ሊቀ፡ካህናት፡ጥዑመ፡ልሳን፡ካሳ
("ያሬድና፡ዜማው"፥ትንሣኤ፡ዘጉባኤ፡ማተሚያ፡ቤት፥ዐዲስ፡አበባ፥፲፱፻፹፩፡ዓ.ም.፥ገጽ፡20-24፡የተቀዳ)
•••
ቅዱስ፡ያሬድ
«ዋይ፡ዜማ፡ዘሰማዕኩ፡በሰማይ፡እመላእክት»
ቅዱስ፡ያሬድ፡ባ፭፻፭፡ዓ.ም.፥ሚያዝያ፡፭፡ቀን፡አኵስም፡ከተማ፡ተወለደ።አባቱ፡አብዩድ፡(ይሥሐቅ)፡ይባላል፤በሌላ፡በኩል፡ደግሞ፥ዐዲስ፡በታተመው፡ገድለ፡ያሬድ፥እገጽ፡፵፪፡ላይ፥አዳም፡ነው ፡ይላል፤"ወተዝካረ፡አዳም፡አቡየ"፡ስለሚል፡ነው።ይኹን፡እንጂ፥ተዝካረ፡አዳም፡የሚለው፡ቃል ፥የሥጋ፡አባቱን፡ሳይኾን፡ቀዳማዊ፡አዳምን፡ይኾናል፡እንጂ፥ወላጅ፡አባቱ፡አይደለም፡የሚል፡ የሊቃውንት፡አነጋገር፡አለ።ስለዚህ፥እንደተባለውም፡ዅሉ፥ቀዳማዊ፡አዳምን፡ነው፡ከማለት፡በ ስተቀር፡የሥጋ፡አባቱ፡ነው፡ለማለት፡አስቸጋሪ፡ነው።እናቱ፡ክርስቲና፡ወይም፡ታውክልያ፡ትባ ላለች፤እሷም፡የያሬድ፡አስተማሪ፡የነበረው፡የጌዴዎን፡እኅት፡ናት።የቅዱስ፡ያሬድ፡አባትና፡ እናት፡የትውልድ፡አገራቸውና፡ርስታቸው፡አኵስም፡ነው።ቅዱስ፡ያሬድ፡በተወለደ፡በሰባት፡ዓመ ቱ፡አባቱ፡አብዩድ፡ስለ፡ሞተ፥እናቱ፡ክርስቲና፡ያኵስም፡ገበዝ፡ለነበረው፡ላጎቱ፡ለጌዴዎን፡ እንዲያሳድገውና፡እንዲያስተምረው፡ዐደራ፡ብላ፡ሰጠችው።
ቅዱስ፡ያሬድ፡አጎቱ፡ዘንድ፡ገብቶ፡መዝሙረ፡ዳዊትን፡በሚማርበት፡ጊዜ፡ትምህርት፡አልገባው፡ አለ፤በዚህ፡ምክንያት፡መምህር፡ጌዴዎን፡ብዙ፡ጊዜ፡ስለሚቈጣውና፡ስለሚገርፈው፥ያሬድ፡መታገ ሥ፡ተስኖት፥ከወላጆቹ፡ቤት፡ወጥቶ፥ማይኪራሕ፡ወደምትባል፡ቦታ፡ኼዶ፡ተደበቀ።ያም፡የተደበቀ በት፡ቦታ፡የቀዳማዊ፡ምኒልክ፡መቃብር፡ያለበት፡ነበር፤በውስጡም፡ወርቅና፡ብር፥ልብስም፡ሞል ቶበት፡ነበር።ያሬድ፥ወዳንዲት፡ዛፍ፡ሥር፡ተጠግቶ፡ዐርፎ፡እያለቀሰ፡ሳለ፥አንድ፡ትል፡አየ፤ ትሉም፡ወደ፡ላይ፡እወጣለኹ፡እያለ፡እመኻከሉ፡ሲደርስ፡ይወድቅ፡ነበር።እንደዚህ፡እያለ፡ለ፮ ፡ጊዜያት፡በተደጋጋሚ፡ሲወጣና፡ሲወርድ፡ከቈየ፡በኋላ፥በ፯ኛው፥ትሉ፡እዛፉ፡ላይ፡ወጥቶ፡የዛ ፉን፡ፍሬ፡ወይም፡ቅጠል፡ሲበላ፡ተመለከተ።
