|
መርስዔ፡ሐዘን፡ወልደ፡ቂርቆስ፡(ብላታ)
•••
("ያማርኛ፡ሰዋስው"፥አርቲስቲክ፡ማተሚያ፡ቤት፥ዐዲስ፡አበባ፥፲፱፻፵፰፡ዓ.፡ም፥ገጽ፡221።)
•••
ምሳሌ፡(ተረት)
ባማርኛ፥ከቀድሞ፡ዠምሮ፥ከአበው፡ሲያያዝ፡የመጣ፡ብዙ፡የምሳሌ፡ንግግር፡አለ።ሽማግሌዎቻ ችን፡'እከሥት፡በምሳሌ፡አፉየ'፡ያለውን፡ሲገልጡ፥'ነገር፡በምሳሌ፤ጠጅ፡በብርሌ'፡ብለው፡ይ ተርታሉ።በግብሩ፡'ምሳሌ'፡ይባላል፤በጥንታዊነቱም፡'ተረት'፡ይባላል።በርሱም፥ሕግና፡ምክር ፥ሌላም፡ልዩ፡ልዩ፡ዐይነት፡ትምህርት፡ይገኝበታል።የሕግ፡ትምህርት፡ከመኾኑ፡የተነሣ፥በ ዱሮ፡ዘመን፥ጨዋው፡ሲተችና፡ሲፈርድ፥ለነገሩ፡የሚስማማውን፡አንዳንድ፡ምሳሌ፡እየጨመረ፡ ይናገር፡ነበር።ይኸውም፥አንቀጽ፡ጠቅሶ፡እንደ፡መፍረድ፡መኾኑ፡ይመስላል።
ለፍርድ፡ጕዳይ፡ሲጠቀሱ፡ከነበሩት፡ምሳሌዎች፡አብዛኞቹ፡ከፍርድ፡መጻሕፍት፡ጋራ፡በምስጢ ር፡የተባበሩና፡የተስማሙ፡ናቸው።እንሆ፥ስለ፡ሕግ፡ከሚጠቀሱት፡ምሳሌዎች፡ጥቂቶቹን፡በሚ ከተለው፡ጽፈን፡እናሳያለን።
፩) ሺ፡በመከር፥አንድ፡በወረወር።[ሺ፡በመከረ፥አንድ፡በወረወረ።]
፪) ካያያዝ፡ይቀደዳል፤ካነጋገር፡ይፈረዳል።
፫) ባንድ፡ራስ፡ኹለት፡ምላስ።
፬) ባፍ፡ይጠፉ፥በለፈለፉ።
፭) ሳይገድሉ፡ጐፈሬ፤ሳይስረግጡ፡ወሬ።
፮) ዓሣ፡ጐርጓሪ፡ዘንዶ፡ያወጣል፤የሰው፡ፈላጊ፡የራሱን፡ያጣል።
፯) ለወሬ፡የለው፡ፍሬ፤ላበባ፡የለው፡ገለባ።
፰) ደባ፡ራሱን፤ስለት፡ድጕሱን።
፱) ተልጅ፡አትጫወት፤የወጋኻል፡በንጨት።
፲) ተዋጊ፡በሬኽን፥ተናካሽ፡ውሻኽን፡(ያዝ)።
፲፩) አንድ፡አይነድ፤አንድ፡አይፈርድ።
፲፪) ባፈሳ፡ይታፈሳል፤በነጠር፡ይመለሳል።
፲፫) ያባት፡ዕዳ፡ለልጅ፤ያፍንጫ፡እድፍ፡ለእጅ።
፲፬) ከኑግ፡የተገኘኽ፡ሰሊጥ፥ዐብረኽ፡ተወቀጥ።
፲፭) የሌባ፡ዋሻ፤የቀማኛ፡መሸሻ።
፲፮) የሰው፡በልቶ፥አያድሩም፡ተኝቶ።
፲፯) እንደ፡ልጅ፡በቀለበት፤እንደ፡ድመት፡በወተት።
፲፰) እካስ፡ያለ፡ታግሦ፤እጸድቅ፡ያለ፡መንኵሶ።
፲፱) ዳኛ፡ይመረምራል፤ጣዝማ፡ይሰረስራል።
፳) ተመመርመር፡ይገኛል፡ነገር።
፳፩) ተአፍ፡ከወጣ፡አፋፍ።
፳፪) ውሻ፡በበላበት፡ይጮኻል።
፳፫) ዋቢ፡ያለው፡ያመልጣል፤ዋቢ፡የሌለው፡ይሰጥማል።
፳፬) የግፍ፡ግፍ፥በዕንቅርት፡ላይ፡ዦሮ፡ገድፍ።
፳፭) ሥራ፡ለሠሪው፥ሾኽ፡ላጣሪው።
፳፮) ከተዘጋ፡ቤቴ፤ከተዳፈነ፡እሳቴ።
፳፯) ለንጉሥ፡ያልረዳ፤ከባሕር፡ያልቀዳ።
፳፰) አያገባው፡ገብቶ፤አያወዛው፡ተቀብቶ።
፳፱) አልሞት፡ባይ፡ተጋዳይ፡
፴) የሞተ፡አይከሰስ፤የፈሰሰ፡አይታፈስ።
፴፩) የበላ፡ዳኛ፤የወጋ፡መጋኛ።
፴፪) ያልጠረጠረ፡ተመነጠረ።
፴፫) አለውድ፥በግድ።
፴፬) ንጉሥ፡አይከሰስ፤ሰማይ፡አይታረስ።
|