|
ይድነቃቸው፡ተሰማ
•••
የነጋድራስ፡ተሰማ፡እሸቴ፡ዐጪር፡የሕይወት፡ታሪክ
("ሠምና፡ወርቁ፡ተሰማ፡እሸቴ"፥ጥቅምት፡፲፱፻፹፭፡ዓ.፡ም.፥ገጽ፡1-9።)
•••
ነጋድራስ፡ተሰማ፡እሸቴ፥ከምኒልክ፡ዘመነ፡መነግሥት፡ዠምሮ፥ኋላም፡በልጅ፡ኢያሱ፥ከዚያም፡በ ንግሥት፡ዘውዲቱ፡በንጉሥ፡ተፈሪ፡በኢጣሊያ፡ወረራ፡ወቅትና፥ቀጥሎም፡እስከ፡ዕለተ፡ሞታቸው፡ ድረስ፡በመንግሥት፡ውስጥ፡ይዘውት፡በነበረው፡ሥራና፡ሥልጣን፡ጭምር፡ባጋጠማቸውና፡በደረሰባ ቸው፡ነገር፡ዅሉ፥በኢትዮጵያ፡የመዠመሪያው፡ሾፌርና፡ሜካኒክነታቸው፥በመዠመሪያው፡ያማርኛ፡ ዜማ፡በዲስክ፡አስቀራጭነታቸው፥በሰነዘሯቸው፡ረቂቅ፡ቃላትና፡ሠምና፡ወርቅ፡ቅኔዎቻቸው፥በኢ ትዮጵያ፡ሕዝብ፡ዘንድ፡ታዋቂነትን፡ሊያተርፉ፡ችለዋል።በመኾኑም፥እስከ፡ዛሬ፡ስለ፡ርሳቸው፡ በጽሑፍ፡የቀረበ፡ታሪክ፡ባይኖርም፥ያማርኛና፡የግእዝ፡ልሳን፡ፉክክር፥የቅኔ፡ሠምና፡ወርቅ፡ ክርክር፡በምሁራን፡መካካል፡በተነሣ፡ቍጥር፥ስማቸውና፡ግጥሞቻቸው፡በቃልና፡በጋዜጦች፡እየተ ጠቀሱ፡ቈይተዋል፤ኖረዋል።
ከብዙ፡ጊዜ፡ዠምሮ፥ርሳቸውም፡በሕይወት፡ሳሉ፥ግጥሞቻቸውን፡በጽሑፍ፡እንዲያስቀሩ፡ከልዩ፡ል ዩ፡አቅጣጫ፡ዐደራ፡ባዩ፡ብዙ፡ነበር።ለምሳሌ፡ያኽል፥ስለሺ፡የሚባል፡ሰው፥ይኸንኑ፡ጥያቄ፡በ ጋዜጣ፡አቅርቦላቸው፥በዚሁ፡ጋዜጣ፡የሚከተለውን፡መልስ፡መስጠታቸው፡ትዝ፡ይለኛል፤
"በግልጽ፡የጻፍከውን፡ሕዝብ፡አነበበው፤
ግምትኽ፡ስለሺ፡የሚቈጠር፡ነው፤
እንግዲህ፡ይጽፋል፡ተሰማ፡ጆሮው።"
ነጋድራስ፡ከሞቱ፡በኋላ፥እነዚህን፡ግጥሞች፡እንዳሳትም፡ከያለበት፡ጥያቄ፡ቀርቦልኝ፡ደጋግሜ ፡ቃል፡መግባቴን፡አስታውሳለኹ።
የተጠናከረ፡ጽሑፍ፡ስላላዘጋጁ፥በተለይም፥የግጥሞቹን፡ሠምና፡ወርቅ፡ፍቺ፡በጽሑፍ፡ስላ ላስቀሩ፥ራሴ፡መፍታት፥ወይም፡የዕድሜ፡ጓደኞቻቸውን፡እየፈለግኹ፥ፍቺውን፡ለማወቅና፡ግ ጥሞቹን፡ለማሰባሰብ፡ሰፋ፡ያለ፡ጊዜ፡ወስዶብኛል።
እኔም፡ራሴ፥የሥራዬ፡ጠባይ፡ብዙ፡ጊዜ፡ካገር፡ውጭ፡ስለሚወስደኝ፥ረጋ፡ብዬ፡ለማዘጋጀት ፡የምችልበት፡የጊዜ፡ዕጥረት፡አጋጥሞኛል።
