ግእዝ ዐማር ኛ

ዋዜማ፡ሥርዐት

ቅጂ

ዜና

ግስ

ስሌት

ግእዝ-ዐማርኛ

ቀለም፡ቀንድ

ዋዜማ፡ሥርዐት•Wazéma System•Wazéma Système

ኢትዮጵያዊ፡የማስሊያ፡መጻፊያ፡ሥርዐት•Ethiopian Computer Writing System•système d'écriture informatique éthiopien

(to view the Amharic text, install the Wazéma Unicode fonts and set your browser’s default Ethiopic font)

Wazéma System•Wazéma Système

ሕዝብ


ሕዝብ፥በየዘመኑ፥ስለ፡ፍቅር፡የገጠማቸው።(ከግል፡ማኅደር፡የተቀዳ)
•••

ያልዩ፡አምባ፡ሎሚ፥የይፋት፡እንኰይ፤
አልነቀል፡አለ፡ልቤ፡ካንቺ፡ላይ።
•••
የበራሪ፡ያለኽ፥የወሬ፡ነጋሪ፤
ትዝታው፡መጣብኝ፥የኔ፡አስተዳዳሪ።
•••
አሰዋ፥ጉደራ፥ሰፊው፡አገር፡ሳለ፥
በዚህ፡በጠባቡም፥በልቤም፡ሰው፡አለ።
•••
የጨለማ፡መንገድ፡እሷ፡እየመራችኝ፥
ስማዳ፥ስማዳ፥ስማዳ፡አገባችኝ።
•••
እኔው፡በሽታዬን፡ደግሞ፡አበራታኹት፤
ይዋል፥ይደር፡እያልኹ፥ቀን፡እየሰጠኹት።
•••
አገባች፡የሚሉ፡አንድ፡ወሬ፡ሰምቼ፥
ደረቴን፡ነጨኹት፥ፊቴን፡ሰው፡ፈርቼ።
•••
እንዳሰኑ፡ፈረስ፥እንዳባ፡ኵራራ
ከወገቧ፡ቀጠን፥ከዳሌዋ፡ኰራ።
•••
ያቺን፡ቀጪን፡ኩታ፡ሆዴ፡እንዲያ፡ሲወዳት፥
አላዋቂ፡ሰፊ፡ባላጨማደዳት።
•••
አትወደኝም፡ያልሺኝ፥የጠላኹሽ፡የታል፤
አንድ፡አንጀት፡ነበረኝ፥ተኝተሽበታል።
•••
እናትን፡አትውደድ፡ለዘጠኝ፡ወር፡ዕድሜ፤
እኔ፡አርግዤኻለኹ፡እስከ፡ዘላለሜ።
•••
ኧረ!፡ተዉ፡ሰዎች፥እንደ፡ራስ፡ነው፡ፍርድ፤
ጭምት፡ያሳብዳል፡ዛርና፡መውደድ።
•••
መውደድ፡አይገድልም፡ሲሉ፥
ቄሱን፡ጦለበው፡አሉ።
•••
ሲታመሙ፡ታሞ፥ሲሞቱ፡ካልሞቱ፥
በምን፡ይታወቃል፡ሰው፡ወዳጅነቱ፧
•••
መድረኩን፡ስዘልቀው፥ደከመኝ፡እላለኹ፤
ወንዙን፡ስሻገረው፥ልቀመጥ፡እላለኹ፤
ገመገሙን፡ስዞር፥መልሱኝ፡እላለኹ፤
ዐደራ፡እማይሰጧት፡ዕቃ፡ረስቻለኹ።
•••
ይኸ፡ዘመን፡ዐልፎ፥ልብ፡አግኝቼ፡አውግቼው፤
