ግእዝ ዐማር ኛ

ዋዜማ፡ሥርዐት

ቅጂ

ዜና

ግስ

ስሌት

ግእዝ-ዐማርኛ

ቀለም፡ቀንድ

ዋዜማ፡ሥርዐት•Wazéma System•Wazéma Système

ኢትዮጵያዊ፡የማስሊያ፡መጻፊያ፡ሥርዐት•Ethiopian Computer Writing System•système d'écriture informatique éthiopien

(to view the Amharic text, install the Wazéma Unicode fonts and set your browser’s default Ethiopic font)

Wazéma System•Wazéma Système

ሕዝብ


ሽለላ

(ከግል፡ማኅደር፡የተቀዳ)

•••

ምርቱም፥ገለባውም፡ተደባልቋልና፥

የምታበጥረው፡ጐራው፡ና፥ጐራው፡ና።

•••

ዐርበኞች፡ሲመጡ፡እየተኳኰሱ፥

ያንበጣ፡ጕዞኛ፡ይመስላል፡ርሳሱ።

•••

እኛው፡መጡ፥እኛም፡አየናችው፤

መድኀኒት፡የጠጡ፡ይመስላል፡ፊታቸው።

እኛው፡መጡ፥እንደ፡ባርማሽላ፡እየተመረጡ፤

በመጡበት፡መንገድ፡መመለሻ፡ሊያጡ።

•••

ራሰ፡ዘናኑ፥እግረ፡ውትርትሩ፥

እጁ፡መርዘኛ፡ነው፤አይኖርም፡አገሩ።

•••

አግዳጅም፡ያገዳል፤ነጓጅም፡ይነጕዳል፤

እጀ፡ዛሩ፡ጋሜ፡የትም፡ይወለዳል።

•••

ልጅ፡ነው፡እንጂ፡አሳሪው፡ገመዱ፤

ቤትማ፡ምን፡ይላል፡ዘግተውት፡ሲኼዱ።

•••

ምናባቱ፤ንብረት፡ምናባቱ፤

ንብረት፡ባይኖረው፡ነው፡ነብር፡መፈራቱ።

•••

ድዋሮ፡ከጉሙ፥ጣርማበር፡የዋሉ፥

ይማግዱት፡ቢያጡ፡ነዶ፡ሣር፡ቅጠሉ፥

በመትረየስ፡ጥይት፥ባረር፡እየቈሉ፥

ያርባ፡ዓመት፡ጭንኵሮ፥ባርማሽላ፡በሉ።

•••

እገጭ፡እጓ፡ሲል፡ነው፡የወንድ፡አብነቱ፤

ሴትም፡ትዋጋለች፡ተረጋ፡መሬቱ።

•••

ጦር፡መጣ፤ጦር፡መጣ፤ጫፉን፡ነቀነቀው፤

ጐበዝን፡ደስ፡አለው፤ፈሪንም፡ጨነቀው።

•••

የወንድ፡ልጅ፡እናት፡ታጠቂ፡በገመድ፤

ልጅሽን፡አሞራ፡እንጂ፥አይቀብረውም፡ዘመድ።

•••

ለበኑም፥መውዜሩም፥መድፉም፥መትረየሱም፥አንድ፡ነው፡ብረቱ፤

ቈራጥ፡ያስፈልጋል፡ክትት፡ያለ፡ዐሞቱ።

•••

ምን፡ያደርጋል፡አኹን፡አግድመው፡ቢሮጡ፤

ያዳልጥ፡የለም፡ወይ፡ሣሩ፥ሰንበሌጡ።

•••

መድፉ፡ሲያስገመግም፥መደርብይ፡ሲያጓራ፥

አይሮፕላን፡ሲጥል፥መርጉ፡ሲያንደባራ፥

የመትረየስ፡ጥይት፡እንደ፡ቡን፡ሲፈላ፥

ርሳስ፡ሾልካ፡ስትኼድ፡በሰውዮው፡ገላ፥

ቀዩ፡ሰው፡ሲጠቍር፥ጥቍሩ፡ሰው፡ሲቀላ፥

ልብ፡አይታመንም፡እንኳን፡ባልንጀራ።

•••

ተጕዘን፥ተጕዘን፥ዕርቅ፡የኾነ፡እንደ፡ኾን፥

ያህያዬን፡ኪራይ፡ማን፡ይከፍለኝ፡ይኾን፧

