኑም፡በጌታ፡እንድትጸኑ፡ነው፡እንጂ፡ላ ጠምዳችኹ፡ብዬ፡አይደለም።
36፤ዳሩ፡ግን፡ማግባት፡ወደሚገ፟ባ፟ው፡ዕድሜ፡በደረሰ፡ጊዜ፡ስለ፡ድንግልናው፡ያፈረ፡ሰው፡ቢኖር፥የወደደውን ፡ያድርግ፤ኀጢአት፡የለበትም፤ይጋቡ።
37፤ሳይናወጥ፡በልቡ፡የጸና፡ግን፡ግድ፡የለበትም፥የወደደውን፡እንዲያደርግ፡ተፈቅዶለታል፤ድንግልናውንም፡በ ልቡ፡ይጠብቅ፡ዘንድ፡ቢጸና፥መልካም፡አደረገ።
38፤እንዲሁም፡ድንግልን፡ያገባ፡መልካም፡አደረገ፡ያላገባም፡የተሻለ፡አደረገ።
39፤ሴት፡ባሏ፡በሕይወት፡ሳለ፡የታሰረች፡ናት፤ባሏ፡ቢሞት፡ግን፡በጌታ፡ይኹን፡እንጂ፡የወደደችውን፡ልታገባ፡ ነጻነት፡አላት።
40፤እንደ፡ምክሬ፡ግን፡እንዳለች፡ብትኖር፡ደስተኛ፡ናት፤እኔም፡ደግሞ፡የእግዚአብሔር፡መንፈስ፡በእኔ፡ያለ፡ ይመስለኛል።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡8።______________
ምዕራፍ፡8፤
1፤ለጣዖት፡ስለተሠዋ፡ሥጋም፥ዅላችን፡ዕውቀት፡እንዳለን፡እናውቃለን።ዕውቀት፡ያስታብያል፡ፍቅር፡ግን፡ያንጻ ል።
2፤ማንም፡አንዳች፡የሚያውቅ፡ቢመስለው፡ሊያውቅ፡እንደሚገ፟ባ፟ው፡ገና፡አላወቀም፤
3፤ማንም፡ግን፡እግዚአብሔርን፡ቢወድ፡ርሱ፡በርሱ፡ዘንድ፡የታወቀ፡ነው።
4፤እንግዲህ፡ለጣዖት፡የተሠዋውን፡ሥጋ፡ስለ፡መብላት፥ጣዖት፡ዅሉ፡በዓለም፡ከንቱ፡እንደ፡ኾነ፡ከአንዱም፡በቀ ር፡ማንም፡አምላክ፡እንደሌለ፡እናውቃለን።
5፤መቼም፡ብዙ፡አማልክትና፡ብዙ፡ጌታዎች፡አሉ፤ነገር፡ግን፥በሰማይ፡ኾነ፡በምድርም፡ኾነ፡አማልክት፡የተባሉ፡ ምንም፡ቢኖሩ፥
6፤ለእኛስ፡ነገር፡ዅሉ፡ከርሱ፡የኾነ፡እኛም፡ለርሱ፡የኾን፟፡አንድ፡አምላክ፡አብ፡አለን፥ነገር፡ዅሉም፡በርሱ ፡በኩል፡የኾነ፡እኛም፡በርሱ፡በኩል፡የኾን፟፡አንድ፡ጌታ፡ኢየሱስ፡ክርስቶስ፡አለን።
7፤ነገር፡ግን፥ይህ፡ዕውቀት፡በዅሉ፡ዘንድ፡አይገኝም፤አንዳንዶች፡ግን፡ጣዖትን፡እስካኹን፡ድረስ፡ስለ፡ለመዱ ፦ለጣዖት፡የተሠዋ፡ነው፡ብለው፡ይበላሉና፥ኅሊናቸው፡ደካማ፡ስለ፡ኾነ፥ይረክሳል።
8፤መብል፡ግን፡ወደ፡እግዚአብሔር፡አያቀርበንም፤ባንበላም፡ምንም፡አይጐድለንም፡ብንበላም፡ምንም፡አይተርፈን ም።
9፤ዳሩ፡ግን፡ይህ፡መብታችኹ፡ለደካማዎች፡ዕንቅፋት፡እንዳይኾንባቸው፡ተጠንቀቁ።
10፤አንተ፡ዕውቀት፡ያለኽ፡በጣዖት፡ቤት፡በማእዱ፡ስትቀመጥ፡አንድ፡ሰው፡ቢያይኽ፥ደካማ፡ሰው፡ቢኾን፡ለጣዖት ፡የተሠዋውን፡ለመብላት፡ኅሊናው፡አይታነጽበትምን፧
11፤ባንተ፡ዕውቀትም፡ይህ፡ደካማ፡ይጠፋል፥ርሱም፡ክርስቶስ፡የሞተለት፡ወንድም፡ነው።
12፤እንዲህም፡ወንድሞችን፡እየበደላችኹ፥ደካማም፡የኾነውን፡ኅሊናቸውን፡እያቈሰላችኹ፡ክርስቶስን፡ትበድላላ ችኹ።
13፤ስለዚህም፡መብል፡ወንድሜን፡የሚያሰናክለው፡ከኾነ፥ወንድሜን፡እንዳላሰናክለው፡ለዘለዓለም፡ከቶ፡ሥጋ፡አ ልበላም።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡9።______________
ምዕራፍ፡9፤
1፤እኔ፡ነጻ፡አይደለኹምን፧ሐዋርያስ፡አይደለኹምን፧ጌታችንን፡ኢየሱስ፡ክርስቶስንስ፡አላየኹትምን፧እናንተስ ፡በጌታ፡ሥራዬ፡አይደላችኹምን፧
2፤የሐዋርያነቴ፡ማኅተም፡በጌታ፡እናንተ፡ናችኹና፥ለሌላዎች፡ሐዋርያ፡ባልኾን፡ለእናንተስ፡ምንም፡ቢኾን፡ሐዋ ርያ፡ነኝ።
3-4፤ለሚመረምሩኝ፡መልሴ፡ይህ፡ነው።ልንበላና፡ልንጠጣ፡መብት፡የለንምን፧
5፤እንደ፡ሌላዎቹ፡ሐዋርያትና፡እንደ፡ጌታ፡ወንድሞች፡እንደ፡ኬፋም፥እኅት፡ሚስታችንን፡ይዘን፡ልንዞር፡መብት ፡የለንምን፧
6፤ወይስ፡ሥራን፡ለመተው፡መብት፡የሌለን፡እኔና፡በርናባስ፡ብቻ፡ነን፧
7፤ከቶ፡በገዛ፡ገንዘቡ፡በወታደርነት፡የሚያገለግል፡ማን፡ነው፧ወይስ፡ወይን፡ተክሎ፡ፍሬውን፡የማይበላ፡ማን፡ ነው፧ወይስ፡መንጋ፡እየጠበቀ፡ከመንጋው፡ወተት፡የማይጠጣ፡ማን፡ነው፧
8፤ይህን፡በሰው፡ሥልጣን፡ብቻ፡እላለኹን፧
9፤ሕግስ፡ደግሞ፡ያን፡አይልምን፧የሚያበራየውን፡በሬ፡አፉን፡አትሰር፡ተብሎ፡በሙሴ፡ሕግ፡ተጽፏልና።እግዚአብ ሔርስ፡ስለ፡በሬዎች፡ይገደዋልን፧
10፤ይህን፡የሚለው፡ፈጽሞ፡ስለ፡እኛ፡አይደለምን፧የሚያርስ፡በተስፋ፡ሊያርስ፥የሚያበራይም፡እንዲካፈል፡በተ ስፋ፡ሊያበራይ፡ስለሚገ፟ባ፟ው፡በእውነት፡ስለ፡እኛ፡ተጽፏል።
11፤እኛ፡መንፈሳዊን፡ነገር፡የዘራንላችኹ፡ከኾን፟፡የእናንተን፡የሥጋዊን፡ነገር፡እኛ፡ብናጭድ፡ትልቅ፡ነገር ፡ነውን፧
12፤ሌላዎች፡በእናንተ፡ላይ፡ይህን፡መብት፡የሚካፈሉ፡ከኾኑ፥እኛማ፡ይልቁን፡እንዴታ፧ነገር፡ግን፡የክርስቶስ ን፡ወንጌል፡እንዳንከለክል፡በዅሉ፡እንታገሣለን፡እንጂ፡በዚህ፡መብት፡አልተጠቀምንም።
13፤በመቅደስ፡ነገር፡የሚያገለግሉ፡ከመቅደስ፡የኾነውን፡ነገርን፡እንዲመገቡ፥በመሠዊያውም፡የሚጸኑ፡ከመሠዊ ያው፡እንዲካፈሉ፡አታውቁምን፧