ከዚህ፡በኋላ፥ቅዱስ፡ያሬድ፡የትሉን፡ተስፋ፡አለመቍረጥ፥ከፍተኛ፡የኾነውን፡ጥንካሬውንና፡ት ጋቱን፥እንዲሁም፡ወደ፡ላይ፡ለመውጣት፡ብዙ፡ጊዜ፡እየሞከረ፡ቢወድቅም፥ካላማው፡ሳይናወጥ፡ከ ብዙ፡ጊዜ፡ድካምና፡ጥረት፡በኋላ፡ያሰበው፡ዅሉ፡እንደ፡ተፈጸመለት፡ተመልክቶ፥ሰውነቱን፡እን ዲህ፡ይላት፡ዠመር፦ሰውነቴ፡ሆይ፥ግርፋትን፡ለምን፡አትታገሺም፤መከራንስ፡ለምን፡አተቀበዪም ።አኹንም፡ትዕግሥትን፡ገንዘብ፡ስላደረግሽ፡እግዚአብሔር፡ይኸን፡ነገር፡ገለጠልሽ፡ብሎ፡ዐዘ ነ፤አለቀሰ።በመጨረሻም፡ወደ፡መምህሩ፡ወደ፡ጌዴዎን፡ተመልሶ፦አባቴ፡ሆይ፥ይቅርታ፡አድርግል ኝና፡እንደ፡ቀድሞው፡አስተምረኝ፡አለው።መምህሩ፡ጌዴዎንም፦እሺ፡ብሎ፡ተቀብሎ፡ያስተምረው፡ ዠመር።ከዚህ፡በኋላ፥ባንድ፡ቀን፡፻፶፡መዝሙረ፡ዳዊትን፥መሓልየ፡ነቢያትንና፡መሓልየ፡ሰሎሞ ንን፥እንዲሁም፡ትርጓሜ፡መጻሕፍትን፥ማለት፥ብሉያትንና፡የሌሎቹንም፡መጻሕፍት፡ቍጥራቸውን፡ ዐወቀ።በኋላም፥በዲቁና፡ማዕርግ፡አኵስም፡ጽዮን፡ቤተ፡ክርስቲያን፡እያገለገለ፡ይኖር፡ዠመር ።በዚያ፡ዘመን፥ድምፅን፡ከፍ፡አድርጎ፡ማገልገል፡የለም፡ነበር።ቀስ፡ብሎ፥በጕረሮ፡እንደ፡ው ርድ፡ንባብ፡እያዜሙ፡ያገለግሉ፡ነበር፡እንጂ፥ይኸውም፡ባንዳንድ፡አገሮች፡እንደሚያዜሙት፡ዜ ማ፡ያለ፡ነበር፡ይባላል።
የቅዱስ፡ያሬድ፡በጋብቻ፡መወሰንና፡የዜማው፡መገለጥ
ቅዱስ፡ያሬድ፥እላይ፡እንደተገለጠው፥ለብዙ፡ዘመናት፡በዲቁና፡እያገለገለ፡ከኖረ፡በኋላ፥ወላ ጆቹ፡ሚስት፡ዐጭተውለት፥በሥርዐተ፡ቤተ፡ክርስቲያን፡ደንብ፡መሠረት፡አጋብተውት፡ይኖር፡ዠመ ር።ዳሩ፡ግን፥በየጊዜው፥አንድ፡ሰው፥ሚስቱን፡ለመድፈር፡ሲል፥ያባብላት፡ስለ፡ነበር፥ያሬድ፡ በነገሩ፡እያዘነ፡ተቀምጦ፡ሳለ፥ከዕለታት፡አንድ፡ቀን፥ሰውዮውን፡ለመግደል፡ዐስቦ፥ጦር፡ይዞ ፡እመንገድ፡ሸመቀ፡ወይም፡አደፈጠ።እግዚአብሔርም፥የያሬድን፡ልብ፡ባወቀ፡ጊዜ፥ከኤዶም፡ገነ ት፥በሥላሴ፡አምሳል፡ሦስት፡አዕዋፍን፡ወደ፡ርሱ፡ላካ።አዕዋፉም፡ሦስት፡ዐይነት፡ቀለም፡ያላ ቸው፡ናቸው፤ይኸውም፡አረንጓዴ፥ብጫ፥ቀይ፡ቀለም፤እነሱም፡በግእዝ፥በአራራይ፡በዕዝል፡ዜማና ፥እንዲሁም፡በአብ፡በወልድና፡በመንፈስ፡ቅዱስ፡ይመሰላሉ።