|
መርስዔ፡ሐዘን፡ወልደ፡ቂርቆስ፡(ብላታ)
•••
("ያማርኛ፡ሰዋስው"፥አርቲስቲክ፡ማተሚያ፡ቤት፥ዐዲስ፡አበባ፥፲፱፻፵፰፡ዓ.፡ም፥ገጽ፡215።)
•••
ሠምና፡ወርቅ።
ያማርኛ፡መዝሙር፥እንደ፡ግእዙ፡ቅኔ፥በሠምና፡በወርቅ፣በኅብርና፡በአንጻር፣...፡ይነገራል።ከዚህም፡የተነሣ፥'ያማርኛ፡ቅኔ'፡ተብሎ፡ይጠራል።የየስሞቹን፡ትርጓሜ፡በሚከተለ ው፡እናሳያለን።
ሠም፡ማለት፥ለወርቁ፡አምሳል፣መርገፍ፡ኾኖ፡የሚነገር፡ቃል፡ነው።
ወርቅ፡ማለት፥ቅኔው፡የሚደርስለት፡ዋናው፡ዐሳብ፡ነው።
ሠም፡ለበስ፡ማለት፥የቅኔው፡ዋና፡ዐሳብ፡(ወርቁ)፡ሳይገለጽ፥ምስጢሩ፡በሠሙ፡ብቻ፡የሚታወቀው፡ነው።
ወርቃ፡ወርቅ፡ማለት፥ቅኔው፥ያለምንም፡ምሳሌ፥በግልጽ፡የሚነገር፡ነው።
ኅብር፡የሚባለው፥አንዱ፡ቃል፡ሠሙንም፡ወርቁንም፡የሚያስተባብር፡ሲኾን፡ነው።
አንጻር፡የሚባለው፥ለምስጢሩ፡ተነጻጻሪ፡የሚኾን፡ሌላ፡ቃል፡የሚጠቀስለትና፡ምሳሌ፡ኾኖ፡የሚ ነገርለት፡ነው።
አፍራሽ፡የሚባለው፥አስቀድሞ፡የተነገረውን፡ዐሳብ፡ተከታዩ፡የሚለውጠው፡ሲኾን፡ነው።
ውስጠ፡ወይራ፡የሚባለው፥ኀይለ፡ቃሉ፡በሠሙ፡ተሰውሮ፡ለኅሊና፡የሚሰማ፡ሲኾን፡ነው።
የቅኔ፡መንገድ፡ከነዚህም፡ሌላ፥ልዩ፡ልዩ፡ስልቶች፡አሉት።ዳሩ፡ግን፥ውሳኔን፡ማብዛት፡ተማሪ ን፡ማታከት፡ይኾናልና፥እነዚህ፡ይበቃሉ፡ብለን፡እናቆማለን።እነርሱም፥ርስ፡በራሳቸው፥እየተ ዛመዱ፡ሲገቡ፡ይገኛሉ።ይልቁንም፥ኅብርና፡ውስጠ፡ወይራ፡ከዅሉ፡ይገኛሉ።
እንሆ፥ዅሉንም፡በሚከተሉት፡ማስረጃዎች፡እናሳያለን።
1፤ሠምና፡ወርቅ፥ያማርኛ፡ቅኔ።
(ሀ)
ወላድ፡ኢትዮጵያ፡/፡ለልጆቿ፡ብላ፥
እጅግ፡ሳይጥሩባት፥/፡ሳይዘሯት፡አብቅላ፥
ስንዴውን፡ጠብቃ፥/፡እንክርዳዱን፡ነቅላ፥
ስትመግበን፡አየን፡/፡በፀሓይ፡አብስላ።
ምሳሌ፡ዘር፡ሀገራችን፥
ንጹሕ፡ዝናም፡መንግሥታችን።(አዝማች)
(ዮፍታሔ፡ንጉሤ።)
(ለ)
ልጅነት፡የያዘው፡/፡ምላሳችን፡መንካ፥
ከቋንቋችን፡በፊት፡/፡ሌላ፡ቋንቋ፡አይንካ፤
