የያዕቆብ፡ወንድም፡የይሁዳ፡መልእክት።

(ክለሳ.1.20020507)

_______________የይሁዳ፡መልእክት፥ምዕራፍ፡1።______________
ምዕራፍ፡1
1፤የኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ባሪያ፡የያዕቆብም፡ወንድም፡የኾነ፡ይሁዳ፥በእግዚአብሔር፡አብ፡ተወደ፟ው፡ለኢየሱስ፡ ክርስቶስም፡ተጠብቀው፡ለተጠሩ፤
2፤ምሕረትና፡ሰላም፡ፍቅርም፡ይብዛላችኹ።
3፤ወዳጆች፡ሆይ፥ስለምንካፈለው፡ስለ፡መዳናችን፡ልጽፍላችኹ፡እጅግ፡ተግቼ፡ሳለኹ፥ለቅዱሳን፡አንድ፡ጊዜ፡ፈጽ ሞ፡ስለተሰጠ፡ሃይማኖት፡እንድትጋደሉ፡እየመከርዃችኹ፡እጽፍላችኹ፡ዘንድ፡ግድ፡ኾነብኝ።
4፤ከብዙ፡ጊዜ፡በፊት፡ለዚህ፡ፍርድ፡የተጻፉ፡አንዳንዶች፡ሰዎች፡ሾልከው፡ገብተዋልና፤ኀጢአተኛዎች፡ኾነው፡የ አምላካችንን፡ጸጋ፡በሴሰኝነት፡ይለውጣሉ፡ንጉሣችንንና፡ጌታችንንም፡ብቻውን፡ያለውን፡ኢየሱስ፡ክርስቶስን፡ ይክዳሉ።
5፤ዳሩ፡ግን፡ዅሉን፡አንድ፡ጊዜ፡ፈጽሞ፡ምንም፡የተማራችኹ፡ብትኾኑ፡ጌታ፡ከግብጽ፡አገር፡ሕዝቡን፡አድኖ፡የማ ያምኑትን፡በዃላ፡እንዳጠፋቸው፡ላሳስባችኹ፡እወዳ፟ለኹ።
6፤መኖሪያቸውንም፡የተዉትን፡እንጂ፡የራሳቸውን፡አለቅነት፡ያልጠበቁትን፡መላእክት፡በዘለዓለም፡እስራት፡ከጨ ለማ፡በታች፡እስከታላቁ፡ቀን፡ፍርድ፡ድረስ፡ጠብቋቸዋል።
7፤እንዲሁም፡እንደ፡እነርሱ፡ዝሙትን፡ያደረጉና፡ሌላን፡ሥጋ፡የተከተሉ፡ሰዶምና፡ገሞራ፡በዙሪያቸውም፡የነበሩ ፡ከተማዎች፡በዘለዓለም፡እሳት፡እየተቀጡ፡ምሳሌ፡ኾነዋል።
8፤እንዲሁም፡እነዚህ፡ሰዎች፡ደግሞ፡እያለሙ፡ሥጋቸውን፡ያረክሳሉ፡ጌትነትንም፡ይጥላሉ፡ሥልጣን፡ያላቸውንም፡ ይሳደባሉ።
9፤የመላእክት፡አለቃ፡ሚካኤል፡ግን፡ከዲያብሎስ፡ጋራ፡በተከራከረ፡ጊዜ፡ስለሙሴ፡ሥጋ፡ሲነጋገር፦ጌታ፡ይገሥጽ ኽ፡አለው፡እንጂ፡የስድብን፡ፍርድ፡ሊናገረው፡አልደፈረም።
10፤እነዚህ፡ግን፡የማያውቁትን፡ዅሉ፡ይሳደባሉ፥አእምሮም፡እንደሌላቸው፡እንስሳዎች፡በፍጥረታቸው፡በሚያውቁ ት፡ዅሉ፡በርሱ፡ይጠፋሉ።
11፤ወዮላቸው፥በቃየል፡መንገድ፡ኼደዋልና፥ስለ፡ደመ፡ወዝም፡ለበለዓም፡ስሕተት፡ራሳቸውን፡አሳልፈው፡ሰጥተዋ ል፥በቆሬም፡መቃወም፡ጠፍተዋል።
