|
በዓሉ፡ግርማ
(ከ"ኦሮማይ"፥ኩራዝ፡አሳታሚ፡ድርጅት፥ዐዲስ፡አበባ፥፲፱፻??፡ዓ.፡ም.፥ከገጽ፡74-76፡የተቀዳ)
•••
«አይገርማችኹም፧»፡አለ፥በእጁ፡ወደ፡ኮሎኔል፡ታሪኩና፡ሦስት፡በረኸኞች፡እየጠቈመ፤ሞቅ፡ያለ ፡ጭውውት፡ይዘዋል።ሦስቱም፡ወደ፡ላይ፡አንጋጠው፡ኮሎኔል፡ታሪኩን፡ይመለከቱ፡ነበር።ለደመራ ፡የቆመ፡ረዥም፡አጣና፡መስሎ፡ይታያል።ያስገረመው፡ነገር፡ምን፡እንደ፡ኾነ፡ኹለታችንም፡አል ገባንም።
«አይገርማችኹም፧»፡አለ፥እንደገና፥«ትላንት፥በጥይት፡ሲደባደቡ፡የነበሩ፡ሰዎች፥ዛሬ፡ዐብረ ው፡እየጠጡ፡ሲጫወቱ፡ማየት፡በውነት፡ያስገርማል።ፍትዊ፡ወዲ፡በርሄ፥ከመንደፈራ፡አስመራ፡ድ ረስ፡ያለውን፡አገር፡ሲያንቀጠቅጥ፡የነበረ፡ነው።በጊዜው፡ብዙ፡ሰዎች፡አስሯል፤ገርፏል፤ገድ ሏል።ብዙ፡አድምቶናል።ዘርዓይ፡ወዲ፡ሐለቃ፥የጀብሐ፡ፖለቲካ፡ትምህርት፡ቤት፡ዲሬክተር፡ኾኖ ፡በሚሰጠው፡ትንታኔ፡ብዙ፡ወጣቶችን፡ወደ፡በረሓ፡ያሸ፟ፈተ፡ሰው፡ነው።የጀብሐ፡ደቡብ፡እዝ፡ ኮሚሳርም፡ነበር።መስፍን፡ጽሩይ፡በኧርበን፡ጌሪላ፡ታክቲክ፡የሠለጠነ፥የሻዕቢያ፡ቀንደኛ፡ፌ ዳዪን፡ነበር።ኮሎኔል፡ታሪኩ፡ከነሱ፡ጋራ፡ያልተዋጋበት፡ቦታ፡የለም።
«እዚህ፡ከተማ፡ውስጥ፥"የብርጭቋችን፡አባት፡ታሪኩ፡ባይኖር፡ኖሮ፥ይሄኔ፡ዐረቄ፡በጣሳ፡እንጠ ጣ፡ነበር"፡ነው፡የሚሉት።ወንበዴዎች፡ደቃምሐረን፡በያዙበት፡ጊዜ፥አሸዋ፡ጠፍቶ፡የጠርሙስና፡ የብርጭቆ፡ፋብሪካ፡ሥራ፡ቀጥ፡ብሎ፡ነበር።እሱ፡ነበር፡ኹለት፡መትረየስ፡ይዞ፥ግራና፡ቀኝ፡እ የተታኰሰ፥አሸዋ፡የሚያስጭነው።እሱን፡ለመግደል፡ያላደረጉት፡ሙከራ፡የለም።በውነት፥ርግጥ፡ አንዳንድ፡ጥፋት፡ደርሷል፤ቢኾንም፡ግን፥እንደ፡ኢትዮጵያ፡አብዮት፡ሆደ፡ሰፊ፡አብዮት፡ያለ፡ አይመስለኝም።አንዳንዴ፡ሳስበው፥"የዋኆች፡ነን፡ወይ፧"፡እያልኩ፡ራሴን፡እጠይቃለኹ።»፡ካለ ፡በኋላ፥ወደኔ፡ዞር፡ብሎ፥«ጸግሽ፥በዚህ፡ላይ፡ለምን፡አንድ፡ጥሩ፡ፕሮግራም፡አትሠራም፧»፡አ ለኝ።
