|
ብላቴን፡ጌታ፡ኅሩይ፡ወልደ፡ሥላሴ፡
("ወዳጄ፡ልቤ፥"፡ምዕራፍ፡14፥፲፱፻፷፫፡ዓ.ም.፥ገጽ፡41።)
•••
በምሥራቅና፡በምዕራብ፥በሰሜንና፡በደቡብ፡እየዞርኹ፡ይህን፡ዓለም፡(መጻሕፍትን)፡ስመለከት፥ድንገት፡በመንገዴ፡አጠገብ፡ትልቅ፡አዳራሽ፡አገኘኹ።
ይህ፡አዳራሽ፡የማነው፡ብዬ፡ብጠይቅ፥የወይዘሮ፡ዓለሚቱ፡ነው፡አሉኝ።
ከወይዘሮ፡ዓለሚቱ፡ጋራ፡በቃል፡እንተዋወቅ፡ነበረና፥በርሷ፡ቤት፡ለማደር፡ገባኹ።
ርሷም፥የበክር፡ልዷን፡ምኞትን፡የምትድርበት፡ቀን፡ኖሮ፥እንዳጋጣሚ፡ዅሉ፡በድግስ፡ላይ፡ደ ረስኹ፤እጅግም፡ደስ፡አለኝ።
ዐሳቤማ፥ወይዘሮ፡ዓለሚቱ፥በቃል፡ካወቀችን፥መጣ፡ሲሏት፡ግባ፡በሉት፡ትልና፡ስበላ፡ስጠጣ፡ዐ ድራለኹ፡ብዬ፡ነበር።
ነገር፡ግን፡ቤተ፡ዘመዶቿ፡እነ፡ቅናት፥እነ፡ምቀኝነት፥እነ፡ተንኰል፥እነ፡ሐሰት፥እነ፡አቶ፡ እንደ፡ጊዜው፡የነዚህም፡የልጅ፡ልጅ፡ዅሉ፥ያልታደመ፡ሰው፡እንዳይገባ፡ብለው፡በሩን፡የውጥር ፡ይዘውታል።
ቢኾንም፥የድግስ፡ቀን፡ስለ፡ኾነ፥ዅሉም፡ሰክረው፡ግር፡ግር፡ሲሉ፥ሹልክ፡ብዬ፡ገባኹ፤ወደ፡ገ በታው፡ቀርቦ፡ለመብላት፡ግን፡አልኾነልኝም።እንዲህም፡ማለቴ፥ለወጉ፡ለማረጉ፡ነው፡እንጂ፤ለ ሆዴ፡ያኽል፡ግን፥እንጀራውን፡ሲያነሡ፡ሲጥሉ፡የወደቀውን፡ፍርፋሪ፡እየለቀምኹ፡እጅግ፡ጠገብ ኹ።
ያ፡ወዳጄ፡ልቤም፡ከኔ፡ጋራ፡ነበረና፡፦ወጥተን፡እንኺድ፡እንጂ፥ለማኝ፡ይመስል፡ፍርፋሪ፡ስን ለቅም፡ልናድር፡ነውን፡አለኝ።
ምነዋ፡ወዳጄ፡ልቤ፤ሞኝ፡ነኽን፤ማየትም፡እንጂ፡አንድ፡ቁም፡ነገር፡ነው።ደግሞስ፥ያ፡ጳውሎስ ፡የሚባል፡ሰው፡"የበሉ፡እንዳልበሉ፡ይኾናሉ"፡ብሎ፡ያጫወተንን፡ነገር፡ዘነጋኸውን፡(፩፡ቆሮ.፥፯፥፳፱-፴፩)።
ይልቅስ፡መሰንቆኽን፡እየከራከርኽ፡ሰርገኞቹን፡አጫውታቸው፡አልኹት።
፦አኹን፡ዅሉም፡ሰክረዋል፤ማን፡ሊሰማኝ፡ብዬ፡መሰንቆዬን፡አወጣለኹ፧አለ።
፦ቢሰሙኽ፡መልካም፡ነው፤ባይሰሙኽ፡በነርሱ፡ይፈረዳል፡እንጂ፡ባንተ፡ይፈረዳልን፡አልኹት፡(ሕዝቅ.፥፫፥፲፰-፲፱)።
፦እነርሱ፡እንዳይሰሙኝ፡የታወቀ፡ነገር፡ነው፤ነገር፡ግን፡ካዘዝኸኝ፡እሺ፡አለ።
|