ምሳሌነታቸውም፡እንደሚከተለው፡ነ ው፤አረንጓዴ፡ቀለም፡በግእዝ፥ብጫ፡ቀለም፡በዕዝል፥ቀይ፡ቀለም፡በአራራይ፡የሚመሰሉ፡ሲኾን፥ በሌላ፡በኩል፡ደግሞ፥አረንጓዴ፡ቀለም፡በአብ፡የተስፋ፥ብጫ፡ቀለም፡በወልድ፡የሥግው፡ቃል፥ቀ ይ፡ቀለም፡በመንፈስ፡ቅዱስ፡ያምሳለ፡እሳት፡ምሳሌዎች፡መኾናቸውን፡የቤተ፡ክርስቲያን፡ሊቃው ንት፡በብዛት፡ይናገራሉ።በዚህ፡መሠረት፥ሦስቱም፡አዕዋፍ፡ያሬድ፡ከቆመበት፡ቦታ፡ፊት፡ለፊት ፡ባየር፡ላይ፡ቆመው፥ከሦስቱ፡አንዷ፡በልሳነ፡ሰብእ፡ያሬድን፡እንዲህ፡ስትል፡ተናገረችው፦ያ ሬድ፡ሆይ፥ሰውን፡ለመግደል፡ስለ፡ምን፡ታስባለኽ፤ክህነትኽ፡ትፈርስ፡የለምን፤ከሚስት፡ይልቅ ፡ክህነትኽ፡አትሻልምን።ጌታችንም፡በወንጌል፡እንዲህ፡አለ፡«አንድ፡ሰው፡ምን፡መልካም፡ሥራ ፡ሠርቼ፡ነው፡የዘለዓለም፡ሕይወት፡የማገኘው፧»፡ብሎ፡ቢጠይቀው፥እሱም፡መልሶ፡እንዲህ፡አለ ው፤«ሕግጋቱን፡ወይም፡ትእዛዛቱን፡የምትጠብቅ፡ከኾነ፥ነፍስ፡አትግደል፡አለው።»፡(ማቴ.፡ም.፡፲፱፥ቍ.፡፲፮-፲፱)፡ታዲያ፡አንተስ፥ሰው፡መግደልን፡ስለ፡ምን፡በልብኽ፡ታስባለኽ፤ክህነት፡ከመንግሥትና፡እዚህ ፡ዓለም፡ካለው፡ነገር፡ዅሉ፡ትበልጥ፡የለምን።ያሬድ፡ሆይ፥አንተ፡ብፁዕ፡ነኽ፤አንተን፡የተሸ ከመች፡ሆድ፡ብፅዕት፡ናት፡አለችው።ያሬድ፡ይኸንን፡ቃል፡በሰማ፡ጊዜ፥ወደ፡ሰማይ፡ተመልክቶ፡ ሦስቱን፡አዕዋፍ፡አየና፡እንዲህ፡አላቸው፦እናንተ፥በሰው፡አንደበት፡የምትናገሩ፥ከወዴት፡መ ጣችኹ፡አላቸው።ከሦስቱ፡አዕዋፍ፡አንዷ፦ከኤዶም፡ገነት፡ወዳንተ፡ተልከን፡መጣን፤ይኸውም፡ከ ኻያ፡አራቱ፡ካህናተ፡ሰማይ፡ማሕሌትን፡ትማር፡ዘንድ፡ልንነግርኽ፡መጣን፡አለችው።ከዚህ፡በኋ ላ፥አዕዋፉ፡ከዐይኑ፡ተሰወሩ።ያሬድም፥በተመስጦ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ሰማያዊት፡ተነጠቀ፤በዚያ ም፡የዕንዚራ፥የአርጋኖንና፡የመሰንቆ፡ድምፅን፥እንደዚሁም፥መላእክተ፡ሰማይንና፡ምድራውያን ፡ደቂቀ፡አዳምን፡የፈጠረ፡እግዚአብሔርን፡በማሕሌት፡በቅኔ፡በከፍተኛ፡ድምፅ፡ጧትና፡ማታ፡በ መንበሩ፡ዙሪያ፡ኾነው፡ሲያመሰግኑት፡በሰማ፡ጊዜ፥ካለበት፡ቦታ፡ዘሎ፡እነሡ፡ወዳሉበት፡ቦታ፡ ሊገባ፡ወደደ፤ነገር፡ግን፡አልተቻለውም።