ሕዝብ
ግለሌ።
(ከግል፡ማኅደር፡የተቀዳ)፡
•••
ዳሞ፥ዳሞ፥ዳሞ፡ግለሌ፥
ገሥግሦ፡ገዳይ፡በሰው፡ቀበሌ።
ግለሌ፡ምሳው፥ግለሌ፡እራቱ፤
መለቃለቂያው፥ደም፡ራጨቱ።
ገለል፡በሉለት፡አንድ፡ጊዜ፡ለሱ፤
ግልግል፡ያውቃል፡ከነፈረሱ።
እሱን፡ተዉት፥እናንት፡ቅደሙ፤
መራር፡ነው፡ደሙ።
የይፋት፡ጐበዝ፥ሞላሌ፡ውልዱ፥
እንደ፡መድኀኒት፡ይበቃል፡አንዱ።
መገን፡ዐዋዲ፥መገን፡ራሳ፥
መሳይ፡አሞራ፡ገድሎ፡ሲነሣ።
መገን፡ራሳ፥መገን፡የኛ፡አገር፥
ፈሪ፡ሲላላ፡የሚኾን፡ማገር።
ዕሠይ፡ልጄ፥ዕሠይ፡ዕሠይ፥
ገደለ፡ወይ።
ያ፡ሳቡ፥ሳቡ፡መጣ፡ወይ፡ደሞ፥
እንዲያ፡ሲርበን፡ሲጠማን፡ከርሞ።
ሳቡ፥ሳቡ፥ሳቡ፡መሸብን፤
የዦቢራ፡እራት፡ግብር፡አለብን።
ስንኳን፡ዐሽከሩን፡ፈረሱን፡ከፋው፤
ሠርክ፡የደም፡ሸማ፡እያስከረፋው።
ደክሟል፥ደክሟል፥ደክሟል፡ፈረሱ፤
ድፋው፡በራሱ።
አንጐፈለለ፡ሰንጌ፡ጭራውን፥
አሻግሮ፡እያየ፡የጦር፡መምጫውን።
አኰበኰበ፡ሰንጋኽ፡እንደ፡ርኵም፤
አባራርዬ፡ባንተ፡አልደረስኩም።
አባረርካቸው፡በቃኽ፡ተመለስ፤
ማንን፡ይተኳል፡አንት፡ብትጨረስ።
ዕሠይ፡ልጄ፥ስሪቴው፡ዘሟል፤
ደሞ፡ይገድላል።
ረ!፡ተው፡ዳለች፥ፍራት፡ምንድን፡ነው፤
ጦር፡ቢወረወር፥ጥይት፡ቢዘራ፡ለኔም፡ላንተም፡ነው።
ታዘበኝ፡ዳለች፤ልታዘብኽ፤
ተዘበኝ፡ቦራ፤ልታዘብኽ፤
ጠፍቼ፡እንደ፡ኾን፡ተኮርቻኽ፤
ገጭቼኽ፡እንደኹ፡ከልጓምኽ።
ገድሏል፥ገድሏል፤ዐርበኛው፡ገድሏል፤
ዝናሩ፡ጐድሏል።
አሳዶ፡ገዳይ፡ጋራ፡ለጋራ፤
ዐሰቴም፡እንደኹ፡ይመስክር፡ቦራ፤
እንግዴህ፡ዳለች፥እንግዴህ፡ቦራ፡ጥሬኽን፡ብላ፤
የተባባልነው፡ጕዳይ፡ተሞላ።
እንኳን፡ጥሬውን፡ይብላው፡ዱቄቱን፤
ዳማ፡አይደለም፡ወይ፡ያቀናው፡ቤቱን።
ናወዝ፡ናወዝ፥ናወዝ፡ናወዝ፥
እንዳትያዝ።
እናቱ፡ተቤት፡አታሳርዘው፤
አባቱ፡ከደጅ፡ዕርፍ፡አያሲዘው፤
ልጁ፡ለግዳይ፡የሚናውዘው።
እምቧ፡እምቧ፡ይላል፡እበረታቸው፤
ከዋልታው፡ነው፡ወይ፥ከምሶሷቸው፤
ልጃቸው፡ገድሎ፥ደግሞ፡ዐማቻቸው።
እዚያው፡ገድሎ፡እዚያው፡ያገራል፤
ያ፡ልጅ፡ይኾናል።
|