14፤እንዲሁ፡ደግሞ፡ወንጌልን፡የሚሰብኩ፡ከወንጌል፡ቀለብ፡እንዲቀበሉ፡ጌታ፡ደንግጓል።
15፤እኔ፡ግን፡ከነዚህ፡ዅሉ፡ምንም፡አልተጠቀምኹም።እንዲህ፡እንዲኾንልኝ፡ይህን፡አልጽፍም፤ማንም፡ትምክሕቴ ን፡ከንቱ፡ከሚያደርግብኝ፡ሞት፡ይሻለኛልና።
16፤ወንጌልን፡ብሰብክ፡እንኳ፡የምመካበት፡የለኝም፤ግድ፡ደርሶብኝ፡ነውና፤ወንጌልንም፡ባልሰብክ፡ወዮልኝ።
17፤ይህን፡በፈቃዴ፡ባደርገው፡ደመ፡ወዝ፡አለኝና፤ያለፈቃዴ፡ግን፡ባደርገው፡መጋቢነት፡በዐደራ፡ተሰጥቶኛል።
18፤እንግዲህ፡ደመ፡ወዜ፡ምንድር፡ነው፧ወንጌልን፡እየሰበክኹ፡በወንጌል፡ካለኝ፡መብት፡በሙሉ፡እንዳልጠቀም፡ ወንጌልን፡ያለዋጋ፡ብናገር፡ነው።
19፤ከሰው፡ዅሉ፡ሐራነት፡የወጣኹ፡ስኾን፡የሚበልጡትን፡እንድጠቅም፡እንደ፡ባሪያ፡ራሴን፡ለዅሉ፡አስገዛለኹ።
20፤አይሁድንም፡እጠቅም፡ዘንድ፡ከአይሁድ፡ጋራ፡እንደ፡አይሁዳዊ፡ኾንኹ፤ከሕግ፡በታች፡ያሉትን፡እጠቅም፡ዘን ድ፥እኔ፡ራሴ፡ከሕግ፡በታች፡ሳልኾን፥ከሕግ፡በታች፡ላሉት፡ከሕግ፡በታች፡እንዳለኹ፡ኾንኹ፤
21፤ሕግ፡የሌላቸውን፡እጠቅም፡ዘንድ፥ያለእግዚአብሔር፡ሕግ፡ሳልኖር፥ነገር፡ግን፥በክርስቶስ፡ሕግ፡በታች፡ሳ ለኹ፥ሕግ፡ለሌላቸው፡ሕግ፡እንደ፡ሌለኝ፡ኾንኹ፤
22፤ደካማዎችን፡እጠቅም፡ዘንድ፡ለደካማዎች፡እንደ፡ደካማ፡ኾንኹ፤በዅሉ፡መንገድ፡አንዳንዶችን፡አድን፡ዘንድ ፥ከዅሉ፡ጋራ፡በዅሉ፡ነገር፡እንደ፡እነርሱ፡ኾንኹ።
23፤በወንጌልም፡ማኅበረተኛ፡እኾን፡ዘንድ፡ስለ፡ወንጌል፡ዅሉን፡አደርጋለኹ።
24፤በእሽቅድምድም፡ስፍራ፡የሚሮጡት፥ዅሉ፡እንዲሮጡ፥ነገር፡ግን፥አንዱ፡ብቻ፡ዋጋውን፡እንዲቀበል፡አታውቁም ን፧እንዲሁም፡ታገኙ፡ዘንድ፡ሩጡ።
25፤የሚታገልም፡ዅሉ፡በነገር፡ዅሉ፡ሰውነቱን፡ይገዛል፤እነዚያም፡የሚጠፋውን፡አክሊል፡ሊያገኙ፡ነው፥እኛ፡ግ ን፡የማይጠፋውን።
26፤ስለዚህ፥እኔ፡ያለዐሳብ፡እንደሚሮጥ፡ዅሉ፥እንዲሁ፡አልሮጥም፤ነፋስን፡እንደሚጐስም፡ዅሉ፡እንዲሁ፡አልጋ ደልም፤
27፤ነገር፡ግን፥ለሌላዎች፡ከሰበክኹ፡በዃላ፡ራሴ፡የተጣልኹ፡እንዳልኾን፡ሥጋዬን፡እየጐሰምኹ፡አስገዛዋለኹ።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡10።______________
ምዕራፍ፡10፤
1፤ወንድሞች፡ሆይ፥ይህን፡ታውቁ፡ዘንድ፡እወዳለኹ።አባቶቻችን፡ዅሉ፡ከደመና፡በታች፡ነበሩ፥ዅሉም፡በባሕር፡መ ካከል፡ተሻገሩ፤
2፤ዅሉም፡ሙሴን፡ይተባበሩ፡ዘንድ፥በደመናና፡በባሕር፡ተጠመቁ፤
3፤ዅሉም፡ያን፡መንፈሳዊ፡መብል፡በሉ፥ዅሉም፡ያን፡መንፈሳዊ፡መጠጥ፡ጠጡ፤
4፤ይከተላቸው፡ከነበረው፡ከመንፈሳዊ፡አለት፡ጠጥተዋልና፥ያም፡አለት፡ክርስቶስ፡ነበረ።
5፤እግዚአብሔር፡ግን፡ከነርሱ፡በሚበዙት፡ደስ፡አላለውም፥በምድረ፡በዳ፡ወድቀዋልና።
6፤እነዚህም፡ክፉ፡ነገር፡እንደ፡ተመኙ፡እኛ፡ደግሞ፡እንዳንመኝ፥ይህ፡ምሳሌ፡ኾነልን።
7፤ሕዝብም፡ሊበሉ፡ሊጠጡም፡ተቀመጡ፥ሊዘፍኑም፡ተነሡ፥ተብሎ፡እንደ፡ተጻፈ፥ከነርሱ፡አንዳንዶቹ፡እንዳደረጉት ፡ጣዖትን፡የምታመልኩ፡አትኹኑ።
8፤ከነርሱም፡አንዳንዶቹ፡እንደ፡ሴሰኑ፥ባንድ፡ቀንም፡ኹለት፡እልፍ፡ከሦስት፡ሺሕ፡እንደ፡ወደቁ፡አንሴስን።
9፤ከነርሱም፡አንዳንዶቹ፡ጌታን፡እንደ፡ተፈታተኑት፥በእባቦቹም፡እንደ፡ጠፉ፥ጌታን፡አንፈታተን።
10፤ከነርሱም፡አንዳንዶቹ፡እንዳንጐራጐሩ፥በሚያጠፋውም፡እንደ፡ጠፉ፥አታንጐራጕሩ።
11፤ይህም፡ዅሉ፡እንደ፡ምሳሌ፡ኾነባቸው፥እኛንም፡የዘመናት፡መጨረሻ፡የደረሰብንን፡ሊገሥጸን፡ተጻፈ።
12፤ስለዚህ፥እንደ፡ቆመ፡የሚመስለው፡እንዳይወድቅ፥ይጠንቀቅ።
13፤ለሰው፡ዅሉ፡ከሚኾነው፡በቀር፡ምንም፡ፈተና፡አልደረሰባችኹም፤ነገር፡ግን፥ከሚቻላችኹ፡መጠን፡ይልቅ፡ትፈ ተኑ፡ዘንድ፡የማይፈቅድ፡እግዚአብሔር፡የታመነ፡ነው፥ትታገሡም፡ዘንድ፡እንድትችሉ፡ከፈተናው፡ጋራ፡መውጫውን ፡ደግሞ፡ያደርግላችዃል።
14፤ስለዚህ፥ወዳጆቼ፡ሆይ፥ጣዖትን፡ከማምለክ፡ሽሹ።
15፤ልባሞች፡እንደ፡መኾናችኹ፡እላለኹ፤በምለው፡ነገር፡እናንተ፡ፍረዱ።
16፤የምንባርከው፡የበረከት፡ጽዋ፡ከክርስቶስ፡ደም፡ጋራ፡ኅብረት፡ያለው፡አይደለምን፧የምንቈርሰውስ፡እንጀራ ፡ከክርስቶስ፡ሥጋ፡ጋራ፡ኅብረት፡ያለው፡አይደለምን፧
17፤አንድ፡እንጀራ፡ስለ፡ኾነ፥እኛ፡ብዙዎች፡ስንኾን፡አንድ፡ሥጋ፡ነን፤ዅላችን፡ያን፡አንዱን፡እንጀራ፡እንካ ፈላለንና።
18፤በሥጋ፡የኾነውን፡እስራኤል፡ተመልከቱ፤መሥዋዕቱን፡የሚበሉ፡የመሠዊያው፡ማኅበረተኛዎች፡አይደሉምን፧
19፤እንግዲህ፡ምን፡እላለኹ፧ለጣዖት፡የተሠዋ፡ምናምን፡ነው፡እላለኹን፧ወይስ፡ጣዖት፡ምናምን፡እንዲኾን፡እላ ለኹን፧
20፤አይደለም፤ነገር፡ግን፥አሕዛብ፡የሚሠዉት፡ለአጋንንት፡እንዲኾን፡እንጂ፡ለእግዚአብሔር፡እንዳይሠዉ፡እላ ለኹ፤ከአጋንንትም፡ጋራ፡ማኅበረተኛዎች፡እንድትኾኑ፡አልወድም።
