|
ዘመድኹን፡ይግለጡ
(ከ"ክቡር፡ደጃዝማች፡ዘውዴ፡አስፋው፡ዳርጌ፥ተዝካር"፥ዐዲስ፡አበባ፥፲፱፻፷፬፡ዓ.ም.፥የተቀዳ)
•••
ደጃዝማች፡ዘውዴ፡አስፋው፡ዳርጌ
"አባ፡በላይ"
(፲፰፻፹፬-፲፱፻፷፬፡ዓ.፡ም.)
የኢትዮጵያ፡ዠግኖች፡ስማችኹ፡ይጻፍ፥
ሥጋማ፡በስባሽ፡ነው፤ስም፡ነው፡የማያልፍ።
እስቲ፡እናነሣሣው፡ዘውዴ፡አስፋው፡ዳርጌን፥
አስቀድሞ፡በፊት፡የተዋጋውን።
ተዋግቶና፡አዋግቶ፡ሐበሻን፡ያስነሣ፥
ጻፉት፡በልባችኹ፡ዘውዴ፡እንዳይረሳ።
አባ፡በላይ፡ዘውዴ፥ያስፋው፡ዳርጌ፡ልጅ፥
አስራቀው፡ውቃቢ፡የሮማን፡ፈረንጅ።
ዘውዴ፡መኻል፡ሸዋን፡ቢበጠብጠው፥
አበሻ፡ተነሣ፡ዅሉም፡ሊጠጣው።
ደንግጦ፡ነበረ፡አስቀድሞ፡አበሻ፤
ዅሉም፡ልብ፡ገዛ፡ባባ፡በላይ፡ጋሻ።
እንደ፡ጫካ፡አንበሳ፡ግርማው፡የሚያስፈራ፤
አያወላውልም፡ዘውዴ፡አስፋው፡ሲሠራ።
አልናገረውም፥እዚያው፡ይቀመጥ፤
ዐምስት፡የገደለ፡በቀለሕ፡ሽጕጥ።
ባሥራ፡ዘጠኝ፡መቶ፡በኻያ፡ስምንት፥
ጣሊያን፡ሙሎ፡ወጥቶ፡ሲመለምል፡ከብት፥
ዘውዴ፡አስፋው፡ዐረደው፡የሐምሌ፡አቦ፡ለት፤
አበላው፡ለዠግና፡ምልምሉንም፡ከብት።
ይኸን፡ሰምቶ፡መጣ፡ብዙ፡መኳንንት፥
የሚያስፈራ፡ቢኾን፡የዘውዴ፡ጥይት።
ዘውዴ፡አስፋው፡ቢነሣ፡በሜታ፡ፈረስ፥
ብዙ፡ሰው፡ጠገበ፡ተርቦ፡የሚያለቅስ።
በዝርዝር፡ተጽፎ፡ሲታይ፡በደብተር፥
ስማቸው፡ነኝ፡ይላል፡ቈራጡ፡ወታደር።
ሥራ፡የሚሠሩ፡ከዘውዴ፡አስፋው፡ጋር፥
ከጃንሜዳ፡ወጥቶ፡የይትረፍ፡አሽከር።
መልካም፡ነው፡እንግዴህ፡ስማቸው፡ቢጠራ፤
ታፈሰ፡ጠብቄ፥ታምራት፡አበራ፥
ዘመድኹን፡ይግለጡ፥አግዜም፡አይቀራ።
እጽፍለታለኹ፡ሥራውን፡በውነት፥
የመትረየሱ፡ቄስ፡ተክለ፡ሃይማኖት።
ጻፈኝ፡ጻፈኝ፡አለ፡ሥራቸው፡በግድ፥
መንግሥቱ፡ዓለማየኹ፥ደባሽ፡ወንድራድ።
ግቻ፡እሚያስነክሰው፡ጣሊያንን፡በተኵስ፥
ጠመንጃው፡ተማች፡ነው፥ፈረሱ፡ትራስ፥
ያባ፡ጠቅል፡አሽከር፡ወልደ፡ዮሐንስ።
መትረየስ፡ሲተኰስ፡ልቡ፡የማይባባ፥
ዘውዴ፡አስፋው፡ያወጣው፡ባሻ፡አርጋው፡አባባ።
የሮማን፡ፋሺስት፡ወቃው፡እያስተኛ፥
