|
ራስ፡ቢትወደድ፡መኰንን፡እንዳልካቸው።
('የደም፡ድምፅ'፥ዐዲስ፡አበባ፥1944፡ዓ.ም.፤ገጽ፡68-71።)
•••
ያቡነ፡ጴጥሮስ፡ጸሎት፥ሌሊት፡በወህኒ፡ቤት።
አቡነ፡ጴጥሮስ፡መብራት፡ያበራሉ፦
በስመ፡አብ፡ወወልድ፡ወመንፈስ፡ቅዱስ፥አሐዱ፡አምላክ፤አሜን።አቤቱ፥ያች፡የምታስደነግጥ፡የ ሞት፡ጽላ፡በላዬ፡ላይ፡ልትወድቅ፡ነው፤ያችም፡የምትመር፡የሞት፡ጽዋ፡ቀረበች።ነገር፡ግን፥አ ንተ፡ከኔ፡ጋራ፡ከኾንክ፡አልፈራም፤የሞትም፡ጽላ፡አያስደነግጠኝም፤የሞትንም፡መራራ፡ጽዋ፡ስ ላንተ፡ፍቅርና፡ስለኢትዮጵያ፡ጥፋት፡እጠጣታለኹ።
አቤቱ፡ጌታዬ፡ኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ሆይ፤እስከ፡መቼ፡ድረስ፡ችላ፡ትለናለኽ፧በኛ፥በክፉዎችስ፡ ምክንያት፡እንዴት፡የወዳጅኽ፡የዳዊት፡ዙፋን፡በጠላት፡ጫማ፡ይረገጥ፧
በዓለም፡ላይ፡የታወቀች፡የኢትዮጵያ፡ሰንደቅ፡ዓላማስ፡ከቤተ፡መንግሥታችን፡ላይ፡ተነቅላ፡እ ንዴት፡ትውደቅ፧
የባዕድ፡ቀንበር፡ተሸክማ፡የማታውቅ፡ኢትዮጵያ፡በፋሺስት፡መዝገብ፡በባርነት፡እንዴት፡ትጻፍ ፧
አቤቱ፡መድኀኒታችን፥በባሪያኽ፡በያዕቆብ፡ዐድረኽ፦ያንበሳ፡ግልገል፡ይሁዳ፡ተንበርክከኽ፡ተ ኛ፤ማንስ፡ይችላል፡ያስነሣኽ፡ዘንድ፤በትር፡ከይሁዳ፡አይጠፋም፥የገዢ፡ዘንግም፡ከእግሮቹ፡መ ካከል፥የሰላም፡ንጉሥ፡እስኪመጣ፡ድረስ፡የሚል፡ቃል፡ኪዳን፡ሰጥተኸው፡ነበር።
ነገር፡ግን፥አሸናፊው፡የኢትዮጵያ፡አንበሳ፥አንተ፡ስለተለየኸው፥ተመቶ፡ወደቀ፤የገዢነቱም፡ በትር፡ከእጁ፡ወድቃ፡ተሰበረች።ስለዚህ፥እረኛችን፡ቀዳማዊ፡ኀይለ፡ሥላሴ፥የኢትዮጵያ፡ንጉሠ ፡ነገሥት፥በሐሳብና፡በሐዘን፡እንደ፡ምናሴ፡በብረት፡ቀፎ፡ውስጥ፡ተይዞ፡ወዳንተ፡ይጮኻል።
አቤቱ፥በቸርነትኽ፡ይቅር፡ብለኸው፥ወደ፡ዙፋኑ፡እንዲመለስና፡የኢትዮጵያም፡ሕዝብ፡ዅሉ፡ከሥ ልጣኑ፡በታች፡እንዲሰበሰብ፡አድርግ።
እኔም፡የተናቅኹ፡ባሪያኽ፥ያንተን፡የመከራ፡ጽዋ፡ተካፋይ፡ለመኾን፡ስለ፡ተዘጋጀኹ፥በጣም፡አ መሰግንኻለኹ።
አቤቱ፥የባሪያኽን፡የእስጢፋኖስን፡የሃይማኖት፡ብርታት፡አሳድርብኝ፤ምግባሬም፡እንድትበረታ ፥አንተ፡ባባትኽ፡ቀኝ፡ተቀምጠኽ፡ልይኽ፤በመሬቱ፡ላይ፡የምታፈሰው፡የኔ፡የኀጢአተኛው፡ደም፡ በፊትኽ፡የተቀደሰች፡መሥዋዕት፡ኾና፥እንደአቤል፡ደም፡ስለ፡ኢትዮጵያ፡ትካሰስ።አቤቱ፥መምህ ሬ፣ፈጣሪዬ፣ጌታዬ፥ዦሮኽን፡አዘንብለኽ፡ስማት፤አሜን።
እንግዴህ፥የዚህ፡ዓለም፡የሕይወቴ፡ብርሃን፡ጠፋች፤ነገር፡ግን፥የሚመጣው፡ዓለም፡የሕይወቱ፡ ብርሃን፡የበለጠ፡እንዲያበራ፡አምናለኹ።
መልአክ፦ጴጥሮስ፤ጴጥሮስ፤ጴጥሮስ፤አይዞኽ፥አትፍራ፤ሥጋኽን፡ነው፡እንጂ፡ነፍስኽን፡መግደል ፡አይችሉም።
አስቀድሞ፡ገና፡በልጅነትኽ፡ለመናኒው፡ላባ፡ተድላ፡ረድ፡ኾነኽ፡ስታገለግል፥ለዚህ፡ከፍ፡ላለ ው፡ጸጋ፡ተመርጠኻል፤ደምኽም፡ለኢትዮጵያ፡ነጻነት፡በጸጋው፡ዙፋኝ፡ፊት፡ቀርባ፥አስታዋሽ፡ት ኾናለች፤አንተም፡ብቻ፡ሳትኾን፥ባደግኽበት፡ገዳም፥በደብረ፡ሊባኖስ፡ብዙዎች፡ወንድሞችኽ፡በ ሰማዕትነት፡ይሞታሉ፤ደማቸውም፡ካንተ፡ደም፡ጋራ።
አቤቱ፥ስለኢትዮጵያና፡ስለኛ፡ደም፡መቼ፡ትበቀልልናለኽ፡እያሉ፡ሊጮኹ፡ነው።አይዞኽ፤የኢትዮ ጵያ፡ነጻነት፡ይመለሳል፤ንጉሠ፡ነገሥቱም፡በዙፋኑ፡ላይ፡ሊያበራ፡ነው።
|