21፤የጌታን፡ጽዋና፡የአጋንንትን፡ጽዋ፡ልትጠጡ፡አትችሉም፤ከጌታ፡ማእዱና፡ከአጋንንት፡ማእድ፡ልትካፈሉ፡አት ችሉም።
22፤ወይስ፡ጌታን፡እናስቀናውን፧እኛስ፡ከርሱ፡ይልቅ፡እንበረታለንን፧
23፤ዅሉ፡ተፈቅዶልኛል፥ዅሉ፡ግን፡የሚጠቅም፡አይደለም፤ዅሉ፡ተፈቅዶልኛል፥ነገር፡ግን፥ዅሉ፡የሚያንጽ፡አይደ ለም።
24፤እያንዳንዱ፡የባልንጀራውን፡ጥቅም፡እንጂ፡አንድ፡ስንኳ፡የራሱን፡ጥቅም፡አይፈልግ።
25፤በሥጋ፡ገበያ፡የሚሸጠውን፡ዅሉ፡ከኅሊና፡የተነሣ፡ሳትመራመሩ፡ብሉ፤
26፤ምድርና፡በርሷ፡የሞላባት፡ዅሉ፡የጌታ፡ነውና።
27፤ከማያምኑ፡ሰዎች፡አንዱም፡ቢጠራችኹ፡ልትኼዱም፡ብትወዱ፡ከኅሊና፡የተነሣ፡ሳትመራመሩ፡የሚያቀርቡላችኹን ፡ዅሉ፡ብሉ።
28፤ማንም፡ግን፦ይህ፡ለጣዖት፡የተሠዋ፡ነው፡ቢላችኹ፡ከዚያ፡ካስታወቃችኹና፡ከኅሊና፡የተነሣ፡አትብሉ፤
29፤ስለ፡ባልንጀራኽ፡ኅሊና፡እንጂ፡ስለ፡ገዛ፡ኅሊናኽ፡አልናገርም።ሐራነቴ፡በሌላ፡ሰው፡ኅሊና፡የሚፈረድ፡ኧ ረ፡ስለ፡ምንድር፡ነው፧
30፤እኔም፡በጸጋ፡ብበላ፥በነገሩ፡ስለማመሰግንበት፡ስለ፡ምን፡እሰደባለኹ፧
31፤እንግዲህ፡የምትበሉ፡ወይም፡የምትጠጡ፡ብትኾኑ፡ወይም፡ማናቸውን፡ነገር፡ብታደርጉ፡ዅሉን፡ለእግዚአብሔር ፡ክብር፡አድርጉት።
32-33፤እኔ፡ደግሞ፡ብዙዎቹ፡ይድኑ፡ዘንድ፡ለጥቅማቸው፡እንጂ፡የራሴን፡ጥቅም፡ሳልፈልግ፡በዅሉ፡ነገር፡ሰውን፡ ዅሉ፡ደስ፡እንደማሠኝ፥ለአይሁድም፡ለግሪክም፡ሰዎች፡ለእግዚአብሔር፡ቤተ፡ክርስቲያንም፡ማሰናከያ፡አትኹኑ።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡11።______________
ምዕራፍ፡11፤
1፤እኔ፡ክርስቶስን፡እንደምመስል፡እኔን፡ምሰሉ።
2፤ወንድሞች፡ሆይ፥በዅሉ፡ስለምታስቡኝና፡አሳልፌ፡እንደ፡ሰጠዃችኹ፡ወግን፡ፈጽማችኹ፡ስለ፡ያዛችኹ፡አመሰግና ችዃለኹ።
3፤ነገር፡ግን፥የወንድ፡ዅሉ፡ራስ፡ክርስቶስ፥የሴትም፡ራስ፡ወንድ፥የክርስቶስም፡ራስ፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ኾ ነ፡ልታውቁ፡እወዳለኹ።
4፤ራሱን፡ተከናንቦ፡የሚጸልይ፡ወይም፡ትንቢት፡የሚናገር፡ወንድ፡ዅሉ፡ራሱን፡ያዋርዳል።
5፤ራሷን፡ሳትሸፍን፡ግን፡የምትጸልይ፡ወይም፡ትንቢት፡የምትናገር፡ሴት፡ዅሉ፡ራሷን፡ታዋርዳለች፤እንደ፡ተላጨ ች፡ያኽል፡አንድ፡ነውና።
6፤ሴትም፡ራሷን፡ባትሸፍን፡ጠጕሯን፡ደግሞ፡ትቈረጥ፤ለሴት፡ግን፡ጠጕሯን፡መቈረጥ፡ወይም፡መላጨት፡የሚያሳፍር ፡ከኾነ፡ራሷን፡ትሸፍን።
7፤ወንድ፡የእግዚአብሔር፡ምሳሌና፡ክብር፡ስለ፡ኾነ፡ራሱን፡መከናነብ፡አይገ፟ባ፟ውም፤ሴት፡ግን፡የወንድ፡ክብ ር፡ናት።
8፤ሴት፡ከወንድ፡ናት፡እንጂ፡ወንድ፡ከሴት፡አይደለምና።
9፤ሴት፡ስለ፡ወንድ፡ተፈጠረች፡እንጂ፡ወንድ፡ስለ፡ሴት፡አልተፈጠረምና።
10፤ስለዚህ፥ሴት፥ከመላእክት፡የተነሣ፥በራሷ፡ሥልጣን፡ሊኖራት፡ይገ፟ባ፟ል።
11፤ነገር፡ግን፥በጌታ፡ዘንድ፡ሴት፡ያለወንድ፡ወንድም፡ያለሴት፡አይኾንም።
12፤ሴት፡ከወንድ፡እንደ፡ኾነች፡እንዲሁ፡ወንድ፡ደግሞ፡በሴት፡ነውና፤ዅሉም፡ከእግዚአብሔር፡ነው።
13፤በእናንተ፡በራሳችኹ፡መካከል፡ፍረዱ፤ሴት፡ራሷን፡ሳትሸፍን፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ልትጸልይ፡ይገ፟ባ፟ታልን ፧
14-15፤ወንድ፡ጠጕሩን፡ቢያስረዝም፡ነውር፡እንዲኾንበት፥ሴት፡ግን፡ጠጕሯን፡ብታስረዝም፡ክብር፡እንዲኾንላት፡ ተፈጥሮ፡እንኳ፡አያስተምራችኹምን፧ጠጕሯ፡መጐናጸፊያ፡ሊኾን፡ተሰጥቷታልና።
16፤ዳሩ፡ግን፡ማንም፡ሊከራከር፡ቢፈቅድ፥እኛ፡ወይም፡የእግዚአብሔር፡አብያተ፡ክርስቲያናት፡እንዲህ፡ያለ፡ል ማድ፡የለንም።
17፤ነገር፡ግን፥በምትሰበሰቡበት፡ጊዜ፡ለሚከፋ፡እንጂ፡ለሚሻል፡ስላልኾነ፡ይህን፡ትእዛዝ፡ስሰጥ፡የማመሰግና ችኹ፡አይደለም።
18፤በመዠመሪያ፡ወደ፡ማኅበር፡ስትሰበሰቡ፡በመካከላችኹ፡መለያየት፡እንዳለ፡እሰማለኹና፥ባንድ፡በኩልም፡አም ናለኹ።
19፤በእናንተ፡ዘንድ፡የተፈተኑት፡እንዲገለጡ፡በመካከላችኹ፡ወገኖች፡ደግሞ፡ሊኾኑ፡ግድ፡ነውና።
20፤እንግዲህ፡ዐብራችኹ፡ስትሰበሰቡ፡የምትበሉት፡የጌታ፡እራት፡አይደለም፤
21፤በመብላት፡ጊዜ፡እያንዳንዱ፡የራሱን፡እራት፡ይበላልና፥አንዱም፡ይራባል፡አንዱ፡ግን፡ይሰክራል።
22፤የምትበሉባቸውና፡የምትጠጡባቸው፡ቤቶች፡የላችኹምን፧ወይስ፡የእግዚአብሔርን፡ማኅበር፡ትንቃላችኹን፡አን ዳችም፡የሌላቸውን፡ታሳፍራላችኹን፧ምን፡ልበላችኹ፧በዚህ፡ነገር፡ላመስግናችኹን፧አላመሰግናችኹም።
23፤ለእናንተ፡ደግሞ፡አሳልፌ፡የሰጠኹትን፡እኔ፡ከጌታ፡ተቀብያለኹና፤
24፤ጌታ፡ኢየሱስ፡ዐልፎ፡በተሰጠበት፡በዚያች፡ሌሊት፡እንጀራን፡አንሥቶ፡አመሰገነ፥ቈርሶም፦እንካችኹ፡ብሉ፤ ይህ፡ስለ፡እናንተ፡የሚኾን፡ሥጋዬ፡ነው፤ይህን፡ለመታሰቢያዬ፡አድርጉት፡አለ።