አትምጪ፡ብለኸኝ፥መጣኹ፡ረስቼው።
•••
ያስነካኸኝ፡ቅጠል፡ምንድነው፡ማብረሻው፤
ሰው፡ጠልቼ፡ቀረኹ፡እስከ፡መጨረሻው።
•••
ፍቅር፡ሲዠምሯት፡ጤፍ፡ቅንጣት፡አታኽል፤
ጕድ፡ዐቧራው፡ጤሰ፥የንጉሥ፡ጦር፡የሚያኽል።
•••
እደጇ፡ጭራሮ፥እቤቷ፡ፍም፡ሞልቶ፥
ረ!፡እሳት፡ብዬ፡ብል፥እምቢ፡አለቺኝ፡ከቶ።
•••
አንቺ፡ሰው፡ትዝታሽ፡ከኮሶ፡ባሰሳ፤
ያስቀምጠኝ፡ዠመር፥ሌሊት፡እያስነሣ።
•••
መሸሸግኽ፡የት፡ነው፤መደበቅኽ፡የት፡ነው፤
የሠራ፡አከላትኽ፡ይታየኛል፡ምነው፧
•••
እንደ፡ሠኔ፡ነፋስ፡የተክለፈለፈች፤
ቅድም፡በልቤ፡ላይ፥አኹን፡ባይኔ፡ዐለፈች።
•••
ተወኝ፡ትቼኻለኹ፤ረሳኹኽ፡ርሳኝ፤
እንደሚጣራ፡ጠጅ፡እየጣለኽ፡አታንሣኝ።
•••
የማይጠፋ፡መብራት፡በልቤ፡ተክለሽ፥
ምን፡ጨለማ፡ቢኾን፡ትታዪኛለሽ።
•••
ያለኽበት፡አገር፡አማን፡ነው፡መሰለኝ፤
እኔን፡ማታ፡ማታ፡ሽብሩ፡ገደለኝ።
•••
ሰው፡በሰው፥ሰው፡በሰው፥ሰው፡በሰው፡ይረሳል፤
እምቢ፡እያለ፡ልቤ፡አንቺን፡ያስታውሳል።
•••
ያንተ፡ሆድ፡ስለቱ፡ቈረጠ፡መሰለኝ፤
እየገዘገዘ፡የኔውስ፡እምቢ፡አለኝ።
•••
መጨነቅ፥መጠበብ፡ለጠጅ፡ብቻ፡ነው፤
ለጠላ፡መድኀኒት፡ተወት፡ማድረግ፡ነው።
•••
ደጅ፡ጠናኹ፤ደጅ፡ጠናኹ፤ደጅ፡ጠናኹ፥ታከተኝ፤
የልብሽን፡ነግሮ፥ማን፡ባሰናበተኝ።
•••
ሰላድንጋይ፡ኾኖ፡ይታያል፡ገዘት፤
ጨዋታው፡ቀርቶብኝ፥ዐይኑን፡ባየኹት።
•••
ያልፈራው፡ጦርነት፥ያልፈራው፡ዘመቻ፤
ልቤ፡ተማረከ፡ባይኗ፡ብረት፡ብቻ።
•••
አንቺ፡ብትይ፡እኔን፤እኔ፡ብል፡አንቺን፤
የልም፡እንጀራ፡ኾነን፡የት፡ተገናኝተን፧
•••
ምር፡ዐዘነ፡ሆዴ፤ቍረንጮ፡ታጠቀ፤
ተለያየን፡በቃ፥ውሃችን፡ዐለቀ።
•••
ይኸን፡ድኽነቴን፥ማጣቴን፡ጠላኹት፤
ገበያ፡አመለጠኝ፡ጧት፡የተስማማኹት።
•••
ረ!፡ተዉ፡ሰዎች፥ለፍቅር፡አትሣሡ፤
እንደ፡ፈረንጅ፡ዕቃ፡ይመጣል፡ዐዲሱ።
•••
አንድነት፡ተቀምጦ፡ያልተጣጣመ፡ሰው፥
እስቲ፡ተለያይቶ፡ናፍቆቱን፡ይቅመሰው።
•••
 

http://www.gzamargna.net

s_t_qq3

ግጥም
ድርሰት
ቅኔ፡ዜማ
ተረትና፡ምሳሌ፡(ይዘጋጃል)

ግጥም፤