ግእዝ፡ካማርኛ፡/፡አስተባብሮ፡ሲያውቅ፥
ከውጭ፡አገር፡ቋንቋ፡/፡ያን፡ጊዜ፡ይንጠቅ።
(አ.፡ኪዳነ፡ወልድ፡ክፍሌ።)
2፤ሠም፡ለበስ፡ያማርኛ፡ቅኔ፤
(ሀ)
ሰፌድና፡ወንፊት፡/፡እያለ፡በጃችን፥
ያልተነፋ፡ዱቄት፡/፡ምነው፡ማቡካታችን፧
(አ.፡ኪዳነ፡ወልድ፡ክፍሌ።)
(ለ)
ያ፡ማዶ፡ተራራ፡/፡ረዥም፡ነው፡በጣም፤
በከብት፡ነው፡እንጂ፡/፡በእግር፡አያስወጣም።
ያ፡ልጅ፡ተራራውን፡/፡ሊወጣ፡ያስባል፤
ዐዋቂ፡ሲያቅተው፡/፡ድኾ፡እንዴት፡ይዘልቃል።
(ማኅተመ፡ወርቅ፡እሸቴ።)
3፤ሠም፡ለበስ፡ውስጠ፡ወይራ።
(ሀ)
ተስቦ፡ገብቷል፡/፡ከቤታችን፤
መቼ፡ይወጣል፡/፡በሽታችን፧
(ዮፍታሔ፡ንጉሤ፥፲፱፻፴፫፡ዓ.ም.።)
(ለ)
እምቢልታ፡መለከት፡/፡የሚሰማው፡የት፡ነው፧
አንዱም፡በስርቆሽ፡በር፥/፡አንዱም፡በግቢ፡ነው።
(ማኅተመ፡ወርቅ፡እሸቴ፥፲፱፻፳፯፡ዓ.ም.።)
(ሐ)
(ጥያቄ)
ሰንበቴያችን፡ደርሶ፥/፡ድግስ፡አለብን፤
እንድትረጂኝ፡ይኹን፡/፡እኽል፡ቅመሙን።
(ምላሽ)
እሺ፥ምን፡ቸገረኝ፥/፡ያለኝ፡ጕልበቴን፤
ለምለም፡ወጥቤታችን፡/፡ታውቃለች፡ምጥን፤
እኛ፡ነጭ፡አዝሙዱን፡/፡እንችላለን፤
አንተ፡ጥቍር፡ቅመም፡/፡አበሱዳን፡ኹን።
(ዮፍታሔ፡ንጉሤ፥፲፱፻፳፩፡ዓ.ም.።)
4፤ወርቃ፡ወርቅ፡ያማርኛ፡ቅኔ።
(ሀ)
ዐጥንቱን፡ልልቀመው፡/፡መቃብር፡ቈፍሬ፤
ጎበናን፡ከሸዋ፥/አሉላን፡ተትግሬ፤
ስመኝ፡ዐድሬያለኹ፡/ትናንትና፡ዛሬ፥
አሉላን፡ለጥይት፥/፡ጎበናን፡ለጭሬ።
ተሰበሰቡና፡/፡ተማማሉ፡ማላ፤
አሉላ፡ተትግሬ፥/፡ጎበና፡ተጋላ።
ጎበና፡ሴት፡ልጁን፡/፡ሊያስተምር፡ፈረስ፤
አሉላ፡ሴት፡ልጁን፡/፡ጥይት፡ሊያስተኵስ።
አገሬ፡ተባብራ፡/፡ታልረገጠች፡ርካብ፥
ነገራችን፡ዅሉ፡/፡የእንቧይ፡ካብ፥የእንቧይ፡ካብ።
ትምህርት፡እንዲሰፋ፥/፡ጕልበት፡እንዲጠና፥
አራቱ፡ጉባኤ፡/፡ይነሡልንና፥
መኰንን፣ደረሶ፣/፡አሉላ፣ጎበና፥
አገራችን፡ትማር፡/፡አኹን፡እንደገና፤
ጎበና፥ከፈረስኽ፡ጋራ፡ተነሥ፡እንደገና።(አዝማች)