12፤እነዚህ፡ከእናንተ፡ጋራ፡ሲጋበዙ፡በፍቅር፡ግብዣችኹ፡እንደ፡እድፍ፡ናቸው፤እንደ፡እረኛዎች፡ያለፍርሀት፡ ራሳቸውን፡ይጠብቃሉ፤በነፋስ፡የተወሰዱ፡ውሃ፡የሌለባቸው፡ደመናዎች፥ፍሬ፡የማያፈሩ፡ኹለት፡ጊዜ፡የሞቱ፡ከነ ሥራቸው፡የተነቀሉ፡በበጋ፡የደረቁ፡ዛፎች፥
13፤የገዛ፡ነውራቸውን፡ዐረፋ፡እየደፈቁ፡ጨካኝ፡የባሕር፡ማዕበል፥ድቅድቅ፡ጨለማ፡ለዘለዓለም፡የተጠበቀላቸው ፡የሚንከራተቱ፡ከዋክብት፡ናቸው።
14-15፤ከአዳም፡ዠምሮ፡ሰባተኛ፡የኾነ፡ሔኖክ፦እንሆ፥ጌታ፡በዅሉ፡ላይ፡እንዲፈርድ፥በኀጢአተኝነትም፡ስላደረጉ ት፡ስለ፡ኀጢአተኛ፡ሥራቸው፡ዅሉ፡ዐመፀኛዎችም፡ኀጢአተኛዎች፡በርሱ፡ላይ፡ስለ፡ተናገሩ፡ስለጭከና፡ነገር፡ዅ ሉ፡ኀጢአተኛዎችን፡ዅሉ፡እንዲወቅስ፡ከአእላፋት፡ቅዱሳኑ፡ጋራ፡መጥቷል፡ብሎ፡ለእነዚህ፡ደግሞ፡ትንቢት፡ተና ገረ።
16፤እነዚህ፡እንደ፡ምኞታቸው፡እየኼዱ፡የሚያንጐራጕሩና፡ስለ፡ዕድላቸው፡የሚያጕረመርሙ፡ናቸው፥እንዲረባቸው ም፡ለሰው፡ፊት፡እያደሉ፥አፋቸው፡ከመጠን፡ይልቅ፡ታላቅ፡ቃል፡ይናገራል።
17፤እናንተ፡ግን፥ወዳጆች፡ሆይ፥በጌታችን፡በኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ሐዋርያት፡ቀድሞ፡የተነገረውን፡ቃል፡ዐስቡ፤
18፤እነርሱ፦በመጨረሻው፡ዘመን፡በኀጢአተኝነት፡እንደ፡ገዛ፡ምኞታቸው፡እየኼዱ፡ዘባቾች፡ይኾናሉ፡ብለዋችዃል ና።
19፤እነዚህ፡የሚያለያዩ፡ሥጋውያንም፡የኾኑ፡መንፈስም፡የሌላቸው፡ሰዎች፡ናቸው።
20፤እናንተ፡ግን፥ወዳጆች፡ሆይ፥ከዅሉ፡ይልቅ፡በተቀደሰ፡ሃይማኖታችኹ፡ራሳችኹን፡ለማነጽ፡እየተጋችኹ፡በመን ፈስ፡ቅዱስም፡እየጸለያችኹ፥
21፤ወደዘለዓለም፡ሕይወት፡የሚወስደውን፡የጌታችንን፡የኢየሱስ፡ክርስቶስን፡ምሕረት፡ስትጠባበቁ፡በእግዚአብ ሔር፡ፍቅር፡ራሳችኹን፡ጠብቁ።
22፤አንዳንዶች፡ተከራካሪዎችንም፡ውቀሱ፥አንዳንዶችንም፡ከእሳት፡ነጥቃችኹ፡አድኑ፥
23፤አንዳንዶችንም፡በሥጋ፡የረከሰውን፡ልብስ፡እንኳ፡እየጠላችኹ፡በፍርሀት፡ማሩ።
24፤ሳትሰናከሉም፡እንዲጠብቃችኹ፥በክብሩም፡ፊት፡በደስታ፡ነውር፡የሌላችኹ፡አድርጎ፡እንዲያቆማችኹ፡ለሚችለ ው፡
25፤ብቻውን፡ለኾነ፡አምላክና፡መድኀኒታችን፡ከዘመን፡ዅሉ፡በፊት፡አኹንም፡እስከ፡ዘለዓለምም፡ድረስ፡በጌታች ን፡በኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ክብርና፡ግርማ፡ኀይልም፡ሥልጣንም፡ይኹን፤አሜን፨

http://www.gzamargna.net