እንሆ፥አኹን፥ከብዙ፡ድካም፡በኋላ፥ግጥሞቹን፡በማሰባሰብ፥ታሪካዊ፡አመጣጣቸውን፡በመረ ዳት፥በተቻለኝ፡መጠን፡ዅሉ፥ቧልቱንም፡ጭምር፡ሳላስቀር፡በመጽሐፍ፡መልክ፡ለማውጣት፡ተ ቃርቤአለኹ።
ግጥሞቹ፥በየጊዜው፥ባንድ፡ወቅት፥ባንድ፡አጋጣሚ፡የተፈጠሩ፡ኹኔታዎችን፡መነሻ፡በማድረ ግ፡የተጻፉ፡ስለ፡ኾነ፥ባንድ፡በኩል፡ፖለቲካዊና፡ታሪካዊ፡ይዘታቸውን፥በሌላ፡በኩል፥ላ ማርኛ፡ቋንቋ፡ብልጽግና፡ቅርስነታቸውን፡አጣምሮ፡ለመመልከት፡ያስችሉናል።
ግጥሞቹንም፡በበለጠ፡ለመረዳት፥በቅድሚያ፡ነጋድራስ፡ተሰማ፡እሸቴን፡ማወቅ፡ስለሚጠቅም ፥የሕይወት፡ታሪካቸውን፡ዐጠር፡ባለ፡ኹኔታና፡በጥቂት፡ገጾች፡አቀርባለኹ።
በመጽሐፉ፡ውስጥ፡ያንዳንድ፡ደብዳቤዎችና፡ጽሑፎች፡ፎቶኮፒ፡ያገባነው፥ርሳቸውን፡የበለ ጠ፡ለማወቅም፡ኾነ፡በዚያ፡ጊዜ፡የነበረውን፡ያሠራር፡ዘዴና፡አጻጻፍም፡ስለሚያመለክት፥ ለታሪክ፡ተመራማሪ፡ይረዳል፡በማለት፡ነው።
ነጋድራስ፡ተሰማ፡እሸቴ፥ካባታቸው፡ካቶ፡እሸቴ፡ጉቤ፡ከጐጃም፡በረንታና፡ከቦረና፡ጨከታ ፡ከናታቸው፡ከእማሆይ፡ወለተየስ፡ሀብቱ፡ከቡልጋ፡መስኖ፡ማርያም፡ይወለዳሉ።
የተወለዱት፥ሐምሌ፡፳፡ቀን፥፲፰፻፷፱፡ዓ.ም.፥ምንጃር፡ቀርሾ፡ዐጥር፡በተባለው፡ስፍራ፡ነው።አባታቸው፡አቶ፡እሸቴ፥የራስ፡መኰንን፡ ጭፍራ፡ስለ፡ነበሩና፥መሰንቆም፡ስለሚጫወቱ፥ራስ፡መኰንንን፡ተከትለው፡ወደ፡ሐረር፡ሲኼ ዱ፥ነጋድራስንም፡በሕፃንነታቸው፡ይዘዋቸው፡ስለ፡ኼዱ፥ያደጉትና፡ዐማርኛ፡ትምህርታቸው ን፡ያጠናቀቁት፡በሐረር፡ነው።
አባታቸው፡አቶ፡እሸቴ፥ሐረር፡እንዳሉ፡በመሞታቸው፥ነጋድራስ፥በወጣትነት፡ዕድሜ፥ዐፄ፡ ምኒልክን፡ተከትለው፡ወደ፡ዐዲስ፡አበባ፡መጡ።
በ፲፱፻፡ዓ.ም.፥ሙሴ፡ሆልስ፡የተባለ፡ጀርመናዊ፡በኢትዮጵያ፡ለብዙ፡ጊዜ፡ከቈየ፡በኋላ፥ወደ፡አገሩ፡ሲ መለስ፥ዐፄ፡ምኒልክን፡በተሰናበተበት፡ጊዜ፥ጀርመን፡አገር፡ወስዶ፡የሚያስተምራቸው፡ሦ ስት፡ወጣቶች፡እንዲሰጡት፡ስለ፡ጠየቃቸውና፥ነጋድራስ፡ተሰማ፡እሸቴም፡በጥሩ፡ሠዓሊነታ ቸው፡በቤተ፡መንግሥቱ፡ስለ፡ታወቁ፦ያ፡ተሰማ፡እሸቴ፥እጁ፡ብልኅ፡ነውና፥መኪና፡መንዳት ና፡መጠገን፡እንዲማር፡እሱ፡ይኺድ፡ብለው፡ዐፄ፡ምኒልክ፡ስለ፡ወሰኑ፥ወደ፡ጀርመን፡አገ ር፡ለመኼድና፥ለኹለት፡ዓመት፡ያኽል፡የኦቶሞቢልን፡አሠራር፡ለመማር፡ቻሉ።
