|
አለቃ፡ኪዳነ፡ወልድ፡ክፍሌ
("መጽሐፈ፡ሰዋስው፡ወግስ፡ወመዝገበ፡ቃላት፡ሐዲስ፥"፡፲፱፻፵፰፡ዓ.ም.፥ገጽ፡181-2።)
•••
አሠረ፡ንጉሥ፡ጠቢብ
ኀላፊያትን፡የሚያዘክር፥መጻእያትን፡የሚያሳስብ።
ዓሣ፡ጐርጓሪ፡ዘንዶ፡ሲያወጣ፡-፡የሰው፡ፈላጊም፡የራሱን፡ሲያጣ
ከኹለት፡ዛፍ፡ለወደቀው፡-፡አላገር፡ቋንቋ፡ማነው፡አንሺው።
የሀገር፡ቋንቋም፡ያላማ፡ቀኝ፡-፡ዅሉን፡ሰብስቦ፡አንድ፡የሚያሰኝ፥
ጋላና፡ዐማራ፡እስላም፡ሳይል፡-፡የፈረስ፡ስሙ፡አባ፡ጠቅል፤
አባ፡ቀስቅስም፡የሚሉት፡አሉ፡-፡ስላነቃቸው፡ጠርቶ፡ፊደሉ።
እኛም፡ተኝተን፡ሕልም፡እንዳናልም፡-፡አባ፡ነጋ፡ነው፡የጊዜው፡ስም፤
የፀሓይ፡መቅድም፡አጥቢያ፡ኮከብ፡-፡የሚታይበት፡ላፍሪቃ፡ሕዝብ፥
የጦቢያውም፡ልጅ፡የሴም፡ቡችላ፡-፡የሚከፍትበት፡ያይኖቹን፡ግላ፤
አፍሪቃን፡ያይ፡ዘንድ፡ባይኑ፡ማሚቶ፡-፡እየቀመለ፡እንደ፡ድሪቶ።
አንዳንድ፡ጊዜ፡እኮ፡የትንቢት፡ቃል፡-፡ሳይታወቅ፡ነው፡ቦጥለቅ፡የሚል።
ቋንቆቻችንም፡ባልና፡ሚስት፡-፡ርስ፡በርሳቸው፡የሚፋቱት
ላይለያዩ፡ተለያይተው፡-፡ያሟግቱናል፡ኹለት፡መስለው፤
ከቶ፡እኛ፡አንችልም፡ልንለያቸው፡-፡እግዜር፡ነውና፡ያጣመራቸው።
ነፍስና፡ሥጋ፡ከተለያዩ፡-፡ሕያው፡እንዳይኾን፡የሰው፡ባሕርዩ
ያማርኛም፡ቃል፡የግእዝ፡ሥጋ፡-፡አለግእዝ፡ነፍስ፡ሬሳ፡ባልጋ፤
ሬሳውን፡ቃል፡የሚሸከሙ፡-፡በግእዝ፡ቋንቋ፡ሲፈታ፡ይስሙ።
ሥረ፡ነገሩ፡ግእዝ፡ሳይጸድቅ፡-፡ፍሬ፡አያፈራም፡ዐማርኛ፡ዐጽቅ።
ነገር፡ከሥሩ፡ውሃ፡ከጥሩ፡-፡የተባለውን፡እስኪ፡መርምሩ፤
እነማናቸው፡ዛፉን፡ሳያውቁ፡-፡ፍሬውን፡በልተው፡የሚጨነቁ፥
ዛፉንም፡ዐውቀው፡ሳይገላልጡ፡-፡ሾላ፡በድፍን፡የሚያላምጡ፤
አለበትና፡ብዙ፡ቍጫጭ፡-፡ሆድ፡የሚያሳምም፡የሚያበሳጭ፤
ቄስ፡ኹኜ፡ቢኾን፡ወይም፡ዲያቆን፡-፡እጠራው፡ነበር፡ስማቸውን።