«ጥሩ፡ሐሳብ፡ነው።"እጃችኹን፡ከሰጣችኹ፥ይገርፏችዃል፤ያሠቃይዋችዃል፤ይገድሏችዃል"፡እያለ ች፥ሻዕቢያ፡የምትነዛውን፡ፕሮፓጋንዳ፡ለመስበር፡ይረዳል።»፡አልኩት።"አብዮትና፡ሰፊው፡ሕዝ ብ፡መሓሪ፡ናቸው"፡የሚል፡አርእስት፡ታየኝ።
«ግን፥ባይመቻቸው፡ነው፡እንጂ፥እነዚህ፡ሰዎች፡የሚተኙልን፡ይመስልኻል፧እኔ፡አላምናቸውም። ትላንት፡ሲወጉንና፡ሲያደሙን፡የቈዩ፡ሰዎች፡ዛሬ፡ተመልሰው፥"ላንድነት፡ቆመናል፤ካብዮቱ፡ጐን ፡ተሰልፈናል"፡ሲሉ፡አይገባኝም።»፡አለ፥መጽሐፈ፡ዳንኤል፡መላጣውን፡በመሐረብ፡እየጠረገ።
ሰሎሞን፥በሐሳብ፡ተመስጦ፥«ከማመን፡በቀር፡ሌላ፡ምን፡ምርጫ፡አለ፧አናምናቸውም፡ከሚል፡አስ ተሳሰብ፡ተነሥተን፡መጥፎ፡ውሳኔ፡ላይ፡መድረስ፡አንችልም።በግድ፡ሆደ፡ሰፊ፡መኾን፡ያስፈልጋ ል።ርስ፡በርሳችን፡የመተማመን፡ነገር፡ጊዜ፡ይወስዳል፤ግን፡መሞከር፡አለብን።አንድ፡ቀን፡ል ጆቻችን፡ተማምነው፡ለመኖር፡ይችሉ፡ይኾናል።ወደዚያ፡የሚወስደውን፡ጥርጊያ፡መንገድ፡መክፈት ፡የኛ፡ፈንታ፡ነው።ግን፥እንዳንተማመን፡የሚያደረጉን፡የውጭ፡ኀይላት፡ናቸው።»፡ካለ፡በኋላ ፥ሲያስብ፡ቈየና፥«የኤርትራ፡ችግር፥እግሩ፡እዚህ፡ይኹን፡እንጂ፥ጭንቅላቱ፡ውጭ፡ነው።ታሪካ ዊ፡አዠማመር፡ታሪካዊ፡ፍጻሜ፡ይኖረዋል።»፡አለ።
ነገሩ፡ስላልገባኝ፥«ምን፡ማለትኽ፡ነው፧»፡ብዬ፡ጠየቅኹት።
ሰሎሞን፡በትረ፥ሰለ፡ኤርትራ፡መናገር፡አይሰለቸውም።ጊዜ፡ካገኘ፥ስለ፡ኤርትራ፡ሲያወራ፡ውሎ ፡ያድራል።«አየኽ፤»፡ብሎ፡ዠመረ፤«ኤርትራ፡ለስድሳ፡ዓመት፡በኢጣሊያ፡ቅኝ፡ግዛት፡ሥር፡ቈይ ታለች።ከዚያ፡በፊት፥ባለፉት፡አራት፡መቶ፡ዘመናት፡የጦርነት፡ዐውድማ፡ሳትኾን፡የኖረችበት፡ ዘመን፡የለም።ኢጣሊያ፡በኹለተኛው፡የዓለም፡ጦርነት፡ስትሸነፍ፥ኤርትራ፡በንግሊዝ፡አስተዳደ ር፡ሥር፡ወደቀችና፥ዐዲሱ፡ፖለቲካዊ፡ድራማ፡ተዠመረ።እንግሊዝ፥እየቈየ፡የሚፈነዳ፡ቦንብ፡በ ኤርትራ፡ምድር፡አጥምዳ፡ነው፡የወጣችው።»፡አለ።