•••

ሎጋ፡ሎጋ፡ቢሉት፥ስሙ፡ነወይ፡ሎጋ፥

በደም፡ካልነከሩት፡እንደ፡እመጫት፡ዐልጋ።

•••

አንድ፡ወንድም፡ያለው፡ሰው፡ኹለት፡ሞት፡አይሞትም፤

ይገድሉታል፡እንጂ፥ትጥቁን፡አይገፉትም።

•••

ጐበዝ፡ጥራ፥ዠግና፡ጥራ፥እንደ፡ሬት፡የሚመር፥እንደ፡ኮሶ፡እሚያሽር፤

ይኸን፡ተወውና፡የመንደር፡ግምሽርሽር።

•••

ውረድ፡በለው፤ይዋጋል፡በግዱ፤

ያገሩ፡መኼጃ፡ሲጠፋው፡መንገዱ።

•••

ጀልጀሌ፡ነው፥ሜዳው፡ጀልጀሌ፡ነው፤ሮጠኽ፡አትዘልቀው፤

ጐራዴኽን፡መዘኽ፥ዞረኽ፡ተናነቀው።

•••

ረ!፡አንሸሽም፤ረ!፡አንሸሽም፤ብንሸሽም፡ተጓደን፤

እወንዶቹ፡መንደር፥ወሲል፡ላይ፡ተወልደን።

•••

በጧት፡ጥመድና፡በጊዜ፡ፍታቸው፤

የሰው፡አገር፡በሮች፡ራትም፡የላቸው።

•••

ምን፡አለበት፥ፈሪ፡ምን፡አለበት፤

ግንባሩ፡ተልጧል፡መዝጊያ፡የገፋበት።

•••

አኹን፡ለምን፡ይኾን፡ፈሪ፡ማቶንቶኑ፤

አይበጠስ፡ቅጠል፡ካልደረሰ፡ቀኑ።

•••

ባንበሳው፡መኝታ፡ዥቡ፡ተኝቶበት፥

ብንን፡ብንን፡ይላል፡በልሙ፡እየመጣበት።

•••

ይተኵሷል፡እንጂ፡ቈንጥር፡አዘልሎ፤

ወዴት፡ደንበር፥ገተር፥የሰው፡ለበን፡ዐዝሎ።

•••

እነበግ፡ዕረዱ፥እነሸማ፡ጋርዱ፥

እናገልግል፡ፍቱ፥እናሽከር፡ወጊዱ፤

ይቸግር፡የለም፡ወይ፡ለብቻ፡መውረዱ።

•••

ወንድሙን፡ሲሰድቡት፡ወንድሙን፡ካልከፋው፥

አጋድመኽ፡ዕረደው፡ደሙ፡እንዲከረፋው።

•••

ጦር፡መጣ፡ይላሉ፤እኔ፡ምን፡ቸገረኝ፤

ለናቴም፡ልጅ፡የላት፤ለኔም፡ወንድም፡የለኝ።

•••

ሽጕጤ፥መውዜሬ፡ቢለዩኝ፡አልወድም፤

ደም፡ተደረቀ፡ነው፡የሚደርሰው፡ወንድም።

•••

የኔስ፡ወንድሞቼ፡ጥይቶቼ፡ናቸው፤

እዚህ፡ተቀምጬ፡እዚያ፡እምልካቸው።

•••

ዠግና፡ብርሌ፡ነው፤ቶሎ፡ይሰበራል።

ፈሪ፥ጥቍር፡ድንጋይ፥ዘላለም፡ይኖራል፤

አገር፡አማን፡ሲኾን፡ወሬ፡ያሳምራል፤

እገጭ፡እጓ፡ሲልም፡እማጀት፡ይገባል።

•••

እሳት፡ቢያዳፍኑት፡ይመስላል፡የጠፋ፤

ያ፡ሰው፡አይደለም፡ወይ፥ዐንገቱን፡ቢደፋ።

•••

ጋማውን፥ጭራውን፡ቢጐነዳድሉት፥

ሰንጌ፡ዐመሉን፡አይተው፡ኰርቻ፡ሲጭኑት።

•••

አትመነው፡የሽፍታን፡ጐፈሬ፤

እንኳን፡በውዥግራ፥ይፈታል፡በወሬ።

•••

እሪ፡በሉ፥በየጋራው፥በየሸንተረሩ፤

ይፈለግ፡የለም፡ወይ፡ያዳኝ፡ውሻ፡ዘሩ።

•••

ስንደዶው፡ርጥቡ፥ስሜን፡ጓሳው፡ጤሰ፤

የጐበዝ፡መነሻው፡ሰዓቱ፡ደረሰ።

•••

 

http://www.gzamargna.net

s_t_qq3

ግጥም
ድርሰት
ቅኔ፡ዜማ
ተረትና፡ምሳሌ፡(ይዘጋጃል)

ግጥም፤