|
ጸሓፌ፡ትእዛዝ፡ገብረ፡ሥላሴ፡ወልደ፡መድኅን
("ታሪከ፡ዘመን፡ዘዳግማዊ፡ምኒልክ፥ንጉሠ፡ነገሥት፡ዘኢትዮጵያ"፥አርቲስቲክ፡ማተሚያ፡ቤት፥ዐዲስ፡አበባ፥፲፱ ፻፶፱፡ዓ.ም.፥ገጽ፡38-41)
•••
ከዚህ፡በኋላ፥ልጅዎ፡ሣህለ፡ሥላሴ፡ነገሡ።ስመ፡መንግሥትዎ፡ምኒልክ፡ነበር።እናትዎም፥ወይዘ ሮ፡ዘነመ፡ወርቅ፡የመንዝ፡ባላባት፡ያፍቀራ፡ጎሌ፡ልጅ፡ነዎ።ሣህለ፡ሥላሴም፡በነገሡ፡ጊዜ፥ዘ መነ፡መንግሥትዎ፡ዘመነ፡ሣህል፡ኾነ።በዚያ፡ዘመን፡እጅግ፡ተድላ፡ደስታ፡በዝቶ፥ሰው፡ከሰው፡ ተስማምቶ፡ኖረ።
ንጉሥ፡ሣህለ፡ሥላሴም፡ለድኻው፡ዅሉ፡በደግነት፡ያዝኑለት፡ነበር።በመንግሥትዎም፡ያለውን፡ድ ኻ፡ዅሉ፡እየሰበሰቡ፡ዕዳውን፡ይከፍሉለት፡ነበር።እንዲህም፡እያደረጉ፥ለተቸገረው፡ዅሉ፡ጥማ ድ፡ጥንድ፡እየሰጡ፥ዕረስ፥ቈፍር፡ይሉት፡ነበር።
ከብዙ፡ደግነትዎ፡ጥቂት፡ከፍለን፡እንጽፋለን፤ለዝክረ፡ነገር፡ወግ፡ታሪክ፡እንዳይረሳ፡ብለን ፡ነው፡እንጂ፥የርስዎስ፡ደግነት፥ቸርነት፡በየወገኑ፡ቢጻፍ፡አንባቢ፡ይደክማል፤ሰሚም፡ይሰለ ቻል።ነገር፡ግን፥እንደ፡ሥነ፡ፍጥረት፡ዕፁብ፡ድንቅ፡እያሉ፡ሊተዉት፡ይገባል።
ያ፩፡አገር፡ድኻ፡ተቀብሎ፡ያ፩፡አገር፡ድኻ፡እንዳይቀርበት፥ምጽዋት፡ለዅሉም፡እንዲደርስለት ፡ያደርጉ፡ነበር።
እንዲህም፡ፈጣሪዎን፡እየወደዱ፥የወንጌልን፡ቃል፥የመንግሥተ፡ሰማያትን፡መንገድ፡እያሰቡ፡እ የመረመሩ፥መንግሥትዎን፡ለልጅዎ፡ለቀው፡ሊተዉት፥በደንስ፡በፍቅሬ፡ግምብ፡የሚኾንዎን፡የሚመ ችዎን፡ቦታ፡ሲያስፈልጉ፡ነበር።ይህነንም፡ሲያስቡ፥ባንኮበር፡ቅዱስ፡ሚካኤልን፥ባንጎለላ፡ኪ ዳነ፡ምሕረትን፥በነገሡ፡በ፳፫ኛ፡ዓመት፡ዐፈር፡ባይኔ፡አቡነ፡ተክለ፡ሃይማኖትን፡ተክለው፥ይ ህን፡ዓለም፡ለወዲያኛው፡ዓለም፡ለመለወጥ፡ዐሰቡ፤ነገር፡ግን፥ወዳጆችዎ፡መነኮሳት፥"ረዐይኬ፡ አባግዕየ"፡እንዲል፦እግዚአብሔር፡የሰጠዎን፡መንጋ፡በትነው፡መኼድ፡አይኾንም፤መንግሥት፡ሳይ ለቁ፡እግዚአብሔር፡የሚወደውን፡ነገር፡ታደረጉ፡አይለየዎም።