(ዮፍታሔ፡ንጉሤ፥፲፱፻፳፯፡ዓ.ም.።)
[…]
5፤ኅብር፡ያማርኛ፡ቅኔ።
(ሀ)
አኹን፡ምን፡ይጠቅማል፡/፡ሱሰኛ፡መኾን፧
ብዙ፡ቤት፡ፈረሰ፡/፡ትናንት፡በዚያ፡ቡን።
(ማኅተመ፡ወርቅ፡እሸቴ፥፲፱፻፳፩፡ዓ.ም.።)
(ለ)
ቍርሳችን፡እንጦጦ፥/፡ምሳችን፡አባይ፤
ሻይ፡ግብዣችን፡ዳሞት፥/፡ቡሬ፡አደባባይ፤
ራታችን፡ጎንደር፥/፡አጣጣሚ፡ላይ፤
ኦቶሞቢላችን፡/፡ላንቻይደለሞይ፧
(ዮፍታሔ፡ንጉሤ፥፲፱፻፴፭፡ዓ.ም.።)
(ሐ)
እግረኛ፡እንዳይኾን፡/፡ይኸ፡ውጋዴን፥
ጊዜው፡ሳያልፍበት፡/፡በደጉ፡ዘመን፥
ከሕግ፡ቤት፡ገብቶ፡/፡ምነው፡ቢወሰን፧
(ደራሲው፡መርስዔ፡ሐዘን፡ወልደ፡ቂርቆስ፥፲፱፻፳፬፡ዓ.ም.።)
6፤አንጻር፡ያማርኛ፡ቅኔ።
(ሀ)
ወዳጅ፡ማለት፡ዐብሮ፡/፡ሲባክን፡ነው፡እንጂ፧
እንደ፡ዐይን፣እንደ፡ዦሮ፥/፡እንደ፡እግር፣እንደ፡እጅ፧
(ለ)
የኔንም፡ጐዦ፡ቈጠሩሽ፤
እንደ፡ሰው፡አዳራሽ።
7፤አፍራሽ፡ያማርኛ፡ቅኔ።
(ሀ)
ማሳለፍማ፡ታውቃለኽ፤
አትሰጥም፡እንጂ፡ተጠላኽ።
(ማኅተመ፡ወርቅ፡እሸቴ።)
(ለ)
እምዬ፡ምኒልክ፡/፡በቅሎ፡ስጠኝ፡ብዬ፡/፡እኔ፡አልለምንኽም፤
ካባ፡ስጠኝ፡ብዬ፡/፡እኔ፡አልለምንኽም፤
ብርም፡ስጠኝ፡ብዬ፡/፡እኔ፡አልለምንኽም፤
አምና፡ነበር፡እንጂ፥/፡ዘንድሮ፡የለኽም።
(ይህ፡ግጥም፡የተገጠመው፥የዐፄ፡ምኒልክ፡መሞት፡ተደብቆ፡ሳለ፥ባ፲፱፻፯፡ዓ.ም.፡ነው።)
8፤ውስጠ፡ወይራ፡ያማርኛ፡ቅኔ።
(ሀ)
ማሽላና፡ስንዴ፡/፡ባንድ፡ዐብረን፡ስንቈላ፥
እያረረ፡ሣቀ፡/፡የባሕር፡ማሽላ።
ከሰል፡የሚኾኑ፡/፡ብዙ፡ዕንጨቶች፡ሳሉ፥
ዝግባ፡ለምን፡ይኾን፡/፡ይቈረጥ፡የሚሉ፧
(ዮፍታሔ፡ንጉሤ፥፲፱፻፳፬፡ዓ.ም.።)
(ለ)
አብርሃም፡ቢጣላ፣/፡ከሣራ፡ከሚስቱ፥
ባሪያውን፡አጋርን፡/፡አስወጣት፡ከቤቱ።
በዚህም፡ተጣልተው፥/፡ወጡ፡አደባባይ፤
ዳኛውም፡ፈረደ፡/፡በኹለቱም፡ላይ።
አንተም፡ሠርተኽ፡ብላ፤/፡አንቺም፡ሠርተሽ፡ብዪ፤
አላጋር፡እንጀራ፡/፡አይበላም፡ወይ፧
(ወልደ፡ጻድቅ፡ጋሼ፥፲፱፻፳፡ዓ.ም.።)
|