|
ማንኩልኽ፡ሞረሽ
«ኑ፡ተሸጋገሩ፡ከገነት፡እገነት»
("ስለ፡ገነት፡ሆሎታ፡የቀዳማዊ፡ኀይለ፡ሥላሴ፡ጦር፡ትምህርት፡ቤት፡መመሥረት፡ብሩራዊ፡ኢዮቤልዩ፡መታሰቢያ"፥ተስፋ፡ማተሚያ፡ቤት፥ዐ ዲስ፡አበባ፥፲፱፻፶፪፡ዓ.ም.፥ገጽ፡36-38)
•••
የገነት፡መኰንኖች፡የሞታችኹ፡ላገር፥
ኢዮቤልዮአችኹ፡በዓላችኹ፡ሲከበር
ዐፈር፡ገላልጣችኹ፡ውጡ፡ከመቃብር፤
በትዝታ፡መንገድ፥ኑ፡በሰልፍ፡በግር፤
በእውን፡ተሰብሰቡ፡ዐብሩ፡ከኛ፡ጋር፤
እንለፍ፡በርምጃ፥በንጉሣችን፡ግንባር።
ኑ፡ተሸጋገሩ፡ከገነት፡እገነት፤
በትዝታ፡መንገድ፥በመንፈስ፡ሰውነት።
ተነሡ፡በመንፈስ፤ተከሠቱ፡ባካል፤
ኑ፡ተቀላቀሉ፡በደስታው፡መኻል።
ሆ!፡በሉ፥ጨፍሩ፤ሰልፉ፡ይደባለቅ፤
የኢዮቤልያችኹ፡ፈንጠዝያው፡ይድመቅ።
ትፈንድቅ፡ቀያችኹ፥መኖሪያችኹ፡ገነት፤
በዝናችኹ፡ትኵራ፥ታጊጥ፡በወንድነት።
ኑ፡ተሸጋገሩ፡ከገነት፡እገነት፤
በትዝታ፡መንገድ፥በመንፈስ፡ሰውነት።
አቅራሩ፤ፎክሩ፤ወኒአችኹ፡ይገልምጥ፤
ጎራዴአችኹ፡ያብራ፤ግርማችኹ፡ያስደንግጥ።
ኢዮቤልዩአችኹ፡ሲከበር፡ይህ፡በዓል፥
ተንጓደን፡ተዋዥበን፡በዠግንነት፡ባህል፥
ይውጣልን፡ናፍቆቱ፥የፍቅሩ፡ሰቀቀን፤
ገነቶች፡ብቅ፡በሉ፤ዝለቁ፡በዚህ፡ቀን።
ኑ፡ተሸጋገሩ፡ከገነት፡እገነት፤
በትዝታ፡መንገድ፥በመንፈስ፡ሰውነት።
ግቡ፤ተሰብሰቡ፤እንኹን፡አንድ፡ላይ፡
በፈለማችኹት፡ግቢና፡አደባባይ።
ተከታዮቻችኹ፡ስንሠየም፡እኛ፤
ሰንደቅ፡ዓላማችኹ፥ቀዳሚው፡ዐርበኛ
በክብር፡ሲሸለም፥ሲቀደስ፥ሲታደስ፥
ሕያው፡ታዛቢዎች፡ኹኑን፡ግርማ፡ሞገስ።
ኑ፡ተሸጋገሩ፡ከገነት፡እገነት፤
በትዝታ፡መንገድ፥በመንፈስ፡ሰውነት።
ኺዱ፡ተላለፉ፡ከገነት፡ለገነት
ኑ፡በሰልፍ፡ግቡ፡ባላማችኹ፡ዙሪያ፥
በንጉሣችኹና፡በኢትዮጵያ።
ያጣጣማችዃት፡መሪር፡የሞት፡ጽዋ፡
ዋጅታለች፡አገርን፡ከጕይ፡ምፅዋዕ።
እንግዲህ፡ዕረፉ፡ደማችኹ፡ካፈራ፤
ሟያችኹ፡ይቀዳጅ፡የነጻነት፡ጌራ።
ኺዱ፡ተላለፉ፡ከገነት፡ለገነት፥
በጽድቅ፡ጐዳና፥በሰማዕትነት።
ዕረፉ፡በሰላም፤ኑሩ፡በነጻነት፤
ተመለሱ፥ግቡ፡እዘላለሙ፡ቤት፥
በኢትዮጵያ፡ሕፅን፥በምትወዷት፡መሬት።
ኑሩ፡በጽድቅ፡ጸጋ፡በሰማዕትነት፥
በትውልድ፡ልቦና፥በታሪክ፡አንደበት፤
ይህ፡ነው፡መደምደሚያው፥ክብሩ፡ላገር፡መሞት።
ኺዱ፡ተላለፉ፡ከገነት፡ለገነት፥
በጽድቅ፡ጐዳና፥በሰማዕትነት።
ዕረፉ፡በሰላም፤ይገባችዃል፡ክብር፤
አይደመደምም፡የናንተ፡መቃብር፤
አይረመረምም፡የዠግና፡ገላችኹ፤
አይረጋገጥም፡የወጣት፡ዐፅማችኹ፤
በምትኮቻችኹ፡ይጠበቃል፡በኛ፥
በኢትዮጵያ፡ተስፋ፥በክብራ፡ዘበኛ።
ኺዱ፡ተላለፉ፡ከገነት፡ለገነት፥
በጽድቅ፡ጐዳና፥በሰማዕትነት።
ዕረፉ፡በሰላም፤ዕረፉ፡በሐሴት፥
በመርሳት፡ከተማ፥በዘላለሙ፡ቤት፤
በቤተሰብ፡እንባ፥በተወላጅ፡ጸሎት
ነፍሳችኹ፡ትቀደስ፥ትለቀስ፡ዘወትር።
በኢትዮጵያ፡ሕዝብ፡ስማችኹ፡ይከበር፤
ይህ፡ይገባችዃል፡የሞታችኹ፡ላገር።
ኺዱ፡ተላለፉ፡ከገነት፡ለገነት፥
በጽድቅ፡ጐዳና፥በሰማዕትነት።
ማንኩልኽ፡ሞረሽ
•••
የገነት፡ሆሎታ፡የጦር፡ትምህርት፡ቤት፡የመዠመሪያ፡ዕጩ፡መኰንኖች፡የስም፡ዝርዝር፤
፲፱፻፳፯፡ዓ.ም.።
|