25፤እንደዚሁም፡ከእራት፡በዃላ፡ጽዋውን፡ደግሞ፡አንሥቶ፦ይህ፡ጽዋ፡በደሜ፡የሚኾን፡ዐዲስ፡ኪዳን፡ነው፤በጠጣ ችኹት፡ጊዜ፡ዅሉ፡ይህን፡ለመታሰቢያዬ፡አድርጉት፡አለ።
26፤ይህን፡እንጀራ፡በበላችኹ፡ጊዜ፡ዅሉ፥ይህንም፡ጽዋ፡በጠጣችኹ፡ጊዜ፡ዅሉ፡ጌታ፡እስኪመጣ፡ድረስ፡ሞቱን፡ት ናገራላችኹና።
27፤ስለዚህ፥ሳይገ፟ባ፟ው፡ይህን፡እንጀራ፡የበላ፡ወይም፡የጌታን፡ጽዋ፡የጠጣ፡ዅሉ፥የጌታ፡ሥጋና፡ደም፡ዕዳ፡ አለበት።
28፤ሰው፡ግን፡ራሱን፡ይፈትን፥እንዲሁም፡ከእንጀራው፡ይብላ፡ከጽዋውም፡ይጠጣ፤
29፤ሳይገ፟ባ፟ው፡የሚበላና፡የሚጠጣ፡የጌታን፡ሥጋ፡ስለማይለይ፡ለራሱ፡ፍርድ፡ይበላልና፥ይጠጣልምና።
30፤ስለዚህ፥በእናንተ፡ዘንድ፡የደከሙና፡የታመሙ፡ብዙዎች፡አሉ፥ዐያሌዎችም፡አንቀላፍተዋል።
31፤ራሳችንን፡ብንመረምር፡ግን፡ባልተፈረደብንም፡ነበር፤
32፤ነገር፡ግን፥በተፈረደብን፡ጊዜ፡ከዓለም፡ጋራ፡እንዳንኰነን፡በጌታ፡እንገሠጻለን።
33፤ስለዚህ፥ወንድሞቼ፡ሆይ፥ለመብላት፡በተሰበሰባችኹ፡ጊዜ፡ርስ፡በርሳችኹ፡ተጠባበቁ።
34፤ማንም፡የራበው፡ቢኖር፡ለፍርድ፡እንዳትሰበሰቡ፡በቤቱ፡ይብላ።የቀረውንም፡ነገር፡በመጣኹ፡ጊዜ፡እደነግጋ ለኹ።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡12።______________
ምዕራፍ፡12፤
1፤ስለ፡መንፈሳዊ፡ነገርም፥ወንድሞች፡ሆይ፥ታውቁ፡ዘንድ፡እወዳለኹ።
2፤አሕዛብ፡ሳላችኹ፡በማናቸውም፡ጊዜ፡እንደምትመሩ፡ድምፅ፡ወደሌላቸው፡ወደ፡ጣዖታት፡እንደ፡ተወሰዳችኹ፡ታው ቃላችኹ።
3፤ስለዚህ፥ማንም፡በእግዚአብሔር፡መንፈስ፡ሲናገር፦ኢየሱስ፡የተረገመ፡ነው፡የሚል፡እንደሌለ፥በመንፈስ፡ቅዱ ስም፡ካልኾነ፡በቀር፦ኢየሱስ፡ጌታ፡ነው፡ሊል፡አንድ፡እንኳ፡እንዳይችል፡አስታውቃችዃለኹ።
4፤የጸጋም፡ስጦታ፡ልዩ፡ልዩ፡ነው፥መንፈስ፡ግን፡አንድ፡ነው፤
5፤አገልግሎትም፡ልዩ፡ልዩ፡ነው፥ጌታም፡አንድ፡ነው፤
6፤አሠራርም፡ልዩ፡ልዩ፡ነው፥ዅሉን፡በዅሉ፡የሚያደርግ፡እግዚአብሔር፡ግን፡አንድ፡ነው።
7፤ነገር፡ግን፥መንፈስ፡ቅዱስን፡መግለጥ፡ለያንዳንዱ፡ለጥቅም፡ይሰጠዋል።
8፤ለአንዱ፡ጥበብን፡መናገር፡በመንፈስ፡ይሰጠዋልና፥ለአንዱም፡በዚያው፡መንፈስ፡ዕውቀትን፡መናገር፡ይሰጠዋል ፥
9፤ለአንዱም፡በዚያው፡መንፈስ፡እምነት፥ለአንዱም፡በአንዱ፡መንፈስ፡የመፈወስ፡ስጦታ፥ለአንዱም፡ተኣምራትን፡ ማድረግ፥
10፤ለአንዱም፡ትንቢትን፡መናገር፥ለአንዱም፡መናፍስትን፡መለየት፥ለአንዱም፡በልዩ፡ዐይነት፡ልሳን፡መናገር፥ ለአንዱም፡በልሳኖች፡የተነገረውን፡መተርጐም፡ይሰጠዋል፤
11፤ይህን፡ዅሉ፡ግን፡ያ፡አንዱ፡መንፈስ፡እንደሚፈቅድ፡ለያንዳንዱ፡ለብቻው፡እያካፈለ፡ያደርጋል።
12፤አካልም፡አንድ፡እንደ፡ኾነ፡ብዙም፡ብልቶች፡እንዳሉበት፥ነገር፡ግን፥የአካል፡ብልቶች፡ዅሉ፡ብዙዎች፡ሳሉ ፡አንድ፡አካል፡እንደ፡ኾኑ፥ክርስቶስ፡ደግሞ፡እንዲሁ፡ነው፤
13፤አይሁድ፡ብንኾን፡የግሪክ፡ሰዎችም፡ብንኾን፡ባሪያዎችም፡ብንኾን፡ጨዋዎችም፡ብንኾን፡እኛ፡ዅላችን፡ባንድ ፡መንፈስ፡አንድ፡አካል፡እንድንኾን፡ተጠምቀናልና።ዅላችንም፡አንዱን፡መንፈስ፡ጠጥተናል።
14፤አካል፡ብዙ፡ብልቶች፡እንጂ፡አንድ፡ብልት፡አይደለምና።
15፤እግር፦እኔ፡እጅ፡አይደለኹምና፡የአካል፡ክፍል፡አይደለኹም፡ብትል፥ይህን፡በማለቷ፡የአካል፡ክፍል፡መኾኗ ፡ይቀራልን፧
16፤ዦሮም፦እኔ፡ዐይን፡አይደለኹምና፡የአካል፡ክፍል፡አይደለኹም፡ቢል፥ይህን፡በማለቱ፡የአካል፡ክፍል፡መኾኑ ፡ይቀራልን፧
17፤አካል፡ዅሉ፡ዐይን፡ቢኾን፡መስማት፡ወዴት፡በተገኘ፧ዅሉም፡መስማት፡ቢኾን፡ማሽተት፡ወዴት፡በተገኘ፧
18፤አኹን፡ግን፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ወደደ፡ብልቶችን፡እያንዳንዳቸው፡በአካል፡አድርጓል።
19፤ዅሉም፡አንድ፡ብልት፡ቢኾንስ፡አካል፡ወዴት፡በኾነ፧
20፤ዳሩ፡ግን፡አኹን፡ብልቶች፡ብዙዎች፡ናቸው፡አካል፡ግን፡አንድ፡ነው።
21፤ዐይን፡እጅን፦አታስፈልገኝም፡ልትለው፡አትችልም፥ወይም፡ራስ፡ደግሞ፡እግሮችን፦አታስፈልጉኝም፡ሊላቸው፡ አይችልም።
22፤ነገር፡ግን፥ደካማዎች፡የሚመስሉ፡የአካል፡ብልቶች፡ይልቁን፡የሚያስፈልጉ፡ናቸው፤
23፤ከአካልም፡ብልቶች፡ያልከበሩ፡ኾነው፡የሚመስሉን፡በሚበዛ፡ክብር፡እናለብሳቸዋለን፥በምናፍርባቸውም፡ብል ቶቻችን፡ክብር፡ይጨመርላቸዋል፤
24-25፤ክብር፡ያላቸው፡ብልቶቻችን፡ግን፡ይህ፡አያስፈልጋቸውም።ነገር፡ግን፥ብልቶች፡ርስ፡በርሳቸው፡በትክክል ፡ይተሳሰቡ፡ዘንድ፡እንጂ፡በአካል፡መለያየት፡እንዳይኾን፥ለጐደለው፡ብልት፡የሚበልጥ፡ክብር፡እየሰጠ፡እግዚ አብሔር፡አካልን፡አገጣጠመው።