በዚያ፡ጊዜ፥ካዲስ፡አበባ፡ከተነሡበት፡እስከተመለሱበት፡ድረሰ፡የፈጸሙትን፡ዅሉ፡ባንድ ፡ደብተር፡ላይ፡በሚገባ፡ጽፈውት፥በልጅነታችን፡እቤት፡እናነበው፡ነበር፤አኹን፡ግን፡አ ልተገኘም።ቢኾንም፥የማልረሳው፤
1.፡በመዠመሪያው፡ገጽ፤
"ጻፉብኝ፡ይላል፡ይህ፡ደብተር፤
አፍ፡አውጥቶ፡የሚናገር፥
በምኒልክ፡አገር።"
2.፡በመጨረሻ፡ገጽ፤
"ተሰማ፡እሸቴ፡ዐዲስ፡አበባ፤
ባዲስ፡ዓለም፡ገባ።"
የሚለውን፡ነው።
ባዲስ፡ዓለም፡በኩል፡የመጡ፡በማስመሰል፥የኤውሮፓውን፡ዐዲስ፡ዓለም፡አይተው፡መምጣታቸ ውን፡ለመጥቀስ፡ነበር።
ነጋድራስ፥መሰንቆ፡መምታትና፡ዜማ፡ካባታቸው፡ተምረው፡ስለ፡ነበር፥ወደ፡ጀርመን፡አገር ፡ኼደው፡በቈዩበት፡ጊዜ፥"ሂዝ፡ማስተርዝ፡ቮይስ"፡ከሚባለው፡ኩባንያ፡ጋራ፡በመዋዋል፥17 ፡ዲስኮች፡ዘለሰኛና፡መዲና፡በማስመዝገብ፡ዐሥራ፡ሰባት፡ሺሕ፡የጀርመን፡ማርክ፡ተከፍሏ ቸዋል።ይህም፥ዐዲስ፡አበባ፡ሲመለሱ፥በሀብታሞች፡ደረጃ፡ለመቈጠር፡ዕድል፡ሳይሰጣቸው፡ አልቀረም።
ነጋድራስ፡ተሰማ፡እሸቴን፡እጅግ፡ታዋቂ፡ካደረጓቸው፡ነገሮች፡አንዱ፥የነዚህ፡ዲስኮች፡ ኢትዮጵያ፡መምጣትና፥ሌላም፡ያማርኛ፡ዲስክ፡ስላልነበረ፥ለኻያ፡ዓመት፡ያኽል፥ዐቅም፡ባ ለው፡ቤተሰብ፡ዅሉ፡በግራሞፎን፡ይሰማ፡የነበረው፡የሳቸው፡ዘፈን፡ብቻ፡በመኾኑ፡ነው።ሌ ሎች፡ያማርኛ፡ዲስኮች፡የተቀረጹት፡ጠላት፡ኢትዮጵያ፡ሊገባ፡ኹለት፡ዓመት፡ያኽል፡ሲቀር ፥በነፈረደ፡ጐላ፥በነንጋቷ፡ከልካይና፡በነተሻለ፡መንግሥቱ፡ተጫዋችነት፡ወደ፡፲፱፻፳፭-፳፮፡ገደማ፡ነው።
ዐዲስ፡አበባም፡እንደ፡ተመለሱ፥የቤተ፡መንግሥት፡መኪናዎች፡ኀላፊ፡ኾነው፥የዘመኑን፡ታ ዋቂ፡ኢትዮጵያውያን፡ሾፌሮች፡አሠልጥነዋል።ስለ፡ዐፄ፡ምኒልክ፡በተጻፈ፡አንድ፡የታሪክ ፡መጽሐፍ፡ላይ፥ነጋድራስ፡መኪና፡ላፄ፡ምኒልክ፡ሲያሳዩ፡የተነሡት፡ፎቶግራፍ፡አለ።ጸሓ ፊው፡ግን፥በስሕተት፥"ፈረንጅ፡ሲያስጐበኝ"፡ብሎ፡ጠቅሶታል።
|