በመጨረሻም፥እነዚያ፡አዕዋፍ፡ወደ፡ርሱ፡ተመልሰው፡ መጡ።ከሦስቱ፡አዕዋፍም፡አንዷ፦ያሬድ፡ሆይ፡የሰማኸውን፡አስተውለኸዋልን፡ብላ፡ጠየቀችው፦አ ላስተዋልኩም፡ብሎ፡መለሰላት፦እንግዲያውስ፡እኔ፡እነግርኻለኹ፤ዐዲሱን፡የእግዚአብሔርን፡ም ስጋና፡ጥራ፤ርሱም፡የጌታችን፡የኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ስም፡ነው፡አለችው።ከዚያ፡በኋላ፥ቅዱስ፡ ያሬድ፥ማሕሌትን፡በያይነቱ፡"ልቤ፡መልካም፡ነገርን፡አውጥቶ፡ተናገረ"፡እያለ፡ከኻያ፡አራት፡ ካህናተ፡ሰማይ፡ተማረ።በመጨረሻም፥ቀድሞ፡ወደ፡ነበረበት፡ቦታ፡ከቀኑ፡በሦስት፡ሰዓት፡ተመለ ሰ።በዚያን፡ጊዜ፥ኹኔታውን፡ከተመለከቱት፡መኻከል፥አንዳንዶቹ፡ይህ፡የዜማ፡ምስጢር፡ለቅዱስ ፡ያሬድ፡የተገለጠለት፡በአስማት፡ነው፡የሚሉ፡ነበሩ፤ነገር፡ግን፥የእግዚአብሔር፡ቃል፡በአስ ማት፡የሚገለጥ፡ቢኾን፡ኖሮ፥በዘመኑ፡ብዙ፡አስማተኞች፡ስለ፡ነበሩ፥ለነሱ፡በተገለጠላቸው፡ነ በር።ዳሩ፡ግን፡በቅዱስ፡ያሬድ፡ገድል፡ላይ፡የዜማው፡ምስጢር፡በአስማት፡ተገለጠለት፡የሚል፡ የለም።የቅዱስ፡ያሬድ፡የገድሉ፡መጽሐፍ፥የጠራ፥ያማረ፡ነው።ኾኖም፥ሐሳውያን፥በቅዱሳት፡መጻ ሕፍት፡ያላገኙትን፡እንደ፡ተገኘ፡አድርገው፡ይናገራሉ።እውነቱ፡ግን፥ቅዱስ፡ያሬድ፡ለማሕሌታ ት፡ለዝማሬያት፡መዝገብ፡የኾነው፥ተግሣፅን፥ምክርን፡በትዕግሥት፡ከመቀበሉ፡ጋራ፡በምሕላና፡ በጸሎት፡ነው።ከዚህም፡የተነሣ፥ቅዱስ፡ያሬድ፥በተመስጦ፡ወደ፡ሰማይ፡ተነጥቆ፥ከሱራፌልና፡ከ ኪሩቤል፡ማሕሌትን፡ተምሮ፡በሦስት፡ሰዓት፡እንደ፡ተመለሰ፥አኵስም፡ከተማ፡ወደምትገኘው፡ወደ ፡ጽዮን፡ቤተ፡ክርስቲያን፡ገብቶ፥እታቦተ፡ጽዮን፡ፊት፡ቆሞ፥ድምፁን፡ከፍ፡አድርጎ፤«ሃሌ፡ሉ ያ፡ለአብ፤ሃሌ፡ሉያ፡ለወልድ፤ሃሌ፡ሉያ፡ለመንፈስ፡ቅዱስ፤ቀዳሜሃ፡ለጽዮን፡ሰማየ፡ሣረረ፤ወ በዳግም፡አርኣዮ፡ለሙሴ፡ዘከመ፡ይገብር፡ግብራ፡ለደብተራ።»፡(ለአብ፡ምስጋና፡ይገባል፤ለወልድም፡ምስጋና፡ይገባል፤ለመንፈስ፡ቅዱስም፡ምስጋና፡ይገባል፤ከ ጽዮን፡አስቀድሞ፡ሰማይን፡ፈጠረ፤ዳግመኛም፡ለሙሴ፡የድንኳኑን፡ሥራ፡አሳየው።)፡ብሎ፡በልሳነ፡ግእዝ፡ዘመረ፡(ዘፀ.፡ም.፡፳፭፥ቍ.፡፰-፲)፡
|