26፤አንድም፡ብልት፡ቢሣቀይ፡ብልቶች፡ዅሉ፡ከርሱ፡ጋራ፡ይሣቀያሉ፤አንድ፡ብልትም፡ቢከበር፡ብልቶች፡ዅሉ፡ከር ሱ፡ጋራ፡ደስ፡ይላቸዋል።
27፤እናንተም፡የክርስቶስ፡አካል፡ናችኹ፡እያንዳንዳችኹም፡ብልቶች፡ናችኹ።
28፤እግዚአብሔርም፡በቤተ፡ክርስቲያን፡አንዳንዶቹን፡አስቀድሞ፡ሐዋርያትን፥ኹለተኛም፡ነቢያትን፥ሦስተኛም፡ አስተማሪዎችን፥ቀጥሎም፡ተኣምራት፡ማድረግን፥ቀጥሎም፡የመፈወስን፡ስጦታ፥ርዳታንም፥አገዛዝንም፥የልዩ፡ልዩ ፡ዐይነት፡ልሳኖችንም፡አድርጓል።
29፤ዅሉ፡ሐዋርያት፡ናቸውን፧ዅሉስ፡ነቢያት፡ናቸውን፧ዅሉስ፡አስተማሪዎች፡ናቸውን፧ዅሉስ፡ተኣምራትን፡ይሠራ ሉን፧
30፤ዅሉስ፡የመፈወስ፡ስጦታ፡አላቸውን፧ዅሉስ፡በልሳኖች፡ይናገራሉን፧ዅሉስ፡ይተረጕማሉን፧
31፤ነገር፡ግን፥የሚበልጠውን፡የጸጋ፡ስጦታ፡በብርቱ፡ፈልጉ።ደግሞም፡ከዅሉ፡የሚበልጥ፡መንገድ፡አሳያችዃለኹ ።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡13።______________
ምዕራፍ፡13፤
1፤በሰዎችና፡በመላእክት፡ልሳን፡ብናገር፡ፍቅር፡ግን፡ከሌለኝ፡እንደሚጮኽ፡ናስ፡ወይም፡እንደሚንሿሿ፡ጸናጽል ፡ኾኛለኹ።
2፤ትንቢትም፡ቢኖረኝ፡ምስጢርንም፡ዅሉና፡ዕውቀትን፡ዅሉ፡ባውቅ፥ተራራዎችንም፡እስካፈልስ፡ድረስ፡እምነት፡ዅ ሉ፡ቢኖረኝ፡ፍቅር፡ግን፡ከሌለኝ፡ከንቱ፡ነኝ።
3፤ድኻዎችንም፡ልመግብ፡ያለኝን፡ዅሉ፡ባካፍል፥ሥጋዬንም፡ለእሳት፡መቃጠል፡አሳልፌ፡ብሰጥ፥ፍቅር፡ግን፡ከሌለ ኝ፡ምንም፡አይጠቅመኝም።
4፤ፍቅር፡ይታገሣል፥ቸርነትንም፡ያደርጋል፤ፍቅር፡አይቀናም፤ፍቅር፡አይመካም፥አይታበይም፤
5፤የማይገ፟ባ፟ውን፡አያደርግም፥የራሱንም፡አይፈልግም፥አይበሳጭም፥በደልን፡አይቈጥርም፤
6፤ከእውነት፡ጋራ፡ደስ፡ይለዋል፡እንጂ፡ስለ፡ዐመፃ፡ደስ፡አይለውም፤
7፤ዅሉን፡ይታገሣል፥ዅሉን፡ያምናል፥ዅሉን፡ተስፋ፡ያደርጋል፥በዅሉ፡ይጸናል።
8፤ፍቅር፡ለዘወትር፡አይወድቅም፤ትንቢት፡ቢኾን፡ግን፡ይሻራል፤ልሳኖች፡ቢኾኑ፡ይቀራሉ፤ዕውቀትም፡ቢኾን፡ይሻ ራል።
9፤ከዕውቀት፡ከፍለን፡እናውቃለንና፥ከትንቢትም፡ከፍለን፡እንናገራለንና፤
10፤ፍጹም፡የኾነ፡ሲመጣ፡ግን፡ተከፍሎ፡የነበረው፡ይሻራል።
11፤ልጅ፡ሳለኹ፡እንደ፡ልጅ፡እናገር፡ነበር፥እንደ፡ልጅም፡ዐስብ፡ነበር፥እንደ፡ልጅም፡እቈጥር፡ነበር፤ጕልማ ሳ፡ኾኜ፡ግን፡የልጅነትን፡ጠባይ፡ሽሬያለኹ።
12፤ዛሬስ፡በመስተዋት፡በድንግዝግዝ፡እንደምናይ፡ነን፡በዚያን፡ጊዜ፡ግን፡ፊት፡ለፊት፡እናያለን፤ዛሬስ፡ከዕ ውቀት፡ከፍዬ፡ዐውቃለኹ፡በዚያን፡ጊዜ፡ግን፡እኔ፡ደግሞ፡እንደ፡ታወቅኹ፡ዐውቃለኹ።
13፤እንዲህም፡ከኾነ፥እምነት፡ተስፋ፡ፍቅር፡እነዚህ፡ሦስቱ፡ጸንተው፡ይኖራሉ፤ከነዚህም፡የሚበልጠው፡ፍቅር፡ ነው።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡14።______________
ምዕራፍ፡14፤
1፤ፍቅርን፡ተከታተሉ፥መንፈሳዊ፡ስጦታንም፡ይልቁንም፡ትንቢት፡መናገርን፡በብርቱ፡ፈልጉ።
2፤በልሳን፡የሚናገርስ፡ለእግዚአብሔር፡እንጂ፡ለሰው፡አይናገርም፤የሚያስተውለው፡የለምና፥በመንፈስ፡ግን፡ም ስጢርን፡ይናገራል፤
3፤ትንቢትን፡የሚናገር፡ግን፡ለማነጽና፡ለመምከር፡ለማጽናናትም፡ለሰው፡ይናገራል።
4፤በልሳን፡የሚናገር፡ራሱን፡ያንጻል፤ትንቢትን፡የሚናገር፡ግን፡ማኅበሩን፡ያንጻል።
5፤ዅላችኹ፡በልሳኖች፡ልትናገሩ፡እወድ፡ነበር፥ትንቢትን፡ልትናገሩ፡ግን፡ከዚህ፡ይልቅ፡እወዳለኹ፤ማኅበሩ፡ይ ታነጽ፡ዘንድ፡ንግግሩን፡ባይተረጐም፡በልሳኖች፡ከሚናገር፡ትንቢትን፡የሚናገር፡ይበልጣል።
6፤አኹን፡ግን፥ወንድሞች፡ሆይ፥ወደ፡እናንተ፡መጥቼ፡በልሳኖች፡ብናገር፥በመግለጥ፡ወይም፡በዕውቀት፡ወይም፡በ ትንቢት፡ወይም፡በትምህርት፡ካልነገርዃችኹ፡ምን፡እጠቅማችዃለኹ፧
7፤ነፍስ፡የሌለበት፡ነገር፡እንኳ፡ዋሽንትም፡ክራርም፡ቢኾን፡ድምፅ፡ሲሰጥ፡የድምፁን፡ልዩነት፡ባይገልጥ፡በዋ ሽንት፡የሚነፋው፡ወይስ፡በክራር፡የሚመታው፡መዝሙር፡እንዴት፡ይታወቃል፧
8፤ደግሞም፡መለከት፡የማይገለጥን፡ድምፅ፡ቢሰጥ፡ለጦርነት፡ማን፡ይዘጋጃል፧
9፤እንዲሁ፡እናንተ፡ደግሞ፡የተገለጠውን፡ቃል፡በአንደበት፡ባትናገሩ፡ሰዎች፡የምትናገሩትን፡እንዴት፡አድርገ ው፡ያስተውሉታል፧ለነፋስ፡የምትናገሩ፡ትኾናላችኹና።
10፤በዓለም፡ምናልባት፡ቍጥር፡የሌለው፡የቋንቋ፡ዐይነት፡ይኖራል፡ቋንቋም፡የሌለው፡ሕዝብ፡የለም፤
11፤እንግዲህ፡የቋንቋውን፡ፍች፡ባላውቅ፡ለሚናገረው፡እንግዳ፡እኾናለኹ፥የሚናገረውም፡ለእኔ፡እንግዳ፡ይኾና ል።
12፤እንዲሁ፡ደግሞ፡እናንተ፡መንፈሳዊ፡ስጦታን፡በብርቱ፡የምትፈልጉ፡ከኾናችኹ፡ቤተ፡ክርስቲያንን፡ለማነጽ፡ እንዲበዛላችኹ፡ፈልጉ።
13፤ስለዚህ፥በልሳን፡የሚናገር፡እንዲተረጕም፡ይጸልይ።