የልቡናዎን፡ዅሉ፡ይሰጥዎታል።የ ልጅዎም፡መንግሥት፡ዐጪር፡ነው።ነገር፡ግን፥ከጐንደር፡ንጉሥ፡መጥቶ፥አገርዎ፡ሸዋ፡ገብቶ፥የ ልጅዎን፡ልጅ፡ይዞ፡ይኼዳል።ያም፡የልጅዎ፡ልጅ፡ከዚያው፡ንጉሥ፡ጋራ፡፲፡ዓመት፡ተቀምጦ፡ይመ ለሳል።በፈጣሪዎ፡ኀይል፥አገሩ፡ገብቶ፥ባልጋዎ፡ተቀምጦ፥አረማውያንን፡አቅንቶ፥በግራኝ፡የኼ ደውን፡አገር፡ዅሉ፡መልሶ፥አብያተ፡ክርስቲያናትን፡ዐድሶ፥ዐልፎ፡ተርፎ፡ይገዛል፡ብለው፡መክ ረው፡አስቀሩዎ።
ከዚህ፡በኋላ፥የእግዚእነ፡ኢየሱስ፡ፍቅር፡አነሣሥቶዎ፡አያትዎ፡የዠመሩት፡ቤተ፡ክርስቲያን፡ መቃኞ፡ነበርና፥አፍርሰው፡ሌላ፡መቃኞ፡ሠሩ።ነገር፡ግን፥የሚያገቡበት፡ታቦት፡አልታወቀም፡ነ በር።
፩፡ወዳጅ፡መነኩሴ፡ነበረዎና፦ያሠራኹትን፡መቃኞ፡ላሳይኽ፡ብለው፡ወሰዱት።ያም፡መነኩሴ፡ለማ የት፡በገባ፡ጊዜ፥ባለሟልዎን፦ዝጋበት፡ብለው፡አስቈለፉበት።መነኩሴውም፥ያለፈቃዱ፥በመደንገ ጥ፡በመባባት፡እዚያው፡ውስጥ፡ዐደረ።በነጋውም፡በሩን፡አስከፍተውም፡አስጠሩት፤በመጣም፡ጊዜ ፦ወዴት፡ዐደርኽ፧ብለው፡ጠየቁት፦አሽከር፡ሳያውቅ፡ቈልፎብኝ፥ብጣራም፡የሚሰማኝ፡ዐጣኹ፤ብቻ ዬን፡ዐደርኹ፡ብሎ፡ነገረዎ።
ንጉሡም፦እንግዲያስ፡የእግዚአብሔር፡ፈቃዱ፡ቢኾን፡ነው፥ብለው፦ብቻኽን፡ስታድር፡ነገር፡ሳታ ገኝ፡አትቀርምና፥ያየኸውን፡ራእይ፡ንገረኝ፡አሉት፤እሱም፦ምን፡ጊዜ፡ተኛኹና፤ተጨነቄ፡ዐድሬ ፡አለዎ።ርስዎም፡ግድ፡አሉት፤መነኩሴውም፡እንዲህ፡አለ፦ሰራዊተ፡መላእክቲሁ፡ለመድኀኔ፡ዓለ ም፡ይቀውሙ፡ቅድሜሁ፡ለመድኀኔ፡ዓለም፡ሲል፡ሰማኹ፡እንጂ፥ሌላ፡ነገር፡አላየኹም፡አለ።ይህን ንም፡በነገረዎ፡ጊዜ፡ንጉሡም፡ደስ፡አለዎ።ታቦተ፡መድኀኔ፡ዓለምን፡አክብረው፡አግብተው፥ዐይ ነተኛውን፡ሕንጻ፡ዠመሩ።ሲሠሩትም፥ሰሎሞን፡ለቤተ፡መቅደስ፡ሥራ፡ወደ፡ኪራም፡እንደ፡ላከ፥ር ስዎም፡የትሕትና፥የፍቅር፡መልክት፡ልከው፡ከጐንደር፡አስመጥተው፡አስዠመሩት።
|