ዳቦ፡የሚልስ፡ካልገመጠው፡-፡መላሱ፡ብቻ፡ምን፡ሊያጠግበው፤
አፍ፡አለዦሮ፡ቢያዜም፡ቢያነብ፡-፡አይታነጽም፡ሸካራው፡ልብ፥
መርጌታ፡ኹኖ፡አቡን፡ሲቃኝ፡-፡እንዲህ፡እንዳለ፡አምጃር፡ዘፋኝ፤
የጦቢያው፡ሰው፡እንዲያው፡ላይ፡ላዩን፥ውስጡን፡ለምን፥
ውስጡን፡ለቄስ፡ለሚናዝዝ፥ቄሱም፡ግእዝ፤
ስሙ፡ፋና፡ወይም፡መብራት፡የነፍስ፡አባት።
እንዶድ፡ሳይዙ፡ወይም፡ሳሙና፡-፡አጥርቶ፡ማጠብ፡ዘበት፡ነውና፥
አለሰዋስው፡አለጥፈት፡-፡ትምህርት፡አይጠራም፡ምንም፡ቢያጥቡት።
የትምርት፡ዕንቅርት፡አለመጣፍ፥-፡አለመስማትም፡ዦሮ፡ገድፍ፤
ዐንገት፡ላለው፡ሰው፡ዙሮ፡ለሚያይ፡-፡ከባድ፡ሸክም፡ነው፡እንደ፡ድንጋይ።
ያኖሩት፡ዕንቅርት፡ስሙ፡አገልግል፡-፡ቢከፍቱት፡ተልባ፡ፍሬ፡ቢስ፡ቅል፤
ያለፈው፡ዐልፏል፡ለወደ፡ፊቱ፡-፡በትምርት፡ይራቅ፡ግብዝነቱ።
ካፍሪቃ፡ወንዞች፡ወርቅና፡አልማዝ፡-፡እንደሚያስገኘው፡እንዳባይ፡ወንዝ
ተርፎን፡እንዲፈስ፡ትምርቱ፡ንግድ፡-፡በዚህ፡ሰዋስው፡ጥርጊያ፡መንገድ
ይልቅ፡ኑ፡እንውጣ፡ወደ፡ገበያ፥-፡ገበያችንም፡ኢትዮጵያ።
መደብሮቿ፡የተዘጉቱ፡-፡ባራቱ፡ማእዘን፡እንዲከፈቱ
ልጆቿን፡በውቀት፡እያሳደገ፡-፡መንገዶቿንም፡እያስጠረገ
እግዜር፡ያቆማት፡ከማኽል፡ቦታ፡-፡በውጭ፡አገር፡ሰው፡እንዳትፈታ።
ያፍሪቃ፡ደንደስ፡ሻኛና፡ጫንቃ፡-፡ጦቢያው፡እንጂ፡ናት፡ምሥራቅ፡አፍሪቃ፤
የሰማይ፡ምድር፡የምድር፡ሰማይ፡-፡የተከበበች፡በነጭ፡አባይ።
ዐይኗም፡ሲመሰል፡በገነት፡ዐይን፡-፡ነጩ፡አባይ፡መደብ፡ጥቍሩ፡ብሌን፤
ባስተያየትም፡ሲመረመሩ፡-፡ማየት፡አይችልም፡ነጩ፡አለጥቍሩ።
ነጩ፡ሲፈተሽ፡ውስጠ፡ጥቍር፡-፡ጥቍሩም፡ሲፈተሽ፡ውስጠ፡ነጭ፡ዘር፤
ሕብረ፡ሰማይ፡ነው፡ጥቍሩ፡አባይማ፡-፡በቂጥኛም፡አፍ፡የማይታማ።
ነጭና፡ጥቍር፡የዓለም፡ዐይን፡-፡ዅሉም፡ተገልጦ፡የሚከድን፤
መክደኛውም፡ሞት፡ወዝ፡ከንባይ፡ነው፡-፡ያዳም፡ሌባ፡ጣት፡የሰፋችው።
|