14፤በልሳን፡ብጸልይ፡መንፈሴ፡ይጸልያል፥አእምሮዬ፡ግን፡ያለፍሬ፡ነው።
15፤እንግዲህ፡ምንድር፡ነው፧በመንፈስ፡እጸልያለኹ፡በአእምሮም፡ደግሞ፡እጸልያለኹ፤በመንፈስ፡እዘምራለኹ፡በ አእምሮም፡ደግሞ፡እዘምራለኹ።
16፤እንዲያማ፡ካልኾነ፥አንተ፡በመንፈስ፡ብትባርክ፥ባልተማሩት፡ስፍራ፡የተቀመጠው፡የምትለውን፡ካላወቀ፥እን ዴት፡አድርጎ፡ለምስጋናኽ፡አሜን፡ይላል፧
17፤አንተማ፡መልካም፡ታመሰግናለኽ፥ሌላው፡ግን፡አይታነጽበትም።
18፤ከዅላችኹ፡ይልቅ፡በልሳኖች፡እናገራለኹና፡እግዚአብሔርን፡አመሰግናለኹ፤
19፤ነገር፡ግን፥ሌላዎችን፡ደግሞ፡አስተምር፡ዘንድ፡በማኅበር፡እልፍ፡ቃላት፡በልሳን፡ከመናገር፡ይልቅ፡ዐምስ ት፡ቃላት፡በአእምሮዬ፡ልናገር፡እወዳለኹ።
20፤ወንድሞች፡ሆይ፥በአእምሮ፡ሕፃናት፡አትኹኑ፤ለክፋት፡ነገር፡ሕፃናት፡ኹኑ፡እንጂ፡በአእምሮ፡የበሰሉ፡ኹኑ ።
21፤ሌላዎችን፡ልሳኖች፡በሚናገሩ፡ሰዎችና፡በሌላ፡አንደበት፡ለዚህ፡ሕዝብ፡እነግራቸዋለኹ፥እንዲህም፡ቢኾን፡ አይሰሙኝም፡ይላል፡ጌታ፡ተብሎ፡በሕግ፡ተጽፏል።
22፤እንግዲያስ፡በልሳኖች፡መናገር፡ለማያምኑ፡ምልክት፡ነው፡እንጂ፡ለሚያምኑ፡አይደለም፥ትንቢት፡ግን፡ለሚያ ምኑ፡እንጂ፡ለማያምኑ፡አይደለም።
23፤እንግዲህ፡ማኅበር፡ዅሉ፡ዐብረው፡ቢሰበሰቡ፡ዅሉም፡በልሳኖች፡ቢናገሩና፡ያልተማሩ፡ወይም፡የማያምኑ፡ሰዎ ች፡ቢገቡ።አብደዋል፡አይሉምን፧
24፤ዅሉ፡ትንቢት፡ቢናገሩ፡ግን፡የማያምን፡ወይም፡ያልተማረ፡ሰው፡ቢገባ፡በዅሉ፡ይወቀሳል፥በዅሉም፡ይመረመራ ል፤
25፤በልቡም፡የተሰወረ፡ይገለጣል፡እንዲሁም፦እግዚአብሔር፡በእውነት፡በመካከላቸው፡ነው፡ብሎ፡እየተናገረ፡በ ፊቱ፡ወድቆ፡ለእግዚአብሔር፡ይሰግዳል።
26፤እንግዲህ፥ወንድሞች፡ሆይ፥ምንድር፡ነው፧በምትሰበሰቡበት፡ጊዜ፡ለያንዳንዱ፡መዝሙር፡አለው፥ትምህርት፡አ ለው፥መግለጥ፡አለው፥በልሳን፡መናገር፡አለው፥መተርጐም፡አለው፤ዅሉ፡ለማነጽ፡ይኹን።
27፤በልሳን፡የሚናገር፡ቢኖር፥ኹለት፡ወይም፡ቢበዛ፡ሦስት፡ኾነው፡በተራቸው፡ይናገሩ፥አንዱም፡ይተርጕም፤
28፤የሚተረጕም፡ባይኖር፡ግን፥በማኅበር፡መካከል፡ዝም፡ይበልና፡ለራሱና፡ለእግዚአብሔር፡ይናገር።
29፤ነቢያትም፡ኹለት፡ወይም፡ሦስት፡ኾነው፡ይናገሩ፡ሌላዎችም፡ይለይዋቸው፤
30፤በዚያ፡ለሚቀመጥ፡ለሌላ፡ግን፡አንድ፡ነገር፡ቢገለጥለት፡ፊተኛው፡ዝም፡ይበል።
31፤ዅሉም፡እንዲማሩ፡ዅሉም፡እንዲመከሩ፡ዅላችኹ፡በያንዳንዳችኹ፡ትንቢት፡ልትናገሩ፡ትችላላችኹ።
32፤የነቢያትም፡መናፍስት፡ለነቢያት፡ይገዛሉ፤
33፤እግዚአብሔርስ፡የሰላም፡አምላክ፡ነው፡እንጂ፡የሁከት፡አምላክ፡አይደለምና፤በቅዱሳንም፡አብያተ፡ክርስቲ ያናት፡ዅሉ፡እንዲህ፡ነው።
34፤ሴቶች፡በማኅበር፡ዝም፡ይበሉ፤ሕግ፡ደግሞ፡እንደሚል፡እንዲገዙ፡እንጂ፡እንዲናገሩ፡አልተፈቀደላቸውምና።
35፤ለሴት፡በማኅበር፡መካከል፡መናገር፡ነውር፡ነውና፥ምንም፡ሊማሩ፡ቢወዱ፡በቤታቸው፡ባሎቻቸውን፡ይጠይቁ።
36፤ምን፡ነው፧የእግዚአብሔር፡ቃል፡የወጣ፡ከእናንተ፡ነውን፧ወይስ፡ወደ፡እናንተ፡ብቻ፡ደርሷልን፧
37፤ማንም፡ነቢይ፡ወይም፡መንፈሳዊ፡የኾነ፡ቢመስለው፡ይህች፡የጻፍኹላችኹ፡የጌታ፡ትእዛዝ፡እንደ፡ኾነች፡ይወ ቅ፤
38፤ማንም፡የማያውቅ፡ቢኖር፡ግን፡አይወቅ።
39፤ስለዚህ፥ወንድሞች፡ሆይ፥ትንቢት፡ለመናገር፡በብርቱ፡ፈልጉ፥በልሳኖች፡ከመናገርም፡አትከልክሉ፤
40፤ነገር፡ግን፥ዅሉ፡በአገባብና፡በሥርዐት፡ይኹን።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡15።______________
ምዕራፍ፡15፤
1፤ወንድሞች፡ሆይ፥የሰበክኹላችኹን፡ደግሞም፡የተቀበላችኹትን፡በርሱም፡ደግሞ፡የቆማችኹበትን፡በርሱም፡ደግሞ ፡የምትድኑበትን፡ወንጌል፡አሳስባችዃለኹ፤
2፤በከንቱ፡ካላመናችኹ፡በቀር፥ብታስቡት፥በምን፡ቃል፡እንደ፡ሰበክኹላችኹ፡አሳስባችዃለኹ።
3፤እኔ፡ደግሞ፡የተቀበልኹትን፡ከዅሉ፡በፊት፡አሳልፌ፡ሰጠዃችኹ፡እንዲህ፡ብዬ።መጽሐፍ፡እንደሚል፡ክርስቶስ፡ ስለ፡ኀጢአታችን፡ሞተ፥ተቀበረም፥
4፤መጽሐፍም፡እንደሚል፡በሦስተኛው፡ቀን፡ተነሣ፥
5፤ለኬፋም፡ታየ፡በዃላም፡ለዐሥራ፡ኹለቱ፤
6፤ከዚያም፡በዃላ፡ከዐምስት፡መቶ፡ለሚበዙ፡ወንድሞች፡ባንድ፡ጊዜ፡ታየ፤ከነርሱም፡የሚበዙቱ፡እስከ፡አኹን፡አ ሉ፡አንዳንዶች፡ግን፡አንቀላፍተዋል፤
7፤ከዚያም፡በዃላ፡ለያዕቆብ፡ዃላም፡ለሐዋርያት፡ዅሉ፡ታየ፤
8፤ከዅሉም፡በዃላ፡እንደ፡ጭንጋፍ፡ለምኾን፡ለእኔ፡ደግሞ፡ታየኝ።
9፤እኔ፡ከሐዋርያት፡ዅሉ፡የማንስ፡ነኝና፥የእግዚአብሔርን፡ቤተ፡ክርስቲያን፡ስላሳደድኹ፡ሐዋርያ፡ተብዬ፡ልጠ ራ፡የማይገ፟ባ፟ኝ፤
10፤ነገር፡ግን፥በእግዚአብሔር፡ጸጋ፡የኾንኹ፡እኔ፡ነኝ፤ለኔም፡የተሰጠኝ፡ጸጋው፡ከንቱ፡አልነበረም፡ከዅላቸ ው፡ይልቅ፡ግን፡ደከምኹ፥ዳሩ፡ግን፡ከእኔ፡ጋራ፡ያለው፡የእግዚአብሔር፡ጸጋ፡ነው፡እንጂ፡እኔ፡አይደለኹም።