አባ፡በላይ፡ዘውዴ፡ያስነሣው፡ዐርበኛ።
መንገዱ፡ሲዘጋ፥ዥግኖች፡ሲያቅታቸው፥
የዘውዴ፡አስፋው፡ስም፡ነው፡የሚያሳልፋቸው።
መርሐቤቴ፡ሞተ፡እንደ፡እስጢፋኖስ፥
ያማሴን፡ባላባት፥ልጅ፡ቆስጠንጢኖስ፥
ለሰው፡ሲል፡ዘውዴ፡አስፋው፡እያለው፡ደስ፡ደስ።
አስቈፍሮ፡ይምጣ፡ጣሊያን፡መቃብር፤
አይስትም፡ተኵሶ፡መስፍን፡በመውዜር።
ዘውዴ፡አስፋው፡መጣና፡በይትኖራ፡ላይ፥
ጅሩን፡ጠቀለለው፡አበበ፡አረጋይ።
ዘውዴን፡ይመርቃል፡ጠግቦ፡ወታደር፥
እንጀራ፡ቢያበላው፡መርቶ፡ከመንደር፥
የመርሐቤቴን፡ጤፍ፥የጋላውን፡ማር።
ኢጣሊያ፡ሊገባ፡ወዲያው፡በግንቦት፥
ፋሺስትን፡ተለመው፡ያበበ፡ጥይት።
እግዚአብሔር፡ይወዳል፡የውነት፡ምስክር፤
የሣህለ፡ሥላሴ፡ያስፋው፡ወሰን፡ዘር፤
መንገድ፡ያስከፍታል፡የዘውዴ፡ግንባር፤
ባላገር፡ያመጣል፡ሳያዙት፡ግብር።
ከጣርማ፡በር፡ይዞ፡ጐዣም፡እስከ፡ቡሬ፥
ያስፈራል፡ዘውዴ፡አስፋው፡የደገላው፡አውሬ።
አባ፡በላይ፡ዘውዴን፡ይሉታል፡አንድ፡ሰው፥
ሽጕጥ፡አነባብሮ፡አንጐል፡የሚያፈርሰው።
የክፉ፡ቀን፡ሥራው፡አይረሳም፡እኮ፤
ብዙ፡ሰው፡ከበረ፡በዘውዴ፡ሥር፡ታኮ።
ፋሺስት፡ሲገባ፡በጨለማው፡ቀን፥
አባ፡በላይ፡ዘውዴ፡የዠግናው፡ብርሃን።
•••
የጃዝማች፡ዘውዴ፡አስፋው፡(አባ፡በላይ)፡ፉከራ፤
ወጣኒ፡ጐበዝ፥ገና፡ዠማሪ፥
በረዥም፡ጥይት፡አነባባሪ።
ኰሰሰ፡ብለው፡ዘውዴን፡አይንቁም፤
እንደ፡ደረሰ፡ያሸናል፡በቁም።
እግረ፡ቀጭን፥ልበ፡ተራራ፥
ቁሞ፡እሚቈየው፡ከነዚያ፡ጋራ።
ዘውዴ፡አባ፡ዘው፡ዘው፥
አይመለስም፡አንዱን፡ሳይነብዘው።
ትንሽ፡እንደ፡መድኀኒት፥
ገሥግሦ፡ገዳይ፡ቀንና፡ሌሊት።
ዘውዴ፡የቀጭን፡ሥራ፥
ልቡ፡እማይካክም፥ሆዱ፡እማይፈራ።
አባቱ፡ታላቅ፡ታዋቂ፥
ልጁ፡በረዥም፡ጥይት፡አስተናናቂ።
ምቀኛው፡ብዙ፥ጠቃሚው፡ጥቂት፤
አቀዣባሪ፡በመውዜር፡ጥይት።
ዘውዴ፡የበላይ፡ጌታ፥
ለብጤው፡ቤዛ፥ላገር፡መከታ፥
በሞት፡አላትሞ፡ጦር፡የሚፈታ፥
እኛ፡ሲመጡ፡አይመርጥም፡ቦታ፤
አያፈገፍግ፥አያመነታ፤
የትም፡ይይዛል፡እንደ፡በሽታ።
|