ዅላችንም፡ጠጋ፡ጠጋ፡አልነው።ሰሎሞን፥ለመናገር፡ብሎ፡የሚናገር፡ሰው፡አይደለም፤ከተናገረ፥ ስለሚናገረው፡ነገር፡ካንጀቱ፡ስለሚናገር፥አድማጭ፡ይስባል።
እና፥ቀጠለ፤«ኤርትራን፡በሚመለከት፥እንግሊዝ፡ኹለት፡ዓላማዎች፡ነበሯት።አንደኛው፡ዓላማዋ ፥ኤርትራን፥በተቻለ፡መጠን፥ባስተዳደሯ፡ሥር፡ማቆየት፡ሲኾን፤ይህ፡ባይቻል፥ኹለተኛው፡ዓላማ ዋ፥ሰሜኑንና፡ምዕራቡን፡ቈላማ፡አገር፥ምጽዋን፡ጭምር፥ቅኝ፡ግዛቷ፡ከኾነችው፡ከሱዳን፡ጋራ፡ ቀላቅላ፡መግዛት፡ነበር።እነዚህን፡ዓላማዎች፡መሠረት፡አድርጋ፥ኹኔታዎችን፡ማመቻቸት፡ዠመረ ች።ፖለቲካዊ፡ስልቶችም፡ቀየሰች።
«የመዠመሪያው፡ፖለቲካዊ፡ስልት፥ኢትዮጵያ፥ለጊዜው፥ኤርትራን፡ፈጽማ፡ለማስትዳደር፡እንደማ ትችል፡አድርጋ፡ለዓለም፡ማሳየት፡ነበር።ይህን፡ለማድረግ፥"ታላቋ፡ኤርትራ"፡የሚል፡ፖለቲካዊ ፡ንድፍ፡አወጣች።ንድፉ፥ትግራይን፡ከአልውሀ፡ምላሽ፡ከኢትዮጵያ፡በመገንጠል፡ከኤርትራ፡ጋራ ፡ቀላቅሎ፡የሚይዝ፡ነበር።ይህ፡ነበር፡የ"ታላቋ፡ኤርትራ"፡ግንዛቤ።እንግሊዝ፥ይህን፡ዓላማዋ ን፡የሚያስፈጽምላት፡መሣሪያ፡አላጣችም።"በሣህለ፡ሥላሴ፡ሥርወ፡መንግሥት፡የተወሰደብኝን፡ዙ ፋን፡ወደ፡ሰባጋዲስ፡ሥርወ፡መንግሥት፡እመልሳለኹ"፡የሚል፡ምኞት፡የነበረው፡ጃዝማች፡ተሰማ፡ አስመሮም፡የተባለ፡ሰው፡ነበርና፥"ታላቋ፡ኤርትራ"፡የተባለውን፡መፈክር፡አስነግባ፡አነሣሣች ው።የወያኔ፡ጦርነት፡ተከፈተ።ዛሬም፥ኢሳይያስ፡አፈ፡ወርቅና፡ወያኔዎች፡የሚያራምዱት፡ይኸን ኑ፡ዓላማ፡ነው።"ኢትዮጵያ፡ኤርትራን፡ለማስተዳደር፡አትችልም"፡የሚል፡ጥርጣሬ፡እየተፈጠረ፡ ስለ፡ኼደ፥እንግሊዝ፡ያሰበችው፡ለጊዜው፡የተሳካላት፡መስሎ፡ታየ።»፡
|