11፤እንግዲህስ፡እኔ፡ብኾን፡እነርሱም፡ቢኾኑ፡እንዲሁ፡እንሰብካለን፡እንዲሁም፡አመናችኹ።
12፤ክርስቶስ፡ከሙታን፡እንደ፡ተነሣ፡የሚሰበክ፡ከኾነ፡ግን፡ከእናንተ፡አንዳንዶቹ፦ትንሣኤ፡ሙታን፡የለም፡እ ንዴት፡ይላሉ፧
13፤ትንሣኤ፡ሙታንስ፡ከሌለ፡ክርስቶስ፡አልተነሣማ፤
14፤ክርስቶስም፡ካልተነሣ፡እንግዲያስ፡ስብከታችን፡ከንቱ፡ነው፥እምነታችኹም፡ደግሞ፡ከንቱ፡ናት፤
15፤ደግሞም፦ክርስቶስን፡አስነሥቶታል፡ብለን፡በእግዚአብሔር፡ላይ፡ስለ፡መሰከርን፡ሐሰተኛዎች፡የእግዚአብሔ ር፡ምስክሮች፡ኾነን፡ተገኝተናል፤ሙታን፡ግን፡የማይነሡ፡ከኾነ፡ርሱን፡አላስነሣውም።
16፤ሙታን፡የማይነሡ፡ከኾነ፡ክርስቶስ፡አልተነሣማ፤
17፤ክርስቶስም፡ካልተነሣ፡እምነታችኹ፡ከንቱ፡ናት፤እስከ፡አኹን፡ድረስ፡በኀጢአታችኹ፡አላችኹ።
18፤እንግዲያስ፡በክርስቶስ፡ያንቀላፉት፡ደግሞ፡ጠፍተዋላ።
19፤በዚች፡ሕይወት፡ብቻ፡ክርስቶስን፡ተስፋ፡ያደረግን፡ከኾነ፥ከሰው፡ዅሉ፡ይልቅ፡ምስኪኖች፡ነን።
20፤አኹን፡ግን፡ክርስቶስ፡ላንቀላፉት፡በኵራት፡ኾኖ፡ከሙታን፡ተነሥቷል።
21፤ሞት፡በሰው፡በኩል፡ስለ፡መጣ፡ትንሣኤ፡ሙታን፡በሰው፡በኩል፡ኾኗልና።
22፤ዅሉ፡በአዳም፡እንደሚሞቱ፡እንዲሁ፡ዅሉ፡በክርስቶስ፡ደግሞ፡ሕያዋን፡ይኾናሉና።
23፤ነገር፡ግን፥እያንዳንዱ፡በራሱ፡ተራ፡ይኾናል፤ክርስቶስ፡እንደ፡በኵራት፡ነው፥በዃላም፡በመምጣቱ፡ለክርስ ቶስ፡የኾኑት፡ናቸው፤
24፤በዃላም፥መንግሥቱን፡ለእግዚአብሔር፡ለአባቱ፡አሳልፎ፡በሰጠ፡ጊዜ፡አለቅነትንም፡ዅሉና፡ሥልጣንን፡ዅሉ፡ ኀይልንም፡በሻረ፡ጊዜ፥ፍጻሜ፡ይኾናል።
25፤ጠላቶቹን፡ዅሉ፡ከእግሩ፡በታች፡እስኪያደርግ፡ድረስ፡ሊነግሥ፡ይገ፟ባ፟ዋልና።
26፤የዃለኛው፡ጠላት፡የሚሻረው፡ሞት፡ነው፤
27፤ዅሉን፡ከእግሩ፡በታች፡አስገዝቷልና።ነገር፡ግን፦ዅሉ፡ተገዝቷል፡ሲል፥ዅሉን፡ካስገዛለት፡በቀር፡መኾኑ፡ ግልጥ፡ነው።
28፤ዅሉ፡ከተገዛለት፡በዃላ፡ግን፡እግዚአብሔር፡ዅሉ፡በዅሉ፡ይኾን፡ዘንድ፡በዚያን፡ጊዜ፡ልጁ፡ራሱ፡ደግሞ፡ዅ ሉን፡ላስገዛለት፡ይገዛል።
29፤እንዲያማ፡ካልኾነ፥ስለ፡ሙታን፡የሚጠመቁ፡ምን፡ያደርጋሉ፧ሙታንስ፡ከቶ፡የማይነሡ፡ከኾነ፥ስለ፡እነርሱ፡ የሚጠመቁ፡ስለ፡ምንድር፡ነው፧
30፤እኛስ፡ዘወትር፡በሚያስፈራ፡ኑሮ፡የምንኖር፡ስለ፡ምንድር፡ነው፧
31፤በጌታችን፡በክርስቶስ፡ኢየሱስ፡ባለኝ፡በእናንተ፡ትምክሕት፡እየማልኹ፥ወንድሞች፡ሆይ፥ዕለት፡ዕለት፡እሞ ታለኹ።
32፤እንደ፡ሰው፡በኤፌሶን፡ከአውሬ፡ጋራ፡ከታገልኹ፥ሙታንስ፡የማይነሡ፡ከኾነ፥ምን፡ይጠቅመኛል፧ነገ፡እንሞታ ለንና፡እንብላና፡እንጠጣ።
33፤አትሳቱ፤ክፉ፡ባልንጀርነት፡መልካሙን፡ዐመል፡ያጠፋል።
34፤በጽድቅ፡ንቁ፡ኀጢአትንም፡አትሥሩ፤እግዚአብሔርን፡የማያውቁ፡አሉና፤አሳፍራችኹ፡ዘንድ፡ይህን፡እላለኹ።
35፤ነገር፡ግን፥ሰው፦ሙታን፡እንዴት፡ይነሣሉ፧በምንስ፡ዐይነት፡አካል፡ይመጣሉ፧የሚል፡ይኖር፡ይኾናል።
36፤አንተ፡ሞኝ፥አንተ፡የምትዘራው፡ካልሞተ፡ሕያው፡አይኾንም፤
37፤የምትዘራውም፥ስንዴ፡ቢኾን፡ከሌላም፡ዐይነት፡የአንዱ፡ቢኾን፥ቅንጣት፡ብቻ፡ነው፡እንጂ፡የምትዘራው፡የሚ ኾነውን፡አካል፡አይደለም፤
38፤እግዚአብሔር፡ግን፡እንደ፡ወደደ፡አካልን፡ይሰጠዋል፥ከዘሮችም፡ለያንዳንዱ፡የገዛ፡አካሉን፡ይሰጠዋል።
39፤ሥጋ፡ዅሉ፡አንድ፡አይደለም፥የሰው፡ሥጋ፡ግን፡አንድ፡ነው፥የእንስሳም፡ሥጋ፡ሌላ፡ነው፥የወፎችም፡ሥጋ፡ሌ ላ፡ነው፥የዓሣም፡ሥጋ፡ሌላ፡ነው።
40፤ደግሞ፡ሰማያዊ፡አካል፡አለ፥ምድራዊም፡አካል፡አለ፤ነገር፡ግን፥የሰማያዊ፡አካል፡ክብር፡ልዩ፡ነው፥የምድ ራዊም፡አካል፡ክብር፡ልዩ፡ነው።
41፤የፀሓይ፡ክብር፡አንድ፡ነው፥የጨረቃም፡ክብር፡ሌላ፡ነው፥የከዋክብትም፡ክብር፡ሌላ፡ነው፤በክብር፡አንዱ፡ ኮከብ፡ከሌላው፡ኮከብ፡ይለያልና።
42፤የሙታን፡ትንሣኤ፡ደግሞ፡እንዲሁ፡ነው።በመበስበስ፡ይዘራል፥ባለመበስበስ፡ይነሣል፤
43፤በውርደት፡ይዘራል፥በክብር፡ይነሣል፤በድካም፡ይዘራል፥በኀይል፡ይነሣል፤
44፤ፍጥረታዊ፡አካል፡ይዘራል፥መንፈሳዊ፡አካል፡ይነሣል።ፍጥረታዊ፡አካል፡ካለ፡መንፈሳዊ፡አካል፡ደግሞ፡አለ ።
45፤እንዲሁ፡ደግሞ፦ፊተኛው፡ሰው፡አዳም፡ሕያው፡ነፍስ፡ኾነ፡ተብሎ፡ተጽፏል፤ዃለኛው፡አዳም፡ሕይወትን፡የሚሰ ጥ፡መንፈስ፡ኾነ።
46፤ነገር፡ግን፥አስቀድሞ፡ፍጥረታዊው፡ቀጥሎም፡መንፈሳዊው፡ነው፡እንጂ፡መንፈሳዊው፡መዠመሪያ፡አይደለም።
47፤የፊተኛው፡ሰው፡ከመሬት፡መሬታዊ፡ነው፤ኹለተኛው፡ሰው፡ከሰማይ፡ነው።
48፤መሬታዊው፡እንደ፡ኾነ፡መሬታውያን፡የኾኑት፡ደግሞ፡እንዲሁ፡ናቸው፥ሰማያዊው፡እንደ፡ኾነ፡ሰማያውያን፡የ ኾኑት፡ደግሞ፡እንዲሁ፡ናቸው።
