|
አለቃ፡መርሻ፡ዘውእቱ፡መርስዔ፡ሐዘን
(ከባላንባራስ፡ማኅተመ፡ሥላሴ፡ወልደ፡መስቀል፡"ዝክረ፡ነገር"፥ነጻነት፡ማተሚያ፡ቤት፥ዐዲስ፡አበባ፥፲፱፻፵፪፡ዓ.ም.፥ገጽ፡297-298፡የተቀዳ)
•••
ኢትዮጵያ፡ባሕር፡ቅጽሯ፥ደም፡ድንበሯ፡ስለ፡ኾነች
[ባርበኝነት፡ዘመን፡የተገጠመ]
ኢትዮጵያ፡የኤዶም፡ገነት፥
መኻሏ፡ልምላሜ፡ዳርቻዋ፡እሳት፥
አትገኝም፡መቼም፡አሻግሮ፡ቢያይዋት።
ሞኞ፡ተላሌ፡ሆይ፡አትበል፡ሰተት፤
ያላሰብኸው፡ናዳ፡ይመጣል፡ድንገት።
በዱሯም፡ይገኛል፡ዣርት፡ሾኽ፡ለባሽ፥
እየቀረደደ፡ዱባ፡እሚያበላሽ።
እናንት፡ወሰንተኞች፡ድንበር፡አታፍርሱ፤
ሥርዐት፡ዐዋቂ፡ነው፥ይቀጣል፡ንጉሡ።
ለፍርድም፡በወደር፡ብትመላለሱ፥
ይላችዃል፡ችሎት፡ከግር፡እሰከ፡ራሱ።
የሸዋ፡ልጅ፡ይርታ፡በሰንጋ፡ፈረሱ።
የሶራ፡ላይ፡ወፌ፥መልካሟ፡ርግቤ፥
ላይ፡ላዩን፡ነይ፥
የኖኅ፡የምሥራች፡ጸንቶ፡ባንቺ፡ላይ፥
ላይ፡ላዩን፡ነይ፥
ሳቢሳን፡ተዪና፥ያንን፡አታላይ፥
ላይ፡ላዩን፡ነይ፥
ዳክዬም፡እንደ፡ወፍ፡ትበሪያለሽ፡ወይ፥
ነፋሱ፡ሲነካሽ፡ውሃ፡ውሃ፡ባይ።
ዘንድሮ፡በረዶ፡መንገዱን፡አገደኝ፤
ውሃ፡ኾኖ፡ባይቀር፡እንዴት፡በነደደኝ።
ዳክዬም፡እንደ፡ወፍ፡ትበሪያለሽ፡ወይ፥
ነፋሱ፡ሲነካሽ፡ውሃ፡ውሃ፡ባይ።
አላወቅሺውም፡ወይ፡ፍሬ፡ነገሩን፥
እወጣለኹ፡ሲባል፡መውረድ፡መኖሩን።
ነገሩን፡ሳታውቂው፡ለምን፡ትሥቂያለሸ፤
ነገሩ፡ሲሰማሽ፡ትንከተከቻለሽ።
ወፎች፡ይንጫጫሉ፥አጥቢያ፡ኮከብ፡ወጣ፤
እባካችኹ፡ሰዎች፡ዐርመን፡እንምጣ።
ዐረም፡አጠለቀው፡ዕርሻዬን፤ወይ፡ጣጣ፤
በጠናበት፡በኩል፡አንድ፡እመም፡እናውጣ።
ፈረስኽን፡ጫንና፡ጋልበው፡ደንገላሳ፤
መለብለቢያውንም፡አውለኽ፡ፉርጋሳ፤
ንጉሡ፡ሲቈጣ፥መትረየስ፡ሲያገሣ፥
ፈረስ፡ሲደነብር፡ውሉ፡እንዳይረሳ።
ተማሪ፡ቤት፡ግቢ፡ተመለሺ፡ቅኔ፤
ወንዶች፡እዋሉበት፡እውላለኹ፡እኔ።
|