49፤የዚያንም፡የመሬታዊውን፡መልክ፡እንደ፡ለበስን፡የሰማያዊውን፡መልክ፡ደግሞ፡እንለብሳለን።
50፤ነገር፡ግን፥ወንድሞች፡ሆይ፥ይህን፡እላለኹ፦ሥጋና፡ደም፡የእግዚአብሔርን፡መንግሥት፡ሊወርሱ፡አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም፡የማይበሰብሰውን፡አይወርስም።
51-52፤እንሆ፥አንድ፡ምስጢር፡እነግራችዃለኹ፤ዅላችን፡አናንቀላፋም፤ነገር፡ግን፥የዃለኛው፡መለከት፡ሲነፋ፡ዅ ላችን፡በድንገት፡በቅጽበተ፡ዐይን፡እንለወጣለን፤መለከት፡ይነፋልና፥ሙታንም፡የማይበሰብሱ፡ኾነው፡ይነሣሉ፥ እኛም፡እንለወጣለን።
53፤ይህ፡የሚበሰብሰው፡የማይበሰብሰውን፡ሊለብስ፥ይህም፡የሚሞተው፡የማይሞተውን፡ሊለብስ፡ይገ፟ባ፟ዋልና።
54፤ዳሩ፡ግን፡ይህ፡የሚበሰብሰው፡የማይበሰብሰውን፡ሲለብስ፡ይህም፡የሚሞተው፡የማይሞተውን፡ሲለብስ፥በዚያን ፡ጊዜ፦ሞት፡ድል፡በመነሣት፡ተዋጠ፡ተብሎ፡የተጻፈው፡ቃል፡ይፈጸማል።
55፤ሞት፡ሆይ፥መውጊያኽ፡የት፡አለ፧ሲኦል፡ሆይ፥ድል፡መንሣትኽ፡የት፡አለ፧
56፤የሞት፡መውጊያ፡ኀጢአት፡ነው፥የኀጢአትም፡ኀይል፡ሕግ፡ነው፤
57፤ነገር፡ግን፥በጌታችን፡በኢየሱስ፡ክርስቶስ፡በኩል፡ድል፡መንሣትን፡ለሚሰጠን፡ለእግዚአብሔር፡ምስጋና፡ይ ኹን።
58፤ስለዚህ፥የተወደዳችኹ፡ወንድሞቼ፡ሆይ፥ድካማችኹ፡በጌታ፡ከንቱ፡እንዳይኾን፡ዐውቃችዃልና፥የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥የጌታም፡ሥራ፡ዅል፡ጊዜ፡የሚበዛላችኹ፡ኹኑ።
_______________1ኛ፡ቆሮንቶስ፥ምዕራፍ፡16።______________
ምዕራፍ፡16፤
1፤ለቅዱሳንም፡ገንዘብን፡ስለ፡ማዋጣት፥ለገላትያ፡አብያተ፡ክርስቲያናት፡እንደ፡ደነገግኹት፡እናንተ፡ደግሞ፡ እንዲሁ፡አድርጉ።
2፤እኔ፡ስመጣ፡ይህ፡የገንዘብ፡ማዋጣት፡ያን፡ጊዜ፡እንዳይኾን፥ከእናንተ፡እያንዳንዱ፡በየሳምንቱ፡በፊተኛው፡ ቀን፡እንደ፡ቀናው፡መጠን፡እያስቀረ፡በቤቱ፡ያስቀምጥ።
3፤ስመጣም፡ማናቸውም፡ቢኾኑ፡የታመኑ፡የሚመስሏችኹ፡ሰዎች፡ቸርነታችኹን፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ያደርሱ፡ዘንድ፡ደ ብዳቤ፡ሰጥቼ፡እልካቸዋለኹ፤
4፤እኔ፡ደግሞ፡ልኼድ፡የሚገ፟ባ፟ኝ፡ብኾን፡ከእኔ፡ጋራ፡ዐብረው፡ይኼዳሉ።
5፤በመቄዶንያም፡ሳልፍ፡ወደ፡እናንተ፡እመጣለኹ፤በመቄዶንያ፡አድርጌ፡ዐልፋለኹና፤
6፤እናንተም፡ወደምኼድበት፡ወደ፡ማናቸውም፡ስፍራ፡በጕዞዬ፡እንድትረዱኝ፡ምናልባት፡በእናንተ፡ዘንድ፡እቈይ፡ ወይም፡እከርም፡ይኾናል።
7፤አኹን፡እግረ፡መንገዴን፡ሳልፍ፡ልጐበኛችኹ፡አልወድምና፤ጌታ፡ቢፈቅደው፡የኾነውን፡ዘመን፡በእናንተ፡ዘንድ ፡ልሰነብት፡ተስፋ፡አደርጋለኹና።
8፤በኤፌሶን፡ግን፡እስከ፡በዓለ፡ኀምሳ፡ድረስ፡እሰነብታለኹ።
9፤ሥራ፡የሞላበት፡ትልቅ፡በር፡ተከፍቶልኛልና፥ተቃዋሚዎችም፡ብዙ፡ናቸው።
10፤ጢሞቴዎስም፡የመጣ፡እንደ፡ኾነ፡በእናንተ፡ዘንድ፡ያለፍርሀት፡እንዲኖር፡ተጠንቀቁ፤እንደ፡እኔ፡ደግሞ፡የ ጌታን፡ሥራ፡ይሠራልና፤እንግዲህ፡ማንም፡አይናቀው።
11፤ነገር፡ግን፥ከወንድሞቹ፡ጋራ፡እጠብቀዋለኹና፥ወደ፡እኔ፡ይመጣ፡ዘንድ፡በሰላም፡በጕዞው፡ርዱት።
12፤ስለ፡ወንድማችን፡ስለ፡አጵሎስ፡ግን፡ከወንድሞቹ፡ጋራ፡ወደ፡እናንተ፡ሊኼድ፡እጅግ፡አድርጌ፡ለምኜው፡ነበ ር፤ዛሬም፡ለመምጣት፡ከቶ፡ፈቃድ፡አልነበረውም፥ሲመቸው፡ግን፡ይመጣል።
13፤ንቁ፥በሃይማኖት፡ቁሙ፥ጐልምሱ፥ጠንክሩ።
14፤በእናንተ፡ዘንድ፡ዅሉ፡በፍቅር፡ይኹን።
15፤ወንድሞች፡ሆይ፥የእስጢፋኖስ፡ቤተ፡ሰዎች፡የአካይያ፡በኵራት፡እንደ፡ኾኑ፡ቅዱሳንንም፡ለማገልገል፡ራሳቸ ውን፡እንደ፡ሰጡ፡ታውቃላችኹ፤
16፤እንደ፡እነርሱ፡ላሉትና፡ዐብሮ፡ለሚሠራ፡ለሚደክምም፡ዅሉ፡እናንተም፡እንድትገዙ፡እለምናችዃለኹ።
17፤በእስጢፋኖስና፡በፈርዶናጥስ፡በአካይቆስም፡መምጣት፡ደስ፡ይለኛል፥እናንተ፡ስለሌላችኹ፡የጐደለኝን፡ፈጽ መዋልና፤መንፈሴንና፡መንፈሳችኹን፡አሳርፈዋልና።
18፤እንግዲህ፡እንደነዚህ፡ያሉትን፡ዕወቋቸው።
19፤የእስያ፡አብያተ፡ክርስቲያናት፡ሰላምታ፡ያቀርቡላችዃል።አቂላና፡ጵርስቅላ፡በቤታቸው፡ካለች፡ቤተ፡ክርስ ቲያን፡ጋራ፡በጌታ፡እጅግ፡ሰላምታ፡ያቀርቡላችዃል።
20፤ወንድሞች፡ዅሉ፡ሰላምታ፡ያቀርቡላችዃል።በተቀደሰ፡አሳሳም፡ርስ፡በርሳችኹ፡ሰላምታ፡ተሰጣጡ።
21፤እኔ፡ጳውሎስ፡ይህን፡ሰላምታ፡በገዛ፡እጄ፡ጽፌያለኹ።
22፤ጌታን፡ኢየሱስ፡ክርስቶስን፡የማይወድ፡ቢኖር፡የተረገመ፡ይኹን።ጌታችን፡ሆይ፥ና።
23፤የጌታ፡የኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ጸጋ፡ከእናንተ፡ጋራ፡ይኹን።
24፤ፍቅሬ፡በክርስቶስ፡ኢየሱስ፡ከዅላችኹ፡ጋራ፡ነው።አሜን፨

http://www.gzamargna.net